#ትህትና አንዱ #የስኬት #ጎዳና ነው።
ትህትና ለራስም የውስጥ ሰላም የሚሰጥ ልዩ የፈጣሪ አምላካችን፤ የአላሃችን ልዩ ስጦታ ነው። የፈለገ የከበደ፤ የገዘፈ ፈተና ቢገጥም ትሁታዊ አቀራረብ ሻካራውን ግንኙነት ልጎ አንፃራዊ ልስላሴ የመፍጠር አቅም ይኖራዋል። አንዳንድ ጊዜ ሳታስቡት እልህ የገቡ ሰብዕናወች ይገጥማሉ። እናንተ የተበሳጩበትን ሁነት ላታውቁ ትችላላችሁ።
ግን ግንኙነቱ ሳንክ እንደገጠመው ስትረዱ ምላሹን ግርጭርጭ መንፈስ ወደፊት ከማምጣት ይልቅ በትሁት መንፈስ ጉዳዩን ለማየት መፍቀድ ብዙ #የጎረቡ ጉዳዮች ፈውስ ሊሰጥ ይችላል። " ኃይል የእግዚአብሄር ነው።" ተስፋም ከእግዚአብሄር ዘንድ ነው። የተስፋ + የኃይል አቅም ትህትና ከታከለበት የስኬት ጎዳና ይጠረጋል።
ይህን በስማበለው ሳይሆን እኔ በዘመኔ ያዬሁት የዕውነት ገጠመኝ ነው። የእናቴ የእብዬ ትህትና ይከብደኝ ሁሉ ነበር። የእሺታዋ መጠነ ሰፊ አቅምም ይከብደኝ ነበር። እኔ ከእሷ መሐጸን መገኜቴ ብቻ ሳይሆን እንደ ጓደኛም አብሮ አደጎች ነበርን። ብዙ በጣም ብዙ ነገሮችን ከእናቴ ወርሻለሁኝ። አባቴ አቨይም የዝምታ ዘውድ ነበር። ስለሆነም ተበድየም ይቅርታ እምጠይቀው እኔው ነኝ። ካሳ ካለም እምክሰው እኔው እራሴ ነኝ። ከሁሉ የሚያስደስተኝ ስጦታ #መስጠት፤ ደስታን በገፍ ማቅረብ ሲሆን ክንዋኔውም በትህትና ነው። ይህም በመሆኑ ውስጤ የጸና ሰላም አለው።
ቆፍጠን ማለትን በሚሹ የሥራ መስኮችም ቆፍጣና ነኝ። ሁልጊዜም በልኬ ነው መኖሬን መምራት እምሻው። እስር ቤትን አውቀዋለሁኝ። ስለዚህም እስር ቤት ያሉ ወገኖቼ ያሳስቡኛል። እስር ቤት እኮ #የመጸዳጃ ቤት የመሄድ ይለፍ ፈቃድ ማግኜት ብርቅ ነው። ግልምጫው፤ መስቃው፤ ግባ ውጣ መባሉ እንደተጠበቀ ሆኖ በተለይ ወረርሽኝ ሲገባ፤ እስረኞች ታመው ህክምና ሲከለከሉ፤ ወይንም ሲደበደቡ፤ እስረኞች የቤተሰብ ጥየቃ ሲነፈጉ፤ የታሰሩ እስረኞች የታሰሩበት ቦታ ሲሰወር ይጨንቀኛል። እጅግ በጣም ነው የሚጨንቀኝ።
ስለሆነም ለሚመለከተው አካል አቤቱታን #በአክብሮት እና #በትህትና አቀርባለሁኝ። አቤቱታ እማቀርበው አንፃራዊ ምላሽ ላገኝበት እችል ይሆናል ብዬ ለማስበው አካል ብቻ ነው። ቀደም ባለው ጊዜ የኢትዮጵያ የጤና ሚር የነበሩት ለዶር ሊያ ታደሰ እና፤ ለኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለዶር ዳንኤል በቀለ ነበር።
ያን ጊዜ ሳቀርብም ተስፋ አትጠብቂ ይሉ የነበሩኝ የቤታችን ታዳሚወች ነበሩ። እኔ ግን በየጊዜው ሙግትም ሲኖረኝ፤ አቤቱታም ሲኖረኝ ለሁለቱ መሪወች በትህትና አቀርብ ነበር። ዛሬ ለኢትዮጵያ የሰብአዊ ኮሚሽን አንድም አቤቱታ አቅርቤ አላውቅም። በህይወት ስለመኖሩም አላውቅም ብዬ በዛን ሰሞን ስጽፍ #አለን የሚል ይመስላል BBC ላይ አንድ ዘገባ ወጥቶ አየሁ። አቤቱ አብንንም እንደዛው ብዬ ስለነበር እነሱም በመግለጫ ብቅ ብለው ነበር።
በፊት ጊዜ ለኢትዮጵያ ጤና ሚር ይሁን ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከማቀርባቸው አቤቱታወች ውስጥ #የተወሰኑት መልስ አግኝቸባቸው ነበር። ፈጣን መልስ የተሰጣቸው በኽረ ጉዳዮችም ነበሩ። ያ መልስ እስር ቤት ላሉ ወገኖቼ ለወቅቱ እጅግ ጠቃሚ ነበር። ጠቃሚ ነገር ለማግኜት በቁጣ፤ በግልምጫ፤ በእልህ፤ በማናህሎኝነት፤ በትርፍ ንግግር፤ ህግ የሰማዩንም የምድሩን በመተላለፍ አይደለም። ይህ የአያዝ ዝንፈት ለትውልድም ፈጽሞ መይጠቅምም።
እኔ ሰላማዊ ሞጋች ነኝ። ያለኝ ብዕር ብቻ ነው። ያለኝ የልብ ንጽህና በትህትና ነው። ያለኝ ህግ አክባሪነት በአክብሮታዊነት ነው። ይህን ድልዳል አድርጌ በጨነቀኝ ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ ላሉ ባለሙሉ ባለሥልጣን አቤቱታ አቀርባለሁኝ። ዱር ቤቴ ያለ፤ ጠበንጃ ያለው ባለው ፍላጎቱን ለማሳካት ሊወስን ይችላል። እኔ የጫካውን ትግልም ባውቀው ሰው በመረጠው መንገድ የመጓዝ ሙሉ መብት አለውና በዝምታ ነው የባጀሁት ጉዳቱን ብቻ እየዘገብኩኝ።
እኔ ደግሞ አቤት ስል አቤቱታ ለማቅረብ ሳስብ ጸሎቴን በቅድሚያ አድርሼ እጽፋለሁኝ። ጹሁፌን በትህትና እና በአክብሮት እቀምመዋለሁኝ። በጹሁፌ ውስጥ የኃይል፤ የመንጠራራት፤ የትምክህት፤ የማጣጣል ወይንም የማቃለል ቃላቶች እንዳይኖሩ በጥንቃቄ ነው እምጽፈው። እርግጥ የፊደል ግድፈት ሊኖርበት ይችላል።
የሆነ ሆኖ እስረኛ ለሆኑ ወገኖቼ ጥንቃቄ እንዲደረግላቸው መሻቴን፤ ስገልጥ ከውስጤ በመነጬ ንጹህ #ትህትና እና #ባልባለቀ አክብሮትም ነው። ቤቴም እንግዳ ሲመጣ ይኽው ነው። ለጎረቤቶቼም ሥራ እሰራ በነበረ ጊዜ ለባልደረቦቼም ትህትና አክብሮት አብረውኝ ናቸው። ይህ የማይመቻቸው ወገኖቼ ሊኖሩ ይችላሉ። እነሱ በመረጡት አቅጣጫ መፍትሄውን ካገኙት እሰየው ነው።
በእኔ ላይ ግን እነሱን እመስል ዘንድ ምንም ዓይነት #ጫና ማሳደር አይፈቀድላቸውም። እኔ ሥርጉተ ሥላሴ ጎርፍ አምጥቶ ደለል የሰራበት ሰብዕና የለኝም። ደራሽ ፖለቲከኛም አይደለሁም። የመብት እና የግዴታየን ጣሪያ እና ግድግዳም አሳምሬ አውቀዋለሁኝ። የእኔን ሰብዕና በትውስት ሰብዕና ፈጽሞ መተካት አይቻልም። የእኔ ትሁታዊ፤ አክብሮታዊ ጉዞ የማይመቻቸው ወገኖቼ የራሳቸው ፔጅ አላቸው፤ በፔጃቸው ያሻቸውን እንደ አሻቸው መፃፍ ባለመብት ናቸው።
እኔን እምመራው #እኔው ነኝ። እኔ የየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት፤ የሲቢል ማህበራት አባል፤ አካል አይደለሁም። ሁኜም አላውቅም። ወደፊትም አልሆንም። የራሴ ቋሚ አሻራ አለኝ እና። እኔ የራሴ እንደራሴም ነኝ። የራሴ መርኽ፤ የራሴ ጎዳና ዛሬ የተቀመረ አይደለም። መቸውንም ሥርጉትሻ የተቀመረችበት መስመር ዕለታዊ፤ ደራሽ፤ ግንፍል ግንፍል በሚል ስሜት የታጨቀ ሊሆን ከቶውንም አይችልም። በጣም ለጋ ወጣት እያለሁ ነበር ሰፊ ኃላፊነት የነበረኝ፤ ያን ጊዜ የሚያውቁኝ ሰወች ዛሬ ላይም ቢያገኙኝ ያው አንድ ዓይነት የሰብዕና አደረጃጀት እና አመራር እንዳለኝ ነው የሚያረጋግጡት። እዚህ ቤት በልጅነቴ የሚያውቁኝ ወዳጆቼ አሉ።
ተለወጠ የሚባለው ውበቴ ብቻ ሊሆን ይችላል። በእኔ በጥሪዬ ውስጥ ቤተሰቦቼ፤ የፖለቲካ ሥርዓት ያስተማሩኝ መምህሮቼ እና አለቆቼ፤ ወላጆቼ እና የጎንደር ከተማ ማህበረሰብ ኮትኩቶ ባሳደጉኝ የሥርዓት፤ የወግ እና የባህል ልክ እራሴን ከርክሜ እና ቀጥቼ "በይበቃኛል" በሐዋርያው ጳውሎስ ዶግማ ሥር የምተዳደር ባተሌ ነኝ። ሚዲያወቼ፤ መጸሐፍቶቼ፤ ጹሁፎቼ #እኔኑ ገላጮች ናቸው።
ለእስረኛ ወገኖቻችን የጤናቸው ሽፋን በመስጠት እረገድ አማራጭ ያለው ካለ፤ በአማራጩ ይጠቀም። ዕውነቱ እና ፋክቱ ግን መሬት ላይ ያለው ተጨባጭ ሁነት የሚያረጋጌጠው እኔ የመረጥኩት መስመር ነው። ለእስረኛ ወገኖቻችን ጥበቃ፤ ጥንቃቄ ሊረዳ የሚችለ የእኔ መንገድ ነው። የኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚር ሆነ የቤተሰብ መምሪያ ኢንስቲቲዩት #ማርበርግ በሽታን በሚመለከት ካቴና ላይ ላሉ ወገኖቻችን #ልዩ ጥንቃቄ፤ ልዩ አትኩሮት ይሰጡ ዘንድ አሁንም በትህትና እና በአክብሮት እጠይቃለሁ።
በዚህ ሴንሲቲብ ጊዜ የማድረግ ሙሉ አቅም ያለውን አካልን አቃሎ ማየት "……… ገሊቦ እራስ ተከናኒቦ ይሆናል። " ባለፈው ጊዜ አቶ ክርስቲያን ታደለ ታመው ሳለ ይታከሙ ዘንድ የጮኽነው ለባለሙሉ ስልጣን ባለቤት ነበር። ያን አሻም ፈንግጠው ብንል ፋታ አልባው የአንጀት ችግር ከቁጥጥር ውጪ ይሆን ነበር። "ማምሻም ዕድሜ ነው" ይላሉ ጎንደሬወች ባለቅኔወች።
መመኜት፤ መፈለግን በብስጭት፤ በእልህ ማድረግ ይቻል ይሆናል። ስኬቱ ግን ቁልቁለት ነው። አማራጭ አለኝ የሚል አካል በአማራጩ ይጓዝ፤ የእኔ መንገድ ግን ብዕሬን እና ብራናየን በትህትና እና በአክብሮት አሰልፌ የምኞቴን ካቴና ላይ ላሉ ወገኖቼ ልዩ ጥበቃ፤ ልዩ ደግሜ ደጋግሜ በአክብሮት እና በትሁት መንፈስ ልዩ ክትትል፤ ስለማርበርግ በሽታም የጥንቃቄ ትምህርትም እንዲሰጣቸው፤ ፓንፕሌትም ተዘጋጅቶም ይታደላቸው ዘንድ ካቴና ላይ ላሉ ወገኖቼ እንዲሰጣቸው አመለክታለሁኝ። በአንድ ክፍል ብዙ እስረኛ ከኖረም ሌሎች አማራጮች እንዲታይላቸውም በትህትና አሳስባለሁኝ።
ስንቅ ለሚያመላልሱት ሁሉ በጣም ነው እምሰጋው። ልጆች እስረኛ ወላጆቻቸውን ለማየት እስር ቤት ባይሄዱ እፈልጋለሁኝ። በሌላ በኩል አዲስ አበባን ጨምሮ የቅዝቃዜው መጠን ከዜሮ በታች የሚለውም በእጅጉ ያሳስበኛል። እስር ቤት እራሱ ቀዝቃዛም ስለሆነ።
ማንም ሰው #ስስትማ ሊሆን አይገባም። እያንዳንዱ ሰው የራሱ ህሊና አለው። የሌላውን ሰብዕ ህሊና ነፃነትን ነቅለህ በእኔን ተካ ሊሊል ግን ፈጽሞ መብት የለውም። ለዛውም ሥርጉትሻን??? እንዴት ተቀለደ??? በራስ አቅም የቆመ ማንነት #ቤቢ ሲተር ፈጽሞ አያስፈልገውም። የእኔ የሚለው #ቋሚ አሻራ ያለው ሰብዕና ፕሮፖጋንዲስት አያስፈልገውም። በእኔ ህይወት በአገሬ ፖለቲካ ብድር የሚያስኬድ አንዳችም ነገር የለም። ያለኝ በቂ ነውና።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ቅኖቹ ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
09/12/2025


አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ