የብልጽግና የስንዴ #ነዷዊነት የጉዞ ቁመና በሥርጉትሻ ዕይታ።
የብልጽግና የስንዴ #ነዷዊነት የጉዞ ቁመና በሥርጉትሻ ዕይታ።
መጽሐፈ ሩት ምዕራፍ ፪ ቁጥር ፯ …
«እርስዋም። ከአጫጆቹ በኋላ በነዶው መካከል እንድቃርምና እንድለቅም፥
እባክህ፥ ፍቀድልኝ አለች፤ መጣችም፥ ከማለዳም ጀምራ እስከ አሁን ድረስ ቆይታለች፤
በቤትም ጥቂት ጊዜ እንኳ አላረፈችም አለው»





#ምዕራፍ ፲፰
ይህ የፖለቲካ ፓርቲ የአደረጃጀት፤ የመርህ አፈፃጸም ጉዳይ #የተማርኩትም፤ #የሠራሁበትም ስለሆነ ትዝብቴን እንሆ … የዕለቱ አትኩሮቴ፣ #በምርጫ ምልክቱ እና #በማንፌስቶ ዙሪያ ይሆናል። #ምንጭ ፎቶውን ጨምሮ ፋና ቴሌቪዥን እና የብልጽግና ፖለቲካል ፓርቲ ፌስቡክ ፔጅ ላይ ነው የወሰድኩት። ከሥር ተያይዟል።
• #የምርጫ ምልክቱ እና ማንፌስቶውን ማንስ ያጸድቀዋል?
አጽዳቂው የአባላት ጠቅላላ ጉባኤ ብቻ ነው።
1) ድርጅት ምንድን ነው? በቀላል አገላለጽ ሁለት እና ከዚያ በላይ ሰወች፤ ተቋማትም ሊሆኑ ይችላሉ፤ በፆታቸው፤ በዕድሜያቸው፤ በሙያቸው፤ በሃይማኖታቸው፤ በኢኮኖሚ አቅማቸው፤ በራዕያቸው ዙሪያ በሚያስማማቸው፤ በሚያግባባቸው ዓላማ እና ግብ፤ ወይንም ፍላጎት የሚፈጥሩት አቅምን፤ ኃይልን እና ጉልበትን የሚያማክሉበት ሥልጡን የሆነ የተቋም፤ የሥርዓት ለመመሥረት የመሰባሰቢያ ስልት ነው። መንግሥት እራሱ ድርጅት ነው።
2) የፖለቲካ ድርጅትስ?
የፖለቲካ ድርጅት የዓላማ እና የግብ ጥምረት ሳይሆን፤ ውህደትን የሚያበስር ተቋም ነው።
3) አንድ የፖለቲካ ድርጅት አካላት አሉትን።
አለው። የመጨረሻው የሥልጣን አካል ብሄራዊ ጉባኤ ሲሆን፤ መሰረቱ አስኳል ከሥር ይጀምራል። ሁለቱ አካላት የወረዳ፤ የዞን፤ የክልል በኢትዮጵያ ዕሳቤ የሚያገናኙ ሊንኮች ናቸው።
የአንድ የፖለቲካ ድርጅት ጉባኤ ብሄራዊ ብቻ ስለሆነ ከዞጋዊ ዕሳቤ የወጣ ተደርጎ ሲተነተን ስለማደምጥ፤ ይህ ዕሳቤ ትክክል አይደለም። የውክልናው መንፈስ ነው አንድን የፖለቲካ ድርጅት ዞጋዊ ወይንም አገራዊ ሊያደርገው የሚችለው።
በብልጽግና አደረጃጀት ብሄራዊ ጉባኤ ብቻ ነው ያለው። ይህ በመሆኑ አገናኝ መስመሩ የተጎረደ ነው። የአባላቱ ከአካላቱ ጋር የሚገናኜው መስመር መተው ድርጅቱ ለውስጥ ህመም ተጋልጧል።
የሆነ ሆኖ ጠቅላላ የአባላት ጉባኤ የቀጥታ አይደለም የውክልና ነው። ማን ወከላቸው? ለሚለው የየደረጃው የተዋረድ አካላት ብልጽግና ስለለው ድርጅቱን ተንሳፋፊ እንዲሆን አድርጎታል።
ሊሆን የሚገባው ግን መሰረታዊ ድርጅት አስኳል የቀጥታ ውክልና አልቦሽ ይሆንና ወረዳውን፤ ወረዳው ዞኑን፤ ዞኑ ክልሉን፤ ክልሉ ብሄራዊውን ቢፈጥር የሰላ ፈጣን ግንኙነት ለመፍጠር ይቻል ነበር።
#ብልጽግና ያለው አካል
3.1 ብሄራዊ ጉባኤ፤
3.2 ማዕከላዊ ምክር ቤት፤
3.3 ሥራ አሥፈፃሚ በሶሻሊስቱ ርዕዮት ፖሊት ቢሮ የሚባለው ይሆናል።
ጉባኤው እስኪሰበሰብ ድረስ የጉባኤውን ኃላፊነት ማዕከላዊው፤ የማዕከላዊው እስኪሰበሰብ ድረስ ኃላፊነት የብሄራዊው ሥ/አ ወይንም ፖሊት ቢሮው የዕለት ተዕለቱን ተግባር ይከውናሉ። ከሥር ያሉት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ነው ያለው።
የአንድ የፖለቲካ ድርጅት ሰነዶች በሦስት ዋና ክፍሎች ይሰናዳሉ።
1) ደንብ። ስለደንብ የሰማሁት የለም።
2) ፕሮግራም ወይንም ማኒፌስቶ። ስለማኒፌስቶ አዳምጫለሁኝ። የብልጽግና ማኒፌስቶ አለንበረውንም? ወይንስ በየምርጫ ዘመኑ አዲስ ያዘጋጃልን? አልገብቶም።
3) መሪ ዕቅድ። ስለ መሪ ዕቅድም የሰማሁት የለም። ብቻ አወን ብቻ በፓርቲ የአደረጃጀት መርሆወች ሦስቱም መሠረታዊ ሰነዶች የሚጸድቁት፤ የሚሻሻሉት በብሄራዊ ጉባኤ ብቻ ነው።
1) ደንብ ለፓርቲ አባላት የፖለቲካ ህይወታቸውን የሚመሩበት ሰነዳቸው ነው። የአባልነት (አባልነት በፈቃደኝነት ነው፤) የአርማ፤ የስብሰባ፤ የአካላት አወቃቀር እና አደረጃጀት፤ የአደረጃጀት መርኽ በሶሻሊዝም ዲሚከራሲያዊ ማዕከላዊነት የሚባለው። የአካላት የኃላፊነት ተዋረድን ይይዛል።አጭር እና ግልጽ ሆኖ ይዘጋጃል።
2) ፕሮግራም (ማኒፌስቶ ) የፖለቲካ ድርጅቱን ዓላማ እና ግብ የያዘ ታላቅ ሰነድ ሲሆን። አጭር እና አቅጣጫ አመልካች ነው።
3) መሪ ዕቅድ ደንቡ እና ፕሮግራሙ ተዋህደው ተግባር ላይ እንዲውሉ የሚያስችል ይሆናል። ሦስት ምዕራፎች ይኖሩታል።
3.1 የአጭር ጊዜ። ከ6 ወራት እስከ አንድ ዓመት ሊሆን ይችላል።
3.2 የመካከለኛ ጊዜ። የረጅሙን እና የአጭር ጊዜውን የሚያገናኝ ሊንክ ነው። (ከአንድ ዓመት እስከ ሁለትም፤ ሦስትም ዓመታት ሊይዝ ይችላል።
3.3 የረጅም ጊዜ ዘለግ ያለውን የተግባር ራዕይ አመላካች ነው። ከ5 - 10 ዓመት ሊሆን ይችላል።
ከደንብ፤ ከፕሮግራም፤ ከመሪ ዕቅድ የሚጨመቅ ሌላ ተጨማሪ ሰነድ ይኖራል። የአፈፃጸም ዝርዝር ሁነቶችን የሚይዝ። የእያንዳንዱን አካላት ኃላፊነት እና ተጠያቂነት በዝርዝር የሚገለጽበት ይሆናል።
#ብሄራዊ ጉባኤው ጉልህ ተግባራትን ይከውናል።
1. ሦስቱን መሠረታዊ ሰነዶች ያጸድቃል።
2.የፓርቲውን ማዕከላዊ ኮሜቴ ወይንም ምክር ቤት ይመርጣል። የጎደሉ ካሉም የማሟያ ምርጫ ያካሄደል።
3. የቁጥጥር ወይንም የኤዲት ኮሚሽን ይመርጣል።
4. የማዕከላዊ ኮሚቴውን እና የቁጥጥር፤ ወይንም ኦዲቲንግ ሪፖርት ያደምጣል፤ ይመረምራል፤ ያጸድቃልም።
#የብልጽግና የሰሞናቱ ስብሰባ ይሁን ጉባኤ አልገባኝም።
ጉባኤ ከሆነ ሰነዶቹ ቀርበው መፈተሽ ይገባቸው ነበር። ማሻሻያ ከኖረም፤ ማሻሻያወቹ ሊጸድቁ ይገባ ነበር። ይህን አላዬሁም። ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ለሆቴል ምረቃት የሚገኙት ለዚህ ታላቅ እና ወሳኝ የምርጫ የመሰናዶ ስብሰባ ይሁን ጉባኤ አልተገኙም። አልገባኝምም።
በሌላ በኩል ማኒፌስቶ በየስብሰባው የሚቀየር ፈጽሞ አይደለም። ይህ ብቻ አይደለም በአዲሱ የብልጽግና ማኒፌስቶ አራት መወች፤ ሁለት ውሃወች ይልና ማኒፌስቶው ከዚህ ቀድም የሠሩትን እንደገመገሙበትም ይገልፃል። ለእኔ ለሥርጉተ ሥላሴ ይህ ማኒፌስቶ ሳይሆን ሪፖርት ነው። ሪፖርቱን ነው እንደማኒፌስቶ አጸደቅኩ የሚለው ብልጽግና። የፖለቲካ ድርጅት ጽንሰ ሃሳብ፤ የአደረጃጀት መርህ የገባቸው አይመስለኝም። በፍጹም ማኒፌስቶ የሥራ ግምገማን አይዝም። ማኒፌስቶ እኮ መጽሐፍ አይደለም። ሊሆንም አይችልም። የእስካሁኑ ስኬቶችን ግምገማ ማኒፌስቶው ላይ እንደተገለጸ ነው አቶ አዳም ፋራህ የገለፁት።
እንዲህ እንዲህ ዓይነቶች ከመርኽ ጋር ይዋጋሉ፤ አባላትን፤ አካላትን ለመምራት #አቃች የሚሆነው። ሥረዓት አልበኝነትም የሚመጣው በዚህ መሰል ፈጽሞ ሊገባ በማይችል ዝንቅንቅ ፍላጎቶች ነው። ሪፖርቱን በአጀንዳ አስይዞ ማጸደቅ ይቻላል። #ማኒፌስቶውን ራዕይን ብቻ ነው መያዝ የሚኖርበት። ለመጽደቅም ጉባኤ ነው የሚያጸድቀው። ሲጸድቅም ፕሬዚዳንቱ መገኜት ግዴታቸው ነው። በየጉባኤው ማኒፌስቶ??? ኦ! ብልጽግና ማዳመጥ የምትችልበትን አቅም ፈጣሪ ይስጥህ። አሜን።
«የፓርቲያችን የምርጫ ምልክት “የስንዴ ነዶ” ነዉ በዚህም መሠረት የፓርቲያችን የምርጫ ምልክት “የስንዴ ነዶ” ነዉ ። ምልክቱም የመደመር፣ የትብብር እና የአንድነት ምልክት ማሳያ ነው፡፡»
«የህዝባችንን ድጋፍ ይዘን መጪዉን ጠቅላላ ምርጫ በማሸነፍ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር የማሸጋገር አላማ ሰንቀናል- አቶ አደም ፋራህ»
የብልጽግና የምርጫ ምልክት አጤ ነዶ። በጣም አሻሚ የሆነ ትርጉም አለው። ዕይታዬን እንሆ ………
• ነዶ የሰብዕናን ሥነ - ባህሬ ከአከለ ወደ #አራት የሚሆኑ ትርጉሞች ነው ያለው። ጠብቆ ሲነበብ እና ላልቶ ሲነበብ ትርጉሙ ይለያያል። ላልቶ ሲነበብ። በሌላ በኩል። ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ቀን የሰጠው የስንዴ ነዶ፤ የሰብዕናን ሥነ - ባህሬ ከአከለ ወደ አራት የሚሆኑ ትርጉሞች አሉት። የማይገናኙ የትርጉም ፍሰት ይኖረዋል።
1) የሣር ዘር የእህል ዛላ ፤ ሣርም ሊሆን ይችላል አንድ ጭብጥ ሙሉ በራሱ በዛላው ሲታሰር፤
2) ነዶ ያልተሰፋ #ልብስ በቦንዳ ወይንም ተመትሮ ለመሰፋት ሲዘጋጅ።
3) የነደደ፤ የተቃጠለ ነገር፤ መንደድ ከጪስ ጋር ይገናኛል፤ ጢስጥንብስ የሚል ትርጉምን ያስከትላል፤ ሊነሳ የማይችል ጥረት፤ ስኬት #ፊትየነሳው ጉዞ ወዘተ ተጫጭሶ ደግሞ የብርሃን አቅም መስጠትም አለ። ማገዶነትን ያመለክታል። መራር ትግልን ለማመልከት ይሆንም ብያለሁኝ?? ለነገሩ ብልጽግና በአሁኑ ወቅት ገዢ፤ አራጊ ፈጣሪ፤ አዛዥ ናዛዥ ነው። አፈጣጠሩም አልጋባልጋ ነው። አንዲት የከፈላት መስዋዕትነት የለውም። ዕድሜ እኔን ለመሰሉ የመዋለ ዕድሜ የነፃነት ፈላጊ ታጋዮች። የሆነ ሆኖ የሚነድ ነገር ጭስም አለው። ጭሶ ወደ አመድ ለመሄድ ጉዞ ጀማሪ … ም ……… ነው።
4) በባህሬ ብስጭት ሆነ ቁጣ ሲይል ወይ ነዶ! ውስጥ ጭስ ሲል።
• #ነዶ።
የታሰረ የጤፍ፤ የዘረ - ገብስ( በልጋ - ዱራኛ - አውራ - ሰነፍ - ጠመጅ - የስንዴ - የሣር ነዶ « መታሰር? ሲታሰር እሱ በሱ ነው፤ ሊቦደስም ይችላል የታሰረበት ጥንካሬ ጊዜያዊ ነው። "መታሰር በራሱ መተንፈስ ሲያቃትት፤ ተጫኝ ሲኖርበት፤ ነፃነት ያጣ ትርታን ያመላክታል።
• አንድ የምርጫ መለያ ምልክት ቀጥ ያለ፤ የማያሻማ፤ ለአሉታዊ ዕይታ የማይጋለጥ፤ ያልተወሳሰበ፥ ግልጽ እና ቀላል ፍቺ ያለው ለተማረም ይሁን ላልተማረም እኩል ሊገባ የሚችል፤ በሁሉም የህይወት ዘርፍ ቤተኛ የሆነ፤ የነፍስ ወከፍ መኖር ላይ የሚገኝ ሊሆን ይገባል። ነዶ የሚቀርበው ለገበሬው ነው። ገበሬ ሆኖም መሬቱ ስንዴን የማያመርት ሊሆን ይችላል። በዚህ ሃሳብም ሁሉን ገበሬ ላይወክል ይችላል።
• «መደመር የሂሳብ ግሎባዊ ቀመራዊ ምልክት አለው «+»። (÷×±><=) እንደ ማባዛት፤ ማካፈል ወዘተ በተጨማሪም ተፈጥሯዊ ምልክት አለው።
#ነዶ ሲመዘን።
ነዶ። እሸት፤ ያፈራ፥ ያሰበለ፤ ያልተወቃ ለዓይን ደስ የሚል፤ ተስፋ የሚሰጥ፤ ራህብን የመቋቋም አቅም ያለው፤ ሃይል - ጉልበት በገብያ ሥርዓት ሊመራ የሚችል የኢኮኖሚ አካል - በገብያ ህግ ሊተዳደር የሚችል እያልን ልንተነትነው እንችላለን፤ የምግብ ዐይነት እራህብን መቋቋም የሚችል፤ በእኛ ባህል ሃዘንተኛ ከቀብር ሲመለሱም የስንዴ ንፍሮ ይቀርባል፤ ፍሬው ከአቃፊ አካሎቹ ከተለዬ በኋላ ቀሪ ክፍሉ ለእንሰሳት መኖም ይሆናል።
• ብልጽግና ፓርቲ የሰጠው ትርጉም ግን ፈጽሞ ከስንዴ ነዶ ተፈጥሮ ጋር የማይገናኝ ነው። «የመደመር፤ የአንድነት የትብብር።» መታሰሩን በአውንታዊ አይቶት ሊሆን ይችላል።
#የሣር ዘር የሆነው ስንዴ ዛላው ሳይሆን ጥራት ያለው ፍሬው በቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ለቅድስና ተልዕኮ የተመረጠ፦ ዘላለማዊ ህይወትን የሚያጎናጽፍ።
በሌላ በኩል ደግሞ ነዶ እንደታሰረ ሲሆን ግን ያልተጣራ ነገር ሣርም አለበት። ለከብቶች መኖ የሚውል።
• «መደመር» ተፈጥሯዊ ምልክት አለው። በእኛም በፊደላችን #ተ አለች። ከፊደላት ተን እወዳለሁኝ። ሁሉጊዜ እጽፋለሁኝ። ተስፋ የሚል ሥም እወዳለሁኝ፤ ሥሙ ከተ ነው የሚነሳው። የጸጋዬ ራዲዮን ለ፲፰ኛ ዐመት ሳስቀጥል ሙሉ ፕሮግራሜ ሲጀምር በተስፋ ነው፤ የመጀመሪያው መጽሐፌ ሥሙ ተስፋ ነው፣ የፊት ለፊት ሽፋኑ ተስፋ ነው።
#አንድ ሌላ ምሳሌ እስኪ ላንሳ፤
• ሞሰብ ብንወስደው መሰብሰብን፤ አብሮነትን፤ ህብራዊ ማዕዳዊነትን - ጥበብን ወዘተ ይተረጉማል( የሞሰብ አሰፋፍ የራሱ ዲዛይን፤ የራሱ ንድፍ ያለው ነው። ብዙ ጉልበት ይጠይቃል። በዓመት ነው አንድ የጎንደሮች ሞሰብ የሚሰፋው። የአንገት አወራረዱ ተግባር በጣም ፈታኝ ነው፤ ይህም ሆን ምልክት ይሁን ቢባል ግን ሞሰብ ያረጃል፤ እዚህ ላይ ይወድቃል።
• #የትውልድ ለትውልድ የሚሆን ዘላቂ፥ ቋሚ፥ ሳቢ፤ አሰባሳቢ የልብ አድራሽ መለያ ምልክት እራሱ ጠሪ የመሆን ልዩ አቅም አለው፤ ተቀበሉ ሳይሆን ምርጫው ላይ አሳታፊ ሰብዕና ከኖረ ብዙ የተሻሉ አማራጮች ሊኖሩ ይችላሉ። ግን አብይዝም ከስኴር በላይ ነው።
#ስንዴም ፈተና አለበት።
1) የስንዴ አረማሞ አለ፣ ፍሬው ጠቀራ ሲያመርት አረማሞ ይባላል። ጥቁር አመድ ይወልዳል።
2) እንክርዳድ አለ።
3) መንቀዝም አለ።
4) መምከንም ይኖራል።
5) የተፈጥሮ ጥገኛ ነው። ድርቅ ከመታው ጫጭቶ ወደ ሳርነት ሊቀየር ይችላል።
6) ወጀብን የመቋቋም አቅም የለውም። የጠነከረ ወጀብ ሲገጥመው ለሽ ሊል ይችላል፤
#ስንዴ የማይፈቀድላቸውም አሉ።
ስንዴ ዘር ሳር ነው፤ ስንዴን #ጉልተ ፍራይ ስላልሆነ ስንዴን ፈቅደውም የማይመገቡት፤ በሃኪም ትእዛዝ የሚከለከሉ ህሙማን አሉ።
ባጠቃላይ የምርጫ ምልክት በፍጹም ጥንቃቄ ሊዘጋጅ፤ አማራጮች ሊሰናዱለት፤ አባላቱም አካላቱም በውክልና ሳይሆን በባለቤትነት ስሜት ሊወያዩበት ይገባ ነበር።
• #ፎቶወቹ …
እኔ ፎቶ ማዬት እወዳለሁኝ። ጊዜ ወስጄ ፎቶወችን አያለሁኝ። የሰማይ ፔንቲንግ ጋርም ተግቼ እሠራለሁኝ። ነገረ ፎቶ ለእኔ የዕይታ አድማሴን እማሰፋበት ልዩ አቅሜ ነው።
የፊት ረድፈኞች የብልጽግና ተሳታፊወች ጥልቅ #ድካም ይታይባቸዋል፤ የውስጥ ደስታን ዝግት ያደረጉት ይመስላል። የፓርቲ የመለያ ምልክት በተሰየመበት ዕለት ትንሽ ተስፋ ለሚመሩት ህዝብ ሊያሳዩ ይገባ ነበር። ውስጣቸው ከብልጽግና ጋር ሳይዳበል ከተዋህደ። ሁለተኛው የተሳታፊወች ፎቶም ለእኔ አንድ ለየት ያለ መልዕክት ልኮልኛል።
በሌላ በኩል የሁለቱ ምክትል ፕሬዚዳንቶች / ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተሮች የፍራፍሬ ዕይታ ፈገግ አድርጎኛል። የብልጽግና አባላቱ የወልዮሽ ዝማሬ ሲዘዋወር ማህበራዊ ሚዲያ ላይ አየሁት። ኦርጅናሉን ዩቱብ ቻናል ላይ አገኜሁት። በውነቱ የተሳታፊወቹ ዝማሬ ከኦርጅናሉ ጋር ቦክስ መግጠሙ ሪኽርሳል ያላተሠራበት ስለመሆኑ ተመልክቻለሁኝ። በጥቅሉ ባየሁት ነገር ብልጽግና ሁነኛ መካሪ እንደሌለው። የፖለቲካ ድርጅት ለዛውም የአገር መሪነት ብዙ ጥንቃቄወችን ማድረግ ይገባ ነበር።
የሥርጉትሻ ቤተሰቦች ረዘም ያለ ጊዜ የወሰደ ዕይታ ነው። ምክንያት ነገረ ትውልድ፤ ነገረ ጉዳዬ ስለሆነ ነው። ምክትል ፕሬዚዳንት/ ምክትል ከቅላይ ሚር አቶ ተመስገን ጥሩነህ። ስለዲጂታሉ ዓለም እና ኢትዮጵያ አንስተዋል። በዚህ ዘርፍ እንኳን አሁን ባለው ሁኔታ እራሱ አበረታች ነው።
በሌላ በኩል ብልጽግናን መምረጥ ማለት " ነገን መምረጥ ነው" ብለዋል። ነገ እራሱ አመጣጡ አይታወቅም እና አገላለጹ ጥያቄ ምልክት አለው።
#ጥያቄወች ……… ለአቶ ተመስገን ጥሩነህ።
1) የሳቸው ውክልና ከአማራ ህዝብ ስለሆነ የአማራ ክልል አሁናዊ ሁኔታን በምን ይለኩታል?
2) ከክልሉ ውጪ ስላሉት አማራወች የፖለቲካ ውክልናስ የሚመሩት ብልጽግና በምን ያህል እርግጠኝነት ተዘጋጅቷል?
3) በአማራ ክልል ያለው እራሱን ችሎ፤ ከመከላከያ ጥገኝነት ወጥቶ ይህን የጸደቁትን ማኒፌስቶ ማስፈጸም ይቻላል ብለው ያምናሉ።
4) የአማራ ክልል መቼ ሰላሙ ይመጣል?
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
12/02/2026
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
**********************************************************
"ብልፅግናን መምረጥ ማለት ነገን መምረጥ ማለት ነው አቶ ተመስገን ጥሩነህ» የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት"
«የፓርቲያችን የምርጫ ምልክት “የስንዴ ነዶ” ነዉ በዚህም መሠረት የፓርቲያችን የምርጫ ምልክት “የስንዴ ነዶ” ነዉ ። ምልክቱም የመደመር፣ የትብብር እና የአንድነት ምልክት ማሳያ ነው፡፡»
«የህዝባችንን ድጋፍ ይዘን መጪዉን ጠቅላላ ምርጫ በማሸነፍ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር የማሸጋገር አላማ ሰንቀናል- አቶ አደም ፋራህ»
«መጪውን ሃገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ብልጽግና ፓርቲ በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝና ጠንካራ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠርና ሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳካ የሚጠበቅበትን ሃላፋነት ለመወጣት በትኩረት እንደሚሠራም አፅንኦት ሰጥተዋል።»
«ብልፅግና ፓርቲን መምረጥ፤ ነጋችንን በዲጂታል ኢትዮጵያ ብሩህ ማድረግ ነዉ ብልፅግና ፓርቲ፤ ቀጣይነት ያለው እና በዲጂታላይዜሽን የታገዘ አገልግሎትን ማስፋፋትን ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ አድርጎ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አቶ ተመስገን ጥሩነህ»
«የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ ክቡር አቶ አደም ፋራህ የብልፅግና ፓርቲ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ማኒፌስቶ እና የምርጫ ምልክት ይፋ ማድረጊያ መርሀግብር ላይ ያስተላለፉት መልዕክት«ብልፅግና ፓርቲ ታሪክን ወደ ሀብት፥ ቅርስን ወደ እሴት የቀየረ ነው! የብልፅግና ፓርቲ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የማኒፌስቶ እና የምርጫ ምልክትን ዛሬ ይፋ አድርገናል። ፓርቲያችን በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሕዝብ ይሁንታ በማሸነፍ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ማሻገር ዋንኛ ግባችን ነዉ፡፡»
«በዚህም መሠረት የፓርቲያችን የምርጫ ምልክት “የስንዴ ነዶ” ነዉ ። ምልክቱም የመደመር፣ የትብብር እና የአንድነት ምልክት ማሳያ ነው፡፡»
«ብልፅግና ፓርቲ ከስድስተኛው ምርጫ በኋላ በኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዘርፎች ላይ ባከናወናቸው ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ለውጦች ውስጥ ትገኛለች።»
«በዲጂታል ኢትዮጵያ ፣ በዲጂታል ፋይናንስ፣ በዲጂታል አገልግሎት እንዲሁም ሀገሪቱን ከዕዳ ወደ ምንዳ የማሻገር ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።»
«በማኅበራዊ መስተጋብሮች በሕዝቦች መካከል ትሥሥር ለመፍጠር ሕዝባዊ እና ባህላዊ በዓላትን እንዲጠናከሩ ተደርገዋል።ይህም ኢትዮጵያ አቀርቅራ እንደማትቀር አሳይቷል፣ ታሪክም ተቀይሯል። ለብልፅግና ፓርቲ ጠንካራና ቅቡልነት ያለው መንግሥት መገንባት፣ በተለያዩ አካባቢ የሚታዩ ግጭቶችን መፍታት፣ የኢትዮጵያ የተጽዕኖ አድማስ ማስፋት እንዲሁም የዴሞክራሲ ፖለቲካን ባህል መገንባት የቀጣይ ጊዜያት ዋንኛ ዕቅዶቻችን ናቸው፡፡»
«የህዝባችንን ድጋፍ ይዘን መጪዉን ጠቅላላ ምርጫ በማሸነፍ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር የማሸጋገር አላማ ሰንቀናል- አቶ አደም ፋራህ ብልፅግና ፓርቲ፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሕዝብን ይሁንታ አግኝቶ በማሸነፍ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገርነትየማሸጋገር ግብ ይዞ እየሰራ መሆኑን የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋና ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ አደም ፋራህ አስታዉቀዋል።»
«የፓርቲው የምርጫ ማኒፌስቶ እና የመወዳደሪያ ምልክት ይፋ በተደረገበት መድረክ እንደተናገሩት: "ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር" የብልፅግና ፓርቲ የ7ኛዉ ጠቅላላ ምርጫ መሪ መልዕክት ሆኖ እንደሚያገለግል ገልፀው: መጪውን ሃገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ብልጽግና ፓርቲ በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝና ጠንካራ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠርና ሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳካ የሚጠበቅበትን ሃላፋነት ለመወጣት በትኩረት እንደሚሠራም አፅንኦት ሰጥተዋል።»
«ብሔራዊ ትርክትና ርዕይ ላይ የጋራ ስምምነት መፍጠር፣ ግጭቶችን በዘላቂነት መፍታትና በደሎችን በሽግግር ፍትሕ ሥርዓት የማረም ተግባርም በፓርቲው ቀጣይ የቤት ሥራዎች የተያዙ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።»
«በሁለቱ ውኃዎች ማለትም ዓባይና ቀይ ባሕር ላይ ያለንን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ እንደሚሠራ የገለጹት አቶ አደም፤ የመደመርና የአንድነት ተምሳሌት የሆነው "የስንዴ ነዶ" የፓርቲው የምርጫ ምልክት መሆኑን ይፋ አድርገዋል።»
«በመድረኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ከፍተኛ የፓርቲ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። ብልፅግና ፓርቲን መምረጥ፤ ነጋችንን በዲጂታል ኢትዮጵያ ብሩህ ማድረግ ነዉ አቶ ተመስገን ጥሩነህ»
«ብልፅግና ፓርቲን መምረጥ፤ ነጋችንን በዲጂታል ኢትዮጵያ ብሩህ ማድረግ መሆኑን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።»
«በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ኢኒሼቲቮች የተገኙ ዘርፈ ብዙ ውጤቶችም የኢትዮጵያን የመፈፀም አቅም ማሳያ መሆናቸዉንም ገልፀዉ፤ ብልፅግና ፓርቲ፤ ቀጣይነት ያለው እና በዲጂታላይዜሽን የታገዘ አገልግሎትን ማስፋፋትን ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ አድርጎ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡»
«የብልፅግና ፓርቲ የሰባተኛው ጠቅላላ ሃገራዊ ምርጫ ማኒፌስቶ እና የምርጫ ምልክት ይፋ ማድረጊያ መድረክ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ መልእክት ባስተላለፉበት ወቅት አቶ ተመስገን እንደገለፁት፤ ብልፅግና ፓርቲ ከትላንት የሚወሰዱ እሴቶች በአግባቡ በመገንዘብ፣ ሊወረሱ የሚችሉትን አምዶች በመለየት አዋጭ የሆነውን ቀጣዩን የኢትዮጵያ ጉዞ መተለሙን ጠቁመው፤ ይፋ የተደረገዉ የፓርቲዉ የምርጫ ማኒፌስቶ ይዘትም ይህንኑ መሰረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።»
«ብልፅግና ፓርቲ ለዲጂታላይዜሽን በሰጠው ልዩ ትኩረት እንዲሁም በዘርፉ ባከናወናቸው ስራዎች ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡን አሰታዉሰዉ፤ አካታች የሆነ ዲጂታል የፋይናንስ ስርዓትን ከማረጋገጥ አኳያ ተጨባጭ እና ሰፋፊ ርብርቦችን እያደረገ እንደሚገኝ በማስታወስ ቀጣይነት ያለው እና በዲጂታይዜሽን የታገዙ አገልግሎቶችን ማስፋፋት ከዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል እንደሆነም ተናግረዋል።»
«አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ ከማድረግ ባለፈ እርስ በእርሳቸው ማስተሳሰር ተገቢ መሆኑን ገልጸው፤ አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል የመስጠት ጅማሮዉም የዚሁ ማሳይ እንደሆነ አንስተዋል።»
«መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በፌዴራል ደረጃ ተግባራዊ በማድረግ፣ አሁን ላይ አገልግሎቱን ወደ ክልል እና ከተማ አስተዳደሮች መስፋፋቱንም አስታዉሰዋል።»
«የሰው ሀብት ልማት የዲጂታል ኢኮኖሚ ዋነኛ ምሰሶ መሆኑን ገልጸው፤ ይህንኑ ለማሳካት የአምስት ሚሊዮን ኮደሮች ስልጠና መርሃ ግብር በሃገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ማድረጉንም ተናግረዋል። #prosperity»
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ