#ኢህአፓ የ2018/ ግንቦት 24 የምርጫ ዕድሉን #ማፍሰስ አይኖርበትም የሚል እምነት አለኝ።

 


#ኢህአፓ የ2018/ ግንቦት 24 የምርጫ ዕድሉን #ማፍሰስ አይኖርበትም የሚል እምነት አለኝ።
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 
 
 
#ምዕራፍ ፲፰
 
አንድ የፖለቲካ ድርጅት የመደራጀት ሚስጢሩ ለፖለቲካ ሥልጣን ነው። አንድ የፖለቲካ ድርጅት የትግሉ ስትራቴጂ መስመር ሰላማዊ ትግልን መርጦ በኢትዮጵያ ሥራ ላይ በሚገኜው ህገ - መንግሥት (ተቀበልነውም// አልተቀበልነውም) ሥር ለመሆን ከፈቀደ፤ እና የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ህጋዊ ፈቃዱን ከሰጠው ዕድሉን ሳያፈስ ወይንም #ሳያሻግተው ሊጠቀምበት ይገባል።
 
ኢህአፓ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅት ታሪክ ውስጥ ብዙ የፖለቲካ ሊቃናትን ያፈራ፤ የፖለቲካ ድርጅትን ጽንሰ ሃሳብ ያስተማረ፤ ተደራጅቶም የታገለ፤ ያታገለ #የትውልድ ፓርቲ ነው። እርግጥ ነው የአደረጃጀት ባህሉ አዲስ ከመሆኑ አንፃር የተለያዩ አንጃወች በየዘመኑ ተከስተዋል። በትግሉም ብዙ የኢትዮጵያ ወጣቶች ተገብረውበታል፤ ታስረዋል፤ ተሰደዋል፤ ወዘተረፈ ፈተና አስተናግዷል።
 
የየትኛው የኢህአፓ መሪ እንደሆን ባላውቅም አንድ የኢህአፓ አካል አገር ቤት በሰላማዊ ፓርቲነት ተመዝግቦ እየታገለ ይገኛል።ለእኔ የተፎካካሪ ፓርቲነት አቅም እንዳለውም አስባለሁኝ። የኢህአፓ ወጣት መሪወች የሚያደርጉትን ቃለ ምልልስ አዳምጣለሁኝ። እኔ እምጽፈው 4/5/6 የፖለቲካ ድርጅቶች በመቀያዬር የሚታወቁ የኢህአፓ የወቅቱ አካላትን አይደለም። 
 
እነኝህ አካላት የድርጅት የማንነት #ቀውስ ስለሚፈትናቸው ለድርጅቱ ፈተና እንጂ ትሩፋት እንደማይሆኑ አስባለሁኝ። ስለሆነም ከእነሱ እምጠብቀው በጥበጥ አድርገው አንጃ መፍጠር ወይንም መንገድ ማሳትን ነው። ሱሰኞችም ናቸው ለዘርፋ። የነበሩበትን አፈራርሰው የአዳዲስ ስብስብ ናፋቂነታቸውን ቁጭ ብለን እያዬን ኑረናልና። አላተረፈምም። 
 
ኢህአፓን የተቀላቀሉ ወጣቶች ንጹህ ህሊናን ይዘው ወደ ድርጅቱ ስለሚቀላቀሉ ሥርዓታዊ እና የጠራ መስመር ይከተላሉ ብዬ አስባለሁኝ። እኔ ዕይታዬን ላጋራ እምሻውም ለእነኝህ #እሸታዊ ትንታግ ወጣት የኢህአፓ መሪወች እና አባላቱ ነው።
 
ስለሆነም ወጣቶች 5 ዓመት እንደ ገና ጠብቀው ሌላ ተስፋን ከሚያስቡ ዕድሜም አቋሚ የለውም ይነጉዳል፤ በመዳፋቸው ባለው ዕድል ተጠቅመው፤ #ለእቅማቸው አዲስ አቅም ጋር ቢገናኙ ምርጫዬ ነው። ባለፋት ሰሞናት የአንከር ሚዲያ እና የኢህአፓን፤ የባይፈርስ ሚዲያ እና የኢህአፓን፤ የአንድ አፍታንና የኢህአፓን ሙግት አዳምጫለሁኝ። ወጣቶቹ ያላቸው የተነሳሽነት አቅም፤ ጥያቄወችን የመመከት ብቃትን አስተውያለሁኝ።
 
የኢህአፓ ወጣቶች የድርጅታቸውን ዓላማ እና ግብ ጠንቅቀው የሚያውቁ፤ እና አቅማቸውንም #ማስተር ያደረጉ ወጣቶች ሆነው አግኝቻቸዋለሁኝ። ስለሆነም ይህ አቅም #ሳይወይብ በዚህ ሙቀት ልክ ወደ ምርጫ ቢገባ የተሻለ ይሆናል ምርጫውን በስማ በለው በአሻጋሪ እያዬ ሌላ 5 ዓመታትን ከሚጠብቅ።
 
ቅንጅት ዕድሉን ተጠቅሞበት ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሌላ ገጸባህሬ በኖረው ነበር። መስዋዕትነቱንም በብዙ ማስቀረት ይቻል ነበር። የዘንድሮ ምርጫ ለቅንጅት 50+ የመሆን ዕድሉም አስተማማኝ ነበር። አዲስ አበባም #የሰማይ የኤዶም ገነት እንዲህ ባልሆነች ነበር። አንድ ነገር ለማትረፍ ሲሆን በመጠኑ መክሰርን ማስላት ይገባል እንጂ ሙሉአቅምን በትኖ ችሮታን ከሌላ ማሰብ አይገባም። 
 
ሁሉንም በኪሳራ አለማወራረድን የፖለቲካ ብስለትን + ዊዝደምን ይጠይቃል። የቅንጅት መራራ ስንብት እና የተበተነው አቅም በአራት አምስት አቅጣጫ መንጎድ ትውልዱን ብዙ ዋጋ አስከፍሏል። የህሊና፤ የተስፊ፤ የፋይናንስ፤ መዋዕለ ዕድሜን የዘረፈ ገጠመኝ ነበር። አሁንም ይህ ገመና ዓመት ድገም ተብሎ፤ ምርጫውን ባለመሳተፍ የጎላ ውሳኔ ከኢህአፓ የሚጠበቅ ታላቅ የሚዲያ የምስራች ነው።
 
#እኔ ግን እላለሁኝ ………
 
ኢህአፓ እንደ አንጋፋነቱ ስሜቱን አስክኖ፤ በእርጋታ እና በማስተዋል አስቦ ዕድሉን ሳያወይብ ወይንም ሳያጨመታትር፤ ታሪካዊውን የራሱን ዘመን በአዲስ ብዕረ - ትንታግ የሚጽፍበት ውሳኔ ላይ ሊደርስ ይገባል ባይ ነኝ። አንጋፋ መሪወቹ በህይወት እያሉ የኢህአፓ የፓርላማ ውድድር እና አሸናፊነት ከተረጋገጠ፤ ኢህአፓ በመንግሥት ሥርዓት ውስጥ የመሳተፍ ዕድሉን ያበራለታል። ጥቂትም ይሁኑ አሸናፊወች ብቻ የኢህአፓ አባላት፤ የኢህአፓ አካላት በታሪካቸው በኢትዮጵያ #ፓርላማ ተመርጠው ቤተኛ መሆናቸው፤ የትግሉን መንፈስ ከሞናትነስ አውጥቶ ያድሰዋል፤ እንዲያሽት ያደርገዋል።
 
በምርጫ መሳተፍ ሥርዓት አስቀጣይ አይሆንም። በፍጹም። ወይንም በምርጫ አለመሳተፍ ሥራ ላይ ያለውን የየትኛውም አገር የፖለቲካ ድርጅት መሪነት አይነቅለውም። ሥርዓት ለመቀየር፤ ወይንም ለውጥ ለማምጣት የሚጠይቀው የንጥረ ነገር ዲስፕሊን ገና አልተደረሰበትም። ህወሃት እኮ በምርጫ ብቸኛ አሸናፊ ነበር? ህወሃት በምርጫ ማሸነፋ ሥርዓቱን አላስቀጠለውም። ይህ ፋክት ነው። ሥርዓቱን የጣለው የተቃዋሚ ድርጅቶች ጥንካሬ እና ብርታትም አልነበረም። በተለዬ መንገድ እና ዘዴ ነበር የሆነው - የሆነው።
 
#የሆነ ሆኖ ኢህአፓ በምርጫ ቢሳተፍ ምን ትርፍ ያገኛል? ለሌሎችም ሃሳቤን በቀና ካዩት ይረዳል። 
 
1) አባላቱን በተሟላ ሁኔታ ማነቃቃት ይችላል።
2) ከገዢው የብልጽግና ፓርቲ ጋር አላስፈላጊ ቅራኔ ውስጥ ገብቶ አቅሙን አያዝልም። ወይንም በቀጣይ አላስፈላጊ መስዋዕትነት አይከፍልም። በምርጫው ኢህአፓ ወሸኔ እንኳን መጣህልን፤ አሸወይና ብሎ ገዢው ፓርቲ ብልጽግና እንደማይጠብቀው አውቃለሁኝ። ግን ከአሻም ይልቅ እሺ ብዙ ያተርፋል። 
 
3) ለኢህአፓ የመዋዕለ ዕድሜ ታጋዮች አንጋፋ መሪወቹ አዲስ የህይወት ተስፋን ያጎናጽፋል።
4) የምርጫ ተሳትፎው ኢህአፓ ያለውን አማራጭ ሃሳብ ለህዝብ ለማቅረብ ይሁን ለማስተዋወቅ የመንግሥት ሚዲያ አክሰስ ያገኛል።
5) ለኢህአፓ ወጣት መሪወች አዲስ የልምድ እና የተመክሮ ማሳ ይገኛል።
 
6) የመመረጥ ዕድል ከገጠመው ፊትለፊት ገዢውን ፓርቲ ብልጽግናን ለመሞገት ምቹ ሁኔታ ይፈጠርለታል።
7) ስለኢህአፓ የወደቁ ወጣቶች እና ቤተሰቦች አዲስ የመጽናናት መንፈስን ያፈልቃል።
ስምንተኛ) ኢህአፓ በመንግሥት መዋቅር የመሳተፍ ዕድሉ በር ይከፈትለታል። ይህ ደግሞ ለየትኛውም የመሪነት እርከን የማይገኝ ዕድል ነው። 
 
9) አዳዲስ አባላት፤ አካላት፤ ትጉህ መሪወችንም የማግኜት ዕድሉ ይሰፋል።
10) የምርጫ አየሩ ሲጧጧፍ ሙቀቱ፤ ተሳትፎው፤ ፋክክሩ ለኢህአፓ አሻግሮ የሚዬው ሳይሆን ቤተኛ የሚሆንበት ስለሚሆን የመደራጀቱ ዓላማ እና ግብ ተቀራርበው እንዲለካኩ የዕድል በር ይከፍታል።
11) ምርጫ የራሱ ህግ እና ሥርዓት ሥላለው አዲስ የሆነ የልምድ ሁነት ያገኛል።
12) በዓለም ዓቀፍ ደረጃም ቢሆን የኢህአፓ የተሃድሶ ጉዞ ሊጀምር ይችላል።
13) ወደፊትም ከሚመጡ የበታች አካሎቹ መሪወች ጋር የመቀራረብ፤ ብቃት የመፈታተሽ አጋጣሚ ያገኛል።
14) ኢህአፓ የራሱን አቅም፤ የራሱን ብቃት ይለካበታል፤ ይመዝንበታል። ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ያለውን የብቃት ልኩን ለመለካት የምርጫ ተሳትፎ አዲስ ራዲዮሎጂ ነው።
15) ድክመቶችን የማወቅ አጋጣሚ ያገኛል ወዘተ ……
 
#ምርጫውን ኢህፓ ባይሳተፍ ………
 
1) ዝምታ ጋር ይተቃቀፋል።
2) በምርጫ ሞክሮ ከሚገጥመው የበለጠ እና የገዘፈ ፈተና ሊገጥመው ይችላል።
4) የትግሉ ባህሬ አዘቦታዊ ይሆንና ወደ መሰላቸት ሊያመራ ይችላል።
5) የድጎማ በጀትም አያገኝም።
6) ኢህአፓ የራሱን አቅም የሚፈትሽበት፤ ከሌሎችም ጋር የሚፎካከርበት የሚዛን ሁነት ዝግ ይሆናል።
7) አዳዲስ ብቁ ወጣቶችን የማግኜት ዕድሉ ይደበዝዛል።
ስምንተኛ) የመሪነት ተስፋው አዝጋሚ ይሆናል።
9) ከምርጫ ህግጋት፤ መርህ እና አስተውሎት ጋር ፈቅዶ ይራራቃል።
10) አዲስ ሃሳብ አፍልቆ ለመፎካከር እንደገና 5 ዓመት የመጠበቅ ግዴታ ይኖርበታል።
11) ዕድል ሲፈስ አቅም ይጠወልጋል። የአቅም መቅኖ ተሳትፎ ነውና።
12) ስለምርጫው የተመክሮ ማሳ ባይተዋርነትን ያስተናግዳል። ወዘተ ……
 
አንድ የፖለቲካ ድርጅት በምንም ታምር በኢትዮጵያ የመንግሥት ሥርዓት ውስጥ ለመሳተፍ ያገኜውን ዕድል ፈቅዶ እና ወዶ ሊሸበሽበው አይገባም። ኑሮውን እሱ እንጂ ሌሎች ስለማይኖሩለት አንድ የፖለቲካ ድርጅት በማንነቱ ውስጥ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን ዕንቁ ዕድሉን ለማንም፤ ለምንም አሳልፎ ሊሰጥ አይገባም። 
 
አንድ የፖለቲካ ድርጅት ከተደራጀበት ዓላማ እና ግብ ማስፈጸሚያው ከሆነው የማኒፌስቶው እንደራሴነት በጎረቤት፤ በደባል፤ ወይንም በስማበለው ሳይሆን እሱ እራሱ በእራሱ ውስጥ ስለመኖሩ ማረጋገጥ ዬኖርበታል። ይህ ሳይሆን ከቀረ ለአንድ የፖለቲካ ድርጅት ጉዞ ከባዱ ሁነት አናርኪዝም ነውና ይህ እንዳይከሰት የሚረዳው የራሱ ታሪክ ሰሪ እራሱ ብቻ ስለመሆኑ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ሲቆርጥ እና ሲወስን ብቻ ይሆናል። ወሰን ሳይሆን #ደንበር ሊኖር ይገባል።
 
አንድ የፖለቲካ ድርጅት ለምርጫ እራሱን በሁሉም መስክ አጠናክሮ፤ ህግን አክብሮ እና አስከብሮ፤ ጊዜን መዝኖ እና ጠብቆ መገኜት እንጂ #የቅድመ ሁኔታ ድርደራ ቀና መንገድ አይደለም። ለመፍትሄም የሚያቀራርብ አይሆንም። በርከት ብሎ ፓርላማ ላይ እውነተኛ ተፎካካሪወች ፓርላማ ውስጥ ከተገኙ እዛው ሞግቶ በድምጽ ብልጫ ዛሬ ለምርጫ አሳሪነት የሚዳርጉ ቅድመ ሁኔታወችን በሃሳብ የበላይነት ማረጋገጥ ይቻላል። መወሰን እና ማስወሰን ይቻላል። ምርጫን አለመሳተፍ የአንድ ሰሞን የዜና ቤተኛ ነው፤ በፓርላማ ተወዳድሮ አሸንፎ ቤተኛ መሆን ግን የሙሉ 5 ዓመታት አጀንዳነትን ያረጋግጣል። ይህ ደግሞ የሚቻለው ዕድልን #ሳያበልዙ፤ የዕድልን ጤናማነት በዲስፕሊን አግዞ ተሳትፎን ማላቅ መቻል። 
 
ኢህአፓ ቀን ብቻ ሳይሆን ሌሊቱንም ጨምሮ ሊተጋ ይገባል። #መዘናጋት አያስፈልግም። ማህል ቤት #መዋለልም አያዋጣም። ሃሳብን ይበትናል፤ መቅኖን ያፈሳል። ያለው ጊዜ አጭር ነው ሃሳብን፤ መንፈስን በቅጡ አደራጅቶ ከጊዜ ጋር አብሮ መጓዝ ያስፈልጋል። ሞራላዊ ብልጫ በተሟላ ሁነት ከኖረ ለኢህአፓ ቀጣይ ተስፋ የአቅም ፏፏቴ ምንጭ ይሆናል። 
 
በመሳተፍ ውስጥ ነው የልምድ ሆነ የተመክሮ መገኛው። የመረጃ ባለቤትነት ሆነ የክህሎት አትራፊነት የሚረጋገጠውም ፈቅዶ በዕድል ጊዜን ሳያባክኑ በመሳተፍ ነው የሚገኘው። ከኢህአፓ አንጋፋ መሪወቹ ውስጥ #ትዳር ሳይመሰርቱ፤ ልጅ ሳይኖራቸው፤ መኖራቸውን ለዓላማቸው የሰጡ መኖርን ያልኖሩበት መሪወች ኢህአፓ እንዳሉት አውቃለሁኝ። 
 
በአካልም አግኝቻቸው ነበር። ተስፋቸው መጠነ ሰፊ እንደ ነበር ያን ጊዜ ለማወቅ ችያለሁኝ። ምንም እንኳን እኔ ከኢህአፓ ድርጅት ጋር ቤተኛ ባልሆንም የተጓዘበት ሁነት ግን የታሪካችን ክፍለ አካል መሆኑን አምናለሁኝ። ፈተናውን ከልጅነት እስከ ዕውቀት በማዬቴ ኢህአፓ በዕድሉ ተጠቅሞ፤ ዕድሉ ቢከፈትለት ምርጫዬ ነው።
 
ምርጫውን ለመቀበል ኢህፓ ከወሰነ #ይቀናው ዘንድ እመኝለታለሁኝ። ሞክሩ። 
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ኑሩልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
10/02/2026
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።