ባለቤት አልባወቹ የኢትዮጵያ ህፃናት #እምታ #በጦርነት፤ በመፈናቀል #ወላፈን #ከትናንት እስከ-ዛሬ የህፃናት #የምጥ - #ማጥ።

 

ባለቤት አልባወቹ የኢትዮጵያ ህፃናት #እምታ #በጦርነት፤ በመፈናቀል #ወላፈን #ከትናንት እስከ-ዛሬ የህፃናት #የምጥ - #ማጥ። 
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 
አሳዛኙ ገጠመኝ ስለ #ህፃናት መብት የሚሞግት ተቋም የለም። መስኪን ለምኛት ነበር በብዕሬ። ቢያንስ የጉዳታቸውን ደረጃ እንኳን ማወቅ ብልሃዊ ጉዞ ነበርና። አልሆነም።
 
#ምዕራፍ ፲፰ 
 
በእያንዳንዱ ጸረ - ተፈጥሮ፤ ጸረ - ሰው ቀውስ ሁሉ የህወሃትም #የሥልጣን መሻትም አለ። ይህንን የቀውስ ትልም ለማክሸፍ ባለሥልጣኑ ብልጽግናም አቃሎ በማዬት ማገዶው ህዝብ ሆነ፤ መሞከሪያ ጣቢያው #ህፃናት ሆኑ። 
 
አቤቶ ብልጽግና እንደኛው #ስሞታ አቅራቢ ነው። ቆፍጠን ብሎ አስቦ፤ ጉዳዩን አጥንቶ ሥርዓት ማስያዝ የሚገባውን ወሳኝ የፖለቲካ ዕድምታ በንቀት፤ በቸለልተኝነት፤ የትም አይደርሱም "በነዋል፤ ዱቄት ሆነዋል፤ አንድ ሁለት ሽፍቶች" እያለ ብቻ ሳይሆን የህወሃትን ሆድ ዕቃወችን #ቁልፍ እና ወሳኝ ቦታ እዬሰጠ የብዙኃን የዕንባን ትዕይንት ፬ኪሎ ላይ ሆኖ እንደ እኛው ይመለከታል። 
 
ለአቤቱ ብልጽግና ዳሩ ሲታረስ ማህሉ ዳር እንደሚሆን ይጠፋዋል ብዬ አልገምትም፤ ጎዳናውን ሳስተውለው……
1) ህዋህትን በዲፕሎማሲው ማህበረሰብ #ለማሳጣት የህዝብ ተስፋ መማገድ አለበት። 
 
ይህ ነው የብልጽግና ቀመር። ሁልጊዜ ዕድሉን መከንበል፤ ዛሬ እኮ ህወሃትን "አትንኩብን"" የሚሉ፤ ትናንት በጸረ - ህወሃት አቋማቸው የሚታወቁ ወገኖች እዬበረከቱ ነው። ህወሃትን አምኖ የአማራ ህዝብን ዕምቅ አቅም ገፍቶ፤ ከኤርትራ ጋር የነበረውን ንፋስ አይገባውም የተባለ የቀለበት ሥርዓት ትቶ አዲስ የፍቅር ግጥግጦሽ ከህወሃቲዝም ጋር ቀጠለ። ለዚህ ነው ተከዳን የሚል ሌላ ሙቀታም ዓውሎ ከች ያለው። 
 
2) በሌላ በኩል የምርጫ ማጫ በጦርነት፤
 
ይህን መሰል የህዝብ ሰቆቃ ስጋት ፈጥሮ ብቸኛው መጠጊያችን ብልጥግና እንዲል ህዝብ እና ለዛ መጣሁ መጣሁ ለሚለው የምርጫ ሂደት #የማሟያ አቅም ለማግኜትም ይመስላል ጦርነት እና ምርጫን ማጫ የሚያማታው። እንጂማ የአየር ላይ የጀት ትርኢቱ ሁለመናውን ላጣ የህወሃት አቅም እንዲህ መንበርከክ ባልተገባው ነበር። ከመላማጣ ሠራዊቱ ወጣ እየተባለ ነው። በጠለምት ግንባርም መጠነ ሰፊ የጦርነት ወላፈን እንዳለ እያዳመጥኩ ነው። ምንጊዜም የህወሃት መንፈስ #የስትራቴጂ አጋርነት ነው ለአቤቱ ብልጽግና ሹማምንት። ማሸነፍ ሚስጢር ነው። ሚስጢር በማን #መዳፍ ውስጥ ነው ያለው???? 
 
#በሁሉም ዘንድ ልብ የማይባለው ጭምት አቅም። 
 
ብልጽግና ሆነያልተረዳው አድፍጦ የተቀመጠው ዝምተኛው ማህበረሰብ አንድ ቀን አንቅሮ ሊተፋው እንደሚችለው ነው። ያለው ወጀብ እኮ ልክ የለውም። ጭምቱን ማህበረሰብ መንፈሱን #ለማስገበር። በዝምታው ውስጥ ለሰከነው ጭምጥ ማህበረሰብ አቅሙን የሚፈታተኑ ብዙ፤ በጣም ብዙ ሰብዓዊ፤ ብሄራዊ ጉዳዮች አሉ፤ የሚዲያ ወጀብም አለ። 
 
ይህ ጭምት ማህበረሰብ፤ እዩኝ እዩኝ ሳይል አቤቶ ብልጽግናን ለክብር ያበቃው፤ ሥልጣኑ እንዲቀጥል ወጀቡን ሁሉ በጥሞና በመግራት ነፍሱን ያስቀጠለው ሳይለንት ማጆሪቲው የኢትዮጵያኒዝም ዘብ አደር ነው። 
 
ኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥቷ ሊኖር ይገባል፤ መሰብሳቢያ ምኽዋራችን ኢትዮጵያዊነትን መጠበቅ ነው ስለሚል። ግን ሲከር መበጠሱ፤ ሲሞላም ይፈሳል። ለዚህም ነው እኔ ትግዕስት ሲያልቅ ፍቅር - ይሰደዳል፤ ፍቅር ሲያልቅ ትዕግሥት ይሰደዳል - የምለው። በዚህ ሁሉ ውስጥ የህፃናት ጉዳት በረከተ። ህፃናቱ ስለመብታቸው የሚሞግት አንዳችም የህፃናት መብት አስከባሪ ነፃ ተቋም የለም። 
 
#የህፃናት #እምታ ………በቸነፈር። 
 
ህፃናት ተሰቃዩ - በጦርነት ወላፈን።
ህፃናት መኖራቸው መረራቸው - በጦርነት ወላፈን።
ህፃናት ቸገራቸው - በጦርነት ወላፈን።
ህፃናት ተስፋቸውን ተዘረፋ - በጦርነት ወላፈን።
ህፃናት አለቀሱ - በጦርነት ወላፈን።
ህፃናት መጫወት አልቻሉም - በጦርነት ወላፈን።
ህፃናት መሳቅ አልቻሉም - በጦርነት ወላፈን።
ህፃናት መኖራቸው ፍዳውን አዬ በመፈናቀል።
ህፃናት እንደ አዋቂወች #ምጥ ላይ ናቸው። ስጋት ላይ ናቸው።
ህፃናት #ቸንፈር ውስጥ ናቸው።
ህፃናት ሰቀቀን ላይ ናቸው በግራቀኝ የጦርነት ወላፈን። መጠጊያ አጡ። መጠለያ አጡ።
ህፃናት ስጋት ላይ፤
ህፃናቱ ፍርሃት ላይ ናቸው። ትናንትም ዛሬም። 
 
እራሱን መግዛት፤ እራሱን በቅጡ ማስተዳደር ባልቻለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ #የሥልጣን #ግብግብ የኢትዮጵያ ተስፋወች ህፃናት ያለማጋነን #ማቅ ውስጥ ናቸው። ስሜን ኢትዮጵያ በጦርነት ወላፈን ውስጥ? 
 
ግን በውነት ስሜን ኢትዮጵያ እና #ህዝቡ ለብልጽግና መንግሥት አያስፈልገውምን? እኛ እማናውቀው ስውር ነገር ይኖር? በብልጽግና መንግሥት 50+ መታመን፤ እንክብካቤ፤ አትኩሮት እማስተውለው ለደቡብ ነው፤ ይህን አስቤ የህወሃትን እንደ አሻው በባዙቃ እንዲቧርቅ መፈቀዱን ስታዘብ ፍች አጣለታለሁኝ። የሆነ ሆኖ ቅዱሳኑ ህፃናት ያሳዝኑኛል። 
 
#ከቶ ባለቤት ለሌላቸው ህፃናት ማን ይሆን ሁነኛቸው????? 
 
#ህፃናት ለአንድ መንግስት ………
 
* ምርቃት፦
** ሽልማት፦
***የእዮር ስጦታ፦
**** የበረከት ማሳ፦
***** የውስጥ ሐሤት ማመንጫ፦
****** የፍቅር ፏፏቴ፦
******* የውስጥ ሰላም አመንጪ፦
******** የብርኃን አቀራራቢ፦
**********የምህረት ዓዋጅ፦
*********** የንጽህና ምስክር፦
************* የድንግልና ዋቢ፦
የአጽናኝነት ብሩህ ሩህ ናቸው። ወዘተ ………
 
የተስፋ መግቦት ህፃናት ናቸው። ግን ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ከአጀንዳ ውጭ ናቸው። ማኒፌሶቶ ላይም የተዘነጉ ናቸው። ስለሆነም የሁሉም መከራ የመጀመሪያ ተጠቂወች እነሱ ህፃናት ናቸው። የፖለቲካ ውክልና አልባ ናቸው። ተቋም ቢኖራቸው በሌላ በኩል ግን ……… ከስሜን እስከ ደቡብ፤ ከደቡብ እስከ ምስራቅ፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ለደረሰው መጠን የለሽ ግፍ እና መከራ #የህወሃት ኔት ወርክም ከሱማሌ ክልል በስተቀር እንዳለ ቢዘገይም ግልጽ ብሎ ተረድቶኛል። 
 
በብልጽግና መንግሥት ውስጥ ለህወሃት አፍቅሮት ያልተገዛው ብቸኛው ክልል ሱማሌ ብቻ። በዚህ አጋጣሚ የሱማሌ ክልል አቶ ሙስጦፌን የመስተዳድሩ ፕሬዚዳንት፤ ቲሙን በሙሉ ትሁት የሆነ ምስጋና አቀርባለሁኝ። ጊዚያችን ብቻ ሳይሆን መንፈሳችን ሁሉ ጥግ ያገኜልን በእነሱ የሰከነ ብልህ አመራር እና ጥበብ ነው።
 
የማከብራችሁ የአገሬ ልጆች እንዴት አደራችሁ፤ አረፈዳችሁ ዋላችሁ?
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
 
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
31/01/2026
ቅድሚያ ለህፃናት ሰላም ይሰጥ!

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።