እቴጌ ጎንደር ሰላምሽ #በመዳፍሽ ነው። የውስጤ ሆይ! እንደ ውርስሽ #አደብ ላይ ከትሚ።

 

እቴጌ ጎንደር ሰላምሽ #በመዳፍሽ ነው። የውስጤ ሆይ! እንደ ውርስሽ #አደብ ላይ ከትሚ።
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 
 May be an image of crowd
እቴጌ ጎንደር ሰላምሽ #በመዳፍሽ ነው። የውስጤ ሆይ! እንደ ውርስሽ #አደብ ላይ ከትሚ።
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 
 
እቴጌዋ ዘመነ -አስተርዬ #ምችት ይለው ዘንድ ሰላምሽን ሰንቂ። ከፈጣሪሽ ጋር የሚኖርሽ ሃዲድ የሚዋብበት ሆነ የሚለመልምበት ዘመነ - አስተርዬን እንደ አባት አደሩ #ስቀሽ ለመቀበል ተሰናጂ። መገበርሽን ለማን? ማገዶነትሽን ስለምን ብለሽ እሰቢው? መገበርሽን ለማስቆም ቁልፋ ከእጅሽ ከመዳፍሽ ነው። "ወልቃይት ብረሳሽ ብለሽ" ስትነሺ ከጎንሽ የነበረ #የቅኔው ጎጃም ሙሉ ህዝብ ብቻ ነው። ግብርነቱም መኖሩን ፈቅዶ እና ወዶ ለሰማዕትነት የሰጠ ድንቅ ህዝብ ነው ቅኔው ጎጃም። በሙሉ መረጃው ከእጄ ይገኛል። ልዩዬ ስለሆነ።
 
ስለወልቃይት ጠገዴ ካነሳሁ ዘንድ ሰላማችሁን ላስከበራችሁ የማስተዋል ባለክህሎት ጀግኖቼ ምስጋናዬ በክብር ይድረሳችሁ። #ለእኛ የህሊናችን ቁልፍ ጉዳይ የመካከለኛው ምስራቅ እና የአፍሪካ ቀንድ ቁልፍ የፖለቲካ አናታዊ ጉዳይ ነገረ ወልቃይት ጠገዴ የወገራ እና የስሜን አውራጃ ጉዳይ ብቻ እና ብቻ ነው። 
 
#ስሚኝማ ወለላዬ ጎንደሪና። 
 
ማን ይሁን? ምን? ከአንቺ ጋር አሳሩን ያልተጋራ ስለአንቺ ሊበይን፤ ከተውንም ልትፈቅጂለት አይገባም። ዘመነ ህወሃት እንደሆን የቀራንዮ የድቅድቅ ጨለማ፥ መተንፈሻሽ ፈተና ላይ የነበረበት ዘመንሽ ነበረ። የአንድ አውራጃ ያህል ክብር አልነበረሽም። ይህን በጥልቀት እሰቢው። ስለክብርሽ፤ ስለዝናሽ፤ ስለልቅናሽ፤ ስለልዕልናሽ፤ ስለ ሁለመናሽ #ርቁቅነት እና ዝልቅነት እሰቢው። ካለደረጃሽ፤ ካለ ቦታሽ ተቀርቅረሽ እንድትገኚ ያደረገሽ አንጡራ ተቀናቃኝሽ #ህወሃት አንገት ያስደፋሽን ዘመን ከቶውንም ሊናፍቅሽ አይገባም። በዚህ መስመር የሚወጠን ማናቸውንም ሁነት #አክ በይው። 
 
በዚህ ጉዳይ እኛ ልጆችሽ ብዙ በጣም ብዙ ተገብረንበታል። ብዙ በጣም ብዙ #መስቃ ሰምተንበታል። ብዙ በጣም ብዙ #ተገለንበታል ጎንደሬ በመሆናችን ብቻ እና ብቻ። ተሰደንም - ያሳድዱናል። ተሰደንም - ያሳድሙብናል። እንቀበር ዘንድም ታትረዋል። አልቻሉም። ያሳካነውን - አሳክተናል። ለምን - ያሳዱናል? ስለምንስ - ያገልሉናል፤ አቅማችን፤ ክህሎታችን ስለሚያርዳቸው። ችለነዋል።
 
 አልተበገርንላቸውም። ሆድዬ ያስተማርሽንን "ሙያ በልብ" ከትመን ቁጭ ብለን የህወሃት የበቀል መዶሻው ቅጥቀጣውን እንዲቀጥል አልፈቀድንም። የልባችን አድርሰናል። "ምን ብቀጥን ጠጅ ነኝ" አይደል ብሂላችን። እንደዛም እንዲህም።
 
ወደፊትም የህወሃት የጎለጎታ ዘመን ቀና እንዲል - አንፈቅድም። ስለሆነም የህወሃትን #የጓጎለ፤ ያጎፈረ መንበረ - ሥልጣን ክትመት አሳውጀን፤ ያን የድል ብሥራት ለመዘቅዘቅ ናፍቆተኛ ልንሆን ፈጽሞ አንችልም። ዛሬ ባለው የብልጽግና መንግሥት ጎደለ፤ አልተሟላም፤ ይስተካከል ለምንለው አመክንዮ ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ሙግታችን ይቀጥላል። የማንም ቁሮም፤ የየትኛውም አካል እና ተቋም ተንጠልጣይም ሳንሆን፤ በራሳችን መርሃዊ ቋሚ እና ዝልቅ አሻራችን እንቀጥላለን። በጭምትነት፤ በማስተዋል፤ በእርጋታ። ኢትዮጵያ ከእግዚአብሄር በታች ግን ከኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ፖለቲከኞች በላይ ናትና። 
 
በዚህ ውስጥ ውስጣችን ውህድ የሆነውን የትግራይ ህዝብ በመኖራችን ንጥረ ነገር ውስጥ ደረጃውን እንደጠበቀ የማስቀጠል ኃላፊነት አለብን። በሁሉም ዘርፍ ውህዳዊ ማንነታችን ጸንቶ በጽናት ይቀጥል ዘንድ ብልህነት የሰርክ መኖ ሊሆን ይገባል። የጎንደር ህዝብ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማንያናን አብዛኛው የንሰኃ አባት ማን ነው? ጋብቻው፤ ጉርብትናው፤ ዝምድናው ሳይሰላ ማለት ነው። ጣዕሙ ለዛው ፍጥረተ ነገሩ ቃናው የእዮርም ነው። ከፖለቲከኞች በላይም ነው። 
 
#ብልኋ ጎንደር ሆይ!
 
በኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ፖለቲከኞች በአብዛኞቹ ዘንድ በክፋ ዓይን የምትታይ በዓት ብትኖር ጎንደሪና ነሽ። ገና በቁንጮዬ ነው በፖለቲካ ህይወት የበቀልቁት፤ ገና በጋሜዬም ነው ሚዲያ ላይ ተሳትፎዬ የተባው ሳጠናው፤ ስመረምረው የማንነት ዝበት ያለበት ሁሉ የሚንጠለጠለው አንች ላይ ነው። በየትኛውም ስብስብ የጎንደር የፖለቲካ ሊቅ፤ የጎንደር ትንታግ ብዕረኛ፤ የጎንደር ብርታት - ጠገብ ጋዜጠኛ፤ የጎንደር ዓራት ዓይናማ የሚዲያ ሰብዕ አይፈለግም። ይገለላል።
 
ዘመኑ ካመጣው የዩቱብ ሁነት እንኳን ጎንደር #በልሙጥነት። ዛሬም ይኽው ቀጥሏል። ከዚህ መለሞጥ ምን አተርፋለሁ ብሎ ጎንደሬ ነፍሱን እንደሚገብር፤ አቅሙን ለምን እንደሚደፋ አይገባኝም። ጎንደር አታተርፍም። እርግጡ ይኽ ነው። በዬትኛውም የውክልና ይሁን የዕውቅና ደረጃ ጎንደር የተገለለች ናት። ለማገዶነት ደግሞ በግንባር ቀደም ተፈላጊዋ ልዕልት ጎንደር ናት። ይህ የገበጣ ጨዋታ ሊቆም ይገባል። 
 
አንዳንዶቹ ትግል ጀመርን የሚሉት #በጸረ ጎንደሬነት ነው። ከዚህ ስብስብ ምን አተርፍ ብሎ ጎንደር እና ጎንደሬ እንደሚማገድ ፈጽሞ አይገባኝም። አሁን የወጣት ናሆሰናይ እና አባኔዘር ማገዶነት ባወጣው // ባወርደው ዕድሜውን፤ መኖሩን፤ ተስፋውን የገበረበት ሁነት አይገባኝም። የገርነትም አለው ዓይነት። ጫካውን ትቶ አስፓልት ላይ ለመንደድ እንዴት ወደ አዲስ አበባ ሊገሰግሥ ቻለ? እሱን የማገዱት ዛሬ ኡጋንዳ እና ኬኒያ ከእነ ሙሉ ቤተሰባቸው ጋር ተሰደዋል። 
 
ቢያንስ ክፋም ደጉም በመኖር ውስጥ ለማየት ዕድል አግኝተዋል። ዘመቻ ናሆሰናይ የሰሞናት ብቻ ነበር። ያን ፕሮጀክት በለብለብ አስኪደው "ጎንደር ይነሳል" ነበር ሃሳቡ፤ ጎንደር ሲነሳ በደም ጅረት አደባባይ ይታደማል። ልክ እንደ ሃውዜን ማለት ነው። በዛ ዓለም ዓቀፍ ተጽዕኖ ይፈልቃል ነበር። ግን በሰው ሳይሆን በፈጣሪ ኃይል ሁለመናው #ረብ አለ።
 
የሚገርመኝ መበለጡን በምልሰት ጎንደሬ አለመገምገሙ ነው። ጎንደሬ ከዚህ በኋላ ብሎ አያስብም። #መማገድ ብቻ። ማገዶነት የማይሰለቸው ባዕት ቢኖር ጎንደሬ ነው። ሁልጊዜ ጎንደር መፈተኛ፤ መሞከሪያ ጣቢያ መሆን። ይህ #ሊበቃ፥ ሊያከትም ይገባል። በየአካባቢው ያለው የትጥቅ ትግል ባይሳካ፤ ቀሪ ኃይሉ መጥቶ የሚሰባሰበው ጎንደር ጫካ ሊሆን ይችላል። እንደ ገና ለመማገድ። እንደገና ስንቅ እና ትጥቅ አቅራቢ ለመሆን። እንደ ገና በባሩድ ለመደብደብ። ከዛ በኋላ ዞር ብሎ የሚያያችሁ አይደለም በተቋም ደረጃ በቀንጣ እንኳን እናመስግንሽ ጎንደር የማይደፈር ዕውነት ነው። ልብ ይስጣችሁ ፈጣሪ ለጎንደሬወች ከሊቅ እስከ ደቂቅ። አሜን። 
 
ትልልቅ የዩቱብ ሚዲያወች እነሱ የተፈጠሩባት ርዕሰ ከተማ ላይ ይህ እንዲሆን አይፈቅዱም። በተለይ ደቡቦች። የጋብቻ ዝምድና እንኳን ጥበቃ ተደርጎለት ከአገር እንዲወጣ ይደረጋል። አይደለም ጫካና ዱራቸው፤ ያደጉበት ከተማ የባሩድ ማስታገሻ ሊሆን ቀርቶ። ሌላው የሚሆነው፤ የሆነው ሁሉ በፈጣሪ በአላህ ፈቃድ ስለመሆኑም ይዘለላል። "በሞኝ ክንድ ዘንዶ ይለካበታል።"
///
ባለፈውም ጽፌበታለሁኝ። የደቡብ ህዝብ #በየዘመኑ የፖለቲካ ውክልና ተጠቃሚ ነው። አሁንም ግማሹ የብልጽግና ካቢኔ ከደቡብ ነው። ለምን? ጫካወቻቸው የሰላም አንባ ስለሆኑ፥ ልጆቻቸው ጨምተው ስለሚማሩ፤ በቀለም ትምህርት በቅተው ስለሚገኙ ክፍት ቦታ በብሄራዊም፦ በአህጉርም ሲገኝ ይመረጣሉ። ባለፈው ሰሞን ከብሄራዊም አልፎ ተርፎ አህጉር ላይ ቁልፍ ቦታ ያገኙ ባለሙያ ከደቡብ ነበር።
ጫካ ላይ የምትገኙ የጎንደር ዕውነተኛ ፋኖወችም የጎንደርን - ልቅና፤ የጎንደርን - ልዕልና በሚገቱ፤ በሚቀናቀኑ፤ ስንጥቅ በሚፈጥሩ ማናቸውም ሁነቶች እባካችሁ አትሳተፋ። የጎንደርን መጫጫታ አቅዶ የሚተገብረው አቤቱ ህወሃት ነው። ህወሃት ከጎንደር በላይ እንደ አንጡራ ጠላት የሚያዬው በዕት የለም። አፍቅሮተ ህወሃትን የሰለቀጡ ለ፬ኪሎ ሥልጣን የሚፎካከሩትም ቢሆኑም አንዳቸውም፤ ጎንደር አጀንዳቸው #አይደለችም። አይተዋትም - አያውቁም። እሷ ስትነሳ ደማቸው ይንተከተካል። ይህን ብልህ ጎንደሬወች ከውስጣችሁ አድርጋችሁ በምታዋጡት አቅም ሁሉ እሰቡበት። እኔ እህታችሁ በጥንቃቄ ነው የምጓዘው።
 
እግዚአብሄር አደረገልኝ በህይወት ዘመኔ ወይንም ሰጠኝ ብዬ እማስበው ሽልማት ህወሃት ፈቅዶ እና ወዶ በትረ መንግሥቱን መልቀቁን ነው። ስለሆነም ህወሃትን አጥቦ፤ ቀሽሮ፤ አድሶ ለማቅረብ በሚደረጉ ቅንብሮች እናቴ እብዬ ሆዴ በአራስ ቤቷ አላበደችም፦ የራሴን #ጥረት ለመቅበር የምፈቅድበት። ፈጽሞ። የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና የህወሃት ትንሳኤ እንደ ገና ቢታወጅ የጎንደር መራራ ስንብት ነው የሚሆነው? ጎንደሬ ሆኖ የህወሃት ህልም እንዲሳካ አይደለም መሰዋት ማሰቡ በራሱ ወፈፌነት ነው። ለአንተ ዲያቢሎስ የሆነብህ መንፈስ እንደምን ትናፍቀዋለህ???
 
#ቆቅነት ይሰነቅ - ለድንቅነት!
 
ወርኃ ጥር ዘመነ አስተርዬ ጎንደር ቆቅ ሆና ትልሟን ልታሳካ ይገባታል። ጫካ የሚገኙ ዕውነተኛ ፋኖወችም ለእናታቸው የሳቅ ተንሳዔ ዘብ አደር ሊሆኑላት ይገባል። ኮሽታ አያስፈልግም። ጎንደር ብዙ እንግዶች ጥር ላይ አሏት። እንግዶቿን እንኳን ደህና መጣችሁ ብላ በረከቷን፤ ረድኤቷን እንዳይስተጓጎል ልታደርግ ይገባታል እቴጌ ጎንደር እና ልጆቿ።
 
አንድ ጊዜ አፍሬያለሁኝ። ጎንደር ለጥምቀት አቅደው፤ ባህላዊ ሙሉወርዳቸውን ዘንከት አድርገው የተገኙ እንግዳዋን አቅል ባነሳቸው፤ ተፈጥሮዋን ባልተረዱ፥ ጠይቀዋት በማያውቋት በዕድሜያቸው ሙሉ አንድ ቀን ተገኝተው፤ ግን በባህሏ ክስለትን ባጩ፤ በኋላም በጦርነት በማገዷት ገፊነት የጎንደር እንግዳ እንዲመለሱ ተሰማ። ያ …… ክብር ሆኖ፤ ያ ……… ማዕረግ ሆኖም ሲተነተን ለሚዲያ ሲበቃ አዳምጫለሁኝ። ዝም ያልኩት ክብሪት መሆን ሰብዕናዬ ስላልሆነ ነው። ብዙ ክስተት ከተረጋጋ፦ ከቆዬ በኋላ አዋዝቼ እምተነትነውም ለዚህ ነው። የወይብላ ማርያም መከራ የተቀበለችው በዚህ ምክንያት ነው።
 
ጎንደሮችን ልይ ብሎ ናፍቆ እና አክብሮ የመጣ የሰው ልጅ ሁሉ በክብር - ተቀብሎ፤ በክብር ማስተናገድ፥ ያን ኦርጋኒክ ተፈጥሯችን የሚጎረብጠው ቡድን ነበር ያን ግድፈት የፈጸመው። ማንም ሚዲያ ያለው ይሁን የሌለው በጎንደር ህይወት የመወሰን ቅንጣት መብት የለውም። ስለ ጎንደር መበየን የሚችሉት እዛው ያሉ ጎንደሬወቹ ነዋሪወቹ ናቸው። 
 
አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው ህውሃት በመቀሌ ከከተመ በኋላ የማዕከላዊ ጎንደር 80ሺህ ህዝብ መፈናቀል፤ የስሜን ተራራ መቃጠል፤ የጎንደር የፖለቲካ ሊቃናቱ ልቅምቅም ብለው ለህልፈት የተዳረጉት፤ የሴራ ጉንጉኑ ሆነ አለባሶው የህወሃት እንደሆነ ይገባኛል። በፋኖ ንቅናቄም እንደ ጎንደር ፋኖ #መሪወቹን ያለቁበት የለም። ጎንደርን ካለመሪ የማስቀረት የህወሃት #ፋሳዊ ትልም በአንድም በሌላም ተሳክቶለታል። ይህ የገባቸው አንድ የደብረታቦር ልባም አዛውንት በሰሞኑ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ሲናገሩ ሰምቻለሁኝ። መንፈስ ቅዱስ አናገራቸው ነው ያልኩት። እንደ ቅድስት ህፃን ኤልዳና ባዬ የኔዓለም አዳሙ።
 
#ጎንደሮች ሆይ! ልባሞች ናችሁ።
 
"ሸማ በየዘርፋ ይለበሳል" ትላላችሁ። በሁሉም ነገር ፖለቲካን አትዘርዝሩት። ዘመነ - አስተርዬ የእዮር ስጦታ ነው። በስጦታው ልክ ተከብሮ ሊፈጸም ሲገባ የፖለቲካ #መበቃቃያ ሊሆን አይገባም። እኔ የታዘብኩት ቁም ነገር፤ የፈለገ ያህል ጎንደሬ ይገበር ዋጋ የሚሰጠው የለም። ዕውቅና የሚሰጠው የለም። የሚያስጠጋውም የለም። ከቁጥር ሊስት የሚያስገባው የለም። ለነገ የሥልጣን ምኞትም መጀመሪያ ሰይፍ የሚመዘዝበት #ጎንደሬ ነው። አይታችሁታል ተገብራችሁም ዕውቅናችሁ ዜሮ በዜሮ ሲሆን።
 
ስለዚህ ተግ ብላችሁ፤ በአስተውሎት የሚያዋጣውን፤ የተሻለውን መምረጥ ይገባችኋል እነ - ጎንደሮች። ቆቅ ሁኑ። ቆቅ ሆናችሁ እናታችሁን ጠብቁ። ቆቅ ሆናችሁ ስለእናታችሁ ቀናዒ ሁኑ። ዘመነ አስተርዬ በሰላም ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ #እርጋን ዕውነተኛ ፋኖወች ልታውጁ፤ ልትፈጽሙ፤ ልታስፈጽሙትም ይገባል። ለአስተረዬ ብሥራት ዕውነተኛ ፋኖወች ዘብ አደርነታችሁን ልታስመሰክሩ ይገባል። እናታችሁን አታስከፋ። እናታችሁን አታስቸግሩ። እናታችሁን አታጎሳቁሉ። እናታችሁን የስጋት አንባ አታስደርጉ።
 
አቤቶ ብልጽግናም እራስህ መዋቅር ውስጥ ስላለው ትብትብም መፍትሄ ፈልግለት። ለነገሩ አትሰማም። ወጣ ገብ እንዳይሆን፤ ወጥ የሆነ ሰላም መንፈስ እንዲኖር፤ ወጥ የሆነ የውስጥ መረጋጋት እንዲኖር ብልህነት የሰነቀ ብዬ ሃሳብ አቅርቤልህ ነበር። ብሄራዊ የምህረት ዓዋጅ እና እራስን የመግለጥ መድረክ እንድትፈጥር። አንተ ግን አቤቱ ብልጽግና እራስህን ብቻ የምታዳምጥ ፍጥረት ስለሆንክ ሁለት ፍሬ ስኬቴ ብለህ በሚዲያ ስታውጅ አደምጣለሁኝ። 
 
ጠንካራ የፖለቲካ ውሳኔ በብልህነት ይጠይቃል የነገረ አማራ ክልል ዕውነት። አለሁ - ትላለህ፤ መኖርህን እየመዘንኩት ነው። እኛን ብትተው የህዝብህ ስሜትን ግብረ መልስ ዕውቅና ብትሰጠው ጥሩ ነው። ሰላም በጥረት፤ በስልት፤ በብልህነት፤ በጥበብ እንጂ በፕሮፖጋንዳ፤ በመፈክር አይገኝም። 
 
የአማራን ህዝብ ውስጥ ለማግኜት ዘንበል አድርጎ ጆሮን ማድመጥ፤ ለችግሮቹ ቅደም ተከተል አውጥቶ የመፍትሄ ጎዳና መጀመር በእጅጉ ያስፈልጋል። የአማራ ህዝብ አይዞህ ሊባል ይገባል። የመንበረ ሥልጣንህ ረቂቅ ዕውነት ከዛ ስለሆነ። አትርሳ የመጋቢት 18/2010 ጥቃት ያወጣ የዕንቁ ስጦታ። የአማራ ህዝብ እና ልቅናው የእኔ ሊባል እንጂ ሊገፋ፤ ጭነት ሊበዛበት ፈጽሞ አይገባም። ግፍም ነው። እዮር ያያል።
የማከብራችሁ የአገሬ ልጆች ዛሬ ምዕራፍ ፲፰ ጀመርኩት። እጅ ነስተናል እኔ እና ፍቅረኛዬ ብዕሬ። መልካሙን ሁሉም እንመኛለን።
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
09/01/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ዕውነት ቦታውን ለቆ አያውቅም!

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።