ትዕግሥት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል። የሜንጫ ሱናሜ ...

እንኳን ደህና መጡልኝ።
ትዕግሥት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል።

„በፊቱ ካለው ብርሃን የተነሳ
ደመናትና በረዶ የእሳት ፍምም አለፉ።“
መዝሙር ፲፯ ቁጥር ፲፪
ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
08.03.2019
ከእመ ዝምታ - ሲዊዘርላንድ።
·       መንገድ።

ጤና ይስጥልኝ ውዶቼ። ደህና ናችሁ ወይ። ዛሬ ወጀብ መሳይ አለ እንዲህ ወደ ቪንቲ። መስኮቴንም እዬነቀነቀው ነው። ኢትዮጵያም የከፋ ወጀብ አለ። የአብይን ካቤኔ ሊንጥ የተሰናዳ። ገና አልፈነዳም ግን የታመቀ መከራ ፊት ለፊት ተደቅኗል። ያው ሽግግር እያደረግን ነው ትዕግሥት አልቆ ፍቅርን ለማሰደድ። ሻንጣዎቹ ፓክን ፓክን ሆነዋል።

የሰው ልጅ ፍቅር ለመስጠት ቅን መሆን አለበት። ተጠራጣሪ ሰው ፍቅር መስጠት አይችልም። እንዲህ ዓይነት ፍጥረት በህይወት ዘመኑ ሁሉ ፍቅርን ሳይሰጥም፤ ፍቅርም ሳይቀበል ዘመኑ ይጠናቀቃል፤ ለነገሩ መስጠትም መቀበልም ፍቅር ከሚያውቅ ቅን ነፍስ የሚገኙ የፈጣሪ ስጦታዎች ናቸው።

ብዙ ጊዜ ለማናቸውም ነገር ስጦታ የሚያዘጋጁ ሰዎች የፍቅር ቅን ሰዎች ናቸው። ለእኔ ፍቅርን የሚፈጥረው ቅንነት ነው ብዬ አስባለሁኝ። ፍቅር ለመስጠት ንፎጎች ምክንያታቸው ነገ እንዲህ ቢሆን፤ ነጋ እንዲያ ቢሆን በማለት ወቀሳን የሚሸሹ ብቻ ሳይሆን ተፈጥሯቸው በአሉታዊ ብክል ፍልስፍና የሚገዛ ይመስለኛል።

የሆነ ሆኖ እኔ የኢትዮጵያ ህዝብን ስመለከተው ፍቅር ለመስጠት ለጋስ ነው። ፍቅር ለመቀበልም ለጋስ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ፍቅር ሲሰጥ በትህትና አክብሮ ነው። ፍቅር ሲቀበልም በትህትና በአክብሮት ነው። ሲጓደል ደግሞ አብዝቶ ይታገሳል። የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ ህዝብ ቁንጥንጥ አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ የሰከነ ነው።

የሚገርመው የኢትዮጵያ ህዝብ ከሰጠው ንጹህ ቅን ፍቅር በላይ ነው አብዝቶ የሚታገሰው። ይህ ደግሞ በፈጣሪ ዘንድ የተከበረ ሥነ - ምግባር ነው። ለዚህም ነው ልዑል እግዚአብሄር ለዚህች አገር የተለዬ ዝንባሌ እና ጥበቃ የሚያደርገው። አሁን እኔ እንደማስበው ማዕከላዊ መንግሥት ሸርተቴ እንደያዘው  ነው።

ነገር ግን የፈጣሪ  አገር ስለሆነች ኢትዮጵ ይኸው በኪነ ጥበቡ አለች። አቶ ሀይለማርያም ደስአለኝ ለቀው ዶር አብይ አህመድ እስኪሾሙ ድረስም ከፍተት ነበር፤ ደርግ ወድቆ ህውሃት ሲመጣም መሰሉ ተደግሟል። አሁንም ሜንጫ የሚያስተዳድራት፤ ፊከራ የሚመራት አገር ሆናለች። ዘራፊዎች ኡሷን ለማፈረስ የሚአውጁትም በህጋዊነት ተከብረው ደልቷቸው የሚኖሩባት። የዚህ ሁሉ ጥበቃ የፈጣሪ ሃይል ነው፤ አሁንም ፈጣሪን እኔ እምማጸነው ይኸውን እንዲያጸናው ነው ጥበቃውን። ምክንያቱም ገጀራ እና ሜንጫ የሚያስተዳድራት አገር እዬሆነች ስለሆነ።

ግድፈት።
·       ግድፈት 1.

በፖለቲካ ህይወት ውስጥ የሚቀድሙ አገላለጹች ሊኖሩ ይገባል። ቃሎች ሃይል አላቸው። ስንኞች አቅም አላቸው። አቅማቸው ለማሸነፍም ለመሸነፍም አቅም አላቸው። ባለፉት ሦስት አመታት የአማራ የማንነት የህልውና ተጋድሎ ለማለት የደፈረ ሊሂቅም የፖለቲካ ድርጅትም አልነበረም። አሁን የዘራውን እያፈሰ ነው። አስፈሪ ነገር እዬተደመጠ ነው ... 

ስለዚህም ነው አሁን የተዛባ የፖለቲካ ሚዛን በሥነ - ልቦና ደረጃ ያለው። አንዶ አብጦ እንዲወጣ፤ ሌለው እንደከሰም ተሰርተበታል። ይህ ትልቅ ታሪካዊ ግድፈት አሁን ያለውን  በአንድ በኩል ያዘነበለ መከራ እንድንቀበል ተገደናል። ይህ ለውጡን በአንድ አቅጣጫ ብቻ ተስፈኛ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን ለውጡ አይሆኑ ሆኖ ውድቅት እዬገጠመው መሆኑ እዬታዬ ነው።

ለዚህ የአቶ ደመቀ መኮነን አንቦ ተገኝተው „ቄሮ ጀግና“ ሲሉ ጎንደር ተገኝተው የአማራ የህልውና የማንነት ተጋድሎ ጀግና ማለት ሲገባቸው ቀበሩት፤ ለዚህም ነው በባህርዳሩ የራት ግብዥ አዲስ የመንፈስ ሜጫ ቻል የተባሉት። እራሳቸውን ማስከበር የሚያስችላቸውን ታላቁን ተጋድሎ ንቀው ሌላ ቤት ሲያነግሡ ዛሬ እሳቸው እንደ ጫጩት ታዩ

https://www.youtube.com/watch?v=dMQpi9gU79I

የስልጣን ሽግግሩ ለሌሎች አመራሮች ትምህርት የሚሆን ነው - / ዶክተር አብይ አህመድ

https://www.youtube.com/watch?v=UdT9AIcPE28

/ / ደመቀ መኮንን በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሽኝት ፕሮግራም ላይ ያደረጉት ንግግር

 


ይህን ሁለቱን ንግግሮች አዳመጦ እንከኑ የት ላይ ነው ማለት ይቻላል … ለውጡን ለመደገፍ ብቻ ሳይሆን ለውጡን ለማምጣት ጭንቅላቱ የአማራ የማንነት የህልውና ተጋድሎ ነበር። ለሳቸውም ለጠ/ሚር አብይ አህመድ የዚህ ስልጣን ባለቤትነት የአማራ ታሪክ ባፍ ጢሙ ተደፍቶ ስለመሆኑ ሊታወቅ ይገባ ነበር። 

ለነገሩ „ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለእዳው አይቀበለውም“ ይላሉ ጎንደሬዎች። አሁን ብቻ ሳይሆን በቀጣይነትም የሚከፈለው ግብር ያነን አመጣጥኖ ለመጓዝ የተሰጠው ዕውቅና በመና ስለተወራረደ ነው። ገና ብአዴን በድርብ ግማድ ይታረሳል።  ሌአለውም ሚዲያ በሉት፤ ተፊካካሪ ሁሉም የእጁን ያገኛታል። ረቂቅ ነው ሚስጢሩ ሆነ መፍቻው። 

·       ግድፈት 2.

ባለፈው ሰሞናት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ አንድ ያወጣት መርሃ ግብር ነበረች። የአዲስ አባባ ማንፌስቶ ነበረች። ያቺ መርሃ ግብር ብዙ ነገርን አጠባብቃለች። አዲስ አበባንም አጣብቂኝ ውስጥ ከታለች። የ97 የቅንጅት ልዕልና ህወሃትን በሁሉም መስክ የወለቀውን ብሎኖኑን እንዳጠናከረበት ማለት ነው። ለኦነጋውያን መልቲ ባይታሚን ነበረች።

የጠ/ሚር ቢሮ ከእንቅልፉ ያስነቃች ደወልም አለርም ነበረች። „ ኢንጂነር ታከለን በምርጫ እንዘርረዋለን“ ያልተገባ፤ ወቅቱን ያልጠበቀ የፖለቲካ ክስረት ነበር። በሌላ ጹሁፍም ይህን አንስቸዋለሁኝ። ጎንደሮች ይህን መሰል ጉዳይ ሲገጥማቸው ‚ሙያ በልብ‘ ብለው ያልፉታል። ከድነው። ሲሳይ ብቃት የሚኖረው ሲከደን ነውና። ያን ብልህነት አልተጠቀመበትም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ - አዝናለሁኝ። እንደ ጀብዱም አላየውም።

ገና ምርጫ ሲሆን የሚገኘውን ድል አስቀድሞ በእርግጠኝነት በልበሙሉነት ተናገረ። ከዚህ በኋዋላ ነው የኦዴፓ መግለጫ፤ የኮንዲኒምዬ ንቅናቄ፤ አሁን ደግሞ የአዲስ አባባ ፖሊስ ማስጠንቀቂያ፤ ወዘተ ... 


Ethiopia: ከአዲስ አበባ ፖሊስ የተሰጠ መግለጫ | Statement by Addis Ababa Police

ራሱ  የጠ/ሚሩ ጋዜጣዊ መግለጫ ቀጠሮ ያን ሃይለ ስንኝ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ባይጠቀም ኖሮ አሁን እሱ ስብሰባ ሲጣራ እሳቸው በጎን ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት አይሰናዱም ነበር። ራሱ ኦዴፓ ያዘጋጀው የሜጫ ሰላማዊ ሰልፍ ሁሉ ከዛ ሃይለ ስንኝ የመነጨ ነው። ምን ያጣድፋል? ምን ያስቸኩላል? በዝምታ ውስጥ ብዙ ነገር አለ። በመስከን ውስጥ ብዙ ትርፍ ነበረ። ገና ለግንቦት ዛሬ የድል ነጋሪት መጎሰም አልነበረበትም። ያ የድል ጭብጥ አስቀድሞ ትጥቅ እንዲፈታ ተደረገ መንፈሱ። ያልተጋባ እርምጃ ነበር። 

ያለወቅቱ የተዘራ ሰብል አይበቅልም በአረም ነው የሚወጣው፤ ቢበቅል እንኳን ቡቃያውን የሚቀናቀነው እጅግ ብዙ ስንክሳር ነው። ስለሆነም አድጎ ጎልምሶ ለማስበል ሰፊ የሆነ የፈተና ጊዜ ነው የሚያሳልፈው። አሁን ንጉሥ ታከለ ኡማን ለመዘረር በምርጫ እና አዲስ አባባን የአዲስ አበቤ ለማድረግ በራሱ ፈተና እና እግርብረት ያሰናዳ ነበር ንግግሩ። ፈተና ያመረተ ሌላ ሸክም ነበር።  

አሁን እንደምንሰማው ከመነሻውም አዲስ አበባን የኦሮሞ አገርነት ምልክት አድርጎ ለማስወስን ከፍተኛ ዝግጅት እንደተደረገ እዬተደመጠ ነው። ይህን ገዝግዞ ለመጣል ለዛውም ባልተደራጀ መንፈስ ለግብ ለማድረስ መከራው ከመከራ በላይ ነው።  ተከድኖ በልጦ መገኘትን ይጠይቃል። እንጂ መጣሁባችሁ እዬተባለ ሊሆን አይገባም ነበር።

ለዚያውም ሁነኛ ድርጅት እንኳን አዲስ አበቤን የሚወክል የለም። በመንፈስ እራሱ ወጥ መንፈስ ገና አልተገነባም። ሚዲያዎች በጊዚያዊ ሁነቶች እንጂ ዘላቂ በሆኑ ሞራላዊ የመንፈስ መሰናዶ አይሰሩም ከርዮት ሚዲያ በስተቀር።

ንግግሩ በርቱ - ተሰናዱ - ብሎን አጥብቁ - በራችሁን ፈትሹ ነበር። ሌላው ቀርቶ በምርጫ ቅስቀሳ እንኳን ያ ቃል ከአንደበት ሊወጣ የሚገባው አልነበረም። እራሱ አዲስ አባቤ ቢያሸንፍ ቃሉ እንኳን የተገባ አልነበረም። 

ውስጡ ሲፈተሽ መጠኑን መለካት ባላውቅም መታበይም ስላለበት። በመታበይ ውስጥ ደግሞ ዴሞክራሲ አይታሰብም። ዲሞክራሲ ፍልስፍናው ሰውን በሰውነቱ አክብሮ ስለሚነሳ። ውጥን በልኩ በድምጹ ልክ ስለሚተምን፤ መብት እና ግዴታን አዋዶ ጥበብ ስለሚያደርግ ዴሞክራሲ በልኩ ማሰብ ይገባል። በሌላ በኩል በመራጩ ህዝብ ላይም ሌላ የመንፈስ ጫና በግራ ቀኙ ስለሚጭን ሰፊ ጥንቃቄ ያስፈልግ ነበር። ግን አልሆነም። 

እኔ ይህን ሳዬው የክስረት ጉዞ ነው። ክሰረቱ ደግሞ መስዋዕትነቱን የበለጠ ያከፋዋል፤ ያከረዋልም። ገዢ መሬትን ተቆጣጥሮ እንኳን እዲህ መሆን አይገባም። እንኳንስ ሙት መሬት ላይ ተሁኖ። ማን አለው አሁን ለኢትዮጵያ ህዝብ? 

አሁን የኦዴፓ ችግር እኮ ይኸው ነው። አዬር ላይ ተንጠልጥሎ ነጮች እግራችን ሳሙ ይለናል። በአንድ ፋክስ እኮ ብትንትኑን ማውጣት ይቻላል። ምክንያቱም 21ኛው መቶ ክ/ዘመን ሰብዕዊነት ነውና ሞቶው።

ብርቱ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ድል ላይ ለመቆምም- ለመዝለቅም። ግንቦት 7 ትልሙ ሳይበረከት ባክኖ የቀረውም ይህን መሰል መንገድ ይከተል ስለነበር ነው። ኦዴዬንስ ለማስደስት በስሜታዊነት ከማሰብ ህይወት ላለው ዘላቂ ለውጥ የሰከነ መንገድ መከተል ነው የፖለቲካ ዘላቂ ትርፍ የሚያስገኘው። 

ብሶ ወቅቱን ካልጠበቁ ንግግሮች መቆጠብም፤ መጠበቅም። ቁጥብነት ያተርፋል እንጂ አያከስርም። ይህ አባባሌ ላይገባችሁ ይችላል። ግን እውነቱ ይኸው ነው። ለህዝብ መስዋዕትነት ተጨማሪ ነገር ማቀድ ካለጊዜው አይገባም። መስዋዕትነትን በሚቀነሱ ጉዳዮች ላይ ነው ሊሠራበት የሚገባው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሴረኛ ብቻ ሳይሆን ቂመኛም ነውና። 

ኦዴፓን ተፈጥሮውን እያዬን ስለሆን አብሶ ከመስከረም ዋዜማ ጀምሮ በጥንቃቄ መራመድ ያስፈልጋል። ሰው የነበሩት ተለውጠው አውሬ ሆነው ነው ያዬነው። ለዚህ ነው እኔ አብን አዲስ አባባ ሚሊዬን አዳራሽ ተከለከልኩ ብሎ ሰላማዊ ሰልፍ ሲጠራ የተቃወምኩት። የብአዴን የሰሜን አሜሪካ ጉዞንም የተቃውምኩት። የሰኔ 16 ሰልፍም ተቃውሜ ነበር። መስዋዕትነት መከፈል ያለበት ከቸገረ ብቻ ነው። እስካሁን በስልት አልባ ጉዞ ትውልድ ሲታጨድ ኖሯል። ተመክሮ ማለት ተሽሎ ለመገኘት አደብ መግዛት፤ መብሰል እና ማፍራት ማለት ነው።

ስለዚህ ብርቱ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። ወደፊትም እንዲሁ ጠንቃቃ መሆን ያስፈልጋል። ምን አልባትም ከህወሃትም የከፋ ገጠመኝ ሊኖር ይችላል። ስለምን ቢባል ቢያንስ ሰሜን ኢትዮጵያ የሥነ - መንግሥት መንፈሳዊ ውርስ ተመክሮ ስላለ የጭካኔው ደረጃ የሚለያይበት ጉዳይ ይኖራል።

ይህን ስል የሄሮድስ መለስ ዜናዊ ምስል እና ማነፌስቶ ያ የተሻለ ነው ብዬ አይደለም፤ የዛ መከራ ነው አሁን የምናዬው፤ ያም መሰረት ነበረው ከጣሊያን ፋሽስት የተወረሰ ነበር።

ብቻ ነገር ግን ጭካኔን አበርትቶ እና በበበለጠ ጭካኔ እያስፈራሩ አገር የመመስረት ህልም እያዬሁ ስለሆነም ነው። ይህን ደግሞ ብዙ ሰዎች ይሰጉበት የነበረ ነው ዛሬ ሳይሆን በቀደመው ጊዜም። የሻሸሜነው ሰቆቃ እኔን ያዬህ ተቀጣ ነበር።

ሚዲያዎች የመንግሥት እንዳይዘግቡት ሁሉ ተደርጓል … ሌላው ህዝብ ግን አንደበቱን፤ ፍላጎቱን፤ መብቱን እንዲሰበሰብ ተደርጓል። የኢንጂነር ስመኛው በቀለ ደመ ከልብነት፤ የአዲስ አባባ ወጣቶች ጭፍጨፋ እስር፤  እና የ አሸናፊው የመንግሥት አካል ድንፋታው፤ የቡራዩ እልቂት እና ዕብለቱ፤ ህዝብ አፈናቅሎ የነበረው የጀብድ ቀረርቶ፤ የለገጣፎ ለገዳዲ መከራ ሁሉን ስናያቸው ከሰውነት ወደ እንሰሳነት የተቀዬረ መንፈስ በኦዴፓ ስለመኖሩ እንረዳለን። ስለዚህ የሚወጡ ቃሎች ህዝበን የበለጠ መንፈሱን እንዲያጎሳቆል ለጨካኞች በር የሚከፍት መሆን የለበትም።

·       የሚበደለው ኢትዮጵያዊነት ነው።

በሌላ በኩል በእነዚህ ተስፋ ባደረግናቸው አመራር የምናዬው የመከራ መንገድ የተጎዳን መርዳት ነውርም ወንጀልም መሆኑን ነው። የተጎዳን መርዳት ወንጀልም ነውርም መሆኑ ሳስብ ኢትዮጵያ ወደ ፓጋንነት እዬሄደች ስለመሆኑም ምልክት ይሰጣል። ይህን በቡራዩ፤ አሁን በለገዳዲ ለገጣፎ እና በጌዲኦ ምስኪኖች ላይ ተከስቷል። ጌዲኦ ላይ ያለው ሮሮ እኮ ተዳፍኖ ከስሎ ያለ መከራችን ነው የወል።

የተጎዱትን ለመርዳት ማዕቀብ መጣሉን የሰባዕዊ መብት መጣሱ ብቻ ሳይሆን የቀይ መስቀል መመሥረትን መርህ፤ የተባባሩት መንግሥታት የመመስረትን መርህ፤ የዩነሴፍ የተመሰረተበትን መርሀ፤ የፋኦ የተመሰረተበትን መርህ ራሱ እዬተፃረረ ያለ ሙጃ እያዬን ነው።

ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አለምን የሚያሰጋ፤ ዓለምን ወደ ኢ-ሰብዕዊ ድርጊት እንዲጓዝ የሚያነሳሳ ክፉ መንገድ ነው። ጨክነው መግደል፤ ማፈናቀል፤ ተስፋ ማስቆረጡ አይደለም ከዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ፤ ለተጎዱት መርዳትም ወንጀል አድርገው ለተጎጂዎች እርዳታ እንዳይደርስ የሚያደርጉበት መንገድ በራሱ ሊፈተሽ ሊመረመር የሚገባው ጉዳይ ነው።

·       የኢትዮጵያ አዲስ ሴት የፖለቲካ ሊሂቃናት ሚና።

አሁን በብዛት ሴቶች ፖለቲካ ስልጣን ላይ አሉ። ለዚህ ምስጋና አቅርበናል በተለያዬ ሁኔታ። ነገር ግን ይህን ስሜት የሚሰጥ ነገር ባሊህ ሊሉት ይገባል ፕ/ ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴም በከንቱ ውዳሴ ተሸብልለው ሳይዘናጉ፤ ቢያንስ ይህን መንገድ ሊያስቆሙት ይገባል።

ኢትዮጵያ እናት አገኘች የሚያስበለው እንዲህ መሰሉን እውነት መድፈር ሲቻል ነው።
ምንግዜም ማንም ሰው ከእውነት ጎን ነው መቆም አለበት። እውነት ዜግነትም ብሄርም የለውም። እውነት የራሱ ማንነት እና የራሱ ተፈጥሮ አለው። እውነት የማንም የምንም ጥገኛም አይደለም። እውነት ራሱን የቻለ የተፈጥሮ ክስተት ነው። ስለሆነም ለእውነት ፍትህ መስጠት የህሊና ጉዳይ ስለሆነ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሴቶች ከእውነት ጎን ይቆሙ ዘንድ ጥሬየን በትህትና አቀርባለሁኝ።

ለተጎዱት ለሚደረሱ ወገኖች ማዕቀብ ሊጣል አይገባም።! የተጎዱትን ጉዳተኞች መከራ እጋራለሁ የሚል ሚዲያም ሊታገድም ሊደበደበም አይገባም። አራዊት ሴቶች ከአራዊት ወንዶችም በላይ ጨካኞች ስለሆኑ እነሱንም የመታገል አሁን በዬደረጃው ያሉ አንስት ሊሂቃን ሊተጉበት የሚገባ አብይ ጣምራ ጉዳይ ነው።

ሌላው ቀደም ባለው ጊዜ አማራ ህልውናዬ አደጋ ገብቷል እና ለዛ እታገላለሁ ብሎ ሲነሳ አይነህ ላፈር መባሉ ይታወቃል። ሲጠነክር ደግሞ ለመቀልበስ ተተግቶበታል። ለድል ሲበቃ ደግሞ ዕውቅና ተነፍጓል። 

አሁን በትልቁ የኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ላይ የሆነው በዚህ የፍልስፍና ድርቀት ምክንያት ነው። አሁን ያለው መከራ ያ ለህልውና የሚደረግ ተጋድሎ ቢፈራም ለኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ላይ ስለሆነ የኢትዮጵያ ሴቶች መታገል ይኖርባቸዋል። የኢትዮጵያ ሴተች መትጋት ያለባቸው  ለኢትዮጵያ ህልውና እንጂ ለሜንጫ ንግሥና መሆን በፍጹም አይኖርባቸውም።

ሴቶች ለልጆቻቸው መታገል መጀመር አለባቸው። ከፊታቸው ላይ በሜንጫ ልጆቻቸው የሚቀሉበት ዘመን አህዱ እያለ ስለሆነ። ይህ በእያንዳንዱ ቤት ደራሽ ማዕበል ነው። አሁን የሜንጫ ሱናሜ ላይ እና ኢትዮጵያ። ስለሆነም ከዚህ ሱናሜ በጥበቡ መድሃኔአለም ይታደገን ዘንድ መጸለይ ብቻ ሳይሆን የመጣውን የመከራ ዘመን ለመግታት ከእንቅልፍ ነቃ ማለት፤ መቀነትን ጠበቅ ማድረግ ሴቶች ይጠበቅብናል።

ኢትዮጵያ ያሉ ሊሂቃን ሴቶች ሥልጣኑ ለመልካምነት እናትነት እንጂ ለሜንጫ እናትነት እንዳይውል እራሳቸውን መርምረው ከእውነት እና ከሰባዕዊነት ጎን ይቆሙ ዘንድ በታላቅ አክብሮት አሳስባቸዋለሁኝ።

ሌላው አይቆርቁርሽም ወይ ለምትሉኝ አይቆረቁረኝም። አሁንም ወደፊትም መልካምነት ከኖረ ያን ደግፌ እቆማለሁኝ። ዶር ደብረጽዮን ገ/ሚኬኤል ስደት የነበሩትን ብፁዕን አባቶችን ሄደው ሲጎበኙ አመስግኜ ጽፌያለሁኝ። ብጹዕ አባታችን አቡነ ማትያስ ዝልፈት እና መደፈር ሲደርስባቸውም ስለምን ብዬ ወጥቼ ጽፌያለሁኝ። ከጎናቸውም ነኝ።
የትኛውም ወገኔ መልካም ሲያደርግ እደግፈዋለሁኝ፤ መልካም ሳያደርግ ደግሞ እወቅሰዋለሁኝ። በእኔ ውስጥ ቂም ኖሮ አያውቅም። 

አልተፈጠረም ቂም በልቦናዬ። ፊት ለፊት በግልጽነት እና በቀጥተኛነት እንደሆን ነው የተፈጠርኩት። በተፈጠርኩበት ንጹህ ተፈጥሮ ለመኖርም የፈቀድኩኝ ስለሆንኩኝ ስለመልካም ነገር ጠበቃ መሆኔ የምደሰትበት ጉዳይ ነው። ለሰከንድ አይጸጽተኝም አብይ ኬኛ ብዬ ለማውያን ኝ ድምጻችን ይሰማ ነኝ ብዬ መውጣቴ። ለዚህ ነው ሀምሌ 18 ለ19 አጥቢያ ወንበሩ ባዶ ሆኖ እንዳዬው ፈጣሪዬ የፈቀደው። ይሕንኑም ነግሬአችሁአለሁኝ።

ሌላውም በቅርቡ አቶ ሃይለማርያም ደስለኝ የቀበሩት አንድ በብረት ሳጥን ከጉድጓድ ካወጡ የተከረቸመ ዕውነት እንዳለም በህልሜ አይቻለሁኝ። ተከፍቶ አላዬሁትም። ሳጥኑን አውጥተው ሊከፍቱት ሲሰናዱ ግን በርቀት እብድ ስለመጣ ስሸሽ መጨረሻውን አላዬሁትም ምን አልባት ያ ቢከፈት ፍች አገኝ ነበር። ንጽሁ ልቡናን ፈጣሪ ያከብረዋል። ብዙ ነገር ይገልጽለታል። 

·       መከወኛ፡፤

„ሸወዱን“ የሚል በርከት ያለ ወገን አለ። አልሸወዱንም። ይህ ሊሆን ግድ ነበር። ይህ ምዕራፍ መኖሩ ለመልካም ነው። ያን ያደረገው ልዑል እግዚአብሄር ነው። ልዑል እግዚአብሄር ያን ያደረገበት የራሱ ምክንያት አለው። 

የኦሮማራ ጥምረት ዛሬን ሰጠን። በዚህ ውስጥ እነሱን ባናከበር ኖሮ ብለን አንጸጸትም። ከዚህ በላይ የኢትዮጵያዊነትን ክብር ግርማ እና ሞገስ አሳይተናቸዋል። የኢትዮጵያዊነት ፍቅራዊነት አሳይተናቸዋል። ኢትዮጵያዊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍ ብሎ ጎልቶ እንዲነገር እዬጠሉትም ቢሆን በአንደበታቸው እንደናገሩት አስደርገናል። ያን ያደረገው የፈጣሪ ሃይል ነበር።

እነሱ ደግሞ አቅማቸው ተፈትኗል። ኢትዮጵያን የጽዋ ማህበር አድርገው እያዬዩት ይመስላል። በዬዕለቱ ከሚወጣው መግለጫ እና የኮሜቴ ጋጋታ ስመለከተው አቅማቸው እየሳሳ መንገዱ እዬጠፋበት እንደሆነ ነው እማዬው።

 ይህ ደግሞ ተነሳነብት ካሉት ኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ጋር በውስጣቸው ግጭት በመፈጠሩ በራሳቸው ጊዜ ክብራቸው እዬተፈጠፈጠ ነው የሚገኘው። በራሳቸው ጊዜ ነው እራሳቸውን እያዋረዱ ነው የሚገኙት። ይህን ያደረገውም ፈጣሪ ነው። ሥልጣኑን አገኙ፤ እኛም እንዳይጸጽተን ደገፍናቸው እነሱም አለመቻላቸውን አረጋገጡ በአንድም በሌላም … 

ኢትዮጵያዊነት ነው ከማንም ከምንም በላይ እያዝረከረካቸው የሚገኘው። ወደፊት ደግሞ ያሸነፋቸዋል። አወዳደቃቸውም ለመጨረሻ ጊዜ ነው የሚሆነው። የቆሙበት መሬት ሽዋ ነው። ሽዋ አንድ ሆኖ የተነሳ ዕለት ሁሉም ያከተማል። 

አሁን እያቆለባበሱ የሚገኙት ሸዋ ነው። ለዚህ ነው አንቦ ላይ አዲስ ፕሮጀክት ባንነው የጀመሩት። ለዚህም ነው ባህርዳር ላይ ጠ/ሚር አብይ አህመድ የተገኙት። የሚይዙትን የሚጨብጥቱን ያሳጣቸው አፈር አለበሰነው ያሉት ኢትዮጵያዊነት ነው። የመሰቀል ደመራ ዝግጅትን በምልሰት መቃኘት ነው። በወታደር ጥበቃ ነበር የተከበረው።

የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ትዕግስቱ ሲያልቅ ፍቅሩን ስደት እንሚልክ ይታወቃል። ከሁሉ የሚከፋው ጭካኔ እና አረመኔነት ሜጫ እና ዱላ ይምራኝ የሚል አይሆንም። ኢትዮጵያ  መንግሥት በዓለም ከመሰረቱት አገሮች ቀደምት አገር የሆነች አላዛሯ ኢትዮጵያ የሰጠችውን ፈቃድ ትቀደዋለች፤ ፊርማ የለባትም ውል የለባትም። ስለምን? ትእግስት ሲያልቅ ፍቅር ስለሚሰደደ።

ከሁሉ የሚከፋው ጭካኔው አይደለም። ከጭካኔው በኋዋላ ለተጎዱ ወገኖች በሚደረሰው እርዳታ ማዕቀቡ የአረመኔነቱን ደንበር የሚያሳይ ስለሆነ የተጠናከረ፤ የተደራጀ፤ ከስሜታዊነት፤ ከጥላቻ፤ ከቁርሾ የወጣ ቅንነትን የሰነቀ የሰከነ በሳል ተጋድሎ ከተደረገ ተንሳፎ ያለ መንግሥት ነው የአብይ ካቢኔ፤ ገና እኮ ነው መሰረት አልያዘም።

ኦደፓ የሚመራው አገር ውስጥ በእሱ እርዳታ ባደራጀው የኦነግ ሠራዊት እና የሚመካው እኮ በቄሮ ነው። ቄሮ ደግሞ የምናውቀው ነው። በዬትኛው አቅሙ ማዕከላዊ መንግሥትን ማርበትበት ይችላል። ስለ ቄሮ ተጋኖ እንዲወራላቸው የሚፈልጉት ኦዴፓዎች ናቸው። በዚህ ማህል ኩዴታ ከመጣ ያልቅለታል።

https://www.satenaw.com/amharic/archives/64877

በመከላከያ ውስጥ ብሔርን ለማመጣጠን ታስቦ በተካሄደው አዲሱ ወታደራዊ ሪፎርም የተገኙ ውጤቶቹ በአጭሩ ሲዳሰሱ። የመከላከያ አራቱ ዕዞች:-

እርግጥ ነው አሁን ሳተናው ላይ እንዳነበብኩት በኦሮሞ አደራጅተውታል ጦር ሃይሉን። ነገር ግን ያ የህዝብ ማዕበልን አይገድብም።  የአንድ ቀን የዝምታ ውሎ ሁሉንም ይንደዋል። አዲስ አባባ በሰከነ የቁጣ የዝምታ ተከታታይ ቀናት ውስጥ ብትሆን ያበቀለታል። 

ኦዴፓ ለአዲስ አበቤ እንደማያዝንለት ማተብም እንዳልፈጠረለት የአዲስ አበባ ህዝብ አይቶታል። ልጆቹ ፍቅሬ አብይ ባሉ ማግስት ነው በአደባባይ የተጨፈጨፉት … አሁንም  በእጥፍ ድርብ እዬተሰናዱ ነው። አፍነው፤ አምቀው ለመቀጠል ሜጫቸውን ስለዋል።

አንሳፈፍነው የሚሉት ብአዴን፤ አጠቃነው የሚሉት ብአዴን፤ አንበረከክነው የሚሉት ብአዴን፤ በንቀት የሚመለከቱት ብአዴን ቢደክም ቢደክም ራሱን ለመከላክል አቅም አያጣም። ከግንባሩ የመውጣት ሁሉ አክሰስ አለው። መታመንን ላላከበር መተመንን መቀማት ነው። ከዛ ከታበዬበት አውልቆ የሚጥለውን እርምጃ መውሰድ።

ኦዴፓ የተጠለለው በአቶ ንጉሡ ጥላሁን ነው። እሳቸውን አውልቆ መጣል የመጀመሪያው ተግባሩ ሊሆን ይገባል ብአዴን።  ነገረ ንጉሡ ጥላሁን ለኢትዮጵያ የተላከ የማዕት ቦንብ፤ ጥቁር ቀን ናቸው። ብአዴን ያለበት ግማድ ሁሉ ከዚህ ጋር የተጠመደ ነው። ብዙ ጥምልምል ስርክርክ የሚሉ የፖለቲካ ማዕቶች ያሉት በዚህ ጃዋርውያን ነፍስ ውስጥ ነው። "ልብ ያለው ሸብ" እንደ ጎንደሮች።

ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር!

የኔዎቹ ኑሩልኝ። መሸቢያ ጊዜ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።