ህወሃት #ቤርሙዳ ትርያንግል ነው። ቀደምት ከተማዋ ናፍቆቴ ደብረታቦር #ጠቀራ መልበሱ ሐሤቱ ለማን ይሆን?
"አቤቱ የቤትህ ቅናት በላኝ።"







#ምዕራፍ ፲፰።
እንዴት አረፈዳችሁ ውዶቹ ውቦቹ። የሚናፍቀኝ፤ የምሳሳለት የደብረታቦር ከተማ መንደዱን ሳደምጥ በሃዘን ውስጥ ሆኜ ነው። በብልጽግና እና በህወሃት መካከል የተደረገውን ጦርነት በሠላም ሲቋጭ ተረፋልኝ ብዬ ከደብረብርሃን ጀምሮ ያሉ ከተሞችን ስዘረዝር #ደብረታቦር ከተማ አንዱ ነበር። ሙሉ ለሙሉ በህወሃት ወረራ እና የበቀል እርምጃ ህወሃታውያን ሳያሳኩት ከቀሩ ከተሞች የደቡብ ጎንደር ርዕሰ መዲና የታሪክም #ቀንዲል ደብረታቦር አንዱ ነበር።
ይህ የሰሞኑ መጥፎ አጋጣሚ የታሪክ #ጠቀራን ሳደምጥ ውስጤ አዘነ። ደብረታቦር አልባሌ ከተማ አይደለም። በጣም ነው የማውቀው። ቀበሌ መንደሮችን ሁሉ። ዝክረ ታሪኩ ዘለግ ብሎ ከሚጠቀስባቸው ከተሞች አንዱ ደብረታቦር ነው። የታሪክ ድርሳንነቱ በክብር ጥበቃ ሊደረግለት ሲገባ እንዲህ አመድ ሆኖ ማዬት ውርዴት ብቻ ሳይሆን #ውርዴም ነው። ማን ይፈጽመው ማን አላውቅም። እኔ ከቦታው ስለለሁኝ፤ ማንንም ስለማላገኝ ትክክለኛውን መረጃ ለማግኜት አልችልም፤ ማን ምን ፈጸመ የሚለውን። በስማ በለው ደግሞ ለህሊና ዳኝነት ይቸግራል።
ግን ከአመድ፤ ከጭስ፤ ከውድመት የሚታፈስ ቅርስ እና ውርስ እንደሌለ ጠንቅቄ አውቃለሁኝ። ያሳዘነኝ ይህ ነው። ወረታም መቀጠሉን ሰምቻለሁኝ። ወረታ ወሳኝ ከተማ ነው። ይህ ለህወሃት ለተስፋው ጥሩ መደሊድል የሚፈቅድ ስትራቴጂያዊ የድል ብሥራትም ነው። ወደ አዲስ ዘመን፤ እንፍራንዝ፤ ጸዳ፤ ጎንደር ከተማ ለማቅናት፤ የአዲስ አበባ ጎንደር መንገድን ለመዝጋት፤ የአማራ ርዕሰ መዲናን ውቢት ባህርዳርን በበቀል ለማንደድ፤ ታሪካዊውን ማርቆስ፤ ፍኖተሰላም፤ ዳንግላ ማንኩሳ፤ ገብሬጉራቻ በጠቅላላ መስመሩን በቀውስ ለሚቀጣው ለህወሃት ፕሮጀክት ወፍ ያወጣዋል። ወረታ ለአማራ ክልል #ብሬን ነው። ለኢትዮጵያም አንከር። ወረታ ላይ ሰሊጥ እና ጥጥ ሲነድ በአንድ ወቅት ተመልክቻለሁኝ። አገር የማንደድ ያህል ነው የተሰማኝ። ያ ሁሉ ድካም ለአፍታ ለኩሶ ማቃጠል ኃላፊነት ጋር ትውውቅ በሌለ ግብታዊነት የተፈፀመ ግራጫማ ክስተት ነበር።
ደብረታቦር ላይ ያዬሁት የአመድ ክምር። የህዝቡ ይህ የመከፋት ድባብ፤ የኗሪው የጭንቅን እንዲመገብ ዓዋጅ ማንንም አይጠቅምም። ብዙ ሰው እንደተጎዳም ሰምቻለሁኝ። ሁሉም እናት አለው። መጽናናቱን እመኛለሁኝ። የሆነ ሆኖ ህዝብን ለማስተዳደር ይሁን ለመግዛት #ተቋማት ያስፈልጋሉ። ተቋማት በየጊዜው እንዲህ እየነደዱ ሥርዓተ - መንግሥትን ለመምራት ታጥቦ ጭቃ ነው የሚሆነው።
ከፋኝ ያለው ፋኖም ቢሆን ተሳክቶለት "መንግሥት" ቢሆን ህወሃትም ሆነ የኤርትራ መንግሥት ቢፈቅዱለት ተቋማቱ መኖራቸው ቢጠቅመው እንጂ አይጎዳውም። ለአማራ የሚፈቀደው ማገዶነት እንጂ የፖለቲካ ቁልፍ ቦታ ከተረፍ ያለፈ ነገር የለው። ሚዲያ ላይ ቀን ከሌት ፋኖ እያሉ የሚሠሩት በባዕታቸው አንዲት የሰላም ህወከትን አይፈቅዱም፤ ለአማራም ለቁልፍ ኃላፊነት አያጩትም። አማራ አንጋች እና ማገዶነት ብቻ ነው የሚፈቀድለት።
የሆነ ሆኖ ተቋማት ጠቃሚ ናቸው። እንክብካቤ እና ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል። ለምን? ቀድመው የተደራጁ ተቋማት ከኖሩም አቅም ይቀንሳል፤ ወደ አልተሰሩት ለማማተርም አትኩሮትን አይሻማም፤ ባጀትን አያቃውስም። በነገራችን ላይ ዕዳቸውን ያልመለሱ ተቋማት ሊኖሩ ይችላሉ። እንዲህ በጭካኔ ከሚነዱት ውስጥ። ይህ ደግሞ ከወለዱ ጋር ሲጨማመር ለትውልድ ተስፋ #አራጣ ነው።
ይህ ተመክሮ የህወሃት ነው። እኔ ከታዳጊ ወጣት እስከ ወጣትነቴ ከተማሪነት እስከ ኃላፊነት ከህወሃት የማውቀው ታሪክ ዝርፊያ፤ ወረራ ውድመት እና ፈንጅ ቀብሮ ሰላማዊ ተጓዦችን መንገድ ላይ ሲያስቀር ነው። ህወሃት እኮ ቤርሙዳ ትርያንግል ነው። በወገራም በስሜንም አውራጃወች ያላደረሰው ሰቆቃ አልነበረም። ሥልጣን ላይ እያለም የጎንደር ከተማን ቅዳሜ ገብያን እራሱ ነው ያነደደው። አንድም የረባ ነገርም አልሠራም። ጎንደር የወረዳ ያህል ክብር አልነበራትም። ድቅቅ ነበር ያደረጋት። እልሁ፤ ቁጭቱ እና #አሻም ጥቃትን ጠንስሶ ህወሃትን ከመንበሩ የነቀለውም ይሄው አመክንዮ ነበር።
ያ መራራ ከርቤያዊ የህወሃት እና የህወሃታዊው ዘመን ያከትም ዘንድ በብልህነት ተከውኖ፤ ግን የህወሃትን ተመክሮ ለማስቀጠል መትጋት ለአደራ፤ ለታሪክ፤ ለትውፊት ይሁን ለትውልድ ከውርዴት የዘለለ #ውርዴ ነው። በጣም የሚሰቀጥጠኝ ነገር ናፍቆተ - ህወሃትነትነት በጎንደሬወች ዘንድ መፈቀዱ ነው። ጄኒራል ምግበ ሲናፈቁ??? #እ --- ግዚኦ ነው። በቀጥታ የማያቸው፤ የማዳምጣቸው ሁነቶች ሁሉ #ህወሃታዊነትን ነው። ይህ በተለይ ለጎንደሬነት የሚሰቀጥጥ #አረማሞነትም ነው።
ተማረ - አልተማረ፤ አወቀ - አላወቀ፤ ተጠበበ - ተኮፈሰ ህወሃት አፍቃሪነት ለጎንደሬ #አረማሞነት ነው። ምኑ ይናፈቃል ህወሃት -- ለጎንደሬ??? ባርነት? ተቀጥቅጦ እንደብረት መገዛት?? በዘመነ ህወሃት ከሥልጣን መነቀል መባቻ ከብአዴን ሊቃንነት ያለቁት ልቅም ብለው #ጎንደሬወች ናቸው። በፋኖ ሊቅነትም ያለቁት #ጎንደሮች ናቸው። አሁን ደግሞ የከተማ ውድመቱ ያው ይኽው በዓት ላይ ነው። ቀጣዩ አፈሩ ከእነህዝቡ ይሆናል። እሱም ይፈጸም ዘንድ ነበር ተጀማምሯል።
#እና እናማ...
ጎንደር ላይ የሰከነ፤ የጠሞነ፤ የአተኮረ፤ አደብ ያለው ህሊና ጠፍቶ እንዲህ ያለ የህዝብ ቁም ስቅል ማየት ለዛውም ለህወሃት ወደ መንበረ ሥልጣኑ መመለስ ይሁን አገራዊ ምኞቱ ተሳክቶ የህሊና ካንሰርን መልሶ ለመትከል ለጎንደር መጣር ለትውልዱ #የአራጣ - አራጣ ነው።
ለምሳሌ ደቡብን ተመልከቱት። እኛ ነበርን በዘመነ ህወሃት የታገልነው።
በሁሉም ዘርፍ በአብይዝም ተጠቃሚ 50+ ደቡብ ነው። የእኛ ልሙጥ ነው። እናመሰግናለን እንኳን ከአቤቱ ኦህዴድ አልተቸረንም። #ስለምንጠረጠር። ከተሞቻቸውም ደህና ናቸው። የዛሬ 10/15/20 ዓመትም የመጀመሪያ ረድፍ ባለዕድል ደቡብ ነው። ለምን? አማራ የቀደመውን ትሩፋቱን እራሱ ይነድለት ዘንን ፈርቲላይዘሩ እራሱ ነው። ጎንደር እራሱን ማግዶ፤ ነገ ደግሞ በጥርጣሬ የሚታይ፤ የሚገለል፤ የሚጠቀጠቅ፤ የሚፈለጥም ይሆናል። የጎንደር እናት ሁልጊዜ ጠቀራ ለባሽ ናት። በየዘመኑ።
ሰሞኑን ለመጀመሪያ ጊዜ የጥበብ ሰወች ዓውደመትን ሊያከብሩ እስቴ በስፍራው ተገኝተዋል። ያን ፍሰሃ ተከትሎ ነው ይህ ጥቃት ታቅዶ የተከወነው። ጥቃቱ ትልሙ ከህወሃት ነው። ህወሃት እንደ ጎንደር የሚቀናበት በዓት የለም። ሊቃናቱ እና ሊሂቃኑ ያልገባቸው ይህ ነው። ጠፍቶባቸዋል የብልህነት ውሉም፤ ስልቱም። የሚገርመው ተቋማት ምን በድለው ነው ለእሳት ሽልማት የሚሰጡት??? ለዛውም ያ በምርኩዝ ታቱ የሚል ከተማ ተይዞ???
#ሰላም የአንድ ወገን ጥረት ብቻ አያሳካውም።
ሰላም ውስጥን አጽድቶ እራስን የሰላም ማህበርተኛ ማድረግ ሲቻል ነው ሰላም የሚገኜው። በንቀትም አይመጣም ሰላም። በመታበይ ውስጥም ሰላም ሊስቅ አይችልም። በስድብ እና ሌላውን በማዋረድም ሰላም አይመጣም። አንድ ሙሉ ፕሮግራም የስድብ ጭድ ሲከመር አዳምጫለሁኝ። ይህ ለሰላማዊ ድርድር አቅምን ያስመዝናል።
የሆነ ሆኖ የትኛው ፋፍሪካ፤ የትኛው የኢንበስትመንት ፍሰት፤ የትኛው አጓጊ ልማት ኖሮ ይሆን ደብረታቦር ላይ ያለውን ለማውደም ታቅዶ የተከወነው። ትምህርት፤ ጤና፤ ጸጥታ ላይ የሚሰሩት ቢሯቸው ነደደ፤ #ሥራፈት ይሆናሉ። ሥራ ካልሰሩ ደግሞ መሃያውን ማን ይከፍላቸዋል? ህዝቡስ አገልግሎት እንዴት ሊያገኝ ይችላል?
ልማት፤ አገልግሎት፤ ጥበቃ ለማግኜት #ግብር ያስፈልጋል። ግብር ፍሰቱ ካለሰላም አይሆንም። ይህን ማገናዘብ እንዴት አይቻልም? በሌላ በኩል የአገር ሠራዊት የከተማ ጠባቂ አይደለም። ሠራዊት ደንበር ጠባቂ ነው። ለዛውም አሁን ኢትዮጵያ በ፬ቱም አቅጣጫ ተወጥራ ባለችበት ወቅት። ህዝብ የራሱን ሰላም በራሱ ልጆች ሊያስጠብቅ ይገባል። ይህ መሆን ካልቻለ ዘላቂ የመኖር ዋስትና ማግኜት አይቻልም።
የፓርላማ፤ የምክር ቤት፤ በየደረጃው ያለ የአመራር አካላት እራሱ #ዘብአደር ሊሆን ይገባል። ቢያንስ የመንግሥትም የብልጽግና ካድሬ እራሱን ይጠብቅ። ለእሱም በሠራዊት አጀብ፤ ለሚመራው ህዝብም የሠራዊት አጀብ ሁልጊዜ እንዴት ይቻላል? ሙሉ ሦስት ዓመት??? ሁልጊዜ ጥገኝነት? እራሱን ችሎ መቆም አለመቻል? መሪነት እኮ እራስን ችሎ መቆም፤ ለሌላውም ጥግ፤ ከለላ መሆን መቻል ነው። #ጧ ጠሽ ባለ ቁጥር እግሬን አውጪኝ???
የደቡብ ጎንደር ዞን ባለስልጣኖች ዘንጠው ስብሰባ የመሩትን ህዝብ ሰላሙን ሊጠብቁለት ይገባል። ይህን ማድረግ ካልቻሉ አቅም የላቸውም ማለት ነው። መሪነት እኮ ሁለገብነት ነው። በሰላም ጊዜ ሲቢል፤ በጦርነት ጊዜ ወታደር መሆን ግድ ነው። መሪነት ድሎት አይደለም። አገልጋይነትም ነው። አገልጋይነት ደግሞ የሚመሩት ህዝብ ለጥቃትም፤ ለበቀልም እንዳይጋለጥ ተግቶ መሥራት ያስፈልጋል። ደሞዝ የሚከፈለው እኮ ለላንቲካ አይደለም። ሥጦታም አይደለም ማህያ።
ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋል ይላል የጎንደር ሰው፤ ባለፋት ሳምንታት ደባርቅ እና ዳባት #ጸረ ህወሃት ሰላማዊ ሰልፍን አድርገው አየሁኝ። የደባርቅም ይሁን የዳባት ከተሞች በምርኩዝ ጎብጠዋል፤ ወድቀዋል። ህዝቡ በጣም ~~~~~~~ፈዟል። አንድ የሚደመጥ መሪም አላየሁም። ከሁሉ የሚገርመው የህወሃት መራሹን የኢህዳግ ሰንደቅ ዓላማ ተሸክመው ወጥተው ነው የህወሃትን የጠለምት ወረራን አውጋዥ ሆነው ያዬኋቸቸው። አዘንኩኝ።
በአጠቃላይ በበጌምድር እና ስሜን ጠቅላይ ግዛት በመንፈሰ ጎንደር ያለው ትንፋሽ አደብ _ የሰጠው፤ ውስጡ _ የተረጋጋ፤ የሚጠቅመው እና የሚጎዳውን ለይቶ _ መዝኖ ይሁን _ ሰፍሮ የሚንቀሳቀስ የመሪ አቅም ያስፈልገዋል። ህወሃት በቀጥታ በሚመራው የቀውስ አውሊያ ተዘፍቆ የጎንደር አማራን ማናቸውም ችግር ለመፍታት አይቻልም። ለጎንደር #አልዛይመሩ ህወሃት እና ህወሃታዊነት ነው። "እግር ሄዶ ሄዶ" እንደሚባለው ልጅ ስታሊን እስከ መተማ ዘልቆ እየመራ ስለመሆኑ አድምጫለሁኝ። ሞት በስንት ጣዕሙ ብያለሁኝ።
ጎንደሬ ጥቃት አይወድም ነበር። አሁን ግን ጥቃትን ፈቅዶ የአገልግሎት ዘመኑ ኤክስፓየርድ ያደረገውን ህወሃት ምራኝ፤ ንዳኝ ማለት አሳፋሪ እና ቀፋፊ _ ልጣጭ ገጠመኝ ነው። ዕድሉን ያግኛት እና ህወሃት ጎንደሬወች ታዩታላችሁ። አመድ ነው የሚያደርጋችሁ። ለዘር የሚተርፍ አይኖርም። የእሱ አፍቃሪ ሚዲያወች ሲያስተላልፋት ውለው የሚያድሩት ነቅሰው አውጥተው በየትኛውም ሙያ የተሰማራውን ጎንደሬውን ነው ሲያብጠለጥሉት፤ ሰብዕናውን ሲንዱት።
የመኖር፤ የትንፋሽ ፍርፋሪ ከህወሃት ጎንደሬ አገኛለሁ ብሎ አንድ ነፍስ ለዚህ እንቅፋት ሁነት ሲገብር የአባቶቻችን የእናቶቹ #የብልህነት ዘመነ ቅብዓ #መፈቅፈቁን ያመላክታል። ነገ በያለበት ጎንደሬ እየታነቅ እስከ ልጅ ልጅ የህወሃትን በቀል ተሰንጎ ይጨልጣታል። ለዚህ እያሰናዳችሁት፤ ለዚህ ድልዳል እየፈጠራችሁ ያላችሁ ሁሉ ከፈጣሪያችሁ ጋር ምከሩ። አፋፍ ላይ ናችሁ። ልብም ይስጣችሁ። አሜን።
ትክክለኛ ጎዳና ላይ አይደለም ያላችሁት።
ህወሃት ወደ መንበሩ ቢመለስም፤ ይሁን ህሊናህን ሰቲትን ሰጥተህ አፍሪካ ቀንድ፤ የአፍሪካ አህጉር ህብረት፤ የተመድ አካልነትን ለህወሃት ብትሸልመው የአንተን አመድነት ቅበላ ይሆናል። ጥቅምህን ተፃረህ የቆምክ ጎንደሬ ሁሉ እሰብበት። ህወሃት በምንም ታምር ለጎንደሬ የሚሆን ድርጅት አይደለም።
ደቡብ ላይ መኖር ዘንጥ ወክ እንዲህ ይላል፤ ማገዶነት የለም። ማገዶ ትሆን ዘንድ አንተ እስከ ህይወትህ፤ እስከ አገልግሎት መስጫህ ድረስ ተቃጥለህ ግን "ጀግና" በሚል ሽፋን ድቀትህ ሲታወጅ ውሎ ያድራል። እያንዳንዱ የኢትዮጵያ መልዕካ ምድራዊ አቀማመጥ ዱር፤ ጫካ አለው። ለምን ከዛ ፋኖ አያደራጁም የሚዲያ ፕሮፖጋንዲስቶች???? የሁሉም ሰላም ነው። ዘመኑን ሁሉ ማገዶው ጎንደር ነው። አሁን ጎጃምም ተጨምሯል። ወሎ እንኳን የለመደበት ነው እንደ ጎንደር። ምድርን ከዕውቀት፤ ከሥልጣኔ አግልሎ እንደምን ትውልድ ይቀጥል ይሆን???
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩሉኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
17.02/2026
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ