• #ብሄዊ የምህረት ዓዋጅ አስፈላጊነት እና፤ ለአፈፃጸሙ አክብሮትን ስለመመገብ።
#ብሄዊ የምህረት ዓዋጅ አስፈላጊነት እና፤ ለአፈፃጸሙ አክብሮትን ስለመመገብ።
የምህረት ዓዋጁ ዱርቤቴ ላሉት ብቻ አይደለም፤ ተንሳፎ ላለው የብልጽግና አካላቱ ጭምር ነው። በሌላ በኩል በፋኖ ምክንያት የታሠሩ የአማራ ልጆች የምህረቱ ማዕከላዊ እንብርት ሊሆን ይገባል። የአማራ ሊቃናት ወላጆች፤ ልጆች፤ ጉልቻወች፤ እጮኛወች፤ ሙያወች፤ ተመክሮወች ተሰቃይተዋል። ይህ ስቃይ በብሄራዊ ሃቀኛ ምህረት እልባት ሊያገኝ ይገባል።
አፋር በርሃ ላይ ታሥረው ስለነበሩት የአማራ የጸጥታ አካላትን ሁሉ ምህረቱ ሊያካታቸው ይገባል። በአማራ ክልል በባህርዳር፤ በዞን እና በወረዳ ያሉ ሺህ የአማራ እስረኞች በምህረት ከካቴና ጋር እንዲፋቱ ሊደረግ ይገባል። ዊዝደም ማለት ለመሪነት ብልህነትን መመገብ ማለትም ነው። ብልህነት ብልጠት አይደለም። ጥበብ እንጂ። ክህሎት እንጂ።
የአማራ እና ወህ ልትል ይገባል። እኔም እረፍት እፈልጋለሁኝ። በጣም ውስብስብ፤ የተፍተለተለ ችግር ውስጥ ነው ክልሉ ያለው። እንደ አገር ኢትዮጵያም የአማራን ህዝብ ቅንነት፤ ገራገርነት ልታጣ አይገባትም። አክብሮ መነሳት፤ ጠንክሮ በማስተዋል መትጋት፤ በብልህነት መከራውን እያዬ ያለውን ህዝብ አለሁልህ ማለት ይገባል። በጥልቀት እንሰበው። በሰፊነትም እንመርምረው። የፋኖ ውስጥነትን በአትኩሮት በፖለቲካ ልቅና ማስተዳደር ይገባል። የህዝባችን ውስጡ፤ ቃናው ምን ምን እንደሚል በእርጋታ፤ በተከታታይ አንዳንዱንም እየደገምኩኝ አዳምጨዋለሁኝ።
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
ምዕራፍ ፲፯። በዚህ ዘለግ ባለ የወግ ገበታዬ ምዕራፍ ፲፯ ይጠናቀቃል። ከጥቂት የጥሞና ቀናት በኋላ ምዕራፍ ፲፰ ይመጣል።
#መኽራዊ አትኩሮት።
ጤና ይስጥልኝ ማህበረ - ቅንነት፦ እንዴት አደራችሁ? እንደምንስ - አረፈዳችሁ። እኔ አምላኬ ክብሩ ይስፋ ደህና ነኝ። በክሪስማስ ሰሞናት ለእኔ አሸወይና ነበር። የመጸሐፍቶቼን ስክሪፕት እማርምበት። በዚህ ሰሞን ነፍስ በምድር ላይ ሥራውን ያቆመ ያህል ጸጥ ስለሚል በርካታ ያላጠናቀቅኳቸውን የአዕምሮ ተግባራት የምከውንበት የመኽር ወቅቴ ነው። በዚህ ዓመት ደግሞ በተለያዩ ሚዲያወች የወጡ የአማራ ህዝብ ድምጾችን ለማድመጥ ፈቀድሁኝ። ዜናወችንም ውይይቶችንም በእኔነት ሙሉ ስሜት ተከታተልኩ። እኔ የየትኛውም የፖለቲካ ጎራ ቤተኛ ባለመሆኔ ውስጤ ፈቅዶ ሁሉንም የስብሰባ ሂደቶች ስከታተል፤ የህዝባዊ ስብሰባ ዘገባወችን በተረጋጋ የውስጥ ሰላም ነው የተከታተልኩት። ይህ ለአስተዋለ ምዛናዊ ዕይታ አውራ ጎዳናዬ ሆኖ አገልግሎኛል።
#ውስጤ።
ገና ቀንበጥ ሳለሁኝ ሰፊ ዕድል አግኝቼ "ምን ላድርግልሽ?" ስባል ወደ ገበሬዬ መልሱኝ ነበር ያልኩት። እኔ ጎንደር ከተማ ተወልጄ ነው ያደግኩት። ቤተሰቦቼም እንደ እኔው። የከተማ ልጅ ሆኜ ገበሬን እንደ ነፍሴ የመውደዴ ሚስጢር የገበሬው ተፈጥሯዊነት ነበር። ኢትዮጵያ አፈጣጠሯ፤ ሥርዕወ ነገሯ ኦርጋኒክ ነው። ይህን ሌጋሲዋን የሚስቀጥለው የአገሬ ገራገር ገበሬ ብቻ ነው። ስለሆነም ነገረ ገራገር የመኖሬ ዓውራ ክፍል ነው። የአማራ ክልል ስብሰባወችን እንድከታተል ያደረገኝ ገፊ ኃይል ናፍቆቴን ገበሬወችን ስላገኜሁ ነው። የአማራ ገበሬ አይደለም ለሃይማኖቱ፤ አይደለም ለህገ መንግሥት ለበሬው አያ ሆይ! እያለ እያባበለ፤ አክብሮ ነው ተግባሩን የሚከውነው። ያዜምለታልም በተፈጥሮኛ ቃና።
ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ 100 ቀናታቸው ሳይጠናቀቅ ከፃፍኩላቸው ሙግት መሰል የወግ ገበታዬ አንዱ የገበሬው የፖለቲካ ውክልና ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ መንግሥታቸው እያንዳንዱን መንደር ሊጠብቅ ስለማይችል የአማራ ህዝብ ራስዘብን ትውፊታዊ የትጥቅ እና አገር የመጠበቅ ይተባህሉን ጉዳይ እንዳያውኩት፤ ይልቁንም ጥበቃ እንዲያደርጉለት በትህትና አሳስቤያቸው ነበር።
ሁለቱም ከአማራ ገበሬ የትጥቅ እና ተፈጥሯዊ ይተባህል ጋር የተያያዘ ነበር። ያን ጊዜ ጹሁፌን ይከታተሉ ነበር ብዬ አምን ስለነበር ዘለግ አድርጌ ነበር ሃሳቤን ያቀረብኩት። በዛን ወቅት በተከታታይ እንደ እኔ የፃፈ ሰው አላስታውስም።
የሆነ ሆኖ ለእኔ ነገረ ገበሬ ከድምጹ፤ ከአኗኗሩ ዘይቤ፤ ከቅንነቱ፤ ከፈርኃ እግዚአብሄር እና ፈርኃ አላህነቱ፤ ለሰው ልጅ እና ለተፈጥሮ ከሚሰጠው ትሁት ደግነት፤ ንጹህ አክብሮቱ፤ ከተፈጥሮ ጋር ካለው የመግባባት ውህድ ማንነቱ ጋር የሚመስጠኝ ህዝብ ቢኖር ገበሬው ነው። ገበሬውን በሚመለከት አደራጁ ሁኜ አብሬው ህይወቱን ስለኖርኩኝ መፈጠር እንደ ገበሬ መጽደቅ ነው ብዬ አምናለሁኝ።
ይህ የማርክሲስት ሌኒኒስት ርዕዮት ብስጭት እና ገበሬ መንደሮች ለዚህ ዓላማ መዋላቸው በብዙ ሁኔታ የአማራን ገበሬ ፈተና ውስጥ ያስገባ የመከራ፤ የሰቆቃ፤ የጭንቅ ህይወት ይኖረው ዘንድ የተገደደበት ህይወት እንደተፈጠረበት አስባለሁኝ። ውስጤ ሁልጊዜም፤ ለምንጊዜም ለዚህ ንጹህ ማህበረሰብ ይጨነቃል።
#የአማራ ክልል ውይይቶች።
ያው ልደት ሲደርስ፤ ልደትን አስታኮ ብልጽግና የተለያዩ ስብሰባወችን በአማራ ክልል ያሰናዳል። የልደት ዋዜማም በብሄራዊ ያደርገውና አትኩሮትን ሻሞ ይይዛል። ምክንያታዊ ነው። ለጊዜው ይህን ልተው እና የሰሞናቱ ህዝባዊ ስብሰባ ገበሬወችም ስላሉበት ከውስጤ ሆኜ ተከታትዬዋለሁ። እንደ ጸሐፊ ትንቢተኛው አቤ ጉበኛ አልወለድም፤ ትንሳኤውን አግኝቶ "ባልፈጠር ይሻለኛል" የሚል ቃል አዳመጥኩኝ። የአማራ ገበሬ ምርር ብሎታል። አንገፍግፎታል፤ አንገሽግሾታልም።
በብዙ ሁኔታ የጎጃም ገበሬ ከአርበኛ በላይ ዘለቀ ንቅናቄ እና ብሄራዊ ሁነት ባሻገር የሰላም ቀጠና ነበር። ኤርትራ፤ ትግራይ፤ ጎንደር እና ወሎ ነበሩ ከንጉሳዊ ሥርዓት መውደቅ ጋር ዱር ቤቴ ላለ የዘመኑ ወጣቶች ምሽግ ሆነው አሳራቸውን ያዩት። ጎጃም ምድረ ገነት ነበር። አሁን ደግሞ ስቃይ። እጅግ አሳዛኝ ክስተቶችን አዳመጥኩኝ።
ጯሂት ትንሽዬ ከተማ ናት። የቅቤ ከተማ ናት። የጎንደር ከተማ ነዋሪ የዓመቱን ቅቤ የሚገዛው ቅቤ ጯሂት ነው። ከጯሂት ቆላድባ፤ ከቆላድባ ጎርጎራ፤ ከአዘዞ ቆላድባ መሄድ ጋዳ ሆኗል። ጯሂትን ያነሳሁት ስለማውቀው እንጂ በጎጃም በብዙ ቦታወች፤ በወሎም መሰሉ ህዝብ ጭንቅ ላይ መሆኑን አዳመጥኩኝ። እኔ ወሎ በዚህ ልክ ይሆናል ብዬ አላሰብኩም ነበር።
"#ሁሉም ልጃችን ነው።"
2) ከፋኖ የተመለሱም፤ ከመንግሥት ጋር ያሉትም የጠቀሱት ጉዳይ መንግሥታዊ መዋቅሩም ውስጥ የዱር ቤቴ መንፈስ እንደ አለ፤ አንድ ወጣት ሲገልጽ እንደ ሰማሁት የወረዳውን፤ የዞኑን የመንግሥት ስብሰባ የፋኖ መሪወች ያደምጡት ዘንድ እንደሚደረግ አድምጫለሁኝ። ይሄ ከፖለቲካዊ ዕድምታ አንፃር ከባዱ ሁነት ነው። የገዘፈውም። ስለምን መዋቅራዊ ኃላፊነት እያሉ ይህን መሰል ኃላፊነት ሊወስዱ ፈቀዱ? ምን ጎድሎባቸው? ምንስ አጥተው። ቁጣ - አያስፈልገውም። ቁንጥጫም - አያስፈልገውም። የልብ መሸፈትን መንስኤ አጥንቶ፤ አለስልሶም ከቂም ይሁን ከበቀል የጸዳ ዘላቂ መፍትሄ መስጠት የአመራር ብቃትን ይጠይቃል።
3) በመንግሥት መዋቅሩ እና በፋኖ የመሻት ማዕከል ውስጥ ልጥፍ ሳይሆን ውህድ ድልድይ እንዳለ ፍንጮቹ ይጠቁማሉ።
4) የዱር ቤቴ ጽንሰ ሃሳብ ከተማንም እንዳካተተ የሚያስረዱ ፖለቲካዊ ዕድምታወች አሉ። ዋና ከተሞች #ደሴት ሆነዋል። ደብረማርቆስ፤ ፍኖተሰላም፤ ደብረታቦር፤ ጋይንት፤ ባህርዳር፤ እብናት፤ አዲስ ዘመን፤ ሐይቅ፤ ወልዲያ፤ ደሴ፤ ዳባት፤ ደባርቅ፤ አጣዬ፤ ጎንደር፤ ደብረብርሃን፤ ሽዋሮቢት፤ አንባጊዮርጊስ ወዘተ ………
……… ፋኖ በጫካ አለ…… መንፈሱ ከተማ ላይም አለ። እትብት ነው። የማንነት አካል ነው ለአማራ ህዝብ። እናት ስንቅ ብትቋጥር፤ አባት ባውንድ ቢሸጉጥ ተፈጥሯዊ ነው። እኔ ጫካ እያለሁኝ። እናቴ መጥታለች። ስትመጣ የለበሰችው ነጠላ ከበላዮዋ አልቆ ነው የደረሰችው። ስታዬኝ ደግም መሬት ላይ ወድቃ ነው የለመነችኝ። ግቢ ብላ። እረፍት ፈጽሞ አላስፈለጋትም። እናት እናት እናት ሁልጊዜ ትጠራ የመኖራችን ሚስጢር ናት እና። ስንቄንም ትልክ ነበር። ታናናሽ እህት እና ወንድሞቼ ስለናፈቁኝ ወደ ጎንደር ቀረብ ስል መጥተው አይተውኛል። ሥጋዊ አስገዳጅ ሁነት ነው። ከዚህ በፋኖ እና በመላ ህዝብ ቤተሰባዊ ሂደት አንፃር ይህን የገዘፈ ቻሌንጅ አቤቱ ብልጽግና በብልህነት ያዬው፤ ይመራው ዘንድ ያስፈልጋል። መብሰልን በመሰጠት ማፋፋት።
ፋኖ በመንግሥት መዋቅርም አለ። በራሱ በብልጽግና አመራር ውስጥም እንደ አለ ተመላሽ የፋኖ መሪወች ሲገልጡ ሰማሁኝ። ከቀጠናቸው ውጪ በሞፈር ዘመት ሂደው ተመላሽ ታጣቂወች እጅ የሚሰጡበት ዓይነተኛ ምክንያትም ይኽው ጉዳይ ነው። መተማመን፤ መታመን አማራ ክልል ውስጥ ስደት ላይ እንዳሉ ምልክቶችን አስተውያለሁኝ። ይህንን ወጥ አድርጎ የተናደ መንፈስን ለማሰባሰብ የቅድሚያ ቅድሚያ በጓዳ ሳይሆን በአደባባዬ በይፋ ብሄራዊ የምህረት ዓውጆ የአማራን ህዝብ የውስጥ መረጋጋጥ አምጦ መውለድ ያስፈልጋል። ቀለም የሌለው እስክርቢቶ አይጽፍም።
5) ካፒቴን ፻አለቃ ማስረሻ ሰጤ ሰርተናል፤ አሳክተናል ካላቸው ወሳኙ "የኃይል መዛባት ፈጥረናል ነው።" እእ። የሃይል መዛባት የተፈጠረ ነገር የለም። የፋኖ መሠረቱ ህዝባዊ ነው። ህዝባዊ ስለሆነ ማዕከላዊ አመራር ለመፍጠር እስካሁን ያልተቻለው የፋኖ የአፈጣጠር ተፈጥሮ ስለማይፈቅድ ነው። ጽፌበታለሁም አውዲዮ ሠርቸበታለሁኝ።
ከዚህ በኋላ 20/40 ዓመት ቢቆይ ፋኖን ማዕከላዊ አመራር ፈጥሮ ማስተዳደር አይቻልም። ስለሆነም የታጠቀ ኃይል ማዕከላዊ አመራር ከሌለው አደጋው ብዙ ነው። የሰማናቸው መከራወች ሁሉ ከፋኖ የአደረጃጀት አፈጣጠር መርህ ጋር ግጭት ስላለ ነው። የፋኖን ተፈጥሮ ሳያውቁም፤ ሳያድጉበትም የከተማ ልጆች ፋኖን እንምራ ሲሉ ያልቻሉበት መሰረታዊው አመክንዮ ይህ ነው። ከዚህ ስንነሳ የፋኖ አንድ ሁለት ከፍተኛ አመራር በሰላምም፤ ይሁን በምህረት ሲገባ የሚዛባ የኃይል ሚዛን አይኖርም። እራሱን እና ጥቂት ተከታዮቹን ይዞ ነው ሊገባ የሚችለው። ይህ የሚሠራው እንደ ህወሃት ላለ ድርጅት መዋቅራዊ ሰንሰለቱ ከላይ ወደ ታች የተዘረጋ ስለሚሆን።
መሠረቱ ከመሠረቱ ነው ነገረ ፋኖ። መሠረቱ ላይ ነው የፋኖ ህልውና በቅሎ የሚያሰብለው። መሬት ላይ በቀበሌ ገበሬ መንደር ላይ ነው ያለው ፋኖ። በሌላ በኩል የፋኖ አደረጃጀት የጎበዝ አለቃ ለመምረጥ እንኳን ማን ቢወልድ ማን አለበት? ለቋራው የፋኖ መሪ የወለው ዋርካው ምሬ ወዳጆ ሊመራው ቀርቶ ሊያስበው የማይችለው ነው፤ ሌላው ቀርቶ የወገራው ሻለቃ መሳፍንት የጎንደር ዙሪያውን ፋኖ ሊመራ አይችልም። እንኳንስ በክልል ደረጃ ማዕከላዊ አመራር፤ ቁጥጥር ሊፈጥር ቀርቶ። ሌላው ብዙ ጊዜ እምሰማው ማኒፌስቶ፤ ዕቅድ እና ስትራቴጂ ነው፤ የኢኮኖሚ፤ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ወዘተን በሚመለከት፥ ይህ የሚያስፈልገው ለላዕላይ መዋቅሩ የህሊና እርካታ ብቻ ነው። ለፋኖ አደረጃጀት ፖሊሲ፤ ማኒፌስቶ ከባድ ነው። ተፈጥሮው በጭራሽ አይፈቅድም።
በሌላ በኩል ፋንኖ በትግል መቆየትም አይቻልም። ፋኖ ለደራሽ ችግር ደራሽ መፍትሄ ሰጪ እንጂ ለረጅም ተጋድሎ የሚሆን የአደረጃጀት ተፈጥሮ የለውም። ገብያ ላይ አይዋልም አይታደርም። ገብያው ሲፈታ ገብያተኛው ወደ ቤቱ ይመለሳል። የፋኖ ተልዕኮም የተመጠነ፤ ቆይታው ለአጭር ጊዜ እና ስኬታማ ነው።
ለረጅም ጊዜ ከሆነ ፋኗዊ ትግል ይከብደዋል። ይህን አልተረዱም ጀማሪ መሪወቹ። አሁን ባለው ውይይት የፋኖ ትግል በተራዘመ ቁጥር የህዝብን ሙሉ መንፈሳዊ፤ ቁሳዊ፤ ሎጅስቲክስ እየሳሳ ይሄዳል። ፋኖነን የግንባሩን ከውኖ ተሎ ወደ መደበኛ ህይወት መመለስ ነው ተፈጥሮው። አሁን እኔ ሴት ነኝ። ለሴት አቅም የምችለውን መሸከም የምችለው።
ስለሆነም ፻አለቃ ማስረሻ ሰጤ በገለጸው ልክ ማዕከላዊ የአወቃቀር ሁነት ከሌለ የሚዛባ የኃይል ሚዛን አይኖርም። ያ ቢሆን ኖሮ መሪው ሲገባ ከጫፍ እስከ ጫፍ ሆ! ብሎ ተንዶ ይገባ ነበር። ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ የራሱን ድርጅት ከአንገት ላይ ይሁን ቁርጭምጭሚት ላይ ወለምታ ሊፈጥር ይችላል። ከዛ በተረፈ ግን ካፒቴኑ ባሰበው ልክ የሚፈጠር ፊኖሚናል ሁነት አይኖርም። ይልቅ ብልጽግና ብሄራዊ የምህረት ዓዋጅ ይወጅ እና ነዋሪውንም፤ የራሱን አካላት ከስጋት ከጥርጣሬ ያድን።
#በዚህ ውስጥ።
በዚህ ውስጥ የአማራ ክልል ህዝብ ተሰቃዬ። የተሰቃየው በግራ ቀኙ በኩል ነው። በመንግሥት በኩል ይሁን በፋኖ በኩል "የመንታ እናት ተንጋላ ሞተች" እንደሚባለው ነው የአማራ ህዝብ የሆነው። ይህን ለመፍታት ብሄራዊ የምህረት ዓዋጅ በእጅጉ ያስፈልጋል። በጣም ሰፊነት ብልሃዊ ጉዞንም ይጠይቃል። እራስን የመግለጥ መድረክ ማመቻቸትም ይጠቅማል።
በዘመነ ኢህአፓ እኔ ተማሪ ነበርኩኝ። ከንቲባ ጽህፈት ቤት ጠራ። ፋሲል ግንብ ተሰበሰብን። ከዛ የማጋለጥ ዘመቻ ተካሄደ። ሰው ሹልክ ሹልክ እያለ ተመመ። እኔ እናቴ ትወጣ ይሆን ስል፤ እናቴ ደግሞ እኔን ትወጣ ይሆን ስትል ሁለታችንም ኢህአፓ ስላልነበር እራስ ማጋለጡ ሳይሳካ ቀር። ቲኒወች ሁሉ ነበሩ። ትምህርት ቤት ስንሄድ ታፍሰን እንታሰራለን። በእንብርክክ እንቀጣለን።
ምግብ በቀን አንድ ገረማሪያም ጎኔ፤ ውሃ የጎሼ በመኪና መጥቶ ይሰጠናል። ተሰቃይተን ነበር። እራስን ከማጋለጥ በኋላ ግን ከኢህአፓ ነፃ የሆነውም ይሁን ኢህአፓ የነበሩት ሁሉ እፎይ አልን። ትምህርት ላቋረጡም የተለዬ ፕሮግራም ተሠራላቸው። አሁን ኢህአፓወች በየክልሉ ቢሮ አለን ሲሉ ሰማሁኝ። ለጎንደሮች የከፈልነው መስዋዕትነት በቂ ስለሆነ ህዝቡን ባያስቸግሩት ደስ ይለኛል። ያን ሁሉ ዶፍ የተሸከምን ያለ ቅንጣቢ ምስጋና የተሸከምን እኛ ነበር። መላ ጎንደር። የአማራ ክልል ህዝብ አሁናዊ ችግር ሳየው የዛን ጊዜው ሂደት ትዝ አለኝ። ይህን ችግር ከውስጡ ለማዳን ከበቀል የጸዳ ብልህነት ይጠይቃል።
#አቅሎ ማየት እና ጢሱ።
በአለፈው የፓርላማ ውሏቸው ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ "ሁለት ሦስት ሽፍታ" ሲሉ አዳምጫለሁኝ። ይህን ያሉበት ምክንያት እኔ ሳስበው
1) ለዲፕሎማሲው ማህበረሰብ የፋኖ አቅመቢስነትን ለማመላከት።
2) ፋኖ ዓለም ዓቀፍ ዕውቅናውን እንዳይፋፋ።
3) ፋኖን ተስፋ የሚያደርጉ ከኖሩ ተስፋ ለማስቆረጥ አስበውበት ነው የተናገሩት።
ለነገሩ አማራዊ ጉዳዮችን አቅሎ ማየት ዶር አብይ አህመድ ያዘወትራሉ። አይጠቅምም። አንድ የተቀባ የአማራ ልጅ የመፍትሄ ጎዳና ሊሆን ይችላል። እግዚአብሄር ያውቀዋል የአብይዝም ወደ ሥልጣን መምጣት ሁነት። የሆነ ሆኖ እሳቸው እንዳሉት ጉዳዩ "የሁለት ሦስት ሽፍታ" አይደለም። የተሳሳተ ብያኔ ነው። ማን? ምን? እንደሆነ የሚታወቅ ነገር የለም። ነጭ ጤፍ፤ ሰርገኛ፤ ቀይ ጤፍ ብሎ መለየት አይቻልም። መዋቅሩ የብልጽግናም እንዲሁ ዋልሎ ነው ያለው።
ለመሆኑ የአማራ ክልል ብልጽግና የማን ነው??? ይህ እራሱ ምህረት ያስፈልገዋል። የአማራ ክልል መንግሥታዊ መዋቅር ይሁን የአማራ ክልል የብልጽግና መዋቅራዊ ሰንሰለቶች የምህረት ዓዋጁ እንደሚመለከተው ማሰቡ ይጠቅማል። ቂም አያስፈልግም። በቀልም አያስፈልግም። እያንዳንዱ ቢያንስ አምስት ቤተሰብ ያስተዳድራል። ስለዚህ ቤተሰባዊ አዲስ ቀውስ ማምረት አያስፈልግም። ያለው ቀውስ በቂ ነው።
አንድ በሙሉ ዕድሜ ያሉ የፍኖተሰላም ተሰብሳቤ "የራቀ ቤተሰብ ከተባለ የአክስት እና የአጎት ልጅ ነው፥ … እንጂ ልጁ፤ ወንድሞ ፋኖ ዱር ቤቴ ያላለ የለም። ሲጀመርማ እኛም ይሁንታ ሰጥተንበታል" ሲሉ አዳሜጫለሁኝ። ፋኖ ተልዕኮው ለአጭር ጊዜ ብቻ ስለሆነ ይሆናል አጀማመሩ ላዬ ፈቅደን ነበር የሚሉት። ፋኖ ተሎ ተልዕኮውን ያሳካል በሚል ሊሆን ይችላል፤ ድምጸቱ በመቅድመ ውሳኔው የብዝኃን ውሳኔ ዝንባሌ እንደነበር ያዳመጥኩት። ያን ጊዜ በቀናት ውስጥ የ፬ ኪሎ ዓዋጅ አድምጠንም ነበር።
በሌላ አደረጃጀት ቢሆን አንድ ዱርቤቴ ያለ የከፋኝ ኃይል የተረዘመ ተጋድሎን መቋቋም ይቻላል። በፋኖ ግን ተፈጥሮው አይፈቅድም። ትልቁ አደጋው ደግሞ ማዕከላዊ አመራር ለመፍጠር ስለማይቻልም ከቁጥጥር ውጭ ይሆናል። የታጠቀን ኃይል ማዕከላዊ አመራር ካላገኛ ከህግ ውጪ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው። ከዚህ ከሰማነውም የሃዘን መከራም በባሰ። አንድ ነገር ከተፈጠረበት ውጪ ከሆነ ኃላፊነቱን እና ተጠያቂነቱን መሸከም አይችልም። የፋኖ አደረጃጀት ከአንድ መንደር በላይ ሊወጣ አይችልም። ቢበዛ ወረዳ እንጂ ተፈጥሮው ለማዕከላዊ አመራር ይከብዳል።
#የብልጽግና መዋቅር።
ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ነው የሚባለው። አካል የለውም። መነሻ መሠረትም የለውም። የአደረጃጀት መርህም አይገዛውም። በዚህ ውስጥ ህዝብን ለመምራት አይቻልም። የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና ሲሰጠው ለብልጽግና እኔ ሞግቼ ነበር። የህዝብ ጉዳት ታይቶኝ፤ ስለ ሠራሁበትም ነው። ካለ ዲስፕሊን የፓርቲ መዋቅርን መምራት አይቻልም። ተንሳፎ ያለ ጉድ ነው። ብልጽግና የፖለቲካ ፓርቲ የአደረጃጀት መርሆችን ተከትሎ አልተደራጀም። ደንብ፤ ፕሮግራም፤ መሪ ዕቅድ፤ ጉባኤ፤ ማዕከላዊ ኮሜቴ፤ ፖሊት ቢሮ አልነበረውም። የራሱ የመለመላቸውም እጩ እና ሙሉ አባላት አልነበሩትም።
ያዬሁት ጨለማ እና ጢሱ ነው። አባላቱ፤ አካላቱ ውርሰ ህወሃት ነው። በውራጅ መንፈስ አገርን መምራት ይከብዳል። ህውሃትም ቀንቶት ልብ አሸፍቶ ተስፋን መሠነቅ የቻለው የራሱ ልጆች፤ የገዛ የልጅ ልጆቹን በብልጽግና ውስጥ ባለሥልጣን ስለሆኑለት ነው። ሚስጢር የባቄላ ወፍጮ ነው የሆነለት። አደጋው ኢትዮጵያን እንደ አገር ማስቀጠል ላይም ነው። የህወኃትን መንፈስ የተወረጄ መዋቅር ሁልጊዜም ኢትዮጵያ ኢመርጀንሲ ሩም እንድትሆን ያደርጋታል። አድርጓታልም። ህወሃት የሚባል የፖለቲካ ድርጅትን የመሰለ በመከራ ማምረቻ ዓለም አስተናግዳ አታውቅም። ሊድንም የሚችል አይደለም።
የብዙ ቀውሶች ጠንሳሽ የህወሃት መንፈስ ነው። ለዛ ነው አቅም በገፍ እየተዋጣ የሚገኜው። ህወኃት ሲፈጠርም፤ ሲጠናቀቅም ኢትዮጵያ አጀንዳው አይደለችም። ይህን ለማስቀጠል ሙሉ አባላቱን መረከብ ዛሬ ዳገት በዳጥ ሆነ ለብልጽግና። ይህም ሆኖ ሙቀቱ ከኖርማሉ ውጭ ሆኖ ቋያ ስለመፍጠሩ አጀንዳው አይደለም ብልጽግና። አለሁም ይላል አቤቱ ብልጽግና መሪ መንፈሱ ህወሃት በአሻው ልክ አካሉን እየዘወረው።
ጠበቃ ፋኖ አስረስ ማረ 80% አማራ ክልልን እየመራን ነው ሲል የተሳለቁ ነበሩ። ዕውነቱ ግን ዕውነት ነው። አገርን ፕሮፖጋንዳ ይምራት ካልተባለ በስተቀር አቤቱ ብልጽግና አማራ ክልል ላይ መውደቁን አምኖ፤ ድክመቱን - ተቀብሎ፤ የአማራ ህዝብን ይቅርታ ጠይቆ፤ እናም አክብሮ የምህረት ዓዋጅ ዓውጆ አንፃራዊ መረጋጋት ለአማራ ህዝብ ሊፈጥር ይገባል። የብልጽግና የአመራር ጥበብ የተሸበሸበ ስለሆነ ነው ይህን መሰል መከራ የአማራ ህዝብ እየተቀለበ የሚገኘው።
የፖለቲካ ፓርቲ መሪነት በሠርግ መልስ፤ በሠርግ ቅልቅልና ግጥግጥ አይደለም። አንድ የፖለቲካ ድርጅት ቢሮ እያደሩ የሚሠራ በትጋት እና በተከታታይነት የሚከወን ኃላፊነት እንጂ ፍሬም ተሠርቶ ከግድግዳ ላይ የሚለጠፍ ዓርማ አይደለም። ስንፍና፤ ዝለት፤ ንቀት የትም አያደርስም። ኢትዮጵያ እንደ አገር ትቀጥል ዘንድ አቤቱ ብልጽግና ከረባቱን፤ ገበርዲኑን፤ ሴቶችም የፋሽን ትዕይንታቸውን ገትተው ወደ ሥራ ሊገቡ ይገባል። ሁልጊዜ ጉዞ? ሁልጊዜ ሽርሽር እና ግብረሰላም፤ መሸርሸርን እያስተናገዱ መጨረሻው ያላማረ ይሆናል።
ይህ ሁሉ መፈናቀል፤ ይህ ሁሉ የተቋማት ውድመት፤ ይህ ሁሉ ፍርሃት እና ስጋት ለአማራ ህዝብ እንዲጋፈጥ መደረጉ የግፍ ግፍ ነው። ሙሉ ድምጽን ሰጥቶ ለኖቤል ያበቃ ህዝብ ፈንግጠው! የተገባ ፖለቲካዊ አካሄድ አይደለም። የአባላት ብዛት ሳይሆን ጥራት። የፖለቲካ ድርጅት አባልነት የገብያ ውሎ፤ የኢቤንት ሽብሸባ፤ የልብስ ፋሽን ትዕይንት አይደለም።
አንድ የፖለቲካ ድርጅት የቆረጡ፤ ትጉኃን በታማኝነት በድንግል እና በንጽህና ተወደው፤ ተከብረው የህዝብን ኑሮውን እየኖሩ ዝቅ ብለው ሊያገለግሉ የሚችሉ ጠንካራ ሠራተኞች ማዕከል ነው። የአማራ ክልል ብዙ በጣም ጎድሎበታል። የጠቅላይ ሚር ቢሮ አትኩሮት ለአማራ ልጆች ስስ ነው። ዕድሉንም አይሰጥም። አያምናቸውም። መተማመንን ለመፍጠር የሚጨበጥ፤ የሚዳሰስ የዕውነት ማሳ ሊኖር ይገባል።
በጠቅላይ ሚር ጽህፈት ቤት ውስጥ ታማኝነት፤ ተቀባይነት እና ተደማጭነት በሚመለከት ሚዛኑንም የጠበቀ አይደለም። የአማራ ሊቃናትን የማግለል ሁነት አያለሁኝ። ከአማራ ሊቃናት ኢትዮጵያ ልታገኝ የሚገባት ንጥረ ነገር ተገድቧል። በሌላ በኩል የዊዝደም መሠረት ለሆነችው ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ በምንም ደረጃ ላይ ነው። የፖለቲካ ውክልና ላይ ኢትዮጵያ መሬት ላይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ግብር ከፋይ መሆኗ ተሰርዟል። ልሙጥ ነው።
ይህ በራሱ የውስጥ መከፋትን ያባብሳል። በፍጥነት ሊታረምም - ይገባዋል። ሁሉም እኩል መሳቅ አለበት። ለአንዱ ቅርብ ለሌላው ሩቅ የወላጅ ጸጋው አይደለም። መንግሥትን እኔ እንደ ጎረቤት ሳይሆን እንደ ወላጅ ነው እማየው። ግዴታም ያለበት መንግሥት ነው። የዜግነት እርቦ፤ የዜግነት ሢሶ ስለሌለ። አህጉር ላይ ይሁን ግሎባላዊ ተቋማት ላይም አማራነት እና ኦርቶዶክስ ተዋህዶነት ልሙጥ ነው። ይህን ጉልላታዊ ጉዳይ አቤቱ ብልጽግና በማስተዋል፤ በብልህነት ሊመረምረው ይገባል። ታዛቢወች ስላለን። ፍትህ ለዕውነት እንላለን።
#አባ ገዳወች።
ሰሞኑን የአማራ ክልል መንግሥት ስብሰባ ላይ ነው። አባ ገዳወች፤ የአገር ሽማግሌወች ተገኝተዋል።" #ጣና ኬኛ" ይሳካ ዘንድ ብዙ ደክመንበታል። ለአማራ ህዝብ ግን መከራ የታጨበት ነው። እና ያ መንፈስ ተመልሶ የሚገኝ አይደለም። ያተረፈው ስሌለ። ምነው በኦሮምያ ክልል ያለውን የአማራን መፈናቀል፤ ወላጅ አልባ ልጆች መበራከት፤ ተሳቆ መኖር፤ #መስቃ መከራ #ተው ለምን አይሉም አባ ገዳወች። አላየነም አልሰማንም። ተጋሩን ያዳኑ እነሱው ናቸው። ይህ ያስመሰግናል።
ለአማራስ ነው ጥያቄው። ይህ ደግሞ ዕውነታዊ ጥያቄ ነው። በብዙ ሁነቶች ነገረ አማራ አይደለም ለስትራቴጂ ወዳጅነት ለታክቲኩም አይፈቀዱም። ለትውልድ ትክከለኛ መንገድ አይደለም። ጠቅላይ ሚር አብይን ለሥልጣን ያበቃ የአማራ ህዝብ ነው። በክብርም አልቆ ወዶ እና አክብሮ በፍጹም ታማኝነት የተቀበለ። አማራ ውለታ ለፈጸመ ግን አባ ገዳወች፤ የኦሮሞ የፖለቲካ ሊቃናት በአማራ ችግር ዙሪያ አጀንዳቸው ሆኖ አያውቅም። የአማራ ህዝብ ድምጽ እንደ አልባሌ ማበሻ ጨርቅ ነው የተወረወረው። ዕድልን ሰክኖ የማስተዳደር አቅም ሊኖር ይገባ ነበር።
አሁን አባ ገዳወች ባህርዳር ሲገኙ የክልሉ መንግሥት ካባ በቦንዳ ስለሚያከፋፍል የዛ በረከት ይድረሰን ካልሆነ በስተቀር የሚያሳኩት ቀንጣ ጉዳይ አይኖርም። ከቅርባቸው ያለውን የአማራ ህዝብ ሰቀቀን፤ የተዋህዶ ልጆችን የፍርሃት ቆፈን እና ቀንበር፥ ሰማዕትነት እንዲወገድ ማስደረግ ይገባቸዋል። በኦሮምያ ክልል ሙሉ የፖለቲካ ውክልና እንዲያገኙ ሊሰሩበት ይገባል።
ኦሮምያ ላይ የአማራ ህዝብ ግዴታ እንጂ መብት የለውም። መምረጥ እንጂ መመረጥ አይችልም። ይሄ ጨምተን በዝምታ ውስጥ የምንገኜው ሰላማዊ ታጋዮችን ውስጣችን ያቆስለዋል። ፌድራሊዝም ያለው የአማራ ክልል ብቻ ነው። ይህ ለብልጽግና ግንጥል ጌጥ ነው። ወጥ አመራር አለኝ ካለ ሙሉ ስምንት ዓመት ሊፈጅበት አይገባም ነበር።
በሌላ በኩል የአማራ ልጅ አዲስ አበባ እንዳይገባ ሲታገድ ማስቆም ይችሉ ነበር አባ ገዳወች። ትውፊታዊ ሥልጣንም፤ ተደማጭነትም አላቸው። የተከበሩ የአባ ገዳ ትውፊት አስቀጣይ ሽማግሌወች ኦሮምያ ጉባኤ ላይ ይገኙ እና ከመሸም ቢሆን ይሞክሩት። ይምከሩ ልጆቻቸውን። ወግ አይቀርም በኦሮምያ ጉባኤም የአማራ የአገር ሽማግሌወች እንዲገኙ ሊደረግ ይችል ይሆናል። የችግሩ መፍቻ ቁልፍ ይህ መሥመር በፍጹም አይደለም።
የፋይናንስ፤ የጊዜ ብክነትም ነው። በእጅ ያለ ዕድልን መፈጸም አለመቻል ነው እኔ እምታዘበው። ኢትዮጵያን ፕሮፖጋንዳ አላበጃትም። ዊዝደም እንጂ። ኢትዮጵያን ፕሮፖጋንዳ አልሠራትም፤ አያስጠጥላትም። ዊዝደም እንጂ። ሙሉ ስምንት ዓመት የአማራ ህዝብን ቀንበር አስቀርቶ በሙሉ አቅሙ በነፃነት የበኩሉን ይወጣ ዘንድ የጠቅላይ ሚር አብይ መንግሥት ህሊናዊ ጉዳይ ሊሆን ይገባል። የኢትዮጵያ ጂኦፖለቲካል ግብግቦችን ለማስከን በመዳፍ ያለን ጉልህ ችግር በቅድሚያ የመፍታት ክህሎትን ይጠይቃል።
ለረጅም ጊዜ እማውቃቸው ፓን አፍሪካኒስት አሉ። ለእኛም ለአውሮፓውያኑ በዓለት እንኳን አደረሰወት እላቸዋለሁኝ። ዘንድሮ የአባይ ግድብ እና ቅዱስ የኋንስን አያይዤ እንኳን አደረሰወት አልኳቸው። በጣም ነው የተበሳጩብኝ። ህዝባችን የመንቀሳቀስ መብቱ፤ የመኖር ዋስትናው ይረጋገጥ። ለደስታው ይደረሳል ነበር ያሉኝ። የየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባል አይደሉም። የሊቃናት መከፋት፤ መበሳጨትን ለማስታገስ የቻለ አቅም መፍጠር የግድ ይመስለኛል። እሳቸው አይወዱትም በዞግ መጠራትን የኦሮሞ ቋንቋ ተናጋሪ ናቸው። ጠቅላይ ሚር አብይ ወደ ስልጣን ሲመጡ የደገፋ ናቸው።
የሆኖ ሆኖ በዝልኝ ሳይሆን፤ በግርድፍም ሳይሆን የአማራን አብዛኛው ህዝብ ምን አስከፋው የሚል ጥልቅ ጥናት ይጠይቃል። ግድፈትን አውቆ እና ተቀብሎም፤ ለእርምትም ፈቃደኝነት ይጠይቃል። በእጅ ያለ ነገር ነው።
ጨዋታን ጨዋታ እያነሳው እንደ አደባባይ ሚዲያ ዘገባ ከቅድስት ኦርቶዶክ ተዋህዶ የጸዱ ቀበሌወች አርሲ ውስጥ መፈጠሩን ሰምቻለሁ። ልሙጥነት እንደ ነገሰ። ሰቆቃውም - ቀጥሏል። ያን ለማስታገስ ለምን አልጣሩም አባ ገዳወች ሆኑ የአገር ሽማግሌወች ባህርዳር ከመጓጓዝ ይልቅ። ወጪውም ቀላል ነው።
#አክብሮት። ሰላም - በግልምጫ? ሰላም - በእርግጫ አይገኝም። ሰላም በፍጥጫ አይገኝም።
በአንድ በኩል ኑ! ግቡ። በራችን ክፍት ነው። በዛው መድረክ "ሽፍታ፥ ጃዊሳ፥ ዘራፊ፥ ጽንፈኛ፥ ወሮበላ፤ ቀማኛ" ይህ አያቀራርብም። በተለይ #የሠራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖች አካላት አገላለጽ - ይቆጠቁጣል። ግሳፄም ነው። ይህ የተገባ አይደለም። በፋኖ በኩልም ለሰላማዊ ሁነት "ከእብድ ጋር አንደራደርም፤ መደራደር ከፖለቲካ ዘርፍ ተቆጥሮ፤ አንድ ሃሙስ የቀረው" ይህም ትክክለኛ መንገድ አይደለም። የአማራን ጉዳይ እንመራለን የሚሉ ሁሉ በጥራት ጥያቄወችን ሰንዶ ለድርድር ተፈቃቅዶ መጀመር ይገባል። ህዝብ ተሰቃይቷል። ያላየው የመከራ ዓይነት የለም። የአማራ ህዝብ ደመ ከልብ ሆኗል። ከጎንደር ቆላድባ? ከደብረታቦር እስቴ? አይቻልም። አልተቻለም።
ትርፍ ነገር ለምን? ፋኖ የሚቃለል ኃይል አይደለም። እእ። ብልጽግናም ዓለም ዓቀፍ ዕውቅና ያለው መንግሥት ነው። እሱንም ማቃለል፤ ማጣጣል የተገባ አይደለም። የአማራ ህዝብም የተከበረ ሰው አክባሪ ህዝብ ነው። የትኛውም የጸጥታ አካል የአማራ እናት እና አባት የወለዷቸው ናቸው። ቢያንስ የአማራ ወላጆችን ማክበር ለምን አቃተ????
1) አሁን ለአማራ ህዝብ ቅርቡ ማነው?
2) ማን አለልኝ ይበል?
3) ማን አይዞህ ይበለው?
5) ማን ያጽናናው? የአማራ ህዝብ መሽቶ እስኪነጋ እርግጠኛ የሚያደርግ የሰላም ዋስትና የለውም? መሪነት እኮ ይህን ማስቻል ነው። መሪነት እንኳንስ የሚቻለውን የማይቻለውን ማሥቻል ነው መሪነት።
#ሁለቱ የግንባር ሥጋ ወጣቶች እና ነገረ መምህርት የሺ። በዚህ አጋጣሚ መምህርቷን የሰማዕቱን መምህር ደረጀን ባለቤት እግዚአብሄር ያጽናወት ልላቸው እፈልጋለሁኝ።
1) አንድ ፋኖ ፍኖተ ሰላም ላይ፤
2) ሌላ የሠራዊቱ አባል የነበረ ፋኖ ዱር ቤቴ ላይ የሰጡት አስተያዬትን ተከትሎ አጥቂው የማይታወቅ ይሆናል። በግልጽነት፤ በቀጥተኝነት የተናገሩ ወጣቶች ስለሆነ በማንኛውም ጊዜ አደጋ ሊደርስባቸው ስለሚችል ወደ ማዕከላዊ መንግሥት ቢወሰዱ መልካም ነው። የግንባር ሥጋነት ብዙ ይጎዳል።
3) የመምህር ደረጄ ባለቤት መምህርት ወይዘሮ የሺም መራዊ ላይ ለልጆቻቸው ይኖሩላቸው ዘንድ የእሳቸው ህይወትም ልዩ ጥበቃ የሚሻው ሆኖ አግኝቸዋለሁኝ። ልጆች አባታቸውን አጥተው እናታቸውን ሊያጡ ስለማይገባ። ይህን መሰል ጉዳይም በአጀንዳ ተይዞ ተከታታይ ተግባር ሊፈጸምበት ይገባል። ጥግ ለሌላቸው ወገኖች ጥግ የመሆን።
4) የአማራ ህዝብ ትራውማ ውስጥ ነው። ልጆች ስጋት ላይ ናቸው። እናቶች ከልጆች በላይ ዘመኑን ፈርተውታል። ይህን የሚያስታግስ አጽናኝ ድምጽ ለአማራ ህዝብ በእጅጉ ያስፈልገዋል።
በሌላ በኩል አስተያዬት የሰጡ ወገኖችን በመንግሥት መዋቅር ባሉ ይሁን በፋኖ አመራሮች ተጨማሪ ጥቃት እንዳይኖር ግራ ቀኙ እንደዬአደረጃጀታቸው ይርጋ ሊሰጡበት ይገባል። በቃው! የአማራ ህዝብ። ነፃ ሆኖ ተፈጥሮ ነፃነቱ አደጋ ውስጥ ነው ያለውና። ህመሙ፤ ሰቆቃው የእኔም ነው ሊል ይገባል የብልጽግና ካቢኔ።
#የአማራ ህዝብ ሥነ - ልቦና በራስ መተማመኑ የተፈተነበት ዘመን።
የአማራ ህዝብ በራስ የመተማመን ተፈጥሯዊ አቅሙ የተመጣጠነ ነው። ከፍም ዝቅም ሳይል በልኩ - ለልኩ። አሁን ግን ጭንቅ ላይ ነው። ፍኖተ ሰላም ላይ ወንበሩ ቢውጣቸው የወደዱ ሰወች አይቻለሁኝ። በቢዲዮ እንዳይቀረፁ ከወንበር ሥር ሲደበቁ ነበር።
የተሳታፊወችን ሙሉ አትኩሮት እና የስሜታቸውን ሁነት ተከታትዬዋለሁኝ። ግብረ መልሱ ደፈር ያለ አስተያዬት ሲሰጥ የሚደነግጡ፤ በትዝብት - የሚዩ፤ በጋቢያቸው እራሳቸውን - የጋረዱ፤ ያዘኑ፤ በተናጋሪወችም የተበሳጩ፤ የፈዘዙ ታዳያሚወችን ወዘተ አይቻለሁኝ። ድባቡ ፈዛዛ ሆኖ ነው ያዬሁት። ጨፌው፤ የአገር አለባበሱ፤ አቀባበሉ እና አሸኛኜቱ ልብ ለልብ ሆኖ አላገኜሁትም።
ወደ ተነሳሁበት በኽረ ጉዳይ ስመለስ የአማራ ህዝብ የውስጥ መከፋት ጥልቅ ነው። ይህ ነው ውስጤን ያሳዘነው። የአማራ ህዝብ በራስ የመተማመን ሙሉ አቅም የነበረው ህዝብ ነው። የአማራ ህዝብ ጸጋ በራስ የመተማመን አቅሙ እና ክህሎቱ ፈተና ላይ መሆኑን አይቻለሁኝ። መራራ ጎምዛዛ ነው።
የስብሰባ ተሳታፊወች አስተያያት ሲሰጡ "ሁለ ነገሬን አጥቻለሁ፤ የፈለገ ያድርጉኝ" የሚሉም ጉልህ ድምፆችንም አዳምጫለሁኝ። ከሁሉ የሚከፋው ስልጣን ላይ ያሉ ***ጫካወች የበቀል እርምጃ እንዳይወስዱባቸው በእጅጉ አሳስቦኛል። እኔ ይህን ሰምቶ መጀመሪያ ይህን መሰል የትጥቅ ትግል ያስወሰነው፤ የመጀመሪያ ተኩስ ያስከፈተ ሰብዕና አክተሩ አለና በምን ሁነት ህይወቱ እንደምትቀጥል አላውቅም። እንደምንም መመገብ እንደሚችል። ለአማራ ህዝብ ቅንጣት አድርጎ የማያውቅ የግማድ መከራ አሸካሚ ነፍስ በምን ሁኔታ ቀሪ የትግል ጊዜ ሊመራ እንደሚችልም አላውቅም። የአማራ ህዝብ ጭንቅ ላይ ነው።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ጥሪ ተደርጎላቸው በፍጹም ለስብሰባ ሊመጡ የማይፈቅዱ መንደሮች እንዳሉም ሰምቻለሁ። ስለሆነም የአማራ ክልል ችግርን ለመፍታት የጨመተ፤ የአማራ ህዝብን ተፈጥሮ ከልብ - ያከበረ፤ ሰብአዊነት ያለው #ብሄራዊ ግብረ ኃይል ያስፈልገዋል። የሚጨበጥ፤ የሚዳሰስ የተግባር ሂደትም ይጠይቃል። ችግሩ በለብ ለብ፤ በግብግብ፤ በዝንጥፍጣፊ ልል እና ልቅ መንገድ የአማራን ህዝብ ዘላቂ ሰላም ማስከበር አይቻልም። በሳል የፖለቲካ ትጋት ይጠይቃል። ሥነ - ልቦናውም ተጎድቷል።
በጣም ስጋቴ ብልጽግና መዋቅር ውስጥ ያሉ መንታ መንገድ መራጮች በአማራ ህዝብ ላይ ሌላ የበቀል ጅራፍ እንዳይሰነዝሩ ብርቱ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። በሌላ በኩል ምርጫ መጣሁ መጣሁ እያለ ነው። ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲወች አማራ ክልል ያለበትን ደመመን የተጫነው አትሞስፌር ተረድተው፤ ምንም ዓይነት ተጨማሪ ጫና እንዳያደርጉበት በትህትና እና በአክብሮት እጠይቃቸዋለሁኝ። ግፍም ነው። አማራ ክልል ቢሮ ከፍተው ምረጡኝ??? በቃው! የአማራ ህዝብ። እለፋት ለዚህ የምርጫ ዘመን። ህወከት ነው የሚፈጥረው። እስከዛሬ የተማገደው ይበቃዋል።
አማራ ክልል ያለው ችግር የከፋ ነው። አየሩ በሙሉ ተወጥሯል። መንተንፈሻ አየር ያስፈልገዋል። የእያንዳንዱ የነፍስ ወከፍ መኖሪያ ቤት ግድግዳ ሳይቀር መተንፈስ ይፈልጋል። ንጹህ የሰላም አየር ለአማራ ህዝብ በእጅጉ ያስፈልገዋል። በዚህ ሁሉ የአማራ ህዝብ የምጸዓት የሂደት ውጣ ውረድ ዘው እንዳልል የረዳኝ፤ ያስወሰነኝን አምላኬ በእጅጉ አመሰግናለሁኝ።
#እራስን ስለመግለጥ።
በቀል ይኖራል ብየ አስባለሁኝ። ተባቃዩ ባለቤት አይኖረውም። ዝንቅንቅ ስብጥርጥር ስለአለ። ስለዚህ እራስን የመግለጽ ህዝባዊ ሁነት ቢኖር መልካም ነው። ቀደም ብዬ የዘመነ ኢህአፓን እና የደርግን ተመክሮ አጋርቻለሁኝ። ህይወቱን ስላለፍኩበት። ብልጽግናም አለሁ ካለ አካላቶቹ እራሳቸውን ይገልጡ ዘንድ መድረክ ሊያመቻችላቸው ይገባል። ሙሉ ህዝብን መበቀልም፤ ሙሉ አካልን ከሥራ አባሮ፤ ከማዕረግ አውርዶ ማሰርም አይቻልም እና። የተጎዳ ህዝብ ላይ ተጨማሪ ምንም ዓይነት ፈተና ከእንግዲህ ሊገጥመው አይገባም። የብልጽግና መንግሥት አይዟችሁን ሊነፍገው አይገባም ለአማራ ህዝብ። አስታራቂው መስመር ይህ ስለሆነ።
#ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶን በሚመለከት።
ልዩ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የሚያስፈልጋት ይመስለኛል። ከፖለቲካ ሙሉለሙለ መገለሏ፥ ልጆቿ በማተባቸው ምክንያት ችግርን ማስተናገዳቸው ዱር ቤቴ እንዲሉ ካስገደዳቸው በኽረ ጉዳይ አንዱ ሆኖ በውይይቱ አዳምጫለሁኝ። በዚህ ምክንያት የተጎዱ የካህን ቤተሰቦች የመኖራቸውን ያህል መርቀው የሸኙም የሃይማኖት አቨው እንደ አሉ አዳምጫለሁኝ። ካህናት ሌላ የእስር ዘመቻ እንዳይገጥማቸው ቅድስት ተዋህዶ ችግሩን የእኔ ብላ መላ እና ጥበብ ብትቀርጽ መልካም ይመስለኛል። ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋርም ፊት ለፊት መወያዬት የሚገባት ይመስለኛል።
1) የአማራ ህዝብ ጥያቄወች የብልጽግና አጀንዳ ሊሆን ይገባል።
2) የጥያቄወች ዕውቅና ማግኜት መሠረታዊ ጉዳይ ነው።
3) ዕውቅና መስጠት ብቻ ሳይሆን የተግባር ሰሌዳም ሊወጣለት ይገባል። በአጭር፤ በመካከለኛ ጊዜ በረጅም ጊዜ ሊፈቱ የሚችሉ በኽረ ጉዳዮች ተለይተው ወደ ተግባር የሚገባበት መሥመር ሊኖር ይገባል።
4) የአማራ ህዝብ ጥልቅ ችግር ከክልሉ መንግሥት፤ ከክልሉ ብልጽግና ጽህፈት ቤት፤ ከአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በላይ ነው። የአማራ ክልልን ችግር በበላይነት በማዕከላዊ መንግሥት ዘንድ ብልህነት፤ በጭምትነት፤ በሰፊነትን የመምራት አቅምን አብዝቶ ይሻል። ዕውነተኛ የሆነ፤ ቅብ ያልሆነ የህዝብ እና የመንግሥት ግንኙነት ለመፍጠር ቅን የሆነ ድልድይ ሊዘረጋ ይገባል።
5) የፖለቲካ ውክልና በሚመለከት የአማራ ሊቃናትን፤ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማንያን ሊቀ - ሊቃውንታት በሚመለከት የካቢኔ አባላትን ዝርዝር፤ ብሄራዊ ጉባኤወች ላይ ያለው የፕሮቶኮል ተዋረድ ሳይው ተመጣጣኝ አይደለም። ማመዛዘንም እንኳን አይቻልም። የሚመዛዘን ሲኖር ነው ማመጣጠን የሚቻለው። ይህ በቅጡ ሊታሰብበት ይገባል።
የባንክ ገዢው ፈቅደው ለቀቁ፤ የሰላሚ ሚኒስትሩ አንባሳደር ሆኑ። ሁለቱም ቦታ የአማራ ሊቃናት ከነበሩ በዞግ ሥልጣን የሚያከፋፍለው ብልጽግና የአማራ ሊቃውንት የማጽዳት ዘመቻ ባያደርገው ጥሩ ነው። የአማራን ህዝብ የውስጥ አለመረጋጋት ሊያሰክን የሚችለው በይበልጥ እያገለሉ በመሄድ ሳይሆን እራስን አይሶ በማቅረብ ሊሆን ይገባል። ይህ የሚረዳው ለራሱ ለብልጽግና ጉዞ ነው።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ የመንግሥት አወቃቀር ሥርዓቱ ሃይማኖታዊ ካልሆነ ለሁሉም አቅም እስከአለው ድረስ እኩል ውክልና ያስፈልጋል። ሚዛኑን ያልጠበቀ ከሆነ ብሶት ሲፈነዳ ዛሬ ሥራ ላይ ያሉ ህጎች ሁሉ ተፈፃሚ አይሆኑም። ሲከር ይበጠሳል፤ ሲሞላም ይፈሳል። ዕውነቱን ለመናገር የአማራ ሊቃናት - ቃና እና ክህሎት፤ በቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዊዝደምን በማሳደዱ ነው ህወሃት መንበሩን ያጣው። ይህ እንዳይደገም ያስተዋለ የእርምት እርምጃ በብልጽግና መንግሥት በእጅጉ ያስፈልጋል።
#አፍቅሮተ ህወሃት በአማራ ህዝብ አክ! ሊባል የሚገባው ፖለቲካዊ ዕውነት ነው።
"እግዚአብሄር በአንድም በሌላም ይናገራል፤ ሰው ግን አያስተውለውም።" ብዙ አሳዛኝ ክስተቶች መፈጣራቸው፤ ህወሃትን ደግሞ ከመሻት የመነጩ ስለመሆናቸው እኔ ከገባኝ ቆዬ። በህይወት እያለሁኝ ህወሃትን ጠግኖ፤ ደልዞ እና ጣጥፍ እንደ ገና ለመንበረ ሥልጣን ለማብቃት የሚደረገውን ትርምስ በሚመመለከት በአትኩሮት እና በጥንቃቄ የምከታተለው ጉዳይ ነው። የጃርት ጉባኤ ካልተናፈቀ በስተቀር ህወሃት የሚናፈቅ ተቋም አይደለም። መናፈቅ መብትም ቢሆን፤ የአማራ ህዝብ ጥቅጥቅ ጨለማ ናፋቂ ሊሆን አይገባም። በዚህ ጉዳይ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ወጥ አቋም ሊኖር ይገባል። ጥርት ያለ ውሳኔን ይጠይቃል።
#ልማት።
ብዙ ቦታ ልማት ተጠይቋል። የተጀመረው ይጠናቀቅልንም የሚል ጥያቄ አዳምጫለሁኝ። ሰላም ስሌለ የመንግሥት ግብር መሰብሰብ አይቻልም። በሌላ በኩል ነባሩን ለማስቀጠል፤ አዲስ ፕሮጀክት ለመጀመር ሰላም ከሌለ እንደምን ይሆናል? ጥያቄው ተገቢ ቢሆንም እስኪ መጀመሪያ የአማራ ህዝብ በሰላም ውሎ ለማደር ይብቃ።
ኪንፋዝ ላይ አንድ አባት ሲናገሩ ሲመጡ ተቋማትን ያፈርሳሉ። እናንተ መንግሥት ስትሆኑ ይህ ተቋም ያስፈልጋችኋል። እባካችሁ ብለን ለመናቸው። አሻም ስላሉ በጋራ ሆነን ተፋለምናቸው ሲሉ አዳምጫለሁኝ። ይህ ሂደት ህወሃት ለእህል ዘረፋ የካቲት ላይ ወገራ እና ስሜን አውራጃወችን ሲወር ያደርገው የነበረ ነው። የአማራ ፋኖ ይህን ያስቀጠለው ህወሃት ሆይ! ናፍቄሃለሁ እና ናልኝ ዓይነት ነው። በዕዳ ውስጥ ላለች አገር፤ ዕዳው ሳይከፈል ተቋማት አመድ ሲሆኑ የአስተሳሰብ ድህነት ነው። ይህም ሆኖ አካባቢያችን ይልማልን ጥያቄ ደግሞ አለ።
#የሰላም ጥሪ እና አፈፃጸሙ።
የአማራ ትግል ከውይይቱ እንደ ተረዳሁት ህዝባዊ ሆኗል። ይህን ህዝባዊ የውስጥነት ጥያቄ አክብሮ ደረጃውን የጠበቀ ብሄራዊ ድርድር ማድረግ የተገባ ነው። ከመሬወቹ ጋርም ይሁን ከህዝብ ጋርም ቢሆን። ከህዝብ ጋር ለመታረቅ የሚያስችል ስኩን የፖለቲካ ተግባር ይጠይቃል። እራሱ የብልጽግና መዋቅር ተንሳፎ ነው ያዬሁት።
መሪነት መሪነት እንጂ ጅራትነት አይደለምና። ብልጽግና አልቻለም። ዋልካ መሬት ውሃ ሲያጣ እንደሚሆን ሆኖ ነው ያዬሁት። የውይይቶቹ ግብረመልስ ይህን ያመላክታሉ። ብልጽግና ከሥር ጀምሮ እራስን የማረም፤ እራስን የመውቀስ ሂደትን ደፍሮ ሊጀምር ይገባዋል።
#ትምህርት ቤት። እንደ መከወኛ።
መምህራን እና የፋኖ ንቅናቄን በሚመለከት እንደ አዳመጣችሁት ነው። የጎጃም የቀለም ትምህርት ልቅና አይደለም ለኢትዮጵያ ለአህጉሩም፤ ለዓለምም ልዩ ነው። የአሳ ተመግቦቱ ልቅና ይመስለኛል የጎጃም ልጆች ትምህርት ዘርፍ ላይ ላቂያ የሚሆኑት። እራሱን የቻለ ጥናት እና ምርምር ይጠይቃል። ይሄ ተስተጓጉሏል። ስለሆነም ምህረትን እመኝለታለሁኝ።
የተዘጉት ትምህርት ቤቶች ብቻ ሳይሆኑ፤ ሥራ ላይ ያሉት በቂ ትምህርት የማይሰጥባቸው ስለመሆኑ ነው ያዳመጥኩት። ትምህርት ስኬቱ የረጅም ጊዜ ነው። አማራ ክልል በዚህ የጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ እንደ ሾለከ ነው ያዳመጥኩት። በጣም በቁጭት ሊታሰብበት የሚገባ መሠረታዊ ጉዳዬ ነው። ለይደር ሊቀጠርም አይገባም።
በሌላ በኩል ያመመኝ ጉዳይ ደግሞ ቢያንስ ትምህርት ላይ ያሉት ተማሪወች የተሟላ የትምህርት ክፍለጊዜ እንዲኖራቸው፤ ጥራት ያለው ክትትል ሊደረግ ይገባል። ይህን ንቅናቄ የጀመሩ ሁሉ፤ በዚህ ጉዳይ ተሳትፎ የነበራቸው ሁሉ አማራ ነገስ? የሚለውን ቢያስቡበት በትህትና እጠይቃቸዋለሁኝ። ለምን በሚቻል ቦታ በሁለት ፔሬድ ወይንም ትምህርት ብቻ ሂደቱ እንደተስተጓጎለ ቢገባኝም፤ መንገዱ ጠቃሚ አይደለም። ካለ ሙሉ ብቃት የሚቀጥል ሥልጡን ማህበረሰብ ሊኖር አይችልም።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አገልግሎትም እረገድ ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ አብያተ ቤተክርስትያናት እንዳሉም አድምጫለሁኝ። ደጀሰላሙ ከተዘጋ ከፈጣሪ ጋር መገናኛው ድልድዩ እንደምን ይሆን?
በሙሉ ያዳመጥኳቸውን ሊንኮች ለጥፌያለሁኝ። ከዜና ጋር የተሠሩትን አዳምጫለሁ ግን ሊንኮቹ አላስፈለጉኝም። ቆራጣ ቆራጣ ስለሆኑ። እኔ የናፈቀኝን ህዝብ ዓይን ዓይኑን እያዬሁ ጥድፊያ ሳይኖር ከውስጥ ለውስጥ ማድመጥን ነው የምመርጠው።
• «መከላከያውም ፋኖውም ልጃችን ነው› የሰላም ናፍቆትና የህዝብ ብሶት:- ታህሳስ «13/2018#Ethioskymedia"
• «በሰሜን ጎጃም ዞን የሰሜን ሜጫና መራዊ ከተማ ነዋሪዎች ጋር የተደረገ ውይይት»
• ስለአማራ ክልሉ ጦርነት ያልተሰሙ አነጋጋሪ ጉዳዮች; የሃይማኖት አባቶችና ባለስልጣናት ውግዘት ገጠማቸው- ታህሳስ 6/2018#Ethioskymedia" auf YouTube
• "አወዛጋቢው ጦርነትና የህዝቡ ለቅሶ: ‹ለሚሊሻም ለፋኖም ሞት እናለቅሳለን› - ታህሳስ 6/2018#Ethioskymedia"
• "ከፍኖተ ሰላም ከተማ፣ ጃቢጠህናን ወረዳ እና ጅጋ ከተማ ነዋሪዎች ጋር በፍኖተ ሰላም ከተማ የተደረገ ሕዝባዊ ውይይት"
• "ሕዝባዊ ውይይት በደቡብ ሜጫ መሐል ገነት ከተማ"
• "ሕዝባዊ ውይይት በደቡብ ሜጫ መሐል ገነት ከተማ"
• "የኪንፋዝ በገላ ወረዳ የሕዝብ ውይይት"
• " የሕዝብ ውይይት በቆላ ድባ "
• "ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም" በጯሂት የተደረገ ውይይት"
• "ሕዝባችን ላይ የጋለ የብረት ቀንበር ጭነንበት ቆይተናል"
• " ከመርጡለማርያም ከተማ እና ከእነብሴ ሳር ምድር ወረዳ ነዋሪዎች ጋር የተደረገ ሕዝባዊ ውይይት"
• "በደብረ ማርቆስ ከተማ አካባቢ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የመንግሥትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ "
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
የማከብራችሁ የአገሬ ልጆች ሆይ!
ከጥቂት ቀናት የጥሞና ጊዜ በኋላ ተመልሰን እስክንገናኝ ድረስ ምዕራፍ ፲፯ በዚህው ተጠናቋል። የፊደል እርማቱን ተከታትዬ እሠራለሁኝ። ምዕራፍ ፲፯ እና የአውሮፓውያኑ አዲስ ዘመን 2026 ጋር አብሮ ይመጣል። ቀጣዩም የእኛ የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የልደት በዓል ይመጣል። ለዛ ክብረቶቼን በሰላም ያድርስልኝ። አሜን። ጥር እና አስተርዬም ይከተላሉ። ሰላምን ይዘው ይመጡልን ዘንድ ምኞቴ ነው።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergure©Selassie
29/12/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አቤቱ አምላካችን ሆይ! ሠላም ለአገራችን፤ ሠላም ለዓለም ህዝብ ይሁንልን ዘንድ እለምንኃለሁ። አሜን።

አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ