#ዋ! የዬኔታ ልቅና #ራስ #ዋሸራ! ሆይ! ሆይ!

 

#ዋ! የዬኔታ ልቅና #ራስ #ዋሸራ! ሆይ! ሆይ!
 
"አቤቱ የቤትህ ቅናት በላኝ።"
 
#ምዕራፍ ፲፱።
 
"ዋሸራ (ደብረ ምዕራፍ ዋሸራ ማርያም) በኢትዮጵያ፣ አማራ ክልል ጎንጅ ቆለላ ወረዳ (ምዕራብ ጎጃም) የሚገኝ ታሪካዊና መንፈሳዊ ቦታ ነው። ከአዲስ አበባ 426 ኪሎ ሜትር እና ከባሕር ዳር 82 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ይህ ስፍራ፣ በርካታ ሊቃውንት የተገኙበት የቅኔ መገኛ ማዕከል በመባል ይታወቃል።ቁም ነገሮች፡የቅኔ አምባ፡ ከዋሸራ የወጡ የቅኔ ሊቃውንት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ታላላቅ ገዳማትና አድባራት በማስተማር ቅኔን አስፋፍተዋል።የቅኔ ዩኒቨርሲቲ፡ የቅኔ ጥበብን ለማሳደግ "የቅኔ ዩኒቨርሲቲ" ማዕረግ የተሰጠው ሲሆን፣ ታላላቅ የበዓላት በዓላት ለምሳሌ የአስተርእዮ ማርያም በዓል እጅግ በደማቅ ሁኔታ በቦታው ይከበራል።"
 
#ብሎት መሆኑን አውቃለሁኝ። በዓለም ውስጥ ላለነው፣ ለኢትዮጵያ የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጆች።
ግን እንዲህ ህሊናን የሚያፈርስ ክስተት ሲኖር ቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ጉባኤ ጠርቶ ቤተ - እግዚአብሄራችን ጋሻ፣ ጦሯ፣ ድሮኗ፣ ኒኩለሯ፣ ባሩዷ፣ ትጥቅ እና ስንቋ #ጸሎት ነው። ፆም ነው። ሱባኤ ነው። ስግደት ነው። ምህላ ነው። ልመና ነው። 
 
እግዚአብሄርን የተረገምንበትን ከልቶ ምህረት ይልክ ዘንድ ተንበርክኮ #ድሆ መለመን አያሽላንም። ይህን ማታዊ ዜና እንዲያስታግሰው፣ እንዲያቆረው ለሁሉ ጌታ አማኑኤል በዕንባ መጠየቅ ይገባ ይመስለኛል። አልቦሽነት ነገን፣ ማግሥትን አልቦሽን #ስለሚቀልበው
 
የወል ሱባኤ ጥቅሙ የአንዱ ባይደመጥ ከብዙኃን የእኔ ቢጤ ኃጣን አንድ #ዕዮባዊ አይጠፋም እና የወል ሱባዬ መያዝ የተገባ ይመስለኛል።
እኔ ቅዱሳን፣ ብጹዓን፣ ደናግላን አቨውን #አሻቅቤ እያዘዝኩ አይደለም። እንቅልፍ አጥቼ ያደርኩበትን ውስጤን ገልጬ እዩልኝ እያልኩ ነው። አጥፍቼ ተዳፍሬም ከሆነ ይቅርታ እንደ አባት አደሩ እጠይቃለሁኝ። 
 
ዋሸራ ላይ ጦርነት ካለ ምን ይተርፋል? ማንስ ይተርፋል? ማንንስ ይማራል? ምንስ ይማራል? መራራ ከርቤያዊ ገጠመኝ ነው። የባሩድ "ድል" በሙሽርነት፣ በቅልቅል፣ በግጥግጥ አይገኝም። እርስ በእርስ ተቀጣጥቶ የተገኜው ስኬት "ድል" ከተባለ። 
 
ድልስ እንደምናያቸው አገሮች ፈጣሪ ሰጥቶን የሄደውን የውስጥ ሰላም ማስጠበቅ፣ ለዛም መሳሳት፣ እኩል አድርጎ ያቆመንን አገራዊነትን ማጽናት። እኛነትን መዋጥ። በፍርሰት፣ በመካሰስ፣ በጥሎ ማለፍ የአደራ ውርርስን ማግኜት ሩቅ ስለሆነ። ጦርነት ድል የለውም። 
 
ድል አለኝ ካለ ጦርነት በቀል፣ ቂም፣ አመድ፣ ቀብር እና አካልን ማጣት ነው። ጦርነት የጥላቻ ማምረቻ ካንፓኒ ነው። የትውልድን ተስፋም ዘራፊ። 
 
ለዛውም በሺህ ዓመታት የማይገኝ የአገር የመሠረት ካስማ የሆነን ዋሻራን እንዲህ እንደ አንድ የዕቃ መሸጫ ሞል ማየት። የትውስት #ናፍቆት በራስ #ፍቀት
 
ያ የዊዝደም፣ የልቅና፣ የልዕልና፣ የዕውቀት ማህባ፣ የቤተ- ግዚአብሄር ተፈጥሯዊ ዩንቨርስቲ በእኛ ዘመን እንዲህ ያለ አደጋ ውስጥ ሲሆን የወል ሱባኤ፣ ብሄራዊ የጸሎት፣ ብሄራዊ የተደሞ፣ ብሄራዊ የጥሞና ጊዜ መሪያችን - የመንፈስ አደራጃችን ቅድስት ቤተ- ክርስትያናችን ልታውጅ ይገባል።
 
ባለፈው ጊዜም በደቡብ ጎንደር ራስ ጋይንት ላይ ይህን መሰል ችግር ገጥሞ እንደ አልባሌ ጉዳይ ታልፏል። አጀንዳም አልነበረም በቤተክርስትያን ሚዲያ ላይ።
 
ይህ ልምድ፣ ይህ ድግግሞሽ #እርቃን የሚያስቀር የሁላችን ገመና ነው። እንደዚህ ትውልድ አባልነታችን ኢትዮጵያ የምትባለው አገራችን ቀለም አልባ ብዕር ከሆነች አጥቂ መንፈሶችን፣ ጥቁር መንፈሶችን የመቋቋም መንፈሳዊ ስጦታ፣ ምርቃታዊ ጸጋ ይሰደዳል።
 
የራሺያ ጥንካሬ፣ ብርታት፣ ዝልቀት ሚስጢሩ እራስን አክብሮ በመነሳት የተገኜ ብልህነት ነው። ራሺያኖች የቀደመ ማንነታቸው የብሄራዊ ክብራቸው መለያ ነው። ፋክክር የለም በቀደምት እኛነታቸው ላይ። 
 
እነሱን የጸነሰ፣ የፈጠረ፣ የቀረጸ የትናንት #ዊዝደም ስለመሆኑ ያምናሉ። ቻይና፣ ጃፓንም መሰሉን ይፈጽማሉ። ይሆኑበታል። የእነዚህ ብልህ አገራት የሥልጣኔ ግስጋሴ ትናንትን አቂመው፣ ከዛ ጋር ግብግብ ፈጥረው፣ አሸነፍነው ብለው ፎክረው አይደለም። በፍጹም። ብልህነት ከማየትም መማር ይቻላል። 
 
መሪ ሁን የዓለም ተሸላሚ፣ ሚኒስተር ሁን ማርሻል፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሁን ተደማጭ የቆምክባት መሬት ጸንታ ያገኜሃት በሚስጢራት የፊደል ገበታ ብልህነት ነው። "ሀ" ሳትል መቼም ዶክተር፣ ፕሮፌሰር፣ ወዘተ ከየት ይመጣል? 
 
ተንሳፎ የተፈጠረ የሰው ፍጥረት፣ ተንሳፎ የተገኜ የዓለም ዕውቅና ያለው አገር የለም። እርሾ አለ። መሠረት አለ። ድልድይ አለ። እርሾው፣ ድልድዩ መሠረቱ ለኢትዮጵያ 60 ዓመት ዕድሜ ያለው የትውስቱ የፖለቲካ ድርጅት አይደለም። ምን አለው? ምንስ አትርፎ ይህን ያህል ትምክህት የሚደለቅለት? 
 
የኢትዮጵያ ብቁ ብልህ መሰረት፣ እርሾ፣ አሻራ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እስከ ዩንቨርስ ድረስ የዘለቀ የምርምር ፍልስፍናዋ እና ስኬቷ ነው። አደራጅታ ያሳካች፣ ብፅዕት ናት ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ። እንደ ሸክላ ጭቃ ተቦክታ በእጅ ያልተሰራች ቅዱስ መንፈስ ያላት።
 
የማንነት ቀውስ ሥልጣን ማሳጣት ብቻ ሳይሆን አገር ሊያሳጣን ይችላል። የችግሩ ምንጭ ይህ ነው። ከማንነት ቀውስ ጋር ታርቆ እኛነትን የሰጠን ዝልቅ ሚስጢርን የእኛ ብሎ መቀበል ይገባል። ይህ ተገፍቶ፣ ይህ ተርቆ፣ ይህ ተገሎ አይደለም ነገ ዛሬ ለራሱ እርግጠኛ የሚያደርገው የሃቅ እንክብል አይኖረውም። 
 
ለቱሪዝም ብሄራዊ ከአባይ ማዶ ጀምሮ ንቅናቄ አለ። ይሄ ጥሩ ነው። ለማመጣጠን ከሆነ። ለፋክክር፣ ቀደምቱን አክስሞ ከሆነ ግን ዲል ያለ ኪሳራ ነው። ፖለቲካ ለሰው ነው። 
 
ሰዋዊ ፖለቲካ ለሰው ልጅ የደስታ ማዕከላት፣ የመንፈስ ማረፊያወች እኩል ጥንቃቄ፣ እኩል አጽህኖት፣ እኩል አትኩሮት፣ እኩል ማስተዋል ይጠይቃል። ከእርዕስ አመራረጥ ጀምሮ።
 
" ድል " ዋሸራ ምድር የቅዱሳን ባድማ እየነደደ፣ በዛ የተጠለሉ ንጹኃን፣ የፈጣሪ ፍጡራን አዕዋፋት፣ እንሰሳወች ነቅለው እየተሰደዱ?
አገር የኖረችው፣ አገር ያለችው፣ አገር እምትቀጥለው እኛነታችነን የእኛ ብሎ ከመቀበል ፈቃድ ይመነጫል። ጦርነት ጨካኝ ነው። ጦርነት የምንወደውን ያሳጣል። እያሳጣም ነው።
 
እኔ ደንግጫለሁኝ። ዋ! ዋሻራ ቅዱስ ጴጥሮስ ሰማዕቱ ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ለጠላት አንገቱን የሰጠልሽ ኢትዮጵያ ሆይ! ሆይ! ይህ ዘመን ናፍቆት ይሆን?
 
ቅርስ፣ ውርስ፣ ማዕዶተ - ዊዝደም መንፈሳዊ #ሸቀጥ አይደለም። እንደ ኤሌክትሪክ ገመድ ጭነህ፣ ቀላቅለህ፣ ቀጣጥለህ የምትፈጥረው።
የተሰጣቸው፣ የበቁት - በጸሎት፣ በሱባኤ፣ በአርምሞ፣ በተደሞ ፈጥረው፣ አደራጅተው፣ አጽድቀው፣ ሐዋርያነቱን የገነቡት ቋሚ ህሊና አዛውንቱ የሊሂቃን መፍለቂያ እንዲህ የጦርነት ቀጠና ሲሆን እኛን እኛ ፈቅዶ እና ወዶ እያጠፋው ስለመሆኑ የእኛነት አቅማችን በአልቦሽነት እየነጎደ ስለመሆኑ ያመሳጥራል። 
 
" ድል " እኛነት እየነደደ፣ ወንድማማቾች በባሩድ እየተላለቁ እንዴት ቃሉ ተደፈረ። ውትድርና ሂሳብ ነው። በራስ #መቀነስ "ድል" እንደምን ይታሰባል? ሉዓላዊ ክብራችን እየተቀነሰ ነው። ዝክረ ዋሸራ እራሱ የኢትዮጵያ ራስ ነው። 
 
ቀድሞ ነገር በዚህ በተከበረ ቦታ፣ በዚህ በጸደቀ ቦታ፣ በዚህ ደግሞ በማይገኝ ቦታ እንዴት የሰማሁት ሁሉ ነገር ሊሆን ቻለ?
ብጹዓን ቅዱሳን ደናግላን ገዳማዊ አባቶቻችን ሆይ! ይህን ፈታኝ ሁነት እንዴት ለሚለው ከፈጣሪ ጋር መምከር የሚያስፈልግ ይመስለኛል። የተረከቡትን አደራ የማስረከብ ዕድሉ እያመለጠ ነው።
 
ቤተክርስትያን ከሊቃናት አዛውንት ዩንቨርስቲወቿ ውስጥ አለሁ፣ እየኖርኩ ነው፣ እየመራሁ ነው እንደምን ልትል ትችላለች? መቀነስ ማነስን ማነስ ማጣትን ማጣት ምንምነትን ማምጣቱን አታጣውም እናታችን።
 
#ዋ! ባለቅኔው #ዋሻራ!
 
የውስጥነት ድንግላዊ አሻራ
ለራህብ የሚራራ
ዋ! ራስ አሻራ
ለአንተም ሆነ አጤ ሰላም ተራራ?
 
ዋ! ዋሸራ የቅኔ አባወራ
የእምዬ ኢትዮጵያ ብራ
የብራና ቀለም ያሰበልክ የመንፈስ አዝመራ
እባክህ አዛውንቱ ሰላምን በዊዝደም ምራ!
 
ዋ! ባለ ቅኔው ዋሸራ!
 
የእኛነታችን የትርታ - ጉልላት
የቅኔ ፏፏቴ ዓውደ - ምህረት
የዓራት ዓይናማ ጥንድ ክብረት
የሚስጢራት ቁመናህ ሥናዊነት
የፍልስፍና ህብራዊነት ተደሟዊነት
የጸዳህ የነፃህ በእኛዊነት።
 
ዋ! ዋሸራ ባለ አሻራ!
 
የአገር ባለውለታ በፆዋሚነት
መቅድመ መለከት በመምህርነት
የኔታ! የዝማሬ ቤተ ማህሌት፣
የጥዋቱ የጥንተ - ቋሚ ዜናዊነት
የዕድምታ ልዕለ - ላቂያነት
የሥርዓት - ምስክረ - አንቀፃዊነት
የዶግማ ብጡለ - ህላዊነት
የዊዝደም ሰናይ - ሉዓላዊነት።
 
#ዋ! አባ ዋሸራ።
 
የዛሬ ያይደለህ በዋና በርነት
የትናንት መቋሚያ የትውፊት
የጥሪህ ጽናጽላዊ መሰጠት
የኢትዮጵያ እዮራዊ ልዩ ሽልማት
የእናትህ አንበል፤ ካፒቴን የጽናት
የቀናው ቅኔ መርከብነት
የኖኽ መንበር ነብይነት
የልዕልና ሐዋርያ አብነት።
 
#ዋ! የቅኔ ዋርካው ዋሸራ!
 
የግርማ - የሞገስ - ማህደረ - አውራነት
የሆይ ማደሪያ የፍጹማዊነት፣
የአቡጊዳ፣ የየኋንስ መልዕክትነት
የሥልጣኔ መኃንዲስ መሠረት፥
እንዲህ ሆንክ - ኧሩ እንዴት - እንዴት?
የንጽህናህ ጸጋነት በመክሊት
አናት ስለናት በህማማት፣
ነበር የተሰጠህ የጸጥታ ሕይወት።
የቅድስናህ ምርቃት ገነታዊነት
#አዛውንቱ ዋሻራ፣ የኔታ ዋሸራ! መገናኛ የእኛዊነት
እኮ! ምን እና ምን ተኋሁኑበት?
 
እራስን አርቆ ማየት አይገባም። ሰው ከሁሉ ይበልጣ። ሰው ሰማዕትነትን ተቀብሎ ያነጸው፣ ያበጀው ቅርስ እና ውርስ ያው የሰው ልክ ማንነት አለው።
 
ሊከበር፣ ልዩ ጥበቃ፣ ልዩ ናፍቆት፣ ልዩ ስስት ለእናት አገሩ ላለው የእናቱ የሆነ ሁሉ የእሱ ነው። አፈጣጠሩ በእኛዊነት ውስጥ ያለ አይደለም የዕውቀት ማዕከል ቅንጣቷ የአፈር ጠረን እሱ እራሱ ነው ሰውነቱ።
 
ኃላፊነት የሁሉም ኃላፊነት ነው። አገር አጥተን ስለማናውቅ ላይገባን ይችላል። አገር አልባነት እየናፈቀን ነው። ኢትዮጵያ የከበደችን ለሁላችን ነው የምለውም ለዚህ ነው።
 
እኛነትን የመቀበል ችግር፣ እራስን አግልሎ ከእንደራሴነት ጋር ግብግብ? ለዛውም በባሩድ? ማስተዋልን የሰጠን አምላካችን እንጠቀምበት ዘንድ ይርዳን። አሜን። 
 
ምንም ዓይነት ሁካታ፣ ግርግር፣ ጫጫታ፣ ፋክክር፣ ጉግስ የማይሹ ባድማወች ልዩ ጥንቃቄ ይጠይቃል። አየሩ እራሱ ሰውኛ ስላልሆነ። ሁላችን #ታመናል እና ምህረቱን አማኑኤል ይላክልን። አሜን።
 
ቸር አስበን፣ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፣ ቀና እንሁን።
 
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ኑሩልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
23/07/026.
 
አቤቱ ፈጣሪ ሆይ ምህረትህ ከእኛ #አይሸሽ። አሜን።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።