#የይቅርታ #ደወል፤ የምህረት ዓዋጅ ለሁላችንም ያስፈልገናል። ሰሞናተ - አጽዋማት የክርስትና ይሁን የእስልምና ሃይማኖት በአጽህኖት ይህን ያጠይቃሉ እና።
"እግዚአብሄር በአንድም በሌላም
ይናገራል፤ ሰው ግን አያስተውለውም።" .


#ምዕራፍ ፲፰
ዛሬን የተሰጠንን ቅዱስ ቀን #ካቴና ላይ ስለሚገኙ ወገኖቼ ሰጥቸዋለሁኝ። ስለሆነም ዛሬን አብረን እንሆን ዘንድ ዘንከት ባለ ኢትዮጵያዊ ትህትና #ቅኖቼን እጠይቃለሁኝ።
እኒህ አባት፤ ጋዜጠኛ፤ ጸሐፊ፤ ደፋር ሞጋች፤ ርትዑ፤ የታሪክ አዋቂ ከአቦይ ስብኃት፤ ከአቶ በረከት ስምኦን፤ አሁን ከጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ጋር በሚር ማዕረግ ፈርሰስ ከሚሉት ከአቶ ጌታቸው ረዳ፤ የጦር መሪ ከነበሩት ከጄኒራል ፃድቃን አይደለም በላይ፤ አቻ የሚሆን ግድፈት ፈጽመዋልን? ይህን ያህል አሳራቸውን የሚዩት?
ወይንስ አዘውንትነታቸው ተጠልቶ ይሆን? #እርግማንም ነው። አንድ መሪ ከቂም እና በቀል የጸዳ መንፈስ ሊኖረው ይገባል። #የምህረት እና የይቅርታም #ሞዴል ሊሆን ይገባል። በመሪነት ውስጥ አንዱ የቅርብ ዜጋ፤ ሌላው የእዳሪ ሊሆን ፈጽሞ አይገባም። መሪነት የውሃ ቅዳ፤ የውሃ መለስ #የኩታራ ድልቂያ አይደለምና።
በብዙ ነገር ዝልቅ ትዕግሥት የሚደረገው አቅም አግባቡን ስቶ ሌላ ላይ እንዳያርፍ ለጥንቃቄ ነው። እንጂማ ……… ያ ሁሉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኛ የተፈታበት ሁነኛ ጎዳናን ዓመት ድገም የሚል ፈጣሪ ከመንበሩ ለቆ አይደለም።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኞች ጉዳይ በማስተዋል ሊታሰብበት የሚገባ በኽረ ጉዳይ፤ በኽረ አጀንዳ ሊሆን ይገባል። ቻሌንጁ ጠፍቶኝ አይደለም። አውቀዋለሁኝ ከምል የኖርኩበት ህይወቴም ነው። ግን ኢትዮጵያ በፖለቲከኞች፤ በጋዜጠኞች፤ በትጉሃን እስር ተርታ በድጋሚ ስትገኝ አንገት ያስደፋል።
ህሊናን ማሰር ለእኔ #በሃሳብ #አለመብቃት፤ #አለመሰልጠንም ነው። ሃሳብን ሃቅ አለኝ የሚል ወገን #በዕውነት፤ #በፋክት በተጨባጭ አመክንዮ ሞግቶ መርታት ይቻላል። ምኑ ይሆን የሚከብደው???
የአባት ታዲዮስ ታንቱ ጉዳይ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል። #ከህሊና በላይ የሆነ በደል ነው እኔ እያስተዋልኩት ያለው። የኢትዮጵያ መንግሥት ዕውነትን ከያዘ ለምን ይፈራል? ለነገሩ ፍትህ ሚር ላይ ያለው አቅም የማሟያ ያህል መሆኑን ተመልክቻለሁኝ። ፍትህ ዕድሜ ጠገብ፤ የጨመተ፤ በተመክሮ የዘለቀ፤ ያስተዋለ፤ የጨመተ ቲምን ይጠይቃል። በዘመነ ህወሃትም ዛሬም እኔ የማዬው ኢትዮጵያ አገሬ በደል አለባት የምለውም የፍትህ ተቋማቷ ነፃነቱን የተቀማ ወይንም የመሆን አቅሙ ፈተና ላይ ያለ ሆኖ ነው።
በዘመነ ህወሃት የህግ ፋክልቲ በኢትዮጵያ ምድር ቢቀር የሚል ጹሁፍ ጽፌያለሁኝ። ያሉ ተቋማት በራሳቸው ነፃነት ይንቀሳቀሱ ዘንድ ሌላ የተጋድሎ ሁነት እንዳለ ነው ያዬሁት።
በዛ ሰሞን ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ባለቤታቸውን ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸውን #እቅፍ አድርገው የፍርድ ቤት ውሎ ላይ ተገኝተው ነበር። ጉብኝትም አድርገዋል። ይህ ጥሩ ነው። ይህን አቅም፤ ይህን #ተነሳሽነት የፖለቲካ እስረኞች የፍርድ ሂደት ሲካሄድ ሊዩ ቢፈቅዱ ኖሮ አቤት እንደምን ያለ የተስፋ #ኢስክራ በነበረ። (* ኢስክራ የራሺያ የፖለቲካ ፓርቲው ልሳን፤ በኢሠፓ እንደ ሠርቶአደር ጋዜጣ ወይንም እንደ መስከረም መጽሄት ማለት ነው።)
እስረኞቻችን የሚደርስባቸው ስውር በደል አለ። ይህም ብቻ ሳይሆን የተሠወሩም አሉ። ለእናት፤ ለፍቅረኛ ምንያህል መርግ መከራ እንደሆን ማሰብ ይገባል። ማየት ተስፋ ነው። በኢትዮጵያ የ፰ ዓመታቱ የድንገተኛ የዜጎች እንደወጡ መቅረት፤ ከሆስፒታልም ሄዶ አለመመለስ፤ መታገት፤ መደፈር፤ መሠወር #ዕውነቱን ፈልፍሎ ለማግኜት ምንአልባት ሞሳድ፤ ወይ ኬጂቢ፤ ወይንም ሲአይኤ ብቻ ይሆናሉ አቅሙ የሚኖራቸው።
የፖለቲካ እስረኞች ጉዳይ ግን ከመዓከል እስከ ወረዳ ያለው የኢትዮጵያ የመንግሥት መዋቅር የሚፈጽመው ነው። ስለዚህ በቀጥታ የሚጠየቀው የኢትዮጵያ መንግሥት መሪው ብልጽግና ፓርቲ ይሆናል። እስሩ ቂም አለበት። በቀል ሊኖርበት ይችላል። የማንነት ቀውስም ሊኖር ይችላል። የሙስና በርም ሊሆን ይችላል።
ገራሚው ነገር ከፋኝ ብለው ዱር ቤቴ ያሉትም ያስራሉ፤ የከፋ እርምጃም ይወስዳሉ። ይህ ማለት ለኢትዮጵያ እናቶች ነገም አስፈሪ መሆኑን ይጠቁማል።
የኢትዮጵያ እናቶች ልጆቻቸውን የት #ይደብቁ?????
#ትናንት አስፈሪ ነበር።
#ዛሬም አስፈሪ ሆነ።
#ነገም የአስፈሪነት ዋዜማው እዬታዬ ነው። በነገራችን ላይ ህወሃት መንበረ ሥልጣኑን ይለቅ ዘንድ የሞገቱት ወሳኝ አመክንዮወች እነኝህ ነበሩ። በምርጫማ 99% አሸንፌያለሁ ብሎ ነበር። ለዚህ ነው እኔ ምርጫ በማድረግ ሥልጣን ማስቀል፤ ምርጫን ቦይኮት በማድረግ ሥርዓትን መቀየር አይቻልም። እያንዳንዱን የዕድል በር ተሳተፋበት እምለው። ልምድ፤ ተመክሮ የሜዳ አሽዋ አይደለም እና።
#አንኳራዊ ጉዳዮች ለትናት ከሰሩ፤ ዛሬስ???? ህወሃትን ከመንበሩ የነቀሉት ……… እነሰኑ ነው የሰበሰበው ብልጽግና።
1) የድምጽ አልባወቹ የኢትዮጵያ እናቶች ዕንባ ጉዳይ። ወይዘሮ #ታደሉ አይረሱኝም። ልጃቸውን ገድለው ከሬሳው ላይ አስቀምጠው ደበደቧቸው። ቃለምልልሱ አለኝ። አሰቃቂው #የሬቻ ጭፍጨፋ እና የጎንደር ቅዳሜ ገብያ #መንደድ የባህርዳር ከተማ #የደም አላባነት ወዘተ ………
2) የኢትዮጵያ ሴቶች የፖለቲካ ውክልና ምንም {}ደረጃ ላይ መገኜት።
3) የኢትዮጵያ ፖለቲካ በአንድ ገዢ ፓርቲ ብቻ መዘወሩ። ተፎካካሪ ዳሽ ____ ላይ መገኜቱ።
4) ኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኞች መናህሬያ መሆኗ። (በተለይ የአማራ እና ዬኦሮሞ ፖለቲከኞች በገፍ ለካቴና መዳረግ)
5) ግፋዊ #ዘግናኝ አገዳደል፤ ግፋዊ የእስር ቤት ድብደባ፤ ግፋዊ የአንደበት ትልልፍ #መስቃ።
6) "ወልቃይት ብረሳሽ ቀኛ ትርሳሽ" ዕድምታ።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
21/02/2026
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
የምህረት ዓዋጅ፤ የይቅርታ ልብ ያስፈልጋል።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ