"#እስረኛ #ይፈታል።" (ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ።)

 

"#እስረኛ #ይፈታል።" (ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ።)
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፈጠርልኝ።" አሜን።
 
በሰሞኑ የፓርላማ ጉባኤ ይህን ተናግረዋል ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ።
ዜናው ጥሩ ነው። 
 
ቀድሞ ነገር ሃሳብ ስለምን ይታሰራል?
 
ተጎድቻለሁኝ፤ ተገልያለሁ ሲል አቤቱታ በብዕሩ፤ በሰላማዊ ሰልፍ፤ በድምጹ ያቀረበ ኃይል ለምን ይታሰራል?
በነፃነት ዙሪያ የተጋ፤ ያስተባበረ፤ ያደራጄ የመራም ሊሆን ይችላል ለምን ይታሰራል?
 
በሌላ በኩል ብልፄውን ደግፎ ያሻውን ቢጽፍ፤ ቢናገር፤ ቢያደራጅ፤ ቢያስተባብር፤ ቢመራም ሃግ የሚለው የሌለ
በአንድ አገር ውስጥ አንዱ በሙሉ ይለፍ የሚንፈራሰስበት፤ ሌላው በካቴና የሚቀጣበት ሃሳብ በማቅረብ ብቻ
ለምን ይህን ያህል የሰፋ የመብት የነፃነት ክፍተት እንደምን ሊፈጠር ይችላል?
 
ለዛውም በህወሃት ዘመን በሙሉ አቅም በብዕሩ የታገለ፤ ያታገለ ሰብዕና እንደምን ይታሰራል?
አሁን ላለው የሥልጣን መንበር የሁሉም የተሳትፎ ጭማቂ አይደለምን?
 
#የእስረኛ ፍቹ ………
 
1) በመላ ኢትዮጵያ በህወሃት ዘመንም በብልፄው ዘመንም ያሉትን ያጠቃልላል ወይ? #የኢህአፓ እስረኞችም ስላሉ።
2) በማይታወቅ #በተሰወረ እስር ቤት ያሉትንስ ይጨምራል ወይ?
 
3) የማይነገርለት፤ አስታዋሽም ያጣው "#የቁም እስረኞችን" እነ አቶ ኦባንግ ሜቶን ይጨምራል ወይ?
(አቶ ኦባንግ ሜቶ ድምጹ ስለጠፋ ሌሎችም እንዲሁ የቁም እስርም ይኖር ይሆን እላለሁኝ በግሌ።
4) ኦነግ ኢትዮጵያ ሲገባ አቀባበሉ በ1300 የአዲስ አበባ የኢትዮጵያኒዝም አቀንቃኞች ከጦላይ
እስር ቤት ከተፈቱት የተወሰኑት ተለይተው እስራቸው የቀጠሉ አሉ እና እነሱን ይመለከታል ወይ?
5) ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ ቤተክርስትያን ጥበቃ ላይ የነበሩትን የቅድስት
ኦርቶዶክስ ልጆች ይመለከታል ወይ?
 
6) አሁንም በቀጠለው የተዋህዶ ልጆች እስር ላይ ብልፄ ምን ሥር- ነቀል አቋም ሊይዝ ይችላል?
ምክንያት የቅድስት ተዋህድ የአደባባይ በዕል በመጣ ቁጥር፤ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ በመጣ
ቁጥር "አሸባሪወች" በማለት በገፍ የሚያስራቸው ዜጎችን ጉዳይ እንዴት ማኔጅ ሊያደርግ አስቧል?
እውነት ለመናገር በቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ጉዳይ ያለው አጠቃላይ ምስል ግብረ መልስ የኢትዮ
መንግሥት ሰርኩላሪዝም ሃይማኖታዊ ነውን? የሚል ጥርጣሬ ያሳድራል። ይህን የውስጥ ጥርጣሬ
የሚፈውስ የተግባር እርምጃ ይጠይቃል። 
 
7) ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ አዲስ አበባ አፓርትመንት ውስጥ እስር ቤት እንዳለ ነግሮን ነበር፤ ያ ቀጥሎ
ከሆነ በዚህ ሁኔታ የታሰሩ ከኖሩ የውሳኔው መንፈስ ይህን ይመለከታል ወይ?
 
ስምንተኛ) ሙዚቃ አዳመጣችሁ በሚል የታሠሩትንስ ይመለከታል ወይ ፍቹ?
9) በዘመነ ህወሃት ብዕረኛ የነበሩ፤ ፈቅደው ከሆነ መብታቸው ነው፤ ግን የመፃፍ መክሊታቸው ላይ
በተጽዕኖ አቁመው ከሆነ፤ ለእነሱስ ፍትኃት ይሰጣል ወይ? ለምሳሌ ጋዜጠኛ ተመስገን ደስአለኝ፤ አቶ ክንፈ
አሰፋ ወዘተ። እነኝህ ወንድሞቻችን ካቴና ሊስት የሉም ግን ተሳትፏቸውን አላይም።
 
10) የአማራ ብልጽግና እራሱ በዘገበው ከ10ሺህ የማያንሱ የጸጥታ ኃይሎች መታሰራቸውን ነነግሮን ነበር።
የታሰሩበትም አፋር በርኃ በድንኳን ውስጥ እንደሆነ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ይዘዋወር ነበር። የእነሱ
ጉዳይ የት እንደ ደረሰ የመረጃ እጥረት አለ። 
 
የሆነው፤ ስለሆነው፤ መሆን ላይ ባለው ሁነት ግልጽ ያለ ማብራሪያ ሊሰጥ ይገባል። የአማራ ክልል ፖለቲካ
እራሱንችሎ ስለማያውቅ መሪው ብልጽግና ከእስረኞችመፈታት ጉዳይ ጋር ይህም እንደ አንድ አጀንዳ ቆጥሮ
ግልጽነት ያለው ዕውነተኛ መረጃ ቢሰጥበት ጥሩ ነው። እኔ እስካሁንም አስባቸዋለሁኝ። በምን ሁኔታ ጉዳዩ
እንደተቋጬ መስማት እሻለሁኝ። ከህወሃት የታደገ አቅም ክብሩ ቀርቶበት መኖሩ ሲንገላታ ማድመጥ ውስጥን
ይጎዳል። መረጃ ያለው ወገንም መረጃውን ቢሰጠን ጥሩ ነው።
 
የአማራ መንፈስን በመጫን፤ በማዋከብ የሚያተርፍ ዘመን ሰጥ ፖለቲካ ሊኖር አይገባም። የአማራ ህዝብም
ኢትዮጵያዊ ነው። በህመሟ ሁሉ እራሱን ሳይሳሳለት፤ ጎጆ ትዳሩን ሞፈር ቀንበሩን ትቶ እሷን አስቀድሞ ሰንቆ
የኖረ ቅን ህዝብ ነው። ምንም እንኳን ሰማዕትነቱ በየዘመኑ ፖለቲካ አመድ አፋሽ ቢሆንም።
 
የህወሃት መንበረ - ሥልጣኑን የማስለቀቅ ህልም ቢያንስ ለመክሊት፤ ለችሎታ፤ ለሙያ፤ ለክህሎት ተፈጥሯዊ
ነፃነቱን ካልሰጠ ድካሙ የውርንጫ ድካም ነበር ማለት ይሆናል። 
 
እርግጥ አሁን ሥልጣን ላይ ያሉት ያን የትግል ዘመን ላይ አብዛኞቹ መዋጮ የዕድሜ፤ የጊዜ፤ የመዋዕለ መንፈስ
ውጭጭ ያላደረጉ ስለሆነ ላያውቁት፤ ህመሙ ላይሰማቸው ይችላል። በውስጡ ለነበሩ ለጸሐፊ ወ/ሮ መስከረም አበራ፤
ለጋዜጠኛ አባይ ዘውዱ፤ ለጸሐፊ አቶ ታዲዮስ ታንቱ ግን ህወሃትን መታገል ማለት ምን ማለት እንደ ነበር ያውቁታል። 
 
ህመሙን፤ ቁስለቱን፤ እንግልቱን፤ የቤተሰብ ሃዘኑን ኑረውበታል። ይህን ሁሉ በጥሞና አስቦ ለይምሰል ሳይሁን
የዕውነት እራስንም ለውጦ፤ እራስንም ወቅሶ የማያዳግም ምላሽ መስጠት ይገባል። ለመፃፍ ይሁን ለመናገር ሙሉ
ነፃነት ለኢትዮጵውያን አይበዛባቸውምና። 
 
በዚህ የኑሮ ውድነት ለእስረኛ ስንቅ ማቀበል ቀርቶ ሄዶ ለማየት ትራንስፖርቱ እራሱ ይከብዳል። ጠበቃ ተክለ ሚኬኤል
አበበ ኢትዮጵያ ሲሄድ የፖለቲካ እስረኞችን በአካል ተገኝቶ ይጠይቃል። አስልቶ ስለሚሄድ ይመስለኛል ፍርድ ቤትም
ተገኝቶ ጉዳዩን ይከታተላል። ለሚያደርገው ፍጹም ቅናዊ ደግነት አመሰግነዋለሁኝ።
 
እሱ እንደነገረን እስረኛ ሊጠይቅ ሲሄድ እንግልት እንዳልገጠመው ስለነገረን ያን ዕውቅና ሰጥቼ ነው የእስረኛ ቤተሰብ
ከኑሮ ውድነቱ ጋር ያለባቸውን ጫና ያነሳሁት። በአስተዳደሩ በኩል የልጅ ተክሌን አወንታዊ ዕይታ ወስጄ ተቀብዬም። የህግ
ባለሙያ ስለሆነ።
 
ነባር የፖለቲካ እስረኞች ከተፈቱ በኋላስ ሌላ የእስር ሳቢያ፤ ትልም ብልፄው ይኖረው ይሆን?
በጣም የገዘፈው ስጋቴ ይህ ነው። 
 
የፖለቲካ እስረኞች በዓለ ቅዱስ የኋንስን ይዞ ከእስር ቢለቀቁልን፤ በመስቀል የአደባባይ በዓል
ሳቢያ ተፈልጎ አዲስ ገብ እስረኛ ታጭቶ ከሆነ የወገራ ሰው ዙሮ ዙሮ ወቅን እንደሚለው ይሆናል።
ወቅን የሚባል ተራራ አለ። ያ ተራራ በየትኛውም አካባቢ ቢኮን ይታያል። ለዛ ነው ተወልጄው ይሁን
ኖሪው የማይሻሻል፤ "አድሮ ጥጃ" የሆነ ጉዳይ ሲገጥመው ይህን ዘይቤ የሚገልጸው። 
 
ብልፄ የሚነሱ ሞጋች ሃሳቦችን የሚመጥን #አቅም መገንባት ያስፈልገዋል። ዓውራ ፓርቲ አይደል?
ሃሳብን ሊፈራ አይገባውም። ዓውራነት መሪነት ነው። መሪነት የሃሳብ ብቃትና ጥረት እጥረት
ሊኖርበት አይገባም። ፍጽምና ባይጠበቅም።
 
እያንዳንዱ ዜጋ መኖሩ እራሱ ስለሚፈትነው ነው ጥያቄ የሚያቀርበው። ጥያቄው በፖለቲካ ተሰልቶ ለእንግልት
የሚዳረገውም መኖርን የመቋቋም አቅሙ ካለው የኑሮ ውድነት፤ የቢሮክራሲ ትብትብነት ካለመላሾ ምንም
መንቀሳቀስ ባለመቻሉ ህዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄወች ውስጥ የነቃው ሊቅ ያን ይዞ መፍትሄ እንዲያገኝ
ገዢውን ብልጽግናን ቢሞግት ምኑ ነው ነውሩ። አንድ ሃኪም ያን ሁሉ ዓመት ተምሮ መኖር ሲፈትነው ፖለቲካ
ሳይሆን አስገዳጁ ራህብና ጥማት ይሆናል። 
 
የቤት ኪራዩ መናር በየለቱ ነው ኪራይ የሚጨመረው፤ የኑሮ ውድነቱ፤ የትራንስፖርቱ ከአቅም በላይ መሆን፤
የጤና ጉድለት እና የመዳህኒት ንረት ወዘተ የሚያመጡት መሰናክሎችን እንዲሻሻሉ፤ አትኩሮት እንዲሰጣቸው፤
ወጥቶ ለመግባት፤ ነግዶ ለማደር #የደህንነት ዋስትና መንግሥትን ቢጠይቅ የተገባ ጥያቄ ነው። ስንቱ የአውሮፕላን
መጓጓዝ ይችላል? አውቶብስ ጉዞ እራሱ መታፈን፤ መታገት ነው። ይህን የሚነሱ ሃሳቦች መኖርን #ለማኖር ሃሳብ ካልተፈቀደለት ድንቡልቡል ህይወት ነው የሚሆነው። መተንፈሻ የሌለው። 
 
ይህ ደግሞ የታመቃል። ውስጡ ለውስጥ ይብላል። ሲበዛ - ይፈነዳል። በፍንዳታው ዳኚ ከንፍሮ ጥሬ
የሚያወጣ አምላክ ካልሆነ አብዛህኛው ይጎዳል። ይህን ሊያድን፤ ይህን ሊፈውስ የሚችለው የሃሳብ ነፃነትን መፍቀድ።
ጥያቄወችን ማድመጥ። ለጥያቄወቹ ዕውቅና መስጠት። የጥያቄወችን ውስጥ አጥንቶ መልስ ሰጭ እርምጃወችን
መውሰድ ነው።
 
ፖለቲካ - ለሰው። ፖለቲካ - ለተፈጥሮ ከሆነ ሰውነትን፤ ሰብአዊነትን ማስቀደም። በጣም ቅብጥ ካሉ ፕሮጀክቶች ይልቅ
የቅደም ተከተል ጉዳይን ቅድሚያ መስጠት ይገባል። አሁን ደብረብርሃን መሰል የተፈናቀሉ ወገኖች ማዕከል ባሊህ
ባይ የላቸውም። የሃይማኖት ተቋማት በቋሚነት በዚህ መሰል ተግባራት እንዲሰማሩ ነፃነት ሊያገኙ ይገባል። የሃይማኖት
ተቋማት መንግሥት ይከፋዋል ብለው እራሳቸውን የሚያቅቡበት ሁነት ሊኖር ይችላል።
 
#ነፃነት ሲኖር አሰባሳቢ ሃሳብ ይፈልቃል። ያ አሰባሳቢ ሃሳብ አገር ጠቀም፤ ህዝብ ጠቀም፤ ትውልድ ጠቀም ለማድረግ
ብልህነት ቢፈቀድለት መኖር ነፃነት ያገኛል። ቁልፋ ጥያቄ የመኖር አኗኗሪ ሁነቶች ነፃነታቸው ሲጠበቅ መኖር ማኖርን
የማኖር አቅም ይፈጥርለታል። 
 
በኢትዮጵያ #የፖለቲካ እስረኞች ሊኖሩ አይገባም። በነፃነት አገር የዜጎች የነፃነት መኖር ካልተፈቀደ
ምኑን ኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዛች አገር ሆነች????
 
ሃሳብ ደግሞ ይጠቅማል። ሃሳብ - ይረዳል። ሃሳብ - ያጽናናል። ሃሳብ - ነዳላን ይደፍናል። ሃሳብ
መንፈስን ይሰበስባል። ሃሳብ ልዩነትን ገርቶ ያቀራርባል። ሃሳብ ከታፈነ ግን ራዕይ #ይጫጫል
ተስፋ #ይጠወልጋል። ምኞት ያራል። መኖር ይሟሽሻል።
 
#ስጋት፤ ፍርሃት፤ ጭንቀት የአቅጣጫ መሃንዲስነታቸው ቢያከትም። እንደ መከወኛ።
ስጋት ፍርሃት፤ ጭንቀት የፖለቲካ ፖሊሲ ሊሆኑ አይገባም። ሞጋች ትውልድን ያሳጣል። በሌላ በኩል
የትውልድን በራስ የመተማመን መንፈስ ይገድላል።
 
ስጋት፤ ፍርሃት፤ ጭንቀት እኮ በሽታ እኮ ነው። ማግለል እንጂ አጭቶ ተጋብቶ መፈጸም እና ማስፈጸም
እራስን በራስ የሚያጠፋ እክል ጉዳይ ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ዜጎች ያገባናል በሚሉት የመኖር
ጥበብ ውስጥ ተሳትፏቸው ሙሉ ነፃነት ሊያገኝ ይገባል። 
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
13/06/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።