የማይድን ምርቅዘት። ግን እስከ መቼ?

ማራራቅ? ግን ለምን? የማይድን ምርቅዘት።
„የኃጢያተኞች ሥራቸው ክፉ ነው ፍጻሜያሜውም ገሃነም ነው።“
መጽሐፈ ሲራክ ምዕራፍ ፳፩ ቁጥር ፲ ቁጥር
ከሥርጉተ©ሥላሴ
 21.08.2018
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።


  • ·     መነሻዬ።

‹‹ስለ አማራ ክልል የሰማነው እና መጥተን ያየነው የተለያየ ነው፡፡በፍቅር ተቀብሎ በፍቅር እያስተናገደን ነው፡፡››ከትግራይ የመጡ ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኞች

ትናንት ማምሻ ላይ ከአማራ የብዙሃን ሚዲያ ይህን መረጃ አገኘሁ እንደ ገረመኝ አደርኩኝ። 

እኔ ይህ ወያኔ ሃርነት ትግራይ የሚባል የጉድ ክምር መቼውንም ዘመን ቢሆን ከአማራ ጥላቻ ይወጣል ብዬ ለማሰብ የመጨረሻ ዕርሜን ያወጣሁበት ዕለት ነበር ማለት እችላለሁኝ።

እንዴት አድርጎ ማስፈራሪያ ጭራቅ አድርጎ እንደሳለን ብቻ ሳይሆን የትግራይን ወጣቶች በምን መልክ በሥነ-  ልቦናቸው ጢባ ጢቦሽ እንደሚጫወት አንድ የታሪክ ማህደር ሊሆን የሚቸል ሚስጢር ነው የወጣው።

እንደምንስ ብለው እነኝህ ሰዎች አገር የመምራት እና ህዝባዊ ሃላፊነት እንደሚሰጣቸው ብቻ ሳይሆን እንደምንስ እንደ አገር ልጅነት ማዬት እንደሚቻል እጅግ ይመራል። የእውነት ይመራል።
ከአንዚህ ሰዎች ጋር የሠሩ የአማራ ልጆችም ቢሆን በምን ያህል ትእግስት እና በምን ያህል ችሎት አብረው 27 ዓመት ሙሉ እንደ ዘለቁ ተመርምሩ ያሰኛል።

አማራ መደራጀት ብቻ ሳይሆን ከዛም በላይ ጥያቄ ቢያቀርብ ሊፈረድበት ፈጽሞ አይገባም። አማራ እኮ 43 ዓመት ሙሉ ብቻም ሳይሆን ዛሬም ጭራቅ ነው ለወያኔ ሃርነት ትግራይ እና ለመሰሎቹም። ይህን መርዝ ተሸክሞ ነው ወያኔ ሃርነት ትግራይ ነገም ልምራ እያለ የሚቀልደው? ይገርም ዘመኑ ነው።

የሆነ ሆኖ እነዚህ ወጣቶች እጅግ አንጀቴ ወስጥ ገብተዋል። እጅግም አሳዝነውኛል፤ እጅግም መስጠውኛል። እነዚህ ንጹሃን በሌሉበት፤ እነሱ ባልፈጠሩት ችግር እና መከራ ነው ፍዳቸውን ነገ ይከፍሉት ዘንድ የተፈረደባቸው። ዕዳ አለባቸው ያልበሉት? ይህ ነው እንደዚህ ትወልድ ታዳሚነታችን ጎርባጣው ዕጣችን። 

ትግሬ ነኝ“ ለማለት ፈራሁኝ ይላል አንዱ ተሳታፊ። እኔ አፈር ልብላ ነው ያልኩት። ምን አልባት እኔ የበዛ ሩህርህና እና ሆደ ቡቡነት ኑሮብኝ ሊሆን ይችላል። አላውቅም ብቻ አንጀቴ ውስጥ ግብቶ ነው የተላዋሰው። „ቆይቼ ግን ትግሬ መሆኔን ተናገርኩኝ“ ይላል ወጣቱ።

ልክ በ27 ዓመቱ አማራ ነኝ ማለት፤ ዛሬም እንደአላባራው መሸማቀቂያ እንደ ሆነው ሁሉ ማለት ነው። እንዲህ አድርጎ በማራቅ ፍልስፍና ነው ወያኔ ሃርነት ትግራይ በትውልዱ ሲጫወት የኖረው፤ ትግራይ ደግሞ የምሽጉ ባለድርሻ ሆና ኖራለች። አልሸከምም ብላ አድማ አታውቅም። 

የሚያሳዝነው የትግራይ ሊሂቃንም ከዚህ የበከተ ፍልስፍና ሊወጡ አለመፈቅዳቸው ነው። እጅግ የበከተ እጅግም ከንቱ የሆነ ፍልስፍና ነው አማራን እንዲህ አድርጎ ጨለማ አድርጎ መቅረጽ።

እነዚህ ወጣቶች በራሳቸው ፈቃድ ነው ወደ አማራ ክልል የመጡት። ሌሎች ደግሞ እዬቀዬሩ ወደ ራሳቸው ክልል እና ቅዱስ እዬተባለ ወደ ተነገሯቸው ቦታዎች ሄደዋል። እነኝህ ግን ተነጥለው አማራ ክልልን ሄደን እንይ ማለታቸው በራሱ ከነበረው የኩሸት ፕሮፖጋንዳ አንጻር ሰማዕትነት ነው። ለሞት የተሸኙ ያህል ነው። ሞታቸውን ፈቀደው የመምጣት ያህል ነው።

የሚገርመው ለወያኔ ሃርነት ትግራይ ይሆን በጠቅላላው ለትግራይ ህዝብ አማራ ጉሮሮው ነው። ለቀን ያደረሰው ነው፤ በችግሩ ሁሉ ለዬዘመኑ ጥግ ሆኖት የኖረ ነው፤ እንደዛ ድርቅ በሚያፍልሳቸው ጊዜ የራሱን ቤተስብ ትቶ እንሱን የሚጨነቅላቸው፤ የሚጠበብላቸው፤ እራሱን የገበረላቸው ነው። ለዚህም ነው አጤ ዮሖንስ መተማ ላይ እራሳቸውን የሰጡለት።

እነዚህ እርጉሞች ደግሞ የበሉበትን ወጭት ሰባሪዎች ወጣት  ቀንበጦችን፤ እነዚህን ሸበላዎች የጨለማ ድርስት እዬተረኩ ከነፍሳቸው ጋር እንዴት ለይተዋቸው እንደኖሩ ሰማን፤ አዬን፤ አዳመጥን። ይህ በራሱ እኮ ወጣቶችን የሥነ ልቦና ተጠቂ ያደርጋቸዋል። ፈርተው ያድጋሉ። በራስ መተማመናቸውን ኢቀማሉ፤ የ አብሮነት ትውፊታቸውን ይነጠቃሉ። ይሄ ነው እንግዲህ የሄሮድ መለስ ዜናዊ ሌጋሲ፤ የግንቦት 20 ድል፤ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ብርሃን¡

ዘመን ቢፈቅድ እኮ እነዚህ የነገ ወጣቶች፤ እነዚህ የነገ ተስፋዎችን ከቦታቸው ሄዶ ሃቁን፤ እውነቱን ማስረዳት በተከታታይም ማስተማር ይገባል። የሚገርመው ትግራይ ወስጥ ቢያንስ የሃይማኖት ተቋማት ምን ሲሰሩ ነው ውለው ይሆን የሚያድሩት? ት/ ቤቶችስ በቃ ይሄው ነው ሥራቸውን?

አማራ የግድ ውደዱን አይልም፤ የግድ ተቀበሉን አይለም፤ እኛ የማንንም መንፈስ ተጋፍተን አናወቅም፤ ድንበር ጥሰን አናውቅም፤ ሽብር ፈጥረን በረት ገልብጠን አናውቅም፤ ያ ቅን ህዝብ እንዲህ በጥቁር ጠቃራ ተጥቅልሎ በንጹሃን ህሊና ውስጥ ይህን መሰል ደባ ሲፈጸመብት መችም የሰማይ እና የምድሩ ጌታ ልዑል እግዚአብሄር ዝምታው እስከመቼ ያሰኛል?

የሆነ ሆኖ ፍርድና ዳኝነቱን ለፈጣሪ መስጠት ብቻ ነው። እኛም ምንስ አቅም አለንና።

የአብይን ሌጋሲ ማስቀጠል ዓራት ዓይናማው መንገዳችን ነው!
የኔዎቹ ኑሩልኝ።
ቸር ወሬ ያሰማን።



አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።