ለመሆኑ የአማራ ህዝብ እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ይታያልን? ትክክለኛ የፖለቲካ ዕውቅና እና ውክልናስ አለውን? ወላጅ አልባ ህፃናትንስ ሞግዚት ቀጥራችሁ ይሆን ወደ ወላጋዊ ሞት የምትሸኟቸውን??? ፍፁም ጨካኞች! ፍፁምም አረመኔወች ናችሁ።
ለመሆኑ የአማራ ህዝብ እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ይታያልን? ትክክለኛ የፖለቲካ ዕውቅና እና ውክልናስ አለውን?
ወላጅ አልባ ህፃናትንስ ሞግዚት ቀጥራችሁ ይሆን ወደ ወላጋዊ ሞት የምትሸኟቸውን???
ፍፁም ጨካኞች! ፍፁምም አረመኔወች ናችሁ።
"ከንቱ የከንቱ ከንቱ፤ ሁሉም ነገር ከንቱ።"
ትናንት ከEMS ጋር አቶ አረጋ ከበደ ያደረጉትን ቃለ ምልልስ አዳመጥኩት። ለቃለ ምልልሱ ፈቅደው መቅረባቸው መልካም ነው። ነገር ግን ለቀረበላቸው ለስለስ ያለ ጥያቄ የሰጡት ምላሽ በሲዊዝ ወይ በሲዊድን እንደሚኖር የአንድ አካል ተጠሪ ሆነው ነው የቀረቡት። ቤታቸው በበላያቸው እዬፈረሰ ለሳቸው ያሉበት ዶፍ አልታያቸው። የጦር ኃይሎች በሚመራው ክልል ሆነው፤ ከከተማ ከተማ በኢሊፍተር እና በብዙ አጃቢ በነፍስ ውጪ እና ግቢ ላይ እያሉ እሳቸው ልማት ጉብኝት ላይ ስለመሆናቸው ተርከዋል።
የአማራ ህዝብ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ፖለቲካዊ ዕድምታም አልገባቸውም። ስለሆነም በጭፍጫፊ ሳቢያወች ላይ ብቻ አተኩረው መልስ ለመስጠት ሞክረዋል። ጥያቄው እራሱ ሞጋች አልነበረም። ለዛም የበቃ ምላሽ ለመስጠት አልቻሉም። ለምሳሌ ወደ አዲስ አበባ አትገቡም የሚለው መከራ ዛሬ የለም፤ ስለቀደመው ተጠያቂ አይደለሁም ባይ ናቸው። የኦነግ ፖለቲካ ስትራቴጅ እና ታክቲክ ፈጽሞ አልገባቸውም ወይንም ለፖለቲካ ሴራው ሊጋባው ናቸው ማለት ነው።
በአማራ ክልል ላይ ስለሚዘንበው የድሮን ጭፍጨፋም እኔ ማርስ ላይ ስለነበርኩ ልጠዬቅ አይገባም የሚል ዕድምታ ያለው ፍፁም የሆነ የጭካኔ ምላሽ ሰጥተዋል። ዬሚመሩትን ህዝብ መከራ እንዳላዩ፤ እንዳልሰሙ አልፈውታል። የጊዜ ጉዳይ እንጂ እሳቸውም ነገ ተረኛ መሆናቸውን ልብ አላሉትም። ደራጎንም ደራጎን፤ መቃብርም መቃብር፤ ሲኦልም ሲኦል ነውና በተራቸው የድርሻቸውን ያቀምስልኛል አብይዝም የመቃብር ሥርዓት። ጠብቁት።
ከወለጋ ተፈናቅለው በአማራ ክልል ስላሉ ምንዱባን የሰጡት አስተያዬት ማህፀንን እንደ ዱባ ይቀረድዳል። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ በሥልጣን ዘመናቸው ኦሮምያን፤ ትግራይን መርተው አያውቁም። እሳቸውም እንደነገሩን የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆነው ሠርተዋል እዬሠሩ ነው። የአማራ ክልል መስተዳድር ፕሬዚዳንት ሆነውም እስከ ዶር ይልቃል ከፍአለ ዘመን አገልግለዋል። አሁን ለኢታማጆር ሹሙ ለጄኒራል ብርኃኑ ጁላ ከአቅማቸው በላይ ስለሆነ የፋኖ ተጋድሎ አስረክበዋል። አቶ አረጋ ከበደም አለቃቸው ጠሚር አብይ አህመድ ሳይሆኑ ጄኒራል ብርኃኑ ጁላ ናቸው። የሚመሩት በኮማንድ ፖስት አዛዦች የበታች ሹማምንቶችም ጭምር ነው።
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ በኦሮምያ ጉዳይ ድርሽ ብለው አያውቁም በአመራር። መብት የላቸውም። እርግጥ ነው የኦነግን ዓላማ በመፈፀም እና በማስፈፀም የሎጅስቲክስ አገልግሎት የኢትዮጵያ አንጡራ ሃብት እንዲፈስ ይፈቅዳሉ። ለዛ የሚመቹ መሪወችንም ይመድባሉ።
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ኢትዮጵያን ሙሉ የመሩበት ወቅት ለ100 ቀናት ብቻ ነው። ትርፍ ዝንፍ የሌለው 100 ቀን። ከዛ በኋላ ሥልጣናቸውን ለማረጋጋት በሠሩት ስውር ሸፍጥ ሁሉም ነገር ከእጃቸው አመለጠ። ሂደቱ የተጀመረው ፀጉረ ልውጥ ከሚለው የሰኔ 16/2010 ትራጀዲ ጀምሮ ኢንጂነር ስመኜው በቀለን ሰውቶ፤ አዲስ አበቤን በአደባባይ የቀጠፈው የቡራዩ አብዮት፤ ሦስቱ ሰኔወች፤ ሦስቱ ጥቅምቶች ወዘተ ………
እና ትናንት መንጥሩ ተብሎ የተመነጠሩ፤ የተነቀሉ ምንዱባን ዛሬ ለዛውም ዛሬ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ እዬሠራን ነው የሚለው አገላለጽ ለእኔ "ቂጥ ገሊቦ ራስ ተከናኒቦ" ይሆናል። ምን አደረጉ እነዚህ መከረኞች ከሞት የተረፋት እንደገና ወደ ሞት የሚሸኙት??? ለምን??? መያዣ ለትግሉ ከሚል አይደለም። ይህን የሚሉ ከኖሩ የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎን በቅጡ ያልተረዱ የግንዛቤ ስስነት ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ።
ምክንያቱም የአማራ የህልውና እና የማንነት ተጋድል የሳቢያ ትግል አይደለም። ፖለቲካዊ ትግል ነው። መልሱም ግሎባል መፍትሄ የሚሻ እንጂ በቁንጣ ቁንጢ ንትርክ መፍትሄው አይመነጭም። የሥርዓት ለውጥ ብቻ ሳይሆን የአስተሳሰብ ሪቦሊሽንም ይጠይቃል። አማራን ለመንቀል ከሥሩ የሚሠሩት ያውቁታል። ለምን እንደጀመሩት ምን ሲሳካም እንደሚያቆሙት።
የካንሰርን በሽታ በፓናዶል ህክምና አይፈወስም። ለአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ አይደለም በረገበ እርግብግቢት ላይ ያለው የቲም አቶ አረጋ ከበደ ቀርቶ የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ሥርዓትም ከአቅሙ በላይ ነው። ትግሉ ሳቢያዊ አይደለም። ስለዚህ ሳቢያዊ መንተፋተፍ ጥያቄውን አይመልሰውም።
የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ኢትዮጵያ ሙሉ ጤናዋን ስታገኝ ብቻ መልስ ያገኜል። እራሱ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ እና ካቢኒያቸው ለአማራ ህልውና መሠረታዊ ችግሮች ናቸውና። ርዕዮቱም፤ መዋቅራዊ አቅሙም የአማራን ህዝብ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ጥያቄወች ሊመልስ አይችልም። በፀረ አማራ የተደራጄ ማንኛውም ተቋም የመፍትሄ አመንጭም፤ አካልም መሆን አይችልም። እኔ ስላልኩት ሳይሆን ሎጁኩ ያስገድዳል።
ከወለጋ የተፈናቀሉት ብቻ ሳይሆን ከአዲስ አበባ፤ ከመላ ኦሮምያ፤ ከመላ መተከል፤ አልፎ አልፎ ከደቡብ የሚፈናቀለው የአማራ ህዝብ ትንሳኤ በሰከነ የሥርአት እና የአስተሳሰብ ለውጥ ብቻ መፍትሄ ያገኛል። "አለባብሰው ቢያርሱት በአረም ይመለሱ።" የአብይዝም የመቃብር ሥፍራ የኦሮምያ ክልልን መስተዳድር ስለቀዬረ፤ ወይንም አሳቻውን አቶ አባ ዱላ ገመዳን በአዲስ ዜማ ስላቀረበ የማይሆነው አይሆንም። እነሱ የተነሱበት ዓላማ አላቸው። ያም ኢትዮጵያን ሃይጃክ አድርገው እዚህ ደርሰዋል፤ እንዳይቀጥሉ ማስቻል ደግሞ ከግርግር፤ ከግልብልብ ፖለቲካ ወጥቶ የሰከኑ ተግባራት እና አስተሳሰቦች አሸናፊ ሆነው እንዲወጡ መትጋት ያስፈልጋል።
የአማራ ህዝብ በደል ለሁለት ትውልድ የዘለቀ ይፋዊ ነው። ውስጥ ለውስጥ የሚያስኬድ የህቡ ድርጅት አያስፈልገውም። ወይንም በጥቂቶች ኮፒራይት ብቻ የሚከወንም አይደለም። የገዘፈ ሁልአቀፍ ትሁት መስመርን ቀይሶ፤ በጠራ ፖሊሲ ግልጽ ስትራቴጅ እና ታክቲክ ነድፎ መንቀሳቀስን ይጠይቃል። የበሰለ የጨመተ የፖለቲካ መስመርን መከተል። በወታደራዊ ክንፋ መሬት ላይ መሪወች አሉት ተጋድሎው። ይህ በጠራ፤ በበሰለ፤ በተደራጄ ሆደ ሰፊ እና አቃፊ፤ አረጋጊ ሶልዳሪቲ ሊታገዝ ይገባል። ትግሉ የህዝብ ነው። መሪወች የህዝብ የሆኑ በሞራል፤ በሥነ ምግባር በድርጊትም እንደ አባት አደሩ ልቅናን በልዕልና ያዋሃዱ ሰውኛ እና ተፈጥሮኛ ሰብዕናን ይጠይቃል። ለዛ እመጥናለሁ ወይንም መጥኛለሁ የሚል ድጋሚ ስህተት ተተግብሮ መስዋዕትነቱን እንዳያበራክተው ተደሞን ይጠይቃል።
ለአንድ የፖለቲካ ትግል ብልጠት ሳይሆን ብልህነት ለድል ያበቃዋል። ተጽዕኖ ፈጣሪነት እና የአመራር ብቃት እና ስኬትም በቅጡ ሊፈተሹ ምርምር ሊደረግባቸው ይገባል። ይህን በዘመናችን ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ የዩክሬንን መሪ እንደ አንድ የመማሪያ ኦብጀክት ወስዶ ትርፍ እና ኪሳራውን መመዘን ይገባል ባይም ነኝ።
የሆነ ሆኖ ወደ ወለጋ እንዲመለሱ የተበዬነባቸው ወገኖቼ ሞት እንደተወሰነባቸው ይሰማኛል። ግፍም ነው። የከፋ በደልም ነው። እነሱ ቢፈቅዱ እንኳን ፈፅሞ ሊታሰብ አይገባም። ኢትዮጵያ ሰውኛ፤ ተፈጥሮኛ ሙሴ እና ቲም ሲኖራት ሁሉም በጊዜው ይከወናል። አሁን ባሉበት ሁኔታ ግን ሊታሰብ አይገባውም።
ሌላው ስለ ራህብ በተነሳው ጥያቄም ዓለም ዓቀፍ ንቅናቄ ይጠይቃል። ራህብ ራህብ ነው። ዘመንኛው የኮንስትራክሽን ሚሩ አብይ አህመድ አሊም ግብረ ሰላማቸውን፤ ሽርሽራቸውን፤ ቅንጡ ቤተ መንግሥት ግንባታቸውን በሙሉ አቁመው ለተራቡ ወገኖች መድረስ ግዴታ ነው። ባለ ኖቤል እኮ ናቸው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ላነሳ እምሻው ሊለምኑ ያፈሩ ረሃብተኞች፤ ዕቃቸውን ለመሸጥ ያፈሩ ወገኖች ቤቱ ይቁጠረው። ዛሬ ባዳመጥኩት ሪፖርት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከአንድ C ወደ D እንደወረደም አዳምጫለሁኝ። እነ አቶ አረጋ ከበደ ያላችሁበትን ዕውነት ከዕውነቱ በመረዳት የሚመጥን አቅምን አምጦ መውለድ ይጠይቃል።
በመጨረሻ በሁለገብ መከራ ተሰቅዞ የተያዘው ህዝባችን ሲከር ይበጠሳል፤ ሲሞላም ይፈሳል ……… ዛሬ በብዙ አፈና የተያዘው ህዝብ ሆነ፤ ይሠራል የሚባለው ህግም መከራው እራሱ መልስ ያሰጠዋል። ይፈነዳል። ጭንቀቴ ማን ያስተዳድረዋል ነው? መሰናዶው ህሊናዊው ሆነ ተቋማዊው መተንበዬ ስለሚያስቸግር።
ለግርባው ብአዴን አመራሮች አቅማችሁን ማወቅ ይጠቅማችኋል። ህዝብ አክብሩ!!! የፈለገ ኃይል ቢኖር ህሊናው እና ልቡ የሸፈተን ህዝብ ማሸነፍ አይቻልም።
የሆነ ሆኖ ወላጅ አልባ የአማራ ልጆችንስ ሞግዚት ቀጥራችሁ ይሆን ወደ ወለጋ የምትመልሷቸውን? ጓዘ ቀላል ጥያቄ ለአቶ አረጋ ቲም።
"...በቤታችሁ ይድረስ!" አሰቃቂው የኢሰመጉ ሪፖርት Wed 27 Dec 2023
https://www.youtube.com/watch?v=s4gGHi0sL-I
EMS - ከአቶ አረጋ ከበደ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ ።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
28/12/2023
ኢትዮጵያን ውስጡ ያደረገው አማራነት በመርህ እና በዕውነት ያሸንፋል።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ