#ለብልፄው ብርሃነ ትንሳኤው ምኑ ይሆን? አቶ ዩሱፍ ያሲን እና፤ ወይዘሮ ማህሌት ሰለሞን ሁለት የቴዲ አፍሮ የቅርቦች መታሰራቸውን ሰማሁኝ።

 

#ለብልፄው ብርሃነ ትንሳኤው ምኑ ይሆን?
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 
ምዕራፍ ፴፩።
 
ብልፄው ትንሳኤን አስመልክቶ የፖለቲካ እስረኞችን ከህሊና እስረኝነት ለቆ ይቆዬኛል ስል ተጨማሪ እስረኞችን አስሮ ነው ያገኜሁት። ከጥሞና ስመለስ። አዝኛለሁኝ። ሰሞነ ህማማት አልፎ ትንሳኤ በዳግም ህማማት??
 
በትንሳኤ እንደምን የሰው ልጅ ይታሰራል? 
 
ትንሳኤ እኮ የኃጢያት ግድግዳ ተንዶ ብርኃን የታወጀበት የሐሤት ሰሞን ነው። 
 
#እናት እንደዚህ ተይዛ ትታሠራለችን?
 
እናትነትን እንዲህ መቀጣጫ ማድረግ ይገባልን?
ዕድሜስ - አይከበርንም?
ሙያ መከበሩ፤ ጥበቃ ማድረጉ ቢቀር እንደምን እንደ ቀራንዮ ዕለት እንዲህ ያለ የግፍ አያያዝ ይፈጸማል?
ይህ አክሰሱ ላላቸው አዲሱ ትውልድ ይበጃል ወይ?
 
ለመሆኑ ኢትዮጵያ ምን ያህል ታዳጊ ወጣት አላት?
በዚህ አፈፃጸም ታዳጊ ልጆች የሥነ - ልቦና ስቃይ አይደርስባቸውምን?
 
"#የብሬ ቀን።"
 
ትናንት "የብሬ ቀን" ነበር ማለት ይቻላል። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ከትምህርት ሚኒስተር ጋር ሆነው ለልጆቻችን እየሠሩ እንደሆነ ማብራሪያ ሲሰጡ ነበር። ምን ዋጋ አለው። ያን የትምህርት ሚኒስተር ድንቅ ጥረት እንዲህም ተናደ እኮ። ለዛውም 5 ሚሊወን የአማራ ህፃናት ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን #ቆዬን ብለን ወረፋ አስይዘን ማለት ነው።
 
ሰሞኑን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ "ወቼው ጉድ" ከሚባል ፖድ ካስት ጋር ረጅም ግን የማይሰለች መምህር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። እሳቸው ስለተጠየቁ ነው ያዳመጥኩት። ከሚበልጡት ሰው በታች ሥር ሆነው መሥራትን መፍቀዳቸው የምመሰጥበት ክስተት ነው ለእኔ። ዕድላቸውን አላፈሰሱም። ከኢትዮጵያ መንግሥታዊ አመራር ዘይቤ ጋርም ተገናኝተዋል።
 
የሆነ ሆኖ የወቼ ጉድ ፎርማቱ ደስ ይላል። ነፃነቱ ያበረታታል። 5 ሰዓት ነው እያረፍኩ አዳምጨዋለሁኝ። ከዛውም ላይ ጽፌዋለሁ ይህን መሰል ውይይት ሴብ ማድረግ፤ መድብል መሥራት እንደሚያስፈልገው። ልዩ ውይይት ነው። ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ጎራ ሊሉበት ይችሉ ይሆናል።
 
ከማህበራዊ ሚዲያ ዞር እምለውም ይህን መሰል የቁምነገር ዓውድን በስክነት ለመፈተሽ ነው። አሁን ዘግዬት ብዬም ሳዬው ሚሊዮኖች ታድመውበታል። አስተያየቶችንም አንብቤያለሁኝ። ቃለ ምልልሱ ዝርዝር መረጃም አለው። ያ ይመስለኛል ለትናንት ክብርት ወ/ሮ ሙፍርያት ካሜል የመሩት ጉባኤ የተካሄደው። ዘለግ ያለ ምስጋናም፤ ከፈላሉ - ቁጣወች እና ትልልፎችም፤ በረድ ብሎ ሥራችን እዩልን፤ የጎደለውን እንሞላለንም፤ ትህትናዊ ነገርም አይቻለሁኝ።
 
ፕሮፌሰር ዶር ብርሃኑ ነጋ እና ውሳኔያቸውን አስመልክቶ ከድርጅታቸው ሲሰናበቱ ባር ባር ብሎኝ ነበር እራሱን አስችዬ ጽፌበት የነበር እኔ ምዕራፍ 18 ከማጠናቀቄ በፊት። ከዛ ቃለ ምልልሱን ሳዬው ታግሼ አዳመጥኩት። አዳምጡት። ጥሩ ልምድ ትቀስማላችሁ።
 
የሆነ ሆኖ የመዋለ ህፃናት ግንባታ፤ ያሉ ትምህርት ቤቶችን የሟሟላት ብቁ አድርጎ፤ የቦሌ ትምህርት ቤት ጉዳይ ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስተር አብዬ አህመድ አንስተዋል። እዛ የሚማሩ ተማሪወች ግን እነኝህ ሁለት የጥበብ ቤተኞች፤ ሌሎችም በአሸባሪነት ተፈርጀው የታሠሩ የአዲስ አበባ ልጆችን ያያሉ። አስተሳሰራቸው በራሱ #አስደንጋጭ ነው። ልጆች ከዚህ ምን ይማራሉ? ትምህርት የቀለም ወይንስ የጦር የመሳሪያ ትዕይንት?
 
ልጆች ከሚሰሙት ይልቅ #የሚዩት ይበልጥባቸዋል፤ #ያሳምናቸዋልም። አማካሪ፤ አቀናባሪ፤ ቃል አቀባይ ለመሆን የሚያስቡ ተማሪወች ራመያቸውን ያጨናግፋል ወይንም ያሳምማል፤ እራሱ የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት፤ የፋና ላምሮት ተከታታይ መደበኛ ተግባርን እርር ቁስል ያደርጋል።
 
ፕሮፌሰር ዶር መራራ ጉዲና ህወሃት የአስቸኳይ ጊዜ ዓውጅ ህወሃት ዓውጆ ግን እሱን ጥሰው፤ በግንቦት 7 ጋባዥነት አውሮፓ ህብረት ስብሰባ ላይ ተገኙ። ሲመለሱ ባዶ እጃቸውን ሳምሶናይት ይዘው ነበር። ሮኬት ታጥቀው እንደተመለሱ ነበር ታጥቆ የጠበቃቸው #አጋዚ። እርግጥ ነው እሳቸውም ህግ ማከብር ይገባቸው ነበር። የተከለከሉ ነገሮችን መጣስ ግን ይወዳሉ። ሁለተኛውን የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅንም ጥሰውም ከአቶ በቀለ ገርባ ጋር ወለጋ አካባቢ ሄደው፤ጊዜያዊ እስር ገጥሟቸው ነበር። ደራሽ ታጋዮች ስላሉ ነው ይህን በምልሰት እማብራራው። 
 
ስለሆነም ያን ጊዜም ልጆችን #ቴሬራይዝድ የሚያደርግ ነው ብዬ ሳተናው ድህረ ገጽ ላይ ጽፌ ነበር። ፕሮፌሰር ዶ. መራራ ጉዲና የኢትዮጵያን ህገ - መንግስት ማክበር እንዳለባቸውም ያጠይቅ ነበር ጹሁፌ። ያ እንደመልካም ነገር ተቆጥሮ እንሆ በዘመነ አብይዝም ተደገመ።
 
ውስጤ በጣም ነው ያዘነው። እጅግ ነው ጥልቅ ሃዘን የተሰማኝ። አንድ አቅጣጫ ብቻ አይደለም መታዬት ያለበት። ተያያዥ ጉዳዮችም ሊጠኑ ይገባል ከእርምጃ በፊት። ሙዚቃ የፖለቲካ ድርጅት አይደለም። የምርጫ ውድድር ላይም አይሳተፍም።
 
ፋና ላምሮት ዛይድ እና ኮከብ ከሚባሉ ባንዶች ጋር በቋሚነት ይሠራል። የወጣቶችን የሙዚቃ ውድድር የሚዳኙ ሦስት ቋሚ እና አንድ ጊዜያዊ ታዛቢ ዳኛም ውድድሩ ሊጠናቀቅ ሰሞናት ያክላል። እነሱን ማሰር ማለት ነው። ነግ ለእኔ ብሎ ማሰብ ይገባል። ሙዚቃ እንደሌላው ክስተታዊ ጸጋ የራሱ ቤተሰቦች አሉት። አድናቂወች አሉት። ኤክስፐርቶች አሉት። ሙያም ነው የሚመረቁበት ባለፈም የሚሸለሙበት። ሥጦታም ነው። ጥሪም ነው የእዮር። ይህን መታገል የሰጠውን መፈተን ነው።
 
"ጥበብ ቤቷን ሠራች፤ ሰባት ምሰሶም አቆመች።" ሥነ - ግጥም እንደ ሐተታ ታቅዶ የሚሠራ አይደለም። እርዕስ ለመስጠት የሚያስጨንቅ ነው። ትርጉሙ እራሱ ለገጣሚው ይከብዳል። በውነቱ ሥነ - ግጥም እና ሥነ - ሥዕል ለእኔ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታወች ናቸው። ተርጓሚው #የዕድምታ ባለሙያ ነው። ከዚህ የላይኛው ጸጋ ጋር መፎካከር የተገባ አይመስለኝም። 
 
ሌላው ……… ሴቶች ዱር ቤቴ ሲሉ፤ ፖለቲካ ሙግት ውስጥ ሲገቡ፤ ሲታሰሩ፤ ሲሰደዱ ያልተፃፈበት #የመከራ ቡፌ ይጠብቃቸዋል። ዕድሜዬን የገበርኩት፤ እንዲህ ኩርኩም ብዬ እራሴን ቀጥቼ የተቀመጥቁት፤ የኢትዮጵያ የጥበብ ባለሙያወች፤ ፖለቲከኞች፤ የሃይማኖት ሰባክያን፤ በተለይ የኢትዮጵያ ሴቶች እናቶች መንገላታት አይገባቸውም በሚል ነበር። እራሳቸው ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድን ወደ ሥልጣን ያመጣው፤ በኃያላን መንግሥታት ይሁንታ ያስገኜው ጉልበታም አመክንዮም ነው ይህ ጉዳይ። 
 
ብልጽግና ያልደከመበትን የሥልጣን መንበር የተቀዳጀው በነፃነት ትግሉ በነፍስ ወከፍ፤ በወልም በተከፈለ መኖርን አሳልፎ #በገበረ ቁርጠኝነት ነበር። ማክበር አልቻልም። አንዲት ምክትል ሚኒስቴር ዲኤታ አሉ "ማን አምጥቶ ደፋብን" ይላሉ። ካድሬ ይባሉ፤ አክቲቢስት ይባሉ፤ ማሟያ ይባሉ አላውቅም። እሳቸውን እንኳን ሥርዓት ሊያስዝ አልቻለም አቤቱ ብልጽግና።
 
#ሌላው የፌድራሉ ፖሊስ መግለጫ ነው።
 
ክራር፤ ጊታር፤ ድምጽ መቅጃ፤ ማይክ፤ አርሞሪካ፤ ፒያኖ፤ እስክርቢቶ፤ እርሳስ፤ ወረቀት፤ ስክሪፕት፤ ከበሮ፤ ሚሞሪ ስቲክ ወዘተ እነዚህ ነው የሚኖሩት ከሙዚቃ ባለሙያወች ቤት ሆነ ስቲዲዮ።
 
"የለሁበትም" ይለናል የአገር ደህንነት አስጠባቂው አካል። ታርጋው ፌድራል ፖሊስ ይላል እኮ። ይህ የአያያዝ ዘይቤ ኡራኖስ ላይ ነው፤ #ጁቢተር ላይ ይሆን የተፈጸመው? መሃል አዲስ አበባ ላይ እኮ ነው። ምን ይሠራል ፖሊስ? ምን ይሠራል ብሄራዊ ደህንነት ተቋሙ?
 
መንግሥት የለሁበትም ካለ #ትይዩ ሌላ መንግሥት አለ ማለት ይሆን? ማነው ይህን የተደራጄ አካል የሚያዘው? እንደ ሃማስ፤ ሄዝቡላ፤ ሃውቲወች ሌላ አገር ይመራዋልን? ይህ ከሆነ አደጋው እጅግ ሰፊ ነው። #ሊባኖሳውያን እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ እየተንገላቱ ነው። የሊባኖስ መንግሥት ሄዝቡላን ማዘዝ፤ ማስቆም አልቻለም።
 
ነገ ለኢትዮጵያ ይህ ሊገጥማት ይችላል። በየትኛውም የመንግሥት ሥርዓት ውስጥ ኢትዮጵያ ይህን መሰል አደጋ ገጥሟት አያውቅም። ራሺያም ሞክራው ነበር። መጨረሻው በምን እንደተጠናቀቀ ይታወቃል። በኤሊኮፕተር አደጋ ፍፃሜው ተደመደመ። 
 
#ፍርሃቴን ላጋራችሁ። 
 
ህወሃትን የሚታገል ታጣቂ ቡድን አፋር ላይ እየተደራጀ ነው ይባላል። ነገ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሚቆጣጠረው በላይ ሊሆን ይችላል። በምንም ተአምር ቢሆን ለለት እርካታ የሚደራጁ፤ ፈቃድ የሚሰጣቸው ስውር መሳሪያ የታጠቁ ሃይሎችን መሠረት ከያዙ በኋላ ማሸነፍ ይከብዳል።
 
ሶርያ እኮ ያ ሁሉ ውድመት ተስተናግዶ፤ የአማፂው መሪ ሱፋቸውን ለብሰው አምጽያን እየመሯት ነው። አሜሪካ፤ ራሺያ ጉዞ አድርገዋል። ባለፈው ሰሞን ጀርመን ነበሩ መሪው። ቅብጥ ያለ አቀባበል እና መስተንግዶ ተደርጎላቸዋል። እርግጥ ጀርመን ከሚሊዮን በላይ ሶርያውያንን ስለተቀበለ ያን #የመመለስ ፕሮጀክት ለማሳካትም ይሆናል። በዛን ወቅት ያን የጀርመን እርምጃ የተቃወመ ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት የህዝብ ድምጽ እያገኜ ነው። ባህላችን፤ ሃይማኖታችን ተበወዘ ከሚል ቅሬታ ይመስለኛል።
 
ጀርመኖች በኳሊዬሽን ለመምራት የተገደዱበት ሁኔታም በዚህ ነው። ይህን ማድረግ የቻሉትም ሥርአትን አስቀድመው ስላደራጁ። ኢትዮጵያ ለናሙና የሆነ ተቋም ፈተናን የሚመክት፤ አናርኪዝምን የሚመክት የላትም። ይህ ልብ ሊባል ይገባል።
 
እጅግ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። "ቁጭ ብለው የሰቀሉትን ቁሞ ማውረድ" ይቸግራል። ለዛውም የታጠቀ፤ የራሱ አመራር ያለው፤ ትልቁ የከተማ የጸጥታ አስከባሪ፤ የፍትህ ሚ/ር አጋር ነው ተብሎ የሚደራጀው የፌድራል ፖሊስ በዲፕሎማሲ ከተማዋ በአዲስ አበባ "የጥበብ ባለሙያወች እንዲህ ሲታሠሩ፤ ቢሯቸው በሌሊት ተከፍቶ ተዘረፈ ሲባል፤ ከጥበብ ባለሙያ ቤት በሌሊት ሲሄዱ" #እጅግ አሳሳቢ ነው። በጣም ከባድ ነው። ያስፈራል።
 
#ብልፄው ግን ………
 
ብልፄው የሃሳብ ሙግት ፈርቶ፤ ሰላማዊ ሰልፍ ፈርቶ፤ የሙዚቃ ክሊፕ ፈርቶ፤ ተከታታይ ተውኔት ፈርቶ፤ ብሄራዊ ንጹሁን ሰንደቅ ፈርቶ ስንቱን ፈርቶ ይዘልቀዋል? 
 
1) ለመሆኑ በአሁኑ ሰዓት እነኝህ ባለሙያወች የት ነው ያሉት?
2) በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?
3) እናት፤ ልጅ፤ ሚስት፤ እህት፤ አክስት የሆናችሁ፤ ያላችሁ ሴት የፖለቲካ ባለስልጣናትስ ይህን ነግ በእኔ ብላችሁ አስባችሁት ይሆን? ግዴለም እሰቡት። ግዴለም አዳምጡኝ። የሚያጎድልባችሁ ነገር የለም። ከነገ መከራ ቢታደግ እንጂ ይህ ሃሳቤ፤ ኪሳራ የለውም።
 
"ፌድራሉ እጄ" የለበትም ሲል፤ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ነገም ያሳፍራል። በዚህ ዓይነት ዘጠና ደቂቃ በኢንተቤ እንደተፈጸመው የሌላ አገር ኮማንዶ ኢትዮጵያ ገብቶ የሚፈልገውን ይዞ ቢወጣስ? በቃ! መልሱ በአላውቀውም ሊደመደም ይሆን። ድሮ የአውሮፓ ህብረት፤ ምዕራብውያን የሚባል ባይወጉበት ያስፈራሩበት የተስፋ ጥግ ነበር። ዛሬ የዘመኑ የፖለቲካ ባህሪ አዲስ ሁነት፤ ለዛውም ተለዋዋጭ። 
 
#ጨካኝ ሃሳብ፤ ጨካኝ ድርጊትን ያስፈጽማል። 
 
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ጸሎት ብዙ ነገር ያስታግሳል እና ለጨካኝ ሃሳቦች፤ ለጨካኝ ድርጊቶች፤ ለፍርሃት አምራች አስተሳሰቦች ሁሉ ፈጣሪ አደብ ይሰጥ ዘንድ በብርቱ መጸለይ ይገባል።ትንሳኤን በዚህ መሰል አስደንጋጭ ሁከት ያ ጨዋ፤ የጨመተ ህዝብ ባይታወክ ጥሩ ነበር። አስፈላጊም አይደለም። 
 
#መሸነፍ ሲሰጥህ ጊዜውን ……
 
መሸነፍን መቀበል ብልህነት ነው። በመሸነፍ ውስጥ የማሸነፍ ኃይል እና ጸጋ አለና። መሸነፍህን ለመቀበል ጊዜ ማግኜት መታደል ነው። መሸነፍህን አዳምጠህ ቀዳዳውን ለመድፈን አቅምህ ከእጅህ ሳለ ማድመጥ ይገባል። ዛሬ ጸጥ ለጥ ብሎ የሚገዛ ህግ ነገ ዕድሉ ላይኖር ይቻላል።
 
በሌላ በኩል መሪነት እናታዊነት ሊሆን ይገባል። ትንሳኤን በስጋት፤ በፍርሃት፤ በጭካኔ መቀበል አይገባም። ለትንሳኤ ባይታመንበትም ክብር ሊሰጠው ይገባል። የራሱ ግሎባል ቤተሰብም፤ ሙሉ አቅምም አለውና። ጸሎቱ፤ ስግደቱ፤ ሱባኤው ከሁሉም በላይ ጉልበታም ነውና። እግዚአብሄርን ማስለቀስም አይገባም።
 
ሌላው በትናንትናው የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ንግግር "ጥበብ እና ብልጽግናን ያቀረቡበት" ዕይታ እና አፈፃጸሙ ትክክል አይደለም። በማለት ውስጥ መሆን ካልተገኜ ስለሚከብድ። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ሥልጣን ከመያዛቸው በፊት የነበሩ ተከታታይ ድራማወች፤ ፊልሞች ተቋርጠዋል። ቀድመው ተዘጋጅተው በእሳቸው ዘመን የተጀመሩትም ተቋርጠዋል። "ደርሶ መልስ፤ የእግር እሳት፤ እረኛዬ፤ ፍቅር እስከ መቃብር" 
 
የአርቲስቶች ድንገተኛ ህልፈት በዚህ ላይ ሲታከል ጥበብ ምን ላይ እንዳለች ኢትዮጵያ ውስጥ ማየት ይቻላል። ሆስፒታል ሾፍሮ ሄዶ ህልፈት፤ ምነው አረፈደ ተብሎ ሲታይ በሥጋ ተለይቶ፤ እንዲያም ሲል በባሩድም፤ ለዚህም እኮ ነው የፊልም ኢንደስትሪው ስለተቀዛቀዘ የኑሯቸው ደረጃ በከፍታ የነበሩ አርቲስቶች ዝቅ ብለው ለመኖር ጋዳ ስለሆነ እኮ ነው ወደ ሌላ መስክ የተሰማሩት አርቲስቶች። የፖድካስት አዘጋጆች፤ ነጋዴወች፤ ወዘተ የሆኑት።
 
#ጥበብ ስትዘጋ ዊዝደም ይሠወራል። 
 
መንበረ መንግሥታት ጥበብን ከፈሩ በሩ በተከረቸመ ቤተ - መንግሥት እንደ ተቀመጡ ይወቁት። ጥበብ ዓይን አላት። ያውም ዓራት ዓይናማ። "ላም እረኛ ምን አለን?" በሚያግባባን ውብ ቃና መግባ ከገደል አፋፍ የምታወጣ ጥበብ ናት። "እግዚአብሄርን መፍራትም የጥበብ መጀመሪያ ነው" ይላል አካል የሌለው የእግዚአብሄር አገልጋይ ቃለ ወንጌል።
 
ብስጭት፤ ትርፍ ነገር፤ ማዋከብ፤ ስጋት መጫን፤ ጥበብን ማገት፤ በጥበብ አድናቂወች ላይ ማዕቀብ መጣል አይጠቅምም። ፈጽሞ አይጠቅምም። "ለእኛ ሳይሆን ለልጆቻችን እየሠራን ነው" ከሚል መንግስት ጫን ተደል ፍርሃት ሰርክ ህጋዊ ዕውቅና ካገኜ ዛሬም፤ ነገም፤ ከነገም በስትያም ባለ ዕዳ ይሆናሉ።
 
በሌላ በኩል ሲከር መበጠሱ፤ ሲሞላም መፍሰሱ በራሱ ጊዜ ሂደት ሊያስማማው ይችላል። ምርጫ ማሸነፍ ሥርዓትን ለማስቀጠል ዋስትና የማይሰጥ መሆኑን በህወሃት ዘመን ከ100% ወደ 0% ቁልቁል ሲያሰኜው አይተናል። ይልቁንም ጠቃሚው ጎዳና ከስሜታዊነት ሰክን፤ አደብ ገዝቶ፤ ጥሞና ወስዶ ሚሊዮኖችን የገዛው ዕውነት ምንድን ነው ብሎ ራዲዮሎጂ መጠቀም ያስፈልጋል።
 
ማንም ባልገመተው ሁኔታ ጭምቱ ሳይለንት ማጆሪቲው የሚሰጠው ግብረ መልስን ሰክኖ ማድመጥ ያስፈልጋል። ዋናው ህዝብ እና መርኃ መንግሥቱ #ጤነኛ ሊንክ አላቸው ወይ ነው ሊመዘን፤ ሊለካ የሚገባው አመክንዮ። ይህን መሰል እናትነትን የመዳፈር ክስተት ገቢራዊ ምላሹ መልካም አይሆንም። ተጨማሪ ጉዳዮችን ያስከትላል።
 
100000 (አንድ ሚሊወን ህዝብ) ይሳሳት ቢባል እንኳን፤ 99 000 000 (ዘጠና ዘጠኝ ሚሊዮን ህዝብ) እንደምን ይሳሳታል? ዕውነት እኮ ቦታውን ለቆ አያውቅም። ድህነት፤ የሰላም እጦት በዓለም ዓቀፍም ድንገተኛ ክስተትም በኮሮና፤ በራሽያ እና ዩክሬን፤ በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት፤ በኢትዮጵያም በድንቅ ኮርድኔሽን የተገታው ማርበርግ በሽታም የፈተን ክስተት አለ።
 
ያን ታግሶ ያለ ህዝብ የሚያጽናናው፤ አይዞህ የሚለው መዝሙር ይሁን ሙዚቃ ማድመጡ እንዴት መታሠሪያው መንገላቻው ሊሆን ይችላል?
 
በቤቱ፤ በዓውዱ፤ በባድማው፤ በትንሳኤው እንዴት? ምን ያጣድፋል? የሚገርመኝ ትርፍ ንግግሩ ህዝብ ይከፋዋል አለመባሉ ነው። አደብ - አቅል - ማስተዋል - መታገስ - ህግ ማክበር - ይሉኝታ - ኢትዮጵያዊነት - ሃይማኖት- ባህል - ወግ - ልማድ - ጥበብ - ክብራቸው ሊጠበቅ ይገባል ባይ ነኝ። የምንከፋባቸውን ክስተቶች አስታግሰን፤ በረድ አድርገን ስንገልፃቸው የመከፋታችን ጥልቀት ተጭነን ነው። እኔ በግል ብጠየቅ በኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኛ ሊኖር አይገባም ባይ ነኝ።
 
ከዚህም ባለፈ የትውልድ ማጭድ የሆነ የፖለቲካ ድርጅት ሰልፍ 60 ዓመት ሙሉ ታይቷል። ኢትዮጵያም ከብዷታል። ስለዚህ ምኞቴ ሰውኛ እና ተፈጥሮኛ የሆነ ቲም ቢመራት እፈቅዳለሁኝ። ኢትዮጵያ የከበደችን ለሁላችንም ነው። እኔ ልጥራት እናንተ ግን አትችሉም ሃሳቡ እራሱ የኢትዮጵያን ኦርጋኒክ ተፈጥሮ ካለማመሳጠር የመጣ ይመስለኛል። እኩል ቤታችን ናት እናት አገራችን። 
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ማህበረ ቅንነት እንዴት አደራችሁልኝ።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ኑሩልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
29/04/026
 
ጥበብ ትከበር፤ ትክበርም።
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።