የኢትዮጵያ ፖለቲካ #ሰው ማትረፍ ለምን #አጀንዳው አይሆንም?
«ሁሉ ተፈቅልኛል፤ ሁሉ ግን አይጠቅምም።»

#ምዕራፍ ፲፰።
እጅግ የማከብራችሁ የአገሬ ልጆች እንዴት ሰነበታችሁ? ደህና ናችሁ ወይ? ጤና ይስጥልኝ አገሬ ፈላስፊት ኢትዮጵያ እንዴት ባጀሽ? እንደምንስ ትሆኛለሽ? ጤና ይስጥልኝ እየኖርኩብሽ ሁልጊዜም የምትናፍቂኝ እመዬ ሲዊዝሻ።
ይገርመኛል። በእጅጉም ያስደነግጠኛል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለሰው ተፈጥሮ ሰውን ለማዳን አይታትርም። እንዲያውም ጉልበት ላለው አካል ምን እዬሠራህ ነው? እንዲህ ተብለሃል? እንዲያ ተብለሃል በማለት የኢትዮጵያ እናቶች #ሰቀቀን ናፋቂ ሆኖ ነው እማዬው። እንዳላዩ ማለፍ፤ እንደ አላወቁ መተው ማንን ይገድላል? ተጨማሪ ስቀቀን ዕድሜ ዘመናቸው ዕንባቸው ለሚፈሰው የኢትዮጵያ እናቶች ስለምን አይታዘንም? ሁሉም #እናት አለው እና። አራት ነጥቦችን ልጅ ቴወድሮስ አስፋው ማብራሪያ ከሰጠበት ለናሙና ማንሳትን ፈለግሁኝ።
ያው የነገዋ ኢትዮጵያ ቀጣይ ታዳሚው እሱ ነውና። የእኛ ጊዜ እያበቃ ስለሆነ። ሚዲያው "#ሰላም" ነው። ቃሉ ይጣፍጣል። የሚጠይቀው ግን ሆኖ መገኜትን ነው። ልጅ ቴወድሮስ አስፋው በፋኖ ተስፋ ሊኖረው የሚችል እስኬው ሲኖርበት ብቻ ስለመሆኑ ጠቅሷል። ኢትዮጵያ እና ኤርትራንም የማን ደም ፈሰሰን እየተየኜ ነው?
ለነገሩ እስኪ #ዓይኑን አተኩራችሁ እዩት የልጅ ቴወድሮስ አስፋውን። የሚነግራችሁ ነገር ያለ አይመስላችሁም።
፬ቱ #ነጥቦቼ።
ይህ የኮነሬል ፈንታሁን መሃቤ የትጥቅ ትግሉን በቃኝ ብለው ወደ ሰላማዊ የትግል አማራጭ መወሰንን አስመልክቶ ልጅ ቴወድሮስ ሃሳብ ለአቤቱ ብልጽግና " የተሻልክ አይደለህም፤ ደካማ ነህ ተብለሃል" አልገባህም እኔ ቅኔውን ልተርጉምልህ እና ምን ትጠብቃለህ?" ብሎ ነው አቤቶ ብልጽግናን እያፈጠጠው ያለው አመክንዮ ነው።
የብልጽግና መንግሥት ተቀምጠህ አትይ ዓይነት ነው። በጣም ነው ያዘንኩት። እኒህ መኮነን በዘመነ ህወሃት ታስረው ነበር፤ በዘመነ ብልጽግናም ታስረው ነበር። ከእስር ይፈቱ ዘንድ በሁለቱም ዘመን ተግቻለሁኝ። በውነቱ ምኞቴ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድም የፖለቲካ እስረኛ ሊኖር አይገባም ብዬ ነው እማስበው። እናት ትታሰብ። ድምጽ አልባወቹ የኢትዮጵያ እናቶች ዕንባ ይታበስ ዘንድ የጥረቴ አቅጣጫ ይህው ነው። እርግጥ ነው ከእስር ከተፈቱ በኋላ ቻሌንጁ በራሱ #የሚተማመን ልዩ የፖለቲካ አቅም እና ሥርዓት ያስፈልጋል። የፖለቲካ ይሁን የፕሬስ እስረኞች ሙግታቸው ስለሚቀጥል። ጥሪያቸው ውስጥ ከኖሩ።
የሆነ ሆኖ ኮነሬል ፈንታሁን መሃቤ የቁም እስረኛ እንዲሆኑ ወይንም ሌላ ፈተና እንዲገጥማቸው መመኜት ሰውኛ አይደለም። በአንድ ጋዜጠኛ ለዛውም በየዘመኑ ለእስር የተዳረገ፤ ህይወቱን ለማትረፍ ለተሰደደ ይህን መሰል ከቁጥብነት በእጅጉ የራቀ ዕይታ የሚበጅ ሆኖ አላገኜሁትም። በእሱ ውስጥ ርህርህና ያለውን ድርሻ መዝኑት። ጭካኔን ለመታገል መስመሩ ጨካኝነት አይደለምና። ስቃይን፤ መከፋትን ለሸሸ ሰብ ለሌላው አለማዘን ያሳዝናል፤ ለዛው የአዲስ ትውልድ ሁነኛ ቤተኛ።
በሌላ በኩል የሃሳብ ገበታ ደግሞ ከትጥቅ ትግል ሰላማዊ ትግልን የመረጡት ኮነሬል ፈንታሁን ማህቤ እና፤ የ፻አለቃ ማስረሻ ሰጤን በሚመለከት የሃሳብ ገበታ አዘጋጅ የልጅ ሞገስ ተረብ፤ ማጣጣል ከዚህ ቀድም አይቸው በማላውቅ ሁነት ነበር። መኮንኑ ከተማ ብርቅ እንደሆነባቸው፤ ካፒቴኑ በመዋዕለ ህፃናት ጉዳይ መመሰጥን እያነሳሳ፤ እያዋዛም ቢሆን የገቡበትን ፋይዳ እንዳሰኜው ሲያደርገው ነበር። በውነቱ ረጅም ጊዜዬ ነው እማዳምጠው እስከ ፍፃሜ። ብቻውን ካሰናዳ። የዕለቱን መሰናዶ ግን እራሱን ስላላገኜሁት ሳልጨርስ ነበር የወጣሁት።
«ኮለኔል ፋንታሁን: ከጫካ እስኪ ኮሪደር | የአፋብን አጋሮች እነማን ይሆናሉ? |የሞገስ ምክረሀሳብ»
የፋኖ መሪወች ሰላምን መምረጣቸው ሰው ከማትረፍ ጋር ሊታይ ሲገባው ከቅንጣት ጋር ማያያዝ የተገባ አይመስለኝም። ለዛውም የሰላም ሚዲያ፤ በተጨማሪም ፋክት ተኮር ሚዲያ ላይ ይህን መሰል ሁነት ማዬት ዘለግ ያለ ግራሞትን አምጥቶብኛል። ልጅ ሞገስ ትጉህ ወጣት ነው። በዛ ደረጃ ነው እኔ እምጠብቀው የነበረ።
አነሰ በዛም በየዘመኑ ለኢትዮጵያ ሠራዊት አባልነት የሠሩ ወገኖች ዛሬ ላሉበት ደረጃ ወጣቶች እንዲበቁ፤ ዜግነቴ #ኢትዮጵያዊ እንዲሉ ያስቻለው የኢትዮጵያ ሠራዊት በሚከፍለው ራስን ለህዝብ የመገበር መርኽ ስለሆነ ክብሩ ቢቀር፤ ማቃለሉ የተገባ ነው ብዬ አላምንም።
2) «የሰራዊቱ እንቅስቃሴና ውጊያው : "#ለማሸነፍ ነው የተዋሃድነው" (ኢትዮ ሰላም ሚዲያ)
በዚህ ላይ ሁለት ቁልፍ ጉዳዮችን ያነሳል። 1) የጎጃም ፋኖ ትግል ለጠቅላይ ሚኒስተርነት ስለመሆኑ፤ 2) የነገረ ተዋህዶ ጉዳይንም በውስጡ እንዳለ ያዬዘዋል። በዚህ አገላለጹ ሁለት አደጋወች ይታዩኛል።
ከዛ በፊት ስለ ጎጃም ልጆች የህሊና ብቃት ትንሽ ልበል። የጎንደር ክፍለአገር ኢሠፓ የወጣቶች ጉዳይ #ጎጃሜ ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ የጎንደር ወጣቶች ማህበርም #ጎጃሜ ነበር። በጎንደር ህዝብ ዘንድ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ትውፊት ተመራጭነት ልቅና ነው። አጤ በካፋን እኮ የጎንደር ሊቀ - ሊቃውንታት እስከ ባዕታቸው ጎጃም ድረስ ሄደው የአባታቸውን ዙፋን እንዲረከቡ፤ እናታቸው እቴጌ ማርያማዊትን ጨምሮ በክብር አምጥቶ ዘውድ የጫነ፤ ያከበረ፤ ያነገሠ ፍጹም ጨዋ ህዝብ፤ ዊዝደም የሆነ ህዝብ ነው። በእኛ ዘመንም የቀጠለው ያ የጥበብ ሂደት ነበር።
ወደ ቀደመው ስመለስ የወጣቶች ጉዳይን በቄን፤ የወጣቶች ማህበር ሊቀመንበርን መኬን ሁለቱንም ወጣቶችን በቅርብ አውቃቸዋለሁ። ሁለቱም መምህር ነበሩ። ቦታው የሚጠይቀውን ሁሉን ነገር ከዲስፕሊን ጋር ያሟሉ ብቁ ነበሩ። የግል ህይወታቸውን የሚመሩበት ስታይላቸውም ድንቅ ነበር። የሰብዕናቸው ንጽህና ዓውዱ ይመስጠኝም ነበር። በጎንደር ሊቃናት እና በጎጃም ሊቃናት የህሊና ፋክክር፤ ምቀኝነት እና ቅናት አይቼም አላውቅም። ህያው ምስክርም ነኝ።
በኋላም እኔ የህዝባዊ ድርጅቶች እና የሙያ ማህበራት ጉዳይ ኃላፊ ስሆን ወጣት ማህበሩን በተጨማሪነት የመከታተል ዕድል ገጠመኝ። የወጣት ማህበሩ ሊቀመንበሩ ብቁ ነበር። በሥራ አጋጣሚ፤ በመኖሪያ ሁኔታ፤ በጋብቻ ዝምድናም፤ እዚህ በስደትም አባት እምለው የማርቆስ ሰብ፤ ጭምት ባለቤቱ ሁለቱም የተማሩ የሚገርም መምህር የሆነ ሰብዕና ያላቸው የቅርቤ ናቸው።
በሁሉም መሥፈርት ስመዝነው የቀለም ትምህርት የመሰጠት አቅም የተለዬ ክህሎት ጎጃሜወች እንደ አላቸው አረጋግጫለሁኝ። የሚገርመኝ። ይህን የእኔ ሃሳብ ልጅ ሞገስ ዘውዱም ስለ ጎጃም ልጆች የቀለም ዕውቀት እኔ በማስበው ልክ ሲመሰክር አዳምጨዋለሁኝ። የማስተዋሉን ሁነትም መዝኜዋለሁኝ። የጎጃም የራሱ የሆነ ቅብዕ አለው በቀለምም ትምህርት፤ የሌላውም እንዳለው ሁሉ። ተዚህ ላይ ኢትዮጵያ ሙሉ እንድትሆን ህብራዊነቱን አክብሮ ማስቀጠል ብልህነት ይመስለኛል።
ወደ ቀደመው ጉዳዬ ስመለስ ልጅ ቴወድሮስ አስፋው ያነሳው አንከር ጉዳይ ለጎጃም ሊቃናት፤ ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ አባላት እጅግ አስጊ ነው። ጠርጥሯቸው፤ ዕወቋቸው፤ የትግላቸውን መዳረሻቸውን ተረዱ። ብልጽግና ሆይ! ይህን ሁነት እንደ አልባሌ አትይ ነው። " ሁሉ ተፈቅዶልኛል፤ ሁሉ ግን አይጠቅምም።" በጣም #አሳሳቢ ማብራሪያ ነው የሰጠው። በዚህ ውስጥም የሚዲያው የተግባር አቅጣጫ ሰውን የማትረፍ ዝንባሌ ልሙጥ ሆኖ አግኝቸዋለሁኝ።
3) «'በሰላም ውለን ማደር አንችልም' : ጠ/ሚንስትሩ ለኢሳያስ የሰጡት የአፀፋ ምላሽና ዛቻ» ( ኢትዮ ሰላም ሚዲያ)
ዛቻ፤ ማጣጣል፤ ማቃለል፤ ትርፍ መሄድ ለኢትዮ ኤርትራ ትውልድ አይበጅም። ከሁለቱ መሪወች አድምጫለሁኝ። ያልተገባ ነው የመሪነት ዲስፕሊንም የፈተነ ነው።
የሆነ ሆኖ በዚህ ዙሪያም የሰላም ታጋዩ ልጅ ቴወድሮስ አስፋው ብልጽግና ሆይ! ምን ትጠብቃለህ ነው? እምትፈልገው ነገር በሰላም ካልተገኜ፤ ዝግጁ መሆንህን፤ ድርጁ መሆንህን ለእኛ ከምትነግረን እስኪ አሳዬን ዓይነት ነው። "ጦርነት" ምኑ ይሆን የሚናፍቀው? በህወሃት እና በደርግ በነበረው ጦርነት ጎንደር ከተማ ሊደርስ ህወሃት ጥቂት ደቂቃወች ሲቀሩት ነበር እኔ በጎንደሮች ማርያም አድርጌ ብቻዬን ጫካ የገባሁት። መሪ ሰው እስካገኝ ድረስ ሸለቆ ውስጥ ሰንብቼ ነበር።
ውሻ #የሰው #እራስ ይዞ ሲመጣ አይቻለሁኝ። በዓይኔ በብረቱ። ሰቀጠጠኝ። በጣም ለረጅም ጊዜ እንቅልፍ አልነበረኝም። እቴጌ ጎንደርንም በቃሽ #አንጋችነት እምለውም ለዚህም ነው። ለዛውም ጎንደርን በውስጡ በፍቅር የሚያጭ የፖለቲካ ሊቅ ይኖራል ብዬ አላምንም። ሁሉ ቦታ ጎንደርን በልሙጡ ነው የማስተውለው። በታዛቢነት፤ በምክክር፤ ዕውቀት በማጋራት {}።
የኤርትራ እና የኢትዮጵያ የአቅም የመለካካት ሂደት በአፈሙዝ ይሆን ዘንድ መመኜት፤ በቀደመው ዘመን መሬት እንደ ደበደቡት አጤወች ዓይነት ነው። የእርስበእርሱ አልበቃ ብሎ ቀጠናውን የሚያውክ ነገር መመኜት የጤና አይመስለኝም። ለዛውም " ከሰላም " ሚዲያ። ጦርነት ሲናፈቅ ማገዶው የወይራ፤ የብሳና፤ የክትክታ፤ የአባሎ እንጨት አይደለም ማገዶው የሰው ልጅ ነው። #ቄራው የእናቶች ማህጸን ነው። ጦርነት ቤርሙዳ ትርያንግል ነው እምለውም ለዚህ ነው። ተመራጭ መንገድ ሊሆን አይገባም። የሰላም ታጋዩ ጋዜጠኛ ቴወድሮስ አስፋው ግን የባህር በር ከአፈሙዝ ውጪ አይታሰብም ይህንንም አሳኩን እና አሳዩን በጦርነት እያለን ነው። እንደ ገና የሺወች እልቂት፤ የሴቶች መደፈር፤ የተቋማት ውድመት፤ የጥላቻ እና የበቀል ሠርግ እና መልስ መናፈቅ¡¡¿¿¿
4) «ጅቡቲ #አንበረከከችን : የኮለኔሉ ጉዳይ 'ለምን ለኛ እጅ አልሰጡም'» (ኢትዮ ሰላም ሚዲያ)
ይህ ድፍረቱ ገርሞኛል። እሺ ኢትዮጵያ አቅም አይኑራት ተብሎ ይታሰብ፤ ይህ ቢሆን እንኳን እራስን በዚህ ልክ ማዋረድ በትውልዱ ቀጣይ ሥነ - ልቦና ላይ መርዝ የመነስነስ ያህል ነው የተሰማኝ። ለዚህም ነው እኔ ኢትዮጵያ የከበደችን ለሁላችንም ነው እምለው። ኢትዮጵያ የፈጠረ አምላክ እንዳላትም አለማመንም ይመስለኛል። ጁቡቲ ማለት በውጭጭ ያለች አገር ናት። የተከበሩ የዩክሬን መሪ ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ በውጭጭ ሁለመና የአውሮፓ ፑቲን ሆነው መውጣት ይሻሉ።
በነገረ ጁቡቲም ሃሳብም፤ ቁስም፤ ተስፋም ሁሉም በውጭጭ ነው። ዴንማርኮች ተገጣጣሚ ቤት የመሥራት ልምድ አላቸው። ጁቡቲም ትንፋሿ የቀጠለው እንደ ቅርጫ ስጋ እራሷን ለቀረመት ያቀረበች፤ የእኔ የምትለው በራስ የመተማመን አቅም የሌላት አገር ናት። ኢትዮጵያ አገሬ የጁቡቲ ወደብ ጥገኛ እንድትሆን ያደረገው፤ በኢትዮጵያ የሚቀናው ህወሃት የቀበረው ፈንጅ ነው። በአሁኑ ወቅት ጊዜ እዬጠበቀ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚል። የሚገርመኝ አዲስ መንገድ ፈልጎ የኢትዮጵያ መንግሥት አማራጭ ሲተልም የባህር መውጫ በር ይሆን ወደብ ሲሞካክር፤ ማቱ የሚፈስበት ከራሱ ዜጎች ነው። እና፤ እናማ ጁቡቲ ስለምን አትንጠራራ?
የግብጹ መሪ ፎቶ ሸው እኮ ጁቡቲ እንድታምነው ነው ኢትዮጵያን ሰቅዞ ለመያዝ ለሚያሚትረው ፕሮጀክቱ። ይህንንም ቢሆን ሚዛን ማስጠበቅ ይቻላል። ብልህ ቢሆን አቤቱ ብልጽግና። በብዙ የሚቻሉ እና የሚያስችሉ አቅም፤ ተነሳሽነት በበቂ #ኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና አለው። ኢትዮጵያኒዝም አቤቱ ብልጽግና ከዲስኩር ማጣፈጫ አሻግሮ አክብሮ ቢይዘው፤ ሆኖ ቢሆንበት፤ ኢትዮጵያኒዝምን ባያቀለው - ባያጣጥለው - ኢትዮጵያኒዝምን የወረት ሳያደርግ ዋጥ ስልቅጥ አድርጎ ቢያጣጥመው የተሰወረው የኢትዮጵያኒዝም የዊዝደም ማሾ ለዘለቄታው ቦግ ይል በነበረ።
የኢትዮጵያ መንፈስ እኮ ተፈሪ ነው። እንደ አሻ የሚደፈር አይደለም። ከተሞከረም ያራግፋል። ማት ይልካል። በሌላ በኩል ቢያንስ ጋዜጠኞች በፍጹም ሁኔታ ፍጹም ጭምት እና ዝምተኛ ዘብ አደር ማህበረሰብ እናት ኢትዮጵያም እንደ አላት እንዴት አይቀበሉም? ህወሃትን ጦርነት፤ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች የፖለቲካ አቅም አልነበረም፤ ህወሃት ፈቅዶ እና ወዶ በሰላም መንበሩን እንዲለቅ ያደረገው፤ እንደገናም መልሶ ስልጣን ለመያዝ ባደረገው ጦርነት ሃሳቡ የመከነው በጦር መሳሪያ ብቻ አይደለም። እሱን በድጋሚ ለሚኒሊክ ቤተ- መንግሥት ያጩ አቅም ያላቸው ኃያላን አገራት እና የራሳችን ሰወችም ነበሩ። ግን እሱም አልተሳካም።
ሰሞኑን የአሜሪካ አንባሳደር በኢትዮጵያ " ምዕራብ ትግራይ " ማለት ተሳናቸው የሚል እሰጣ ገባ አለ። ከሰኔ መግቢያ 2023 ጀምሮ ስለ ህወሃት የሚዲያ ሰርክ ማብራሪያ እና ተያያዥ ጉዳዮች "ምዕራብ ትግራይ " የሟሸሸው በጭምቱ ማህበረሰብ ሰላማዊ ጥረት ነው። የዛሬ አይደለም። ይህን ማመሳጠር፤ በጥሞና ያቃተው በፖለቲካ መያዦነት ጅዋጅዊት ጨዋታው የብልጽግና መንግሥት ቢገርመኝም፤ የጭምቱ ማህበረሰብ የአቅሙን ዲካ መለካት ባይቻልም መዳፈሩ የሚገባ አይመስለኝም። ጭምቱ ማህበረሰብ ከኢትዮጵያዊነት ጋር ያለው ውህድ መስተጋብር ተገማች ሆኖ አያውቅም። ኢትዮጵያኒዝም ዘብ አደር አለው። እዩኝ እዩኝ የማይል።
ብዙ ጊዜ ሥም እየተነሳ እከሌም፤ አያ እንቶኔም፤ እትዬ እከሌም "መሪያችን " ናቸው የሚል ሚዲያ ላይ አዳምጥ ነበር። ይህ ሳይለንት ዲስክርምኔሽን ነው። ምክንያቱም ስለእኔ እኔ እንጅ ሌላ ሰው መሪ ሊመርጥልኝ ስለማይችል። " ጁቡቲ አንበረከከችን" የወል ሆኖ ነው የቀረበው። እራሱን በዚህ ልክ ማወረድ ይችላል ልጅ ቴዲ። " ጅቡቲ #አንበረከከችኝ" እኔን ግን "ችን" ብሎ በፍጹም ሊያካትት አይገባም። የእኔን ዕድል እምወስነው እኔ፤ የእኔን የፖለቲካ አቋም እምወስነው እኔ እንጂ በስማ በለው አይሆንም።
ብዙ ጊዜ ሚዲያውን ሲሰራ የወል አድርጎ ነው። ስንት ናቸው? በቲም፤ በተቋም፤ በፖለቲካ ድርጅት የሚመራው ኃይል ካለው ለምን ይፋ አያደርገውም። "አምነንበታል" ነው የሚለውና። ምን አልባት ሳብስክራይብ ስለአደረግንለት ቤተኛ አድርጎን ይሆን???? ስደት ላይ ስላለ ቢደጉመው በሚል ቅንነት እንጂ ከውጥኑ ጀምሮ የእሱ ፈንገጥ ያለ ዕይታ ግጥሜ ሆኖ አያውቅም። በብልጽግና እና በህወሃት ጦርነት ጊዜ በወልቃይት እና ጠገዴ የነበረውን ምልከታም ሞግቼው ነበር። እኔ እንደ ጥላሁን ግዛው ነው እማዬው - ለዘመኑ። ጥላሁን ግዛው የአማራ ህዝብን ለስቃይ የማገደ ዕዳ ነበር --- ና።
ወጣት ቴወድሮስ አስፋው እሱ ነፍሱን ሳስቶላት በወጣትነት ዘመኑ ስደት ላይ መገኜቱን አስቦ ሰው ማትረፍ ስልት እና እስትራቴጂ ተኮር ላይ ቢተጋ ያምርበታል። ሰላም ማለት ለሰው ልጅ የመኖር ነፃነት ትንፋሽንም ፈቅዶ መለገስ ነውና። ቅኔ እተረጉማለሁ፤ ብልጽግንና አልገባህም ፈልፍለህ ተረዳ፤ ምህረት ብታደርግም ቅሉ አንተን የሚዩህ እንዲህ እና እንዲያ ነው …… ማሳጣት ጥሩ አይደለም።
በሌላ በኩል ፈላስፊትን፤ ሳይንቲስቷን፤ ዩንቨርሷን፤ ህጋዊትን፤ተደሟዊትን፤ ይሉኝታን ያነገሰችውን አገርም አቃሎ፤ አሳንሶ ከማይለካካ አገር ጋር አለካክቶ፤ ለዛውም አሳንሶ ማዬት ቢቀርበት ጥሩ ነው። ባትናገረም ቀናተኛ አምላክ ኢትዮጵያ አላትና። እርግማን ይኖራልና።
ሌላው እርዕስ ምርጫ ላይ ብርቱ ጥንቃቄ ይጠይቃል። በምንሠራቸው ሁሉ አክሰሱ ላላቸው ታዳጊ ወጣቶች ይታሰብ። ይህ መሰል ሁነት የታዳጊ ወጣቶችን ህሊና ሸፕ የማድረግ አቅም አለው። ኢትዮጵያ ከጁቡቲ አንሳ??? ሎቱ ስብኃት። ወይ መዳህኒዓለም አባቴ።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
27/01/2026
ኢትዮጵያን አቃሎ ከማዬት ምልከታ እራሳችን እናድን።
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ነው።
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
• ሊንኮች።
«ብልፅግናም ተሽሎ አይደለም'»
«ብልፅግና ያልተረዳው የኮለኔሉ ቅኔያዊ ንግግር : የእስክንድር "ይቅርታ"
«የሰራዊቱ እንቅስቃሴና ውጊያው : "ለማሸነፍ ነው የተዋሃድነው" : የአሜሪካው ባለስልጣን በኢትዮጵያ»
«ጅቡቲ አንበረከከችን : የኮለኔሉ ጉዳይ 'ለምን ለኛ እጅ አልሰጡም'»
«'በሰላም ውለን ማደር አንችልም' : ጠ/ሚንስትሩ ለኢሳያስ የሰጡት የአፀፋ ምላሽና ዛቻ»
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ