ዕንባ በጎርፍነት። መታመን ሲነጥፍበት።

 

ዕንባ በጎርፍነት። መታመን ሲነጥፍበት። 
 
«… ዓይኖቼ በሰወች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኽውንን ማዳንህን አይተዋልና፤ …»
(ሉቋስ ምዕራፍ ፪ ከ፳፱ ጀምሮ …)
 
«መጨረሻውን መገመት የማይቻል አሳዛኝ ታሪክ #story #lovestory #ethiopianpodacst #ethiopia
 
አመንዝራነት #ዙነት ነው። ደዌም። ስሜቱን መቆጣጠር የማይችል ሰብዕና በሞቱ ውስጥ አዘውትሮ የሚኖር ይመስለኛል። በተለይ እሱን አምነው የተከዱ ነፍሶች ግን ሰማዕታት ናቸው። ምክንያቱም የተፈጠሩበት መክሊት፤ ጥሪ፤ መልዕክት ሁሉ በመከዳታቸው ውስጥ አለና ሊደረመስ ይችላል። ለዚህ ወንጀል ተጠያቂ የሚሆነው ሰብዕና በከረባቱ ይኖራል፤ በገበርዲኑም ይኖራ፤ ባለፈም የፖለቲካ ሰብዕናም ውስጥ ዘው ማለትም ይኖራል። ሁሉም ግን ወና ነው። #ቃ ያለም።
 
አንጎልማ ዲንቢጥም አላት። ሰውነት ህሊናዊነት ነው። ስሜትን መግዛት እንደምን ይሳናል? አመንዝራነት ህሊናን ወደ ዲንቢጥ ተፈጥሮ መልስልኝ የማለት ያህል ነው። ለዛውም በወግ በማዕረግ የተዳረ፤ የተኳለ ሰብዕና ውስጡ ጽዳት ከሌለው፤ አባትነቱም አባት አይሆንም። ባልነቱም እንዲሁ የግፋፎ ካንፓኒነት ይሆናል።
 
እሙኃይ ዓለምነሽ ለመጨረሻ ጊዜ ልጃቸውን የጠየቁት ---- "ትልቁ የዓለማችን #ዓውሬ ማን ነው ብለው ጠየቋት።" ዕጸገነትም የምታውቀውን ዘረዘረች። እናት መለሱላት። "የዓለማችን ትልቁ አውሬ #ሰው ነው አሏት።" እኔም እስማማለሁኝ። የምለየው የአውሬነቱ ሥራ አስኪያጅ ክፋ ሃሳብ ነው ብዬ አስባለሁኝ።
 
አውሬው ደግሞ አግብቶ ወግ አይቀርም ደግሞ ድጋሚ ትዳር ሲይዝ ይቅርታም አይጠይቅም። ነገር ግን የላይኛው ፍርዱን ይሰጣል። ህይወትን አደናቅፏል እና። መኖርን ግማድ አሸክሟልና። ያ ዕብን ሰብዕና ከወለደም ዕዳው ወደ ልጆቹ፤ የልጅ ልጆቹ እንደሚሸጋገርም አያስበውም። ለነገሩ አንጎል ብቻ ካለው ሰብዕና የሚጠበቅ ነው።
 
ቤተ - ሥርጉትሻ እንደምን አደራችሁልኝ ክብረቶቼ? እኔ አምላኬ ክብሩ ይስፋ ደህና ነኝ። 
 
ወደ አራት ጊዜ ያዬሁት ቢዲዮ ነው። ሼርም የማደርገው በድጋሚ ከማምንበት ጽኑ አመክንዮ ይነሳል። የጎላ የማህበራዊ ኑሮ ዘይቤ መታመንን ካልሰነቀ የነገ ትውልድ ዕጣ ፈንታ እንዲህ በዕንባ ጎርፌ በመከፋት ውቅያኖስ የሚቀዝፍ ይሆናል።
 
በዚህ ታሪክ ውስጥ በአንድም በሌላም ሁላችንም አለንበት። የታሪኩ አፈፃጸም፤ የታሪኩ ሂደት፤ ታሪኩ የተፈጸመበት ሁነት፤ ታሪኩ አህዱ ያለበት ዓውድ፤ ታሪኩ የተከወነበት ባዕት ሊለያይ ይችል ይሆናል።
 
በታሪኩ ጭብጥ የመከዳት ጉጉዳይ ግን ዕውነትን ያመሳጠረ ስለሆነ ስክሪፕቱ መምህርነቱ ለዘመናት ሊቀጥል የሚገባው፤ ታላቅ የሴትነት፤ ፍጹማዊ የታማኝነት ጸጋ እና በረከት የረበበት፤ የክቡር ዶር. አዲስ ዓለማዬሁ የፍቅር እስከ መቃብር ታሪክ ዕውን የሆነበት፤ ውስጣችን - የፈተሼ፤ ውስጣችን - የመረመረ፤ ውስጣችን - ያስተማረ ታላቅ የፊደል ገበታ ነው - ለእኔ። 
 
በእኔ ህይወት ኢኮኖሚ ላይ የለሁም በሌሎች ዘርፎች ግን በማህበራዊ ህይወት፤ በፖለቲካዊ ህይወት፤ በሃይማኖታዊ ህይወት ታማኝነት በኽረ ጉዳይ ነው።
 
እኔ የምሻው ታማኝነት ተማላውን ታማኝነት ሳይሆን ፍጹም ታማኝነት ነው፤ ከእኔ ጋር በማንኛውም ሁነት ታቅዶም ይሁን በገጠመኝ ትውውቅ ከኖረ ፍጹም ታማኝነት ዘንበል ሳይል፤ ትርኪምርኪ - ቡቶቶ ሳያስፈልገው ላነበው፤ ልጨብጠው፤ ልዳስሰው፤ ልኖርበት ግድ ይላል። ያ ካልሆነ ማናቸውም የግንኙነት ዓይነት በዝምታ ይቋረጣል። ወቀሳ ነቀሳ አይኖርም። ቂም በቀል ድርሽ አይልም። ጥላቻ የሚባል ነገር ዝር አይልም። በቃ! በዝምታ መከዳትን ሸሽቶ መኖር መገለጫዬ ነው። ይህን የሰጠኝ አምላክ የተመሰገነ ይሁን። አሜን።
 
 
የልጅነት ጊዜ ቁጥብነት የዘለቀው። ዝምታ - የነገሰበት። ማንበብ - የማይደክምበት። ርህርህና ያልተለየው ነበር። አቨይ አባቴ መምህር እና የቤተ- መፃህፍት ባለሙያ ስለነበር ማንበብ በጥዋቱ አስጀመረኝ። እናቴ እቭየ ደግሞ ሞድ ታስጠናኝ ነበር። ስለሆነም ብዙም የልጅነት ጊዜ በአልባሌ ጉዳይ ያተኮረ አልነበረም። በጣም በበዛ ሁኔታ ኃላፊነት ከመወጣት ጋር የተመሳጠረ መሻት ነበረኝ።
 
አክስቶቼ አንዷ "መልካም ሰው" ትለኝ ነበር። እኔ መልሼ መልካሜ እላት ነበር። ሌላው "ደግ ሰው" ት ትለኝ ነበር። እኔም ደግዬ እላት ነበር። ሁለቱም መሃን ስለነበሩ እንክብካቤ በገፍ ነበር። እያያ አጎቴ "ፍቅር" ሲለኝ የእናቴ ትንሽ እህት ናኒቴ ደግሞ "ዋናችን" ትለኝ ነበር። ሌላው አጎቴ "እህትእናት" ይለኝም ነበር። በልጅነቴ ያለኝን ሁሉ ሰጪ ነበርኩ ይባላል። አብሮኝ ያደገው መስጠት፤ ከሌላ አለመቀበልን አጽድቆ ከእኔ ጋር እንሆ ጎለመሰ። ተመስገን። 
 
ስናድግ ድንጋይ ሠርተን፤ ቤት መሥርተን ስንጫወት አንዷ ጓደኛችን "ልጅ ያለው አልፈልግም" ስትል፤ ሌላዋ "ዘመድ አዝማድ ትዳሬን ስለሚያውክ የሌለው" ትላለች። እኔ ደግሞ ብመነኩስ እንደምወድ ገልጬ ካገባሁ ግን ብዙ ቤተሰብ ያለው፤ እናት አባት ያለው፤ ልጅ ያለው ስል ይደነግጡ ነበር።
 
እቀጥላለሁ ልጅ ያለው ከሆነ እኔ ብመከን ፍች አይፈጸምም። ፍች የሚባል ታሪክ አስፈሪም ነው። በአንድ ሰው ጸንቼ፤ ሞት ከመጣ እንኳን እኔን ያስቀድመኝ፤ እሱ ያልኖረበት ዓለም እኔ ምን ያደርግልኛል ወንጌሌ ነበር። 
 
ምንኩስና ከልጅነት ጀምሮ የምመኜውም ነበር። ሞክሬውም ነበር። የአባቶች ፈቃድ የአንቺ ተጋድሎ በዓለም ውስጥ ነው፤ ታግለሽ አሸንፊው አሉ፤ ይኽው ቅዱሳኑ እንዳሉት በምጓዝበት ሁሉ ስንዝር ስራመድ በጋሻ ፈተና።
 
የሆነ ሆኖ የጎንደር ልጅ ማህበረ - ሥላሴን፤ አብረንታት ዋልድባን ገዳማትን፤ የጣና ሃይቅ መካነ ገዳማትን እየሰማን እናድጋለን። አቨይም እናቱም እሙኃዬ ልጅ አያድግላቸውም ነበር። አበይ በአባቱ ደባርቄ፤ አዲስጌ፤ በየዳ ጃናሞራ ስለነበር ዋልድባ ሄዶ ተስሎ ነው የወለደኝ።
የምንኩስና ናፍቆተኝነቴ በእናቴ ወገን የቤተ እግዚአብሄር ሊቀ - ሊቃውንታት ናቸው፤ ባላበቶች ናቸው፤ ካህናት ናቸው፤ በአቨይም ወገን በተለይ በአባቱ ወገን እንደዛው ነው። 
 
ስለዚህ ዓለምን ንቄ እንዳድግ፤ ክብሬን ጠብቄ የማስከበር ጽናትን ተመግቤ ነው ያደግኩት። የባለታሪኳ የዕጸገነት እና የእናቷ የእሙኃይ ዓለምነሽ ታሪክ እና ተጋድሎ አስተዳደጌን በምልሰት እቃኜው ዘንድ አደረገኝ። አባቴ አቨይ ቁጥብ ነው የነበረው። እናቴም ያን ቁንጅና ክድን አድርጋ፤ ከ80/ ላይ / 80 ተፈጽሞ ይህን ዓለም በምንኩስና እስከተሰናበተችበት ድረስ ሳታነሳው፤ ሳታወሳው፤ ሳትወቅስ፤ ሳትዋቀስ፤ሳትከስ፤ ካሳ ሳያስፈልጋት በፍቅር ሁሉንም ገዝታ በሳቅ እና በእሽታ መኖሯ አጊጦ ተከወነ።
 
እኔ የእቭዬ ቁንጅና ይማርከኝ ነበር። ብዙ የትዳር ዓይነት ሲመጣ። በተለይ ሥራ ከያዝኩ በኋላ እህት እና ወንድሞቼን እኔ ላሳድግ አንቺ አግቢ ብዬ ለምኛት አውቃለሁኝ። እሷ ግን በጽናት ዱር ቤቴ ያለውን ትዳር ትጠብቅ ነበር።
 
ትዳሯ አገር ሲገባ የተፈጸመውን በፍጹም ሐሴት አስተናገደችው። ከ80 ላይ 80 ተፈጽሞ ነበር። ያም የጫካ ህይወቱ የፈጠረው ጫና ይመስለኛል። የሆነ ሆኖ የጎንደር ክብርት እናት፤ የጎንደር ክብርት ሚስት፤ የጎንደር ክብርት እህት፤ የጎንደር ክብርት አክስት የገዘፈ ታሪክ በዚህ ዙሪያ አላቸው። 
 
የጎንገ።ደር ሴት ለትዳሯ የምትከፍለው መስዋዕትነት ቤተ - መጸሐፍትነት ነው። ይሞክሩታል። ካልተሳካ ክውን ሽክፍ ብለው ልጆቻቸውን ያሳድጋሉ። ያልሞከሩትም በንጽህና እና በድንግልና ኖረው በድንግልና በሥጋ ይለያሉ። ለምን?
 
የጎንደር ሴቶች በልባቸው የታተመው የገዳማዊነት አስተምኽሮ ነው። ይሄን ማህተም የሚያስቀጥል ገጠመኝ ከሌለ በቃ ገድመው ይኖራሉ ብዙወቹ። ከትምህርት ቤት በቀጥታ ምንኩስና ህይወታቸው ይሆናል። 
 
በትዳራዊ ህይወት መታማንን በልኩ ስለማያዩ። ይቆርጣሉ። ይወስናሉ። በወሰኑት ህይወት ጸንተው ይኖራሉ። እርግጥ ነው ከጋብቻ እስከ በሥጋ መለዬት የሚኖሩ ታሪኮች አሉ፤ የእኔ የሚታዬ ወላጆች የአባዬ እና የናናዬ ህይወት በኽረ ምሳሌ ነው። የአክስቶቼም እንዲሁ። ታዲያ አለመታን ከዬት ይመጣል ለሴቶች ማለቴ ነው። ከሆነ በአንድ ጸንቶ መዝለቅ፤ ይህን አቅም አግኝቶ መከወን ያልቻለ አቅመ ቢስ፤ ካፒቴኑ የስሜት ልቅነት ከሆነ ገጠመኝ ከኖረ ሰብሰብ ብሎ መኖር በስንት ጣዕሙ።
 
በገጠርም በከተማም የክት እና የዘወትር ነፍስና ስጋ ሊኖር አይገባም የሚል አህትዮሽ ሳይነጋገሩ ጎንደሬ ሴቶች የተስማሙበት ውል አለ። መኖርን ለማሸነፍ ከዚህ ወጣ ያለ ገጠመኝ ይኖራል። ነገረ መሽታ ቤት እና ጣጣው። ይህን በተለዬ አግባብ እኔ አየዋለሁኝ። 
 
ከዚህ ባሻገር ባሉ የአኗኗር ዘይቤወች ግን ዕውነት ቦታውን ሸሽቶ አያውቅምና ዕውነቱ ዕውነትን #ያጎልለዋል።። ክድን ብሎ የተያዘ የጎንደር ሴቶች የጽናት መክሊት አለ። ከእሙኃይ ዓለምነሽ ታሪክ ውስጥ ያልተነገሩ፤ ያልተፃፈባቸው፤ የቁም መናኝ ተሁኖ የሚኖርበት ሰማዕትነት አለ። እናትነት ልዩ ጸጋ ነው ግን ተሸሽቶ፤ ልጅ መኖርም ሽልማት ነው፤ ግን ተመንኖበት በሴትነት ማንነት ውስጥ ተፈቅዶለት የሚኖርበት ገዳማዊ ህይወት በሁሉም ጓዳ አለ።
 
አዲሱ የጎንደር ትውልድ ከአንድ አባት እና እናት ልጆቹ ይወለዱ፤ ያድጉ ዘንድ ቁርጠኛ ውሳኔ ላይ ሊደርስ ይገባል ባይ ነኝ። እርግጥ ነው በሃይማኖት ፈቃድ ከኖረ ይህ ሃሳቤ ላይመለከት ይችላል። ሌሎቻችሁ ግን ትዳርን ያህል ታላቅ ተቋም የጎዳና አዳሪ እንዳታደርጉት በአጽህኖት ላሳስባችሁ እወዳለሁኝ። አንዲት ሴት ሁሉ አላት። ስለዚህም በቂ ናት። ሌላ አያስፈልጋችሁም። 
 
 
የጎንደር - እናት፤ የጎንደር - እህት፤ የጎንደር - አክስት ከቤቷ #ሆሚኮኖሚክስ ናት። ልክ 7 ዓመት ላይ የሙያ ቡፌ ተዘርግቶ ሴት ከሆነች ትማራለች። የሚቀር የሙያ ዓይነት የለም። የቀለም፤ የሃይማኖት፤ ብሄራዊነት፤ የኃይማኖት ጽናትን፤ የባለሙያነት ትምህርት ቤት ውስጥ እኩል ይሰጣል። 
 
እና ቤት ውስጥ ባለሙያ ሚስት እያለች የሌላ ምኞት ከምን ይመነጭ ይሆን? የት እንደቀዱት አላውቅም። እቴጌ ጎንደር የሙያ እማወራናት። የያዘችው ሁሉ የሚጥምላት - የሚያምርላት።
 
ጎንደር መሬት ላይ "የብትን በርበሬ " ወጥ የማይታሰብ ነው። ነውርም ነው። አንድ ጊዜ በዓመት ድልህ ይዘጋጃል። ከሁዳዴ ፆም መፍቻ፤ ከህማማት በፊት ስንዱዋ ታሰናዳዋለች። ማስተካከያው በየዓይነቱ ቅመም ይዘጋጃል። ጎንደሪና ቅመማቅመም አብቃይ ናት። ዓዋዜ ብዙ ዓይነት ነው። ሽሮ ክረምት ከመምጣቱ በፊት ይሰናዳል፤ አልጫ ቀይ ተብሎ። የወጥ ዓይነት ቁጥር የለውም። በጥራትም በጥንቃቄም ተምረን እናድጋለን። ቦዘና፤ ዝልቦ፤ እልበት፤ ቃተኛ፤ ዝልዝል፤ ጥብስ፤ ኧረ ስንቱ?
 
ህብስቱ፤ ሙጌራው፤ ቃተኛው፤ አነባበሮው፤ ሊፍተሩ፤ ፍርንዱሱ፤ በተሃው፤ ቡቡኙ፤ ኮረፌው፤ ጠመጁ፤ ሰነፋ፤ በልጋው በሶው፤ እልበቱ ዓዋዜው ከተገባችው ሚስት ዘንድ አለ? እና ቅልውጡ ለምን? 
 
ይህን ጥሶ የሄደ ስሜት ነው እንደ ዕጸገነት ዕንባ በጎርፍነት፤ ፍጹም ታማኝነት ህማማት የሚሆንበት። ትዳር መምሥረት መፍታት፤ ከትዳር በላይ መመኜት እና ድርጊቱን አዲሱ ትውልድ ቀጥቶ መቃብር ሊልከው ይገባል ብዬ አምናለሁኝ። በዕፂ እና በእናቷ ህይወት ሊያበቃ ይገባዋል።
 
የስንት ብቁ፤ ስንዱ የውስጥ ውበት ዕጣ ፈንታ - ተከፍቶ፤ ተበድሎ፤ ተሰቃይቶ፤ መክሊት ተደፍቶ፤ ችሎታ መክኖ፤ ክህሎት መኖ የሚኖረው በህሊናዊነት ቀራኒወነት ነው። ሁልጊዜ መሄድ፤ ሁልጊዜ መጓዝ ለምኑ ይሆን????
 
#ነገረ - ጫት።
 
በዚህ ቃለ ምልልስ እየሰቀጠጠኝ የሰማሁት አልኮልን መድፈር እና ጫት ነው። እኛ ስናድግ፤ ወላጆቻችን ሲያድጉም ጫት ምን እንደሚመስል ሳያውቁ፤ ሳናውቅ ነው ያደግነው።
 
አንድ የዩንቨርስቲ ሙሁር ጫትም ቃሚ፤ አልኮሊስትም። ህሊናዬ ሊሸከመው ያልቻለው ጉድ ነው። ይህ እኮ ሸክም ነው። ለምን የከተማው ከንቲባ ጽህፈት ቤት የጫት ገብያ እንዲቆም አያስደርግም። እኔ አንገቴን ደፍቻለሁኝ። ስንት ዓይነት እራስን አለመግዛት ነው ትውልዱን እየፈተነው የሚገኜው። ኧረ ተንቀሳቀሱ? የምን #ዳ! ነው? ቀጠሮው ለመቼ ይሆን????
 
የእናቷ ምናኔ ያስደነገጣት ዕፂ ቢራ መደበቂያዋ ነበር። ይህም የማላውቀው ታሪክ ነው። እርግጥ ነው ጠላም ጎንደር ጠላ ለስድስት ወርም ይሆናል። መልኩ ጣዝማ ነው የሚመስለው፤ ጠጅም ቤት ስለሚዘወተር ዓይነታውን ሳይሆን ቅራሪ ልጆች ጠጥተው ሊያድጉ ይችላሉ። ቡቡኝ ለስላሳ ነው እኔ እማውቀው። ይህ ጉዳይ የጎንደር ወጣቶችን የሚከታተል ተቋም ካለ፤ ዩንቨርስቲውም እራሱ ፕሮጀክት አዘጋጅቶ በነፃ ሊያስተምር ይገባል። 
 
ይህን መሰል ደባል ባህሬ ለገዳማዊቷ በዕታችን ለእቴጌ ጎንደር ይህ መንገድ ዕዳ ከሜዳ ነው። ጎለጎታ ነው። ቀራንዮ ነው። #ጫት? እግዚኦ ነው???? እኔ እኮ ጠላን ጣዕም አላውቀውም። የአረቂን ጣዕም ትናንትም ዛሬም አላውቀውም። ማወቅም አልፈልግም። ለምን? ልቅነትን ስለሚያላብሰኝ። ከዛሬ ጀምሮ ጎንደር ከጫት ንግድም፤ ተጠቃሚነትም ነፃ ልትሆን ይገባል።
 
ጫት ባህላችን አይደለም። ጫት ትውፊታችን አይደለም። ጫት የታሪካችን አካል አይደለም። በታሪካችን ማንነት ልክ ትውልዱን አጽንቶ ማስቆም ያስፈልጋል። ጫት በጎንደሮች ብሂላችን አይደለም፤ እኛም ለጫት አልተፈጠርነም። ጫትም ለእኛ የሃብት ምንጭነት አልተፈጠረም። ጫት የኢኮኖሚ እንብርት የሆነላችው ክልሎች ይኖራሉ። ይህ እንደ ባህሉ ሊያዝ ሊተዳደር ይችላል። ለእኛ ለጎንደሮች ግን ጫት የትውልድ መቃብር ነው። ለዛውም ሰፊ እንጦርጦስ።
 
#ነገረ ትዕግስት። "ሙያ በልብ፤ ልብ ያለው ሸብ።" የጎንደሬወች ቅኔ ነው።
 
ይህ የወል ባህሪያችን ነው። የተሰጠን አምላካዊ፤ አላኃዊ ስጦታን ትዕግሥትን የምንከባከብበት ዘይቤ ድንቅ ነው። የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ላይ " ሁሉ ተፈቅዶልኛል፤ ሁሉ ግን አይጠቅምም። " የሆነው ሁሉ፤ የገጠመ ፈተናን ሁሉ Timing ምራኝ ማለት ልቅና ነው። ብዙ በጎንደር ሴቶች ላይ የተፈጸሙ፤ የተከደኑ በደሎች አሉ። ይኖራሉም። ይሁን ብሎ አምቆ ማስቀመጥ ፈጣሪ ከሰጠን ትዕግሥት በላይ ነው። ፈጣሪ ከመረቀልን ቅንነትም በላይ ነው።
 
ያ ሁሉ በደል የተፈጸመባቸው እሙኃይ ዓለምነሽ፤ ከበዳያቸው እግር ሥር ወድቀው ይቅርታ ጠይቀዋል። ይህን ዕንቁ ምርቃት በምድር ላይ በእኛ ትውልድ ማዬት የእናታችን የቅድስት ክርስቶስ ሰምራን ንጽህና፤ ቅድስና አየሁበት።
 
እሙኃይ ዓለምነሽ በዛ መከፋት ውስጥ ሞትን ፈቅደው፤ ተሰቃይተው መጨረሻ ሞት አሻም ብሏቸው መዳኑ ሲገኝ ደግሞ ምነና። ይህን ዘመን በሰማዕትነት እንደምን እንዳስተማሩት እሙኃይ ዓለምነሽ ታምር ነው። በረከታቸው ይድረሰን፤ ይደርብንም። አሜን።
 
ቤተሰቦቻቸው መከፋታቸውን የተጋሩበት ብልህነት "የአታንሱባት ጥበብ"፤ ማጽናናትን የመገቡበት መንገድ አስቀንቶኛል። በደል በተደጋጋሚ የደረሰባቸው፤ ከዛ ጋር የሚፋለሙ አንስት እናት፤ እህት፤ አክስት አይዞሽ በእጅጉ እንደናፈቃቸው ሊያልፋ ይችላሉ። 
 
ስለሆነም ቤተሰብ ዕፂን አመሰግናለሁኝ። ወንድሞች በተወሰነ ደረጃ ግዴታቸውን ለመወጣት ቢሞካክሩም ያቺ ቀንበጥ ዕጣ ነፍሷን በሞት አፋፍ ላይ ያሉትን እናቷን በጭነት መኪና ይዛ፤ ሙሉ 5 ወር ያስታመመችበት መንገድ እና ብልህነት የፊደል ገበታ ነው።
 
ጡረታ ሰፈር እኔ አድጌበታለሁኝ። ከጨዋ ሰፈር ቀጥሎ ማለት ነው። ለነገሩ ወደ አባቴ ስሄድ አደባባይ እየሱስም ይታከልልኝ። ጡረታ ሰፈር አገነባቡ የኢትዮጵያ ጀግና ሰራዊት በጡረታ ይሁን በህመም ከሰራዊቱ ሲሰናበት የሚኖሩበት ሰፈር ነው። ትንሿ ኢትዮጵያ ናት።
 
 እናቴ ከጨዋ ሰፈር ወደ ጡሮታ ሰፈር ስትዛወር ጎረቤቶቿ ሲያዝኑ ተጨማሪ እህት እና ወንድም ሳገኝ አትዘኑ ነበር ያለችው። እናቴ ማህበራዊ ናት። ጥሮታ ሠፈር በዕቅፋ ነበር የተቀበለን። ዕፂ እያወራች ያደኩበት ድባብ መጣብኝ። አወጋጓ እራሱ ሐሤት ነው የመገበኝ። 
 
#ኃላፊነትን ስለመቀበል፤ ስለመፍቀድም መሰጠት በጎንደር ህይወታችን ነው።
 
እንግዲህ ጎንደር ስናድግ "ሀሌታ " ኃላፊነትን በጥዋቱ መለማመድ ነው። በተለይ አንስት ከተሆነ። ደርሼ ለእናቴ የህሊና ጉዳይ ነው። ይህን ሁላችንም ያለፍንበት ባያኮራም ግን ለህሊና እረፍት ይሰጣል።
 
የእናቷን ውስጥ ውስጧ ያደረገችው ዕፂ ከቴሌ ባር እስከ ጊፍት ሾፕ፤ ጥረቷ ጥበቧ ይደንቃል። እናቷ ሲመንኑ ፍቅሯን የገለጸችበት ሁነትም አሳዛኝ ቢሆንም እናቷን በልጅነት ከፍተኛ የሞራል ልዕልና ያስቀጠለችበት ሁነት ይደንቃል። በእናቷ ምናኔ ውስጥ ልቧ - እስትንፋሷ - ትር ታዋ በዓቷ ማድረጓ ልዩ ጸጋዋ ነው። እናት ያለው ሁሉ አስተምኽሮዋን ሊከተል ይገባል። ያጠፋችው ሰከንድ የለም። "ተምሬ ሥራ እስክይዝ እናቴን ባጣስ?" 
 
#የእህት እና ወንድም ተመግቦ ህልም። 
 
በአባቷ ወገን እህት እና ወንድም ቢርባት፤ በእናቷ ወገን እህት ወንድም ቢጥማት እሷ ባሰበችው መንገድ ሳይሆን ቀርቶ እንዳትጎዳ ፈጣሪ ጥበቡን የሰራበት መንገድ ለእኔ ትንግርት ነው። ስለዚህም ፈጣሪን ደግማ ደጋግማ ታመሰግነው ዘንድ እንደ ታላቅ እህት ልመክራት እፈልጋለሁኝ።
 
ብዙ የምታዝንበት፤ በእጅጉም የምትከፋበት ገጠመኝ ሊኖርም ይችላል ብላ ልታስብ ይገባል። ከእህት ይልቅ ሌላ የጋብቻ ዝምድና፤ በጊዜ ገጠመኝ የተገኜ ተጽዕኖ ፈጣሪም ሊሆን ይችላል የሚቀረብበት፤ እሷ እንዳልተፈጠረች የምትታይበት ገጠመኝ ኑሮ ከምትቆስል ይልቅ ይህ የተሻለ ነው ብሎ ፈጣሪ መጥኖ የሰጣትን ታክብረው። የእኔ ምክር ይህ ነው። መኖር ቁጥር ብቻ ሊሆን ይችላል።
 
ሁለተኛ ላሳስባት የምሻው አልኮልን ኃራም እንድትል ሲሆን። በተጨማሪም የእናቷ የቅድስና ምርጫ ምርቃቷ ስለመሆኑ አምና ልትቀበለው የሚገባ መሆኑን አበክሬ ልገልፅላት እወዳለሁኝ።
 
#በቀልን ማሸነፍ።
 
በዚህ ታሪክ ውስጥ ተበዳይ፤ በዳይ እግር ሥር ወድቆ ይቅርታ መጠየቅን ሰምተንበታል። መላዕክነት ነው። በሌላ በኩል የገማ በደል ሲደርስ ቤተሰብ በደል በፈጸመው ላይ ስሜታዊ እርምጃ እንዳይወስድ አምቆ መያዝ፤ ልዩ መሰጠት ነው።
 
#ቂምን መርታት።
 
ቂመኝነት መጀመሪያ የሚጎዳው እራስን ነው። ቂመኛ አለመሆን ተጠቃሚ የሚያደርገው የእራስን ማንነት ሰብዕና አጽድቶ ማስቀጠል የሚያስችል ልዩ ስጦታ ነው። ይህ ታሪክ ያሰተማረው አንኳር ቁምነገር ነው። በደለኛን ለመክሰስ የተወሰደ እርምጃ የለም። ይህ ተጋድሎ የምህረትን ኃያል ተጋድሎ ያስተምራል። 
 
#ጥላቻን መመከት።
 
የባለታሪኳ እናትልጃቸውን በአባት ፍቅር መግቦት አሳደጉ። ዕውነተኛ የፍቅር ተፈጥሮ ይህ ነው። ከዛ ሁሉ የመከራ ዘመን በኋላ ስራ ፍለጋ እሙኃይ ዓለምነሽ ሄዱ። ሥራ አገኙ። ለፊርማ እና ለውል ማናጀሩ ዘንድ ቀረቡ።
 
ያች ቅጽበት። መጀመሪያ ቁሞ ያዩት ሞቱ የተባሉት ሙሉ 6 ዓመት ጥቁር የተለበሰላቸው፤ ጸጉር የተላጨላቸው፤ የቆረቡበት አመክንዮ፤ በክፋ ሃሳብ ተሸካሚው ሰብዕ ግፍ በፍቅር አስተናግዱት ባለታሪኳ። 
 
ቀጣይ ጥቃት በበደለኛው ላይ እንዳይፈጸምም ዋጋ ከፈሉ። ባለታሪኳ፤ ሌላው ቀርቶ የባለቤታቸውን ቤተሰቦች፤ ጓደኛ፤ አማጫቸውን ሳይወቅሱ፤ ሳይነቅሱ ዝምታን ዘውድ የደፋበት ክህሎት ከምድራዊው ሰው ያሰኛል። ለትውልዱ ልዩ ገቢራዊ ሽልማት ነው።
 
ሌላው ልጃቸው ዕጸገነት መጠጊያ ያደረገችው የወንድ ጓደኛዋን ክህደት ሳያስደነግጣት፤ እንዳመነዘረ ስትሰማ ዕዳውን የከፈለችበት አግባብ ከድንቅ በላይ ነው። እጅግም የሚመስጥ።
 
በፆታ ትንኮሳ ላይ ዕጽዬ ያሳየችው ጥንካሬ እኔም ያለፍኩበት፤ እየኖርኩበትም ያለሁበት የፈተና መስክ ነው። ጀግናዬ ናት። 
 
ስትጫወት፤ ስትተርክ፤ ስታነባ አብሬያት ቁጭ ብዬ የማዳምጠው ነው የሆነልኝ። ከዕንባ ወጥታ ፈገግታ፤ ከዛም ወደ ዕንባ ጎርፍ፤ ከዛ ውሽክ ስትል፤ እንደ ገና ዕንባ፤ የእጅ እንቅስቃሴዋ፤ የዓይኗ ትዕይንት ልቤን ገዙት። በውነት የውስጠኛ የቅርቤ የሆነች ወጣት ሆነችልኝ። እቅፍ አድርጌ ብተኛ በጣም ወደድኩኝ። ትስባለች። ተፈጥሯዊ የሆነ ሰብዕናዋ ከውጥ ተደላድላ እንድትቀመጥ ያደርጋል።
 
የፊልም ፕሮዲሰረች ትጋት፤ የዕንባመነት ዲታነት፤ የዓይን ተዋናይነት ካሰኛችሁ ዕጸገነት ህይወቱ ናት። የሙዚቃውን ፋናላምሮት አንዱ መንገድ ነው። በዚህ አጋጣሚ ሁለገብ የጥበብ ሰው አቶ ሰውመሆንን እባክህ እያት ማለት ፈለግሁኝ።
 
እናቷን አስታማ አድና። ቤተክርስትያን መኪና ተከራይታ ስታመላልስ እንደማንኛውም ደልዳላ፤ ወይዘሮ እናት ያለችው አግባብ፤ እናቷን ስታጣ በራሷ ላይ የወሰደችው እርምጃ እና የከፈለችው ዋጋ፤ ዝቋላ ገዳም ድረስ ሄዳ አለኝታነቷን ያመሳጠረችበት ጎዳና እናትም፤ ልጅም መሆንም ምንኛ ታላቅ የመኖር ስጦታ እንደሆን አየሁኝ። ለዚህ ነው ፍቅርን በመኖር መግለጽን ልንማረው ይገባል የምለው።
 
ሌላው እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መክሊት፤ ጥሪ፤ መልዕክት ይዞ ይወለዳል የምለውን ዕውነት በዚህ ታሪክ ውስጥ ተገናኝቸዋለሁኝ። እናት፤ ልጅ፤ መላ ቤተሰብ ሁሉንም ሁነውልኛል።
 
የፖድካስቱን ዋና አዘጋጅ አቶ ፌፄም ፍሰኃን በትሁት መንፈስ አመሰግነዋለሁኝ። አድማጭነቱ፤ መመሰጡ፤ ዕውቅና መስጠቱ፤ መፍቀዱ፤ ዕንባው፤ ትዕግስቱ፤ የአጠያዬቁ አርት ሁሉ ግጥሜ ስለሆነ ሳብስክራይብ አድርጌ አክብሬ ከማደምጣቸው የአገር ቤት ሚዲያወች አንዱ ነው። ቅንነቱ በጣም ይገርመኛል። ለትውልድ እምመክረው ቅን ሁኑ። ቅን ሆናችሁ የምታጡት ነገር ቢሆን እንኳን ፈጣሪን አላህን ታስደስቱበታላችሁ።
 
ሌላው በታማኝነት ለፈጠረን አምላካችን ህግ፤ ቀኖና እና ዶግማ ለሥጋ ፈቀዳ ብለው ወጣቶች፤ እንዳይጥሱት በትህትና ላሳስባችሁ እወዳለሁኝ። ፍጹም ታማኝነት የህይወት መርኽ ማድረግ አቅምን ይጠይቃል። የሆኑበት ደግሞ ጀግኖች ናቸው።
 
በዚህ አጋጣሚ ምስክርነት ለመስጠት ያህል ሲዊዝ ውስጥ ፍቺ አንድ ጊዜ ብቻ ሰምቻለሁኝ። ከዚህ ዞግ፤ ሰፈር፤ ሙያ፤ የሃብት መጠን አይታሰብም። ፈጣሪ ከሰጠው ጋር በጋራ መኖር ይለፍ የተሰጠው ነው። አብዛኞቹ የተዋህዶ ልጆች ቆርበው ነው የሚጋቡት። የሰከነ የትዳር አትሞስፌር ነው ያለው። በትውልድ ግንባታ ላይም እቴጌ ሲዊዝሻ የመጡ ወላጆች ስኬታማ ናቸው።
 
ሌላው አጋጣሚ የሰጠኝ ቤተሰቦቼ ከሽዋ እና ከጎጃም ነበር። ትዳራቸው በፍጹም ታማኝነት የውሃ ልኩ የጸና ነው። የሚደንቅ መከባበር ነው ያዬሁት። ምስጉን ናቸውም። ሥልጣኔም ነው ለትዳር ህግጋት በፍጹም ታማኝነት መገኜት።
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
 
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
26/05/025.
 
ሰማዕትነት በምድርም ለደጋጎች፤ ለጽኑወች የተሰጠም ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።