በእምዬ ሲዊዘርላንድ፤ ዙሪክ ክፍለአገር፤ በዙሪክ ከተማ በራዲዮ ሎራ የብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ራዲዮ ከተመሰረተ ዛሬ #መስከረም 18.2025 ልክ ፲፯ (17) ዓመቱ። ተመስገን። አሜን።
በእምዬ ሲዊዘርላንድ፤ ዙሪክ ክፍለአገር፤ በዙሪክ ከተማ በራዲዮ ሎራ የብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ራዲዮ ከተመሰረተ ዛሬ #መስከረም 18.2025 ልክ ፲፯ (17) ዓመቱ። ተመስገን። አሜን።
#ምንጊዜም ኢትዮጵያ!
ይህ ቀን ለእኔ ልዩ ነው።
ይህ ቀን ለእኔ ትርጉሜ ነው።
ይህ ቀን ለእኔ ሚስጢሬ ነው።
ይህ ቀን ለእኔ ከእናት አገሬ ጋር ቃሌን በማዘውተር የማስርባት ዕለቴ ነው።
ምንጊዜም #ኢትዮጵያ!
የጸጋየ ድህረ ገጽም በተመሳሳይ ዓመት ሰኔ 18 ነበር የጀመርኩት። በቲም ይሠራ ስለነበረ መቀጠል አልቻለም። የእኛ ነገር እንዲህ እና እንዲያም ነውና። ዛሬ የአባይ ሚዲያ ያለበትን ደረጃ ተመልከቱት። በተመሳሳይ ዘመን ነው የበቀሉት። ዛሬ አባይ ሚዲያ ቢጠሩት አይሰማም። አጋዥ ያገኜ ሚዲያ የት እንደደረሰ ተመልከቱት። መዝኑትም። ያ ብሩክ፤ ትሁት ሰው አክባሪው ባለቤቱም የአይቲ ባለሙያ ስለሆነ ጥገኝነት የሙያ አላስፈለገውምና። አስቀጠለው። እንኳንም ቀናው።
የሆነ ሆኖ የጸጋየ ራዲዮን ብቻየን ስለምሰራው #ህልውናው ቀጥሏል። የጸጋዬ ራዲዮ በጭምቷ በእምየ ሲዊዘርላንድ፤ ዙሪክ ክፍለአገር፤ ዙሪክ ከተማ በተናፋቂው እና በተወዳጁ፤ 24 ሰዓት በሚተጋው #በራዲዮ #ሎራ በ97.5 መካከለኛ ሞገድ በወር ሁለት ጊዜ በዕለተ ሃሙስ የቀን ቅዱስ #ከ15.00 እስከ 16.00 እንደ አውሮፕውያኑ ሰዓት አቆጣጠር በአማርኛ ቋንቋ ይቀርባል።
ይህን ተግባር ስደተኛ ካንፕ ውስጥ የምትኖር አንዲት ባተሌ ስትወጥን በባከነ ጊዜ የሚባዝን መንፈስ ራዲዮ ፕሮግራሙ #ተከሰሰ። የሚገርማችሁ ከዚህ ቀድሞ ሌላ ክፍለ አገር ሄጄ በነፃ ስሰራም ኃላፊዬ ተከሳ ነበር። ከሳሾቹ የእኛው ጉዶች ነበሩ። እሱን ለማገድ ዳርዳር ሲሉ ሙሉ አቅም አለኝ እና ከምኖርበት ክፍለ አገር ስጀምር ደግሞ #ክሱ ቀጠለ። ሥራ ፈቶች #ጤናማ ትጋት ጤናቸውን ያውከዋል።
የቀደመው የመኖሬያ ፈቃድ የሌላት ለሌላ ክፍለአገር ሄዳ ልትሰራ አይገባ ነበር። እሰቡት በነፃ ለሚሠራ ሥራ። የትራንስፖርት ወጪ እራሴው ነበር ለምሸፍነው። እማድረውም ሌላ ቤት ነበር። ምክንያቱም ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ጨርሼ ቤት እስክደርስ ድረስ እኩለ ሌሊት ይሆናል። ትራንስፖርት የለም ወደ መኖሪያ ቤቴ ለመሄድ። በእግሬ ደግሞ ድልድዩ ያስፈራኝ ነበር። እማድረው ከመምህሬ ቤት ነበር። መምህሬ የራሷን አልጋ ለቃ እሷ ከሥራ ቢሮዋ ታጣፊ አልጋ ላይ ነበር የምትተኛው። መምህሬ ትኖር የነበረው ሌንስቡርግ ከሚባል ከተማ ነበር። እሷ የስደተኛ የመጋዚን ዝግጅት እና ህትምት መምህሬ ነበረች። የልጆች ጋዜጠኛ ነበረች።
አሁን በተጨማሪነት ህዝብ ግንኙነት ላይ ትሰራለች። እሷ እራሱ ፕሮግራማችን በመደበኛ ታዳምጠው ነበር። ዛሬ ቃለ ምልልስ ነበራችሁ ሁሉ ትለኝ ነበር። ስከሰስ እጅግ በጣም ነበር የገረማት። ኢንተርኔት ላይ እንድጀምር ሁሉን አመቻችታልኝም ነበር። እኔ ግን ራዲዮ ሎራ አመልክቼ ጀመርኩኝ። የዛን ጊዜ የቅንጅት መሪወች ከእስር እንዲፈቱ አብራኝ ብዙ ሥራ ሠርታለች። ውዴ ናት።
የሚገርማችሁ ግን ገና አንድ ፕሮግራም እንደ ሠራሁኝ በምኖርበት ክፍለ አገር ስጀምር ደግሞ #በአክራሪ ኦርቶዶክስ እና አክራሪ #ኦሮሞነት ተከሰስኩኝ። ከሳሾቹ እኮ ኦርቶዶክሶች እኮ ናቸው። የእኛ ነገር ዕድላችን ሁልጊዜ #ክንብል ቢል ምን ያስፈርዳል? ስኬታችን #ቢርቅ ወይንም ቢያመልጠን ምን ይደንቃል? #ምርቃታችን ቢነሳ ምን ይገርማል? የእኛ ነገር የፍላጎታችን ቋንቋ ዘመነ ባቢሎንን ጠሪ እኮ ነው። አገራችን ስትከብር #የሚቆጠቁጠን፤ #የሚያርመጠምጠን። ደስታ ይራቀን ብለን የምንጸልኝ ግርዶሾች።
ውስጣችን አሽዋማ ነው። ጥረታችን የጉም ሽንትነትም ከውስጣችን ጠራጠሮ መሻት ጋር የተያያዘ ነው። ከእጃችን የገባ ወርቅ ሁሉ ቀልጦ የሚፈሰው፤ የኢትዮጵያ እናቶች ዕንባ መፍሰሱን ማስቆም ያልቻልነው #ቅንነትን የምንፈራ፤ #ቀናነት የሚርደን ስለሆነ ነው። ያልታደልን። የእኛ ላይበቃ ሁለተኛ ትውልድም በዚኽው ይቀጥል ዘንድ የፈቀድንም ይመስላል። እራሳችን አርመን እና አርቀን ስህተቶቻችን ላንመለስባቸው ሃራም ማለት አቃተን።
የጸጋዬ ራዲዮ ፕሮግራሙ ክሱ #የኦሮሞ አክራሪነት ነበር። እኔ ኦሮሞ #ሳልሆን የኦሮሞ ጽንፈኛ እንዴት ልሆን እችላለሁኝ??? በኦርቶዶክስ ተዋህዶም ራዲዮ ፕሮግራሙ በጽንፈኝነት ተከሷል። ራዲዮ ሎራ በአደረገው ጥልቅ ማጣራት ግን ምንም ዓይነት #የጽንፈኝነት መንፈስ እንደሌለው ካረጋገጠ በኋላ አስቀጥሎታል። የምስክርነት ደብዳቤውን እለጥፈዋለሁኝ።
እኔ ዕውነቱን ብነግራችሁ በተፈጥሮየ #ክርር ያለ፤ #ምንችክ ያለ ግትር ያለ ችኮ ባህሬን የማስተናግድ ሴት አይደለሁም። የማውቀው ወይንም የቀረብኩት ወይንም የምተጋለት ሰብዕና ይህን መስመር የሚከተል ከሆነም አልቀጥልም። ሁሉ ነገር ከእኔ ቤት #በልኩ ነው። ሃይማኖቴን ቅድስት ተዋህዶን አከብራለሁ - እወዳለሁኝ። ይህ አሊ አይባልም። ፆታዬን እወዳለሁ አከብራለሁኝ። ይህም ዕውነት ነው።
ግራ ቀኙን ማንነቴን ኢትዮጵያዊነቴን ሆነ አማራነቴን እወዳለሁ አከብራላሁኝ። ይህም ሃቅ ነው። ሙያዬን እወዳለሁኝ አከብራለሁኝ። ይህም ፋክት ነው። ሁሉንም ግን #በልካቸው ነው። ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ ነው ሙሉ ትኩረቴን፤ ሙሉ አክብሮቴን የምለግሳቸው። በጥንቃቄ ። ከስሜታዊነት በጸዳ መልኩ ነው።
ወጣት እያለሁም ከዕድሜዬ በላይ ያን ያህል በተለያዬ ጊዜ የተለያዬ ጊዜያዊም ይሁን ቋሚ ኃላፊነት ሲሰጠኝ የተረጋጋው፤ በልኩ የሆነው ደልዳላው ተፈጥሮዬ ነው ያገዘው። በአኗኗሬም ውስብስብ ያለ፤ በአመጋገቤም ብዙ ነገሮች ያካተተ አይደለም። ቀለል ያለ ህይወት ነው የሚመስጠኝ። የተወሳሰበ ጉዳይም፤ ሆነ አኗኗር ውስጥ አልሞክረውም።
አኗኗሬም በሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ "#የይበቃኛል" ዶግማ የተከረከመ ይዘት ነው ያለው ግን - ፃዕዳ። በህይወቴ ሙሉ የግል የቤት፤ የእርሻ ይሁን የቢዝነስ የግል ቦታ ኑሮኝ አያውቅም። ተመኝቼም አላውቅም። ኃላፊነት ላይ እያለሁኝ ብዙ ሰው ቦታ ሲመራ እኔ እና አንድ ባልደረባዬ ብቻ ነበርን የቤት መሥሪያ ቦታ ያልተመራነው። የቤት መሥሪያ ቦታ አያስፈልገኝም።
በህይወቴ ሙሉ የግል መኖሪያ ቤት፤ የቤት ይሁን የሥራ መኪና በአዕምሮዬ መጥተው አያውቁም። እግረኛ ነኝ። እራሱ አለባበሴ ክረምት የስፖርት ቱታ በጋ ቀላል ያለ ታይት ወይንም በስፖርታዊ ጫማ ነው ምርጫዬ። በማህበራዊ ግንኙነቴም #ጥንቅርቅር ያሉ ጉዳዮች አይገቡኝም። ስለሆነም የተከሰስኩበት የኦሮሞነት እና የተዋህዶ አክራሪነት ለእኔ የተፈጠሩ አይደሉም። በፍጹም።
የማከብራችሁ የአገሬ ልጆች እኔ "መሬትን ስትረግጧት #ቀስ ብላችሁ እርገጧት። መሬትን ስትራመዷት #አትደብድቧት" ከሚሉ በጣም ጥልቅ የሆነ የሥነ - ምግባር የሞራል ልዕልና ጸጋ ካላቸው ቤተሰቦች ነው የተፈጠርኩት፤ አስተዳደጌም በዛው ልክ ነው። ሰው ቢናገረኝ ወዲያው መልስ እንኳን አይመጣልኝም። ጠብ ነገር ካለ እኔ በዚያ ዙሪያ የለሁም። አልገኝምም። ጭቅጭቅ የሚባል ነገር አልወድም። ስለ ሰውም ምንም ዓይነት መረጃውን ማወቅ አልሻም። ምን አገባኝ። ጊዜ ማባከን ነው።
እኔ እምታወቀው እኮ ስልክ ባለመመለስ ነው። ነገር ግን በመንገዶቼ ሁሉ ብዙ ፈተና ይገጥመኛል። ለምን? የበለጠ እንድጠነክር። የበለጠ ጠንቃቃ እንድሆን ይመስለኛል። በማህበራዊ ግንኙነቴም ወዲያው መቀላቀል አላውቅበትም። እጅግ በጣም ቁጥብ ነኝ። ግን ፈተናው አይለቀኝም።
የሆነ ሆኖ የተከሰስኩበት የብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ራዲዮ እንሆ ዛሬ ፲፯ኛ ዓመቱ ዛሬ ሞላው ። ተመስገን አማኑኤል። እኔ እራሴ ላምን አልቻልኩም። ብዙ በጣም ብዙ ብሄራዊ ተግባራት ተከውኖበታል። ብዙ በጣም ብዙ የእዕምሮ ውጤቶች ቀርበውበታል። ዝግጅቴ ሙሉ ነው። አንድ ዓመት አይሞላኝም ለሙዚቃ እንኳን ጊዜ ስሰጥ።
ቀደም ባለው ጊዜ የምወደው በተፈጥሮ በውሃ ፏፏቴ፤ በወፎች፤ በውቅያኖስ፤ በዝናብ ድምጽ ነበር ፕሮግራሙን እማቀነባብረው። አሁን ከሆነ ባቲን፤ ትዝታን፤ አንቺ ሆዬን አንባሰልን ማስተዋወቅም አንድ ዘርፍ ቢሆን ብየ ጀምሬዋለሁኝ። ያለፈው ሳምንት ሙሉው ለአዲ ዓመት የተዜሙ ኢትዮጵያዊ የምሥራችን ናፋቂ፤ ተስፋን ዘካሪ አገር በቀል ሙዚቃወችን ነበር ያቀረብኩት። ለዛ ይመስለኛል እኔም አገር ቤት እንዳለሁ የተሰማኝ። ባለፈው ዓመት ሁለት ጊዜ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ብቻ ሙሉ ሰዓቱን ሰጥቼው ነበር። በውነቱ እኔ በሥንኞች ላይ እንጂ ጥልቅ የሆነው የሙዚቃ ዕውቀት በሚመለከት ዕውቀት ተመክሮ የለኝም። በልጅነቴም ሙዚቃ አድማጭ አልነበርኩም። በልጅነት ማንበብ ነበር መደበኛ ተግባሬ።
እግዚአብሄር ይመስገን የጸጋዬ ራዲዮ በየጊዜው የገጠመውን ፈተና ተቋቁሞ እዚህ ደርሷል። ነገም ፈተናው ይኖራል። አንድዬ ያውቃል። ያለፈው ሃሙስ በዕለተ ቅዱስ የኋንስ ዝግጅት ነበረኝ። ኢትዮጵያ ያለሁ ነበር የመሰለኝ። ዛሬ ፕሮግራም የለኝም። ለምን? የጸጋዬ ራዲዮ በወር ሁለት ጊዜ በዕለተ ሃሙስ ከ15.00 -16.00 በአማርኛ ቋንቋ የሚቀርብ በመሆኑ የሚቀጥለው ሃሙስ ነው ዝግጅት ያለኝ። እያሰገረ ነው ፕሮግራም የሚኖረኝ። በሚቀጥለው ሳምንት መሰናዶዬም በውነቱ ፲፯ኛ ዓመቱን በሚመለከት ልዩ ዝግጅትም የለኝም።
ቀደም ሲል የራዲዮ ፕሮግራሙ የትግል ራዲዮ ነው የነበረው። አሁን ደግሞ በተፈጥሯዊነት እና በሰዋዊነት ላይ አተኩሮ ነው የሚተጋው። የግድፈቱ ምንጭ የሰዋዊነት እና የተፈጥሯዊነት ህግጋት መጣስ ነው ብዬ ስለማምን። ትውልድን በግሎባል ደረጃ በሰዋዊነት፤ በተፈጥሯዊነት መቅረጽ ችግሮችን ያስታግሳቸዋል ብዬ አስባለሁኝ። የሰው ልጅ ወደ ተፈጠረበት ረቂቅ ጸጋ ካተኮረ የተፈጠረበት ሚስጢር ይገባዋል። ያ የሰው ልጅ የተፈጠረበት ሚስጢር ከታወቀ ለክፋት እና ለክፋ ሃሳብ፤ ለምቀኝነት እና ለተንኮል፤ ለጥላቻ እና ለቂመኝነት፤ ለበቀለኝነት እና ለወንጀለኝነት የሚያጠፋው ብናኝ አቅም፤ ጊዜ አይኖረውም የሚል ሙሉ ዕምነት ነው ያለኝ።
ትውልድን ጭካኔ አያስቀጥለውም። ትውልድን ክፋ ሃሳብ አያድነውም። ትውልድን ጥላቻ ህሊናውን ገዝቶ ወደ ብቃት አያሸጋግረውም። ትውልድን በቀል ለአደራ አያበቃውም። ትውልድን ስውር እና ግልጽ ወንጀሎች ለተረጋጋ የመኖር ሥልጣኔ አያበቃውም። በተዛባ፤ በተሰባበረ ድልድይ ትውልድ ለግሎባላይዜሽን የሥልጣኔ እና የልዕልና ደረጃ እኩል ሊያበቃው ፈጽሞ አይችልም።
ስለዚህም ትውልድን ቀና አድርጎ፤ ቀጥ አድርጎ በንጽህና ለመነጽ ጥረቱ መስመሩ ዕውነት፤ መርኽ፤ ቅንነት፤ ርህርህና ወዘተ ጋር ማገናኜት ብዙ ኮረኮንች የመኖር መንገዶችን ያስተካክላል ብዬ አምናለሁኝ። በተለይ ሥልጣን ላይ ያለ፤ አክሰሱ ያለው አካል ሁሉ ትውልድን የሚያድን፤ መኖሩን የሚያሰለጥን፤ ለተፈጠረበት መዋዕለ ዕድሜ የተአጋጋ የሰላም ዋሴትና ላይ መጨነቅ መጠበብ አለበት ብዬ አስባለሁኝ። እግዚአብሄር አላህ የፈጠረው ፍጥረት ነፃነቱ ከታገተ መኖሩ ይስተጓጎላል።
ይህ ደግሞ ከፈጠረ አምላክ አላህ ጥበብ ጋር መጣላት ስለሚሆን ነፃት ነፃ ይሁን የዘወትር ትጋቴ ነው።አውዳሚው ጦርነቶች ሊታቀዱ አይገባም። የተጀመሩትም ሊቆሙ ይገባቸዋል። የሰው ልጅ ክብር በሰው ሰራሽ የጥፋት መሳሪያወች ሊጎሳቆል አይገባም ባይም ነኝ።
የጸጋዬ ራዲዮ የየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባል፤ አካል፤ ደጋፊ አይደለም። ከምንም ነገር ጋር ንክኪ የለውም። ከየትኛውም ተጽዕኖ ፈጣሪ ፍላጎት ጋርም ምንም ግንኙነት የለውም። ጥገኛ ሃሳብ አያስተናግድም።
በተፈጠረበት አሻራ ልክ የኦርጋኒኳን ኢትዮጵያ ተፈጥሮ አክብሮ የሚያስከብር በራሱ አሻራ እና አቅም ላይ ጸንቶ የቆመ ነው። የራሱ ሃሳብ፤ የራሱ ግብ እና ዓላማ ያለው ምንም ዓይነት የሃሳብ ድህነት ትውር የማይልበት ህግ አክባሪ፤ ለማንኛውም ብሄራዊ፤ ሉላዊ፤ ሃይማኖታዊ፤ ሰዋዊ ህጎችን የማይተላለፍ ራዲዮ ነው።
በሃይማኖትም ዘርፍም እንዲሁ። ለሁሉም ሰዋዊ ሃይማኖቶች፤ ለሚያምኑም ለማያምኑም ዜጎች በሰውነታቸው እኩል ክብር ያለው ዕውነት፤ መርህ፤ የሰባዕዊ መብት መጣስ የለበትም ብሎ የሚያምን ራዲዮ ነው። ለእናቶች ዕንባ ስስ ልብ ያለው። ለሴቶች መደፈር የሚቆረቆር ሚዲያ ነው። በጤነኛ ሃሳቦች ላይ የሚተጋ እራሱን የቻለ ሚዲያ ነው።
ማህበረ ቅንነት ኑሩልኝ። አሜን።
ኦኦ እንዴት አደራችሁ? እንደምን አረፈዳችሁልኝ።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
18/09/2025
ተመስገን አማኑኤል አባቴ። አሜን።
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ