ነፃነቱን #ለነፃነት ቅድሚያ በመስጠት የነፃነት ህይወትን የኖረበት #የመሰጠት አባወራ - የጥበብወርቅ #ብራ።
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
አርቲስት፤ ሞደሬተር የሳቅ #አጤ አቶ ነፃነት ወርቅነህ ጥበብን አክብሮ - ተቀብሎ፤ በህይወቱም - ኑሮበት በሥጋ የተለዬ የዘመናችን የሳቅ #ጉልላት ነበር። እኔ ወንድሜ ሃይልዬ ቁርጥ እሱን ይመስልም ስለነበር በበዛ #ስስት የምመለከተው አርቲስት ነበር። ሃይልዬም ዘመኑ ባይፈቅድለትም ኮመዲ ዓይነት ነበር። ሃይልዬን ስናጣው የ፳ወቹ መግቢያ ላይ ስለነበር አርቲስት ነፃነትን ሳይ ዕድሜ ኑሮህ ቢሆን እሱን ትሆንም ነበር እያልኩ ከራሴ ጋር እወያይ ነበር።
በጥበብ ቤተኞች ዘንድ "#ድንገቴ" የአዘቦት ጉዳይ ሆነ። ዜና ከመደበኛ ወጥቶ በቀን ሦስት አራት ጊዜ "ሰበር፤ የሰበር ሰበር፤ ልዩ ሰበር" የሚሉ ድምፆች ከአብይዝም ጋር አብረው የመጡ ሲቆዩ ወደ ባህል ሊሻገሩ የሚችሉም ይመስላሉ፤ አያያዛቸው። "ሰበርን" ማዘውተር አዘቦትኛ የመሆን ያህል ሆኗል። "ሰበር" ስለምን ተወዳጅ ሆነ?
መደንገጥም ስላለበት ቀስ በቀስ እየተዋህደ የመጣም ይመስላል። የሆነ ሆኖ ድንገቴ ሁነቶችን እኔ #ደራሽ በሚል እተካዋለሁኝ። አማርኛ ቋንቋ ዲታ ስለሆነ ለህዝባችን ሥነ - ልቦናዊ ጸጥታ፤ የማረጋጋት ዓውዶችን ቢፈጥሩ ሚዲያወች መሻቴ ነው። ህዝባችን ስንቱን ይቻል? ቢያንስ በእጃችን በሚገኜው እራሳችን አርቀን ወይንም ገርተን ጭምቱን ህዝባችን ለድንጋጤ በማያጋልጡ ሁነቶች ብንተጋ ሰውኛ ይሆናል። ጥረታችን። እንተዛዘን እንደማለት።
እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ #መክሊት ይዞ ይወለዳል፤
እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ #መልዕክት ይዞ ይወለዳል፤
እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ #ጥሪ ይዞ ይወለዳል፤ ይህ የእኔ ፍልስፍና ነው። በመጸሐፍትም ለህትምት የበቃ ነው። የሰው ልጅ ሦስት ጸጋወችን ይዞ ይፈጠራል ብዬ አምናለሁኝ። ሦስቱን በጥዋቱ አውቆ በጥንቃቄ መምራት ከቻለ ለስኬት ይበቃል። ካንጠባጠበው ግን ስኬቱ ይርቃል። በሙያ ዘርፋ የተሰጠውን አውቆ በህይወቱ ኑሮ በሥጋ ከተለዩን ወገኖቻችን አንዱ ሞደሬተር // ኮመዲ አርቲስት ነፃነት ወርቅነህ ነው ብዬ አምናለሁኝ።
የታደለ፤ የተሰጠው፤ የተሳካለት የጥበብ ሰውነት ደራሽ ሁነት #ሲቀድመው እንደ ሰው ያሳዝናል - #ያስፈራልም። በጉልህ የሚታወቁ የጥበብ፤ የሚዲያ አንቱወች ጥንቃቄ ቢያደርጉ ጥሩ ይመስለኛል። ተመክሮው እራስን ከመጠብቃ ጋር ቢዋህድ እንደማለት። "ሁሉ ተፈቅዶልኛል፤ ሁሉ ግን አይጠቅምም" የሐዋርያው ወንጌላዊው የቅዱስ ጳውሎስን ዶግማዊ አስተምህሮ የእኔ ማለት ይገባል ብዬ አስባለሁኝ። በፊልም - ምርት፤ በሞደሬተር፤ በጥበብ ዘርፍ፤ በፖለቲካም ዘርፍ በተጽዕኖ ፈጣሪነት ረድፍ የምትገኙ ሁሉ፤ #አመጋገብን፤ #አዋዋልን፤ የኑሮ #ስታይልን በጥንቃቄ መምራት፤ በቁጥብነት ማስተዳደር ይገባል ባይ ነኝ።
ይህ የተጽዕኖ ፈጣሪወች የድንገቴ ጭልፊት መቼ ክንፋ ተመቶ ይህን መሰል የገዘፈ ድንጋጤ፤ ሃዘን ኢትዮጵያችን ከማስተናገድ የምትገላገልበት ሁነት በእጅጉ፤ በጣም ይናፍቀኛል። ለእኔ #ቅስፈት ነው። የወደፊቱን ጊዜውን፤ ሰዓቱን፤ ሰከንዱን፤ ደቂቃውን በእጅጉ ፈራሁት። ለቡርቧክስ የፊልም ፕሮዳክሽን፤ ለሰይፋ በኢቤኤስ ሸወች፤ በንግግር ጥበብ የተሰጣቸው አነቃቂወችም ……… ጥንቃቄ ቢያደርጉ፤ ጤናቸውን ቢቆጣጠሩ፤ ካልታቀደ #ደራሽ ግብዣወችም ቢታቀቡ ጥሩ ነው። ለትውልድ አብነታቸው ጥልቅ ስለሆነ።
እርግጥ ነው በዕድሜም ሆነ አልሆነም በተግባራቸው እንዲህ ተቋም የሆኑ ሰብዕናወችን በሥጋ መለየት "#ሞቱ" ማለት አይቻልም። ለዛው ተተኪ ትውልድ ያለው። ነገር ግን መሰሉን ወይንም ኮፒውን ማግኜት ስለማይቻል #አሻራውን ለዘለቄታ ለማስቀጠል የተሰጣቸው፤ የሚችሉም ቢታትሩበት መልካም ነው።
#ሳቅ - መስጠት፤ #ሥጦታ - መስጠት፤ #ደስታን - መቸር፤ #ምህረትን - መፍቀድ፤ እርቅን #ማብራት፤ ቅንነት #መመገብ፤ ትህትናን #ማጠጣት፤ አክብሮት #መለገስ፤ ርህርህናን #መፍቀድ፤ አጽናኝነትን #ማበረታት የፍቅር ተፈጥሮ አንከሮች ናቸው። በዚህ ውስጥ ህይወቱ መምህር ሆኖ የኖረውን ወንድማችን ቤተ - ነፃነትን፤ ቤተሰቦቹን፤ አድናቂወችን፤ ተከታዮችን፤ ጥበብን እራሷን፤ እግዚአብሄር አምላክ ሙሉ የመጽናናት አቅም ይሰጥ ዘንድ ፈጣሪዬን እየተማጸንኩኝ፤ ለእሱም እረፍቱ ከቅዱሳን ጋር ይሆን ዘንድ ፈጣሪዬን እለምናለሁኝ።
የሃዘን ዳርቻ ያድርግልን። አሜን።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ቸር ያሰማን። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
25/01/2025
ፈላስፊት ኢትዮጵያ እግዚአብሄር ያጽናሽ። አሜን።


አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ