#ስሜናዊነቴ ህወሃትን ቤቴ ለማለት ከሆነ በአፍንጫዬ ይውጣ።

 

#ስሜናዊነቴ ህወሃትን ቤቴ ለማለት ከሆነ በአፍንጫዬ ይውጣ።
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 
#ምዕራፍ ፲፰።
 
#እፍታ ለአፍታ።
አወን እርግጥ ነው በአባቴም በእናቴም ስሜናዊ ነኝ። ስሜናዊነቴ አንዱ ማንነቴ ነው። ግን ያን ጊዜ የማይስተምረውን የጭካኔ አስኳል ጋር ለሠርግ - መልስ፤ ለቅልቅል እና ለግጥግጥ ከሆነ ስሜናዊነቴ በአፍንጫዬ ይውጣ።
 
የሚገርመኝ የጽጥምዶ ባላንበራሶች ዛሬ ደርሰው የወልቃይት፤ የጠገዴ፤ የአዲረመጥ፤ የአዳርቃይ፤ የጠለምት፤ የራያ ተቆርቋሪ ሆነው መምጣታቸው ነው። እንደ ሽንብራ ቂጣ መገላበጡ የእውነትን ልክ #ሊከልሰው ፈጽሞ አይችልም።
 
ዛሬም ህወሃት ከዛ #ከታቆረ ሃሳቡ ፈቀቅ ሊል ያልቻለ፤ ድውይ ድርጅት መሆኑ ዓለምም እያዬው ነው። ኡኡታው፤ ለማሳጣት ከፍ ዝቅ ማለቱ፤ መሸነፋን ለመቀበል አቅል አጥቶ መክለፍለፋ ዘመን ሊያስተምረው አልቻለም። እንጂማ ቢገባው የእሱ አንቱነት ከግንቦት መግቢያ 2023 ጀምሮ ማክተሙን አላወቀም። 
 
#ለማንኛውም ሰብ ይሁን ተቋም እኔ የምለው ……
 
1) መውደቅን መቀበል ብልህነት ነው። መሸነፍን መቀበል ብልህነት ነው። ምክንያቱም በመውደቅ ውስጥ መነሳት፤ በመሸነፍ #ከርስ ውስጥ ማሸነፍም ስለሚቻል።
 
መሸነፍ ብቻውን አይቆምም። የሙሉ ዕድሜ ተመክሮ መግቦ ነው። በመሸነፍ ውስጥ እራስን የማየት አጋጣሚ ይገኛል። መሸነፍን ለሚቀበል። ዕውቅናም ለሚሰጥ። ይህ ሲሆን በመሸነፍ ውስጥ ዳግም ጥፋትን ላለማጨት ህሊናን ያሰናዳል።
 
2) መውደቅም ቢሆን ከብዙ ኪሳራ ጋር ቢሆንም፤ እራስን ከወደቁበት ረግረግ ለማውጣት የጥሞና፤ የተደሞ ጊዜ ቢሰጠው በአዲስ አቅም፤ በእሸት ጉልበት አገግሞ ቀና ማለት ይቻላል። ግን መውደቅን በማመን፤ ዕውቅና መስጠት ከተቻለ ነው።
 
ህወሃት ሁሉንም የነሳው ነው። ለእኔ ህወሃት #ቤርሙዳ ትርያንግል ነው። እኔ የህወሃት ብርቱ ሞጋች ነበርኩኝ - በሥልጣን ዘመኑ። ከመጋቢት 10/18/2010 ዓም በኋላ ምን አድርግ ብላችሁ ነው ቁም ስቅሉን እምታሳዩት ብዬ ሞግቸለታለሁኝ።
 
ምክንያቱም ህወሃት ፈቅዶ እና ወዶ ሥልጣኑን መልቀቁ ሊከበርለት ይገባል። ጥቃቅን ነገሮች እየተመነዘሩ ህወሃት ሊነሳ ሊጣል አይገባም በማለት ሞግቻለሁኝ።
 
ጦርነት ለኢትዮጵያ አያስፈልግም ያልኩት መጀመሪ እኔ ነኝ። ከሰፊ ማብራሪያ ጋር። ያው እኔ ሠራዊት ስለለኝ በኋላ አንዲት ቅንጣት ቃል የተናገሩት ሲሞጋገሱ አይቻለሁኝ።
 
ይህ ያልተመቻቸው የቤቴ አባሎች ፕሮፖጋንዲስት እንድሆን ጠይቀው በአሻም መራራ ስንብት ሆነ። እኔ ጎንደር ከተማ ተወልጄ አድጌ በምንም ታምር ጦርነትን #አቅባጭ ልሆን ፈጽሞ አልችልም። አይታሰብም።
 
በጦርነቱም ወቅት የየትኛውም አካል #ደጋፊ አልነበርኩም። ዓለም ዓቀፍ ተቋማት እና ሚዲያወች የሚያወጡትን መረጃ የግራ ቀኙን ጉዳት በገለልተኝነት ነበር እምዘግበው። የመቀሌ ተያዘች ፈንጠዝያ ላይ ሦስት ነገሮችን ጽፌ ነበር ስለ ደስታ።
 
1) ደስታችሁን በልክ ያዙት። ሌላ ደስታ ሲጨምርላችሁ መደርደሪያ እንዳታጡ።
2) ደስታችሁን መጠኑን አትለጥጡት፤ ፈጣሪ እንዳይቀጣችሁ።
3) ደስታችሁን ያጣችሁት እለት ተስፋ ቆራጭነት እንዳይመጣ ልክ ይኑራችሁ ብዬ።
#የአማራ ህዝብ ልቡን ጥሎ አለልኝ የሚለው አምላካችን // አላኃችን ብቻ ነው።
 
ጦርነቱ ከመነሳቱ በፊትም ይሁን በኋላ፤ የአማራ ህዝብ አይደለም የስትራቴጂ፤ የታክቲክ ሁነኛ በኢትዮጵያ እንደሌለው አበክሬ ገልጫለሁኝ። የአማራ ህዝብ ኖረኝ፤ አለኝ የሚለው ወዳጅ የሳሙና አረፋ ነው። ከውስጥ ህወሃት ያስቀመጠው የደመንተኝነት ዕዳ አለ። ስለሆነም የአማራ ህዝብ አቅሙን፤ ኃይሉን፤ ቅንነቱን ሚዛኑን አስጠብቆ በልኩ፤ ስለልኩ ማዕከላዊ አስተዳደር ይኖረው ዘንድ ነበር ስመክር የነበረው።
 
የአማራ ህዝብ አንድ አገር ሁነኛ እንደሌለው፤ ጥረት የሚጠይቁ ትጋቶች እንደሚያስፈልግ፤ አቅም ከመበተን፤ አቅምን ከራስ አቅም ጋር ከማዋከብ፤ የተረጋጋ አስተውሎታዊ ግንዛቤ ለራሱ የአማራ ህዝብ ፖለቲካ እንደሚያስፈልግ በስፋት ጽፌያለሁኝ፤ በድምጽም ሠርቻለሁኝ።
ነገር ግን ማህበራዊ መሠረቱን ያጣ ሁሉ የሚተመው ወደ አማራ ህዝብ የህልውና እና የማንነት ተጋድሎ ሆነ እና ከዓላማውም፤ ከተልዕኮውም ጋር ግጭት የሚፈጥሩ ሁነቶች ተፈጠሩ።
 
ይህም በመሆኑ እኔ ሁሉንም ነገር በጥሞና እተከታተልኩ ነው ያለሁት። ያ … ሁሉ መገበር፤ ያ … ሁሉ ድቀት፤ ያ … ሁሉ መፈናቀል፤ ያ … ሁሉ ፈተና ቁጭ ተብሎ ቢመረመር ትርፍ እና ኪሳራውን መመዘን ይቻል ነበር።
 
ይህም ሆኖ በስሜናዊነት ሥም አዲስ ዓይነት ስብስብ ህወሃት አዳኝ ሆኖ ከእሱ ፍርፋሪ ነፃነት፤ ከእሱ የምጽዋት የፖለቲካ የውክልና ዕድል ለአማራ ይገኛል ተብሎ መታሰቡ ይሰቀጥጠኛል። ለምን ተብሎ? ለማንስ ተብሎ???? 
 
#እነ ደራሽ ተቆርቋሪወች። 
 
ዛሬ አንድ ቀን የአማራ ጉዳይ የእኔ ብሎ የማያውቅ ሰብ የአማራ ህዝብ ተቆርቋሪ ሆኖ፤ በዚህ ሁሉ መከራ ህዝባችን እንዲገረፍ ተደረገ። ህወሃት እራሱ ድምጹን ሰጥቶ ሥልጣኑን ያስለቀቀው ስሜናዊነት አልነበረም። ወይንም በትጥቅ ትግል አይደለም። ወይንም በጠንካራ የፖለቲካ ድርጅቶች አቅምና ችሎታ አልነበረም።
 
የእግዚአብሄር ጥበብ የህወሃትን ውሎጉዞ አመራር ሲያሰናብተው፤ ለራሱ ለህወሃት፤ ለተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ ዱብዕዳ ነበር። በሰው እጅ ያልተሠራ የፈጣሪ ዊዝደም ነበርና።
 
ህወሃት ስሜናዊነት ትዝ ብሎት አያውቅም። እንዲያውም ቀጥቅጦታል። ይህ ጂኦግራፊያዊ ሁነትን የመጠቀም አቅሙ የተፈለገው የገራገሩ የአማራ ህዝብን ግብር መሰላል አድርጎ የተለመደው "በሞኝ ደጅ ሞፈር ይቆረጣል ወይንም በሞኝ ክንድ ጉድጓድ ወይንም ዘንዶ ይለካል ነው።"
 
#ህ
 
ወደፊትም እኔ የማስበው መስዋዕትነት የሌለበት ሰላማዊ ሁነት፤ ሰብአዊነት እና ተፈጥሯዊነት በእኩልነት በአገራችን ይሰፍን ዘንድ ማስተዋልን፤ ጥበብን፤ ታጋሽነትን፤ ቅንነትን፤ ርህርህናን፤ አጽናኝነትን፤ አይዟችሁ ባይነትን ዕውቅና ሰጥቶ፤ ከራስም ጀምሮ በሚወሰድ ሰላማዊ ጉዞ የችግሮቻችን ሁሉ መፍቻ ሊገኝ ይችላል። ይህም ህወሃት ታቅፎ እና ተደግፎ ሊሆን አይገባም። #በቃው! ህወሃት። አታሽሞንሙኑት፤ አትሞሻሽሩትም። 
 
ግን ህወሃትን እንፈልጋለን የሚሉ ሰብዕናወችን ፍላጎት እኔ ልጫን አልችልም። የአሻቸውን የመወሰን ባለሙሉ መብቶች እነሱው ናቸው እና። "ከባለቤቱ ያወቀ ………" እንደሚባለው። ነገር ግን የሳት መጫሪያነት እኔ ልሆን አልፈቅድም። ከልጅነት እስከ ዕውቀት የማውቀው ድርጅት ነውና።
 
ህወሃት ሥልጣኑን ከለቀቀ በኋላ ወጀብ ነበረበት። እኔ ግን የወጀቡ ማህበርተኛ አልነበርኩም። "ሸማ በየዘርፋ ይለበሳል" ይላል ቅኔኛው ጎንደሬ። በዚህ ጉዳይ በትዕግሥት፤ በመቻል ውስጥ ሆኜ ነበር እኔ የቆየሁት። መቀሌ ከተለቀቀለት በኋላ፤ ዕድል ሲያገኝ የአማራ ህዝብን እና የአፋርን ህዝብ በቁርሾ እንዴት እንደወቃ ሳይ የማይድን እንደሆን ማህተሙ ተመታ።
 
አቶ ጌታቸው ረዳ " ህወሃት ይድናል ብዬ አላስብም" ማለታቸውን የሪፖርተር የዜና ክፍል በንባብ ተርጉሞ አቅርቦት አዳምጨው ነበር። ቢገባቸው ሚኒስተሩ ህወህት #ድኖ አልተፈጠረም። ሲወጠንም፤ ሲጠነሰስም ጤነኛ ሁኖ ህወሃት አልተፈጠረም። ምንም እንኳን እሳቸው እኩሌታ ዕድሜው ላይ ቢቀላቀሉም።
 
ኢትዮጵያን ከመሠረቱ ቀደምት ማህበረሰቦች ተጋሩ አንዱ ነው። ህወሃት ያን በማን አለብኝነት፤ ደፍቶ የራሱን ዕንቁ ተፃሮ ነፃ ህዝብ ተገዢ ነበርኩኝ ብሎ ዝቅታን ፈቅዶ ሲነሳ፤ ያን ጊዜ በማይድን #አልዛይመር በሽታ ተይዞ ነበር። አብሮ ላበጃት፤ አብሮ ለቀመራት፤ አብሮ ለአደራጃት አገር ኢትዮጵያ እግርጌ ነኝ ሲል የጤናው፤ ከጤናው አልነበረም።
 
ህወሃት - የበታችነትን ይሁነኝ ሲል፤ ዝቅታን ወዶ - ሲያቅድ ከዚህ በላይ ህመም ምን አለና??? ህወሃት ዛሬ ሳይሆን ሲጠነሰስ፤ ሲደፈደፍ፤ ሲጠመቅም የበታችነትን ጭልጥ አድርጎ በአንድ ትንፋሽ ጠጥቶ ነው። ይህ አለመታደል ዝቅ ሲል፤ ከፍ ሲል ደግሞ የእርግማን ነው።
ትናንት የባከነው ጊዜ፤ የጠፋው ትውልድ ሳይቆጨው ዛሬም ከመሃል አልታረስ፤ ከዳር አልመለስ ብሎ ኢትዮጵያን በሁለገብ ቀውስ ወጥሮ አሳሯን ያሳያታል። ያምሳታል። ያንገረግባታል። ህውሃት ለአቅመ አዳም ደርሶ አያውቅም።
 
1) የትኛውም የጭካኔ ግፍ አለ ቢባል አምራቹ ህወሃት ነው።
2) የዜግነት መገለል አለ ከተባለም ዶክትሬቱ የመነጨው ከህወሃት ነው።
3) የሰው እርድ አለ ከተባለ ከማንነት ቀውስ የፈላ የጭካኔ ዶክተሪኑ ፈላስማ ህወሃት ነው።
4) ቀውስ አገረሼ ቢባል አራጊ ፈጣሪው ህወሃት ነው። 
 
ህወሃት ምን አይነት አኞ እና አሰልቺ ድርጅት መሆኑን ከፍጥረቱ እስከ ውድቀቱ ከጋሜዬ እስከ ሙሉ ዕድሜዬ ያዬሁት ዕውነት ነው።
ስለሆነም ስሜናዊነቴ ይሁን ውዱ እና ክብሩ የጋብቻ ዝምድናዬ፤ የጉርብትና ይሁን የአብሮ አደግ ጣዕሜ፤ የጓድነት ይሁን የሥራ ባልደረባነት ጣፋጭ ዘመኔ ከተጋሩ - ጋራ ነበር።
 
ይህ ሂደት የትናንቱ ቀጣይነትም የምፈቅድለት ጉዳዬ ቢሆንም፤ ህወሃትን - ተሸክሞ፤ ህወሃትን - አዝሎ፤ ህወሃትን - አሽኮኮ አድርጎ፤ ያን የማይድን ድርጅት ጉልላት ለማድረግ የሚታሰብ ነገር ሁሉ ለእኔ #ሃራም ነው።
 
ሌላው ቀርቶ የትኛውም የትግል ዓይነት እኔ እምከተለው ሰላማዊ ነው፤ በዚህ ከመጡ ግን በአፍንጫዬ ይውጣ። ቅንጣት አቅም አላዋጣም። ዝምታዬ መስማማት አይደለም። ሊሆንም አይችልም።
 
#ኢትዮጵያኒዝም እና የህወሃት ጠላትነት።
 
ይህ ሁሉ የነፃነት ግንባር እኮ የህወሃት ሥሪት ነው። የፋና አሟጋች ጋዜጠኛ አንቀጽ 39 ማን ነክቶብኝ ብሎ ሳያፍር ይከራከራል። እንዲህ ዓይነት ውስጥን የሚፈርስ ልስን ጉድ ነው ኢትዮጵያን ያሸከማት።
 
ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያኒዝምን ፈተና ውስጥ አሰጥሞ ማይክ በተያዘ ቁጥር መስቃ የሚሰማበት የጸረ ኢትዮጵውያዊነት የስክርቢቱ ጸሐፊ ህወሃት ሁኖ፤ ስለሆነም ህወሃትን አቅም አጉርሶ ለዳግም መንሰራራት፤ አዲስ ሙሽራ ለማድረግ ሽር ጉዱ የትም አያደርስም። የውርንጫ ድካም ነውና። ለድል እንዲበቃ ህወሃት ተከናንቦ የማንፈቅድ ሰወች አለንና።
 
የሚገርመው ስሜን ጎንደር እና ስሜን ሽዋ ለህወሃት አንጡራ ጠላቶቹ ናቸው። በዘመኑ ያደቀቃቸውም እነኝህን የማህበረሰብ ክፍሎች ነው። የሚገርመኝ እያወቁ ከዛ ጃርት የህወሃት ድርጅት ጋር ከፍ ዝቅ ለሚሉት ማፈርን ፈጣሪ አምላክ ይልክላቸው ዘንድ እለምነዋለሁኝ። ስሜነኝነት የሚጠቅም፤ የሚሠራ ቢሆን የዘመነ ህወሃት እስር ቤቱ በስሜን ጎንደር ልጆች ባልተሞላ ነበር።
 
ለህወሃት ምንም ነገር ብታቀርብለት አይጥመውም። ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የምትመራው ሙሉ 32 ዓመት በማን ነው? የተደራጄ መዋቅር ነው ያለው። የንሰኃ አባት አመዛኙ ከየት ነው? ይህም ሆኖ ራስ ገዝ ሲኖዶስ ከማቋቋም ህወሃትን አልገደደውም።
በቅድስት ተዋህዶ ሙሉ ቅብዓ ያለው ቅዱስ ባዕት በራሱ ላይ እሾህ በቅሎ ይኽው ዘመን ከዘመን መስቀሉ ኑሮው ጎለጎታ ይሆን ዘንድ የእጅ ሥራው የህወሃት ነው። ህወሃት ጸረ ኦርቶዶክስ ተዋህዶም ነው። 
 
#ሌላው ፋክት ደግሞ።
 
የወልቃይት የጠገዴ ጉዳይ አልነበረም ህወሃትን የመጀመሪያ ጦርነት ያስከፈተው። እእ። ማዕከላዊ ሥልጣን ናፍቆት ነው። ግን "የቆጡን አወርድ ብላ የብብቱን ጣለች" አደረገው የንፁኃን --- ቅንነት። 
 
ስለሆነም ከሽንፈቱ በኋላ፤ ማጣፊያ ሲያጥረው፤ የሠራ አካላቱ በኪሳራ ሲጥለቀለቅ ያ መከረኛ ህዝብ ምን ይነገረው???? የወረራቸው የጎንደር ይሁን የወሎ ግዛቶች በእጁ በመዳፋ የነበሩ ናቸው። ጦርነቱን የከፈተው ግን ለመንበረ አገራዊ ሥልጣን ነበር። ዕውነቱ ይህ ነው። ዕድሉን ባገኜበት መርሳ ወጣቶችን የመርዝ መፈተኛ ሁሉ አድርጓቸው ነበር። ይህ ስሜናዊነት ነውን? ይህ ኢትዮጵያዊነት ነውን?
 
ሰው ሁኖ ተፈጥሮ የጭካኔ አዟሪትን፤ የሴራን - ሽክርክሪት፤ የተንኮልን - ፈትልን፤ የበቀልን ዘሃ ሲሸምን ውሎ የሚያድር ጉድ ኢትዮጵያ ተረገሚ ሲል ፈጣሪ ይህን ትሬኮላታ ድርጅት ፈጠረባት። እቴጌ ጎንደርም "ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ዘወትር ሲያለቅስ ይኖራል" ሆኖ ዘመኗን ሁሉ ተሸክማ ግን መከራ ስታፍስ ኖራለች።
 
#በዚህ ውስጥ ከዚህ አረማዊ ድርጅት
 
1) የነፃነት - ልቅምቃሚ፤
2) የእኩልነት ፍርፋሪ፤
3) የፖለቲካ ውክልና ቅርጥምጣሚ፤
4) የተስፋ ፍጋፍግ፤
5) የመኖር አንቡላ ካልሆነ በስተቀር በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠርንበትን ሰውነት ክብሩን፤ ማዕረጉን፤ ሞገሱን ልናገኝ አንችልም።
ስለሆነም ሃራም ህወሃት፤ ሃራም አፍቅሮተ ህወሃት የሚል ውሳኔ ከእያንዳችን በግል ከሁላችንም በጋራ ያስፈልጋል።
 
 
በታሪካችን ጎንደር ለማገዶነት፤ ለአንጋችነት እንጂ ለትፍህስት አንድም የፖለቲካ ሊቅ አስቦን አያውቅም። ጎንደር ሲነሳ የሚያንገሸግሻቸው፤ የሚያንዘፈዝፋቸው የሚዲያ አካላት እና ፖለቲከኞችን ነው ስናይ፤ ስንታዘብ የኖርነው።
 
1) ክስተቶችን በማንቦጅቦች፤
2) ሁነቶችን በማንከልከል፤ ዕውነትን በማዋከብ፤
3) ጤነኛ ዕድሎችን አቃቂር በማውጣት አካለ ጎደሎ በማድረግ፤
4) በፕሮፖጋንዳ ወጀብ በመወዛወዝ፤
5) ፋክቶችን በድሪቶ ዕብለት በመጀቦን፤ የሚገኝ ትርፍ ስሌለ ከዘለለው ጋር ባለመዝለል፤ ከአጎረፈው ጋር ባለመጉረፍ፤ #ከአጎፈረው ጋር ባለማጎፈር የሰከነ፤ የተረጋጋ፤ ማዕከላዊ ዕሳቤን ያከበረ ሚዛናዊ ሂደቶችን በአስተውሎት እየመረመሩ፤ ሳያንጠራሩ፤ ወይንም ሳያንኳስሱ፤ ወይን ለፈንጠዝያ ሳይሸጡ ሳይለውጡ ጨምቶ አብሮ ለመጓዝ እስከ ዛሬ የኖርንበት ሁለገብ ተመክሯችን እንዲያግዘን ልንፈቅድለት ይገባል።
 
ትናንት አብሮን ነበር፤ ዛሬም ከእኛ ጋር አለ። ነገም አይቀርም ይመጣል። ሁልጊዜ ከእኛ ጋር ያለ የፈጣሪ ስጦታ አለን። እሱም ዕውነት ነው። ዕውነት እኛን ፈጥሯል። ዕውነት እኛነትን ሰጥቶናል። ዕውነት ትናንት በአከበረን ልክ ዛሬም አክብሮ አስከብሮናል። የነገ ተስፋ ሲመጣም ዕውነት አብሮ ይመጣል። ለምን? ዕውነት ቦታውን ለቆ ስለማያውቅ።
 
ብዙው የቀውስ ዓይነት ህወሃት ሠራሽ ነበሩ። በቅኖች አቅም ተጠቅሞ ህወሃት የቀውስ መናህሬያ ያደረገው የአማራን ህዝብ የህሊና ማሳን እና በዕቱን ነው። በአማራ ህዝብ ሁለመና ህወሃት ሰራሽ ሁነቶች ሁሉ ይቀናሉ። ይህ ሊደንቀን አይገባም። ልንታበይበትም አይገባም።
ህወሃት ሥልጣን ላይ እያለም ይሁን ሥልጣኑን ለቆ፤ ጦርነት ላይ እያለም ቢሆን በማናውቃቸው ሰብዕናወች ውስጥ ሁሉ ህወሃት የልቡን አድርሷል። አብረን ተጃጅለናል። 
 
ህወሃት የአማራን ህዝብ መኖር አመሰቃቅሏል። ህወሃት የቀናባቸውን ተቋማት አውድሟል። ህወሃት ተስፋን አድቅቋል። ህወሃት ሰላማዊ መኖርን አመድ አድርጓል። የሚቀናበት አቅማችን በተዘዋዋሪ ተጠቅሞ የራሳችን የጉዳት፤ የዕንባ ምንጭ እኛው እንሆን ዘንድ የሚበቃውን ያህል ተውኗል።
 
ቢያንስ ከዚህ ሁሉ እምሽክ ካደረገን የቀውስ ናዳ ነቅታን በቃን የአፍቅሮተ ህወሃት ሰላዮች ማለት ይገባናል። ይህን ስል የአማራ ህዝብ አስተማማኝ፤ ደልዳላ ሁነኛ አለው እያልኩ አይደለም። ብልህነትን ሰንቆ መስዋዕትነትን መቀነስ፤ ዕድሎችን ሳያፈሱ አሉ በሚባሉ ዕድሎች ሁሉ ለመጠቀም መፍቀድ ከብልህነት በላይ ነው። 
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
 
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
24/02/2026
 
በቃን! የህወሃት ሙሽርነት።
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።