ውህድ ማንነትን አናስደንግጠው። #ክብርት ወ/ሮ አምለሰት ሙጬ ፖለቲከኛ ናት ብዬ አላምንም። ስትሆን ለሙግቱ እኔው እበቃታለሁኝ።
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
ምዕራፍ ፲፱።
#እፍታ።
ማህበረ ቅንነት እንዴት ሰነበታችሁልኝ? እኔ አምላኬ ክብሩ ይስፋ ደህና ነኝ። የብርኃን ሰሞናቱን አስመልክታችሁ እንኳን አደረሰሽ ላላችሁኝ አዱኛወቼ ሁሉ ውስጤ ለእናንተ ያለውን ልዩ ጣዕም ያለውን አክብሮት በትህትና አቀርባለሁኝ። ኑሩልኝ። አሜን። ማድመጥ፤ ጥሞና፤ ዘለግ አድርጎ ለማሰብ አደባዊ መሆን ይረዳል። ለዛ ነበር ጥፍት ያልኩት። ይህ ባህሌም ነው።
#ጠብታ።
ውህድ ማንነት በየትኛውም ዓለም ሁነኛ ባለቤት የለለው፤ ውሃ በቀጠነ ቁጥር ለጥቃት የሚጋለጥ የሰብዕና ዓይነት ነው። ውህድ ማንነት በተለምዶ ከሁለት እና ከዚያ በላይ ከሆኑ ቤተሰቦች መገኜት ብቻ አይመስለኝም።
ከእኔ ተመክሮ እንደ ተማርኩት ከሆነ ከአኗኗር ዘይቤም አዳዲስ ማንነቶች ሊመጡ ይችላሉ። ልክ እንደ ፆታ፤ እንደ ኃይማኖት፤ እንደ ሆቢ፤ እንደ ሙያ፤ እንደ ቁመና፤ እንደ ዞግ፤ እንደ ዜግነት፤ እንደ ሃይማኖት ወዘተ። አሁን እኔ እምኖርበት አገር ሲዊዘርላንድ ነው። ከተማዬ በዙሪክ ክፍለ አገር በደጓ ቪንተርቱር ከተማ ነው።
ሌላ ዓለም ከሚኖሩ ጓደኞቼ፤ ቤተሰቦቼ ጋር እንኳን ለየት የሚያደርገኝ የአኗኗር፤ የአለባበስ፤ የአስተሳሰብ፤ የምልከታ ሁኔቴ በራሱ አዲስ ማንነት ሰጥቶኛል። ሁላችንም ስደተኞች ሆነን ኮሬያ ስሜን እና ደቡብ፤ ህንድ፤ ቻይና፤ አሜሪካ፤ ካናዳ፤ በወል መጠሪያው አውሮፓ፤ በተናጠሉ ሲዊዝ ስንኖር ሳላውቀው ማንነታችን በዛ አገር የአዬር ባህሪ፤ ባህል፤ ወግ እና ልምድ ይገነባል።
የብዙ ነገሮች የፍላጎት መቀራረብ እርቀት፤ ግጭት አለፍ ሲልም ፍጭት ምንጩ በውስጣችን ካዳበርነው የልምድ፤ የተመክሮ ማንነት የመነጨም ነው። …… ብዬ በእርግጠኛ የምግልጸው በዕውንም በህይወቴ ስለደረሰ፤ ስላጣጣምኩት፤ ወይንም ስለፈተነኝም ነው። ከአንድ መሐጸን ተፈጥሮ አማርኛ ቋንቋው እራሱ አያግባባንም። ይህ መሆኑ ተፈጥሯዊ ነው። ሊሆንም ግድ ነው።
ከተለያዬ የዘር ሐረግ የመገኜታችነን ረቂቅ ሚስጢር የሚያውቀው የሰማዩ ዳኛ አማኑኤል ብቻ ነው። ለምን ውህድ ማንነት እንደተሰጠን። ዓለማችን በሙሉ በሽግሽግ፤ በስብጥር፤ በውህደት የተቃኜ ህዝብ ነው ያላት። እድገቱ በሉት ስልጣኔው የዚህ ውጤት ነው። ከአንዱ ሙቀት፤ ከሌላው ቅዝቃዜ፤ ከአንዱ ፍጥነት ከሌላው ዳታ ወዘተ …… ይቀመርና የዓለማችን ገጽታ ተገነባ።
#ማማር። መዋብ። ማጌጥ።
የዓለማችን ማማር፤ መዋብ፤ ማጌጥ ምንጩ የውህድ ማንነት ጸጋ፤ ክህሎት፤ ልምድ፤ ተመክሮ፤ ብቃት ፈጣሪ በሰጠን የጊዜ ቀመር ውስጥ በተፈጥሯዊ ሂደቱ ንጥር ሆኖ መኖራችን ብሩህ፤ ቀለማም ይሆን ዘንድ የፈጣሪ፤ የአላህ ምርቃት በመሆኑ ነው።
ይህን ስንተላለፍ፤ ስንጥስ፤ ወይንም ስንጠቀጥቅ ምርቃታችን ይነሳል። ምርቃት ሲነሳ ወናነት ይነግሳል። ወናነት ደግሞ ለትውልድ የሚያስተርፈው የህሊና ጥሪት የለውም። ሁልጊዜ ተተኪ ትውልድ ከእኔ በግል፤ ከሁላችን በጋራ ምን ይጠበቃል ማለት ይገባል።
1) እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መክሊት ይዞ ይወለዳል።
2) እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ ጥሪ ይዞ ይወለዳል።
3) እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መልዕክት ይዞ ይወለዳል።
ስለሆነም እያንዳንዱ ልጅ ለእቴጌ ዓለማችን ፖስተኛ ነው። የውህድ ማንነት ጸጋ ሲታከልበት የአቅም፤ የችሎታ፤ የመሰጠት ኩነት ይማከላል። "ከአንድ ብርቱ ሁለት መዳህኒቱ" ቅኝቱ ይኽው ነው። የትዳር ሚስጢሩም ይኽው ነው።
ስለዚህ በዓለም የአኗኗር ዘይቤ በአብሮ መኖር የሚገኙ በረከቶች ሊከበሩ እንጂ መሳቀቂያ፤ ማስፈራሪያ፤ ማስደንገጫ፤ ሊሆኑ አይገባም። ከግብጽ፤ ከጣሊያን፤ ከሱዳን፤ ከዴንማርክ፤ ከቻይና፤ ከህንድ፤ ከሳውዲ፤ ከአንጎላ፤ ከሀንጋሪ፤ ከቼክ፤ ከጀርመን፤ ከአሜሪካ፤ ከካናዳ፤ ከእንግሊዝ፤ ከኤርትራ፤ ከሲዊዲን፤ ከፊሊፒን፤ ከግሪክ፤ ከፖርቹጋል፤ ከስፔን ወዘተ ከ193 በላይ አገሮች የሚወለዱ፤ የተወለዱም ልጆች አሉን። ይህ በመታደል፤ በመመረቅ የሚገኝ እንጂ ስለተፈለገ የሚታፈስ የመንፈስ ኃብታት እንኳን አይደለም።
ስለተሰጠን ጸጋ፤ ስለተመረቅንበት እዮራዊ ሽልማት አምላካችን፤ አላሃችን ልናመሰግነው እንጂ ልንወቅሰው አይገባም። ውሃ በቀጠነ ቁጥር ልንጠረጥረው፤ የፈተና ግንባር ፈጥረን ልናፋልመው አይገባም።
በክርስትና እምነት እና አስተምኽሮ ተፈጥሮን ከጥፋት ውሃ የመታደግ ዶግማዊ ስጦታ የኖኽ መርከብን እንሰብ። ውኽድ ማንነት ለእኔ የኖኽ መርከብ ነው። የጸጋ፤ የበረከት፤ የመሰጠት፤ የመመረቅ የመዳንም ህብራዊ ጣዝማ ነው።
#ክብርት ወ/ሮ አምለሰት ሙጬ ፖለቲከኛ ናት ብዬ አላምንም። ስትሆን ለሙግቱ እኔው እበቃታለሁኝ።
አንድ ጊዜ ክብርት ቀዳማዊ እመቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው ጎንደር ከ30 ደቂቃ በላይ ህልውና ያልነበረው ዳቦ ቤት አሰርተው፤ " ዳቦ ብሉ ተብላችኋል" ብለው ተናገሩ። ሌላ ሞጋች አያስፈልገወትም እኔ እበቃወታለሁ አልኩና ፃፍኩኝ። እኔን ደግሞ አይችሉኝም - በሙግት። ፖለቲካ ጥሪወት በፍጹም አይደለም። ይተው! ብዬ አክብሬ ፃፍኩኝ። ይድረስ ብዬ በአድራሻቸው ነው የፃፍኩት።
በዛው ዘመን ሰሞናትም ጅማ ዳቦ ቤት ያስመርቁ ነበር። ተከታትዬ አዳመጥኳቸው። ብናኝ የፖለቲካ መንፈስ አልነበረውም። እና እኔ
ወ/ሮ አምለሰት ሙጬ ፖለቲካ ውስጥ ስትገባ አልሳሳላትም በትጋት እሞግታታለሁኝ።
ዕውነትን እምገፋበት ምንም ምክንያታዊ ሁነት የለም እና። ለዕውነት የክት እና የዘወትር፤ የቤት እና የዕዳሪ ብሎ ነገር በእኔ ቤት የለም። እርግጥ ነው ሴቶችን ለመሞገት #ዳ የምልበት ሁነት አለ። በተለይ ፖለቲካ ውስጥ ሲገቡ በዛ መገኜታቸው ሊደነግጥ ስለማይገባ። የሴቶች ፖለቲከኝነት አድዮ አበባ ነው። ለመዝለቅም ሩቅ፤ ለመቀጨትም ቅርብ።
"#አረንጓዴ መሬት" (ባለቤቱ ወ/ሮ አምለሰት ሙጬ)
ክብርቷ ገና በአፍላ ዕድሜዋ ምን አስነስቷት "አረንጓዴ መሬት" ዶክመንቴሽን እንደ ሠራች ዛሬ ድረስ ይገርመኛል። የጠቅላይ ሚኒስተር አብይን "አረንጓዴ አሻራን" ማለቴ አይደለም።
ጎንደር ወደ በኖኽ መርከብ መሰል ወደ ተሠራው ጥንታዊው ደብር ወደ ደብረብርኃን ሥላሴ ቤተክርስት ሲኬድ ከቆባስጥል ቁልቁለት መጠናቀቅ ጋር ከአባ እንቁባህሬ ቤት ልንደርስ ስንል ዳገት አለ። ዳገቱን ተሻግሮ ወደ አንገረብ አቅጣጫ ሰፊ ኮረብታ አለ። ከዛ የእኔ አባት አባባ መሬት ገዝተው ይሁን ተመርተው ትዝ አይለኝም ደን ያለሙ ነበር። ደኑ የጽድ ነበር። ለምን ጽድን እንደመረጡም ሚስጢሩን አላውቅም።
የሆነ ሆኖ አባባ እጃችን ይዘው ይሄዱ እና በየሥማችን እዬወሰዱ ያስተክሉን ነበር። "የሰቲት በርኃማ ወላፈን ጎንደርን ቆላ ያደርጋታል" የሚል ስጋት ነበራቸው። ጎንደር ከተማ ወይና ደጋናት። ይህንን ተመክሮ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ጎንደርን በሚመለከት በነበራቸው አወንታዊ ዕይታ በ2010 ዓ.ም ጽፌውም ነበር። በኢሠፓ ዘመንም በየስብሰባው መጨረሻ የጉባኤ አባላት በሥማቸው ችግኝ እንዲተክሉ ይደረግ ነበር።
ይህቺ ወጣት እንደ እኔ የልጅነት ጊዜ ይህን የመሰለ ተመክሮ ቢኖራት በሆነ። ግን ጥሪዋ አህዱ ያለው በዚህ መሰል ተፈጥሯዊ ጸጋ ነው። በጣም የሚገርመኝ ትጋት ነው። ከዛ በቋሚ አምደኝነት በጹሁፍ "በረቂቅ" የብዕር ሥም፤ በሞዴል፤ በፊልም ፕሮዳክሽን፤ በቻሪቲ ተግባራት ሙያውን ለማለምለም በትምህርት አሳድጋ ንቁ እና ብርቱ ተሳትፎ ስታደርግ ቆይታለች።
"ምን አለሽ" ፊልምንም ራሷን ችላ፤ ሥልጡን በሆነ ጥራት ባለው ፕሮዳክሽን ሠርታ ለዕይታ አብቅታለች። "#ጧፍ እስከማርንም" ያን ገድለኛ የፍቅር እስከ መቃብር መጸሐፍ በደራሲ፤ በሙዚቃ ጥበበኛ ባለቤቷ ልዩ በሆነ አቅም፤ ነፍስን በሚገዛ ሁነት መርታም፤ በተዋናይነት ሠርታም አሳይታናለች። የናፈቀኝን ጎታ ያዬሁት ያን ጊዜም ነበር።
የሶሚክስ (ሁለገቡ የጥበብ ድንቅ በሰውመሆን ይስማው)ተጀምሮ የተቋረጠው የፍቅር እስከ መቃብር ፊልም ጥንስሱ ነፍሱ ከዚህ ጋር የተያያዘ ይመስለኛል። እርግጥ ነው ክስተታዊ መጽሐፍ የመንደር ምስረታውን አክሎ ጥቂት ክፍል እንደታዬ ተቋርጧል።
እኔ "ፍቅር እስከ መቃብርን፤ ዘጠና ደቂቃ በኢንተቤ፤ ምጽዓተ እስራኤል እና ፌያሜታን" እያንዳንዳቸውን 15 / 15 ጊዜ አንብቤያቸዋለሁኝ። ትረካውንም አልጠግበውም። "ፍቅር እስከ መቃብር" በጣም የሚናፍቀኝ ሆኖ የሰብለወንጌል እና የበዛብህ ታሪክ ግን ዘመን የሚፈትነው ክስተታዊ ጸጋ ነው ፍቅር እስከመቃብር።
አንድ ቀን ነፃነቱን ያገኜ ዘንድ ህልሜ ነው። የጥበብ እገዳ ዊዝደምን ክው አድርጎ ያደርቃል። ኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያ ማለት የተበጀችበትን እውነት እዬሸሹ ከሆነ ዛሬም፤ ነገም፤ ተነገ ወዲያም ምፃት ላይ ይሆናሉ። የትውልድ ቀረፃ እክል ይገጥመዋል።
"#ጧፍ" ምርቃቱ ተከለከለ። ያን ጊዜ ህወሃቲዝም ነበር። ፍቅር እስከ መቃብርም በጦርነት ውስጥ ተዘጋጅቶ ተቋረጠ። በዘመነ አብይዝም። የትውልዱ የፈጠራ ችግኝ እና ሰብላማነቱን እንዲህ ይፈትነዋል።
በማን? በየዘመኑ የኢትዮጵያ ተጠራጣሪ የፖለቲካዊ ባህል። ጥበብ ቢያስተምር እንጂ መንበረ መንግሥት ስጡኝ ጥያቄ የለውም። መንበረ ሥልጣን ለቋሚ ፖለቲከኞች የመተው ጥበብ ያለውም ጥበብ በነፃነት ከተከወነ፤ አድማጭ ከተገኜ ስስት የሚባልለት መንበር ይረጋል። ይረጋጋል። ክፍተትን የሚያሳይ ራዲዮሎጂ ነውና ጥበብ። አድማጭ ብቁ ካገኜ። ጥበብ እና ፍጥረቱን አትፍሩ።
"#ምን አለሽ።" (ፊልሙ የአመለ ነው።)
አገራችን ኢትዮጵያ ትርታችን ለሆን ሁሉ "የምን አለሽ ገጽታ" እንድናይ ማድረግ በራሱ ቋሚ ተቋምነት ነው። ሰፈሩን፤ የአኗኗር ዘይቤውን፤ ድህነት እና ድሎቱ እንደምን በአብሮነት እንደሰከኑ ወዜን አዬሁበት። ጠረኔን አጣጣምኩበት። "ምን አለሽ" ተራን እራሱን እኔ አላውቀውም። አዲስ አበባ በተለያዩ ኮርሶች፤ በኗሪነትም ባያትም ቅሉ።
"ማያ" የሚባል ፕሮዳክሽን አላት። "አንድ ቀን ከአምለሰት ጋርም" የሚመስጥ ዕሳቤ ነው። አሁን "ቆይታ ከአምለሰት" ጋር ፖድካስት አላት። አልፎ አልፎ አዳምጠዋለሁኝ። መደበኛ አይደለሁም። ባደመጥኩት ሁሉ ግን አንድም ቃል የፖለቲካ መደበኛ ቃላትን ስትጠቅስ ሰምቼ አላውቅም። ካልሰማሁት ከኖረ ልትነግሩኝም፤ ልታርሙኝ ትችላላችሁ። በፖለቲካ ጭብጥ ዙሪያ ያወያዬቸው ጠንከር ያለ ሙግት ከኖረ። ቃለ - ምልልሷ ለተጠያቂው ሆነ ላድማጩ የእናት ጓዳ ነው። ለስላሳ ነው። የማያስደነገጥም።
የፖለቲካ ተግባር ሥራው አብዝቶ ቁጭ ብሎ መሥራትን፤ ቁጭ ብሎ በቋሚነት ማሰብን፤ ቁጭ ብሎ ጥሞና ወስዶ ማድመጥን፤ በተከታታይ እና በትጋት በቦታው መገኜትን ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ አቅሙ ሲኖር፤ ሲገኝ ነው። መማር ብቻውን ፖለቲከኛ አድርጎ መሰጠቱን አያብራራም። ከቅባ ከጥሪ ጋር የተያያዘም ነው።
በሌላ በኩል እያንዳንዱ ሙያ የራሱ ሜቶሎጂ አለው። የያንዳንዱ ሙያ ቃላቶቹ የተለዩ ናቸው። ህክምና ላይ ቁርጥማት፤ ቁርጠት፤ ግፊት፤ ህመም፤ አለ።
ፖለቲካ ሙያ ነው። ፖለቲካ ፍልስፍና ነው። ፖለቲካ ሳይንስ ነው። ዓለም የሚመራበት ቁንጮ ክስተት ነው - ፖለቲካ። ፖለቲካ አንቱ የተባሉ ቋሚ ሠራተኞች አሉት። በተለምዶ፤ በተመላላሽነት የሚሠራ የአዘቦት የመዝናኛ ተግባር አይደለም - ፖለቲካ። ቢሮክራሲ፤ መደራጀት፤ ማደራጀት፤ መምራት፤ ለመመራት መፍቀድ፤ ተናጋሪነት፤ ስክነት ወዘተ ይጠይቃል። ይህን የምለው ፖለቲከኛ የሚባለው ሰብዕና መበራከቱ ብቻ ሳይሆን የተሳሳተ ፍረጃም ስለአለ ነው።
የክብርቷ ፖድካስት የታቀደ ጥያቄ እንኳን አይቼበት አላውቅም። መግቢያው በተደጋጋሚ ስለምትለው ቋሚ ሊመስል ይችላል። ጥያቄወቿ መነሻወቻ አብዛኛውን ጊዜ ደራሽ ወይንም ድንገተኛ ናቸው። ይህ ማለት ከእንግዶቿ መልስ፤ እንግዶቿን ከመረጠችበት ሰብዕና የሚመነጩ ናቸው። ተጠያቂወቿ ከሚሰጡት መልስ ያልታሰበ ቦታ ላይ መዝዛ ትጠይቃለች። እምታዘወትረው ቃል "ኢንተረስቲንግ" ነው፤ የሚገርማት ታሪክ ሲገጥማት።
የሚዲያዋ ፎርማት ተጽዕኖ ፈጣሪነት ላይ አተኩሮ ነው እማዬው። ሌላው አቅርቢልን ስለተባለችም ይሁንታ ሰጥታ የምትተገብርም አይመስለኝም።
#ትዳር እና እናትነት።
የተሳካ ትዳር፤ አጓጊ የእናትነት ሁነት አያለሁኝ። ይህ ሊያስመሰግናት፤ ከሁለገብ ተልዕኳዋ ጋር እንደምን አስማምታ የማስቀጠል መቻሏ ጸጋዋ ነውና ሊያስከብራት፤ ሊያስመሰግናት፤ ዕውቅና ሊያሰጣት ይገባል ባይ ነኝ። ሊያሸልማትም። ከመጀመሪያ የትዳር አጋሯ ጋር ነው ያለችው። የነገ ተስፋ ልጆችም ስለአላት የገዘፈውን የእናትነት ኃላፊነቷን እየተወጣች ያለች እህት ናት።
በትዳሯ አጋሯ የጥበብ ተግባር ላይ በየዘመኑ በሚገጥመው ወጀብ እና ፈተና፤ እንግልቱን ተቋቁማ፤ ጥሪዋን ሳታጓድል እናትነቱን፤ ሚስትነቱን፤ ልጅነቱን፤ እህትነቱን፤ የጥበብ ቤተኝነቱን አስተካክላ፤ በሚዛን፤ በብቃት መከወን መታደልም ነው። መሰጠትም።
እኔ አድናቂዋ፤ አክባሪዋም ነኝ። ከምሳሳላቸው ጥቂት ግን ብርቱ አብነታዊ የአገሬም፤ የዓለም ዓቀፍም አንስቶች ውስጥ አንዷ ናት። ውህድ ማንነቱን እራሱ የምወደው፤ የሚስበኝ፤ ምክንያታዊነቱ ተስፋዬን የሚያፋፋ ነው።
እርግጥ ነው ከ20 ዓመት በላይ በዘለቀው የሚዲያ፤ የጸሐፊነት ሰብዕናዬ ጽፌያት፤ አንብቤያት፤ ተርጉሜያት፤ መስጥሬያት አላውቅም። እኔ በጣም ለጋስ ነኝ። ቅናት፤ ምቀኝነት ስላልፈጠረብኝ በማየው መልካም ነገር ሁሉ ስለአገሬ ልጆች ይሁን በዓለም ዙሪያ ስላሉት ወገኖቼ እጽፋለሁ፤ እሞግታለሁ። ሰብዕናቸውንም በነፃ እገነባለሁኝ። አወንታዊ ሃሳብ ካለኝ ብቻ ዩቱብ ላይም ዕይታዬን አጋራለሁኝ።
ሁለገቧ ወ/ሮ አምለሰት ሙጬ የዕውቅና፤ የተጽዕኖ ፈጣሪነት ጥገኝነት የሚያማትር ምንንም ሁነት የላትም። ለጥሪዋ ብቁ ናት። እራሷ #ተቋም ለመሆን በቂ ናት። ተጽዕኖም ፈጣሪ ናት። እርጋታዋን አብዝቼ ዕወድላታለሁኝ። ለሴት ልጅ ውበቷ መጨመቷ ነውና።
በመጡ፤ በሄዱ ቁጥር የአንድ የጨመተ ሰብዕና ሊንገላታ አይገባም። እኔ ክብርት ወ/ሮ አምለሰት ሙጬን እምመድባት ከሳይለንት ማጆሪቲው ጋር ነው። አብዛኛው የሳይለንት ማጆሪቲው ጭምትነት ውህድ ማንነትም ይመስለኛል። ጥናቱን ምቹ ሁኔታ ገጥሞኝ ባልሰራበትም።
ጭምቱ ማህበረሰብ ለአገሩ ባላ እና ወጋግራ፤ ፒላር እና ሚዛን አስጠባቂ ከመሆኑም በላይ ለአገር፤ ለአህጉር፤ ለዓለም የአኗኗር ዘይቤም ሐዋርያ ነው ብዬ አምናለሁ። ሳይለንት ማጆሪቱ ቅናት የሌለበት ቀና፤ ቅን፤ አወንታዊም ነው ብዬም አምናለሁኝ።
ጭምቱ ማህበረሰብ በእኔ አረዳድ ከጎረፈው ጋር የማይጎርፍ፤ ከዘለለው ጋር የማይዘል፤ ግራ ቀኙን በርጋታ፤ በአደብ፤ በአቅል የሚያስተውል፤ ከውስጡ የሚደርስ ዕውነት ሲያገኝ ካለ ካድሬነት፤ ካለ ጉርሻ ወይንም ድጎማ፤ ካለ ፕሮፖጋንዲስት ለመወሰን፤ ለመወገን የማይቸገር ሙሉ አቅም ያለው ወሳኝ የማህበረሰብ አካል ነው። አብዝቼ እኔ ለፖለቲከኞች እንደ አለ ላማትቆጥሩት ሳይለንት ማጆሪት ቦታ ይኑራችሁ እላለሁኝ።
ሳይለንት ማጆሪቲው ከአንድ የውሳኔ አቅም ሲደርስም ሳይጠራራ በራሱ ጊዜ ነጥቡ ላይ በትክክለኛው ጊዜ እና ወቅት፤ ዘመንና ምዕት ከች የሚል "ሙያ በልብ" የሆነ ካሽ የማህበረሰብ ክፍል ነው። ይገናኛል። ይህ ጸጋው ነው።
የምንም ዓይነት የማንነት ልዩነት አይገድበውም። ማዕቀቡን ጥሶ ወጥ ኃይል ሆኖ ይገናኛል። አንዲት አገር አለኝ የምትለው ቋሚ የመንፈስ ዘብ- አደር አለ ከተባለ ሳይለንት ማጆሪቲው ነው።
የጭምቱ ማህበረሰብ የሰብዕና አደረጃጀት፤ በዝምታው ውስጥ ያለው ፍሬ ነገር ወቅታት ቢፈራረቁ ዕውነት፤ መርኽ፤ ፋክት በሚለው ዓውደ ምህረት ላይ ህብራዊ ሆኖ ንቅንቅ የማይል ሁነኛ አቅም ነው። ቅኔ ነው።
ክብርት ወ/ ሮ አምለሰት ሙጬ ሆይ! ከልጅነት እስከ ዕውቀት በተሳተፍሽባቸው ሁነቶች ሁሉ ኤትክስሽ፤ ሞራልሽ፤ ጭምትነትሽ፤ ትጋትሽ፤ ዲስፕሊንሽ ሁሌም ይመስጠኛል። ደርባባ ነሽ። ደልዳላ ነሽ። እግዚአብሄር አምላክ ይህን ስክን ያለ የመሰጠት ምርቃትሽ ሳይባክን ይቀጥል ዘንድ ፈጣሪ ይርዳሽ። አሜን።
ፖለቲካ እና ፖለቲከኝነት የተለምዶ ማህበርተኝነት የኢቬንት ጉዳይ፤ ወይንም የቅዳሜ ገብያ ውሎም አይደለም። ለዚህ የተፈጠሩ ባለሙያወች አሉበት። የቅኔው ጎልማሳ የአርቲስት፤ የጸሐፊ፤ የፓን አፍሪካኒስቱ (የዶር. የክብር ) ቴወድሮስ ባለቤት መሆን፤ ወይንም የየዘመኑ የካቢኔ አባል የትዳር አጋር መሆን ፖለቲከኛ አያሰኝም። አያስብልም።
አርቲስት ቴዲ አፍሮ ፖለቲከኛ ነው መባል ባይገባኝም፤ አይደለም ቋሚ የፖለቲካ ሠራተኛ ቢሆን እንኳን። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስተር የአቶ ኃይለማርያም ደስአለኝ ባለቤታቸው ክብርት ወ/ ሮ ሮማን ተስፋዬ ፖለቲከኛ ተብለው ሲወቀሱ፤ ሲነቀሱ ሰምቼ አላውቅም። ዕውነትን በማስተዋል መመርመር ያስፈልጋል።
ሌላው እናት እንድትጨነቅ፤ እንድትሰጋ፤ ትትርናዋ እንዲጎሳቆል፤ ልፋት ድካሟ እንዲጓጉል፤ እንዲስተጓጎል የምትጠረጠርበትን መስመር መቀየስ የተገባ አይደለም። ወ/ሮ አምለሰት እናትም ናት ለወላጆቿም ልጅም ናት።
እስር ቤት ለሴቶች ውሃ ያዘለ ተራራ ነው። ወዘተረፈ ፈተና አለበት። ሁሉ አይነገርም። መከራው ጥልቅ ቢሆንም ሜዳ ላይ እንደ ቄጤማ ሊነሰነስ አይገባም። ሁሉም ከእናት ነው የተፈጠረው እና በጥልቀት፤ በማስተዋል እናታዊነት ማለት ለልጆች ምን ማለት እንደሆን ሊመረምረው ይገባል። የዓይን ብርሃን ከፋች ልጅ ነው። ልጅ የሚገኜው ደግሞ ከእናት ብቻ ነው። የራስ ልጅ ይሁን ከደግነት የሚገኝ ልጅ ትርጉም እናታዊነት። እናት ፈውስ ናት።
እናት ብርሃን ናት። እናት ከደስታ በላይ ሐሴት ናት። እናት ትውልድም ናት። እናትነት የትኛውም ተቀናቃኝ ፈትኖ የማያሸንፈው እዮራዊ አምላካዊ ስጦታ ነው። ፈጣሪን የሚያከብር፤ ለአላህ ህግጋት የሚገዛ ማንኛውም ሰብዕ ሚስጢሩን ከዚህ አንፃር ሊያዬው ይገባል።
በሌላ በኩል እንደ አገር ልጅነት ነገ ካስፈለገን ልጆች ከእናት አባታቸው ጋር ማደጋቸው ቁልፍ ነው። እናትነት ችግር በገጠመው ሁነት፤ ልጆች ሲማሩ ህሊናቸው ይወጠራል። ይፈራሉ። ፍርሃቱ ወደ ሥነ - ልቦና ህመም ሊወስዳቸው ይችላል። ይህ ደግሞ በራስ የመተማመን አቅማቸውን ይጎዳዋል። ይህን በትውልድ ተስፋ ጋር ስናዬው የማግሥት ድርቀትን ያመጣል።
የተጓዝንበት መንገድ ትክክል አይደለም። ብዙ አጥፍተናል። ይህ ዘመን እንማርበት ዘንድ ሰሌዳውንም ቾኩንም አሰናድቶ እዬጠበቀን ነው። ከእኛ የሚጠበቀው እሺታ፤ ይሁንታ ብቻ ነው።
እሺታው ሆነ ይሁንታው ምንም የቂም፤ የቅናት፤ የጥላቻ፤ የበቀል፤ የቁርሾ እራፊ ሊኖርበት አይገባም። በተለይ ትልልቅ ሚዲያ የምትመሩ ወገኖቼ ከስሜታዊ አገላለፆች እራስን ማቀብ በእጅጉ ያስፈልጋችኋል ብዬ በትህትና እና በአክብሮት አስባለሁኝ።
ልጆች የማህበረሰብ ናቸው እና። ቆይታችን አጭር፤ ስንብታችንም የአፍታ እፍታ ነውና። ለትውልድ የጭንቀት የብድርን ኢንፓዬር አናደራጅ። ከሁሉ ፈጣሪ፤ አላህ ይከፋብናል። ልዑል እግዚአብሄር የፈጠረን - ለማሳጣት፤ ችግርን - ለማባባስ ሳይሆን ህሊናችን ለዳኝነት ዘብ እንዲቆም ነው። ጥሪያችን። ህሊና የተሰጠን ለዚህ ብቻ ነው።
ግድፈት ሰውኛ ነው። ማረሙን መፍቀድ ትልቅነት ነው። እኛ የራሳችን ሐዋርያ መሆን ከፈቀድን፤ ሰውነታችን አክብሮቱን፤ አትኩሮቱን በራሱ ጊዜ ያበጃዋል። ማዕከላችን ሰውኛ እና ተፈጥሯዊ ቢሆን ነው ትክክለኛው ጎዳና።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል በብዙ ተጎድተናል። የኢትዮጵያ እናቶች ተሰቃይተዋል። ቢያንስ እኛው ጉዳትን በማያስከትሉ ሁነቶች፤ አገላለፆች፤ የቃላት አጠቃቀሞች ላይ ጥንቃቄ እናድርግ። ዕይታዬ በትህትና ነው።
ወገኖቼ ሆይ! ጥንቃቄ ያተርፋል እንጂ አያከስርም።
#ፎቶወች አለጥፍም። ያሰርዙታል ሥራ አልቦወች።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
28/04/026
ማዳን #ከመዳን ይጀምራል።
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ