#የ2018ዓ.ም የምርጫ መቅድመ ሙግት ካዳመጥኩት - ትዝብቴ።
#የ2018ዓ.ም የምርጫ መቅድመ ሙግት ካዳመጥኩት - ትዝብቴ።
"እግዚአብሄር በአንድም በሌላም
ይናገራል፤ ሰው ግን አያስተውለውም።"
#ምዕራፍ ፲፰።

«የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመጀመሪያው የክርክር መድረክ»
https://www.youtube.com/watch?v=DG6SHFL76_0
ሊንኩን በጥዋቱ ሼር አድርጌዋለሁኝ። በተጨማሪም መቅድመ ውይይት ስለሆነ ልፅፍበት ፈለግሁኝ። በቅድሚያ የሴቶች ተሳትፎ ለፆታ ተዋፆ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሴቶችን የፖለቲካ ግንዛቤ አቅም ጋር አቻ ሆኖ ሲገኝ ተስፋ ሰጪ ነው። እኔ ለሴቶች ተሳትፎ ልዩ ስስት አለኝ። ሴት ስለሆን ብቻ መድረክ ይሰጠን አይደለም። እእ። አቅም ያላቸው ሴቶች ተመጣጣኝ የፖለቲካ ውክልና ሊሰጣቸው ይገባል ነው የእኔ የትግል ማዕከል። በዘርፋ የፖለቲካ ሊቃናት ሴቶች ከእነሱ #ድፍረት ማነስ ካልሆነ በዘመነ አብይዝም ያለው ሁነት የሚያበረታታ ነው። ብዙ የፖለቲካ ሴት ሊቃናት ወደፊት መጥተዋል። ይህ የውሳኔ አቅም በአወንታዊነት የማየው ነው።
ሌሎችም ተፎካካሪወች ይህን አትራፊ እና ቀና መንገድ በመከተላቸው አመሰግናቸዋለሁኝ።
1) #የመወዳደሪያ ዓርማ።
1.1) የስንዴ ነዶ ባለፈው በስፋት ስለገለጽኩት አልመለስበትም። ነዶ (የጨርቅ ነዶ፤ የእሳር እህል ነዶ፤ የመቃጠል ዓዋጅ፤ የብስጭት መግለጫ) ቃሉ ለማስታወስ ያህል አሻሚ ትርጉም ያለው ስለመሆኑ አጠይቄ ብቻ አልፈዋለሁኝ። (የብልጽግና የምርጫ መወዳደሪያ መለያ ነው የስንዴ ነዶ።)
1.2) ሚዛን። ከገጠር እስከ ከተማ የሁሉንም ትርታ የሚገዛ ነው። (የኢዜማ የምርጫ መወዳደሪያ መለያ ነው ሚዛን።)
1.3) የእጅ ባትሪ። የግል የሆነ፤ ማንም የማያዘው፤ ጨለማን የሚረታ ወዘተ …… (የኢሶዴፓ የምርጫ መወዳደሪያ መለያ ነው የእጅ ባትሪ)
3.1.1 ) አንደኛ ካለፈው ከብልጽግና ፓርቲ ከአንፖል ምልክት ጋር ተወራራሽ ተልዕኮ ያለው ነው።
3.2.2 ) የእጅ ባትሪ መብራት መጣ ቀረ ጉዳዩ እንዳልሆነ ቢጠቀስም፤ የባትሪ #ድንጋይ ጥገኛ መሆኑ ሊታለፍ የማይችል ሃቅ ነው።
4) ዓውራ ጣት ቀላል፤ ብዙ ማብራሪያ የማይሻ ግልጽ የምርጫ ምልክት ነው። ከቅንጅት ሁለት ጣት ጋርም ተቀራራቢ እንዲሆን ታስቦ ሊሆን ይችላል። ትርጉሙም መንፈሱም ብዙ ማገዶ አይሻም (የትብብር ለኢትዮጵያ የምርጫ መወዳደሪያ መለያ ነው።)
2) #አድሎዊነት።
ለሁሉም የፖለቲካ ተፎካካሪወች የማጠቃለያ ንግግር እኩል ደቂቃ ተፈቀደ። ይህ በጎ ነገር ነው። ነገር ግን የብልጽግና ተወካይ እና የኢዜማ ተወካይ የማጠቃለያ ንግግር ሲያደርጉ ፋና ቴሌቪዥን የሁለቱን በፖለቲካ ድርጅቶን #ዓርማ ፊት ለፊት ስክሪን ላይ ሲያሳይ፤ የኢሶዴፓ እና ትብብር ለኢትዮጵያ ግን ዕድሉ #ተነፍጓል። ይህን መሰል ግለት ለወደፊቱ ሊታረም ይገባዋል።
3) #እንግሊዘኛ ቋንቋ መቀላቀሉ ጠቃሚ አይደለም።
ምርጫ ዕድሜው የፈቀደለትን ሁሉ የሚያሳትፍ ጉዳይ ነው። ይህ ከሆነ ዘንዳ ተፎካካሪወች ጭብጣቸውን ከትውስት ቋንቋ ይልቅ ተርጉመው አገር በቀል አድርገው ቢያቀርቡት ለመራጮቻቸው የቀረበ ግንዛቤ ይፈጥራል። ዥንጉርጉር ከሆነ ግን እንግሊዘኛ ለማይችለው ሰፊ ወገን የመረዳት ችግርን ያመጣል። በመሃልም አለመግባባትን ሊፈጥር ይችላል። ጉልበት ቆጣቢም አይደለም። የአማርኛ ቋንቋ አቻ ፍች ለሌላቸው ቢሆን እንኳን አጠጋግቶ መተርጎም ወይንም ቀለል ባለ ምሳሌ ማቅረብ ጥሩ ይመስለኛል።
4) "#አስቻይ ሁኔታ" ዕድል ቆሞ አይጠብቅም። Timing ወሳኝ የሆነ የብልህነት መክሊት ነው።
ተደጋግሞ እምሰማው ዕድምታ ነው። ይህ ለመራጩ ህዝብ አቋምን የወለሌ ገበታ የሚያሰኝ ጎጂ ዕድምታ ነው። በሌላ በኩል መንፈስን፤ ሃሳብን፤ የማድረግ አቅምን ያዘናጋል፤ ይበትናል፤ ለውሳኔም ሳንክ ይሆናል። አንድ የፖለቲካ ድርጅት በራሱ ጉዳይ ላይ ራሱን ችሎ ነው መቆም ያለበት። A እንዳይከፋው፤ Bንም እንዳይከፋው ብሎ ማህል ላይ ሊዋልል አይገባም። እራስን ለፈተና የሚዳርግ፤ ጥርጣሬን በየአቅጣጫው የሚያፈልቅ፤ አቅምን የሚያዋልል ሁነት ነው። ወስኖ መነሳት፤ ወስኖ መንቀሳቀስ በእጅጉ ያስፈልጋል።
ለሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ያለው "አስቻይ ሁኔታ" ለሁሉም እኩል ሊሆን ይገባል። በሌላ በኩል ጊዜ ቆሞ ስለማይጠብቅ በግርግር ዕድል ሊያመልጥ ይችላል። በበቂ ፍላጎትን ለመግለጽ፤ በፍላጎት አፈፃጸም ላይ የተቻለውን ለማድረግ የራስን ዕድል በራስ ቅድመ ሁኔታ አስሮ መወጠን በውነቱ አድካሚ መንገድ ነው። ዕድል ቆሞ አይጠብቅም። በዚህ ጉዳይ ላይ በተለይ ኢህአፓ ዕድሉን እንዳያፈስ ሃሳቤን ዘርዝሬ ጽፌበታለሁኝ። ሰከንዳድ፤ ደቂቃ፤ ሰዓታት፤ ቀናት፤ ወራት እና ዓመታት የራሳቸው የጥሪ፤ የማድረግ አቅምም ንጥረ ተልዕኮ አላቸው። ካለፈ አለፈ ነው። ወርቅ ከቀለጠ ይፈሳል።
5) #ንግግር እና ምርጫ።
ሙግት ርትዑ አንደበት ይጠይቃል። ለምሳሌ አንድ ሰው በኤኮኖሚ ሳይንቲስት ሊሆን ይችላል። ፈላስፋም ሊሆን ይችላል። ግን የንግግር ጥበብ ዕውቀት ይሁን ተሰጥኦ ከሌለው ዕውቀቱን አውጥቶ መሸጥ ካልቻለ ዕድል ሊያመልጥ ይችላል።
በፖለቲካ ህይወት ውስጥ መድረክ የሚርበው ርትዑ አንደበትን ነው። እንኳንስ የምርጫ ፋክክር ላይ። ንግግር ጸጋም፤ ተስጥኦም ሲሆን ክህሎቱን በሥልጠና ማግኜት ይቻላል። አንድ የፖለቲካ መሪ #የአዘቦት ተናጋሪ ሊሆን አይገባም።
ይልቁንም ተናፋቂ፤ ተጠባቂ፤ አጓጊ፤ ሳቢ እና ተደማጭ ሊሆን ይገባል። የፖለቲካ ሊቃናት ድርጅታቸውን ወክለው ሲቀርቡ በሙሉ የራስ መተማመን፤ የተነሱበትን መሠረታዊ ዓለማ ወይንም የንግግር ጭብጥ #በቅተውበት ሊሆን ይገባል፤ በሌላ በኩል በያንዳንዷ ደቂቃም #መኖራቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።
6) #ለፖለቲካ ድርጅት የፖሊሲ አቀራረብ ከፕሮፖጋንዳ የጸዳ ሊሆን ይገባል።
እንኳንስ ሁሉ ኖሮት ሥራ ላይ ያለ ገዢ የፖለቲካ ድርጅት ቀርቶ፤ የትኛውም የፖለቲካ ድርጅት የንግግር ማዕከል ጭብጥ ዘለቅ፤ ፋክት ገብ ሊሆን ይገባል። አክቲቢስትነት፤ ፕሮፖጋንዲስትነት የራሳቸው ባህሪ፤ መድረክ አለ። ይህ ግን ለነገ ምን አለህ? ምን ይዘሃል፤ ስንቅህ ከምን ይነሳል፤ እንደምንስ ተልዕኮህን ለማሳካት አስበኃል፤ የሃሳብህ ምንጭ ርዕዮትህ ምንድ ነው? ……… መልሱ ራህብ የሚለቅ፤ በጥማት ወጀብ የሚያንገላታ ሊሆን አይገባም።
7) #የውስጥ ብስጭት በፋክክር ላይ ያለው ፋይዳ።
ለምራጫ በሚደረግ በሳል የፖለቲካ ፋክክር የሚፈትኑ #ያደሩ የቁጭት መስኮች ሊኖሩ ይችላሉ፤ በዛው ወቅትም የሚፈጠር ክስተት ሊኖርም ይችላል። በንግግር ዝበት ግንፍልተኝነት ሊገፋፋ ይችላል። በዛ መድረክ እራስን አስታግሦ ለጭብጦቹም የመቻልን ማጫ አጎናጽፍ በተረጋጋ፤ በሰከነ ለስለስ ባለ የድም ቃና ጭብጦችን አደብ አስገዝቶ ማቅረብ ይገባል።
ስምንተኛ) #መንግሥት ተሁኖ ስለተከወነ ተግባር።
ብልጽግና የኢትዮጵያን ሥርዓተ መንግሥት የሚመራ አውራ ፓርቲ ነው። ግዴታውን ስለተወጣ ችሮታ እንዳደረገ እራሱን አግንኖ ማቅረብ አይገባም። ሌሎቹ ዕድል ቢያገኙ ከእሱ የተሻለ፤ ወይንም ያነሰ ተግባር ቢፈጽሙ በመንግሥት ሙሉ ባጀት ለተፈጸመ በግዴታ ሁነት እንደ ልዩ የስጦታ ገጸበረከት ይታይልኝ ማለት አይችልም።
ጥያቄው ለቀጣዩ ፭ ዓመታት ምን አቀዳችሁ ነው ጥያቄው፤ እንጂ በመጀመሪያ የምርጫ ዘመናችሁ ምን ሠራችሁ አይደለም። አዲስ በር አለ፤ በዛ በር ገብተህ አገር ለመምራት ምን ከእጅህ አለ ነው አንኳሩ ጉዳይ።
9) "#መደመር አገር በቀል ነው።"
9.1) "መደመር" የትናንት የአንድ ሰው ዕሳቤ ወይንም ፍልስፍና ነው። ብልጽግና አገር በቀልነት ከናፈቀው ዝምተኛው ማህበረሰብን፤ አፍሪካውያንን፤ ተፈርያውያንን ሊገዛ የሚችለው #የእከሌ ሊባል የማይችለውን #ኢትዮጵያኒዝም ስለምን ፈራው? አቅምም፤ ሚስጢርም ያለው ከዚህ ልዑቅ ማንነት ውስጥ ነበር እኮ፤ ለምን ብልጽግና ሽሽት አስፈለገው????
9.2) "መደመር አገር በቀል" ከሆነ ፍልስፍናው ኢኮኖሚው በዚህ ፍልስፍና ውስጥ ስለምን አልሰከነም????
9.3) ሌላው በትላልቅ ግዙፍ መጸሐፍት አገር ሲመራ ያን የሚገነዘብ ስንት ሚሊዮን ህዝብ ይሆን ብሎ ብልጽግና አስቦበታል። ብልጽግና ታሪኩን በመጽሃፍ ሊያዘክር ቢችልም "የመደመር" መጸሐፍን ህትምት እየተከተለ ለመምራት መደመር ለሚያነቡ ብቻ፤ ለዛውም ሞናትነስ ካልሆነባቸው ይሆናል። እኔ ግን እምለው አጭር ግልጽ እና ቀጥተኛ ጭብጦችን ቀምሮ ቢነሳ ጠቃሚ ይመስለኛል።
9.4) "መደመርን" ከኢትዮጵያኒዝም በላይ የማየቱም ጉዳይ ሊታረም ይገባል ብዬ አስባለሁኝ። የየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት መሻቱ፤ ራዕዩ፤ ዓላማ እና ግቡ ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵኒዝም በላይ አይደለም።
9.5) "መደመር" በየትኛው አገር ተመክሮ፤ "በመደመር ፍልስፍና" ኢትዮጵያ የመሞከሪያ ጥንቸል ልትሆን አይገባም። ከሁለቱ ጋዜጠኞች ከጠያቂውም፤ ከትብብር ለኢትዮጵያም ተሟጋች የቀረበ ጥያቄ ነው። "የመደመር ፈላስፋው ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ እራሱን አስችለው ሊመልሱት የሚገባ ይመስለኛል። እንደ ሌላው አመክንዮ የስብሰባ ቀን ጠብቀው፤ እግረ መንገድ የሚመለስ ጉዳይ አይደለም።
9.6) ለመያዝም ያስቸግራል። ቀጣይም አራተኛ ይመጣ ይሆናል።
10) #ያልገባኝ።
በየዓመቱ ማኒፌስቶ የማዘጋጀት ሁነት ፈጽሞ አልገባኝም።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ የገበሬው ማህበረሰብ የፖለቲካ ውክልና የለውም። ገበሬው የመምረጥ ግዴታ እንጂ #የመመረጥ መብቱ ልሙጥ ዕድል የለውም። ገበሬው የብልጽግና ፓርቲም የማዕከላዊ ምክር ቤት ሆነ የሥራ አስፈፃሚ ኮሜቴ አባል አይደለም። ይህን ጉዳይ ጠቅላዬ ሚር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን እንደመጡ በወርሃ ግንቦት 2010 ዓም እኔም ዜጋ ከሆንኩኝ በሚል ረጅም ጹሁፌ ውስጥ በትህትና ካቀረብኳቸው ጭብጦቼ አንዱ አብክሬ የገለጽኩት ስለ ኢትዮጵያ ገበሬ የፖለቲካ ውክልና ነበር። በተለያዬ ጊዜም ጽፌበታለሁኝ።
12) #በጉጉት የምጠብቀው "የይሁነን ቃል እና ሁነቱ።
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ ቀጣዩ ምርጫ ላይ ሞጋች ፓርላማ ናፍቆናል ብለውናል። በዚህ ፈተና ስለማለፋቸው በአለፈው መልክ ከሆነ ይከብዳል። አንዳንድ ክሊፖችን ላስተዋለ አወንታዊውን ብቻ እንጂ ሞጋቹን ሃሳብ ብዙም ሲያቀርቡት አይቼ አላውቅም። የሆነ ሆኖ ለዚህም "ይሁነን ብለን የራሳችን ዕድል እያጠፍን ለተፎካካሪወች እንሰጣለን" ብለውናል። እኔ ይህንን ቃል በጉጉት እጠብቀዋለሁኝ። እስከታች ድረስ ገቢራዊ ስለመሆኑም ጊዜ ሰጥቼም እከታተለዋለሁኝ።
13) #ስለ ለላም ወሳኝ ድርሻ፤ ማገርነት፤ ምሰሶነት፤ ህሊናዊነት ጠንከር ብሎ አልተነሳም።
#ክወና።
ባለፋት የትግል ዘመናት የምርጫ እርግጫ ሲወገዝ፤ ሲሞገት ሲጣጣል ቆይቷል። አላተረፈም። ባአላተረፈ ጎዳና መጓዝ የትውልድ ሥነ ልቦናን ያጫጫል። እራስን አርሞ በሚገኙ የዕድል ቀዳዳወች ሁሉ መሳተፍ አትራፊ ነው። ልምድ፤ ተመክሮ፤ መነቃቃት ብዙ ነገር ይፈጥራል።
ባይሆን ጫና፤ ግለት፤ እስር፤ ወከባ፤ ማስፈራሪያ፤ መሰዋት እንዳይኖር ሁሉም ተግቶ በዲስፕሊን ራሱን ገርቶ በሚችለው ልክ ሊሳተፍ ይገባል ባይ ነኝ።
ለሁላችሁ የቀና፤ የተቃና ዕድል ይኖራችሁ ዘንድ እመኛለሁኝ። መልካም ዕድል። አሜን።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
22/02/2026
ዕውነት ቦታውን ለቆ አያውቅም።
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ