መረጃ በወቅቱ ካልቀረበ ይፋድሳል፤ ዕሴቱንም ይቀንሳል፤ በሌላ በኩል አንድ ሥርዓተ #መንግሥት ሥርዓትን መፍቀድ ግዴታው ነው።

 

መረጃ በወቅቱ ካልቀረበ ይፋድሳል፤ ዕሴቱንም ይቀንሳል፤ በሌላ በኩል አንድ ሥርዓተ #መንግሥት ሥርዓትን መፍቀድ ግዴታው ነው።
 
"እግዚአብሄር በአንድም በሌላም
ይናገራል፤ ሰው ግን አያስተውለውም።"
 
 No photo description available.
 
#ምዕራፍ ፲፰።
 
የዶክተር ገዱ ምስክርነት እና የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ የመስካሪ ፈላጊ ሂደት ምን ያመሳጥርልናል?
 
እንዴት ናችሁ ማህበረ ቅንነት? እኔ አምላኬ ክብሩ ይስፋ ደህና ነኝ። 
 
አንድ ጭብጥ በጣም ሲገርመኝ ሰነበተ። የእኔ የህይወት ተመክሮ የፖለቲካ ፓርቲ ቋሚ እና መደበኛ ሠራተኛ ስለነበርኩኝ ድርጅቴ ኢሠፓ ለተልዕኮ ሲያሰማራኝ ከቡድን መሪ፤ የቡድን ጸሐፊ ጋር ነበር። በተጨማሪም እራሳቸውን ችለው የሚጓዙ ቲሞች ከኖሩም ከፖለቲካ ድርጅቱ በቀጥታ አመራር የሚያገኙ ወደ ተግባር ከመሰማራታቸው በፊት ወጥ የሆነ የተልዕኮ አቅጣጫ ይሰጣቸዋል።
 
ከተልዕኮ መልስም ሪፖርት ማቅረብ ግዴታቸው ነው። የአቅም ማኔጅመንት የሚታቀደው፤ የሚፈጸመው ከጉዞው #ግብረ መልስ ይሆናል። እኔ የቡድን መሪ ሆንኩኝ፤ ወይንም ሌላ የቡድን መሪ ኖረኝ የማይጓደልበት የዲስፕሊን መርኽ ድርጅቴ ኢሠፓ ነበረው። ለዚህ ነው እኔ የፖለቲካ ፓርቲዬ ኢሠፓ መራራ ስንብት ካደረገ በኋላ በድንግልናዬ የቀጠልኩት። እንኳንስ ፓርቲ የሆነ ተቋም አባልም፤ አካልም መሆን እማልፈቄደው የተፈጠርኩበት ድርጅቴ የፖለቲካ ዲስፕሊኑ፤ ተመክሮው፤ እኛን የቀረጸበት መንገዱ አንቱ ነበር። ከጠቀመ ላጋራችሁ ፈቀድኩኝ። 
 
1) እኛ ለተልዕኮ ስንላክ የተልዕኳችን አጠቃላይ መንፈስ #ይነገረናል። ሁላችንም በተልዕኳችን ላይ #እኩል ግንዛቤ እንዲኖረን የወል ማብራሪያ ይሰጠናል። ተልዕኳችን አጠናቀን ስንመለስም አጠቃላይ ሪፖርት በስኬት፤ በችግሮች፤ እና የመፍትሄ አቅጣጫወች ተኮር የሆነ ዘገባ እናቀርባለን።
 
2) ለትምህርት ስንላክ፤ ለወቅታዊ ጉባኤ ስንላክ ሳይቀር ቲም ሊደር ይኖረናል። አጠቃላይ መግለጫ ይሰጠናል። ተልዕኳችን አጠናቀን ስንመለስም በወልም፤ በግልም በነበሩ የቆይታችን ሂደቶች ላይ ያተኮረ #ሪፖረት እናቀርባል። ሁሉ ነገር የተሰነደ ነው። በፎቶ በቢዲዮም ሊሆን ይችላል። 
 
3) ዕድለኛ ወጣት ነበርኩኝ እና ክፍለ አገራዊ ተልዕኮ ለመከወን በክፍለ አገሩ ፓርቲ #ዋና ጸሐፊው የተመራ ሉዑክ ወደ ተለያዩ ክፍላተ- አገሮች የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ስንጓዝም የቡድን ሰብሳቢ፤ ሁለት ጸሐፊወች ይመደባሉ። የጸሐፊነት ዕድሉም ደርሶኝ አይቸዋለሁኝ። በየለቱ የከወናቸው የወል ተግባራት በጋራ ይገመገማሉ፤ ይወቃሳሉ፤ የቀጣዩ የትኩረት አቅጣጫ ማብራሪያ ይሰጥበታል።
 
ጉዞው ሲጠናቀቅ ጠንካራ #ሪፖርት ይዘጋጃል። ለክፍለ አገሩ ፓርቲ ምክር ቤትም መደበኛ ስብሰባም ሪፖርቱ ይቀርባል። ከእኛ ጋር ያልተጓዙ አካላቱ ሙሉ መረጃ እንዲኖራቸው ይደረጋል። መረጃ አካላቱ ለምነው ወይንም በተማህጽኖ አይደለም የሚጠይቁት።
 
መብታቸውም ነው። በሌላ በኩል የልዑኩ አካላት ሪፖርት የማቅረብ የወል ግዴታቸው ነው። #አይዘገይም። መንገድ ላይ ሆነን ዘገባውን ጨርሰን ነው ቢሮ የምንገባው። የመጀመሪያ የቢሮ ተግባራችን ሪፖርቱን ለታይፒስቶች መስጠት ነው። ሥርዓቱ መርኃዊ እና ወጥ ነበር። ለተመሰጠረ ጉዳይ ተልዕኮ ሲኖርም ቲሙ፤ የሚመለከታቸው አካላት ባይተዋር አይደሉም። 
 
#የዘገየው የኢትዮኤርትራ የጦርነት ጥምረት እና የጉዳቱ ሁነት።
 
ባለፈው የፓርላማ ቆይታ የኤርትራ መንግሥት ሠራዊት በትግራይ ክልል ላደረሰው ሁለገብ #ጥቃት የኢትዮጵያ መንግሥት ልዑክ ልኮ እንደነበረ እጅግ #የዘገዬ መረጃ በጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ አንደበት ተነገረ። እኔም ሼር አድርጌው ነበር። ለምስክርነት ጠቅላይ ሚኒስተሩ የጠሩት ስልጣን ላይ ያሉትን ሳይሆን ከሥልጣን የለቀቁትን ዶር ገዱ አንዳርጋቸውን እና አቶ ደመቀ መኮነንን ነበር። አዲስ ኮንፓስ ከውስጥ አገኜሁ ብሎ ዶር አብርሃም በላይን እና ሌሎችንም አክሏል።
 
ለምን ዶር. ገዱ አንዳርጋቸው ለምስክርነት ቀረቡ የሚለው የፖለቲካ ስሌቱ #አቦሰጥ አልነበረም። ታስቦበት የተከወነ ነው። የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ የሥልጣን ቆይታ መረጃ፤ ምላሽ የሚለጣቸው ጉዳዮች ሲኖሩ ጥገኝነት ጠይቀው አጋድመው፤ ከሆነ ነገር ጋር አያይዘው እንደ ዋዛ ብሄራዊ ጉዳዮችን ማቅረብ የተለመደ ነው።
 
የሆነ ሆኖ በለመድነው መልክ ጥንዝል ያለውን የፋክት አጋጣሚ ነግረውናል። ለምን ዛሬ??? ህዝብ ለማዳን ሰብአዊነት የዘለቀው መልካም ድርጊት ስለምን መያዦ ሆኖ እንደቆዬ፤ ማንን እንደጠቀመ፤ ማንን እንደጎዳ ዶር አብይ ያውቁታል። የሆነ ሆኖ ፓርላማ ላይ ቀረበ።
 
ይህን የምስክርነት ጥያቄ #ለክራቸው ሲሉ እንዲመልሱት የተማህጽኖ መልዕክት የተላከው ለዶር ገዱ አንዳርጋቸው ነበር። እንደ እኔ ፖለቲከኞች አጣብቂኝ የሆኑ ጉዳዮች ሲገጥሙ "#ዝምታ" ብልህነት ነበር። አቶ ገዱ መጀመሪያ በጹሁፍ፤ ከዛ በቃለ ምልልስ መልስ ሰጡ። የእኔ ጉዳዬ ምልልሱ አይደለም። ጉዳዬ የመንግሥት፤ መንግሥትን የሚመራው የብልጽግና ፓርቲ ዲስፕሊን ጉዳይ ላይ ነው። #ስለክር መነሳቱ ግን የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ይመስለኛል። 
 
#ብልህነት ቢሰነቅ፤ ወይንም ሥርዓት አዳኝ መሆኑ ቢታመንበት ኖሮ ………
 
1) አንድ መንግሥት ከሌላ አገር መንግሥት ጋር የሚያደርገው ግንኙነት #ዝርግ ሊሆን ይገባል ብዬ አላምንም።
2) ይህ ብቻ ሳይሆን ልዑካን ሲልክም የጋራ ተልዕኮ ለእያንዳናዱ የቡድን አባላት በወል #በቂ ማብራሪያ ሊሰጥ ይገባል።
 
3) ለአቻ መንግሥታት የሚላከው መሠረታዊ ጉዳይም በመንገድ ቁጥር፤ በፕሮቶኮል ጥንቅቅ ብሎ፤ ካለምንም #የፊደል ግድፈት፤ በማያሻሙ ቃላት ተሰንዶ፤ አባላቱ ባሉበት ሰነዱ ተነቦ፤ ውክል አባላቱ እያዩት በፖስታ #ታሽጎ ሊሰጥ ይገባል። ንባቡ በድምጽ ቢያዝም ይጠቅማል።
 
4) ልዑኩ ተልኮውን አጠናቆ ሲመለስ #መልሱ በአቻው ሰነድ ቀመስ እንዲሆን ማስቻል ይገባል። ከተቻለ ድምጽ ቢታከልበትም ይገባል። ይህን ሂደት በኢትዮኤርትራ ጉዳይ አላየሁም። ይህን አለማዬቴ ኢትዮጵያ በህወሃት እና በብልጽግና ጦርነት ጊዜ ከምዕራባውያን እና ከአውሮፓ መንግሥታት ጋር የነበረው የዲፕሎማሲ ሁነት፤ በአባይ ጉዳይ፤ በወደብ፤ በባህር በር ጉዳይ፤ የተቃዋሚ ኃይሎችን ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ስታስገባ ለምታደርጋቸው የልዑካን ጥረቶች ሁሉ ክፍትፍት ያለ ሁነት እንደነበረ ያሳያል። 
 
ይህን የመሰለ ሰዋዊ ተልዕኮ እንደ ተርቲም ነገር ተቃሎ መስክር // አትመስክር የሚዲያ ማዘከሪያ መሆኑ እጅግ የሚያሳዝን፤ የሚያቆጭ ጥቃትም የሆነ ግዙፍ ግድፈት ነው ብዬ አምናለሁኝ። ሌላም ሰው ተሰባሪ ነው። አንድ ልዑክ ደርሶ ስለመመለሱ እርግጠኛ የሚያደርግ ነገር የለም። የጉዞው ዓላማ እና ግብ ቀድሞ ሥርዓትን ተከትሎ ቢሰነድ ግን ይጠቅማል። በፈለገው ሁኔታ ለሚገጥም ሁነት ቋሚ፤ ሃውልት የሆነ የሠለጠነ ተግባርን ሰንዶ የማስቀረት ሁነት ሥርዓት አድርጎ ለማስቀጠልም እርሾ ይሆናል። 
 
አሁን የአባይ ግድብን ከውጥኑ ጀምሮ ይመራ የነበረው ግሎባል ኮሜቴ ተግባር እራሱን ችሎ ካሪክለም መሆን የሚችል ሂደትን መከተሉን አዳምጫለሁኝ። ያ የሃቅ ባላ እና ወጋግራ ማንኛውንም ወጀብ የመቋቋም አቅሙም ሙሉዑ ነው። የተደራጄ፤ የነጠረ ጥንቅቅ ያለ የተግባር ክንውን ነው እኔ የታዘብኩት። ሰነዱ ቢኖር አውጫጫኝ የሚያስቀምጥ ነገር አይኖርም። እኔ ያን ጊዜ ርዕስ ሰጥቼ የፃፍኩትም የTiming ጉዳይም ነበር። መረጃ በወቅቱ ካልቀረበ #ይፋድሳል፤ ይዝጋል፤ ዕሴቱንም ይቀንሳል። 
 
በዚህ መልክ የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት አመክንዮ ተከናንቦ፤ በዝግ ሁኔታ፤ ምንነቱ ሳይታወቅ፤ ስኬቱ እና ውድቀቱ ሳይሰነድ፤ የሁለቱም አገር ህዝቦች ሳያውቁት፤ ጥረቱም፤ የፈሰሰው መዋለ ንዋይም፤ የጠፋው ጊዜም፤ ያረረው ተስፋም፤ የተመገበው መዋለ መንፈስም የአንድ እድር ያህል ሰነድ አልቦሽ መሆኑ የታሪክ ግድፈት ነው። እራሱን የቻለ #ማንነት የነበረው ክስተት ነበር።
 
ግድፈቱ ግድፈት አጭቶ፤ ግድፈትም ወልዶ ግንኙነቱም ተውሸልሽሎ ሌላ መከራ ለማጨት ሂደቱ በቀጣይነት ምን ሊሆን እንደሚችል #በምንትሶ ዘውግ ላይ ይገኛል።
 
እያንዳንዱ ጥረት፤ እያንዳንዱ ክስተት፤ እያንዳንዱ ኢቬንት #ማንነት አለው። ማንነትን አሳምሮ መወጠን፤ ለመቀጠሉም ይሁን ለመጠናቀቁ ታሪክ ቀመስ ሥልጡን ትሩፋትን ይገነባል። ዕድል ካገኜ ባህል ሊሆን ይችላል። ባህል ማላት እኮ የሰው ልጅ የለት ኑሮውን ለመምራት በሚያደርገው ተጋድሎ ያለፈባቸውን የጭብጥ ሁነቶችን አማክሎ፤ ጨምቆ ዕድሜ ጠገብ ሲሆን ባህል ይሆናል። 
 
አሁን አዲሱ የኮሪደር ልማት ዛሬ ሥራ ነው። ነገ ዕድሜ ሲሸምት ባህል ይሆናል። ከነገ ወዲያ የዓለም ቅርስ ቤተኛ ይሆናል። ከኤርትራ መንግሥት ጋር የነበረው ግንኙነት ከቀን አንድ ጀምሮ የነበረው ሂደት፤ አድራሻው እስከማይታወቀው ፍፃሜ ድረስ ክንውኖቹ ለተመክሮ ወደ ባህል ደረጃ የመድረስ ዕድላቸው #ጨንግፎ ነው የተጀመረው። 
 
ከሌሎች አገሮችም ጋር የሚኖረው የሉዑክ ቡድን ስምሪት፤ ስኬት፤ ግድፈት እና የእርምት እርምጃ ወጥ የሆነ ሥርዓታዊ ሂደትን ሊከተል ይገባዋል አንድ መንግሥት። ሥርዓት ካልተፈጠረ የሚነግሰው ሥርዓት ዓልበኝነት ነው። ይህን መሠል ልቅ ሁነት ነው ለተቋማት የብቃት አቅም በሙሉዑነት እና በቋሚነት ለመፍጠር የማያስችለው።
 
አንድ መንግሥት ሥርዓትን ወዶ እና ፈቅዶ #በራሱላይ እንዲሠራ ካላደረገ ጉዞው በአጭር ሊቀር ወይንም መሰናክል ሊፈጠርበት ይችላል። ብዙ አመክንዮዊ ጉዞወች ዝርክርክ ብለው ባለባት ሁኔታ፤ ዛሬን ማስቀጠል ነገን በተስፋ መጠበቅም ይቸግራል።
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
 
22/02/2026
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ዕውነት ሸሽቶ አያውቅም።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።