ህወሃት እና የአዝመራ #ዘረፋው በወርሃ የካቲት ትውፊቱ ነው። ህዋህታዊነትስ - ምን #ጠቀመ፤ ምን አከሰረ?

 

ህወሃት እና የአዝመራ #ዘረፋው በወርሃ የካቲት ትውፊቱ ነው። ህዋህታዊነትስ - ምን #ጠቀመ፤ ምን አከሰረ?
 
"ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ዘለዓለም ሲያለቅስ ይኖራል።" መጥኒ ላንች እቴጌ ጎንደር። ልብ በአቅል ግዢ ከአጤወችሽ። 
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 
#ምዕራፍ ፲፰። ዘለግ ያለን ትዕግሥት እና ማስተዋል የናፈቀው የወግ ገበታ ነው ለማህበረ ቅንነት። 
 
#መቅድመ ፍሬ ነገር።
 
ጤና ይስጥልኝ የአገሬ ልጆች እንዴት አደራችሁልኝ? እኔ አምላኬ ክብሩ ይስፋ ደህና ነኝ። ከእኛ ቅዝቃዜውም ለክፋ አይሰጥም። ካናዳ እና አገረ አሜሪካ ያሉ ወገኖቻችን ከቶ እንደምን አድረው ይሆን?
 
በውነቱ ህወሃትን በሚመለከት ምንም ለማለት ፈጽሞ አልፈልግም ነበር። ከምል "ሙያ በልብን" ብከውን የተሻለ ቀና መንገድም ነው ብዬ አምናለሁኝ። ለዛውም እኔ የልቤ ደርሶ፤ መሻቴ ተሳክቶ #የጃርት ጉባኤው የህወሃት ተንጠራርቶ፤ ተወራኜቶ #አራጦ የመግዛት ዘመኑ #እርሾ አልባው ክትመቱን ከማዬት በላይ መታደል ስለለ ግራ ቀኙን በትዝብት፤ በዝምታ ማየቱ ምርጫያ ነው።
 
ነገር ግን ዘመኑን ሁሉ በድንጋጤ፤ በጭንቀት እና በስጋት እንዲኖር የተፈቀደበት፤ የተፈረደበትም ሁነትን አስመልክቶ ለአዲሱ ትውልድ ትንሽ መረጃ ብሰጠው አይከፋም በሚል ነው አመጣጤ። ህወሃትን መንገድ መሪነት የተቃጠለ፤ ኤክስፓየርድ ያደረገ የአስተሳሰብ ድህነት ነው። የህወሃት ጉዞ በየትኛውም ሁነት ሊገታ ይገባል።
 
" #ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል፤ ዘለዓለም ሲያለቅስ ይውላል።"
 
ወርኃ የካቲት የስሜን ጎንደር ገራገር ንጹህ ገበሬ ዓመቱን ሙሉ የለፋበት አእዝርቶቹን ሳይዘራ፤ ሳያርም፤ ሳያጭድ፤ ሳይወቃ የኖረ #ሰነፍ ድርጅት ህወሃት ይዘርፈዋል። በቁሙ አዝመራውን ይሰርቀዋል። ህውሃት የወጣለት ሌባ ነውና። ይህ የመኖሩ መረብ ነው። ካለ ጎንደር የተፈጥሮ ሃብት ህውሃት ነፍሱ ከሥጋው የተለየች የቁም እንቅልፍ ተቋም ነው። በሁሉ ነገር ይጎመጃል፤ ይሳሳል፤ ይቀናል፤ ይመቀኛል ልክ እንደ ሰው በጎንደር። የ2018 ዓም ጥር እና ጎንደር ተውባ ሲይም፤ ደሙ መንተክተኩ የተለመደ ነው። ሁሉም ነገር ወደ ጎንደር ህወሃትን ያላሳበደ ማነን - ያሳብድ??? ህወሃትን ወደ ግብታዊ እርምጃ ያልወሰደ ማንን ይውሰድ? 
 
ለዚህም እኮ ነው አፍቅሮተ ህወሃታውያን የጎንደር ጌጥማ ትውፊት ላይ ቃጠሏቸው ያገረሸባቸው። ለጎንደር ጥምቀት ባህሉ እና የማተቡ ጉዳይ ነው። ባባህላዊነቱ ሁሉም ጎንደሬወች ይጋሩታል፤ ሁሉም የሃይማኖት አማንያን ይመሰጠሩበታል። በማተባዊ ጉዳይ ደግሞ ጎንደር የየትኛውም ባዕት ዓይነት ከሊቅ እስከ ደቂቅ ውስጡን የሚሰጥበት ክስተት ነው። ባለፋት ሦስት ዓመታት የጥምቀት ሁነት ሲደበዝዝ ለህወሃት እና ለአምላኪወቹ የሠርግ ጊዜያቸው ነው። በሁሉም ትብብር በጫካውም በ፬ኪሎውም መንፈሳዊ ስምምነት የጎንደር አቅል ወደ ቦታው ተመልሶ ዔጹብ ድንቅ ሲባል መክለፍለፍ ሆነ።
 
ጥምቀት ለእኛ መሞሸሪያችን ነው። በልጅነት የአንድ ቤተሰብ ልጆች ተመሳሳይ ልብስ ይገዛልናል። እንሶስላ ወይንም ጉርሽጥ እንሞቃለን። እንሶስላችን የምንሞቀው ማታ ነው። አንተኛም ሌሊቱን ሁሉ እናየዋለን። ጠቆረ አልጠቆረ ብለን። ከሰሞናቱ ሰርዴታ፤ አለባሱ፤ ግጫ፤ ታሬ፤ ታሬ እና ቁንጮ፤ አፍሮ፤ ጎራ ወዘተ የሚባሉ የጸጉር ስታይሎች ሁሉ ይተገበራሉ። #ሙሽሮች ነን። ነጋ አልነጋ አልጋው ላይ መጋደማችን ካልሆነ በስተቀር ከእንቅልፍ ጋር አንገናኝም። ወጣትነታች በሐሴሤት ፍንድቅድቅ በነፃነት የሚልበት ዕለታችን ነው። ጎንደር ላይ አራቱም የጥር ቅዳሜ እና እሁድ ቁጥር ስፍር የሌለው የሠርግ ጊዜያችን ነው። ጎንደሬ በግንቦት ጋብቻ አይፈጽምም። 
 
ከዛ እነ ደርባቤ "አሼበል ገዳዩ" ያቀነቅናሉ ወጣቱ፤ ጎልማሳው ይጨፍራል። የጎንደሮች ማርያም፤ የደፈጫ ኪዳነምህረት፤ የፈንጠር፤ የቁስቋም፤ የወለቃ አካባቢ ገበሬወች ቁምጣቸውን ለብሰው፤ ጎፈሪያቸውን ከምክመው፤ ከራሳቸው አጭር ሬክታንግል ሻሽ አድርገው በየአቅጣጫው ሆ! እያሉ ሲገቡ ፒያሳ ትቀውጣለች፤ የኮለኮሏትን ያህል ፍንክንክ፤ ፍልቅልቅ ትላለች። ታቦታቱም በዝማሬ በከበሮ በዛ በሰጠ መንገድ እንደ ሃይማኖታችን ሥርዓት ወደ ማደሪያቸው ይተማሉ። በተለይ ሁሉም ታቦታት መስቀል አደባባይ ሲገናኙ ደወሉ፤ ድባቡ ፃድቅ ነው። ሁሉም አይቀርም። ባህላዊውም ሃይማኖታዊውም።
 
ይህ ለእኛ ለጎንደሮች አንጡራ ባህላችን ነው። ዕንቁ ትውፊታችን ነው። አልማዛዊ አደራች ነው። ይህ የሚርገበግባችው ካሉ መንገዱን ጨርቅ ያድርግላቸው። የአንዳንዶቹ ድፍረት ይገርመኛል። እራሱን ያላዳነ በቅናት ነጠዝ የሚወራጭ መንፈስ " ጎንደር ሃኪም ያስፈልጋታል" ብሎ ቅራሪ እርእስ ሰጥቶ አና ብሎ ዓይኑን በጥሬጨው አሽቶ ያፈጣል። በምን አቅሙ?
 
ጎንደርን መተርጎም፤ ማመሳጠር ቀርቶ የተፈጠርንባት፤ የቋረቅንባት፤ የተማርንባት፤ ለቁምነገር በቅተን የሠራንባት፤ የመረንባትም በዓታችነን ለመተርጎም፤ ለማመሳጠር አቅሙ የለንሜ። ጎንደር ከጎፈረው ጋር የምታጎፍር፤ ጎንደር ከአጎረፈው ጋር ጎርፍ የሚያሰኛት የጎሸ ዕሳቤን ተቀማጭ ሁን ብላ ፈቃድ የምትሰጥ በዓት አይደለችም። ሁሉ አላት። ሁሉንም መሆን ትችላለች። ሚስጢርነቷ ርቁቅ ነው። የመመስጠሯ ሚስጢር መሠረቱ ኢትዮጵያዊነትን ምራኝ፤ ግዛኝ፤ እንዳሻኝ አድርገኝ ብላ በድንግልና መጽናቷ ተክሊሏ ሆኗል። 
 
ቁጥር ስፍር የሌላቸው የቅድስት ተዋህዶ ልጆች ወደ ሌላ ሃይማኖት እየተመሙ ነው። ከቻላችሁ፤ መምህር ነን ካሊችሁ ይህንን አድኑ፤ አሳዛኙ ክስተት ይህ እንጂ ወጣቶች ወጣትነታችሁን ኮርኩም፤ ፍለሃችሁን ቀፍድዱ የተገባ አይደለም። ወጣቶች በሥርዓት ዕድሜያቸው የሚፈቅደውን የፍሰሃ ሰናይ ይመገቡ ዘንድ የጉሮሮ አጥንት አትሁኑ። ዘመናቸው ነው። ገዳም አይደለም ጎንደር ከተማ። ለ45 ቀናት ሥጋ ቤቶች ሁሉ ተዘግተው ያን መሰል ተደሟዊ ሱባኤ የማድረግ ክስተታዊ ሁነት በታሪካችን የታዬው ጎንደር ላይ ነው። ሥርጉተ ሥላሴ ቁጥር ፪ ዩቱብ ቻናል ላይ ይገኛል። ይህ ድንቅነት አዲስ አበባ ላይ "የጃንደረባው ትውልድ" በሚል የተጀመረው ከዛ ትውፊት ነው።
 
ጎንደር አደባባይ እየሱስ ላይ ከልደታ እስከ አጋይስት ዓለሙ ሥላሴ ድረስ ምህላ፤ ሱባኤ ቋሚ ነው። ኢትዮጵያ ጠና ያለ ፈተና ሲገጥማት ሁለት ፯ ይሆናል የሱባኤው ቆይታ። አብረንታንት ገዳም እኮ ከሰኔ እስከ ብርኃነ ልደቱ ፆም ነው። ሱባኤ ነው። ለእኛ ለጎንደሬወች ስለማተባችን ፕሮፖጋንዲስት አያስፈልገንም። በዚህ አጋጣሚ እቴጌ ዳጊ "ጉድ በል ጎንደር" በሚል ያስተላለፈችው ቅዱስ መልዕክት ለተሰወረ ህሊና በሩን ይከፍታል እና አዳምጡት ትህትናዊ ዕይታዬ ነው። እቴጌ ዳግምሻ ኑሪልኝ። አሜን።
 
ዋናው ፍሬ ነገር እርማቸውን ጎንደር የተገኙ ፖለቲከኞች እንግዶቿን የዛሬ አራት ዓመት አስመልሰዋል። ያም አልበቃም ብሎ ልደትን ጥቁር እንድትለብስ፤ ባዕቷ ጭንቅ እንድትጎናጸፍ አድርገው የህወሃትን ጎርባጣ ፍላጎት አሳክተዋል። ወይብላ ማርያምም ልጆቷን በማዕዷ እንድታጣ የተደረገበት ሚስጢሩ ይህ ነው። ዘንድሮ ደግሞ ዕውነተኛ ፋኖወችም ልብ ገዝተው፤ በብልጽግና ውስጥ ያሉ ሳቦታጅ አምራቾችም ቀን አጋልጧቸው፤ መንግሥትም በቂ ትኩረት ሰጥቶ ያን የመሰለ የከበረ፤ ግርማ ሞገስ ያልተለየው ትውፊታዊው ሂደት በመከወኑ ያረሩ፤ ኩምትርትር፤ ጭምትርትር ያሉ ሰብዕናወች ቅናታቸው የእንክርዳድ ያህል ነበር። ዕውነት ግን አሸንፏል።
 
#አንጡራ ባላንጣነት።
 
ለህወሃት #ከጎንደር በላይ እንደ አንጡራ ጠላት የሚዬው ህዝብ የለም። ህወሃት የማንነት ቀውስ ያለበት ድርጅት ነውና። የማንነት ቀውስ ያለበት ሰብ፤ ተቋም ይሁን የፖለቲካ ድርጅት #ድፍድፋ በቀውስ እና በሽብር የተዘለለ ነው። ሊድን የማይችለው ህወሃትም ለዚህ ነው። ትግራይ ዘመኗን ሁሉ በዚህ ልቡን ባልሰጣት፤ እራሱን ባላስከበራት፤ ባጣ ቆየኝ ባደረጋት ድርጅት መታመሷም ፈርኃ እግዚአብሄር፤ ፈርሃ አላህ እና በልባም ልጆቿ የመመራት ዕድሏ ስለራቀ ነው። 
 
ህወሃት ፍጥረቱ ዘረፋ ላይ የተመሠረተ ነው። ቅጥፈቱም ዓይን ያወጣ። ክህደቱም መለያ ማልያው ነው። ዕብለቱ እና #ጥምዝምዝነቱም የሦስት ጉልቻ የመሠረቱ ናቸው። ሴራ እና ተንኮሉ ህሊናው የተዋቀረበት ማገሩ ነው። ቀውስ እና ጭክኔው ተፈጥሮው የተቀመመበት ንጥረ ነገሩ ነው። ጃርታዊው ህወሃት ቀውስ ያቅዳል፤ ቀውስ ያደራጃል፤ ቀውስ ይመራል በዚህ ትርፍ ይዝቃል። እያምታታ ነው እኮ የኖረው። የሰለጠነውን ዓለም ሳይቀር አሳስቷል። 
 
ይህን የማይድን ድውይ #ጃርታዊ ፍጥረት አዝዬ፤ ወይ አሽኮኮ አድርጌ ወይንም #ለስኜ እታደጋለሁ ብሎ ማሰቡ፤ ይድናል ብሎ አቅም ማዋጣቱ የተመድን የታህሳስ 10/1948 ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ ድንጋጌ መዳጥ ይሆናል። ጸረ ጎንደርነትም ነው ቁልጭ ያለው ዕውነት ገፆቹ ሲገላለጡ። የአማራ ህዝብ ያለውን ሁለት የደንበር አንጡራ መብትንም ፈቅዶ መግፈፍ ነው። ይህንን በአደብ ማያት፤ መመርመር፤ በአትኩሮት ፈልፍሎ፤ አበጥሮ እና አንተርትሮ ማያት ይገባል።
 
#ሰቲት ከወደብ በላይ ነው። በሳል ፖለቲከኛ ከውስጡ አትኩሮቱን ካልነፈገው። ሌላ ሰቲትን በሚመለከት፤ የወገራ እና የስሜን አውራጃወችን የወሰን ጉዳይ የመኖራችን መሪ አመክንዮ ነው ለእኔ ለጎንደሪዋ። በሚስጢሩ ውስጥ ዊዝደምን መሰነቅ መመረቅ ነውና። በደራሽ ሁነት ዘላቂ ክብረ ልዕልናችን ሊሸጥ፤ ሊለወጥ አይገባም። ክብርን ደፍቶ ወይንም ሸቅጦ የትውልድን ተስፋ ማበራከት ፈጽሞ አይቻልም። ወልቃይት ጠገዴ የአባቶቻችን፤ የእናቶቻችን አጽም የአደራ ማህለቃችን ነው። 
 
ህሊና ያለው፤ ሰው ሆኖ የተፈጠረ፤ የሚያስብ፤ ርህርህና ያለው፤ ስለ ትውልድ የሚጨነቅ ምራቁን የዋጠ ሰብዕና ከዚህ ጃርታዊ ተፈጥሮ ፍላጎት እና ምኞት ጋራ አንዳችም መስተጋብራዊ ሁነት ሊፈጥር አይችልም። ህወሃት አይድንም። ህወሃት አይጠገንም። ህወሃት አይሻሻልም። እንደ ገና ሞቶ ቢፈጠርም ህወሃት #እፋኝት ነው። ሲረገዝ አባቱን ሲወለድ እናቱን እየገደለ የኖረ ድርጅት ነው።
 
……… ምክንያት አፈጣጠሩ ከጨለማው ጋር ውህድ ሆኖ ስለተፈጠረ። ህወሃት በነፍሱ #ሳጥናኤል ነው። የሰርክ የህይወቱ እንዝርት የሚሾረው #በማንአንሸነት፤ በማንአህሎኝነት፤ በማምታታት፤ በቅጥፈት፤ በጸረ ሰውነት፤ በማንነት ቀውስ እና እረብሻ፤ በበቀል እና በቂም፤ በህውከት እና በብጥብጥ ተቦክቶ የተጋገረ ስለሆነ።
 
…… #ነገር ግን…… 
 
በጫናም ቢሆን ፈቅዶ እራሱንም እጩ አድርጎ አቅርቦ ተወዳድሮ #ሁለት ድምጽ አግኝቶ መጋቢት 18/2010 ሲሸነፍ፤ እሺ ብሎ መንበሩን ሲያስረክብ፤ በውነት ከእኔ በላይ የመሰከረለት፤ ተውት አትጨቅጭቁት ያለ፤ ቲካቲካ የሚሉትን ሁሉ እከሌ ተከሌ ሳልል የሞገተለት፤ ለረጅም ጊዜ በዝምታ ታግሶ የጠበቀው የለም። ጦርነቱን ደጋፊ አልነበርኩም። ጉዳቱን ከመዘገብ ውጪ ከውቂ - ደብልቂው፤ ከፌስታ ርችት ትኮሳው ውስጥ አልነበርኩም። ግን ህወሃት ፈጽሞ ሊድን የማይችል "ከንቱ፤ የከንቱ ከንቱ ሁሉም ነገር ከንቱ" እንደሚለው መጸሐፋ ሲፈጠር ሞቶ የተፈጠረ ሙትቻ ሆኖ ነው የሚኖረውም ስለሆነ ዘመኑሁሉ በመታመስ በማምታት ቁምስቅሉን ያያል። በእሱ ምክንያት ብዙ በጣም ብዙ ዋጋ ኢትዮጵያም ከፍላለች። 
 
እቴጌ ጎንደር በእጅጉ አዝንልሻለሁኝ። ይህ ጃርታዊ ድርጅት ከተፈጠረባት ቅጽበት ጀምሮ አሳርሽን እንሆ ታያለሽ። ጥቃትሽን ያወጡልሽ ልጆችሽ ድካምም ያሰተዋለው አንድስም እንኳን የለም። "ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ዘላለም ሲያለቅስ ይኖራል" በዕውን የተፈጸመብሽ በዓት። የሚገርመው፤ የሚደንቀው የሚያንቀጠቅጠው እና የሚሰቀጥጠው የእትብትሽ ክፋይ የህወሃት መቃብራዊ ኑሮን ናፋቂነት፤ የናፈቃቸው ልጆች መኖራቸውን ሳደምጥ ነው። #እምምምም! ብሎ ያስምጣል። የጓጎለ ሰብዕና፤ ጥሪውን ያስተጓጎለ ጎርበጥባጣ ህሊናም ሊጸለይለት ይገባል። ልብ ይስጣቸው - ለልጆችሽ። አሜን። 
 
በዘመናት ሁሉ ተፈጥሮ ፊት ስታዞር ተጋሩ ወደ ሌላኛው ቤታቸው ጎራ ሲሉ እቅፍ ድግፍ አድርጋ ጎንደር ህይወት፤ #ትንፋሽ ስትለግሳቸው፤ አክብራ አድምቃ ሳቅ ስትመግባቸው ነው የኖረችው። ሁሉም ነገር የሚጫነው ከቤት ወደ ቤት ነበር። ያ ሲከወን በፍቅር በተድላም ነበር። ሰቲትም ከኤርትራም፤ ከትግራይም ለሚመጡ ወገኖቿ ጎንደር አክብራ ተቀብላ በአቅማቸው፤ በችሎታቸው ልክ መኖርን የምትሰጥ ፍጹም ትሁት በዕት ናት ጎንደሪና። እጇ አመድ አፋሽ ሆነ እንጂ።
 
በቤተክህነትም በኩል ያሳደጉን፤ የቤተሰቦቻችን የንሰኃ አባቶች ተጋሩወች ናቸው። ትናንትም - ዛሬም። እኔ ፊደል ያስቆጠሩኝ የቅኔ መምህር አባ በጽሃ፤ ያሳደጉኝ አባ ኃይለማርያም፤ አባ ጌራ፤ አባ አስረስን በመፃህፍቶቼ ውስጥ ሁሉ አካትቻቸዋለሁኝ። ለአባ ጌራ እና ለአባ ኃይለማርያም ምግብ ሰርክ ተዘጋጅቶ የሚላከው ከታላላቆቹ ከቤተሰቦቼ ስለነበረ፤ እነሱን ለማግኜትም ሽሚያ ነበር። አባ ኃይለማርያም የአራዳ ጊዮርጊስ አለቃ ሆነው ከወንድሜ ጋር ልጠይቃቸው ስሄድ የፈካ ገፃቸው ስንቄ ነው። እንዲህ ዓይነቱን ውስጣዊ ትስስር ነው ሳንክ ሆኖ ጃርታዊው ህወሃት ሰላሙን እየዘረፈው የሚገኜው። በጋብቻም በየቤተሰባችን ውህድ ማንነት አለ። 
 
#ወርሃ የካቲት የህወሃት የዘረፋ ቤተኝነት።
 
ይህን መሰል ጤናአዳም ህብራዊነት ህወሃት ከተፈጠረ በኋላ ግን አረም አበቀለበት። የህወሃት ምሽጉ በቀል፤ ትጋቱ ምቀኝነት፤ ጉዞው መስፋፋት እና ጥቅለላ ሆነ። በዘመነ ህወሃት ጎንደር መኖሯ ቀራንዮ ነበር። በደርግ ዘመን ደግሞ ተማሪ እያለሁም፤ ሥራ ላይ ሆኜም ህወሃት የየካቲት 11 ዓመታዊ በዓሉን ለማክበር፤ ትንፋሹንም ለማስቀጠል ከየካቲት ዋዜማ ጀምሮ ወደ ስሜን ጎንደር ይተማል። ለመስረቅ። መስረቅ ጀብዱ ነው ለህወሃት።
 
የንጸሁን ገበሬ ድካም ማሳ ላይ ያስቀረዋል። ልቅም አድርጎ ይዘርፋል። ይህን የስሜን እና የወገራ አውራጃ ህዝብ የሚያውቀው ዕውነት ነው። ዘረፋ ብቻ አይደለም ትምህርት ቤት - ያፈርሳል፤ ድልድይ - ይሰብራል፤ መዳህኒቱን ደፍቶ መዳህኒት መያዣውን #ቆርቆሮ ይዞ ይሄዳል። የቢሮ ቁሶችን ስብርብር ያደርጋል። ይህን በጦርነቱ ጊዜም የአሁኑ ትውልድ ደርሶበት አይቶታል።
 
ሰሞኑን በጠለምት ያደረገው የጦርነት ዘመቻ ያው የገበሬውን ምርት በቁሙ ለመዝረፍ ነው። አገር ለመሆን ያሰበ ቲም አዝዕርት ዘረፋ ለዛውም የንጹሁ ገበሬን ድካም ተስፋ መዝረፍ አረመኔነት ነው። ይህ አረመኔ ቡድን ዕድሜውን ሙሉ በዘረፋ፤ በወረራ፤ በውሸት እና በቀውስ ተጀብኖ የቀጠናው አባል ለመሆን የሚያስበውን ትልሙን ለማሳካት አማራነት ከጎንደር ባሻገር ባሉ የጎንደር የራሷ ልጆች፤ እራሳቸውን በባዕታቸው ለማሰደድ በፈቀዱ ያለው ትልም ይዘገንናል።
 
የሚገርመኝ የኢትዮጵያን ክብር ስትመኝ ከትግራይ ሌላ፤ ከስሜን ጎንደር ሌላ ተብሎ የፖለቲካ ቅመር እራሱ ከጥንስሱ ሃሞታዊ ዘመንን ናፋቂ ነው። ሙሉ አገርን ከእነ ክብሯ፤ ከእነ ማዕረጓ አለማሰቡ " የሰው ልብ መንገድ ያዘጋጃል፤ አካሄዱን ግን እግዚአብሄር ያቃናላታል" ዕውን እንዳይሆን መግታት ነው። ትግራይ ሆይ! ትገነጠይ ዘንድ የመውጫ መግቢያ ደንበር ይኖርሽ ዘንድ፤ የነጭ ወርቀ ዘቦ ባድማን መርቀንልሻል፤ ብቻ ፬ ኪሎን አጋፍሪን ተብሎ በሚታሰብበት ፕሮጀክት ጎንደሬ ሆኖ መሳተፍ መራራ እርግማን ነው። #ጨለማነትም
ለኢትዮጵያ ቀለማም ሁነት ትግራይም፤ ስሜን ጎንደርም ያስፈልጋሉ።
 
 እነኝህን ሁለት በዓቶች እንዳሻችሁ ብሎ ኢትዮጵያን ማሰብ ቁልቁለት ነው። ህወሃት ሱዳን ጎንደርን ቢወር፤ ቢያደቅ ምኞቱ ነው። የህወሃት ፋክክር ከጎንደር ጋር ነው። ህወሃት ሲፈጠር በቃኝን አያውቅም። ዕድሉን ካገኜ መተማ፤ ቤንሻንግል ጉምዝ፤ ጋንቤላ፤ ሙሉ ጎንደር አይቀርለትም። ህወሃት ካልመከነ ኢትዮጵያ ሰላም ውላ አታድርም። ይህን ሰላሟን ለማስጠበቅ የማይዋልል፤ ቁርጠኛ ውሳኔ ቆፍጣና ፖለቲካዊ እርምጃ ያስፈልጋል። በቅድስ ተዋህዶ ለ፴፪ ዓመታት እጬጌው ትግራይ ናት።ህወሃት ይህ አላረካውም፤ አዲስ ቅዱስ ሲኖዶስ ፈጠረ። እርካታ ቢስ፤ ሰላመቢስ ድርጅት ነው ህወሃት። 
 
ህወሃት ሲኦል ነው። ሲኦልነቱ ለጎንደር ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለፓን አፍሪካም ነው። በሳል፤ የተጠና፤ ፋክት ዘለቅ መረጃወችን አቀናብሮ በዓለም፤ በአህጉሩ መድረክ ዘነዘናውን ማስቀረት ይቻል ነበር። ግን የኢትዮጵያ ፖለቲካ የውስጥ ኦርጋን የቅደምተከተል ችግር ብቻ ሳይሆን ግሽፈትም አለበት። ለዚህም ነው ሰርክ ኢትዮጵያ ሃዘንተኛ ትሆን ዘንድ የተፈረደባት።
 
አንድ መንግሥት ከብሄራዊነት ሉዓላዊነት ይልቅ የኮንስትራክሽን ስኬት ፌስታው ከሆነ እንዲህ ባለ ሁኔታ መደፈሩ ግድ ይሆናል። በዛለ አንበሳ፤ በሰሜን እና በደቡብ ሱዳን ያሉ የራሳችን ቀየወች ተወረዋል፤ ዜጎቻችንም ታግተዋል፤ ደንበሩ ተከፍቶ የብዙ ወንጀሎች መንሸራሸሪያ ሆኗል። ለዚህም ይመስለኛል በሰሞኑ ገለፃቸው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ "ፈሪ" ሲሉ ትርፍ የተናገሩት። አይቸባቸው አላውቅም ነበር።
ይህ ለአንድ አገር የጸጥታ፤ የደህንነት፤ የፖለቲካ ልዑአላዊነት አደጋ ነው። አደጋን አትኩሮት ሰጥቶ በተጠና፤ ምራቁን በዋጠ ስኩን ፖለቲካ እራስን ማስከበር ይቻል ነበር። ቸለልተኝነት፤ ንቀት፤ አቃሎ ማዬት፤ የራሱ ጉዳይ ባይነት እንሆ ሙሉ ፰ ዓመት መኖር በኢትዮጵያ በብዙ የመከራ አውታሮች ተሰቅዞ እንዲያቃስት ተፈርዶበታል።
 
 
ደቡብ ደቡብ ነው። ደቡብ የኢትዮጵያ አካል እንጂ እራሱን ችሎ ኢትዮጵያ ሊሆን አይችልም። ከካቢኔው 50+ ደቡብ ነው። እነሱ ደግሞ የጨመቱ ስለሆኑ ማን ይምጣ ማን? ማን ይግዛ ማን? ዕድል ሰጥ ዘመናቸውን እያጣጣሙ መኖር ልማዳቸው ነው። ስለሆነም በማዕከላዊው የፖለቲካ አቅም እና አቋም ላይ ኮስተር ባሉ ብሄራዊ ጉዳዮች ላይ ጽኑ አቋም አመንጭቶ መሞገት የማይታሰብ ነው።
 
ለዚህም ነው በጎደሎ - ካቢኔ፤ በጎደሎ - ፓርላማ፤ በጎደሎ - የፌድሬሽን ምክር ቤት ግንጥል ጌጥ የሆነ አመራር እያዬን የምንገኜው።
ህወሃትን በሚመለከት እንዲያገግም፤ እንዲያገረሽ፤ እንዲበጠብጥ፤ እንዲያውክ የፈቀደለት ማዕከላዊ መንግሥት ነው። ምክንያቱም እኔን ካልነቀነቀኝ ምን ግዴ ዓይነት ነው። ተቆርቋሪነት፤ ጥቃትን አሻም ማለት እንዳያመነጭ ብልጽግና በህወሃት ውራጅ መንፈስ ላይ ነው ጥገኛ ሆን መንግሥቱን እያዋቀረ እዬመራም የሚገኜው። ደህንነቱን፤ ጸጥታውን ለማን ነው ብልጽግና የሸለመው? ሁለመናቸው ህውሃታዊ በሆኑ ሰብዕናወች ላይ ነው። 
 
አይሆኑ ሆኖ የወደቀ፤ ገዥ አጥቶ የከሰረን ድርጅት መንፈስ መሠረቱን ህገ - መንግሥታዊ መረቡን በጣጥሶ አዲስ መፍጠር ሲቻል በለኝ አለ ብልጽግና፤ ይኽው የአማራ ህዝብ በአንድም በሌላም፤ በግልጽም በስውርም እምሽክ ድቅቅ አለለት። ከህወሃት የተረፋ በዓቶች የኢትዮጵያን ሠራዊት በመዳፈር፤ ህዝቡ ቁምስቅሉን እንዲይ የራሱ የአማራ ልጆች ለህወሃት ፍላጎት አስፈፃሚ ሆነው ተገኙ።
 
ታስታውሱ ከሆነ የደቡብ አፍሪካው ስምምነት ሲበሰር የመጀመሪያዋ ዘገባ አቅራቢ እኔ ነበርኩኝ። የዳኑ ከተሞችን ሁሉ ዘርዝሬ እንኳን ተረፋችሁልን አልኩኝ። ከመራዊ እስከ ደባርቅ፤ ከደባርቅ እስከ ደብረብርሃን፤ ከደብረ ብርሃን እስከ ሰቲት፤ ከሰቲት እስከ አዲስ አበባ፤ ከአዲስ አበባ እስከ ባህርዳር፤ ገብሬጉራቻ ወዘተ …… የእነኝህ ከተሞች እንደ ወሎ፤ እንደ ደቡብ ጎንደር፤ እንደ ወቅና ጭና በከፊል ጥቃቱ ያልደረሰባቸው መሆን ለህወሃት የህሊና #ቋያ ነበር።
 
በሦስት ዓመቱ የፋኖ ትግል በተዘዋዋሪ ይህ ያንገበገበው የህወሃት ህልም ተሳክቷል። ለህወሃት የራስውድመት ስጦታ ተበርክቶለታል። የአማራ ህዝብ የጦር አውድማ፤ የድሮን መፈንጫ ሆኗል። አይደፈሩም የሚባሉ መንፈሳዊ ጥንካሬወች ሁሉ በየዓይነቱ እንዲደፈሩ ሆኗል። ይህ ለጃርቱ ጉባኤ ለህወሃት ዳግሚያ ተንሳዔው፤ ለአማራ ህዝብ ስውር የሆነ አሉታዊ ተጽእኖ ፈጣሪ ክስተት ነበር።
 
በዚህ አሉታዊ ክስተት የልብ ልብ ያገኜው ግራጫማው፤ ሁልጊዜ በሰው ልጅ ሰቀቀን ነፍሱ የምትንቀሳቀስ ቁስለኛ ድርጅት ህወሃት ጠጋኝ፤ አራሽ መንፈስ፤ በበቂ አገግሞ፤ የልብ ልብ አግኝቶ ጠለምትን ይደቁስ ዘንድ ሁኔታውን ያሳካው ለህወሃት ያለው ስኬቱን የማበረታት ማዳበሪያ የተባረከለት ሁነት የፈጠረው ሃቅ ነው። 
 
ነገም የራሱ የጎንደር ልጆች ህወሃትን መርተው ጎንደር አስገብተው የበቀል ብርንዶውን ይከሰክስ ዘንድ ሊያመቻቹ አይችሉም ብዬ ላስብ አልችልም። ፈጽሞ። የማይካድራው፤ የጭናው፤ የንፋስ መውጫው፤ የደብረታቦር አቅራቢያ በዓቶችን መከራ እሰቡና፤ የቀንበጦችን ሰማዕትነትም በጥልቀት በአስተውሎት መርምሩት እስኪ።
 
#እርገት ይሁን።
 
ዛሬ ሥማቸው የማይነሱት የወጣት ናሆሰናይ፤ ወጣት ኪሩቤል፤ ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳሽን ይዞ ሰማዕትነትን የተቀበለው ታዳጊው አበበ፤ ዋዋ ጎቤ፤ የልጅ ውባንተ ትንታግነት፤ ወጣት አባኔዘር ወዘተ ወጣትነታቸውን የገበሩለት የአማራ ህዝብ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ጎንደርን በጠራራ ጸሐይ ለህወሃት ለማስረከብ ከሆነ፤ የእነኝህ ንጹሃን አጽም ከመቃብር አውጥቶ የማቃጠል ያህል ነው የሚሰማኝ። ዋጋቸው፤ ውለታቸው ይህ ሊሆን አይገባም ነበር። 
 
ለህወሃት ብርዳማ ሁነት ሙቀት የለገሰው አሁን ላይ ፍንትው ብሎ እየታዬ ነው። እኔን እራሴው አጥፍቼ የአንተ የንግሥና ተራራ ቦግ ይበልልህ በየትኛው የጎንደር ዘመን ይህ አሳቻ ቁልቁለታዊ ፌዝ እንደተፈጸመ አላውቅም። የአባቶቻችን አደራ እና ትውፊት እየተደረመሰ በየጊዜው በሚፈጠሩ ፍላጎቶች መገበርን አለማቋረጥ ለእኔ የላንቁሶ ውሃነት ነው።
 
ህወሃት ከነዝክትሉ፤ ከእነ ድሪቶው ዌልካም እየተባለ እኮ ነው። ይህን መሰል የፖለቲካ ዝርግነት የእናቴ እናት ጢጢዬ " ብልሃት የሌለው ቅላት" ትለዋለች። በዚህው ይቋጭ።
 
በውነቱ ስለህወሃት የልቤን በጊዜው ስለአደረስኩ በዝምታ ነበር የምከታተለው። ነገን ቁንጮ መሪ እሆናለሁ ብሎ አኮበኩባለሁም ከአለ ዝምታው ይጣሳል። ለጎንደሮች በመጨረሻው ልላችሁ እምፈልገው ልቦና ግዙ፤ ጥሞና ውሰዱ ነው። በማስተዋል - ተራመዱ። "ልብ ያለው ሸብ" "ሙያ በልብ" ላይም ከትሙ። 
 
ጥንቃቄ የሚያስፈልገው በኽረ አመክንዮ ግን በጎንደር ለሚኖሩ እናንተን ጥግ እና ከለላ አድርገው እምነት የጣሉባችሁን የተጋሩ ልጆች ክብር፤ ትህትና አደራ እንዳትነፍጉ። ጭንቀት እንዳይገባቸው። እንደ አባት አደሩ አንተ ትብስ አንቺ ትብስ ተባብላችሁ በሰላም ኑሩ። ቀኗ አጭር ሌሊቷም ቆራጣ ናትና የቆይታችን ዘመን ነፍሳችንም እንሰባት።
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
28/01/2026
 
ፍቅር ሲያልቅ ትዕግሥት ይሰደዳል።
ትዕግሥትም ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።