የለወጥ ሃሳብ እና ዘመነ ኦሮሙማ ...

 

እንኳን ወደ ከበቡሽ ሚዲያ በሰላም መጡልኝ።

 

ዕለተ ማክሰኞ ዕለተ ተናኜ

በከበቡሽ የቁራሽ እንጀራ ብራና

በሰብለ ህይወት አዝመራ

ለራህብ የሚራራ።

 

የለውጥ ሃሳብ።

          የለውጥ ሃሳብ ሂደትን 
               ማዕቀብ በመጣል ማስቆም

               ወይንም የታቆረ ማድረግ 
               አይቻልም። በፍጹም። 
               ተፈጥሯዊ ነውና!

 „በታካች ሰው እርሻ፤ አዕምሮ በጎደለው ሰው ወይን

 ቦታ አለፍሁ። እነሆም፣ ሁሉ እሾህ ሞልቶበታል፤

ፊቱንም ሳማ ሸፍኖታል። የድጋዩም ቅጥር ፈርሷል።“

   (መጸሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ ፳፬ ቁጥር ፴፩)





·       በር።

 

ለእኔ በማሰብ ልቅና የአስተሳሰብ ለውጥ ይመጣል ብዬ አምናለሁ። የነቃው የህሊና ክፍል አዲስ ሃሳብ ሲያፈልቅ ሃሳቡን የሚቀበል ህሊና፤ አዕምሮ ሊኖረው ይገባል። ይህ አዕምሮ ያፈለቀውን አዲስ ሃሳብ የሚመጥን የሰብዕና አቅም የሚኖረው ከአቅሙ ከራሱ በመመንጨቱ ነው።

 

አዲሱ ልቅና ያለው አስተሳሰብ/ ሃሳብ የትውስት ወይንም የብድር አይደለም። ስለምን? አዲሱ ዬአስተሳሰብ ልቅና ካለው ከራሱ ህሊና፤ የአዕምሮ የአቅም ፏፏቴ የመነጨ ስለሆነ ዲስፕሊኑን የመሸከም ብቻ ሳይሆን በቅጡ አደራጅቶ የመምራት፤ የማስተዳደር አቅሙ ተመጣጠኝ ነው።

 

.. ብቻም ሳይሆን ሚዛናዊነቱ በራሱ የአዕምሮ የውሃ ልክን የሚያስጠብቅ ተጠባባቂ የሃሳብ ማህበር ዘብም ይኖረዋል። ይህን ሃሳብ ከአቶ እስክንድር ነጋ የባልደራስ ለዕውነተኛ ዴሞክራሲ የመነሻ መርህ የካቴና ስንቅነት፤ እና በዬዘመኑ የአዲስ አስተሳሰብ ባለቤት ከሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው የማፈለቅ አቅም ኳራንቲ መግባት ጋር እስኪ አስሉት።

 

እንደገናም የማህበራዊ ንቃተ ህሊናው የመሸከም ዲስፕሊን አንጻር መዬት ይጠቅማል። ቀድሞ ነገር የኢትዮጵያ ፖለቲካ ማህበራዊ ንቃተ ህሊና አጀንዳው ሆኖ አያውቅም። መነሻ የሌለው መድረሻ ሲያልም የኖረ ልም።

·       ምጥነት።

 

የወገቡ ስፋት 35 ሴንቲሜትር የሆነ ልብስ የ52 ሴንቲሜትር ስፋት ያለው ልብስ ቢጠለቅለት መዋኛ ገንዳ ነው የሚሆነው። ወይንም 35 ሴንቲሜትር የወገብ ስፋት ላለው 10 ሴንቲሜትር ስፋት ያለው ልበስ ቢባልም ይሄም በጅ የሚል አይሆንም። አሁን የገዳ ኦሮሙማ  እና የምርኩዞቹ አዲሱ ችግርም ይሄው ነው።

 

ቢደረደሩ፤ ቢከመሩ፤ እንደ ተራራ ቢቆለሉ፤ አንደ አነባበሮ ቢነበባሩ ለጥ ብሎ በተኛው የዛገ ሃሳብ ውስጥ ከመዝገጥ በስተቀር ዘለግ ብለው የመታዬት አቅምም ወርድም የላቸውም። አዲሱን ሃሳብ የአዕምሮ ደረጃ የሚመጥን አዕምሮ የላቸውም። አንድ ሰው ቁመቱ የሚያድገው አስከ ተፈቀደለት ድረስ ነው። ያማ ባይሆን ሰማይ ጠቀስ ይሆን ነበር የሁላችንም ቁመት።

 

አሁን የእነሱ ገዳኢዝም በጎሳዊ ቀመር ፍልስፍና እደግ ተመንደግ እዬተባለ ነው። ግን ያረጠ ነው የ50በ60 ህልም። የነርብ ሲስተሙ ከዚህ በላይ መሄድ አይችልም። አቅም የለውም። ዘመኑን መሸከም አይችልም። ወይ ይፈነዳል ወይ እንደ ለመደበት ለሽ ብሎ ይተኛል። ይሄ ስለተባለ ሳይሆን የዕድገት ሂደት ነባራዊ ሁኔታዎችና ተፈጥሯዊነት የሚያስገደዱት ረቂቅ ህግ አለ። ይህን የእድገት ህግ በሰው እጅ አንቦልቡሎ ወይንም ጠፍጥፎ ማስኬድ አይቻልም። አዲስ ሃሳብ በራሱ አዕምሮ እድገት የሚፈጠር ብቻ ነውና።

 

እነ ማበህረ ደራጎን በሄሮድስ መለስ ዜናዊ አንቀልባ በአቶ ዬታቆረ ጥብቆ ህሊና ሊመጥነው በማይችል ቅዠት ውስጥ ሆነው እናያለን። ቅዠታቸውን ለማስቀጠል ያላቸው የአዕምሮ ብቃት አቅሙ አልተመጣጠነም። ያልገባቸው ጉዳይ ይሄ ነው። ስለዚህ ባነሰ ግምት ስድስት ዓይነት ጦርነቶች ተከፍቶባቸዋል።

 

አንደኛው፣ … የሻገተው አስተሳብን ለመሳቀጠል ያለ ከራሳቸውም ጋር ራሳቸው ጦርነት ውስጥ ይገኛሉ።

ሁለተኛው፣ …  በራሳቸው ማህበርተኛ ወስጥ የተፈጠረ አዲስ ሃሳብ አቅም አለ አስምጧቸዋል።

ሦስተኛው፣…  በሃሳብ ልዕልና በሚያምኑ አቅሞች ሙግቶችን የመቋመቋቋም ግብ ግብ ላይ ናቸው።

 

አራተኛው፣ … በራሱ በወያኔ ሃርነት ትግራይ ውስጥ የተከደነ የጦርነት ቀጠና ውስጥ የተጠለለ የዲፕሎማሲ ተጋድሎ አለ።

 

አምስተኛው፣ … ከሁሉም ያልሆነ ግን የመንፈስ አቅሙ ሙሉዑ የሆነ፤ ልኩ ያልታወቀ አቅም ልዩ ኃይል አለ፤ ይሄ „ጸጥተኛ ፤ ጭምታዊ ድምጽ silent majority“ የሚባለው።

 

ስድስተኛው፣ … የድሮ ዓለምዓቀፍ ወዳጆቻቸው ሂደቱን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪም በቅርበት እዬተከታተሉት መሆኑ ሌላው ፈተና ነው።

 

ለዚህ ሁሉ ፈተና የማህረ ሌንጮ ህልማቸውን የሚሸከም የአስተሳብ/ የሃሳብ፤ የሰብዕና፤ የአዕምሮ ደረጃው ነገቲብ ላይ ነው። የዛገ ብርት ዝግት እዬጨመረ በሄደ ቁጥር ቀለሙ ብቻ ሳይሆን አገልግሎት የመስጠት አቅሙም ያኑ ያህል እዬተፈረፈረ ይሄዳል። ቀብር።

 

በሂደቱ ራሱን መሸከም እያቃተው ለበለጠ ክስመቱ ሆነ ዕድሜ ማጠሩ እራሱን በራሱ ያጣፋል። በዚህ ማህል በተነደለ ቁጥር መወተፊያ የሆነው የለበጣ ግርዶሽ ገመናው የአደባባይ ሲሳይ መሆኑ አይቀሬ ይሆናል። እራሱ „የሞጋሳው ብልጽግና“ ሥርዓታዊ ጉባኤ የሚጀመርበት ቀን ሆነ የሂደቱ መለጠጥም ከዚህ የመነጨ የውልቅልቅ ምርተት ነው። በውስጡ ቀዝቃ የሆነ የፍርኃት እና የራድ ጦርነት አለ።

 

በዛገ እና በማረተ ሃሳብ ውስጥ አዲስ የሚፈጠር በውስጥ የሚበቅል ነገር አይኖርም። ባትሪው አልቋል ወይንም ተቃጥሏል፤ እድገቱ ቁሟል። ጊዜው አልፏል። ከዜሮ በታች ነው። ይህ ማለት ቀዝቅዟል - ዝቅ ባለው ዕሳቤ፤ ከፍ ሲል ደግሞ ግግር በረዶ ሆኗል። እንዲህ እንዲሆን ያደረገው የታሰረበት ንድፈ ሃሳባዊ የአደረጃት መርህ የቀደመ ዕድገትን እየፈራ ራሱን የካሮት ሥር ስላደረገው ነው።

 

ዘመን ጥሎት ያለፈው ጎሳዊ የሶሻሊዝም ቅሪተ አካል ሲፈርስ ከበላይ ነው። በዛ ላይ ዘመን የጣለው የተፋው ገዳ ሲታከልበት ደግሞ ድፍርስ ሞት ነው። ፍልስፍናው አንጡራ ጠላቱ የህሊና የአዕምሮ እድገት ፍቀት ወይንም ፍገት ነው። ህሊና አዕምሮ ሲያድግ የሚበልጥ ሃሳብ ስለሚያፈልቅ ሞቱ ስለመሆኑ ጠንቅቆ ያውቀዋል።

 

·                     ስለሆነም ከሞቱ በፊት አሟሟቱን የሚያበጅ ሳይሆን አሟሟቱን የሚያፋጥን ከይሲ ተግባራትን ከመፈጸም አይቆጠብም - የዛገው። የአስተሳሰብ ድህነት አለበታ! ስለሆነም የአስተሳስብ ድህነቱን ለመሸፈን ጭካኔው ሆነ አፈፃጸሙ የሚራው በደመንፈስ አዕምሮ ነው። ስለምን? መረጋጋት የሚያስችል እርሾ፣ ብጣቂ የሃሳብ አቅም ፍርፋሪ ስሌለለው። ፍርፋሪ አለ ከተባለ፤ ፍቅረ ንዋይ፤ ዝሙት፤ ጠበንጃ፤ የኢ-ሰብዕዊነት እርምጃ። አስከዛሬም ባለቀ ባትሪ እዬተገፋ ነው የተኖረው - ሪሞርኬ።

·         መጠበቅ። 

 

ዝገት ካለበት ከታቆረው ውስጥ ስለሆነ፤ እራሱን እያጠፋ ስለመሆኑ አይታዬውም። ዝገቱ ሆነ ምርተቱ ከውስጥ ነው። እርምጃው ውስጡን እያደሰ ወደ ፊት  በአሸናፊነት የሚያስገሰገስው ይመስለዋል። እእ።

 

ስለዚህ በህልም ሰረገላ ራሱን ኮፍሶ እያሰመጠው ነው የሚሄደው። በቆየበት ዘመን ሁሉ እዛው ላይ ሲዳክር ስለኖረ የሃሳብ ልቅና የፈለቀበትን አካባቢ ሊይ አያስችለውም። ግርዶሽ አለበት።

 

ግርዶሹ ራሱን እያታለለ መኖር እንደሚችል ግብረ ምላሽ ይሰጣዋል። የተነፋ ህልም። መቃተት። ለመጪው ጊዜያት በዓለም ከሚኖሩ ሁለት ኃያላን አንዷ ኢትዮጵያ ትሆናለች የህሊና ዱድማ ዳንቴል የጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድን ድውይ ዕሳቤም ከዚህ አንጻር ማዬት ይቻላል።

 

የፕሮፖጋንዳ መሳሪያዎቹ፤ የጸጥታ ማስከበሪያ ስልቶቹ፤ የደህንነት መዋቅሮቹ እነሱን እንዳሻቸው እንዲፏልሉ የሚያስችለው የኤኮኖሚ አቅም የሚፈጥሩለት መዋቅራዊ ሰንሰለቱ ቀን ሲያጡ እንደሚክዱት ወይንም ከአገልግሎት ውጪ እንደሚያደርጉት አያሰተውለውም የዘገው ዕሳቤ። በዘመነ ህወሃት የነበረው ዛሬ ተገልብጦ የሌላ ታንቡር መደላቂ ሆኗል። ነገም ይኽው ይቀጥላል። አያድኑትም!

 

አንድ አደጋ ያለበት አካባቢ ለማዬትም የሃሳብ አቅም ወይንም ድርጁ አዕምሮ ያስፈልገዋል። ሽሁራር በበላው ቸረቸራ አዲስ ጥንስስ አይጠነሰሰም። 

አሁን ግብ ግቡ „ዘመን“ „ታሪክ“ „ሁኔታን“ ያደመጠ አዲስ ሃሳብ ጎልቶ፤ ደርጅቶ፤ ጎልብቶ እንዲወጣ ማሰብ፤ ማሰብ፤ ማሰብ ያስፈልጋል እንደ አቶ ልደቱ አያሌው ህሊና። ለዚህ ነው ልደትን ተማሩት የምለው። ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ፈላስፋ ናቸውና አቶ ልደቱ አያሌው።

 

ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ የዛገው ሃሳብ ይህን አዲስ ሃሳብ ይዞ የወጣውን መንፈስ ጥሶ ለመውጣት አያስችለውም። ስለምን? መቀበልም እኮ አዕምሮ ሲኖር ነው። የተሟላ ሰብዕና ሲኖር ነው። አንጎል ብቻውን መኖሩ የአስተሳሰብ ድህነትን ሊከላ አይችልም። በፍጹም! አንጎልማ እንሰሳትም እኮ አላቸው አይደል? ለዚህ ነው የአቶ ልደቱ አያሌው ዘመኑን ያነነበ የሃሳብ ልቅና በጎን ሌላ ተፎካካሪ ተሰናዳለት በማዕከል ግዞት ተፈረደበት። እኔ የማህበራዊ ንቃተ ህሊና መሪ ነን የሚሉት ኩስምን ጥንዙል አቅም በዚህ ልክ ነው እማዬው።

 

አዲሱ ሃሳብ አዳጊ-  ተራማጅ እና ስልጡን ነው። ያሸትም። የልቅናው ምንጭ  ሰዓት ነው። ሰ ዓት ይለፍ ይሰጠዋል። ፈሪዎች ደግሞ ይጫኑታል፤ ይወሩታል፤ ይጠልፉታል ወይ ያግቱታል።

 

ነገር ግን አዲሱ ኃሳብ ሁሉጊዜ ያሽታል መቃብር ውስጥም ሆኖ። ይህ የሚሆነው የትውስት ውራጅ ሳይሆን በራሱ ህሊና የበቀለ ስለሆነ የራሱ ስልት እና ታክቲክ እየፈጠረ፤ ወቅቱን እያደመጠ በሄደ ቁጥር የፈለቀው አዲስ ሃሳብ እዬዳበረ፤ እያደገ፤ እዬጠነከረ የመሄድ ተስፋው የፋፋ ይሆናል። ይህ የፋፋ አዲስ ዕሳቤ ህሊናዊ ሂደት በራሱ የሚሰጠው፤ የሚፈጥረው ሌላ የሙቀት ስበት gravity ስበቃም አለው።

 

ለዚህ አዲስ ሃሳብ ከማረተው አስተሳሰብ አፈንግጠው የሚወጡ አዳዲስ ቡቃያዎች / ችግኞች በራሳቸው ጊዜ ይኖራሉ። እነዚህ ድርብ ግፊት እና ግጭት ሲፈጥሩ የማረተው ሃሳብ ቀስ እያለ አቅሙ እዬተሸበሸበ፤ ግርማው እዬሟሟ፤ ተስፋው እዬሸሸው ይሄዳል።

 

ትግሉ የአልሞትም ባይ ተጋዳይነትን ስለሚጨምር የሚያስከፍለው መስዋዕትነት የከፋ ይሆናል። ግን አዲሱ ሃሳብ በአዲስ አቅማዊ ስልትና ስትራቴጂ በጥበብ ስለሚመራ አሸናፊ መሆኑ አይቀሬ ነው። ይህ ስለተፈራ ነው አብሮነት የተሰረዘው በገዳ ምርጫ ቦርድ። አብሮነትን የገዳ ምርጫ ቦርድ በድፍረት እና በማናህሎኝነት ሲሰርዘው ኢትዮጵያን ሰርዟታል። ኢትዮጵያ መለያ ማልያዋ አብሮነት ነውና።

በሌላ በኩል አብሮነትን ተስፋ ያደረጉ መንፈሶች ሁሉ ጆኖሳይድ ተፈጽሞባቸዋል። አሰምሌሽንም ተፈጽሞባቸዋል። ይህ በጣም ረቂቅ አመክንዮ ነው። በ እኔ ውስጥ እኔ ስኖር ብቻ ነው ሊታዬኝ የሚችለው።

 

አንድ ኢትዮጵያዊ ተቋም ሲደረመስ በእኔ ውስጥ ያለችው መንፈስም አብሮ መደረመስ ታውጆበታል ማለት ነው። አብሮነት ጆኖሳይደ ሲካሄድበት እኔንም ይጨምራል። እኔ ተቋሜ ኢትዮጵያ ናት።

 

ኢትዮጵያ ደግሞ የ አብሮነት ማህደር ናት። ሥሙ ትውፊቴም ትሩፋቴም ነው። ትውፊቴን የፖለቲካ አመንዝራዋ የገዳ ልዕልት ወ/ት ብርቱካን ሚዲቅሳ ሲፈጽሙት በእኔንም ላይ ፍርዱ። እሳቸው 16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዛገው ገዳቸው ላይ ነው ያሉት እኛ ደግሞ 21ኛው ምዕተ ዓመት ሰውኛ እኛዊነት ላይ እንገናኛለን። መመጣጠን ያልቻልነውም በዚኸው አመክንዮ ነው።

 

ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት „ጸጥተኛ ድምጽ silent majority“ አባልተኞችም የቀና ቀን ጠባቂዎች ናቸው። ስብጥራቸው ሁሉንም የአቅም አይነት ያሟላ ነው። እነኝህ ከሁሉም ጋር ያልነበሩ ድርጁ መንፈሶች የበቃ የአቅም መቅኖ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው።

 

ለእነኝህም ተቋማቸው ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው። ስለዚህ እነኝህ ጨዋ ስኩን መንፈሶችም በድምጽ አልባው የገዳ የምርጫ ቦርድ ቦንብ ተደርምሰዋል። አስተካሿ ተኳሿም የገዳዋ ልዕልት ወ/ት ብርቱካን ሚዲቅሳ ናቸው። ጸረ አብሮነት። ጸረ የአማራ ሊቃናት ልቅና። ሴቶች ቂመኛ በቀለኛ ሲሆኑ ከማዬት በላይ የከረፋም የመገለም ነገር የለም። ይጎፈንናል። 

 

እኔን መሰል ነፍሶች የዛገው ሃሳብ የእኔ ሳይላቸው ረስቷቸው ወይንም ባሊህ ሳይላቸው የቆዩ በመሆኑ ባለቤት መሆን የሚችል አዲስ ሃሳብን ለመቀበል ንጹህ ሰሌዳ ናቸው ማለት ይቻላል።

 

የዚህ መንፈስ ቅን እና ንጽህና ያለው ስለሚሆን ወደ አዲሱ ሃሳብ የመጠቃለል ዝንባሌያቸው ሰፊ ነው። ለዚህ ነው ጭምት፤ የሰከኑ፤ በሳል ፖለቲከኞች የልደቱን ጎዳና በጥሞና እዬተከታተሉት የሚገኙት።

 

በፖለቲካ ሊቃናት ቃለ ምልልስም እስከ አሁን የሳቸውን ያህል በነፍስ ወከፍ አድማጭ ያገኜ አንድም የፖለቲካ መሪ የለም። ፖለቲካችን ከካድሬ ግርግር እና ኳኳቴ፤ ከፕሮፖጋንዳ ታንቡረኛ ወጥቶ ስክነት አስፈልጎኛል ወግዱልኝ እያለ ነው። ነፍስ ያለው ጆሮ ከተገኜ።

 

እኔ እንደማስበው እነዚህ መንፈሶች „ጸጥተኛ ጭምታዊነት ድምጽ silent majority“ ያልተነካ የአዕምሮ አዱኛ ያላቸው፤ በስብዕናቸውም አንቱ የሆኑ፤ አደብ የገዙ፤ ጭምቶች፤ የማይቸኩሉ፤ በቁጥርም ብዙኃን በመሆናቸው እጅግ ጠቃሚ ሃይሎች ናቸው።

 

በተለይ እነሱ መስጥረው የያዙትን ምኞት ጋር አዲሱ ሃሳብ ካፈለቀው „ከአዲሱ ሃሳብ“ ማህጸን ጋር ተመሳሳይ ወይንም ተቀራራቢ ከሆነ ለመጠቃለል ጊዜ አይፈጅባቸውም።

 

ምክንያቱም ጊዜና ወቅት ጠበቂዎች በመሆናቸው የተስፋ ዘበኞች ለመሆን ማቄን ጨርቄን ሳይሉ በቀጥታ አቅማቸውን ለአዲሱ አስተሳሰብ ይሰጣሉ። ያዘሉት፤ አሽኮኮ ያደረጉት ቅምጥ ሃሳብ ወይንም ጣዖት ሰብዕና የለምና።

 

„ጸጥተኛ ድምጽ silent majority“  ቅኖች ናቸው። ህሊናቸውን፤ ውስጣቸውን ብቻ ሳይሆን ሰብዕናቸውን ፈቅደው ይሸልማሉ።

 

ከዚህ ላይ አዲሱ ሃሳብ ለእነዚህ ንጹህ መንፈሶች የተለዬ ጥንቃቄ እና አያያዝ ለማድረግ በህሊናው ቃል ማሰር አለበት። ድምፃቸውን ሲያሰሙ የሚያደምጥበት ድርብ ጆሮ፤ ሰፊ ልቦና ሊኖረው ይገባል።

 

ስለምን? ዝምታን ሰንቆ የተቀመጠ አዕምሮ የአቅሙን ልክ፤ የባህሬውን ሁኔታ፤ የሚወስደውን የእርምጃ ዓይነት፤ የማስታዋሉን ልኬታ ኮቴ ማወቅ አይቻልም። የተከደነ ሲሳይ ነው። ናድ ብለው ከሄዱ አዳጋው ሰፊ ነው የሚሆነው። ፍቅር ሲያልቅ ትዕግስት ይሰደዳል እኔ የምለውም ለዚህ ነው። …

        

·         በጥበብ መከራን ስለመሻገር።

 

በዚህ ሂደት የቀደመው የዛገው ሃሳብ ከራሱም እያመለጡ በሚሄዱት፤ እንደገናም ባሊህ ብሏቸው የማያውቃቸው፤ ባለቤት ያልነበራቸው ህሊናዎች አብዛኛውን ቁጥር የያዙቱ በመሆናቸው ወደ አዲሱ አስተሳስብ ሲጠቃለሉ ከባህር የወጣ አሳ ይሆናል። ግማቱ ከአናቱ ይሆናል። የማረተው ወይንም የዛገው ሃሳብ ማህል ሜዳ ላይ አውላላ ሜዳ ላይ ተንገዋሎ ይቀራል።

 

በዚህ ወቅት የዛገው መንፈስ ስለሚወራጭ፤ ገርጭራጫም፤ ብስጩም ስለሚሆን የሚጠፉ ነፍሶች ስለሚኖሩ ሽግግሩን በቀላል መስዋዕትነት ለማድረግ „አደብ“ „ጭምትነት“ እንደ ፍልስፍና ሊወሰድ ይገባዋል። እያንዳንዱ መሬት ላይ ያለ ግለሰብ ሆነ ድርጅት ለራሱ ራሱ ዘበኛ / ተቆጣጣሪ/ ጠበቂ መሆን ይኖርበታል።

 

ማስተዋልን የህሊና መሪ ማድረግ ይገባል። ብልህነትን የሰብዕና አዕምሮ ማድረግ ያስፈልጋል። በተለይ የእኔ ብለው ሃሳብ ለሚሰነዝሩ ቅኖች ሰፊ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ንጹህ ልባቸውን ማሰረከብ ግድ ይላቸዋል። „እግዚአብሄር በአንድም በሌላም ይናገራል፤ ሰው ግን አያስተውለውም“

 

ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ እልህን/ ቁጣን ዋጥ አድርጎ መያዝ ያስፈልጋል። ህግ ተላላፊ መሆንም አይገባም። ባሩድን የተማመነ አውሬ በተፈለገው ጊዜ፤ የፈለገውን የማድረግ ኃይል አለው። በተለይ ሐገር ቤት ያሉት የሚናፍቁኝ ወገኖቼ ጥንቃቄያቸው ብልህ መሆን ይኖርበታል።

 

ከዚህ ጋር በተያያዘ በምግብ ብክለት፤ በመኪና አደጋ፤ በቤት ቃጠሎ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በተደራጀ ሁኔታ እርምጃ ሊኖር ይችላል። ስለሆነም በሁሉም ዘርፍ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል ወገኖቻችን። ትግሉ መጨረሻው ከማይታወቅ የክፋት ጉድጓድ ጋር ነውና … ከሲኦል ጋር … 

 

በዚህ ሂደት መጻፍ የሚፈልግ፤ ቃለ-ምልልስ ማድርግ የሚሻ ካለ የዓውደ ዓመት ዶሮ እንዳይሆን በትዕግስት የሚያልፋቸው ነገሮች ሊኖሩ ይገባል። ይህም ሆኖ የዛገው መንፈስ ጠብ አጫሪ እርምጃዎችን ሊወስድ ይችላል።

 

በገፍ የመጨፍጨፍ፤ የማሰር፤ የማሳደድ፤ የማፈን፤ የመሰወር፤ ቤት እዬገባ የመደብደብ፤ ባለፈም የመድፈር  ወዘተ … አቅም የለውም ብሎ መዘናጋት በፍጹም አይገባም። አቅም የአዕምሮ የሥነ - ልቦና ነው የሌለው፤ የጭካኔ እና የመሳሪያ መዋቅሩ የተለመደው በመዳፉ ነው።

 

ገፍቶ ከመጣ የማይቀረው ነገር ሊቀር እንዳማይችል የተፈጥሮ ግዴታ ቢሆንም፤ ግን በስልት፤ በጥበብ፤ በልበ ሰፊነት መያዙ መስዋዕትነቱን ይቀንሰዋል።

 

ምክንያቱም አሁን የግጭቱ ዓውድ አዲስ ሃሳብ ይዞ የተነሳ መንፈስ አለ። እንደ ድርጅት እንደ ግለሰብም። እንደ ግለሰብም አዳዲስ መሳጭ ሰብዕናዎች እያዬሁኝ ነው በተለይ ውጭ አገር። ዕጹብ የሆነ ድንቅነት። መስጥም ግዝትም ንድትም የሚያደርግ ድንግል ሞጋች እጬጌው ሂደት የሸለመን ይመስለኛል።

 

ወደ ቀደመው ሃሳቤ ስመለስ የዛገው ሃሳብ የጦርነቱ መስክ መሰረት ከሆነው ጠላቴ ያለውን ማህበረሰብ እና ሃይማኖት በተጠናከረ ሁኔታ ጥቃት በመሰንዘር የአቅጣጫ ለውጥ በጫና ማምጣት ግቡ ይሆናል። ሂደቱ እጅግ የታመመ በመሆኑ ጥንቃቄ የሁሉም ዜጋ ሊሆን ይገባል።

 

የልተገባ እልህ አስፈላጊ አይደለም። አይዟችሁ የሚል መንግሥት በሌለበት ሐገር የሚኖረው የኢትዮጵያ ህዝብ ጥጉ ፈጣሪው በመሆኑ ሁሉም እንደ ዕምነቱ በጸሎት ከፈጣሪው ጋር መተሳስር ያስፍልገዋል። የተደሞ ጊዜ ነው። የጥሞና ጊዜ። የወል የመከራ ጊዜ ነው። የዕንባ ወቅት ነው።

 

የዛገው የጉራጁ ኢህዴግ ኦህዴድ የማረቱ ምርኩዞቹ የዚህን የአዲስ ዘመን መንፈስ ሰላሙን በማወክ ትንፋሹን ማባከን ቀዳሚው መስካቸው ነው። የማያዋቀው ነገር ግን የአዲስ ሃሳብን ሂደት ማስቆም ቀርቶ መገደብ አለመቻሉ ነው። አንድ ጊዜ ተፈጥሯል። እንደ ጉርሻ ዋጥ ተደርጎ ጸጥ የሚባልበት አይሆንም። አዲስ ሃሳብ ምጡ እስኪ ወለድ ድረስ ነው። ከተወለደ በኋዋላ ግን በራሱ ጊዜ እድገቱን መቀጠሉ የተፈጥሮ ህጉ ነው።

 

አንድ በህክምና ዶር. የተመረቀ ሰው በዕወቀቱ ላይ የተለዬ ስልጠና እዬወሰደ ያዳብረዋል እንጂ እንደገና ወርዶ 7ኛ ክፍል ላይ ስለተፈጥሮ ሳይንስ ልማር አይልም። ምክንያቱም አቅም ፈጣሪው አዕምሮ ወደላይ ከመዝለቅ በስተቀር ወደ ታጅ መውረድን ስለማይፈቅድለት።

 

አሁን ያለውን ቡቃያ የለወጥ መሻት በዛገ የምርኩዝ ጋጋታ፤ በወዬበ ኳኳቴ በፈለገው ዓይነት መጠራቅቅ መቋቋም አይችልም የአዳማ ሥርዕዎ መንግሥት። ይህ የለውጥ መንፈስ ከብሄራዊ አልፎ፤ አህጉራዊና ዓለምዓቀፋዊ ጫናም ፈጥሯል። ረቂቅ ነው። የፈጠረው ጫና በፍጹም ሁኔታ ኦህዴድ በሚያስበው መልክ በግርድፍ የሚሾከሾክ የገብስ ቆሎ አይደለም። በፍጹም።

 

·       መታዬት።

 

የዛገው ሙጣጭ ሃሳብ አዲሱን የለውጥ መንፈስን መቀበል ብቻ ሳይሆን ከአዲሱ መንፈስ ጋር ለመቀጠል እንኳን በግትርነት የሚሆን አይሆንም። የሚመጥን የአዕምሮ ብቃት፤ የሰብዕና ንጽህና፤ የሥነ - ምግባር ሞራል፤ የሥርዓት መዋቅራዊ ደርጁነት የለውም። ያስፈራውም ይሄው ነው። ቀውስ ባጀቱ የሆነውም ለዚህ ነው።

 

አሁን ኢትጵያ ከዬትኛውም ፍልስፍና ያፈነገጠ እና የወጣ ተፈጥሯዊነትን አቤት! ወዴት! ያለ አዲስ የሃሳብ ልቅና ላይ መገኜትን ትሻለች። ይህ ስለፈለገችው ሳይሆን የ21ኛው ምዕተ ዓመት ግሎባል ስጦታዋ ነው።

 

ስለሆነም ከአራዊት መንጋ፤ ከዘረፋ ጅረት፤ ከደም ማፈሰስ ሱስ፤ ከመስፋፋት ትዕቢት፤ የምትላቀቅበት አዲስ የሃሳብ ዓዕማደ ተስፋ ላይ ናት ባልልም በሃሳብ የላቁ ሰብዕናዎች ግን አያለሁኝ። ይህን የሃሳብ ቡቃያ የመሸከም አቅም የለውም እንኩቶው የዛገው የ50በ60 አዲሱ አብይዝም። ያረጠ ነው። ልማር ልስተካከል ከአረንቋ ልውጣ ካለ ድሪቶውን ሙጃውን አስወግዶ አዲስ ጆሮ ይግዛ።

 

የዓለም መርህ ያለው የሰዋዊነት መንፈስ ላይ ነው። ሰው መሆን! ለሰውነት ጠበቃ፤ ጋሻ፤ መከታ መሆን! ሰውን እንደ እንሰሳ የሚያታይበት፤ ሰውን እንደ ግዑዝ ከረጢት ነገር የሚታሰርበት - የሚፈታበት፤ ሰውን በጅራፍ ተዘቅዝቆ ታስሮ የሚቀጣበት፤ በራስ ወገን የመርዝ መፈተኛ የሚሆንበት፤ ሰው እንደ በግ የሚሸለትበት ዘመን በማክተም እና ለማስቀጠል በሚባዝኑ የመንፈስ ደኃወች መሃከል ነው ጦርነቱ።

 

ቀደም ባለው ጊዜ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ይውደቅ እንጂ ከዛ በኋዋላ ችግር የለም የሚሉ አመክንዮዎች በርካታ ስለነበሩ፤ መንፈስን ጥግ ለመስጠት አልተቻለም ነበር። አስፊሪ የሆኑ የጨለማ አምክንዮች ነበሩ።

 

አሁን ነገስ ምን? ለሚለው አስከ ታች ድረስ አቅም እያበቀለ፤ አቅምን በብቃት ኮትኩቶ እያበቃ የመጣ ድርጁ ኢትዮጵያዊ መንፈስ አለን ወይ ይህም ሌላ ሞጋች አምክንዮ ነው። ቢኖርስ ይፈቀድለታል ወይ?

 

ለዚህ አቶ ልደቱ አያሌው እና ድርጅታቸው ኢዴፓ፤ ኢንጂነር ይልቃል እና ኢኃን ውጥኑ፤ የሁሉቱ ጥምረት አብሮነት እንቅፋቱን ማጥናት ይገባል።

 

በሌላ በኩል የተግባር ተክልል የአቶ እስክንድር ነጋ እና የቲሙ ካቴና ሁኔታ በልባምነት ማስተዋል ይገባል። ይህ የአቅም ተከታታይነት በተጠባባቂ አቅም በሙሉ ስብዕና የተገነባ ሊሆን ይገባል። ይህን አቅም ተተኪ አልባ ለማድረግ ያለው ቁልፍልፍ ነገር በዘመነ ህወሃት ከነበረው የአሁኑ እጅግ የከፋ ነው ጥልፍልፍ ነው። የኃይል አሰላለፉ ስብጥር ስንቅር ነወ። ለዚህ ነው ብዙውን ጊዜ በዝምታ እማልፈው።

 

አንድ ሰው ቢወድቅ ሌላ ተተኪ ብቃት ያለው ሊኖረው ይገባል። አንድ ሰው አቅም አንዲኖረው እርስ በርሳቸው ረቂቅ በሆኑ፤ ዘመኑ በሚጠይቃቸው መስመራዊ፤ መንፈሳዊ፤ ሞራላዊ፤ ሰዋዊ፤ እኛዊ መሠረት ያዬዘ ዲስፕሊናዊ አቅም አለን ለማለት የዛን ባለ አቅም ዲስፕሊን ሊሸከም የሚችል አለን ወይ ብሎ መጠዬቅ የህሊናዊነት ጉዳይ ነው።

 

በሌላ በኩል የኦሮሞ ፕሮቴስት እና የአማራ የህልውና ተጋድሎ ዕውቅን በመስጠት ረገድ የነበረው ዝበት አሁን ሚዛኑ ተቀብሯል። የዚህ ሚዛን አለመጠበቁ ሌላ አገርን አደጋ ላይ የጣለ ሰቆቃ ላይ እንገኛልን። ኦሮማራ ኢትዮጵያን የመምራት አቅም ሳይኖረው ነበር አቅም የለገስነው።

 

ቅደመ ሁኔታም አላበጀነም፤ ውልም አልሰራልነትም ነበር። በተጠቅለል ተጥቅሎ የገማ እንቁላል ሆነ። ወይ እሱ ወይ ኢትዮጵያ ሊተርፉ አልቻሉም። ያ ሁሉ ግሎባል ድካም ለማህበረ ሌንጮወሻቢያ መደንከሪያ ሆነ። ዜጎች በአገራቸው ላይ የመኖር ዋስትናቸው አጡ።

 

በራሱ ጊዜ የበቀለው የተስፋ አቅም ሙት በቃ ተፈርዶበታል። በገማ እንቁላል ላይ ተስፋን ማጨት ስላማይቻል። በዚህ ውስጥ የስሜን ፖለቲካ ድቀት እና  የኢትዮጵያም ተስፋ በማስቀጠል ቀርቶ ከዚህ ለመነሳትም ፈጽሞ ያልተደፈረ አመክንዮ ነው። ይህም ብቻ አይደለም የቅድስት ተዋህዶ መከራ እና ከፖለቲካውም ከአገሯም መሰደድም ሌላው የመከራው መንኮራኩር ነው።

 

የጥገና ለውጡ በራሱ ተጋድሎውን የመሸከም አቅም አምጦ ሊወልድ ግድ ይለው ነበር። ግን ካለ አቅሙ በተለጠጠው ተቃባይነት በራሱ ጊዜ ዳጥ ውስጥ ነው የወደቀው። ተባባረን ያስወገድነው ሥርዓት ከእነ ሙሉ መዋቅሩ ለማስቀጠል ያለው ፋታ የለሽ ግብግብ የነገን ተስፋ ያረግበዋል።

 

በተለይ በተፎካካሪ ጎራ ያሉት የአማራ ሊቃናት የገነቧቸው የፖለቲካ ድርጅቶች በዓዋጅ በገዳዋ እቴጌ ወ/ት ብርቱካን ሚዲቅሳ የፖለቲካ አመንዝራነት መቃብር ተልከዋል። በአማራ ተጋድሎ ከተቀቀሉት ማህበረሰቦች ጎልተው የሚታዩ አንድም የአማራ ሊቃናት ወደ ቀጣዩ የምርጫ ውድድር አይገቡም። ጎንደር፤ ጎጃም በልሙጥነት። በገፍ መከራ የተቀበሉ ማህበረሰቦች።

 

20ሺህ እስረኞችን ያሰተናገዱ ባዕቶች። ይሄ በመደዴ ሊታለፍ የሚገባው አመክንዮ አይደለም። ተጥቅልሎ ወይንም ተደብልብሎም ማለፍ አይችልም። ፈጽሞ። ምንጥር ተደርገው ከጨዋታ ውጪ ነው የተደረጉት። እስከ ፈጠራ ልቅናቸው ድረስ።

 

ይህ ደግሞ የተስፋ መውደቅ ምልክት ነው። የአማራ ኦርቶዶክሳውያን የፖለቲካ ሊቃናትን ያገለለው አዲሱ የገዳ ምርጫ ቦርድ ጽልመታዊ ጉዞ ኢትዮጵያን ማቅ እያለበሳት ነው። ድቅድቅ ጨለማ ውስጥም ከቷቷል። የዳግሚያ ጉዲት ዩዲት ዘመን ልንለው እንችላለን።

 

የስሜን ፖለቲካ በማግለል ዘመቻ ላይ እዬኳተነ የሚገኜው የኦዳ ሥሯወ መንግሥት እና የገዳ ምርጫ ቦርድ ሂደቱ በአንድ እጅ ማጨብጨብ ነው የሚሆነው።

 

ይህ የተመጣጠነ የመንፈስ መግባባት በዛገው ብረትም የፈጠረው ድንጋጤ ስለ አለ ነው አቶ ልደቱ አያሌው፤ አቶ እስክንድር ነጋ፤ ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት የታሠሩት። አሁንም እኔ ተፈቱ አልልም። በዚህ ውስጥ የዶር ደስ አለኝ ጫኔ በፈቃድ ከሰልጣን መወገድም ሌላው ትራጀዲ ነው። ኦርቶዶክስ እና ተዋህዶ ከፖለቲካ ለማውጣት ያለው ረቂቅ ዘመቻ የተሳካ ቢመስልም እነኝህ ኃይሎች  „ጸጥተኛ ፤ ጭምታዊ ድምጽ silent majority“ የሚባለው ውስጥ ቀላል የማይባል ኃይል እኔን ጨምሮ እንዳላቸው አይታወቅም።

 

የአማራ የህልውና ተጋድሎ መስዋዕትነቱ ዕውቅና እንዳያገኝ ከወያኔ ባላነሰ ውጪ ሐገርም ሰፊ ፈተና ነበር። ዛሬም። የአማራ የህልውና ተጋድሎ እጅግ በተሻለ ሁኔታ ግራ ቀኝ እስሩን ጥሶ ወጥቶ እኩል እውቅናውን ማስጠበቅ ቢቻልም ይህን ዲስፕሊን ከግርግር ፖለቲካ አውጥቶ ስኩን ድል ያገኝ ዘንድ ያለው ተስፋ ግን ሙቀቱን ለመለካት ጊዜ የሚጠይቅ ይመስለኝ።

 

በአደባባይ ከሚሰሙትም፤ ከሚደመጡትም በላይ ያሉ ረቂቅ የመንፈስ ሃብቶች አሉት ተጋድሎው። ስለምን? አዲሱ ሃሳብ ስለነገ ያለው ዕይታ ያልደፈረሰ፤ ያልተስረከረከ ግልጽና ቁልጭ ያለ በመሆኑ ምክንያት አቅሙን አቅም ለማድረግ በቅርበት ውህድነትን ዘመን በራሱ ጊዜ፤ ፈጣሪ አምላክም በኪነ - ጥበቡ ስለባረከው። ይህ ማለት ግን ዲስፕሊኑን መሸከም ካልተቻለ ያ ቅምጥ ኃይል ልቦናው ሊሸፍት ይችላል። ሊበተነም። እኔን ጨምሮ።

 

የሆነ ሆኖ ከዚህ አፈንግጦ የዛገው ብረት በማረተ ሃሳብ ጊዜውን በጅ በለኝ ቢለው ብዙም የሚያወላደው አይሆንም። ጅው ወደ አለው ገደል ራሱን የሚለቀው ራሱ ይሆናል።

 

ቅራኔው እዬተካረረ፤ እዬተወጠረ በሄደ ቁጥር በራሱ ነፍሶች ላይ የዘለዓለም የበቀል ስንቅ ተክሎ ያሸልባል። ትናንት ዛሬ እንዳልሆነ ሁሉ ነገም በራሱ ቀን ስለሚመጣ ዛሬ ሊሆን አይችልም።

 

·       ነፃ የወጣ ኢትዮጵያዊ የአዕምሮ ነፃነት!

 

ሃሳብ ነፃ የወጣ ነፃ የአዕምሮ ነፃነት ነው። ነፃ የወጣ ስል የአዕምሮ ነፃነቱ የትውስት ሰብዕናን፤ የትውስት ፍልስፍናን፤ የትውስት አቅምን፤ በትውስት አዕምሮ የተፈጠረ ንድፈ ሃሳባዊ ቀመርን በፍጹም ሁኔታ የተጸዬፈ ነው።

በአካልም በመንፈሰም የዬትኛውንም ሐገር ፍልስፍና ወይንም የኤኮኖሚ አቅም፤ ወይንም የዲፕሎማሲ ጫና አልሞ የተነሳ አይደለም የራስ አቅም።

 

 ይህ ራሱን ችሎ በራሱ ጊዜ ነፃነቱን አውጆ የተነሳው ሃሳብ በቀጥታ የ21ኛው ምዕተ ዓመት ወዳጅ የሆነውን ሰዋዊነት፤ ተፈጥሯዊነት ኢትዮጵያዊ ቀለም ሰጥቶ የተነሳ ከሆነ ስለሰው ግድ የሚላቸው፤ ስለተፈጥሮ ግድ የሚላቸው ባለ አዕምሮችን ቀልብ ሲስብ ፕሮፓጋንዲስት ወይንም ቀስቃሽ ወይንም በፕሬስ ውደሳ ተቀባይነቱ ጥገኛ አይሆኑም። ጥራት ያላቸው ማስተዋሎች ብቻ ይደግፉታል። ያ ደግሞ ለግብ ያበቃል።

 

ዛሬ ሁሉንም በጋራ የሚያገናኘው አንድ ተፈጥሯዊ መርህ አለ ሰብዕዊነት። ከብዙ ቅን መንፈሶች ጋር የተሰራው ሃዲድም በዚህ መስመር ነው።

 

አንደኛ … በራስ ወገን የታሰብ ከሆነ፤

ሁለተኛ … አቅሙ ስፋቱና መጠኑ ባለጥሪት ከሆነ፤

ሦስተኛ … ከማንም እና ከምንም ከዬትኛውም ሐገር የውለታ ጥገኝነት የሌለበት ከሆኑ።

አራተኛ … ሁሉንም በአኩልነት በእቅፉ ለማድረግ ከልቡ ከፈቀደ፤

አምስተኛ … ተረስተው፤ ተዘንግተው የኖርትን ሁሉ ፍቅርን በገፍ ከሰጠ። ስድስተኛ … ነገስ ለሚለው አደራውን ለመወጣት ያለው የህሊናው መሳናዷዊ አቅሙ ሙሉዑ ከሆነ፤

ሰባተኛ ሲጠልፉ ሲያነቅዙ ለኖሩት ጠለፋ ካልተመቼ፤

ከሁሉ በላይ ኢትዮጵያን ከነክብሯ፤ ከነግርማ ሞገሷ የእኔ ብሎ ከሚስጢሯ ከተነሳ ለቅኖች ቅደመ ሁኔታ ሳያሰኛቸው በመንፈሱ ተስፋን እንዲሰንቁ ያደርጋቸዋል።  

·       መውጫ።

 

ጊዜ እና ቦታ፤ ሁኔታ እና ዕድል የሚነሱትም የሚያሳጡትም አለ።  … ያ እንዳለፈው ሁሉ ይህም ያልፋል። ሲሞላም ይፈሳል ሲከርም ይበጣሳል። እጬጌው ሂደትን ጠብቀኝ ማለት አይቻልም፤ አብሮ መጓዝ ብቻ ነው ምርጫው።

 

በስተቀር መንጠባጠቡ በመፈጥፈጥ ይሆናል። ሰማይን ንጋት እንዳይሰጥ የሚያደርግ ወይንም ጸሐይ ብርሃን እንዳትሰጥ የሚያደርግ የተፈጥሮ ህግ የለም።

ህግ ጣሹ በህግ ጥሰቱ ውስጥ ራሱን ጥሶ ግብዕቱን ይፈጽማል።

 

በዚህ አሰልቺ በሆነ ደንዛዛ አቅም - ጊዜ  - ማቃጠሉ ቅራኔውን ቢያባብሰው እንጂ ሊፈታው አይችልም። ጨው ለራስህ ብትል … ይብቃኝ እነ እንቅልፍ ከተለመደው የሄሮድስ መለስ አንቀልባ ጋር አንጎላቹ … ፍዝ።

 

ትንሽ ስለነገ ስላልተፈጠሩት የትግራይ ህፃናት የማታስቡ የግዴለሾች ናችሁ እላቸው ነበር ህወሃቶችን፤ ይህን አመክንኞ እኔ በጽሞና ያስገንዝብኳችሁን ስላልፈጸማቸውሁ ድቀት እና አመድ ማፈስ ለዛ ህዝብ እንሆ ሆነ።

ነገም የኦሮሞ ህዝብ ዕጣ ክፍሉ ይኸው ይሆናል። እርግጥ ነው አዲስ እሸት ዕሳቤ ይዘው የተነሱ ሞጋች ሰብዕናዎች አያለሁኝ ከ ኦሮሞ ማህበረሰብ። ይህ በጣም ወቅታዊ ልባም እርምጃ ነው። አብይዝም ሌንጮዊዝም አይወክለኝም ብሎ ደፍሮ የወጣ ብቃት፤ ልቅናውን ለመግለጽ አቅም እስኪያንስ ድረስ ምስባክ ክሰተት የሆነ አንበሶች እያዬሁ ነው።

 

ኢትዮጵያን ያመሷት ህዝቃዬሊዝም፤ ጃዋርይዝም፤ ለማይዝም፤ በቀለይዚም፤ ጉዲናይዚም፤ አራራሳይዝም ሁሉ ከማይችለው ፈተና ውስጥ ላይ ነው የሚገኙት። ቅባዕውም፤ ርጋታውም፤ ክህሎቱም የ ኢትዮጵያዊነቱም ህብራዊ ቀለሙም፤ የርህርህናው ዲካም የሰማዬ ሰማያት ነው።

 

ይህን መሰል የሰማይ ሽልማት በዘመነ ተጋሩ አይደለም በማለዳ በበሰበሰበት  ሰዓት እንኳን አላዬሁም ነበር። ይህ የስጦታ አቅምም ቢሆኑ ባለው ነገር ላይ በቁንጣ ቁንጢ ንትርክ ጊዜያቸውን ካቃጠሉ መዳኛው ከባድ ነው።

 

በፍጥነት የተደራጀ ሊሠሩ፤ ሊሆኑ የሚገባቸው የተግባር ማሳዎች ሊኖሩ ይገባል። በምን? እንዴት? የት? መልስ መሰጠት ግድ ይላል … በዞግ ሶሻሊዝም በገዳ የጨለማ ጉዞ ብቻ ሳይሆን ገደልም ላይ ነው ያለችው ኢትዮጵያ። እናት ኢትዮጵያ አሳቻ መንገድ ላይ ናት። አብሮ ከመከስከስ በስተዋል ፍጥነትን መጥለፍ።

 

·         ማስታወሻ።

 

ይህ ፎቶዬ የልጅነቴ ነው። በዚህ ዕድሜ ትልቅ ኃላፊነት ነበረኝ። በዚህ ኃላፊነቴ ውስጥ የነበረኝ ስክነት ይገርመኛል። ማትራሰ ነፍቼ ቢሮዬ ነበር እማድረው። እጅግ ለሰማይ እና ለምድር የከበዱ ሊቀ - ሊቃናት ለ ኔ ፖለቲካ ሰብዕና ደክመዋል። ለፍተዋል። ብርቅ ነበርኩኝ። ሥራ አገሬ ነው። ትናንትም ዛሬም። ከወጣትነቴ ጋር ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮ በሰጠኝ ጸጋ ደስታን በማራቅ ግዴታን መወጣት በሚል ተላለፈን። ወጣትነት እና ጉልምስና ምን ያህል ይመጣጠኑ ይሆን? ጹሑፉን ለኩት እና በይኑት ቅኖቹ አዱኛዎቼ።

ሮቡ ዕለተ ተናኜ እንዲህ ዓይነት ስክን ያሉ ጹሑፎችን እምናይበት ነው።

 

ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር!

የኔዎቹ ለዘንካታ አድማጭነታቸሁ ፍቅርን በአክብሮትን ልሸልም።

እግዚአብሄር ይስጥልኝ። መሸቢያ ጊዜ።

 

ከሥርጉተ©ሥላሴ (Sergute©Sselassie)

 24.02.2021 (ከጭምቷ - ሲዊዘርላንድ ከደልዳዋ ደርባበዋ ቪንቲዬ)


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።