ለእናት #ቋሚ የዕንባ ቋት መሆን ከምን ይመደብ ይሆን? ግን እቴጌ ጎንደር ስለምን #የበቀል መሞከሪያ ጣብያ ሆነች?

 

ለእናት #ቋሚ የዕንባ ቋት መሆን ከምን ይመደብ ይሆን? ግን እቴጌ ጎንደር ስለምን #የበቀል መሞከሪያ ጣብያ ሆነች?
 
እግዚአብሄር በሚያውቀው ሚስጢር በዘመነ ኢህአዲግ የነበሩ አንቱ ሊቃናቶቿ አልቀዋል። በፋኖም በብዛት መሪወቿ አልቀዋል።
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 
#ምዕራፍ ፲፱።
 
እንዴት ሰነበታችሁ ክብረቶቼ? 
 
ይህን የመከራ ዜና የሚሰማ መምህር፤ ቤተሰብ እናት፤ አሳዳጊ በተለይ ሰርክ ዕንባ የታወጀለት #የህክምና #ፋክልቲ እንደምን ያስተናግደው ይሆን? ሰርክ ከእነኝህ ንጹህ ሆነው ከተፈጠሩ የህክምና ባለሙያወች፤ እጩወች ላይ ስለምን የበቀል ዱላ ተበራከተ?
ከውስጤ ፈጽሞ ሊወጣ ያልቻለ የህክምና ሊቅ አለ። ሁልጊዜ የዶር አንዷዓለም ዳኜ ፎቷቸውን አየዋለሁኝ። ከህሊናዬ ሊወጡ አልቻሉም። ታትመዋል። 
 
#ግን ጎንደር ከተማ ማን ይሆነው መሪዋ?
 
በኢትዮጵያ መማር፤ ጥበብን መፍቀድ፤ ስፖርትን መውደድ፤ ሙዚቀኛ - ተዋናይ - ጋዜጠኛ ጸሐፊ መሆን፤ ወይንም ፖለቲከኛ መሆን፤ ሃኪም መሆን፤ #ሰው ሁኖ መፈጠር እራሱ መከራ ነው? እንደምን ይህ #ሰንሰለታማ #የቂም እና #የበቀል ሂደት ሊቆም እንደሚችል አላውቅም።
 
በጣም ብዙ፤ እጅግ ብዙ በህክምና ዙሪያ የሚተጉ ተደግመው የማይገኙ የህክምና ስፔሻሊስቶች ልክ እንደ ዶር አንዱዓለም ዳኜ ዓይነት #በስጋ ተለይተዋል። በሰው እጅ #ሰማዕትነትን ተቀብለዋል። በርካታ ትዳር ፈርሷል። በርካታ ልጆች ያለአባት ወይንም ያለ እናት ቀርተዋል። ለዚህ ጉዳይ ብቻ ጸሎት፤ ሱባዬ ያስፈልጋል ብዬ የፃፍኩትም ከዚህ ቀደም ለዚህ ነበር። 
 
#ይህ አንድ ሃዘን ብቻ አይደለም።
 
ጎንደር እንደ ልማዷ #ምህላ ታድርግ። ለእሱም ፈቃድ ያስፈልግ ይሆናል። የማን? የማይታወቅ አቅም ካለው ኃይል። ከአቤቱ ህወሃትም ዘንዳ ሊሆን ይችላል። በብዙ የማያቸው ህውከቶች፤ ጥቃቶች መሬት ላይም ይሁን ሞገድ ላይ ጎንደር ላይ የበረታ ነው። ለምን? አማኑኤል አባቴ ይመርምረው። 
 
ቤተሰብ ተቋማትን አምነው ነው ልጅን ያህል #ስስት - #ተስፋ - #ፍቅር የሚልኩት። የጎንደር ዩንቨርስቲ በራሱ የሚተማመንበት የደህንነት አቅም ሳይኖር ልጆች በጋራ የስፖርት ፕሮግራም እንዲዩ መፍቀዱ በእጅጉ አሳዝኖኛል። ቅድመ ጥንቃቄ ያስፈልግ ነበር። ያልተገባ መቀደም እና መከራን ተቋሙ ሊያስተናግድ አይገባም ነበር።
 
ባለፈው በአርሰናል የኢትዮጵያ እግር ኳስ አፍቃሪ የድጋፍ ተሳትፎ ላይ የነበረው ሁነት የፖለቲካ ቻሌንጅ ፈተና ግጥሞት ነበር። ያ መምህር ሆኖ ከዚህ መሰል የወል መከራ ለመዳን #ጥንቃቄ ሊመገብ ያስፈልገው ነበር። 
 
ጎንደር በተፈጥሮዋ ደመ መራራ ናት። ጎንደሬወችም የፈለገ ጭምት፤ ክውን ሽክፍ ብለው ይቀመጡ ከ እስከ የማይባሉ የፈተና ማዕበሎች ይገጥማቸዋል። በሌላ በኩል እቴግ ጎንደር #ቅመም እና #ደማቅም ናት። ስለሆነም ጎንደር ላይ የሚከወኑ ብሄራዊ ይሁን፤ ዓለም ዓቀፋዊ ክስተቶች ብርቱ ጥንቃቄ ይጠይቃሉ። እቴጌ ጎንደር ጎንደር ብቻ አይደለችም። እንደዛ አትሰቡ። 
 
ሰሞናቱ እያንዳንዱ ሰከንድ ጸሎት እና ብርቱ ጥንቃቄ ያስፈልገው ነበር። ከህማማት በላይ #ከባድ ነበር። በተለይ ኃላፊነት ያለባቸው የተቋማት አስተዳደሮች ይህን ያህል መዘናጋት አያስፈልግም ነበር። ጦርነቱ እኮ #ኮረጆ ላይ ነበር። 
 
ለሚያልፍ ቀን ትውልድ በየዘመኑ በሚመጡ የምርጫ #ሽርሽሮች ይህን መሰል የልጅ፤ የትዳር፤ የትውልድ ግብር ሊከፍል አይገባም ነበር። አሳዛኝክስተት ነው። #ሰማዕቷ ሺብሬ ደስአለኝ የማትረሳ ምልክት ነበረች። የተሰዋችለት ዓላማስ አድራሻው የት ይሆን ያለው? ማንስ እሷን ያስታውሳት ይሆን? 
 
የሆነ ሆኖ ንጹኃን ናቸው እጩ ተማሪወቹ። ምን ያውቃሉ? ስለምንስ ስቃይ ይታውጅባቸዋል? የህክምና ሙያ እጅግ አድካሚ፤ በብዙ ጥረት የሚገኝ፤ የሙሉ ዕድሜ የጥረት ውጤት ነው። ሙያው በራሱ ሰብዓዊ፤ ተፈጥሯዊ፤ #አጽናኝ እና ለእርዳታ ቅርብ የሆነ #ቅዱስ ነው። ምንጊዜም፤ በየትኛውም ሁኔታ ኢትዮጵያ ሃኪሞች ያስፈልጋታል፤ የተማረ ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ ያስፈልጋታል። ይህን በብልህነት ማሰብ ያስፈልጋል። ትግሉ ይሁን ፕላኑ ከራስ ፍላጎት ያለፈ ለትውልድ ከሆነ።
 
 
የኢትዮጵያ እናት መሐጸኗ ሁልጊዜ #በሰቀቀን ተመግቦት መሆን አያሳዝናችሁም? ለምን በእናቶች ላይ አንጀት ቁርጥ የሚያደርግ ውሳኔ ትወስናላችሁ? 
 
በደቡብ ያሉ ዩንቨርስቲወች ተማሪወች አይደለም ኳስ ጨዋታ ማዬቴ፤ ዕድሜያቸው የፈቀደው በምርጫ ተመዝግበው ሙሉ ተሳትፎ አድርገዋል። በሰላም ነው ወጣቶቹ የተሳተፋት። ማንም ከልካይ የለባቸውም በምርጫ የተሳተፋት ይሁን #ያልተሳተፋት። ይህ የመብት መበላለጥ ወጣገብነትን በህሊና ላይ ያለው ተጽዕኖ መዝኑት።
 
ለዚህ ነው በጭምቱ የደቡብ ህዝብ የፖለቲካ ሊቃናት ሁልጊዜ እምመሰጠው። ነገን ያሰቡ ናቸው። ከነገ በስትያንም የማደራጀት አቅም አላቸው። ለየትኛውም ጊዜ፤ ለየትኛውም የመንግሥት ዓይነት ባለሙያ ያስፈልጋል። 
 
በመጨረሻም።
 
ሰመዕትነትን ለተቀበሉ ተማሪወች ቤተሰቦች መጽናናትን እመኛለሁኝ። ቁስለኛ ለሆኑትም የውሻ ቁስል ያድርግላቸው። አሜን። ጎንደር ላይ በየትኛውም ሁኔታ ኃላፊነት ላይ የተቀመጣችሁ ሁሉ ድርብ፤ ንብርብር ኃላፊነት እንዳለባችሁ ብታውቁ ጥሩ ነው። ጥንቃቄ ያተርፋል እንጂ አያከስርም። በብዙ መዘናጋት፤ ብዙ ተስፋን እንዲህ ይሰባብራል። 
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን፤ አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
Sergute©Selassie.
ሥርጉተ©ሥላሴ።
02/06/2026.
 
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
 
----------------------------------------------------------------- 
ከሃኪም ፔጅ ያገኜሁት ዝርዝሩ ይህ ነው።
ለእናት በጎንደር ተማሪዎች ላይ የሽብር ወንጀል ተፈጠረ!!!
=============================
" አንዱ ተማሪ ድንገተኛ ክፍል ላይ እንደደረሰ ህይወቱ አልፏል። ሁለቱ ደግሞ ኦፕራሲዮን ክፍል ከገቡ በኋላ ነው ህይወታቸው ያለፈው " - የጤና ባለሞያ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ
በጎንደር ዩኒቨርስቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ ተማሪዎች ተሰብስበው የአርሰናል እና ፒኤስጂ የቻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ጨዋታ እያዩ በነበረበት ወቅት በተከሰተው ፍንዳታ የተጎዱ ተማሪዎች ለህክምና ወደ ዩኒቨርሲቲው ሆስፒታል መምጣታቸውንና የሞቱ ተማሪዎች እንዳሉ አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ የጤና ባለሞያ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አረጋግጠዋል።
በዩኒቨርሲቲው ሆስፒታል እንደሚሰሩ የገለጹልን እኚሁ የጤና ባለሞያ ፍዳታው የተከሰተው ትናንት ምሽት 2 ሰዓት ተኩል ገደማ መሆኑን ገልጸውልናል።
" ማን እንደጣለው አይታወቅም ቦምብ ፈንድቶ ነው በርከት ያሉ ተማሪዎች ተጎድተው የመጡት። የሞቱ አሉ መባሉም እውነት ነው " ሲሉ ተናግረዋል።
" አንዱ ተማሪ ድንገተኛ ክፍል ላይ እንደደረሰ ህይወቱ አልፏል። ሁለቱ ደግሞ ኦፕራሲዮን ክፍል ከገቡ በኋላ ነው የሞቱት። ሦስት ተማሪዎች ናቸው የሞቱት " ሲሉ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።
የተጎዱ ተማሪዎች ስንት ናቸው ? ያልናቸው ባለሙያው " የተጎዱት በርከት ያሉ ተማሪዎች ናቸው። ቁጥሩን በትክክል አላውቀውም ግን በርከት ያሉ ተጎጂ ተማሪዎች ናቸው የመጡት " ብለዋል።
ተማሪዎች የተግጂዎችን ቁጥር 20 አድርሰውታል፤ በርከት ያሉ ሲባል 20 ይሆናሉ ? ስንላቸው፣ " ይሆናሉ አዎ። እንደዛ ይሆናሉ " ሲሉ መልሰዋል።
ፍንዳታው የቦምብ መሆኑን እንዴት እንደታወቀ ሲገልጹ ፥ " ቦምብ መሆኑን ያወቅነው ከጉዳቱ አንፃር ፍንጥርጣሪዎቹ ቁስል ላይ ስለተገኙ ነው " ብለዋል።
የተግዱት የዩኒቨርሲቲው ሆስፒታል ውስጥ ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አስረድተዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ግንቦት 23 ቀን 2018 ዓ/ም
See less

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።