ቅጽበታዊው #ስምረት ፓርቲ ገና ጮርቃ እኮ ነው። በደል ይረሳል ወይንስ #ይለመዳል? አዲስ ልብስ #የጭካኔን ገመና አይሸፍንም።
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
#ምዕራፍ ፲፰።
#ጠብታ።
እኔ ሥርጉተ ሥላሴ የአዳዲስ የፖለቲካ ድርጅት ምሥረታ የሚያስፈነድቀኝ፤ የአዳዲስ የፖለቲካ ድርጅቶች ምርጫ በመጣ ቁጥር በአዲስ ማራኪ ሥያሜ መዋህድ ይሁን መቀናጀት ፋሲካዬ ነው ብዬ አቅም የማባክን ሰው አይደለሁም። ይህን አፍንጫህን ላስ አቶ ሂደት ላይ ጽፌዋለሁኝ ሌላ ጊዜም ስለ አጤ ሂደት እንዲሁ ጽፌለሁኝ። በከንቱ እምናፈሰው አቅም ቁስ ጉዳይ አይደለም። እሱ ቀላል ነው።
መኖሩን በእስር፤ በመታገት፤ በመሰወር፤ ነፍሱን በማጣት ለሚቀማው ትውልድ ጠቃሚ መንገድ አለመሆኑን ቀድሜ ተረድቸዋለሁኝ። ትርፈ ቢስ አልቦሽነቱን ትርጉሙም፤ ሚስጢሩም ገብቶኛል። እንኳን መላ አካለት በጭካኔ፤ በመታበይ በዝና ሱስ፤ በሚዲያ ንግሥና መውደቅ መነሳት ላይ አቅም ላባክን።
#ቆባ ላይ ያለ ድርጅት ልኩን በልኩ ቢያደርገው።
የአባ ሻንቆ ፍታውራሪ አርበኛ መለሰን በዓት ትናት የተፈጠረ ሩብ ዓመት ያላስቆጠረ የፖለቲካ ድርጅት ለዚህ ግዙፍ ሚስጢርን አቅፎ ለተቆረቆረ በዓት ባለቤት ነኝ ብሎ ሲነሳ ከትከት ብዬ #ስቄያለሁኝ። ያን ሁሉ የማይካድራ ደም በከንቱ ያፈሰሰ፤ በድፍን ወሎ፤ በወገራ ጭና፥ በንፋስ መውጫ የፈጸመው ሞልቶ የተረፈው ግፍ ሱፍ አስለብሶ በሽልማት፤ በሽርሽሽር፤ በሰርግ መልስ እና ቅልቅል ድለቃ ትወና ዓይን አይችለው የለ ሚዲያ ግልምት እስኪለን ድረስ አየን። ማፈሪያነት፤ ጸረ ሰውነት ባለ ክብር ሆኖ ሲጎማሸር የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለሰብአዊነት፤ ለተፈጥሯዊነት ያለው የህሊና አቅምን ፍንትው አድርጎ ያሳያል።
ያን ጊዜ፤፦የደከምንበትን፤ ወጣትነታችን የገበርንበትን፤ የነፃነት ትግላችን አሳልፈን የሰጠን አንድ ነፍስ ያለው የውስጥ የሆነ ጥግ ከማጣት የመነጬ ነበር። እርግጥ ነው " በኢትዮጵያዊነት ሱሴ" ሰውን ጠርጥሮ ከመነሳት አምኖ መጎዳት የቅኖች መስመር በመሆኑ ግድፈቱ እየተዘዋወረ ቅንነታችን ቢወቃውም፤ አሹሙሩን መስቃውን እያዳመጥን እኛ ብንችለው እንኳን፤ የእነኛ የንጹኃን ደም ግን ምንጊዜም #ይጮኃል። ሰው ሆኖ በሰውነት ለተሰራ የፖለቲካ ሊቅ፤ ከዛ የሰው ልጅ የእርድ ግፍ በኋላ ቀና ብሎ ለመሄድ መቻሉ በራሱ ሁልጊዜ የሚገርመኝ ጉዳይ ነው። በወል ዓለም ለምኔ የሚያሰኝ ነው የሙሉ ፶ ዓመታት የግፍ ናዳ።
ስምረት ፓርቲ ዓለም ዓቀፍ ሁነትን ከያዘ ጭብጥ ጋር ደርሶ ፍልሚያ ከመግጠም፤ ያገኜውን ዕድል ሳያፈስ እቴጌ ትግራይ በአብይዝም ዘመን ህወሃት #ታብዮ ያጣችውን የፖለቲካ ውክልና በልኩ ለማግኜት ጥረት ሊያደርግ ይገባ ነበር። ብዙ በጣም ብዙ ሊሠሩ የሚገባቸው ወሳኝ ፖለቲካዊ ጉዳዮች አሉና። የሰውን እርድ ያህል ግፍ አስቀምጥ በሥልጣን ኮረቻ የሰብዕና ግንባታ ሂደትን ለማጎልበት መታሰቡ እራሱ ወንጀል ነው። አብሶ ለህግ ሰው። አቶ ጌታቸው ረዳ ያጡንት፤ የሠሩበት ያስተማሩት #ህግ አንድን ንጹህ የከተማ ሙሉ ነዋሪ በአላሰበት ሁነት በአረማዊነት #ማረድ፤ ሲረዳ፤ ሲንከባከብ የቆየን #ሠራዊት በግፍ መረሸን ይፈቀድ ካልተባለ።
#በደል ይረሳል ወይንስ ይለመዳል?
ይህን ዕርዕሰ ጉዳይ ብዙ ጊዜ በዘመነ ህወሃት ጽፌበታለሁኝ። ታጋሹ የአማራ ህዝብ ብዙ በጣም ብዙ ታግሶ እና ችሎ መኖሩ ለዓለም ታሪክም ዕንቁ ስጦታ ነው። በደሉን ሁሉ መርሳት እምንፈልገውም ትውልዱ ቂም መውረስ ስሌለበት ነው። ያ ያገርሽና --- ትርምስምሱ ይቀጥል ከሆነ ያ ህወሃት ፈቅዶ፤ እራሱም ድምጽ ሰጥቶ መንበሩን የለቀቀበት ይሁን፤ በጦርነት ወደ ሥልጣን እመጣለሁ ብሎ አፋር እና አማራ ክልልን እየተበቀለ የገሰገሰበት ሁነት አከርካሪው በድምጽ አልባ ዕውነት የጨነገፈበት አመክንዮን ቁጭ ብሎ መመርመር ይገባዋል #ቆባው ስምረት።
ይህን ጥያቄ አረና ቢያነሳው አይደንቀኝም። እንዲያው ስምረት ፓርቲ ደርሶ ቁንጮ ልሁን ሲል ግን ይገርማል።
1) ትግራይ በፌድሬሽን ምክርቤት የፖለቲካ ውክልና የላትም።
2) ትግራይ በፓርላምም ውክልናዋ ልሙጥ ነው።
3) ትግራይ በካቢኔ ይሁን በጠቅላይ ሚር ጽህፈት ቤትም የረባ ይህ ነው የሚባል የፖለቲካ ውክልና የላትም። ይህ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ እኔ አግልዬ የምመለከተው ጉዳይ አይደለም።
ሌላው ህወሃት በፈጸመው ህዝባዊ የበደል #ክርፋት የተነሳ ህውሃት ሲነሳ የሚያንገሸግሸው ዜጋ አለ። ስለዚህም ይህን የሻከረ፤ ያመረቀዘ ቁስለት በትህትና፤ በቅንነት፤ በርህርህና፤ በመጸጸት፤ ይቅርታ በመጠየቅ፤ ዝቅ በማለት ማለስለስ ሲገባ ላይ ቁጢጥ ልበል፤ እንደ ጉልላት ልታይ የተገባ አይደለም። ይልቅ አቶ ጌታቸው ረዳ ጥሞና ወስደው እመራለሁ ከማለታቸው በፊት ንሰሃ ቢገቡ የተሻለው መንገድ ነው። በሌላ በኩል ዕውቀቱ ሰውነትን የሚደፈጥጥ፤ ሰውነትን የሚጫን፤ ሰው ላይ የሚጨክን፤ ሰብአዊነትን የሚቀጠቅጥ ከሆነ አለመማሩ፤ አለማወቁ በስንት ጣዕሙ።
የተበደለው ሰብዕ ደግሞ በአፍቅሮተ ህወሃት አይዲኦሎጂ የተበከለን ማንኛውንም መንፈስ የመሸከም አቅም የለም። አይኖርምም። ሰው ከተሆነ። ሰብዕና ወደ አረማዊነት ከተቀየረ ግን እንዲህም፤ እንደዛም ያደረጋል። ያለ አቅም ያንጠራራል እንደማለት። የተበከለ ታሪክ፤ በደም የተከዘነ አካልነትን በገብርዲን ተጎናጽፎ ክብር እና ልዕልና መመኜት የፈቀደ ሊፈቅድ ይችላል፤ ዘመን እንዲሰጠው እኛም ፈቅደን ስለነበር በጅልነት ይሁን በቂልነት። እንዲህ ምልሰት ወደ ኢህአዲግነት እንደሚሆን ቢታወቅ የክስረት ጎተራ ለመሆን ባልፈቀድን ነበር። ሞታችን ይሁን ስደታችን ለሰብዕነት ካልነበረ።
ሥምረት ማህበራዊ መሠረቱ ትግራይ ላይ ነው። ገና መሠረት አልያዘም። እያረገረገ ነው። ለሌሎች የማይፈቀደው ሁለገብ ትግል ሰላማዊ እና የትጥቅ ትግል በአብይዝም ተፈቅዶለት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አደምጣለሁኝ። ይህ አደረጃጀት ነገ ምን ሊያመጣ እንደሚችል ተመክሮ አልቦሽ ጅማሬ መሆኑ ይገባኛል። "ቁጭ ብሎ የሰቀሉትን ቁሞ ማውረድ" #ለአብይዝም ሊሆን እንደሚችል ልብ ልክ ነው። ጠብቁት። የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች እርስበርሳቸው አይተዋወቁም።
እራስህ አደራጅተህ፤ እራስህ አስታጥቀህ፤ እራስህ የሎጅስቲክስ ድጋፍ እየሰጠህ እንደ ኢዝቦላ ወይንም ሃማስ ነገ ላይ ማኔጅ ለማድረግ ይከብዳል። ብልህነት የጎደለውም ስልት ነው።
በሱዳን ሳምሪ፤ በማህል ትግራይ ህወሃት፤ በአፋር ሌላ ታጣቂ መንፈስን ፈቅዶ በአራት አቅጣጫ መወጠር ትርፍ ሳይሆን #ኪሳራ ነው። ጎልቶ እና ጎልብቶ እንዲወጣ የሚያስፈልገው የበቃ #የሃሳብ አቅም ሊሆን በተገባ ነበር። የተፈቀደለት ታጣቂ ምን ተመግቦ ምን ሊያተርፍ ይህን ያህል የሎጅስቲክስ ድጋፍ እንደሚደረግ እንቆቆ ወይንም #አሳንጋላ ነው። የአቶ ጌታቸው ረዳ መፎግላትም አቅም ያጎራረሰው፤ እንክህ እንክህ የሚለው የአብይዝም የአያያዝ ሁነት ነው።
ማንም የሌለው፤ ጥግ የሌለው ሙሉ ፶ ዓመት በበቀል፤ በሚከረፋ በቀል የሚቀጠቀጠው የወልቃይት፤ የጠገዴ፤ የጠለምት፤ የራያ፤ የአዳርቃይ፤ የአዲረመጥ ህዝብ ብቁ የሆነ የብልህ መሪ ውሳኔ አጥቶ እንሆ ነፍሱ ተንጠልጥላ ዘወትር አፋፍ ላፋፍ ትማስን ዘንድ ተፈርዶባታል። የኳስ ያህል እንኳን የማይካድራ የወል ጭፍጨፋ፤ የጭና የጅምላ ጭፍጨፋ ከውስጥ ለውስጥ ሊገባ አለመቻሉ ሰው በገበርዲን፤ ሰው በከረባት፤ ሰው በሚኒ፤ ሰው በካባ ተንቆጥቁጦ ቢታይም ከሰብአዊነት ውጭ ራሱን ሸሽቶ እንደሚኖር ዘመኑ በራሱ #ሐዋርያችን ነው።
አብይዝም በዘመነ ኢህአዲግ ግርባው ብአዴን ሙሉ 45 ድምጹን ሰጥቶ ለክብር እንዳበቃው አንድ ቀን ትዝ ብሎት አያውቅም። ሌላው እግዚአብሄር የሚያውቀው ልዩ የደግነት እና የበዛ የቅንነት አቅም በልዩ ሁኔታ ያላሰብው የዕድል ሎተሪ ያገኜበት ጥበብ ዕውቅናም አስታዋሽም አግኝቶ አያውቅም። ለዚህ ነው የአማራ ህዝብ ከአንዱ የግፍ ናዳ ወደ ሌላው የጭካኔ ገደል ሲወረወር ባለቤት አልባ ሆኖ የምናየው።
በቀጣይ ስለሚሆነው ጉዳይ በትዕግሥት፤ በማስተዋል፤ ማዕከላችን ሰዋዊነትን አድርገን መትጋት ይኖርብናል። ብስጭት አያስፈልግም። ትርፍ ነገር አያስፈልግም። መዘላለፍ አያስፈልግም። በወጋችን በባህላችን ልክ አብሮነታችን ሳናስከፋ የዕውነት አምላክ ሃቅ ቀን ይሰጠው ዘንድ በንጹህ ልቦና መጸለይ ያስፈልጋል።
ውዶቼ እንዴት አረፈዳችሁ? እንደምንስ ዋላችሁልኝ።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
24/02/2026
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ