#አደብ #ያጣ #ፍላጎት፤ #አደብ #ያጣ #ውድቀት #ያመጣል።

 #አደብ #ያጣ #ፍላጎት#አደብ #ያጣ #ውድቀት #ያመጣል

"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።

May be an image of one or more people and people smiling
#ምዕራፍ ፲፯

#ለምን?

1) ስኬት በአደብ ያጣ ፍላጎት ስለማይገኝ።
2) አደብ ያጣ ፍላጎት ቁንጥንጥ ነው።
3) አደብ ያጣ ፍላጎት ስርክራኪ ይበዛዋል።
4) አደብ ያጣ ፍላጎት ተናዳፊ ስለሆነ።
5) አደብ ያጣ ፍላጎት የውስጥ ሰላሙ የታወከ በመሆኑ።
6) የመነሻ ገፊ ፍላጎቱ የራሱ አቅም ሳይሆን የጥገኛ አቅም ተሰላቢ ስለሚሆን።
7) አደብ ያጣ ፍልጎት ጎርፍ ይበዛበታል።

 
ስምንት) አደብ ያጣ ፍላጎት በሦስት ወር የሰው ልጅ ጽንስ ልጅ ሆኖ እንደሚወለድ ነው የሚያስበው። ኢ ተፈጥሯዊ ነው። ሁሉም ነገር የራሱ ስበታዊ፤ ስክነታዊ ሂደት ይጠይቃል። በአገራችን ባህልም "የእነ ተሎ ተሎ ቤት ግድጌዳው ሰንበሌጥ።"
9) አደብ ያጣ ፍላጎት ውጥኑ ቀን ቢወጣለት እንኳን ዕድሉን ለማስቀጠል አደብ አይኖረውም። መነሻው ሶርሱ አደብ የለሽ ነውና።
10) አደብ ያጣ ፍላጎት አድራጊውም፤ ተደራጊውም ስክነት ከአጣ ሰብና ስለሚነሳ ያረገረገ ስለሚሆን።

አንድ ፍላጎት #ያረገረገ ከሆነ ደግሞ የተነሳለትን ፍላጎት አጽንቶ ለማስቀጠል አቅም ያንሰዋል። የትኛውም የአቅም ዓይነት #በጀት ነው። የመንፈስ ይሁን የልምድ፤ የልምድ ይሁን የክህሎት፤ የክህሎት ይሁን የመሰጠት፤ የመሰጠት ይሁን የመንፈስ፤ የመንፈስ ይሁን የመዋዕለ ንዋይ አቅም በጀት ነው። የሂሳብ ሥራ ይጠይቃል። ለዚህ ዕውቅና መስጠት፤ አቅምን ማሰባሰብ፤ አቅምን ማደራጀት፤ አቅምን መርቶ ለስኬት ለማብቃት አደብ ወሳኝ ጉዳይ ነው።

#ለምን ያረገርጋል አደብ የለሽ ፍላጎት?

#ተርገብጋቢ ስለሚሆን። ገፊው ኃይል ያልተረጋጋ ስሜት ሊሆን ስለሚችል፤ ተርገብጋቢ ፍላጎትን ይዞ የግል ህይወትን፤ ማህበራዊ ህይወትን፤ ከፍ ባለው ሁኔታ #ፖለቲካዊ #መሻትን አጽንቶ ለማሳካት ከመነሻው እርጋታ ካነሰው፤ ፍፃሜውም የተነሳበትን የአነሳስ አቅም መሠረት ስለሚያደርግ አደብ አልቦሽ + አደብ አልቦሽ= አደብ አልቦሽ ይሆናል ማለት ነው ትልሙ የአጤ ስኬት።

አደብ ያጣ #ችኩል ፍላጎት ቢቀናው እንኳን #የለት እንጂ ዘላቂ የመሆን አቅሙ፤ ይሁን ዕድሉ #የጫጫ ነው የሚሆነው። ይጨነግፋል። ቀድሞ ነገር አደብ ያጣ ፍላጎት ያለውን የራሱን አለኝ የሚለውን አቅም እንኳን አጥንቶ እና አደራጅቶ ስለማይጀምረው ክልፍልፍነት ስለሚያጠቃው፤ አለኝ ለሚለው ለራሱ የውስጥ ተቀማጭ አቅም እንኳን አቅም ለመሆን አይችልም። ጎንደሮች ቅኔውን "ልክን ማወቅ ከልክ ያደርሳል" የሚሉትም ለዚህ ነው።

አቅምን አውቆ በአቅም ልክ መፈለግን ለማሳካት ከመነሻው ተፈላጊው ንጥረ ነገር #አደብ ለአንድ ፍላጎት #የውሃ ልኩ ሊሆን ይገባል። ጥንስስ በጥቂት እርሾ ሊሆን ይችላል። የጠላ ጥንስስ በትንሽ ጌሾ እና ብቅል ሊሆን ይችላል። ጠላውን ጠላ ለማድረግ ግን ሂደት ይጠይቃል። የሰከነ ጥረትም። ያልበቀለ ገብስ የብቅልን ሚና አይጫወትም። እንኩሮው ካልበሰለም ሌላ ችግር ይፈጥራል። ጌሾው በዝቶ ብቅሉ ካነሰ፤ ወይንም ብቅሉ በዝቶ ጌሾው ካነሰም የጠላ ሂደቱ አይሳካም።

በጥዲፊያ አንድ ጥንስስ ጠላ ሁንልኝ ቢባል ጠላ ሳይሆን ቡቡኝ ወይንም የጤፍ ጠላ ይሆናል። በነገራችን ላይ ከጤፍ ጠላ ይሰራል። ግን አይሰነብትም። ወዲያው ነው ከጥቅም ውጪ ሆኖ ሆምጣጤ የሚሆነው። በጎንደሮች የአነጋገር ዘይቤ ብክን ብክን፤ ጥድፍድፍ፤ አቅል ማጣት ሰብዕና ያለው ሲገጥማቸው አቶ ሀን፤ ወይንም ወይዘሮ ለን የጤፍ ጠላ የሚል ቅጥያ እንደ ብራንድ ይሰጧቸዋል።

የሆነ ሆኖ አደብ ያጣ ፍላጎት ተጠንስሶ ስኬት አቀባበል ቢያደርግለት እንኳን ፍላጎትን አጽንቶ ህዝብ ጠቀም ለማድረግ፤ ዕድሉን ለማዝለቅ ግን ነገን፤ ተነገወዲያን፤ ከዛም ወዲያ ያሰበ ርጋታን አሻም ብሎ ስለማይነሳ #ይጨነግፋል። መጨንገፋ የሚከፋው ፍላጎት አለመሳካቱ ሳይሆን እራሱንም ሰብዕናውን ውሃ ልኩን ያሳጣዋል። ይሸበሽበዋል።

ሰክኖ በማየት ብቻ ሳይሆን በአትኩሮት ፍላጎትን መመርመር፤ ማደራጀት እና ማስተዳደር ይገባል። ከግል ህይወት ጀምሮ ያሉ ማናቸውም ንቅናቄወች በአንድም በሌላም ከትውልድ ጋር ስለሚያያዙ። ዛሬ ደግሞ ግሎባላይዜሽን ነው። አንድ ቦታ የተፈጠረ ክስተት ሌላውንም ይነካካል። ስለሆነም አዲሱ ትውልድ

1) የራሱን ፍላጎት አጥርቶ ማወቅ፤ ፍላጎቱን ማጣመር የሚችልበት መስመር ከእሱ በታች ባለ አቅም ሳይሆን፤ ሲሆን ላቅ ያለ፤ በስተቀር አቻው ጋር ሊሆን ይገባል እንጂ በተዝለፈለፈ አቅም ውስጥ ሆኜ ፍላጎቴን አሳካለሁ ብሎ መወጠን አይገባውም። የሚጣመርበትን የዛኛውን የፍላጎቱን ባዮግራፊ በቅጡ ማጥናት ይገባል። ሌላ ፍላጎት ባክልበት ከሌላ ሰብዕና የራሴን አቅም ያዳብራል ወይንስ ያከሽፈዋል??? ለዚህ መልስ ሊኖረው ይገባል።

2) በሌላ በኩል አዲሱ ትውልድ ፍላጎቱን አጥርቶ፤ አደብም መግቦ የእሱን የራሱን ፍላጎት በቅጡ ለመምራት እራሱን በአደብ #ማብቃት ይጠበቅበታል። ሰኞ ተጸነስኩ፤ ማክሰኞ ተወለድኩ፤ እሮብ ክርስትና ተነሳሁ ………ይህ ፋንታዚ አይጠቅምም። ጊዜ የራሱን አደብ ለሌላው የሚድረው የሚኩለው አቻውን አደብ ሲያገኝ ብቻ ይሆናል።

3) የትውልዱን አቅም የሚሹ ብዙ ክስተቶች አሉ። ስለሆነም እንወክላለን የሚሉ የፍላጎት #ፍሰትን በአስተውሎት አተኩሮ መፈተሽ ይገባዋል - ትውልዱ። ምክንያቱም አደብ ያጣ ፍላጎት ብቻውን ሳይሆን አካባቢውን ጨምሮ ንደቱን ስለሚያሸጋግረው። አብሮ ከመንኮት ይታደጋል አትኩሮት።

ከሁሉ የሚከፋው የግብታዊነት ውጥኖች ብዙውን ጊዜ ተስፋ ቆራጭነት ሊከሰት ይችላል። ተስፋ ቆራጭነት ደግሞ ለመኖር ሳንክ ነው። ኩምሽሽ ያደርጋል - ዝቅ ሲል። ከፍ ሲል የሥነ- ልቦና ቀውስ ያመጣል። ትውልዱ ባልጸኑ፤ በሂደትም በማይጸኑ፤ በራሳቸው አቅም፤ ክህሎት - ብቃት እና ተመክሮ ያልተነሱ የሌሎችን አቅም እና ችሎታ #ተሻሚ #አዳኝ ፍላጎቶችን ጥግ ማድረግ አይኖርበትም። ፈጽሞ።

ብዙ ጊዜ አደብ የነሳቸው ፍላጎቶች ጊዜ ሰጥቷቸው ቢቀናቸው ይሉኝታ ቢስ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህም የውስጥ መከፋትን ሊያመነጭ ይችላል። የውስጥ መከፋት ሌላ የሚያጢያጢስ ሁነቶችን ሊያስከትል ይችላል። ጉዳቱ ታምቆ "ከአፈርኩ አይመልሰኝ" ሊሆን ስለሚችል የብቻ ጠቃጠቆ መከራ ይሆናል። መደበቅ፤ መሸማቀቅ ብቻ ሳይሆን እራስን #መጥላትም ሊያመጣ ይችላል።

ስለሆነም ለአዲሱ ትውልድ ፍላጎት የሚበጀው፤ ለራሱ ፍላጎት አደብን መመገብ፤ ከሌላ ፍላጎት ጋር አቅሙን ማዳበር ካሰኘውም የዛኛውን ፍላጎት #ባዮግራፊውን በአግባቡ ጊዜ ሰጥቶ ማጥናት ይገባዋል። በተለይ በድንገተኛ ሱናሜ፤ ማዶ ላይ በተኮፈሱ የራስ ያልሆኑ ተንጠልጣይ የአቅም ሽሚያወች እና ጥድፊያወች ላይ ቤተኛ ከመሆን በፊት ማየት ብቻ በቂ አይደለም። ኦብጀክቱን አቅርቦ በአትኩሮት መመልከት፤ መመርመር ያስፈልጋል። በማየት እና በመመልከት ማህል የሰፋ ልዩነት አለ። የሆነ ሆኖ ብንን ብንን ከሚል ፍላጎት ጋር የራስን ስኩን ፍላጎት ማዋህድ ኪሳራን ፈቅዶ መቀበል ይሆናል።

በዚህ ውስጥ የዩክሬኑን ፕሬዚዳንት የተከበሩ ዘለንስኪ ለዓለም አዲስ ትውልድ ካሪክለም ቢሆን ምኞቴ ነው። ሁልጊዜ እጽፈዋለሁኝ፤ አውዲዮም ሠርቸበታለሁኝ፤ የዩክሬን ህዝብ ይህን ያህል ዋጋ የሚከፍልበት ሚስጢር ታምቆ የሚገኘው የፕሬዚዳንቱ አነሳስ እና የፍላጎት ሁነት ብዙ፤ በጣም ብዙ ያስተምራል። የሃማስም የመስከረም 26 አክሽን በራሱ ለጋዛ ህዝብ ያስገኘውን ጥቅም እና ጉዳትንም መርምሩት።

በጣም ከባዱ የህይወትም፤ የአገር ፈተና ሁለት አደብ የነሳቸው ፍላጎቶች ከተጣመሩ ተያይዞ ገደል ነው የሚሆነው። ትምህርት ቤት ዩንቨርስቲ ብቻ አይደለም። ከምናየው፤ ከምንሰማው ኩነት ወደ ራሳችን አቅርበን ምርምር ብናደርግበት ዓለማችን ዩንቨርስቲ ናት።

በማንኛውም ሁኔታ ውድቀት እና ስኬት፤ ተስፋ እና ተስፋ ቆራጭነት፤ ሥልጣኔ እና ሥልጣኔን የሚቃረን የጦርነት የሥልጣኔ ሂደትን አጥኑት። ብቃት፤ አቅም፤ ችሎታ፤ ክህሎት ሁሉም አደብ ይጠይቃል። ሁሉም የተረጋጋ #አቅል ይጠይቃል።

ለምሳሌ ምግብ ተጣድፋችሁ ተመገቡ፤ መጠጥንም አጣድፋችሁ ጠጡት እና መዝኑት። በሌላ በኩል ስትመገቡም በአደብ፤ ስትጠጡም በአደብ ሲሆን ጤናም ሰላምም በመዳፍ ይሆናል። ይህን የትኛው የተረጋጋ ሰላም ለኦርጋናችሁ እንደሚመግብ፤ የትኛው ደግሞ የውስጥ ኦርጋናችሁ በጥባጭ፤ ረባሽ፤ አዋኪ እንደሆነ።

ሌላም ምሳሌ ብሰጣችሁ እንጀራ ሊጡን አፍሳችሁ ሳይረጋ፤ ዓይኑን ጨርሶ ከፍቶ ደርሻለሁ ሳይል፤ ሲደርስ ጠርዞቹ በራሳቸው ጊዜ ምልክት ይሰጣሉ። ይህ ሳይሆን ብታወጡት አይደለም እንጀራ በሊጥነቱ እንኳን አይቀጥልም። የነበረውን ማንነት ያጣል። ስለዚህ ነባሩ የሊጥነት ማንነት አይቀበለውም። አዲሱም ማንነት ሊጣዊ እንጀራነትም አይቀበለውም። " ሁለት ያጣ ጎመን "

ስክነት፤ እርጋታ፤ አደብ መታበይን፤ ከአቅም በላይ የተንጠራራ ፍላጎትን በልኩ መጥኖ ከርክሞ ለስኬት እንዲበቃ ያደርጋል። ከአደብ ጋር ሥርዓት ወሳኝ ነገር ነው። አንድ ሰው የህይወቱ ፍኖተ ካርታ ያስፈልገዋል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ። አንድ ሰው በነደፈው የህይወት ፍኖተ ካርታ ሊመራ ያልቻለ ፍላጎት ስኬቱ #ጢስ ይሆናል። እንኳንስ ሌላ የሚያረገርግ ፍላጎት አክሎበት።

ብልህነት፤ ጥበበኝነት፤ ልቅና፤ ልዕልና ዊዝደም ከሚክለፈለፍ መንፈስ ጋር ቤተኛ አይሆኑም። እመኑኝ ብየ አላስቸግራችሁም። ህይወቱን ሞክሩት ውጤቱን ለኩት፤ ያልኩት ከገጠማችሁ ኑሩበት። ደልዳለን የሰከነ ማንነት አደራ ያወጣል። ትውልድን በከበረ ማንነት የመቅረጽ አቅሙ ሙሉ እና እርግጥም ይሆናል።

ውዶቹ፤ ክብሮቹ ውቦቹ እንደምን አደራችሁልኝ። እኔ አምላኬ ክብሩ ይስፋ ደህና ነኝ።

ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።

ኑሩልኝ። አሜን።

እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።

ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
11/12/2025

ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ዕውነት ቦታውን ለቆ አያውቅም።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።