#ሰብአዊነት ከምህረት #ይጀመር። #መሪነት ከሰዋዊነት ነው የሚጀምረው።
"የቤትህ ቅናት በላኝ።"
#ምዕራፍ ፲፰
በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ካሉ ነዋሪወች ጋር ብልጽግና ያደረገውን ውይይይት በሙሉ አዳመጥኩት። አንዳንዱ ሙሉ ሳይሆን ከፊሉ ተቆርጦ በዜና መልክ ይቀርብ ስለነበር እሱንም ታግሼ በጥሞና ተከታተልኩት። ግብረ መልሱ #ወጥ ነው። ህዝቡ "መከላከያ፤ ፋኖ፤ ሚሊሻው፤ አድማ በታኙም ልጃችን፤ ወንድሞቻችን፤ የእህት የወንድሞቻችን ልጆች፤ የአክስት አጎቶቻችን ልጆች፤ የኛው የራሳችን ወገኖች ናቸው።" ሲሉ ነው ያደመጥኩት።
ይህ ማለት ሃዘኑም፤ ደስታውም የጋራ እና የወል ነው የሚል ዕድምታ አለው። ስለሆነም ከግብረ መልሱ የተረዳሁት የመፍትሄ አቅጣጫ ብሄራዊ የምህረት ዓዋጅ ቢታወጅ #ወጥ የሆነ የውስጥ መረጋጋትን ይፈጥራል ብዬ አሰብኩኝ። ስለሆነም ይህን ጉዳይ የመጀመሪያ ረድፍ እርምጃ የብልጽግናን መንግሥት ይወስድ ዘንድ ጠየቅኩኝ። አቤቶ ብልጽግና ሊሰማኝ ፈጽሞ አልፈቀደም። የተፃፈው ለብልጽግና ሆኖ #ፋኖ ግን ሰምቶ የምህረት ዓዋጅ ማወጁን አዳመጥኩኝ።
በገዢው ፓርቲ ቁብ ያልተሰጠው ቁምነገር ከፋኝ ብሎ ዱር ቤቴ ባለው ፋኖ መደመጡ ጥሩ ነገር ነው። የእኔ ጉዳዬ መኖሩ ሰላም ላጣው የአማራ ህዝብ እና የክልሉ ነዋሪ የውስጥ #መረጋጋትን በአንፃራዊ ሁኔታ ያመጣ ዘንድ ነበር ብሄራዊ የምህረት ዓዋጅ ያስፈልጋል ያልኩት። እርግጥ ነው ብሄራዊ የምህረት ዓዋጅ፤ ለሚያውጀው አካልም አቅም፤ ኃይል ያሰባስባል። የመረጃ #ፍሰቱንም ያጠናክራል። መተማመንም #በአንፃራዊነት ይፈጥራል።
የእኔ ግን ወሳኙ የሚያስጨንቀኝ ጉዳይ የህዝቡ ስቃይ እና ፈተና የማያባራ #ጥቁር ለባሽነት ነው። ብዙ የአማራ የፖለቲካ እስረኛ በማዕከላዊ መንግሥትም፤ በክልል፤ በዞን እና በወረዳ በሚገኙ እስር ቤቶችም በገፍ ይኖራል። ክልሉ በፋመ ጦርነት ሆኖ፤ ከፊሉ ቤተሰብ በፋኖ፤ ሌላው በግራ ቀኙ #እስር ቤት መሰቃዬት፤ ስንቅ ለማቀበል ብቻ ሳይሆን ቤተሰብ ስንቅ የሚያቀርበውም #ሊያጣ ይችላል፤ ኑሮው ውድ ነው። በዛ ላይ የገብያ ግሽፈት አለ። የብር የመግዛት አቅሙ ወጣ ገብ ነው። በዚህ ውስጥ መኖርን ማስቀጠል የገዘፈ ፈተና ነው።
ስለሆነም የአማራ ህዝብ በየትኛውም ወገን ምህረት ቢታወጅለት ይጠቀማል። ፋኖም ብልጽግናም ከሚጠቀመው ባላነስ ህዝብ ይጠቀማል። ምክንያቱም ፋኖ ከቀዬው ሲርቅ ፋኖን አስጠጋችሁ ተብሎ በመንግሥት ቅጣት ይደርስበታል፤ ፋኖ ቀዬውን ሲቆጣጠር ደግሞ መንግሥትን ደግፋችኋል ተብሎ ያ መከረኛ ህዝብ ይሰቃያል። ይታሰራል። ይገለላል፤ ይቀጣልም። ይህን ሊፈውስ የምችለው የምህረት ዓዋጅ ብቻ እና ብቻ ነው። የምህረት ዓዋጁ ለታሰሩትም ጠቃሚ አመክንዮ ነው።
#ቢታሰር፤ #ቢታገት፤ #ቢጠረጠር፤ #በክፋ ዓይን ቢታይ፤ #ቢቀጣ፤ ቢገደል፤ #ቢሰወር ያው አንድ #የአማራ ህዝብ ነው። የአማራ ሊቃናቱ ይታሰራሉ፤ ይገደላሉ፤ ተቋማቱ #ይነዳሉ ይወድማሉ። በሁሉም ዘርፍ ተጎጂው ያው የአማራ ህዝብ፤ በተጨማሪም ለሥራም ይሁን ለኑሮ ወደ አማራ ክልል የሄደ ነዋሪ ነው የጥቃቱ ሰለባ የሚሆነው። የአማራ ክልል ነዋሪ ተጎጂነቱ መቀነስ ሲገባው እየጨመረ ነው ያለው። ውይይቱን ፍሬ እንዲያፈራ ያደረገው ሁነት የልደት እና የጥምቀት በዓላት በሰላም መጠናቀቃቸው ብቻ ነው። ከዚያ ባሻገር ስጋቱም፤ እንግልቱም፤ በዘለቄታ #የቀነሰለት አንዳችም ነገር የለም። ይህንን ለማስታረቅ ነበር የምህረት ዓዋጁ የሚያስፈልግ መሆኑን አበክሬ የገለጽኩት።
አሁንም በብልጽግና መንግሥት በኩል ብሄራዊ የምህረት ዓዋጁ በእጅጉ ያስፈልጋል። ከምንም ነገር በላይ ቀድሞ ሊከወን የሚገባው ይህ በኽረ ጉዳይ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት እሱን አምኖ ለሚኖር ህዝብ ቋሚ የሆነ የዋስትና መብትን ሊያረጋግጥለት ይገባል። የት #ይጠጋ ይህ ህዝብ????
በፋኖ በኩልም የሚይዟቸውን ከተሞች ከመያዛቸው በፊት በጥሞና ሊያስቡበት የሚገባ ቁምነገር በቋሚነት ይዞ ለማስተዳደር የሚችል ወታደራዊ ቁመና ያላቸው መሆኑን ሊያረጋግጡ ይገባል። ይህም ብቻ አይደለም ለነዋሪው #አኗኗሪ ሁነቶችን ለማሟላት የሚስችሉ የኢኮኖሚ፤ የአስተዳደር እና የአመራር አቅም እንዳላቸው እርግጠኛ የሚያደርግ ነገር ሊኖር ይገባል። ይህን ፋኖ አሁን ባለው ቁመና ይችላል ወይ? እኔ በውስጡ ስለለሁ አላውቅም።
የኢትዮጵያ መንግሥት የበጀት ፍሰቱን #ቢያቆም፤ ማንኛውንም የትራንስፖርት ሁነት፤ በረራ ያለባቸውን ጨምሮ ቢያቆም፤ #አትኩሮቱን ቢያነሳ፤ #ኔት ቢቋረጥ ይህንን የህዝብ የመተንፈሻ ቧንቧ ዓይነተኛ ጉዳይ ፋኖ ማሟላት ይቻላል ወይ? የነገውስ ተስፋ በታቀደው ልክ ማግኜት ይቻላል ወይ????
#ማዳንን ስለማዳን።
አደብ ገዝቶ፤ አቅልን ሰብስቦ፤ ከስሜታዊነት ወጥቶ #ዘለግ አድርጎ ማሰብ ያስፈልጋል። ውስጥን #ማረጋጋት ይጠይቃል። ውስጥ እየተሸበረ፤ ውስጥ ሳይረጋጋ ሌላውን መምራት፤ ማድመጥ ፈጽሞ አይቻልም። መሪነት እኮ ከሰዋዊነት ነው የሚጀምረው። መሪነት እራስን በዲስፕሊን ለማስገዛት ከመወሰን ይነሳል።
ውቦቹ ውዶቹ ማህበረ ቅንነት እንዴት ናችሁ?
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
17/02/2026
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ