#ትዕግሥትን ፈታኙ ከመንግሥት ኮምንኬሽን የተሰጠ መግለጫ ትዝብቴ።

 

#ትዕግሥትን ፈታኙ ከመንግሥት ኮምንኬሽን የተሰጠ መግለጫ ትዝብቴ። 
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 
#ምዕራፍ ፲፰። 
 
 
           May be an image of newsroom and text
 
 
ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ አሊ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ ሃሳቤን በምዕራፍ ከፋፍዬ ሳቀርብ ቆይቻለሁኝ። እሳቸው ድፍን ፰ ዓመታትን አሳለፋ፤ እኔ ደግሞ ፲፰ ምዕራፎችን አጠናቀቅኩኝ።
 
አንድ ሃሳብ ይቀረኛል። ዛሬ ምዕራፍ ፲፰ አጠናቅቃለሁኝ። መጪው ህማማት ነው። ማድመጥ። መጠሞን ያስፈልጋል። ከትንሳኤ በኋላ እንደ አማኑኤል ፈቃድ የጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አገዛዝ አብይዝም ፱ ዓመቱን አህዱ እንዳለው ሁሉ እኔም ፲፱ ምዕራፌን እጀምራለሁኝ።
 
ምዕራፍ ፲፰ የጨመተ፤ ያስተዋለ፤ ዘለግ ያሉ ዕይታወቼን ያጋራሁበት። በብሎጌም ከጠበቅኩት በላይ መነበብ የቻለ ጊዜ ነበረው። እርግጥ ነው በህይወት ውስጥ ያሉ ገጠመኞችን ትኩረት ለመስጠት አስቤ፤ ፖለቲካው ጊዜውን እየተሻማ በዛ ዘርፍ ብዙም አልሰራሁም። 
 
ፖለቲካም የህይወት አካል ነውና በአገር ጉዳይ ያገባኛል ብሎ፤ ጉልበቱን፤ ሃሳቡን የሚያጋራ ሰብ የዜግነት ግዴታውን የፈቀደ፤ በመብቱም ያልቀለደ ነው ብዬ አስባለሁኝ።
 
ዝምታ ውበት ቢሆንም ከዘመኑ ሥጦታ ጋር ሳይገናኙ ዳር መቆም ህይወትን ሞናትነስ ያደርጋል እና ዘመናችን በሰጠን፤ እጅግ በተደራጄ፤ ቀልጣፋ እና ስልጡን ዘመን ሰጥ የሚዲያ ፎርማት ተጠቃሚ መሆን በእጅጉ አልፈላጊ ነው። እያንዳንዱ ሰውም ሰብዕናውን የሚገነባበት፤ የራሱን አሻራ የሚያስቀምጥ ነፃ እና ለታረመ አንደበት ብቁ የሆነ ዕድል ስለሆነ ተጠቃሚነቴ ይቀጥላል።
 
 
የሰሞኑን የብልጽግና መግለጫ ሦስት ጊዜ ጀምሬው በአራተኛው ተሳካልኝ። #ትዕግሥትን አብዝቶ የሚፈትን መግለጫ ነበር። መግለጫው ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ዓሊን ወደ ሥልጣን የመጡበትን ፰ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ከመንግሥት ኮምኒኬሽን ሚኒስተር ተሰጥቶ በፋና ቴሊቢዥን በሁለት ተብዓት እና አንስት አንባብያን ተቀማጥሎ የቀረበ ነበር።
 
ጥራቱን ስለምወድለት ማዳመጥን ከወሰንኩኝ ፋና ቴሌቪዥን የዘወትር ምርጫዬ ነው። እናም በስንት ትግል አዳመጥኩት። እየገረመኝም። የቃላቶቹ ውበት፤ የሐረጋት የፍሰት ዜማ ህልም ባይሆን ያሰኛል። ብዕርም ብራናም አይችለው የለ እያልኩኝ ፈትኖኝ ግን ፈተናውን አሸንፌ አዳማጥኩት።
 
ሃሳቤ ዘለግ ብሎ፤ መግለጫውን በአጫጭር ሐረጋት፤ ወይንም በአንድ ቃል አቅርቤያለሁኝ። የፃፍኩት መንፈሱን የ፰ ዓመታት የተስፋ ቆይታ ከአብይዝም ጋር እንዴት ታለፈ? እጁ፤ ልግስናው አመድ አፋሽ ስለሆነው የአማር ህዝብ ልግሥና፤ ቅንነት እና ገራገርነት ያስገኜለት ውጤት ምን ይሆን የሚለውንም በስሱ አንስቼበታለሁ።
 
#ከትናንት በስቲያ (በስዋሰዋዊ ቋንቋ የሃላፊ ጊዜ ሃላፊ።)
 
ብዙው አሁን ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የምናየው የአብይዝም ደጋፊ እሳቸው ወደ ሥልጣን ከመጡበት ዕለት ጀምሮ የመጣ ነው። ዘግይቶም ገቢ የሆነ የደጋፊ መንፈስም ሊኖር ይችላል።
 
አብዛኛው የአብይዝም ተሿሚ ይሁን የቅርብ ሰውም እንዲሁ አዲስ ገቡ የበለጠ እጅ አለው። እርግጥ ነው በአገር ጉዳይ ያገባኛል ብሎ በሚያምኑበት መስመር መትጋት መልካም ነገር ነው።
 
እኔ ከዚህ ቀደም እንደፃፍኩት በቃ በጋሜዬ ነው ፖለቲካ ህይወትን የተቀላቀልኩት። ከዕለታት አንድ ቀን የጀርመን ዊንግ አብራሪ ፈቅዶ ከተራራ ጋር እራሱን ጨምሮ አምነውት የተጓዙት አንዳቸውም ሳይተርፋ እንደወጡ ይቀራሉ።
 
ዘገባው በCNN በተከታታይ ለ15 ቀናት ቀጠለ። በተለይ የሟቾቹ አስከሬን ማሰባሰብ በኢሊኮፍተር ሰው በገመድ እየተንጠለጠለ ተከወነ። ያቺ ቀን ነበረች ለእኔ አዲስ የሃሳብ በር የከፈተች።
 
ግን የዕውነት ክፋ ሃሳብ ወይንስ ክፋ ሰው ይሆን ዓለማችነን እያስጨነቀ ያለው የሚል ሃሳብ ላይ አተኮርኩኝ። ሰውን የሰው ልጅ አቅዶ ይጎዳዋል ወይንስ ክፋ ሃሳብ።
 
በዓለም ያሉ በፍቅር ተፈጥሮ ላይ የሚሠሩ ተቋማትን አሰስኩኝ። አፍሪካ ምን እየሰራች ነው ብዬ ጉግል ሳደርግ ዶር ምህረት ደበበን አገኜሁ፤ በዚህው ሰበብ ዶር አብይ አህመድ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስተር ሆነው አገኜኋቸው።
 
ከዛን ጊዜ ጀምሮ ቃለ - ምልልሳቸውን፤ ስብሰባቸውን፤ ንግግራቸውን ማዳመጥ ጀመርኩኝ። ዛሬ ያ መንፈስ በልኩ ቀጥሏል ብዬ አላምን። ያን ጊዜ ሰው ተኮር ክንውናቸው እርህርህና፤ ማስተዋል፤ አክብሮት የነበረበት የሚመስጥ ሰብዕና ነበራቸው።
 
እሳቸው ውለታ ቢስ ቢሆኑም ወደፊት ሲመጡ በትጋት በሁሉም መስክ ተግቶላቸዋል። የእሳቸው መንፈስ ግን ፍለጋ ላይ የነበረው የውስጤ በሚሉት ወገን ተኮር ሆኖል። ይህ ሁሉ ሚዲያ ላይ በድጋፍ፤ በስልጣን የተንተሸበሸው ሁሉ አንዲት ሐረግ በሳቸው ዙሪያ ያልፃፈ፤ ያልሞገተ #ያልመሰከረም ነበር። 
 
#የአማራ ቅንነት ፈጣሪ ከሰጠው በላይ ነው።አውዲዮም ሰርቸበታለሁኝ።
 
የአማራ ህዝብ ገራገር፤ ሰው አማኝ፤ አንጋሽ፤ ቅን፤ ግልጽ፤ ሰብዓዊ፤ ተፈጥሯዊ፤ ግልጽና ቀጥተኛ፤ ቀና ቅንም ህዝብ ነው። የፈጠረው አምላኩም፤ አላሁም ዕውቀቱን ያልነሳው፤ ብልህነቱን ያልነፈገው፤ የረገጠው ሁሉ እንዲያምር እንዲሰምር ያደረገው የውስጥ ንጽህናውን አይቶ ነው።
 
በዛ ጭንቅ የዘመነ ህወሃት ትግል ውስጥ ሁለመናውን ገብሮ የታገለ፤ ያታገለ፤ ጠፈፍ ያለ፤ የሰከነ፤ ያስተዋለ ትግል አድርጎ ለስኬት ያበቃም የአማራ ህዝብ ትትርና፤ ትጋት እና መስዋዕትነት ነው። ግን የአማራ ህዝብ እጁ አመድ አፋሽ ነው።
 
በምንም ሁኔታ ከህወሃት ፈቅዶ ስልጣን መልቀቅ ጋር ኦህዴድ ላገኘው ተጨባጭ ድል #ቁልፋን ድርሻ የተወጣው የአማራ ህዝብ መሆኑ ለአፍታ ሊረሳ፤ ሊዘነጋ፤ የኮፒራይት ሽሚያ ሊደረግበት ባለፈም በእሱ ላይ ምላጭ ሊሳብበት የሚገባ ባልሆነ ነበር እንኳንስ #ድሮን???
 
የህወሃት ፈቅዶ ሥልጣን መልቀቅ ኢትዮጵያን ገንጥዬ አገር እሆናለሁ ለሚል ለማናቸውም ነፃ አውጪ ያበደ ግሎባል የይሁንታ መንፈስ ፈጽሞ የለም። አይታሰብምም። በዚህ ለሚጠረጠር፤ ውስጡ ስለመጽዳቱ አስተማማኝ ሁነት ሳይኖር "በኢትዮጵያ ሱሴ፤ በጣና ኬኛ" ግልብ ግልብልብ ተዘናግቶ የራስን ዕድል አሳልፎ መስጠት ክርስቶስ እንጂ የሰው ልጅ ሊያደርገው የማይሞክረው ሰማያዊ ክስተት ነበር። አማራ ግን ንጽህ ልብ በመታመን ጸጋ የዳበረ የህሊና ብቃት ስላለው አምላኩን፤ አላህን ሳያስከፋ #ፈጽመው
 
ግን የአማራ ህዝብ #ተካደ፤ ተንገላታ፤ ተሳደደ፤ ተነቀለ፤ ተጣጣለ፤ ተናቀ፤ ተገፋ፤ መስቃም ጎረፈለት። ይህ የተገባ ያልነበረ ብሄራዊ ግድፈት ነው። ዛሬም የማያቸው፤ የማስተውላቸው፤ የምታዘባቸው ሁነቶች "ኢትዮጵያ አዲሲቷ የተስፋ አድማስ ናት መጋቢት 24/ 2018" የሚለው የብልጽግና መግለጫ 
 
1) ለአማራ ህዝብ ትናንት ሠርቷልን?
2) ዛሬስ እየሠራን ነው?
3) ወደፊትስ ይሠራልን? ጥያቄው ይህ ነው።
 
እራሴን ስገመግመው የሳሳሁለት፤ የቆጠብኩለት አንድም ንጽህና አልነበረም። እንደ እኔ በተከታታይ የፃፈ፤ የሞገተ አልነበረም። ዶር አብይ አህመድ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስተር እያሉ ንግግራቸው የታረመ፤ ብሄራዊ ስሜታቸው ለጋ ቢሆንም ሊዳብር ተስፋ የነበረው፤ ጠንካራ ሠራተኛ፤ ለትውልድ የሆነ ቋሚ አሻራ ለመፍጠር በትጋት የሚሠሩ፤ ለዝቅተኛው ማህበረሰብ ትኩረት የነበራቸው ስለነበር በዚህ መጠን ልክ ከውስጣቸው የአማራን ህዝብ ያርቁታል የሚል ቅንጣት ቅንጣቢ ጥርጣሬ አልነበረኝም። 
 
የአማራ ህዝብ ውለታ ለኢትዮጵያም፤ ለኦህዴድ፤ ለቅንጡው የማህበረ - ኦነግ ፖለቲካም ከሰማይ የወረደ ጸጋ ነበር። ያን አክብሮ፤ ዕውቅና ሰጥቶ ማስቀጠል ሲገባ ገና በጥዋቱ ከአማራ ህዝብ ጋር ቲካቲካው ቀጠለ። ያሳዝናል። ዘለፋው በአደባባይ ሆነ። ማሸማቀቁ የሰርክ ሆነ። ወደ ርዕሰ መዲናው ለመግባት በታቀደ ሁኔታ ታገተ።
 
የአማራ ህዝብ ቁም ስቅሉን አዬ። በሚኖርበት በዓት ከቤተክርስትያን እንደገባች ውሻ ተንከለከለ። መጠጊያ አጣ። ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅኑ ሊቃናት፤ ክልሎችም አጋሩ ሆነው ሊቆሙ አልቻሉም። ትራጀዲ ነው። 
 
የአማራ ልጅ በብአዴን አማካኝነት ሙሉ 45 ድምጽ ተሰጥቶ ከሁለት ድምጽ በላይ ያልሰጠው ደቡብ የከበረበት፤ በልዕልና 50+ የኢትዮጵያን የካቢኔ ይሁን የፖለቲካ ነክ ውክልናን በታማኝነት ያገኜው ጭምቱን የደቡብ ክልል ነው። ሲዳማ ተከብሮ ነው ክልል እንዲሆን በአጭር ጊዜ የተፈቀደለት።
 
የአማራ ህዝብ ቅንጣት ጥያቄ አትኩሮትም፤ ዕውቅናም ሳይሰጠው ከዚህ ተደረሰ። ከእዳሪ ልጅነትም በጣም በሩቁ የተገፋው የአማራ ህዝብን መሳደድ፤ መገፋት፤ መፈናቀል፤ ሞት እና እርዛት ሥጦታው ሲሆን ማዬት እንደ አንድ ኢትዮጵያዊት የአማራ ልጅ ውስጥን ያቆስላል። የውነት ውስጥን ያቆስላል።
 
ለኦህዴድ ካለምንም ቅድመ ሁኔታ የታክቲክም፤ የስትራቴጅም ወዳጅ፤ የቅርብ ሊሆን የሚገባው የአማራ ህዝብ መሆን ሲገባ ኦህዴድ ሆነ ማህበረ ኦነግ ግን አንጡራ ጠላት አድርገው የሚያዩት ግን የአማራ ልጅን ነው። ኦህዴድን ባለታሪክ፤ ባለ ክብር አድርጎ ከህወሃት ሞት ያዳነውን የአማራ #ቅንነት ነው።። ከክብር ላይ ክብር ያጎናጸፈውን። በውስጥ ልቡ ያመነውን ሌሎችም እንዲያምኑት ያስደረገውን የአማራ ህዝብ በተለያዩ የቅጣት ዓይነቶች ኦህዴድ ፈተነው። 
 
እርግጥ ነው የአማራ ህዝብ ለኦህዴድ ሹመኞች የሰጠው ይለፍ የቆጠቆጣቸው፤ ያን ምልዕተ ድጋፍ የራሳቸው ለማድረግ በጣሩ ሰብዕናወች ምክንያት #ፋክክር አይቻለሁኝ። የብዙ ስብራቶች መሠረታዊ ምክንያትም እንደሆነ አውቃለሁኝ። በአማራ ህዝብ ትግል ያልነበሩ፤ ትዝም ብሏቸው የማያውቁ የአቅም ሽሚያውን አና አሉ።
 
ይህም ቢሆን ተጠቃሚው ኦህዴድ በጨመተ ትዕግሥት ሊስተዳደር ይቻል ነበር። የአማራ ህዝብን ቀጥተኛ የጥቃት ሰለባ ከማድረግ የማይገኜውን የታምር ታምር ዕድል ላጎናጸፈ ማህበረሰብ ሰፊ ዕድል በመስጠት፤ በመደጋገፍ ታማኝነትን በድርጊት በማስዋብ ሂደቱን #ደም አልባ ማድረግ ይቻል ነበር። ሥልጣኑንም ቢሆን የአማራ ሊቃናት በፈቀዱት ቦታ ይሆኑ ዘንድ ይሁንታቸው መርኽ ሊሆን ይገባ ነበር።
 
ለፖለቲካ ጉዞ የብልጥነት ሃሳብ ሳይሆን ብልህነት ርዕዮት ነው ጠቃሚው ጉዳይ። የብልጥነት ሃሳብ በእኔ ግልጽ አገላለጽ #አጭበርባሪነት ነው። ይህ ለፖለቲካዊ ቀጣይ ጉዞ የአደጋ ምልክት ነው። ሙሉ ፰ ዓመታት የአማራ ልጅ ይታሠራል። ፍቱልን በልመና። ሞት በገፍ ነው። የአማራ እናት ማቅ ለብሳ አይዞሽን ተነፍጋ፤ በአገሯ መሬት የስቃይ ሁሉ ሰለባ ሆነች።
 
አንዲት እሳር ያላቀበሉ ደግሞ ሚኒስተር፤ ሚኒስተር ዲኤታ፤ ኮሚሽነር ወዘተ ናቸው። ህወሃት አግልሏቸው ለነበሩ ክልሎች ቦታ የሚሰጠው በዘመነ ኢህአዳግ የአማራ የነበረው ኃላፊነት ሁሉ ለእነሱ ተሰጥቷል። ትምህርት ሚኒስተር፤ ጤና ሚኒስተር፤ ጉምሩክ ወዘተ …… ይህ የአማራ ሊቃናትን ከሚኒስተርነት፤ ከካቢኔ አባልነት፤ ከምክትል ሚኒስተርነት የማፈናቀል ሂደት በ፰ ዓመታት ውስጥ እየተለሞጠ፤ እየተለነቀጠም የመጣ ነው።
 
በዘመነ ኢህአዲግ ወደ ፖለቲካ ውክልና ብቅ ያሉትም ከአቶ ጌታቸው ተስፋዬ፤ ከሰማዕቱ ኢንጂነር ስመኜው በቀለ፤ ከቲም ዶር አንባቸው መኮነነን ጀምሮ በተዋረድ ያሉ ባለስልጣናት በአንድም በሌላም ረገፋ። አንድ ብቁ፤ ጨዋ ምራቁን የዋጠ የሪ የአማራ እናት በስንት ዘመን ታገኝ ይሆን። 
 
ጦርነቱ እና ትምህርት፤ ጦርነት እና የፖለቲካ ውክልና ለአማራ ህዝብ የሰቆቃ መድረክ ሆነው ቀጥለዋል። በጣም የሚገርመኝ በአማራ ክልል የመሪወች አሟሟት፤ በፋኖም ዘርፍ የአማራወች መሰዋት አብዛኞቹ ጎንደሬወች ናቸው። ይህን በጥልቀት ሳይ ህወሃት መራሽ ኩነት ሥርሰዶ በአማራ ክልል እንዳለ አስባለሁኝ። ህወሃት የበቀሉን ፋስ ሲያሳርፍ፤ የሚገታ፤ የሚመክት ተጠቃሚው ብልጽግና መሆን ሲገባ ሂደቱ እንዲያውም የተመቸው ይመስለኛል። 
 
የህወሃት እና የብልጽግና ጦርነት የፍጅት ማት የወረደውም በአማራ መኮንኖች ላይ መሆኑ የአማራ ህዝብ ሊቃናት እራሳቸውን ችለው የመቆም አስፈላጊነት ያጠይቃል፤ አቅማቸውንም በቅጡ የማስተዳደር ብልህነት ይጠይቃል። ነገም ዓመት ድገመኝ የሚለው መከዳት ደንበርም ወሰንም የለውምና።
 
በዚህ ውስጥ አብይዝምን አምና ያን ግሎባል አቅሟን አፍርሳ አገር የገባችው ቅኒት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ፤ ማህበረ ምዕመኗ፤ መስቀሉ፤ ተተኪዋ የአብነት ተማሪወቿ፤ ገዳማቷ፤ ንዋዬ ቅድሳቷ፤ ተስፋዋ ሁሉ አገር ከተገባ በኋላ በስጋት፤ በጭንቀት፤ በፍርሃት በፍርሃት ተውጣ በአገሯ ውስጥ ቤተክርስትያኗ ስደት ላይ ናት።
 
ኢትዮጵያ አንድ ጠቅላይ ሚኒስተር፤ ሁለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር አላት የቅድስት ኦርቶዶክስ ልጅ ግን አንዳቸውም አይደሉም። ከፖለቲካ ውክልና መገለል ለጥቃት ዒላማ መሆን ነው። 
 
ይህን ወደ ክልል፤ ወደ ዞን፤ ወደ ወረዳ ሲወርድ ልሙጥ ሆኖ ይገኛል። ይህ ሁነት በዚህ ከቀጠለ መልካዓ ኢትዮጵያ ሙሉ- ለሙሉ የመቀየር #ቶን ሊኖረው ይችላል። አልተጀመረም እያልኩ አይደለም። እያዬሁት ነው። እየተያዬን ነው። ለብልጽግና ግን ይህ ጠቃሚ ጉዞ አይደለም። ዝምታችን ሊያከብረው ይገባል። ትናንት አምነን የሰጠውን ቃል አለማግኜት፤ "የመጀመሪያውን ሻሽ በምን ቀበርከው፤ የኋለኛው እንዳይሸሽ" በትክክል የተፈጸመ ነው። 
 
ከኦህዴድ የፈለቀው ብልጽግና "የማነው ይሉናል እኛም #የኦሮሞ ነው እንላቸዋለን።" በባሌው ጉብኝት ላይ ዶር አብይ ተናግረውታል። ሰሞኑኑም ኦሮሞ አገር መራ ብለው ያሉት ነገር በፍጹም በህሊናችን የሌለ ነገር ነው። በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ለታነጸ አማራ ኦሮሞ ደሙ ነው። በጣም ብዙ የአማራ ብልህ ልጆች ሠርተናል። "ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል" ይላሉ ጎንደሬወች። የሬቻን ጭፍጨፋ ዕውቅና ያሰጠ የአማራ ልጅ ነው። ሁለት ጊዜ የህወሃት እስር መፍትሄ እንዲያገኝ ጥረቱም አማራ ሰራሽ ርህርህና ነው። 
 
በጸረ አማራ አግላይነት የመበቀል፤ ቅድስ ኦርቶዶክስን የማዳከም ተግባር አቅዶ መሥራት በዚህ ጉዞው ብልጽግናን #የትውልድ አድርጎ የማጽናት ዕድሉ ፈተና ላይ ሊወድቅ ይችላል። የሳይለንት ማጆሪቲው ቴርሞ ሜትር ምን እንደሚያስብ ፈጽሞ ለማወቅ አይችልም።
አበክሬ እንደምገልጸው ትዕግሥት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል፤ ፍቅርም ሲያልቅ ትዕግሥት ይሰደዳል። ነገን ለማግኜት ዛሬን በውል አደብ ገዝቶ ማድመጥ ያስፈልጋል። አማራ በብልጽግና ፍዳውን አይቷል። የመከራ ቡፌ ነው ህዝቡ ያዬው። እድገት፤ ትፍስህት ቀርቶበት በዛ ምርኩዝ በሚሻው ቤቱ ለድህነቱ ሰላም በተሰጠው። 
 
#ከአባይ ወዲህ እና ከአባይ ወዲያ የአብይዝም ጎዳና። 
 
ለብልጽግና ከአባይ ወዲህ የይበቃናል ጉዞው ዋጋ ያስከፍለዋል። ኢትዮጵያ ቢያንስ ከህወሃት የተረከባትን ኢትዮጵያ ብልጽግና የማስቀጠል አቅም የመፍጠር ሁነቱን በግብታዊነት ሳይሆን እግዚአብሄርን፤ አላህን፤ በኢነርጂም ይታመናል ይመስለኛል - እሱንም፤ በፒኮክም አምልኮ እንዳለ አስባለሁኝ - እሱንም፤ በተፈጥሮም እንዲሁ ማመን አለ በወንዝ ብቻ በታመነው ዕምነት ቅድሚያ ሩጫውን ገትቶ አደብ ገዝቶ ማድመጥ በእጅጉ ያስፈልጋል።
 
ኢትዮጵያ ካለ አማራ ቅመምም አትቀጥልም። ብትቀጥልም አትሰነብትም። በአማራ ውስጥ ያለው ንጥረ ነገር ከቅንነቱ፤ ከሰው አማኝነቱ ከንጽህናው ይመነጫል። የአማራ ህዝብ ለተፈጥሮ ልዩ አክብሮት አለው። ሲያርስ በሬውን እንደ ፈጣሪው በሬ ሆይ! እያለ እየተንከባከበ እያዜመ፤ እያሞጋገሰ፤ እያጀገነ፤ ጉሮሮዬ እያለ ነው ቀንበር ጭኖ የሚያርስ። በጥልቀት ማዬት ያስፈልጋል።
 
የወጣቶች ብስጭት፤ የወጣቶች ቁጣ፤ የወጣቶች ዱር ቤቴ መፍቀድ እንደ አገር መሪነት በመሪነት ልክ አትኩሮት ሰጥቶ ማድመጥ፤ ለመፍትሄውም አደብ ገዝቶ ፌካዊ ያልሆነ የመደማመጥ መድረክ መፍጠር የተገባ ነው። ጦርነት ለእኔ ቬርሙዳ ትርያንግል ነው።
 
ለማስቆምም፤ ለመግታትም የሚቻልበት ገጠመኝ ዕድሉ ስስ ነው። በመሐል ህዝብ፤ ትውልድ፤ አደራ፤ ቃል ሊታሰብላቸው ይገባል።
እኔ ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ አሊ መጋቢት 24/2010 ያደረጉትን ንግግር ደግመው ቢያደምጡት ጥሩ ይመስለኛል። የድምጹ #ቃና ደግመን አልሰማነውም። ምርቃቱ ተነስቶ ይሆን? ያ ቀን ፈጣሪ ኢትዮጵያን በቃሽ ያለበት ዕለት ነበር። ግን የእግዚአብሄር፤ የአላህ ተስፋ ተርጓሚ አጥቶ ፈ- ሰ- ሰ- ሰ- ሰ- ሰ - ሰ - ሰ ………
 
#የ፰ ዓመቱ ትጋት በተነሳበት ተስፋ ወይንስ?
 
በ፰ ዓመታት ውስጥ የአብይዝም ትጋት የለም ማለት አይቻልም።
 
1) ትጋቱ የቅደም ተከተል ችግር ነበረበት፤
2) ትጋቱ ህዝበ - ጠቀም የማድረግ ሁነቱ ዝቅ ያለ ነው።
3) ትጋቱ በውስጡ የያዘው የቅምጥ ፍላጎት መቀየጥ በራሱ የሳይለንት ማጆሪቲው መንፈስ እንዲሸፍት ያደረገው ይመስለኛል።
4) ትጋቱ የአማራ ህዝብ እንደ ህዝብ ስልታዊ በሆነ ሁኔታ ከኦሮምያ፤ ከአዲስ አበባ፤ ከቤንሻንጉል ጉምዝ የተገፋበት ከውስጡ አዝኖ የቆረጠ ውሳኔ እንዲወስን ያስገደደው ነበር ማለት ይችላል።
 
5) ሌላው ትጋቱ ብወዛ፤ የህሊና ነቀላ ተከላ አለበት፤ የባለቤትነት እና የባይታዋርነት ስሜት ፋፍቶበታል፤
 
6) በትጋቱ ሃዲድ ማህበራዊ ትስስሩ፤ ዕቁቡ፤ ዕድሩ፤ ሰንበቴው፤ ጽጌው፤ ማህበሩ፤ ተዝካሩ የቀደሙ ይተባህሎች፤ የኢትዮጵያዊነት የመገለጫ አውታሮች፤ መረቦች ተበጣጥሰዋል።
 
7)የስማርት ሲቲ፤ የኮሪደር ልማት ወዘተ በሚባሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች #የእኛነት ቀለም ተጠቅጥቋል፤ ተበትኗል፤ ፈራርሷል።
ስምንት) ድንገተኛ የአርቲስቶች ህልፈት፤ የአማራ ህክምና ባለሙያወች መታደን እና ህልፈት ተከታታይነት የምንጩ ነገር አሳሳቢነት።
9) የአዲስ አበባ ነዋሪ የ5ቱ ሰማዕትነት ውሾን ያነሳ መባሉ …የታሠሩትም ፍትህ ማጣት …
 
10) የአጣዬ፤ የሽዋ ርቢት፤ የሻሸመኔ፤ የዝዋይ፤ የአክሱም፤ የአፋር፤ የሃይቅ፤ የንፋስ መውጫ፤ የጭና፤ የማይካድራ፤ የኮንበልቻ፤ የደሴ፤ የደብረታቦር፤ የአለፋ ጣቁሳ ወዘተ ነዲድ ሰዋዊነትን፤ ተፈጥሯዊነት የተፈተነበት የመከራ ጊዜ እንጂ የሳቅ ጊዜ ነበር ለማለት በራስ ላይ ማላገጥ ይሆናል።
 
11) እንደ ቀደመው ሁሉ የቅድስት ተዋህዶ አማንያን እና የአማራ ሊቃናት ተከታታይ ቋሚ የእስር ሁኔታ …
 
ብልጽግና ተኝቷል ልል አልችልም ለሚደላቸው ዲታወች የእረፍት ማሳለፊያ ቅንጡ ሆቴሎችን፤ ፓርኮችን፤ መንደሮችን አቅዶ እየሰራ ነው። ችግኝም፤ ስንዴም፤ አበባ፤ የወለል አድዮ ያበበት ምንጣፍ፤ የተዋቡ ቢሮወች እና ወንበሮች በዘርፋ ተግቷል። ባዶ ካዝና ለተረከበ መንግሥት፤ ዕንባን ያስቆማል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት መንግሥት ማጽናናትን መድፈር ከተሳነው ድካሙ ለሰው ወይንስ ለማን የሚል ጥያቄ ያስነሳል። 
 
እርግጥስ በተባለው ልክ ነውን የሚለውን በአካል ስለአላዬሁ ባልመሰክርም አሚኮንም ሌሎችንም ስከታተል …አንድ ምሳሌ ላንሳ የብልጽግና ተፎካካሪወች "ኮሪደር" እያሉ ሲያዘክሩ እሰማለሁኝ። ስለጎንደር ልንገራችሁ። ፋሲል ግንብ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም የሰጠውን ምስክርነት ከብልጽግና መንግሥት በላይ አምኜ ነው ፕሮፋይሌ ያደረኩት። #ጀሶ ይመስል ስለነበር በጣም ከፍቶኝ ነበር።
 
ፒያሳን ደግሜ የማየት ናፍቆት በፍጹም የለኝም። ለምን? ከፖስታ ቤት የአባ ተስፋማርያም ስቴሽነሪ፤ ኢትዮጵያ ሆቴል፤ የአባ በየነ ግሮሰሬ፤ ፎቶ ልዑል፤ ሲኒማ ባር እምፈልገው ቀለም የጥንት የጥዋቱን ነበር። አሁን ደመና ነው የለበሰው። እጅግ ያሳዝናል። ያስምጣልም። እድሳት ጥሩ ነው። ግን የነበረው ገጹ ጠፍቶ ሊሆን አይገባም።
 
ሌላ ፊት ለፊት ከፓስታ ቤት እስከ ግምጃ ቤት ድረስ አስፓልት አለ። ተሰርቷል። በስተጀርባው ከመዳህኒዓለም ተነስቶ ጊዮርጊስን፤ አጣጣሚ ሚኬኤልን፤ ተክልዬን ቆብ አስጥል አደባባይ እየሱስ አስፓልቶ አልቆ አፈሩ ጉድጓድ ሆኗል። በተጨማሪ ከጉምሩክ እስከ ደብረብርሃን ሥላሴም ገበጣ ጨዋታ ነው። ከሠሩ አድምተው፤ አጥርተው መሥራት፤ ካልሰሩ ደግሞ መተው። የግብር ይውጣ ሊሆን አይገባም። ኤንም እንዳይከፋው፤ ቢንም እንዳይከፋው ከሁሉም እንገኝ ሊሆን አይገባም።
 
ሌላው መገጭ ነው። ሰልችቶኛል ስለመገጭ መስማት፤ አባይ ግድብን በከፍተኛ ልዕልና የፈጸመ መንግስት በደርግ ዘመን የተወጠነ መገጭን ለማጠናቀቅ ምን አገደው? ርብም እንዲሁ፤ ከመተማ የሚነሳው ቁሞ ቀር ፕሮጀክትም አለ። አዲሱ ቀርቶ። የጸጥታው ችግር ያልመርካት እኮ ነው። 
 
#ህም። 
 
ከሊቅ እስከ ደቂቅ በሁሉም ቦታ በአህጉራዊ ሉላዊ ተቋማት ሁሉ የኦሮሞ ሊቃናት ቦታ ይዘዋል፤ ሜጋ ፕሮጀክቶች በኦሮምያ የትውልድ ተግባር እዬተከወነ ነው። በአማራ ክልል የትኛው ፕሮጀክት ነፍስን ለትውልድ የሚታደግ ታሰበለት?
 
አስደንጋጩ አዲስ አበባ ከሁለት ተገመሰች፤ ይህም አልበቃ ብሎ ባይ ባይ አዲስ አበባም ስልታዊ ሆኖ እየቀጠለ ነው፤ ይህም ሆኖ ኦነግ ታጣቂ አለው። ሁልጊዜ ዕድል፤ አትኩሮት አክብሮት አይነፈገውም። ምን ጎደለብኝ ብሎም ጫካ ክልትምትም እንደሚል አላውቅም። ሥልጣን ያሉት እነሱው ናቸው።
 
በአማራ በኩል ሚዛን ያስፈልጋል። የነበረውን የፖለቲካ ውክልና፤ አትኩሮት፤ ተጠቃሚነት ያጣ፤ የተገበረበትን የወልቃይት የጠገዴን፤ የአዲአርቃይ፤ የማይጠምሪ፤ የጠለምት፤ የራያን ጥያቄ በሥነ ልቦና ላይ ያለው ጨዋታ ይሻክራል። 
 
የአማራ ጥያቄ ሙሉ 32 ዓመት አንድ አማራ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆኖ አያውቅም። የአዲስ አበባን የባለቤትነት ጥያቄ ያላስመለሰ፤ በሌላ ክልል ፈጽሞ የሌለለ አማራ ክልል ብቻ የአዊ ዞን፤ ከሚሴ ዞን ወዘተ ተብሎ የአማራ ህዝብ በክልሉ የፖለቲካ ውክልና ቀረመት ላይ ያለ ህዝብ ቢከፋ፤ ቢያኮርፍ፤ ሆድ ቢብሰው ምን ይደንቃል? 
 
ያን የመሰለ በአማራ ህዝብ ዘንድ የእልልታ አቀባበል ደፍቶ ብልጽግና ዛሬ ክልሉ አይሆኑ ሲሆን ማየት እንደ መሪ፤ እንደ ካቢኔ ምቾት ምኑ ይሰጣል? 
 
የብልጽግና የድጋፍ መሠረት ደቡብ እና ኦሮምያ???? ይህ እንቅልፍ ያስወስዳል ----- ን? ከዚህ ጋር አያይዤ የማነሳው በስጋት፤ በቀውስ፤ በፍርሃት፤ በዕንባ አገር መምራት የህዝብ ታላቅ የምሥራች ሊሆን ይችላልን? 
 
1) አማራ ክልል በማን ነው እየተመራ ያለው?
2) ማነው የአማራ ክልል ለዘመናት እንዳይነሳ አድርጎ ድቀት ስንቁ እንዲሆን ያስደረገው?
3) አማራ ክልል ላይ ቀደምት ገዳማት ስለምን የድሮን ቁርስ፤ የድሮን ምሳ፤ የድሮን መሞከሪያ እራት እና መክሰስ ሊሆኑ እንደምን ቻሉ? 
 
#መግለጫው ስለ አብይዝም ስኬት እንዲህ ይነግረናል። 
 
1) "ኢትዮጵያን ከውድቀት ስጋት አላቆ ወደ ልዕልና ያሸገረ ነው።" ------ ነውን?
2) "የትንሳኤ ጉዞ" ----- ነውን።
3) "የታሪክ ብርሃን" ለማን? ለኢትዮጵያ ወይንስ ለአማራ---------????
4) "የሃሳብ ልዩነትን በጸጋ የሚቀበል" አንዲት ቀንጣ ጥያቄን በነፃነት መግለጽ ይቻላልን? ስለምን የአማራ አክቲቢስቶች፤ የአማራ ጋዜጠኞች፤ የአማራ ጸሐፍት፤ የአማራ ፖለቲከኞች የካቴና ስንቅነታቸው ቀጠለ?
 
5) "ፖለቲካዊ ቅራኒወችን በማክሰም ህብረ- ብሄራዊነትን የወል አገራዊ ዕሴቶችን የሚያሰርጽ ሥርዓት ዕውን ሆኗል" አማራ የሚለውን ኃይለ ቃል ለመስማት አቅሙ አለን? እንኳንስ የአማራንፖለቲካ የማድመጥ? ማለቴ የቀልድም አይነት አለው። 
 
6) "ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ የሚያስቀድም ለጎረቤት አገሮች ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጥ" ለጎረቤት አገሮች ቅድሚያ መስጠት ስሜን እና ደቡብ ሱዳን ጥሰው ድንበር ሲያለሙ፤ ሥያሜ ሲሰጡ፤ የጋንቤላ ኢትዮጵያዊ ህፃናት በድፍረት ሲዘርፋ ምርቃት ስለሆነለት ይሆን ብልጽግና ለጎረቤቶቼ ቅድሚያ ሰጠሁ የሚለን። ባለፋት ወራት "ፈሪ" ሲሉ የኢትዮጵያን መንግሥት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ሲወርፋ ይህን ለማጠየቅ ይሆን? ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ ያ ፋሳዊ ቃል ሊቆጠቁጣቸው ይገባል። ኢትዮጵያዊነት በዚህ ልክ ሲደፈር።
 
"ዜጋ ተኮር" ከመቼ ጀምሮ? ያን ሞት ጠሪ የህወሃት ህገ - መንግሥት፤ የህወሃት የአሰራር ዘይቤ ተሸክሞ? ደብረብርሃን ጨምሮ የተፈናቀሉ ሰወች ዜግነቱ ቀርቶ እንደ ጎረቤት አገር ዜጎች ቢታዩ ምንኛ መታደል በሆነ ነበር።
 
በትናንቱ የፋና መድረክ ወ/ት/ሮ ትዕግሥት ሃሚዲ ብልጽግናወች "ሰው ተኮር፤ ሰው አክባሪ ነን" ሲሉ፤ በብዙ ወራት ውስጥ የሚገኜው ሳቄ መጥቶ ነፃነቱን ሰጥቼ አፍነሸነሽኩት። 
 
ያዳላል ብልጽግና ላላቸው፤ ለዲታወች፤ ለተማሩ ለዞጋዊ ሁነቱ ለስትራቴጂ አጋሮቹ ሊሆን ይችላል። በባህሪውም፤ በተፈጥሮውም ብልጽግና ሰዋዊ አይደለም። ከሰው ችግኝ ይበልጥብኛል የሚል ፓርቲ እኮ ነው። በታሪኩ ሦስት ቀን የሃዘን ዓውጆ ያውቃልን፤ ተጸጽቶ ያውቃልን በህዝቡ ሰቆቃ፤ ሦስት ቀን ብሄራዊ የሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ አውለብልቦ አይቼ አላውቅም። ያን ቢያደርግ ይከብርበት ነበር። ግን አጽናኝነት፤ አይዟችሁ ባይነት ለብልጽግና መክሊቱ በፍጹም አይደለም። አልተሰጠውም። "ዝሆን ነን እንቀረጥፋለን፤ እንበላለን" ብሎናል እኮ።
 
ለሰው ጥንቃቄ አንሶ፤ ለቅርስ ለውርስ ደንታ ቢስነት ሰፍቶ፤ ዜግነት ተወርውሮ ድሮን ታምኖ ሲላክ በራስ ህዝብ ላይ ይህ ይሆን ሰው ተኮርነቱ? ይህ ይሆን "ዜጋ ተኮር?" በውነቱ ብልፄው ልጆቹን ለፕረዘንቴሽን ሲልክ በጥንቃቄ እንዲያስቡ ቢያደርግ ጥሩ ነው። ሰርክ መርዶ በሆነበት አገር "ትንሳኤም ህይወትም" እኛ ነን ያስተዛዝባል፤ እናንተንም ያዘናጋል። 
 
7) "የክልሎቹ አስተዳደሮች እራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር የተለማመዱ" የትኛውን ክልል? የአማራን አይደለም። አመራሩ በጅምላ እስከ ተፈጀበት ድረስ + ከተሞችን ጨምሮ በቀጥታ ይመራ የነበረው በጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ነበር።
 
የጎንደር ከንቲባ የአሁኑ ፰ኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ሳይሰነብቱም ይቀየራሉ። ተከታታይ የአመራር ነፃነት ለአማራ ክልል ብልጽግና ሰጥቶ አያውቅም። እንዲያውም የአማራ ከተሞች መልካቸው፤ መንፈሳቸው ሁሉ #እየተበወዘ ነው።
 
እኔ በግሌ መከፋቴን አምቄ ዝም የምለው እኔ የማዋጣው አቅም ለማን ጥገና ይሆናል የሚለው በአደብ፤ በጥሞና ማኔጅ ማድረግ ስላለብኝ እንጂ ጠፍቶኝ አይደለም። ልምዱም፤ ተመክሮውም አንሶ፤ አቤት የሚባልበትም አድማጭ አቅም ጠፍቶ አይደለም። 
 
በዚህ ፈታኝ የዘመኑ የፖለቲካ ባህሬ ፈጣን የሆነ ተለዋዋጭ ባህሬ እንደ አገር ብሄራዊ ጉዳይ፤ እንደ ህዝብ ልጅነትም ጥልቀት ያለው የማስተዋል ሰብዕና ሊኖር ስለሚያስፈልግ ነው ዘለግ ያለው ዝምታን ያስቀጠልኩት። ለዛውም ብልጽግና የራሱን የተልዕኮ ሁነት ማሳለጥ ካልሆነ "ላም እረኛ ምን አለን" አያዳምጥም። አዋቂም ጥበበኛም እራሱን አድርጎ ነው የሚያዬው ብልፄው። "መደመር" ግን ይተነፍሳል ወይንስ ኦክስጅን አሰኝቶት ይሆን? የተቀነሰው ሚዛን ስለሚደፋ። 
 
ስምንት ) "አካታች የፖለቲካ ሥርዓት ለመገንባት ብስለት ያለው እርምጃ" ይህ #ለተመጋጋቢ ፓርቲወች ከካቢኔ ጀምሮ ሥልጣን ማጋራቱ ለራሱ ሲል ነው። ልግሥናው ግን ይገርመኛል። ልግሥናው ለተመጋጋቢ ፓርቲው ለአንድ ለኢዜማ ነው። ማድረጉ በዘርፋ እራሱን ችሎ የሚሠራ አቅም፤ ጥገኛ ያልሆነ፤ በአዳዲስ የአሰራር፤ የአፈፃጸም ስልቶች የብልጽግናን ክፍተት ሞልቶለታል። ተጠቅሟልም። 
 
ሌላው አብን ነው። እብን እኔ ተጠማኝ ወይንም ተቀላች ነው ባይ ነኝ። ብልጽግና ልክ እንደ ኢዜማ እኩል ክብር ለአብን አለመስጠቱን በሰሞኑ ክርክር እጩ ጠቅላይ ሚኒስተሯ ከጋንቤላ በዓለም አደባባይ ዝቅ ከፍ አድርገው ዘልፈውታል። "ባለቤቱን ካልፈሩ አጥሩን አይነቀንቁ።" ፊት ስላገኙ ነው። ብልጽግና ከአብን 6 ሰው አግኝቷል። እንኳን ደስ አለው። እንደ ትርፍ ካየው። ይህም ሆኖ አዲስ አበባ ላይ አብን በ2013 ዓም፤ በ2018ዓም ዳሽ ነው። ይህ ደግሞ ፖለቲካዊ የአለቃ ውሳኔ ነው። 
 
9) "……… ኢትዮጵያውያን በለውጡ ብስራት ከመጠፋፋት ፖለቲካ በመዳን የዴሞክራሲ ልምምድ መሸጋገራቸውን ያሳያል" የአማራ ክልል ሊቃናት በጀምላ ማለቅ ከምን እንመድበው? ዴሞክራሲ እግር አውጥቶ አስገቡኝ ቢል በኢትዮጵያ ፖለቲካ አይፈቀድም። የተከለከለ መንገድ ነው። ዴሞክራሲ የሚያቀነቅነውም ከእሱ ከእራሱ ሲደርስ በራሱ ላይ ሽሽትን ይመርጣል ፖለቲከኛው እከሌ ተከሌ አይባልም። አሁን ከሆነ ዴሞክራሲን ፈጽሞ የማላስበው ነው። ቅንጦትም ነው። መኖር ይቻል እስኪ ህዝባችን። ከስጋት ይዳን ህዝባችን።
 
ሰው በአገሩ ወጥቶ በሰላም መግባት ይቻላል። አይደለም እናንተ እሬሳችሁ እንዳይመጣ ዓዋጅ ከሰማን እኮ የሳምንት እድሜ ነው። ጠቅላይ ሚር አብይም ትውፊትን የሚያቃጥል የቀብር ሥርዓት እንዳፈለቁ በሰሞኑ የቃና ቃለ ምልልሳቸው አዳምጫለሁ። 
 
መንገዳችን በሃዘንተኛ፤ መንገዳችን በተከፋ ድምፆች ሊጎዳ አይገባም። ስንብት በተገኜው ቦታ። አፈር ማልበስ ግን ቤተሰብ ብቻ። ሰቅሰቅ ብሎ ሊያስለቅስ የሚችል መራራ ጉዳይ ነው የነገሩን። እርግጥ ነው በሰማዕቱ ኢንጂነር ስመኜው ቀብር ላይ የአዲስ አበባ ህዝብ ለጀግናው ኢንጂነር ቀብር ነፃነቱ ተነፍጎ ነበር። 
 
10) "………ከተሞችን ወደ ዘመናዊነት በማሸጋገር ንጹህ ሥልጡ አገልግሎት ሰጪ እና የተቀናጄ መሠረተ ልማት በኮሪደር ልማት ከተሞች አዲስ ገጽታን የተላበሱ ሲሆን ……" የታሪክ ሽሚያ ነው። የህዝብ ባህላዊ ትስስር በጣጥሶ አዲስ ማንነት የማብቀል ዝምተኛ የዲስክርሚኔሽን ምህንድስና ነው። ድል አይደለም። ማት ነው። ማቱ ለማህበራዊ ሳይንስም ይተርፋል።
 
11) "ዲጅታሉ ዘርፍ።" ኃላፊዋም ወ/ት ፍረህይወት ታምሩ ጥንቅቅ ያሉ ትጉህ ናቸው። በጉብኝትም ሥራ እንዲፈቱ ተደርጎ አይቼ አላውቅም። በህወሃት እና በብልጽግና ጦርነት ጊዜ ከተፈጠረው እሰጣ ገባ ውጪ ውጤቱን አያለሁኝ። ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድም በዘርፋ ዕውቀት አላቸው። ይከታተሉታል። የድሮ ህልማቸውም ነበር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ እያሉ አስቀድመን መዘጋጀት ካልቻልን ከዘመኑ ጋር መጓዝ ይሳነናል የሚል ቃለ ምልልሳቸውን አዳምጬ ነበር ከ10 ዓመታት በፊት።
 
የዘርፋን ጥረት በበጎ የማየው መልካም ጅምር እና ስኬት ነው ማለት እችላለሁኝ። ብዙ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚወች ለለት ኑሮም የረዳው ዘርፋ ያሳዬው የመሻሻል ውጤት ነው ብዬ አምናለሁኝ። አሁን በኢራን ጦርነት ምክንያት እክል ካልገጠመው በስተቀር። እሱም ብልጽግና ሰራሽ ሳይሆን የዓለም ሁኔታ አስገዳጅ ስለሚያደርገው፤ ብልጽግናን በፍጹም ተጠያቂ ሊያደርገው አይችልም።
 
ከዚህ ጋር ተያይዞ ግሽፈት፤ የነዳጅ እጥረት፤ የኑሮ ውድነት፤ መግጠሙ ግሎባል ነው። እርግጥ ነው ጦርነቱን አስቁሞ በወሳኝ ህይወትን ሊታደጉ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ባጀትን እንደገና ማደላደል የሚያስፈልግም ይመስለኛል። 
 
12) " …… ማህበራዊ መስተጋብር እንዲጠናከር የአገር ጌጥነት አንድነት አቅም እንዲሆን ተደርጓል በድርቅና በመሬት መንሸራተት የተደረገው አገራዊ ድጋፍ የዚህ ጽኑ አንድነት ማረጋገጫ ነው።" ለማፍረስ ቢባል የተሻለ ነው። በብዙ ሁኔታ ብዙ ቀደምት ሁኔታወች አደጋ ላይ ናቸው። አዲስ አበባ ላይ በፍጥነት በዘመቻ ታቅዶ ነባሩ ማንነት ድምጥማጡ ጠፍቷል።
 
በቀደምት ባህላዊ፤ ወጋዊ፤ ትውፊታዊ፤ ታሪካዊ፤ ሃይማኖታዊ ትስስሮች ላይ የማህበረ ኦነግ ፖለቲካ የሚበረግግበት ክስተት ነበር። እሱን አጅሬው ሳያስጠጡ እያለሳለሱ ለግብ አብቅተውታል። 
 
በሰሞናቱ የጋሞ የመሬት መንሸራተት በሁኔታው ዓለማቀፋዊ ትኩረት የተነሳ ብልጽግና የርህራሄ አብርሃም ሆኖ ለመውጣት ሞክሯል። እኔ እማውቃቸው ደግ እና ሩህሩህ ሰብዕናወች የብልጽግና አምልኮ ካጠቃቸው ወዲህ፤ ስለመከፋት፤ ስለ ድህነት፤ ስለጉስቁልና፤ ስለሞት፤ ስለ ችግር ማድመጥ ፈጽሞ አይፈልጉም።
 
የቦረና ራህብ እኮ ጠያቂ አጥቶ በራስ ጥረት የአካባቢው ተወላጆች ነበር የታተሩት፤ እሱም ታግዶ ነበር። መጨረሻ ላይ ግን ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ዘግይተው ሄደዋል። "እኔ እምሞት ዛሬ ማታ እህል የሚደርስ በፍልሰታ" ሃዘን ነክ ጉዳይ ሲገጥም ጠቅላይ ሚር አብይ ጉዞ ላይ ናቸው። በባለ ክንፋ። 
 
የብልጽግና ዕውነተኛ ደጋፊወች ሩህሩሃን ሳይቀሩ ተለውጠዋል። የሰው ልጅን ሰቆቃ አቃለው ነው የሚያዩት። አይደነግጡም። እኔ ሰው በዚህ ያህል ሰብዕናው ተቀይሮ አይቻለሁኝ። ይህን ገጠመኝ ወደ ትልቁ የመንግሥት መዋቅር ስንወስደው በአገር ውስጥ መፈናቀል ኢትዮጵያ በዓለም ፩ኛ ናት። ቀውሱ፤ ሴራው፤ ተንኮሉ ህወሃት ሠራሽ ሊሆን ቢችልም፤ ሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት ሰዋዊ፤ ተፈጥሯዊ መሆን ቢችል ኖሮ ይህን ያክል ዕንባ ሰርክ አይፈስም ነበር። ማስቆምም ይቻል ነበር።
 
ሰሞኑን የአሜሪካ መንግሥት ከአዲስ አበባ በስተቀር ዜጎቼ ኢትዮጵያ ቅስቅስ እንዳትሉ ብሎ ደረጃ ሦስት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። አዛኝ፤ ተጨናቂ፤ ለዜጎቹ አሳቢ መንግሥት ሲኖር እንዲህም አለ። 
 
"ኢትዮጵያ በአስተማማኝ ፖሊሲ ላይ ትገኛለች እያደገ በመጣው የዲፕሎማሲ ብቃቷም አዲሲቱ የተስፋ አድማስ ለመሆን ችላለች" እንደ አፋችሁ ያድርግላት። የትኛው ፖሊሲ? ስንት ፖሊሲ ነው? 
 
#ኢኮኖሚን፤ ደህንነትን በሚመለከት በተባለው ልክ ስለመሆኑ ኤክስፐርቶች ይመልሱታል።
 
ብዙ የመፍትሄ ቀናት፤ ወራት፤ ወቅታት አልፈዋል። ለደግነት፤ ለርህርህና፤ ለሰዋዊነት፤ ለተፈጥሯዊነት ግን ቅድመ ሁኔታ አያስፈልገውም። ማህበርተኛ፤ ቤተኛ ለመሆን ዛሬን መጠቀም ብልህነት ነው። መጸጸትም ሊኖር ይገባል። የአማራ ህዝብ ተበድሏል።
 
የይይቅርታ፤ የምህረት፤ ለማድመጥ የመፍቀድ ደግሞ የተበደለው፤ የተገፋው ማህበረሰብ ሊሆን ይገባል። ምክንያቱም ከፈጣሪ፤ ከአላህ ጋር የሚያገናኜው ብቸኛው መስመር የይቅርታ ቀና መንፈስ ነውና።
 
ኢትዮጵያዊነት በራሱ አስተምህሮዋ፤ አፈጣጠሩም #ኦርጋኒክ ነው። ኢትዮጵያዊ ለመሆን ካላቃተ። ኢትዮጵያዊነት ዕምነቱም፤ ፈለጉም አዳኝነት ነው። ከተፈቀደለት። ይፈውሳል። ያፋፋል። የዊዝደም ሸማን ያጎናጽፋል።
 
"የሀገራዊ ለውጡ 8ኛ ዓመትን አስመልክቶ ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የተሰጠ መግለጫ"
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ኑሩልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
04/04/026
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ዕውነት ወጌሻም ይሁን ጋራጅ አያስፈልገውም።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።