#ምህረት፤ #ይቅርታ መንገድን ያቀናል - ያቃናልም፤ ዓላማን ያሳካል፤ #ለትውልድ ይሆናልም ከደከምን ላይቀር ለእኩል ሳቅ እንትጋ።

 


#ምህረት#ይቅርታ መንገድን ያቀናል - ያቃናልም፤
ዓላማን ያሳካል፤ #ለትውልድ ይሆናልም ከደከምን ላይቀር ለእኩል ሳቅ እንትጋ።
 
"እግዚአብሄር በአንድም በሌላም
ይናገራል ሰው ግን አያስተውለውም።"
 
 
 
#ምዕራፍ ፲፰።
 
በአብን፤ በባልደራስ መፈጠር በርካቶች ታሠሩ፤ ተንገላቱ፤ ኑሯቸው #ተበተነ። ለስደትም የተዳረጉ አሉ። ግን ያ ሁሉ መስዋዕትነት በየባዕላቱ በዓድዋ ይሁን በካራማራ የተከፈለላቸው ግብር ምን #አፈራ??? ምንስ አሳካ??? የፖለቲካ ድርጅቶች አስበው የሚነሱት ትውልዱን ነው። ትውልዱ በየዘመኑ ማገዶ ሲሆን አንድ እስክርቢቶ ገዝቶ ላላስተማረ ሰብዕና ግንባታ ሲል ነው የመፈጠሩን ተልዕኮ የሚገብረው። ይህን ዕውነት ተቀብሎ ለእናት ማህጸን ቢራራለት ጥሩ ነው። ልጅ የዳንቴል ሥራ ውሎ አይደለምና።
 
ቢያንስ ተው ስንል ቢደመጥ ብዙ፤ በጣም ብዙ ነገር ማትረፍ ሲቻል ጫን ያለ የጭንቀት እና የማቅ ሁነት ተፈጠረ። እራሱ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዱም ብዙ የሚስጥራቷ መድብል ታውኮ ነው የባጀው። ዝም የምለው ሁሉ ነገር ጠፍቶኝ፤ ጉዳቱ ሳይሰማኝ ቀርቶ አይደለም። ከዛሬ ነገ #ማስተዋል ቀን ከሰጠው ብዬ እንጂ። የአማራ ክልል ማቅ መልበስ ውስጤን ያቆስለዋል። ብዙ ወገኖቻችንም ተፈናቅለዋል። የዛ ገራገር ገበሬ ሁነትም ውስጤን ያውከዋል። 
 
ይህ …… #ትናንትም ሆኗል፤
 
ዛሬም እዬሆነ ነው።
ነገም ይቀጥላል። ድምጽ አልባወቹ የኢትዮጵያ እናቶች የማህጸናቸው #ቄራነት ይቁም ብለው ብሄራዊ ንቅናቄ እስካልጀመሩ ድረስ። በአዳዲስ ስያሜ፤ በአዳዲስ ውህድነት ወይንም ቅልቅል ማገዶ የሚሆነው ነፍስ እንደ እለት ጉዳይ ይታያል። ገብያ ተሂዶ እንደሚሸመት ሸቀጥም ይታያል።
 
ከቅንጅት ጀምሮ የተፈጠሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ሲበተኑ ሰው አስፈልጓቸዋል፤ ይህም ብቻ አይደለም በተበተነው ልክ ውግዘቱ፤ በክፋ ዓይን መተያዬቱ፤ በጥርጣሬ ውስጥ መማቀቁ፤ ለዛውም ለስኬት ሳይበቃ የቅረቱስ???
 
በሌላ በኩል ወደ ኋላም ከኢህአፓ ጀምሮ ተጸንሰው ለወግ ለማዕረግ ሳይደርሱ ጨንግፈው ለሚቀሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ሰው አስፈልጓቸው ነበር። ሁላችንም፤ የምንወዳቸውን አጥተንበታል፤ እኛ እራሳችን ወጣትነታችን፤ ውበታችን፤ ማህበራዊ ግንኙነታችን ነዷል። ስለሆነም በክፋ ዓይን እየተያዬን ዛሬም ለማያፈራ ጉዳይ፤ አካይ ብክነት ለተጨማሪ ስቃይ እና መከራ እንደገና ሊታጭ አይገባም። እኔ #ይበቃል ባይ ነኝ። ስሜታችን ዋጥ አድርገን የየራሳችን መባተል እናዳምጠው እስኪ። 
 
እንዲያውም እንደ እኔ ለኢትዮጵያ #ኦርጋኒክ ተፈጥሮ #የትውስት የፖለቲካ ድርጅት ሊመጥን ስለማይችል ተፈጥሯዊ፤ ሰዋዊ #የቲም አመራር ከፖለቲካ ድርጅት ውጪ ኢትዮጵያ ቢኖራት ምኞቴ ነው። የፖለቲካ ድርጅት መሪነት አላወቅንበትም፤ አላሳካንበትም። የቂም እና የበቀል መደበር በየዘመኑ ከማደራጀት ውጪ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም ያስጠበቀ፤ የኢትዮጵያ እናቶችን ዕንባ ያበሰ፤ አይዞችሁ ያለ፤ ያጽናና፤ እኛንም ከስደት #የታደገ በሳል የፖለቲካ ትርፍ የተገኜበትን ዘመን እኔ አላየሁም።
 
ስደት በቃን! ብለው አገር የገቡ የምናውቃቸውም፤ የማናውቃቸውም የፖለቲካ መሪወች አቶ ኦባንግ ሜቶ፤ ዶር ሙሳ ኮንቴ፤ ጋዜጠኛ እና ፖለቲከኛ ክንፋ አሰፋ፤ ኮነሬል ጎሹ ወልዴ ወዘተ … ያሉበትን ሁኔታ አናውቅም። ስለዚህ በልፋት በድካም ውስጥ አገሬ ብትናፍቀኝ፤ አገሬ ሽው ብትለኝ፤ ላያት ብሳሳ እና ብጓጓ ምን ለማግኜት??? ነፃነት ሁሉንም ነው። በድህነትም ለመኖርም #ነፃነት ይሻልና። 
 
ዱር ቤቴ ያሉትንም እያዬሁ ነው። ከብዙ ዘመን እስር በኋላ ጫካ ያሰኜው እስኬው ፋኖን እመራለሁ እንዳትል ብዬ ገና ከእስር ቤት ሲወጣ ጽፌ ማድመጥ ተስኖት #ሞከረው፤ ስኬቱን፤ ድሉን ለኩት። ከባልደራስ እስከ ፋኖ በአዲስ አበባ እና በአማራ ክልል የታሰረው፤
 
 የተሠወረው፤ ባሩድ የበላው፤ የወደመው፤ የተፈናቀለው ማን ጠያቂ? ማን ተጠያቂ? ይሆንበታል። ማን ይቅርታ ይጠይቅበታል? ማንስ ምህረት ሰጪ፤ ማንስ ምህረት ጠያቂ ይሆናል? ሳይንስ ቀመር ነው። መማር ሊኖር ይችላል። ከመማርም ባለፈ መምህርም እንደ ፕሮፌሰር ዶር መራራ ጉዴና ይኮናል። መማር እና መምራት ይለያያሉ። ተጽዕኖ ፈጣሪነት እና አገር መምራት ለ21ኛው ምዕተ ዓመት #ዘለንስኪዝም ከካሪክለም በላይ ናቸው። 
 
አቅም ሊኖር ይችላል። የራስን አቅም ጥቅም ላይ ለማዋል ብልህነት እና ስልት ይጠይቃል። ከሁሉ በላይ ለእኔ ብሎ የሚሰዋው መኖር በህሊና ማዕከላዊ #ማዘዣ ጣቢያ ሊሆን ይገባል። በገፍ ትውልድ ሲገበር፤ በገፍ መኖር ቅጥ መጠኑን ሲያጣ ተጨማሪ ፈተና ላለመሆን በጊዜ አቅምን ለክቶ መስዋዕትነትን መቀነስ መቻል ብልህነት ነበር። 
 
በየለቱ መርዶ። በየለቱ ድል እና ሽንፈት። በየለቱ ውድመት እና ዕንባ። በየለቱ ገዳዩ ያልታወቀ የሙህራን እልቂት ዛሬን እያቃጠለ፤ ነገን የዶግ አመድ እንደሚያደርገው አለማሰብ፤ በማን ማገዶነት፤ በማን ምድጅነት የሚለውን አለማጥናት ዕዳነት ነው። ዕዳነቱም በጥምር #አራጣነት ነው። 
 
በዚህ ሁሉ ስጋት፤ በጠነ ሰፊው ፍርሃት፤ በጥልቁ - መራድ፤ በጥቁሩ * መጨነቅ፤ በዳመናማ ዕንባው፤ የሚወዱትን ማጣት፤ የቅርስ፤ የውርስ፤ የከተሞች ውድመት ውስጥ ጨርቃቸው ያልቀየሩ እናቶችን እንግልት በጥልቀት ሊታሰብበት ይገባ ነበር። ይሳካል ብለው ቀን ከሌት ከመኖር ጋር እየታገሉ፤ በግራ በቀኝ ወጨፎውን ታግሰው ሁለመናቸውን የሰጡት #ስደተኛ ወገን ሁልጊዜ መባተልንም ከውስጣችሁ ሁናችሁ መርምሩት።
 
ብስጭት፤ መከፋት፤ ተስፋ ማጣት፤ መከላተም፤ እንቅልፍ ማጣት ሁሉም እኛኑ፤ የእኛውን ወገን ጎድቶታል። በዚህ መሃል ተጠቃሚ ሊኖር ይችላል - ጥቂት። ያም ከጭንቀት ጋር #የተጣባ ስለሆነ የህሊና ሰላም አይሰጥም።
 
በዚህ መሃል ፊት - ለፊት የተገኙ ሺወች #ለካቴና ተዳርገዋል። የሚያስታውሳቸው የለም። በግራ ቀኙ ያለቁም ወገኖች አሉ። ሁሉም እናት አላቸው ( ፋኖ፤ ባልደራስ፤ አድማ በታኝ፤ ሚሊሻ፤ ፖሊስ፤ ሠራዊት፤ ) ይህ ሁሉ ወጣ ገብ - ጉዞ፤ ዳጥ እና ማጥ ነገን ከቀጣይ - ጭንቀት - - ፍርሃት - ከስጋት - ከካቴና - ከሞት ይታደጋል ወይ? በየጊዜው ህብረቱ ቀጥሎ ለትውልድ ይሆናል ወይ? ሁሉም አብሮ እየወጣ እየወረደ ስለሆነ ከራሱ ጀምሮ ይመዝነው።
 
ቢያንስ እስር ቤት ያሉት በኢትዮጵያ መንግሥት ሥር ያሉት፤ ዱር ቤት ባሉትም ውስጥ ያሉ እስረኞች #ነፃነታቸውን አግኝተው ለጸሐይ ይበቁ ዘንድ በወል ብንተጋ ጥሩ ይመስለኛል። ተጨማሪ እስረኛ፤ ተጨማሪ ማገዶነት እንዳይኖርም ጥንቃቄ ያስፈልጋል። በሞኝ ክንድ ዘንዶ ይለካበታል ነው እማዬው። አይደለም ክልላቸውን የጋብቻ ቤተሰባቸውን ያሸሹ አማራ ክልል ቋያነቱን ይቀጥል ዘንድ ሌት ተቀን ሲባትሉ አያለሁኝ። 
 
ሌላው በየክልሉ፤ በየዞኑ፤ በየወረዳው በየአዳራሹ ብዙ ሺህ እስረኛ አለ የፖለቲካ። ተቋሙ፤ መዋቅሩ የማን፤ ለማን ይስራ? ጉዳይ አይደለም። ብቻ ያ መከረኛ የአማራ ህዝብ ለቀጣይ ማገዶነትም ታጭቷል። ይህ ሁሉ ውጥንቅጥ፤ የመከራ ቁልል የትውልዱን አስተሳሰብ ያቀጭጫል። ፍርሃት በራስ መተማመንን የሚዘርፍ ባላንጣ ነውና። በራሱ ዕምነት የለለው ቀና ብሎ ለመሄድ አይችልም። ዕዳ ነው።
#ትውልዱ የአዲስ አበባ እና የአማራ ክልል።
 
ማገዶነቱን ከጠረጴዛ ላይ ቁጭ አድርጎ ያወያዬው። የመገበሩን #ሚስጢር ይገምግመው። ትርፍ እና ኪሳራውን ያስላው። በግለሰብ ሰብዕና ግንባታ ላይ እኔንም ጨምሮ ያቃጠልነው ጊዜ፤ ያባከነው የህይወት ዘመን ሁሉ ለመመርመር እንፍቀድ። ሥርዓት፤ ተቋም መገንባት ከግለሰብ ሰብዕና ግንባታ በላይ አትኩሮት ብንሰጠው የቦትሰዋናን የገነት ህይወት መዳፋችን ላይ ማድረግ እንችል ነበር።
 
ፖለቲካችን ከመርዝም የከፋ ነው። በብስጭት ከአንደበታችን የሚወጡ ቃላት ለትውልድ ህሊና ማዳበሪያ የማይሆኑ ናቸው። ይሰቀጥጣሉ። አገር - ማለት፤ ብሄራዊነት - ማለት፤ ኢትዮጵያ - ማለት፤ አፍሪካዊነት - ማለትን እንደ ገና፤ አወን እንደገና እንመረምራቸው ዘንድ - እንፍቀድ። የቆምንበት አፋፍ ለትውልድ ማትረፋን እንገምግመው። እንወስንም። 
 
የሃሳብ - መበተን፤ የሃሳብ - መወራጨት፤ የሃሳብ - መመሰቃቀል፤ የሃሳብ መጨመታተር ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገን እንዳያሳጣን #እንጠንቀቅለት። ችኮላው፤ ጥድፊያው፤ አቅል ማጣቱ፤ #አደብን ማሰደዱ፤ ስሜታዊነቱ፤ መነቃቀፋ እስከዛሬም አልጠቀመም ወደፊትም አይጠቅምም።
 
በገዢው የኢትዮጵያ መንግሥት፤ በዱር ቤቴ ባሉ ወገኖቻችንም ለእስር የተዳረጉ ወገኖች ከቂም የጸዳ ምህረት ይደረግላቸው ዘንድ በትህትና ለባለድርሻ አካላት ሁሉ እጠይቃለሁኝ። ለእናታቸው፤ ለትዳራቸው፤ ለልጆቻቸው፤ ለቤተሰቦቻቸውም ይታሰብ። ለእናት መዳህኒቷ - ልጇ፤ ለወላጅ ፈውሱ - ልጆቹ፤ ለትዳር እርካታው ሰላማዊ ህይወት!
 
#ዛሬን በጥሞና
#ነገን በቅንነት ጥገና ትውልድ ይድን ዘንድ እንበርታ።
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ቸር ያሰማን። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
21/02/2026
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ጥላቻን፤ ጥላቻ አያክመውም።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።