የባህር በር ጥያቄ 100% #የእኔም ነው። የወደብ ጥያቄ 100% #የኔም ነው። ጥያቄው #የሚሊዮኖችም ነው።

 

 May be an image of map and text that says 'Khartoum@ ERITREA Asmara SUDAN DJIBOUTI @Djibouti Addis Ababa Vatiley ETHIOPIA RAITI @Hargeisa SOMALILAND UGAND Kam SOMALIA KEN Lake EVicton Victon RWANDA Mogadishu BURUNDI 589501 INDIAN OCEAN TANZANIA Dar TANZANIA@DarEsSalam DarEsSalaam Dar Es Salaam'
 

የባህር በር ጥያቄ 100% #የእኔም ነው። የወደብ ጥያቄ 100% #የኔም ነው። ጥያቄው #የሚሊዮኖችም ነው።
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 
 
ሰሞኑን ከኤርትራ መንግሥት በሚሰጡ መግለጫወች ዕድምታቸውን ሳጠና የባህር በር ጥያቄ፤ የወደብ ጥያቄ የኢትዮጵያ ተፈላጊ እና የህልውና ጥያቄ ሊሆን የማይችል፤ የኢትዮጵያ ዜጎች ጥያቄም እንዳልሆነ፤ የአብይዝም ሰብዕና ሌጋሲ አስቀጣይ እንደሆነም የሚገልጽ ዓይነት ነው። እንደዚህ የኤርትራ መንግሥት ባያስብ ጥሩ ነው። የአንድን የነፃነት የፊደል ገበታ የሆነችን አገር ብሄራዊ ጥያቄ ከደረጃ በታች ባያወርዱት ጥሩ ነው፤ የኤርትራ መንግሥት ሊቃናት እና ደጋፊ ወገኖች። በኢትዮጵያ ሥም ያሉ፤ ለኤርትራ መንግሥት የበለጠ የሚሳሱ ሰብዕናወችን ሳይ በውነት አዝንላቸዋለሁኝ። 
 
በዘመነ ህወሃት የወልቃይት፤ ጠገዴ ጥያቄ ሲነሳ አንድነት ፓርቲን የተቀላቀሉ የአማርኛ ቋንቋ ሊቅ ተጋሩ ይህ "የገብያ ግርግር ነው። 100% "የአማራ ሊቃናትም የማይገዙት ነው" ብለው በሰጡት መግለጫ ማንነት በገብያ ህግ የማይተደደር ነው፤ ምክንያት ማንነት ሸቅጥ ስላልሆነ በሚል ሞግቻቸው ነበር። ዛሬ ላይ ሆነው ሲዩት የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ ከኢትዮጵያም አልፎ #ቀጠናዊ ዘውድ ደፍቷል። 
 
ደክሜበታለሁኝ። ተመስገንም ብያለሁኝ። ዛሬ ያ ቀጠና ሰላሙ ተረጋግቶ እፎይ ብሏል። " አድርገህልኛል እና አመሰግንኃለሁኝ"
ስንት ነፍስ የተገበረበት፤ ስንት መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰበት የቀይ ባህር ወሳኝ ቀንድነታችን ጉዳይ፤ #ተዘግቶ የቆዬን አጀንዳ ይለፍልህ ብለው // ይለፍ የሰጡት ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ናቸው። በፋኖ ጠንካራ ንቅናቄ ጋር ተያይዞ የመጣ ውሳኔ ነው። ብሄራዊ ስሜትን የመሸከም ለዛም ሰማዕት የመሆን አቅም ያለው የአማራ ህዝብ ከፋኝ ብሎ ወደ ጫካ ሲተም በአቀለሉት ልክ አለመሆኑን ሲገነዘቡ፤ ይህን አጀንዳ አጎልብተው አመጡት። በነገረ ኢትዮጵያ ላይ የአማራ ህዝብ እንደ ህዝብ ቦርቧራ፤ ገራገር ነውና። 
 
እርግጥ ነው ልብ ልንለው የሚገባው ጉዳይ፤ ከዛ ቀድሞ #የባህር ሃይል ጉዳይ ለዶር አብይ አህመድ አጀንዳቸው ሆኖ እንደነበር አስታውሳለሁኝ። የባህር በር ለተጨማሪ የተፈጥሮ አደጋም ዘብ አደርም ነው። የሆነ ሆኖ ዶር አብይ ይህን በኽረ ጉዳይ ፖለቲካቸውን ለማረጋጋት፤ የአሻራ ምዕራፋቸውን አቅም ለመመገብ፤ የታሪካቸውን ዝክረ ነገረ ታኮ እንዲኖረው ለማድረግ ፈልገው ሊሆን ይቻሉም/// አይቻሉም የኢትዮጵያ የባህር በር/// የኢትዮጵያ የወደብ ጉዳይ የእኔም የህሊናዬ ቁልፍ ጉዳዬ ነው። የእኔም ነው። 
 
እኔ አፈፃጸሙ ላይ #በሰላማዊ ሁነት፤ በሰፋ በታገሰ ጎዳና፤ አቅል ባለው በሳል #የዲፕሎማሲ ተግባር እንጂ በጦርነት ሊሆን አይገባም ነው ጉዳዬ። የወሎ፤ የጎንደር፤ የትግራይ፤ የኤርትራ እናቶች በጦርነት ነው የኖሩት። ይበቃቸዋል ጦርነት። እርግጥ ነው አሁን ባለው የኤርትራ መንግሥት እና የኢትዮጵያ መንግሥት መፈራቀቅ ጥያቄውን፤ በንግግር የመፍታት ተስፋው ብዙ ላይሆን ይችላል። እኔ ግን "ለእግዚአብሄር የሚሳነው የለም" ባይ ነኝ። የበርሊን ግንብ እኮ #በጎርባቾቢዝም መልካም ፈቃድ ፈርሶ ጀርመን ከኃያሎች ጎራ ናት በአሁኑ ዘመን ያለችው። የብዙ የተከፋ የሌላ አገር ዜጎችም መጠጊያ። ሶሪያውያን እኮ በሚሊዮን ነው መኖራቸውን የተሸለሙት። 
 
እኔ በውስጤ ኤርትራን አግልዬ አላውቅም። ኤርትራን አሳንሼ ወይንም አጣጥዬ፤ ወይንም አቃልዬም አላውቅም። ለምን? ኤርትራ ልዑአላዊ አገር በአሁኑ ጊዜ ብትሆንም የእኔ ነበረች፤ አማኑኤል ሲፈቅድልን ፖለቲካ ሰራሹ ልዩነት ሲናድ የተሰጠን ብዙ መልካም ነገር አለና በዛ አቅም የአህጉር ያክል ተፎካካሪ ሆኖ የመውጣት ዕድል ይኖራል የሚል ተስፈኛ ነኝ። ተስፋ - አያልቅምና። ተስፋም - ከእግዚአብሄር ዘንድ ነውና። ብልህ፥ አርቆ የሚያስብ የፖለቲካ ቲም አለመኖር ነው ይህ ሁሉ መከራ። 
 
የሆነ ሆኖ የኤርትራ ፖለቲካ፤ የህወሃት ፖለቲካ በሚመለከት የሰለጠንኩበት ስለሆነ ፕሮፖጋንዲስት አይስፈልገኝም። ኢትዮጵያዊነት ለሁለቱ ፖለቲከኞች እንደምን እንደ ባላንጣ እንደሚታይም አውቃለሁኝ። ከሆነም የኢትዮጵያ #ማስተር ማይንድ ህወሃት ወይንም ሻብያ የመሆን ህልመኞች መሆናቸውንም አውቃለሁ። የባድመ ጦርነትም መሠረተ - ግንዱ ይህ ነው ብዬ ነው እማምነው። የኤርትራ መንግሥት አገርነቱን ካረጋገጠ በኋላ ኢትዮጵያ ተገዢ፤ ታዛዢ፤ ትሆን ዘንድ ተፈለገ። ከዛ አይዋ ህወሃት አፈነገጠ፤ ተበቀለም።
 
#በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሊቃናት ስብጥር።
 
የኤርትራ እና የተጋሩ የፖለቲካ ሊቃናት በየዘመኑ በሚኖረው ላዕላይ መንግሥታዊ መዋቅርም እንክህ እንክህ የሚባሉ፤ የሹም ዶሮወች ነበሩ። ቁልፍ ኃላፊነትን - የማይነፈጉ፤ የተሻለ ዕድል የሚመቻችላቸውም ነበሩ። ያ ግን አርክቷቸው አያውቅም። ሶፍትዌሩም፤ ሃርድዌሩም የመሆን ህልመኛ ናቸውና። አይጠግቡም። ይህ ደግሞ በየዘመናቱ እያገረሼ የሚከሰት ጉዳይ ነው። ከመገንጠል በኋላ የፈለገውን ያገኜ አካል የራሱን ውስጥ አደራጅቶ ሲፈልግ ሲንጋፖር፤ ሲፈልግ ጃፓን፤ ሲፈልግ ቻይና ለመሆን መንገዱን የያዘበት አልነበረም። አሁንም ከኢትዮጵያ እራስ አለመውረድ ብቻ ሳይሆን፤ እንቅፋት ለማምረት መትጋት የጤና አይመስለኝም። ምን አለበት ኢትዮጵያን ቢተዋት? አይቻላቸውማ። ከፍታ በታለመው ልክ አልተገኜም። 
 
የሆነ ሆኖ የሰይጣን ጆሮ ይደፈን እና ህወሃት ምኞቱ ቢሳካ አገር ቢመሠርት፤ የሰርክ አጀንዳው እንደ ኤርትራ መንግሥት #ኢትዮጵያ ትሆናለች። ኢትዮጵያ ትንፋሽ አስቀጣይ ፍቱን ናትና። ኢትዮጵያ የተሰጣት የራሷ ጸጋ ያላት አገር ናት። ያን መውረስ፤ ያን መቦጨቅ አልተቻልም። እዮራዊ ስለሆነ። ይህ ካልተቻለ የውስጥ ሰላሟን ሴራ እያደራጁ ማመስ ፕሮጀክታቸው ነው የሁለቱም።
 
ከሥልጣን ስንብት በኋላ፤ ጥገቷ ኢትዮጵያ ከእጅ ስታመልጥ፤ የህወሃት ዘመናይ ጦርነት ለማሳካት ያሰበውን ቀርቶ "የቆጡን አውርድ ብላ የብብቷን ጣለች" ሆኖበት እንሆ ይነኽረራል። ኢትዮጵያን አይደለም መሆን ያልቻለም፤ በመምሰልም የሚገኝ ትሩፋት ስሌለ። የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የስኬት #ልሙጥነት እሷን ተቀናቅነው ወይንም ክደው በውስጣቸው ይነሳሉ፤ ማህል ላይ ይቀራሉ፤ ቢያተርፋ የሚዲያ አንበሳነትን ብቻ ነው።
 
የሆነ ሆኖ የኤርትራ መንግሥት የተሳሳተ ግምቱን ቢያሻሽለው መልካም ይመስለኛል። የባህር በር ይሁን የወደብ ጥያቄ የኢትዮጵያ ገዢ ፖለቲካል ፓርቲ ጉዳይ ብቻ አይደለም። የሚሊዮኖች ድምጽም ነው። የአጤው ዘመን ትውልድና መንፈስ፤ የደርግ ዘመን ትውልድ እና መንፈስ ትርታው ከወደብ እና ከባህር በር ጋር የተያያዘ ነው። ይህ የማይነቃነቅ ጽኑ እና ዘላቂ አንከር ጉዳያችን ነው።
 
ብዙውን ጊዜ ነገረ አባይ ከኢኮኖሚ ጋር ይያዛል፤ እርግጥ ነው ነገረ የውሃ ፖለቲካ በጥልቀት ስናስበው ኤሌትሪክ #ሥልጣኔም ነው። በሌላ በኩል ግን የክብር፤ የሉዓላዊነት፤ የራስ - መተማመን፤ ክብርን የማስመለስ የአቅም ጉልላትም ነው። ለሰከንድ ለኢትዮጵያ ተኝተው የማያውቁት የግብጽ የፖለቲካ ሊቃውንታት የሚያባትታቸው የኢትዮጵያ ታላቅነት ህልም ስኬት ነው።
 
የግብጽ የፖለቲካ ሊቃናት እንደ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ተምሳሌት፤ አንከር የመሆን ህልመኞች ናቸው። ጥሰው፤ ጠቅጥቀው፤ ጨፍልቀውም መውጣት ይፈልጋሉ። የሚገርመው ቅኝ ተገዢ የነበረች አገረ - ግብጽ፤ #አሻቅባ ቅኝ ያልተገዛችን የጀግኖች አንባን ኢትዮጵያን በእጅ አዙር ቅኝ ልግዛት ብላ ነው እየተንደፋደፈች የምትገኜው። በያንዳንዱ የኢትዮጵያ እርምጃ እክል እና ሳንክ ያመርታሉ። ይህን የሚያባብል፤ ይህን የሚያቆላምጥ አልጫ ሰብዕና መኖሩ ይገርመኛል። ይህ እኮ በየዘመኑ ሥልጣን ከሚይዝ መንግሥት ጋር የሚያያዝ አይደለም። የማንነት ክብር መለያ ሰንደቅ ዓላማ ነው። የታተመ። 
 
በኤርትራ በኩል እንደመያዣ የተያዘው አሰባችን ነው። አሰብ በእኔ ዘመን የወሎ ጠቅላይ ግዛት ነው የነበረው። አይደለም አሰብ ኤርትራ የኢትዮጵያ ፲፬ኛ ክፍለአገር ነው የነበረችው። አሰብም፤ ምጽዋም የኢትዮጵያ ነው የነበሩት። ኢትዮጵያም ጂኦ ፖለቲካል አቀማመጧ ፒላር ነው የነበረው። ይህ በስማ በለው ሳይሆን በእኔ ዕድሜ የነበረ የዕውነት ፏፏቴ ነው።
 
እንደሚታወቀው የእርስ በርስ ጦርነቱ በውስጥ አርበኞች በሻቢያወወያኔ በውጭ አገር ደጋፊወቻቸውም ይሁንታ አሸናፊ ሆኑ። እርግጥ ነው ኤርትራን ያስገነጠሉ የውጭ አገር መንግሥታት አሁን ላይ ቁጭ ብለው ሲዩት፤ የኤርትራ ስደተኛ መበራከት ውሳኔያቸውን እንደገና ደግመው እንዲዩት ሊያስገድዳቸው ይችላል። ጦርነቱም በአንድም በሌላም ቀጥሏል።
 
#ህም። 
 
የኤርትራ መንግሥትን ለኢትዮጵያ ማስተር ማይንድነት ለሚቀበል ተቃዋሚ ለመያዣነት የተቀመጠ የፖለቲካ ጥሪታቸው አሰባችን ነው። የሚገርመው ኢትዮጵያ ከአሰብ ባሻገር ለምታደርገው የወደብ እና የባህር በር ጥረት ይህም ይጎረብጣቸዋል ለኤርትራ የፖለቲካ ሊቃናት። ግብፅችም በተመሳሳይ። ስስታምነትን ወይንም ምቀኝነትን እግዚአብሄር አላህ ይመርምረው። የሰሞኑ የእስራኤል መንግሥት ለሱማሌላንድ የሰጠው የአገርነት ዕውቅና ጠዝጥዟቸዋል ግብጽንም ኤርትራንም። በየትኛውም የኢትዮጵያ የጥረት ዓውድማ እንቅፋት ፈጣሪወች ግብጽ እና የኤርትራ መንግሥት መሆናቸው ዕውነቱን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው የምለውም ለዚህ ነው።
 
የሚያስተባብሯቸው አገሮች በሞግዚት ጥበቃ ነፍሳቸው የቀጠሉትን ነው (ጁቡቲ እና ሱማሌ)። የማያውቁት፤ የማይረዱት ሳይለንት ማጆሪቲ የሚባል #ዕምቅ ሃብት ኢትዮጵያ ያላት መሆኑን ነው። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ሲመጡ እኮ ያ ሁሉ ኤርትራ እና ግብጽ በቅንጅት ይመሩት የነበሩት ጸረ ህወሃት የተቃዋሚ አካል አገር ውስጥም ውጭም ዓይኑ ጉድ እንዲያይ ነበር ያደረገው ያ ቅምጥ የኢትዮጵያ ቅዱስ መንፈስ ጭምት አቅም። በባህር - በር፤ በወደብ ጉዳይም የዚህን ማህበረሰብ ልዩ የአቅም ጥሪት እና ዲስፕሊኑን፤ ጭምትነቱን ማክበር ይገባል ባይ ነኝ።
 
የኢትዮጵያ የወደብ ይሁን የባህር በር ጥያቄ ብቻውን የቆመ፤ የተነጠለጠለ፤ በህዝቧ የተገለለ አይደለም። የደማችን መዘወሪያ ሞተራችን እንዲሆን የፈቀድንለት እንዳለንም ሊታወቅ ይገባል። ጉዳዩ የኢቬንት ጉዳይ አይደለም። ጉዳዩ የገብያ ግርግር ጉዳይ አይደለም። የውስጣችን የመገለጫ ሚስጢራችን ነው። ዝልቅና ምጡቅ ህልማችንም ነው። በህወሃት ሴራ ያጣነው የክብር መንበር - በርጋታ፤ በአደብ፤ በጥሞና ወደ መንበሩ ይመለስ ዘንድ በሰከነ የሎቢ ተግባር ሊተጋለት ይገባል። በሳል የዲፕሎማሲ ተግባርን ይጠይቃል።
 
ለአባይ ግድብ #የተቋቋመው በጣም ስኩን፤ የተደራጄ ኮሜቴ ህልውናው እንዲቀጥል ማድረግ ዊዝደም ነው። አቤቱ ብልጽግና ለዚህ አካል ዕውቅናውን አድሶ ካላስቀጠለው $አይጥ ወልዳ ወልዳ ከጅራቱ ስትደርስ" እንደሚባለው ይሆናል። አንድ የገዘፈ ፓን አፍሪካኒስት ፕሮጀክት ተለጣፊ ሳይሆን ራስ ገዝ ሆኖ እንዲሠራ ማድረግ በጣም ጠቃሚ ጉዳይ ነው። አባይ ግድብን በሚመለከት ሙሉ ሰነዱ በመረጃ ተደግፎ ለትውልድ እንዲሆን የማድረግ አቅሙ ድንቅነት ከኮሜቴው ብቁ ክህሎት እና አቅም ይመነጫል። ለተደራጄ የባላንጣ ጉዳይ የተደራጄ ሙሉ አቅም ይጠይቃል።
 
ልክ በዛ ልክ ደረጃውን የጠበቀ ስለ ባህር በራችን፤ ስለወደባችን የመሻት የተስፋ ጉዞ በጥራት እና በስክነት ጉዳዩን የሚከታተል ባለቤት ያስፈልገዋልም ባይ ነኝ። የተዘጋው ሲከፈት #ብርሃን ይኖራል። የበራው መብራትን ማስቀጥል፤ መንከባከብ ይገባል። የኢትዮጵያዊነት የሚስጢር መገለጫው ባህረ መዝገብ ስለሆነ። ሂደቱ በቅጡ መሰነድ ስላለበት። ተስፋው እራሱን የቻለ ነፃነት ስለሚያስፈልገውም። ከዚህ በተጨማሪ በዚህ ዙሪያ ከፕሮፖጋንዳ ያለፈ የጽንሰ ሃሳብ ትንተና በባለሙያወች በትጋት እና በተከታታይ የመስጠቱ ተግባር በሚዲያ፤ በበራሪ ጹሁፍ፤ በመጋዚን፤ በራዲይ ሊሠራበት ይገባል። በጉዞ ውስጥ ቂም እና በቀል፤ ስሜታዊነትም ሊኖር አይገባም። ዕውነት እና ታጋሽነት ግን ሊበረታቱ ይገባል።
 
"ጥያቄያችን የባህር በር አይደለም፤ ወልቃይት ጠገዴን ለህወሃት አስረክበን ምኞታችን በትረ መንግሥት ፬ኪሎ ነው" የሚል ዝልብ ፖለቲካን በእጁጉ ነው እምጸየፈው። ለነገሩ ወጥኖ መጨረስ የሚሳነው ሰብዕና የገዘፈውን የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና የመሸከም አቅሙ ከፋንታዚ የማያልፍ ስለመሆኑ ጊዜ ራዲዮሎጂ ነውና አሳይቶናል።
 
ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያ ከሱማሌላንድ ጋር ባደረገችው የመግባቢያ ሰነድነት ብቻ ነው የሱማሌላንድ ያለፈውን ምርጫዋ የዓለም ዓውደ ምህረት መሆን የቻለው፤ እስራኤልም ሙሉ ዕውቅና የሰጠችበት ፖለቲካ ውሳኔ ማዳበሪያውን፤ መደላደሉን ጉዝጓዙን፤ የመጀመሪያውን የነበልባል ወላፈን ያስተናገደው የኢትዮጵያ መንፈስ #ቅብዓ ቅዱስ ስለመሆኑ ቅንጣት ጥርጣሬ የለኝም። 
 
እስራኤል ለሱማሌላንድ ለሰጠችው ዕውቅናም እኔ ክብር አለኝ። #ስለሚገባቸው። ምርጫ ላይ ያላቸው ፖለቲካዊ ብቃት እኮ ከበቂ በላይ ነው። የውስጥ ሰላማችው እራሱ መምህርም ነው። ምን አልባት ለወደፊት የብዙ አገሮች የዓይን ማረፊያ የመሆናቸው ዕድላቸውም ሰፊ ነው። እግዚአብሄር የሰጣቸው ቦታ እጅግ ስትራቴጂያዊ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ እርክክብ ዘይቤያቸው ለአፍሪካ አዲስ ካሪክለም ነውና።
 
ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ፈተና ውስጥ ሲገቡ #ዝም የማንል ሰብዕናወች አለን። ዝምታችነን አክብሩልን እንደማለት። ብንሰደድም፤ አገር ላይ ቢኖርም ጉሮሯችን፤ መጠሪያችን ምልክታችን እማማ፤ እምዬ፤ እናትዓለም ኢትዮጵያ ናት እና። ለእኔ ኢትዮጵያ ፍልስፍና፤ ኢትዮጵያ ሳይንስ፤ ኢትዮጵያ ህግ፤ ኢትዮጵያ ዩንቨርስ ናት። 
 
እኔ በግሌ ለረጀም ጊዜ ኢትዮጵያን አገሬን ሳስባት፤ ዕውነት ለመናገር ክብሯ እና ተፈጥሯዊ ጸጋዋን እንደ አገር ሳይሆን እንደ #አህጉር ነው የማየው። ችግሩ ሥልጣን ላይ ያሉትም፤ ለሥልጣን የሚፎካከሩትም እንግዛት፦ ገዛናትም የሚሏትን አገር ልክ አያውቁትም። ለዚህም ነው እኔ በድፍረት ኢትዮጵያ #የከበደችን ለሁላችንም ነው የምለው። ይገርመኛልም በኢትዮጵያዊነት ላይ አድማ ሲመታም። 
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
የእኔ ስጦታወች ኑሩልኝ።
መሸቢያ ምሽት።
 
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
09/01/2026
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
የወደብም፤ የባህር በር ጥያቄ #የእኔም ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።