#ስፖርት የፍቅር ተፈጥሮ #ሐዋርያ ነው - ለእኔ። አዶናይወዲላን።

 

 

 

#ስፖርት የፍቅር ተፈጥሮ #ሐዋርያ ነው - ለእኔ። አዶናይወዲላን።
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 
#ምዕራፍ ፲፱።
 
ክፋ ሃሳብ በእጅጉ እየፈተናት በምትገኜው እቴጌ ዓለማችን ስፖርት ነፍስ ሆኖ፤ ነፍስ ሰጥቶ፤ ፍቅር ሆኖ፤ ፍቅር ሰጥቶ ይሞግተዋል ክፋ ሃሳብን። ከስፖርት ውስጥ አንዱ እግር ኳስ ነው። ዕውነተኛው የፍቅር ተፈጥሮ የሚገኘውም #ከእናት እና #ከስፖርት #ማልያ ነው ብዬ አስባለሁኝ። ለዚህ ነው አዘውትሬ ልብ ሳይሆን እናት ትሁን የፍቅር ተፈጥሮ የምለው።
 
በዓለማችን ክፋ ሃሳብን ሞግቶ የሚያሸንፍ፤ ዕለታዊ ተግባሩ የፍቅር ተፈጥሮ የሆነ የማስተማሪያ፤ የሚዲያ፤ ዓለም ዓቀፍ ተቋም ባይኖርም የስፖርት ማልያ ግን ይህን ኃላፊነት ለመወጣት አዘውትሮ ይጥራል።
 
የዓለም የሳቅ ጊዜ የዕውነተኛው አለ፤ ወይንም ተገኜ ከተባለ ከስፖርት ፍቅር እና ከእናት የሚፈልቀው ወይንም የሚመነጨው #ንጽህና ስለመሆኑ አምናለሁኝ። እግር ኳስ ፍጹም ልዩ ነው። #የሐሤት ተልዕኮ የተሰጠው። የዓለምን ሙሉ አደብ በፍቅር የሚገዛ።
 
እኔ እግር ኳስ እወዳለሁኝ። ለረጅም ጊዜ በአምደኝነት በተሳተፍኩባቸው ፔጆች፤ በራሴም ሚዲያ ዘገባውን እሰራለሁኝ። ማዬት በማልችልበት ጊዜ ከስደት ወደ ስደት ሂጄ የአውሮፓን እና የዓለም ዋንጫን እከታተል ነበር። በፍቅር፤ በጉጉት ከውስጤ ደስ ብሎኝ የምመለከተው የመኖር አርት ቢኖር #እግር ኳስ ነው።
 
የዓለምን አርቲቡርቲ፤ የዓለምን ኳኳቴ፤ የዓለምን የክፋ ሃሳብ ፈተናን ረሳ አድርጋችሁ ወደ ዕውነተኛው የመፈጠራችን ሚስጢር፤ ወደ ንጽህናችን የሚወስደን ጎዳና ቢኖር ለእኔ እግር ኳስ ነው።
 
የእግር ኳስ ፍቅር #አያረጅም። የእግር ኳስ ፍቅር የጥልን፤ የማግለልን፤ የልዩነትን ግድግዳ ንዶ በአንድ ሜዳ ከድንቡልቡሏ እና ከኔት ጋር አገናኝቶ እስኪ #እርፍ በሉ የሚል ብቁ ሐዋርያ ነው።
 
እርግጥ ነው በአስተዳደር፤ በአመራር፤ በቅናት የሚፈጠሩ ሳንኮች ቢኖሩም፤ የማልያ ፍቅር ያን ተቋቁሞ ነፍስን ከነፍስ ያገናኛል። እኔ ከሥነ- ጽሁፍ ባላነሰ እግር ኳስን ከልቤ እወዳለሁ። አከብራለሁም።
 
በሌላ በኩል የስፖርት ማንነት ከአገር ብሄራዊ ሰንደቅ፤ ከአህጉር ውስጥነት፤ ከዓለም ነፍስ ጋር በእጅጉ የተዋኃደ ታምረኛ የጥበብ ትንግርትም ነው። 
 
በስፖርት #ርህርህና የተንገላቱ ነፍሶች ወህ ይሉበታል። በስፖርት #የደግነት ዓውደ ምህረት የባተሉ ነፍሶች እፎይ ይሉበታል። በስደት ክልትምትም ያልን ሰብዕናወች ለአፍታ ሸክማችን አውርደን እርፍ የምንልበት ትጉህ አጽናኝ ዋርካችን ነው እግር ኳስ።
 
ኢትዮጵውያን ጥናት አልተሰራበትም እንጂ፤ ዕድልም አልቀናንም እንጂ የእግር ኳስ ፍቅራችን ተመስጥሮ ያለ አንከራችን ነው። የምንደግፋቸው ቡድኖች፤ አህጉራዊ ይሁን ብሄራዊ ቲሞች፤ ሊጎች ሊለያዩ ይችላሉ።
 
የእግር ኳስ ጥበቡ ንባቡ፤ ትርጉሙ፤ ሚስጢሩ ግን ኢትዮጵውያን የገባን ነን ብዬ አምናለሁኝ። ያ የእግር ኳስ ንባቡ፤ ትርጉሙ ሚስጥሩ ደግሞ እናት አገራችን የተፈጠረችበት #ኦርጋኒክነት ነው ብዬ አምናለሁኝ።
 
ሰሞኑን ባለው #አዶናዊው የፍቅር፤ የመተማመን፤ የመዋህድ፤ የቅንነት፤ እራስን መሆን የመቻል አቅም ንቅናቄ "አላስፈላጊ፤ የተጋነነ፤ የሰብዕና ግንባታ፤ አልባሌ ጉዳይ" አድርገው የተመለከቱት አሉ። መብት ነው።
 
ለእኔ ግን አንድ #ሁነኛ ድምጽ ለእናት አገሬ ለኢትዮጵያ የማግኜት ብልህነት ነው ብዬ አምናለሁኝ። የኢትዮጵያ ታዳጊወች፤ ወጣቶች ከሚያጨናንቁ የፖለቲካ ሁነቶች ባሻገር ለአንድ ቀን ፈገግ ብለው ስለአዬኋቸውም ደስ ብሎኛል። የተከለከለ፤ የተገደበ ሁነት አላዬሁምና።
ዛሬ እንዲስቅ፤ ነገ በሳቅ እንዲጠብቅ፤ ከነገ በስትያም ለሳቅ እንዲጓጓ ለውጣቶች #ዕውነተኛ #የነፃነት ቀን፤ ለወጣቶች ውስጣቸውን የሚያሳዩበት #የግልጽነት ቀን እንዲህ ያስፈልጋቸዋል።
 
የሙዚቃ ባለሙያወች ኮንሰርት ሲያዘጋጁ ወቅቱ እንዲህ ነው፤ እንዲያ ነው የሚል #አጋጅ ሁነት በየዘመኑ ሲመጣ ከውስጤ አዝናለሁኝ። ለአርቲስቶች መክሊታቸውን መገደብ ይሆናል። የአንድ ባለመክሊት ስጦታ ከፈጣሪ ነው። ያን ማዕቀብ መጣል ማለት ፍልሚያው ከሰጩ ጋር ይሆናል። በዘርፋ ጥሞናዊ እርጋታ ሊደረግ ይገባል። በጥበበኞች ጥሪያ ላይ ማዕቀብ ሊጣል አይገባም ባይነኝ።
 
1) እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መክሊት ይዞ ይወለዳል። ተሰጥዖ።
2) እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ ጥሪ ይዞ ይወለዳል። ቅብዓ።
3) እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መልዕክት ይዞ ይወለዳል። ፖስተኛ ነው። ይህን በአምዴም፤ በመጻህፍቶቼ ላይ ጽፌዋለሁኝ። ሰጩ አምላካችን አላኃችን ነው። 
 
በሌላ በኩል የሙዚቃ ኢንደስትሪው ቢሰፋ አገር ጠቀም የመሆን አቅም አለው። በምንዛሬ ሆነ በዕውቅና። ሌላው አንድ አርቲስ የብዙወች ተስፋ የመሆን አቅም ያመነጫል። ያን ዕድል ከማስደንገጥ ወይንም ከማሸማቀቅ ይልቅ #መጠበቅ ያስፈልጋል። 
 
በተጨማሪም በተፈጥሮው ልክ እንደ ውሃ ሙዚቃ ሳይሰሙ መዋል ማደር የማይችሉ ሚሊዮኖች ይኖራሉ። ለእነሱም ጊዜ መስጠት ያስፈልጋል። እንዲሁም 365 ቀናት ውስጥ ጥቂት ቀናት የሰው ልጅ እፎይ የሚልበት ሁነት መፍጠር የሁሉም ግዴታ ነው። ለዚህም ነው ኮንሰርቶች ማዕቀብ ሲጣልባቸው ውስጤ የማዝነው። አተንፍሱ እኮ እየኖራችሁ #ሙቱ ነው።
 
በዚህ የሰሞኑ አዶናያዊ የቅንነት ንቅናቄ ውስጥ የትውልዱን የዘመን አሰተዳደር፤ የትውልዱ የአመራር ክህሎት፤ የትውልዱ ዘመን ሰጥ ስልጣኔወችን ለመልካምነት የመዋል የላቀ ጥበብ አይቸበታለሁኝ። 
 
በወጣቶች የግል ጥረት ላይ በዚህም በዚያም ወጀብ ማብዛት አያስፈልገም። የወጣቶች በራስ የመተማመን አቅማቸው፤ በአገራቸው በኢትዮጵያ ያላቸው #የመታመን መሰረት ሊታወክ አይገባም። ይልቁንም እንክብካቤን በአወንታዊነት መመገብ በእጅጉ ያስፈልጋል።
ይህ የዲፕሎማሲ ጥረት እና ስኬት ተጠቃሚዋ እትብታችን፤ እናታችን አገራችን ናት። ሳቋ - ሳቃችን፤ መከፋቷ - መከፋታችን ለሆነው ውስጣችን ያለ ደንበር ለፈቀድንላት ልጆቿ እረፍት ይሰጣል። ስናርፍም ሰላም እናገኝበታለን። 
 
ነገን ለማን? ከነገ በስቲያን እንዴት? ለሚለው ዕውናዊ መልስም ይሰጣል። ዲፕሎማሲ በቢሮ ብቻ ሳይሆን ዘመን ሰጥ ሥልጣኔወችን በአግባቡ፤ በቅጡ ማኔጅ የማድረግ ቅንነት ስለመሆኑ #ሐዋርያዊ ተግባር እንደተከወነ አምናለሁኝ። ልጅ አዶናይ ብሩክ ቅዱስ ይሁን። አሜን። በአባይ ጉዳይ ላይ ለሚነሱ ዕውነት ላልሆኑ ጉዳዮች ሁሉ ይህን መሰል ጥበባዊ ሂደት መመከት ይችላል። 
 
በወጣቶች ህሊና፤ በታዳጊ ወጣቶች መንፈስ ፈላስፊት ኢትዮጵያ፤ ሳይንቲስቷ ኢትዮጵያ፤ ዩንቨርሷ ኢትዮጵያ ከትናንት በስቲያም፤ ትናንትም፤ ዛሬንም የሚያገናኝ ኮንፊደንስ የሚገነባው በዚህ መልክ ነው።
 
ለነገ፤ ለነገ በስትያ ወጣቶች፤ ታዳጊወች እንዳይሾልካቸው የሚያስፈልገው ዋናው በኽረ ጉዳይ #የተመጣጠነ #በራስ የመተማመን አቅማቸው ነው። ይህ ለቀጣይ ለሆነው ትውልድ ትንፋሹ ሊሆን ይገባል።
 
እርግጥ ነው ወጣትነት የሚፈተንብት ባህሬ ይኖራል፤ ችኩልነት ግብታዊነት ወዘተ፤ ያልተገቡ የውጭ ቀሰማ ወይንም ኩረጃም ሊኖር ይችላል፤ ይህን መሰል ገጠመኝ ወጣቶችን እልህ ሳያጋቡ በትህትና፤ በዝግታ ማስተማር ከእኛ የሚጠበቅ ግዴታ ይሆናል።
 
በተረፈ ከእኔ በፊት ይሁን በእኔ ዕድሜ ዙሪያ ያሉ ፖለቲከኞች በጥልቀት ከራሳቸው ጋር ቁጭ ብለው ሊወያዩበት የሚገባው አንኳር ጉዳይ በትውልድ ለትውልድ ያለውን ጋፕ ዕውቅና ሰጥቶ፤ የወጣቶችን ዘመን ላለመቀማት ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።
 
ዘመን የሰጣቸው ወጣቶች ታዳጊወች በዕድላቸው፤ በፍላጎታቸው፤ #በራዕያቸው ላይ ይወስኑ ዘንድ ፈቅዶ ቦታ መልቀቅ ያስፈልጋል። በተጨማሪም በራስ የመተማመን አቅማቸውን፤ ቀና ጥረታቸውን ከመፈታተን፤ ህሊናቸውን በክፋ ሃሳብ ከማጥመድም ይሁን ከማወክም መቆጠብ ያስፈልጋል።
 
ወጣቶች ይሁኑ ታዳጊወች አሳምረው #ይበልጡናል። በውነት ይበልጡናል። የሚበልጡን በብዙ ሁነት ነው። ስለዚህም #ከንቦች ተሽለን ልንገኝ ይገባል። ንቦች አዲስ ትውልድ ሲመጣ በክብር የተደራጀውን እርስታቸውን ለአዲሱ ትውልዳቸው ፈቅደው ያስረክባሉ።
 
ሁለተኛውንም ይሁን ሦስተኛውንም የቡቃያው ትውልድ የአገር ውስጡንም፤ የውጩንም የህሊና አቅማቸውን እና ትጋታቸውን እየተከታተልኩ ነው። አብዛኞቹ ያስተዋሉ፤ የጨመቱ፤ የሰከኑ፤ ብልህ የሆነ ሰብዕና አያለሁ። ይህ ተስፋ ለአገሬ ለኢትዮጵያ ይሁን ኢትዮጵያ ለአህጉሩም ይሁን ለግሎባል ዓለሙ ለሚኖርባት የኃላፊነት ተስፋ እጅግ ጠቃሚ ነገር ነውና ሊከበር፤ ሊበረታታ ጥበቃ ሊደረግለትም ይገባል። 
 
#የአርሴናል አወንታዊ ደግ ደጋፊ ኢትዮጵውያን ኢትዮጵያ ኩርኩም ያለ ዕሳቤ ሳይሆን ሥልጡን፤ ድንበር አልባ ቅንነት እንዳላት አስመስክራችኋል። የእኔ አዱኛወቼ እንኳን ደስ አላችሁ። 
 
ማህበረ ቅንነት ክብረቶቼ እንደምን አድራችሁ አረፈዳችሁ?
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
 
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ.
Sergute©Selassie።
23/05/026.
 
ስፖርት የፍቅር ተፈጥሮ ሐዋርያ ነው።

 ዲላን ከለንደን እስከ አዲስ አበባ | አዶናይ ስለ ጃኒ በይፋ አወጀ?#MeseToday#DylanPage

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።