ሕይወት #የሚቀለው የሰው ልጅ ለመኖር #ፍላጎት ሲኖረው ነው።

 

ሕይወት #የሚቀለው የሰው ልጅ ለመኖር #ፍላጎት ሲኖረው ነው። 
 
የመኖር #ፍላጎቱ ምኽዋር ደግሞ ሰላም።
 
ለእኔ ሰላም ፲፫ኛው ፕላኔት ነው። 
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 
 May be an image of one or more people, people smiling and jewelry
 
ለመኖር ፍላጎት ማመንጨት የሚቻለው #በስኬት ብቻ አይመስለኝም። የተሳካላቸው ፈቅደው መራራውን ስንብት ሲወስኑ ስለምናይም /// ስለማድመጥም። ለመኖር ፍላጎት መኖር #መማርም ብቻውን፤ የመኖር ፍላጎትን ያበረታታል ብዬ አላምንም - እኔው። ለመኖር ፍላጎት አስቻይ ሁኔታ የሽልማት ብዛትም አይመስለኝም። ሽልማቱ ሲቀር ወይንም ሲቀንስ መኖር #በቁዘማ ውስጥ ሊታክት ይችል ይሆናል።
የመኖር ፍላጎት እንዲቀጥል ቤተሰብ መመስረት፤ ልጆች መኖር፤ ጥሩ ቢላ ሠርቶ ምቾትን ማስተናገድ ብቻውን ለመኖር ፍላጎት መጨመር ሚና ሊኖረው ይችላል ብዬም አላስብም።
 
መኖርን የሚያኖረው #የውስጥ #ሰላም፤ የከባቢ ሰላማዊ አየር፤ ከጭንቀት ጋር የማይነካካ ገጠመኝ ሲኖር የሰው ልጅ መኖርን ሊፈልገው፤ በመኖሩ ተስፋ ሊያደርግ፤ መኖሩን እንደ አንድ #በኽረ መሪ ኃይል አድርጎ ሊወስደው ይችላል ብዬ አስባለሁኝ።
 
ቁልፍ ግን የሰው ልጅ ለሰላም ያለው አትኩሮቱ ቀጫጫ።
የመፍትሄ ጎዳና ግን የሰው ልጅ ለሰላም ያለው አክብሮቱ ስስ።
የውስጥ ሐሤት አመንጭ ሆኖ ግን የሰው ልጅ ውስጡን ያሸፈተበት።
ሰላም የማሰብ አቅምን አፋፍቶ የህሊና #ብቃትን የሚያጎለብት ግን የሰው ልጅ የሚሰጠው ትዕግስት ኮሳሳ።
የፍልስፍና ልቅና ገላጭነት ባለቤት ሆኖ ግን የሰው ልጅ በመቻል አቅም ጥብቆነት እንዲሰቃይ የሚደረገው።
 
የሰላም ጎዳና፤ ሰላሚዊ - እርምጃ፤ ሰላማዊ - ሩጫም፤ ልቅናም ይሁን ልዕልና፤ ስኬትም ይሁን የሐሤት #ብር - አንባር ነው። ሰላም ከጭቅጭቅ፤ ከብስጭት፤ ከግንፍልተኝነት፤ ከገረጭራጫ ምልከታ እና ህውከት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም። ሰላም የስኩን ሰብዕና መለያ ነው። ሰላም ረጋ ላለ ተፈጥሮ የተሰጠ እዮራዊ የቅብዐ ምልክት ነው። 
 
ሰላም የሰብአዊነት መለኪያ ማንነት ነው። ሰላም በተፃራሪው ቆሞ ከሚፈታተነው ጭካኔ ጋር በሽሽት፤ ሳይሆን ሆኖ በማሳየት በድርጊት እና በምግባር የአሸናፊነት ዓውዱን ያስከብራል።
 
ሰላም #ደፋር ነው። ሰላም #ሰነፍ አይደለም። ሰላም ትጋቱ በተፈጥሮው ልክ ነው። ሰላም በአስተውሎት ውስጥ በቅሎ - የሚያበቅል፤ ሰብሎ የሚያሰብል የጽድቅ ጎዳና፤ የምርቃት ዓውደ - ምህረት #የዊዝደም ምዕራፍ መክፈቻ ቁልፍ ማንነት ያለው ሽልማታችን ነው።
ሰላም በልኩ፤ ለልኩ የተፈጠረ አስተካክሎ ሰብዕናን የሚቀረጽ #ሐዋርያም ነው። ሰላም ከሙያም፤ ከዕውቀትም በላይ የሆነ በፈጣሪ አምላክ ፈቃድ የተሰጠን የሁላችንም ልዩ ሰማያዊ ስጦታ ነው። ካወቅንበት።
 
የሰው ልጅ እንቅልፍ ሊኖረው ይገባል። እንቅልፍ የተስተካከለ የጤና #የምስራች ነው። እንቅልፍ መተኛት የሚቻለው የውስጥ ሰላም #እርጋ ሲባል ነው። የውስጥ ኦርጋኖች የተግባራቸው የመገምገሚያ፤ እራሳቸውን የማደራጃ ሁኔታ ክንዋኔው የሚሳካው ሰላም በውስጥነት ዕድል ሲያገኝ ነው።
 
ዛሬ በምድራችን ውስጥ ምን ያህሉ ህዝብ በእንቅልፍ መዳህኒት እንቅልፋን ያግዝ ይሆን?
ዛሬ በዓለማችን ሁሉ ሞልቶ ተርፎት፤ ምን ያህሉ ህዝብ በሥነ - ልቦና ህመም ይሰቃይ ይሆን?
ዛሬ በዓለማችን በውስጥ አለመረጋጋት ምክንያት ስንቱ የዓለም ህዝብ በስጋት፤ በፍርሃት ይሰቃይ ይሆን?
ዛሬ በዓለማችን ውስጥ ምን ያህል የሰው ልጅ በብስጬት ሰብዕና ይታወቅ ይሆን?
ዛሬ በዓለማችን በሰላም እጦት ምክንያት በግጭት ይሁን በጦርነት ምን ያህሉ ህዝብ በሰቆቃ ውስጥ መኖሩን ያስተናግድ ይሆን።
እንዲህም እንዲያም እያደረግን እንዘርዝረው፤ እንበትነው ብንል ሰማይ እና ምድር የተፈጠረበትን ሚስጢር በሩን ሊከፍትልን ይችል ይሆናል።
 
የሰላም ብሄራዊ፤ አህጉራዊ ሆነ ግሎባላዊ ጸጋ እና በረከቱን ዘርዝረን፤ ፈትሸን ብናየው የተስፋ፤ የምኞት፤ የስኬት፤ #የሥልጣኔ ቀጣይነት፤ ከደስታ በላይ የሐሤት #ምኽዋሩ ሰላም ሆኖ እናገኜዋለን። ለእኔ ዕውነተኛ ሰላም ፲፫ኛው ፕላኔት ነው። ለሰላም የሚተጉ ሰብዕናወችም ይሁኑ ተቋማት #ብጹዑ ናቸው - ለእኔ። የሰላም ሰብዕና ሐዋርያዊነትም ነው - ለእኔ። ለሰላም የሚተጉ ሰብዕናወች #የጸደቁ ናቸው ለእኔ።
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
17/02/2026
ሰላም የማያዳላ #የጸደቀ ሥጦታ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።