እስኪ ልጅ ጋሻው መርሻ ይሞገት። በምን የመረጃ ጥናት 95% የአማራ ክልል ሰላም ነው እንዳለ አልገባኝም።

 

እስኪ ልጅ ጋሻው መርሻ ይሞገት። በምን የመረጃ ጥናት 95% የአማራ ክልል ሰላም ነው እንዳለ አልገባኝም።
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 
አብን ነፍሱ ስለመኖሩ አላወቅኩም። ስለዚህ ሙግቴ በግለሰባዊ ዕይታ ብቻ ቢሆን እፈልጋለሁኝ። ግን ብዕሬ ከፈቀደች እና ካሰኛት ሳይለንት ዲስክርምኔሽን አልፈጽምባትም። እንዳሰኛ ትሰጥስጠው።
 
ልጅ ጋሻው መርሻ አንዳቤቴ ነው ሲባል ሰምቻለሁኝ። አንዳቤት ለእናት አገሩ ለኢትዮጵያ በየዘመኑ አርበኛ ማፍራት፤ የቤተክህነት ሊቀ - ሊቃውንትን ለእናታችን ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ማበርከት ተመክሮው ቢሆንም፤ እንደ ልጅ ጋሻው መርሻ #ፈንገጥ ያለ ሃሳብ አቅራባ ግን ሰምቼ አላውቅም። ስለሆነም አቶ ጋሻው መርሻን ሳዳምጠው ሁልጊዜ "የአንድአቤት" ሥያሜ ይገርመኛል።
 
አንድአቤትን በአካል አውቀዋለሁኝ። ብዙውን የጎንደርን ቀበሌ መንደሮች በእግሬ እየተጓዝኩ አውቃቸዋለሁ። የአንዳቤት የማይረሳኝ እርጎው ነው። ዛሬ የቅኒት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጆች ቄራ የሆነው አርሲ ጢቾ አውራጃ አምኛ ወረዳ በተመሳሳይ የተመገብኩትን እርጎ አንዳቤት ላይ አግኝቸዋለሁ። እርጎ ከምለው አንጠልጥዬ በክብር የቅቤ እርጎ ብለው ዕውነቱን ያደረጀዋል።
 
የአንደቤትን ገበሬወች፤ የሴቶች ማህበር እና የወጣቶች ማህበርን አመራር ሳወያያቸው አንድአቤት እንደ ሥሙ ሆኖ ነበር ያገኜሁትኝ። እናቴን የእሽታ ልዕልቴን ለምን አንድአቤት ተባለ ብዬ ከሥራ ወደ ጎንደር ስመለስ ጠዬቅኳት። እሷም ከቤተሰብ የሰማችውን ነገረችኝ።
በጥንት ጊዜ ገዢወች እየተዘዋወሩ ነበር ፍርድ የሚሰጡት። 
 
አንድአቤትም እንደሌሎቹ ባድማወች የተጉላላ ፍትህ በማጣት የተቸገረ፤ ፍርድ የጎደለበት፤ ያለቀሰ፤ በመንግሥት የተከፋ ይኖራል ብለው ሲያስቡ አንድም ሰው ክስ፤ ቅሬታ፤ አቤቱታ አላቀረበም። ገዢወቹ ከዛሬ ነገ አቤቱታ አቅራቢ ይመጣል ብለው ሲጠብቁ እነሱን የሚንከባከብ እንጂ ከሳሽም፤ ተከሳሽም ሊቀርብ አልቻለም። በዚህ ምክንያት እንዲያው ለዘር ወደ እኛ መጥቶ "አቤት" የሚል አንድስም እንኟን ጠፋን ብለው በመገረም ቦታውን "አንድአቤት" አሉት ብላ ነገረችኝ። ዕውነት ለመናገር በእኔ ቆይታም ያስተዋልኩት ቁምነገር ይህን ነበር።
 
እና ……… ከዚህ አንፃር ሁልጊዜ አዘውትሬ ልጅ ጋሻው መርሻ ብቅ ሲል ሚዲያ ላይ የአንድአቤት ኳሽ አይልነት፤ የበዛ መጨመት፤ እና እሱ የሚሰጣቸው፤ የሚያቀርባችው ሃሳቦች፤ ሃሳቦቹን ሲገልጽ የሰውነቱ ጄስቸር ይገርመኛል። አንድአቤት በእስቴ ወረዳ የሚገኝ ሲሆን፤ እስቴ ለም፤ ለስላሳ፤ ቅን እና ትጉህ የሆነ ማህበረሰብ የሚኖርበት ቦታ ነው። አሁን ባድማው ከፋኖ ንቅናቄ የዳነ አይመስለኝም። የቅርብ መረጃም የለኝም።
 
የቢቢሲ ጋዜጠኛ ጥያቄ ከማቅረቧ በፊት መሠረት ያለውን መረጃ በሚገባ ማጥናት የሚያስፈልጋት ይመስለኛል። የአብን መከፋፈል ከፊሎቹ ወደ ብልጽግና የኃላፊነት መዋቅር መግባታቸው አይመስለኝም። ከምሥረታው ጀምሮ አብን እና ባልደራስን እከታተል ነበር። በዛን ወቅት ከመስኪ ጋር አቶ ክርስትያን ታደለ በፌስቡክ ጠንካራ ሙግት ነበራቸው።
 
ያ ጠንካራ ሙግትን ያጨው ጉዳይ አቶ ክርስቲያን ታደለ አቶ በለጠ ሞላ ለሚኒስተርነት የዛን ጊዜ አቶ ነበሩ ሲሾሙ "#እንኳን ደስአለን አብን ለዚህ በቃ" ያሉት አቶ ክርስትያን ታደለ ነበሩ። መስኪ የሞገተችው ይህን ነበር። 
 
እና በሁለቱ መሃል በሚደረጉ ሙግቶች ሚዛን ያልጠበቀ ዕይታ ስለገጠመኝ መስኪ ደራሽ ብዕረኛ፤ ደራሽም ታጋይ እንዳልሆነች በድፍረት ህወሃትን በቋሚ አምደኝነት በብዕሯ የሞገተች ብርቱ፤ ትጉህ ጸሐፊ መሆኗን እኔ ስለማውቅ፤ እሷን የመተቸት፤ የማቃለል አቅሙ ከአብኖች ሊመጣ አይገባም ነበር የእኔ የጹሁፌ አንከር ጉዳይ። ከአብን በፊት የአብን መሪወች በጸረ ህወሃት ትግል ጎልተው አናውቃቸውም።
 
አሁን በዘመነ ብልጽግና አቶ ክርስትያን ታደለም፤ መስኪም እስር ቤት ይገኛሉ። እግዚአብሄር አምላክ ለቤታቸው ያብቃቸው። አሜን። የሆነ ሆን የሙግቱ ሥረ ነገር ማን ትክክለኛ እንደሆነ መመዘን ትችላላችሁ። በተጨማሪ በዛ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት አቶ ክርስቲያን ታደለን ያቀርብ ስለነበረ ለሠራዊቱ #አነቃቂ ንግግር እንዲያደርጉ አቶ ክርስትያን ታደለ ተመድበው ንግግር አድርገዋል።
 
በዛን ጊዜም አዲስ ድምጽ በንግግሩ ውስጥ የአማራ የጸጥታን ኃይል አቶ ክርስትያን ታደለ ዕውቅና አልሰጡም ብሎ ሲሞግት አዳምጫለሁኝ። ለሠራዊቱ ያደረጉትን የአቶ ክርስትያን ታደለን ንግግርም አዳምጫለሁኝ። ስለሆነም ግብረመልሱ የሚያጠይቀው "ቸርነቱ ለጋሽነቱ" ያላለቀበት አቤቱ ብልጽግና በፓርላማም ቁልፍ የኃላፊነት ቦታ ለአቶ ክርስትያን ታደለ እንደሰጠ ሁሉ ለሌሎችም የኃላፊነት ቦታ ሰጥቶ አይተናል።
 
ሌላው ወደ አምስት የሚጠጉ የአብን አካላት በኢትዮጵያ ፓርላማ በሰፋ ልዩነት ብልጽግናን አሸንፈው ገብተዋል። ይህም እኮ ትልቅ የሆነ #የሥልጣን እርከን ነው። ከምርጫ መወዳደሩም ሌላው አናታዊ የፖለቲካ ውሳኔ ነው ምርጫ ለመወዳደር መወሰኑ። 
 
በሌላ በኩል መወዳደሩ ሌላ ኃላፊነትን እና ተጠያቂነትን ሼር ለማድረግ የተወሰደ ፖለቲካዊ ብልህ እርምጃ ነው። በምርጫ ሲያሸንፋም እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ የፓርላማ አባል ሆኖ መቀጠልም ሌላው የነጠረ ዕውነት ነው። ሥልጣን ለማይፈልግ አንድ ቀን አብሮ ለመቀጠል መርግ እኮ ነው። በዚህ መሃል ነው ከህግ አግባብ ውጪ ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ የፓርላማ አባሉ አቶ ክርስትያን ታደለ የታሠሩት፤ ሲታሰሩም እንግልት ደርሶባቸዋል የሚል ዘገባም አድምጫለሁኝ። አሳዛኝ ክስተትም ነው። 
 
ከሁሉ የከፋው ግን ሲታመሙ ህክምና እንዳያገኙ ጫና በመደረጉ ሂደት ከአንድ መንግሥታዊ ሥርዓት የማይጠበቅ ሁነቶችን አዳምጬ ጽፌበትማለሁኝ።
 
የሆነ ሆኖ የአብን መሪ አካላት በፓርላማ፤ በአዲስአበባ ምክር ቤት፤ በአማራ ክልል ምክርቤት፤ በማዕከላዊ መንግሥት መዋቅር፤ በአማራ ክልል መዋቅር፤ በፓርላማውም ውስጥ በተለያዬ ኃላፊነት ቦታወች እየሠሩ "የክፍፍላችሁ መሠረት ኃላፊነቱን መቀበላቸው ነው የሚል የማጠቃለያ ጭብጥ ላይ ዕውነቱ አያደርሰነም።
 
በዕኔ ዕይታ በየትኛው ሁኔታ የሚገኙ ዕድሎችን ሳያፈሱ፤ በጊዜው መጠቀም ዘመን ሰጥ ገጠመኝ ስለሆነ ሊበረታታ እንጂ ሊነቀፍ ይገባል ብዬ አላስብም። ለዚህም ነው ኢህአፓ በምርጫው ሊሳተፍ ይገባል ብዬ እምሞግተው። ዕድሉ አይገኝም፤ በመንግሥት ሥርዓት ውስጥ በመዋቅር መሳተፍ ከየትኛውም ዩንቨርስቲ ተገብቶ ከሚገኘው ዕውቀት በላይ፤ ተመክሮው ሙሉ ሰብዕናን ያጎናጽፋል ላወቀበት፤ በተጨማሪም ለቀጣይ #የመሪነት ሂደትም ወሳኝ ነው።
 
ዶር አረጋይ በርሄ፤ ፕሮፌሰር ዶር ብርሃኑ ነጋ፤ ዶር በለጠ ሞላ፤ ነፍሳቸውን በገነት ያኑር ፈጣሪያችን እና ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ዘመናቸውን ያበራው የህዝብ አገልግሎት #በምንዳ በሰዓት ወጥቶ የመግባት ዲስፕሊንን ሁነት መሳተፍ መታደል ነው። ዕድሉን መጠቀምም ብልህነት ነው። 
 
ማንም ሰው በሥርዓተ - መንግሥታዊ ሁነት ሳያልፍ ለየትኛውም ቁልፍ የመንግሥት ቋሚ መሪነት ብቁ ሊሆን አይችልም። የዛ ሰብ ተፈጥሯዊ፤ ሙሁራዊ ዕውቀት ስክነት #እርጋን የሚጎናጸፈው በሥርዓተ - መንግሥት ሂደት ሲታለፍ ብቻ ነው። ይለፋም ለአገር መሪነት የሚሰጠው ማህተሙ ይህን መሰል ተመክሮ ነው።
 
በዚህ ዘርፍ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተሞክሮ የማያውቅ ቸርነት ልግሥና ነው በብልጽግና በኩል ያዬሁት። የብልጽግና መንግሥት ስስታም ቢሆን ኖሮ ይህን ዕድል ለመስጠት አይደፍርም። እንገነጠላለን ለሚለውም ኦነግ ዕድሉን ሰጥቷል እኮ ቸርነቱ ያላለቀበት አቤቶ ብልጽግና አሳይቶናል። የመስቃ ቡፌ መቅርቦ ቀራኒወን አስጎብኝቶናል።
 
ስለዚህ በቢቢሲ የቀረበው የአጠያዬቅ ዘዬ ሚዛን የመታ ሆኖ አላገኘሁትም። በዘመነ ህወሃት ይህ አይታሰብም፤ አይደፈርምም። አሸነፍኩ ያለ የፖለቲካ ድርጅት ያለ የሌለውን የሥልጣን እርከን ያጋፍፋል እንጂ ችሮታውን ለሚፈቅዱ ተደማሪወች ይሁን ብሎ አምኖም፤ መስጠቱ አዲስ ታሪክ፤ አዲስ ምዕራፍ ነው ግሎባሊም ትርፍ ዝቆበታል ብልጽግና።
 
ብዙ የፖለቲካ ሰብዕናወች የአብን እና የኢዜማን እርምጃ አልወደዱትም። ይወቅሱታልም። እኔ ደግሞ ዕድልን ማፍሰስ የተገባ አይደለም፤ የብልህነት #ፍልሰትም ነው ባይ ነኝ። ዕድሜ ዘመኑን ታግሎ ማሳካት ያልቻለ ነፍስ እንዲህ የፖለቲካ ዕድላዊ ችሮታ ሲያገኝ ሎተሪ ነውና በሎተሪው ለመጠቀም መፍቀድ ብልጠት ሳይሆን ፖለቲካዊ #ሥልጣኔም ነው። 
 
የፖለቲካ ድርጅት የሚደራጀው ለፖለቲካ ሥልጣን ነው። ሥልጣኑን ቢገኝ ከነበረው ወይንም ካለው በተሻለ ፖሊሲ የህዝብን ጥያቄ እንመልሳለን ነው። በሌላ አገርም ተሸናፊ የፖለቲካ ድርጅቶች ከሌሎች ጋራ ኳ`ሌሽን በመፍጠር አሸናፊ ሆነው አገር ይመራሉ። ይህን ለናሙና ያህል በጀርመን SPD እና CPD በየምርጫ ዘመኑ የሚያደርጉት ነው። ባይቀናጁ ትውልዱ አዲስ የፖለቲካ ድርጅት ፈጥሯል። ዕድሉን ካገኜ ፈተናው ለመላው አውሮፓ ይሆናል። 
 
ልጅ ጋሻው መርሻ ወደ አብን ሲመጣ ሰማያዊ እንደነበር ሰምቼ ያን ጊዜም ጽፌበት ነበር። ከዜግነት ፖለቲካ ወደ ዞጋዊ ድርጅት የፖለቲካ ማንነት መዘዋወር፤ የፖለቲካ የማንነት ቀውስ ስለሚያመጣ አብን አንጃ ያሰጋዋል ሁሉ ብዬ ጽፌያለሁኝ። ብሎጌ ላይ አለ። 
 
የሚገርመው ተስፋ የተጣለበት አብን፤ የሚሊዮኖችን ድምጽ አብከንክኖ ሳይሰክን የአብን ችግር ከብሄራዊነት አማራነት ወርዶ የሠፈር #ቅርቃር ውስጥ መግባቱ ትልቁ ለውድቀቱ አስተዋፆ እንደአደረገ አይቻለሁኝ። ፓርላማ ላይ ግሎባል የሆነ መንፈስ እናዳምጣለን፤ ፌስቡክ ላይ ሠፈር፤ መንደር ወዘተ። ይሄ አይደለም አብን ሊፈውስ ለኢትዮጵያም ክፋ #ቹፌ ነው። 
 
ልጅ ጋሻው መርሻ በማዕከላዊ ጎንደር ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የህወሃቱ የደህንነት አካል ሱር ኮንስትራክሽን በሠራው ሴራ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በማዕከላዊ ጎንደር 80000 (ሰማንያ ሺህ) ህዝብ ሲፈናቀል፤ አቧራ ለብሶ እዛው እየዋለ ሲሠራ ነበር። ሲያግዝም ነበር። ይህ ታሪክ ሊረሳው የማይችል የአብን ጉልህ ተሳትፎ ነበር። ቀውሱን የጠነሰሰው ህወሃት፤ ያደራጀው - ህወሃት፤ የመራው - ህወሃት ነበር። ጉዳቱ ከባድ ነበር። ሙሉ አንድ ዓመት ተማሪወችም መምህራንም ሥራ አልነበራቸው። ገበሬ መንደሮችን እያንዳንዳቸው በአካል አውቃቸዋለሁኝ። ፍጹም ደግ እና የሰላም ቀጠና ነበ
 
#አብን እና አዲስ አበባ።
 
አብን ክብሩን ለባልደራስ ገብሮ፤ አዲስ አበባ ላይ ራሱን ችሎ መወዳደር ሲገባው በአማራ ህዝብ ላይ የታሪክ እጥፋት ፈጠረ። አሳዛኝ ትራጀዲ ነበር። በ2013 ዓም የምርጫ ሂደት የአብን ዓርማ አዲስአበባ ላይ ታውሮ ነበር። በብዙ ሁኔታ ፖለቲካዊ ዕድምታው መጠነ ሰፊ ነው። ያን የመሰለ ዕድል በዛ መልክ አልፈስፍሶ፤ ዕድሉን ፈቅዶ እና ወዶ አፈሰሰው። 
 
#የአማራ ክልል 95% ሰላም ነው። (አቶ ጋሻው መርሻ)
 
ይህ #ስላቅ ነው። ይህ የብልጽግናን መንግሥት ማዘናጋት ነው። ይህ የአማራ ክልል በመንግሥት ተገቢውን ትኩረት በጸጥታው ዘርፍ እንዳያገኝ መሰናክል ነው። ይህ በጣም ስስ የሆነ የኃላፊነት እና የተጠያቂነት ሁነትን አጋላጭ እና አላጋጭ ምልከታ ነው። 
 
በአማራ ክልል የሚካሄዱ ጉባኤወችን የሚመራው እኮ በሠራዊት ነው። ይህ አንገት አያስደፋንም??? በመጀመሪያ ፋኖን ደግፈን ነበር ሲል ህዝብ፤ ሰላማዊ ታጋዩ አብን ምናችንም አልነበረም፤ ምርጫችን ፋኖ ነው ማለቱ እኮ ነው። በዚህ መሃል ያለውን ጋፕ በክንድ ሳይሆን በጋሻ ለኩት። ትልቅ የፖለቲካ ክስረት ነው። ያ እሳት የላሰ ትውልዳዊ ድጋፍ ባክኖ ቀረ።
 
"ከንቱ፤ የከንቱ ከንቱ፤ ሁሉም ነገር ከንቱ።"
 
ለመሆኑ ወንድም ዓለም የት ይሆን የባጀህው?#ጁቪተር ወይንስ ኡራኖስ ላይ???? አማራ ክልል ሰላም የሰፈነበት ቦታ የሰቲት ሁመራ ዞን ብቻ ነው። ምርጫቸውም ብልጽግና እንጂ አብን ከነመፈጠሩም ትዝ ብሏቸው አያውቅም። በፍጹም። ዞኑ ሰላም ነው ሲባልም እሱም ጠለምት፤ አዳርቃይ፤ ማይጠምሪ፤ አዲረመጥ፤ ዋልድባ አካባቢ ተጀምሮ እስኪጨረስ በህወሃት የስጋት ወላፈን እየተገረፋ ነው ያሉት። "ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ዘላለም ሲያለቅስ" ይኖራል እንዲሉ።
 
በተረፈ የአማራ ክልል ቋያ ነው። በመቼ ዘመን የተፈጠርክበት አካባቢ በድሮን አሳሩን ያዬው፤ በየትኛው ዘመንስ ይሆን ደብረታቦር ከተማ እንዲህ ጭስ እና አመድ ተመገቢ ተብላ የተበየነባት???? የመንግትሥት ተቋማት አመድ ሆነዋል። ሠራተኞች ሥራ ፈላጊ ናቸው። ህዝቡም ከአገልግሎት ውጪ። ስላቅ ከሆነ እንስማማ። ሰላምን በተለጠጠ ፕሮፖጋንዳ ማስከበር አይቻልም።
 
ህሊና፤ ውስጥነት ያስፈልጋል። መሃል ላይ ያሉ ብዙ መንፈሶች አሉ። አስተማማኝ መጠጌያ የሚሹ። አለኋችሁ፤ አይዟችሁ የሚል ዕውነተኛ አጽናኝ መንፈስ ይሻል። እናንተ ደግም የላችሁም። ያላችሁት "ትህነግ፤ ትህነግ፤ ትህነግ ……?" በልጧችኋል ያ የአማራ አንቱ ተቋም፤ የሊቃውንት ጉባኤ አንሶ አቶ እስታሊን እስከ መተማ ይመራችኋል። ይህ ክብር ይሆን???? 
 
ሰርክ የህክምና ባለሙያወች መርዶ አለ። ህፃናት ይታገታሉ፤ ይደፈራሉ፤ ይገደላሉ፤ እናቶች ከልጃቸው ተለይተው ይሰወራሉ፤ በመጨረሻም ልጆቻቸውን ትተው ይገደላሉ??? ይህ ጎምዛዛ ሃዘን ለድርጅታችሁ የቸኮሌት ኬክ ይሆን??? ግን የትላይ ይሆን ያላችሁት። አቤቱ ብልጽግና ያን የሚሊወን ንቅናቄ ባለእርስት ታደርጉልኛላችሁ ብሎ ሲጠብቅ እናንተ ወደ ወላጆቻችሁ ለመሄድ ዘበኛ አስፈለጋችሁ???? ይህን ስጽፍ በሠራዊቱ እገዛ ከተሞች ላይ ሄዳችሁ ህዝብ ሰበሰብን ልትሉ ትችላላችሁ። 
 
የእናንተ ነገር የሳሙና አረፋ ሆኖ ነው የቀረው። ለእናንተ የአብን ዓርማ #ፒን አሰርታችሁ ከገበርዲን ወይንም ከከረባታችሁ ላይ ማጌጫ ነው። በቃ። በምንም ታዕምር በዛ መራራ ተጋድሎ፤ በምን የተሰበሰበ ህሊና የአብን ሊቀመንበር ዶክተሬታቸውን እንደሰሩ ይገርመኛል። ቢሮ እየታደረ ሊሠራ የሚገባው ኃላፊነት እንዲህ የወለሌ ገበታ እንዳለ እንደ አነባ አረፈ። 
 
ሰላማዊ ትግል ማለት ሹመትን ተቀብሎ ጸጥ ብሎ መገዛት አይደለም። አልነበረምም። ያን ሁሉ ድካም አምክናችሁ፤ መሃንነቱ ላይበቃ በረዶ ውስጥ ጨመራችሁት። ዝም የምንላችሁ እኮ ሃሳብ ጠፍቶን አይደለም። አለመኖራችሁን ስላረጋገጣችሁልን እንጂ፤ አለን ስትሉማ ያልታያችሁን አለመኖር ራዲዮሎጂያችሁ እንሆናለን። የደከምንበት፤ የባተልንበት፤ ክፋ ደግ የሰማንበት ተጋድሎ ነበርና። 
 
ልጅ ጋሻው መረሻ ጦርነቱ ለዛሬ ብቻ እንዳይመስልህ። ድሮን የቀጠቀጣቸው በዕቶች በየትኛውም የአማራ ክልል ለቀጣዩ ትውልድ #ዕዳ ናቸው። የሚጸነሱ፤ የሚወለዱ ልጆች በአካልም በአዕምሮም የተጎዱ ይሆናሉ። ዓዝዕርቱም መሬቱ ስለሚመረዝ መርዝ አብቅለው መርዝ ይመግባሉ። ይህ ዛሬ ለአማራ ፖለቲከኞች አይገባችሁም። ዕዳው ግን 10/15/20 ዓመት ይሆናል። የማግሥት የአማራ ትውልድ ተፈጥሯዊ ጥንሰቱ ሳይቀር ጭስ ሲትጎለጎልበት ይታየኛል።
 
ከቃጠሎ በፊት እስቴ የቤተክርስትያን በዕል ነበር፤ ሃይማኖትህን ባላላውቅም የጥበብ ሰወች ከአዲስ አበባ ወደዛ ሲሄዱ ለምን አብረህ አልተጓዝክም፤ ስንፈት፤ የሥራ ብዛት ወይንስ ፍርሃት? ሰላም ከሆነ ማለቴ ነው? ሰላም በመፈክር አይቀሸርም። 
 
5 ሚሊዮን የአማራ ወጣት ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆኑ ሰላም ስለሰፈነ ይሆን? ብዙወቹ ታዳጊ ሴቶች ይደፈራሉ፤ ከዛ የዳኑት ወደ ከተማ ሰውነታቸውን የሥራ መስክ አድርገው ለመኖር ወስነው እንደሚንቀሳቀሱ መራራ ዘገባወችን አንብቤያለሁኝ። ሌሎቹ ደግሞ ጋብቻ እንዲፈጽሙ መገደዳቸውን አደምጣለሁኝ። የተደራጃችሁበት ዓላማ የት ነው ያለው? ሸፈተ ወይንስ ግዞተኛ ሆነ????
 
የደብረታቦር አልበቃ ብሎ የጎንደርን ጉሮሮ ለማነቅ #ወረታ ላይም የተፈጠረው ክስተት ዕውን ሰላም ስላለ ነው? ወረታ ላይ ሰሊጥም እንደ ጧፍ የነደደበት ጊዜም ነበር። ሰሊጥ ከቡቃያው ጀምሮ ጠንቃቃ ገበሬን ይጠይቃል። ሰሊጥ አፋን ከከፈተ ወደ በቀለበት መሬት ይመለሳል። ያን ፈተና አልፎ ለውጭ ምንዛሬ የተመረተ ጥቃትን አስተናገደ። ለህወሃት ሠርግ እና መልስ ሆነ።
 
#የአማራ ክልል የየከተሞች ስብሰባ እና ዕድምታው ለአብን ምን ግብረ መልስ ሰጠው ይሆን?
 
በነገራችን ላይ እንደ ጯሂት ስብሰባ የገረመኝ የለም። የጯሂትን ሰላም ማስቀጠል አቅቶ???? እግዚኦ ነው። የሆነ ሆኖ አማራ ክልል ላይ የተካሄዱ ውይይቶች ለአንተ ግድ እንዳልሰጠህ ተገንዝቤያለሁኝ፤ ወይንም በአወንታዊ አይተኽው ሊሆን ይችላል። 
 
ለመሆኑ በአማራ ክልል በትናንሽ ከተሞች የተካሄዱ ህዝባዊ ስብሰባወች ሂደት ላይ አጀንዳ ይዛችሁ ተወያያችሁበትን? በምን ወርድ እና ስፋት??? ደብረታቦር ላይ ህዝባዊ ስብሰባ በተካሄደ ወር ሳይሞላ ነው ደብረታቦር ከተማ በጭንቀት ተገርፋ የነደደችው። ለመሆኑ አንተ እስቴ መሄድ ብትፈልግ ካለ ሠራዊት አጀባ መሄድ ትችላለህን???
 
የሁሉንም የአማራ ክልል ስብሰባወች፤ ስብሰባወች ተቆርጠው በዜና መልክ የቀረቡትንም በሙሉ አዳምጫለሁኝ። አብን አብሰንት ነበር። የአማራ ህዝብ ከነመፈጠራችሁ ረስቷችኋል። የገረመኝ የምርጫ ውድድር ላይ ገበርዲን ለብሳችሁ መታደማችሁ ነው። ማን አላችሁ? ምንስ አላችሁ እና………? እራሱ ብልጽግና አይዞህ ያላችሁትን አቅም አምኖ የነበር ይመስለኛል። ግን ምንም። {}።
 
ኦነግ ከወንበሩ ቁጭ ብሎ ብልጽግናን እያዘዘ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በጥድፊያ እና በትጋት እያሠራ ነው። እዛም ጦርነት አለ። የእናንተ ነገር ጽድቁስ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ ነው። ለውጡ - ምንጩም - እርገቱም በልባሞች የተሠራ ክንዋኔ ሆኖ ያን ለድል የሚያበቃ ብቃት ከርስተ - ኢህዴግ፤ ከልጁም ከአብን አልተገኘም። 
 
አንዲት ጥያቄ ሳታስመልሱ በቃ! ሙሉ 7 ዓመት እናንተን አሹልኮ ነጎደ። ያ ሁሉ ድካም ለዶር በለጠ ሞላ የሚኒስተርነት፤ የክብር የልዕልና ሹመት፤ ብርቅነት፤ ለጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ልባዊ ወዳጅነት አልነበረም። ቢያንስ እየፍተለተለ፤ እየተበተበ፤ እየተልፈስፈስ ያለውን "የወልቃይት ብረሳሽን" ቃልኪዳን እንኳን ለፍፃሜ ለማድረስ አልቻላችሁም።
 
ለመሆኑ ደብረብርሃን ላይ ያሉ ምንዱባንን ፕሮግራም ይዛችሁ አይታችኋቸው ታውቃላችሁን?
 
ወለጋ ላይ ወላጅ አልባ ልጆችን አቋጥራችኋቸው ታውቃላችሁን? 
 
የፖለቲካው ውክልና ቀርቶባቸው ደራ፤ አጣዬ፤ ኤፍራታ ወዘተ ያሉ በየጊዜው በስጋት ለሚናጡ ወገኖቻችሁ አጽናኝነታችሁን መግባችኋቸዋልን?
 
እንደ ሃይማኖታተቸው ፆም ፍች ላይ ተፈናቃይ ወገኖቻችሁን አይታችሁ ታውቃላችሁን? 
 
የነገረ አማራ አመክንዮ #አጀንዳችሁ ነው ---- ወይ???
 
ሙሉ አማራ ክልል በመፈናቀል ላይ ነው ያለው ሃይቅ፤ ወረባቦ፤ ራያ፣ ጠለምት፤ ደባርቅ ትዝ ብለዋችሁ ያውቃሉን? ሰርክ አንተ እራስህ ትመላለስበት የነበረውን የጎንደር ከተማን ካዬህው ስንት ጊዜ ------ ሆነህ?
 
አልሰማህም ጎርጎራ ላይ በተካሄደው ጉባኤ ላይ? "ቆላድባ ናፍቃናለች" ሲባል? ከጎንደር - ቆላድባ፤ ከቆላድባ - ጧሂት፤ ከጧሂት - ጎርጎራ፤ ከጎርጎራ - ደልጊ በየብስ መንቀሳቀስ ይቻላልን?
 
ከጎንደር ጸዳ - ከጎንደር እንፍራዝ - ከጎንደር ማክሰኝትስ???? ከጎንገር ባህርዳር ፍኖተሰላም ማርቆስ ገብሬጉራቻ አዲስ አበባ፤ ከወሎም እንዲሁ ካለ አጃቢ እንኳን ሌት ቀን ይደፈራልን??? በቋሚነት ትኬት ቆርጦ በአውቶብስ ገመድ ገዝቶ የመጓዝ ያህል ነው። ሰው በአውሮፕላን የሚችለው ብቻ ይጓጓዛል።
 
በዓለ ጥምቀት ጎንደር ላይ መንግሥት ሌት ተቀን ለፍቶ ነው ያሳካው። ደክሞ። ጎንደር ደሴት ሁናለች። ነገ የማትገኝ ከተማ ያለባት የጸጥታ ችግር ጎን አያሳርፍም። ነዋሪው ጉሮሮው ቱሪዝም ነው። ሰላም ከሌለ እንደምን የኑሮው ውድነት ይቻል። መኖር እኮ ማይክ ሳይሆን እህል ውሃ ያስፈልገዋል። የፖለቲካ ድርጅት ሥራ እዛው ቢሮ እየታደረ፤ የህዝቡን ኑሮ እየተኖረ እንጂ በግምት አይሆንም።
#አማራ ክልል በአስቸኳይ ጊዜ ሥር ነው ያለው። 
 
ዕውነቱ ያ ነው። መከላከያ ከተማ ሲጠብቅ ውሎ ያድራል። ፖሊስ ምን እንደሚሠራ አላውቅም። ክልሉ ላንቁሶ ነው። እራሱን ችሎ መቆም አይችልም። መከላከያ ከተሞችን ቢለቅ ምን እንደሚሆን አማራ ክልል አላውቅም???? የላችሁም - እናንተ። የአማራ ጥያቄ እና የእናንተ እንደ ድርጅት የአብን አቅም ከማይክ ውጭ ክህሎቱም፤ ብልህነቱም - ችሎታውም የለም። አልተመጣጠናችሁም።
 
በዬስብሰባው ህዝቡ ወጥ ሃሳብ ነው ያቀረበው " ሠራዊቱ፤ ፋኖ፤ አድማ በታኝ፤ ሚሊሻ፤ ፖሊሱ" የእኛ ናቸው። እናንተን ያነሳ "አብን" ያለ አንድም ሰብ የለም። በአማራ ህሊና ተሰርዛችኋል። ድንኳን ጥላችሁ ሃዘን ልትቀመጡ ሲገባ 95% የአማራ ክልል ሰላም ነው። ደንበር በሚጠብቅ ሠራዊት 24 ሰዓት ሌት ተቀን እየተጠበቁ ከተሞች። 
 
ይህም ስለሆነ በጣም ጊዜ ሰጥቼ ካዳመጥኩ በኋላ ነበር የኢትዮጵያ መንግሥት ብሄራዊ የምህረት ዓዋጅ፤ እራስን የማገለጥ ሁነት ይፍጠር ያልኩት። የህዝብ ቁጥር ሳይሆን የአማራ ህዝብ መንፈስ ከአብን፤ የአማራ ህዝብ ከመንግሥት ጋር ከማን ጋር ያለው? መመዘን፤ መሰፈር ያለበት ከዚህ አንፃር ነው። እንደምን ማቀራረብ ይቻላል? በሳል መሪ ይጠይቃል። ብልህ የቲም አመራር ይጠይቃል። 
 
የሰጠኽው መረጃ ፍጹም የተሳሳተ የመንግሥትን መዘናጋት ፈጥሮ የአማራ ህዝብን ለከፋ አደጋ የሚያጋልጥ ነው። ህዝብ ፋኖን "ልጃችን፤ የወንድም እህታችን ልጅ፤ እራቅ ሲል የአጎት አክስታችን ልጅ ነው፤ ካህኑም ይህን ሂደት እንደ ሰማዕትነት አይቶ መርቆ ይልካል፤" ይህን ነው ያዳመጥኩት። በየትኛው ካልኩሌተር፤ በየትኛው የጥናት ቴሰስ ይሆን ይህን መረጃ የምትሰጠው??? "95% የአማራ ክልል ሰላም ነው።" ፋንታዚ ነው። 
 
 
ህዝብ ጥልቀት ባለው በፍርሃት ቤርሙዳ ትርያንግል ውስጥ ነው። መገመት ከሚችለው በላይ የአማራ ህዝብ በጭንቀት ውስጥ ነው። ሁለት ነገር ላንሳ ……?
 
1) መንግሥትን ቢወቅስ ዕዳውን ማን ይሸከምለታል?
 
2) ፋኖን ቢነቅስ የት ውሎ ሊያድር? 
 
3) ሌላው ቀርቶ ውጭ አገር የሚኖሩት ሁለቱንም ፋኖንም የኢትዮጵያ መንግሥትንም ፈርተው በማይነገር በጸጥታ አፍ ባለው መቃብር ውስጥ ነው የመናገር ነፃነታቸው። 
 
ይህን ምጥ እንዴት? በማን አመካኝነት መገላገል ይቻላል? 
 
እራሱ የብልጽግና መዋቅር "ቀኜ" በሚባል የተደራጄ ቡድን እንደሚመራ ነው እኔ ያዳመጥኩት። ይህ ከባድ ሁኔታ በግልብል - ዕሳቤ፤ በግርድፍድፍ ሁነት መፍትሄ አያገኝም። ሙሉ ፰ ዓመታት እናንተ ለሽ ብላችሁ እንቅልፋችሁን ስትለመልጡ ህወሃት በአማራ ክልል የራሱን ሴል አደራጅቶ የአማራን ህዝብ ሰላም ብቻ ሳይሆን ሥልጣኔውን አመድ እያደረገው ነው። ይህ ጥቃት አያንገበግብም? ይህ ጥቃት አይቆጭም? ይህ ጥቃት እንቅልፍ ያስተኛልን??? 
 
ይህ ክብር አይደለም።
ይህ ሞገስ አይደለም።
ይህ ልብን ሞልቶ የሚያናግር አይደለም።
 
ወይ ደብቁኝ - ሊያሰኝ፤ ወይ በቁጭት ተነስቶ በሳል የመፍትሄ ፖለቲካዊ አቅጣጫ ነድፎ ወደ ተግባር መለወጥን ይጠይቃል። ለነገሩ መሽቷል። በውነት ለአብን መሽቶበታል። ዕውነት ለመናገር አብን ለብልጽግናም ያስተረፈው የፖለቲካ ዕሴት የለውም። ብልጽግናም በአብን ተማምኖ አማራ ክልል ላይ መለመላውን ነው የቀረው። የሰቲት ሁመራ ዞን በጠንካራ አይበገሬ አመራሮቹ ጸንቶ ይገኛል።
 
አብይዝም ከአባይ ወዲህ ይበቃኛል ካላለ በስተቀር የተሰበረውን የአማራ ህዝብ እና የኢትዮጵያ መንግሥት ድልድይ ጠግኖ ለማስቀጠል ብሄራዊ የምህረት ዓዋጅ የግድ ነው። አብንም ምንም ላይ ሆኖ የሚያበረክተው አንዳች ነገር ስለለ ህዝብ የሚድንበት አዲስ ብልህ ሌላ፤ ፍጹም ሌላ መስመር ለአማራ ህዝብ ሊዘረጋለት ይገባል። ተክዷል። በተራራቀ መንፈስ ተደጋግፎ ትውልድን ማስቀጠል ስለማይቻል፤ ኢትዮጵያም ከአማራ ንጥረ ነገር ንጥፈት ካላሰኛት በስተቀር ይህን በኽረ ጉዳይ ቸል ልትለው አይገባም። 
 
ጭራሽ የአማራ ክልል መንግሥት የማይቆጣጠራቸው ቀበሌወች እንዳሉስ ማህበረ - አብኖች አታውቁምን???
 
አብን ልዩ የሚስብ፤ የሚያሰባስብ፤ ደማቅ ህዝባዊ ንቅናቄ ነበር። በጣም በብዙ ሰው ዘንድ ተስፋ የጣለበት። ተወዳጅ የነበረ ንቅናቄ። እማረሳቸው ወጣቶች ነበሩ። ብቁ። እርግጥ ነው ሲመሠረት ከሌላ ድርጅት የመጡ አባሎቹን ኃላፊነት መስጠቱ በወቅቱም ጽፌበታለሁ፤ የተጋባ አልነበረም። በሌላ በኩል አብንም አካላቱም በመስዋዕትነት ውስጥ ተፈትነው ሳያልፋ የተሰጠው ድጋፍ እና ያገኜው ተቀባይነትም በራሱ ችግር ፈጣሪ ነበር።
 
አብን የገዘፋ የአማራ ህዝብ ጥያቄወችን ሥልጣን ላይ ካለው የብልጽግና መንግሥት አካል ጋር ተደራድሮም ይሁን ተፎካክሮ ለማስመለስ ጥረቱም ስኬቱም አልቦሽ ሆኖ ቀርቷል። ሲዳማ እኮ ጠብታ መስዋዕትነት ሳይከፍል፤ በደመቀ ምጣድ ከች ብሎ ዕውቅና ያለው ተግባርም ሳይፈጽም ለድል በቅቷል። ያ "ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳሽ" ሂደቱ ከብሮ፤ ለስኬት ይበቃ ዘንድ ጨምቶ በተከወነ ፖለቲካዊ ተግባር ህወሃትን ከመንበሩ ቢነቅለውም፤ የተነሳበትን ዓላማ ለማሳካት ግን መሪ አጥቶ እንዲህ ፈሶ ባክኖም ቀረ። አሁን እንደ ጢባጢቦሽ ኳስ የማዝናኛ ኢቬንት ሆኗል።
 
ይህም ብቻ ሳይሆን ሰላማዊ ንቅናቄወቹ በራሱ በአብን እያታገቱ በሩ ተዘጋ። አብን ለአማራ ህዝብ ሰላማዊ ንቅናቄ ጣልቃ እየገባ የጉሮሮ አጥንት ሆኖ ስብሰባወችን ቋንጃ ሲሸበሽብ ነበር። ለራሱ መሠረት እራሱ ታግሎ አደበዘዘው። በምን አቅሙ ነው የተደላደለውን የብልጽግና ፖለቲካ ድርጅት መሞገት የሚችለው? ምን አለው? ማንስ አለውና???
 
ምን ያልተደረገ አለና። "ራስ ሳይጠና ጉተና" ሆኖ በመጨረሻ እራሱ አብን ፈቅዶ የደረበው ባልደራስ ለእራሱም ይሁን ለአማራ ተጋድሎ ፈተና ሆኖ አረፈው። የአማራ ህዝብ አሁናዊ ሁኔታ በመሪ እጦት ከነበረውም በሚያሳዝን ሁኔታ ይገኛል። በ60 ዓመታት ውስጥ በሰላም ቀጠና የሚታወቁት ሁሉ የአማራ አምራች በዓቶች ሁሉ የባሩድ መሞከሪያ ጣቢያ ሆኑ። የድሮን መፈተኛም። ቅድስት ኦርቶዶክስም ሌላ ፍጹም ሌላ ዓይነት መስዋዕትነት ከፈለች።
 
በቆረጣ የተገባው ሃዲድ ሁሉ ትርፍ አልቦሽ ድካም ብቻ ሳይሆን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በነፍስ ወከፍ ሳይቀር በራሱ በክልሉ ስጋት ቀሰሰ። ከክልሉ ውጪ የሚኖሩ አማራወች ጉዳይማ ሰማይ ላይ የተንጠለጠለ ዳቦ ሆነ። ይህ ክብር ሆኖ ሚዲያ ላይ ሊያስገኝ የሚችል አይደለም።
 
#የሁለቱ በሚኒስተርነት ማዕረግ የራያወች ፍልሚያ።
 
ለነገሩ ራያ ባይሆን ዶር በለጠ ሞላ የሚኒስተርነት ማዕረግን አያገኙትም ነበር። ለዛውም የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ርስትነት በመሪነት ህልም ነበር። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ "ውዴ" ለሚሏቸው ታማኞቻቸው የሚሰጡት ብቸኛ ተቋም ነው። ደህና አድርገው፤ የትውልድ አድርገው በእጃቸው የሠሩት ተቋም ነው። እዛ ሳሉ የነበራቸው ሰብዕና፤ ትህትና፤ አዛኝነት እንደናፈቀኝ ሳልጠግበው መነነ።
 
የሆነ ሆኖ ሰሞኑን ሁለት ራያወችን በሚኒስተርነት ማዕረግ ብልጽግና የማን ደም ፈሰሰም እያሰኛቸው ነው። አጋጠመህ ብልፄው! ትወደዋለህ ----- እና፤ ትፈልገውማለህ እንዲህም እንዲያም ……
 
አቶ ጋሻው መርሻን በሚመለከት በሙሉ ህሊናዬ ከ15 ዓመታት በላይ የምከታተላቸው ሚዲያወች ተበሳጭተው ያስተላለፋትን የእላፊ ንግግር ሳዳምጥ በውነቱ ሰቀጠጠኝ። በሌላ በኩል ብስጭት አይሎ ስድቡ፤ ውርዴቱ፤ ማቃለሉ አይጠቅም ለትውልድም፤ ለትውፊትም።
ይህን በተለይ ትላልቅ ዕድሜ ጠገብ ሚዲያወች ለልጅ ጋሻው መርሻ ተብሎ ሳይሆን አክሰሱ ላላቸው ልጆች ዕዳ ማስቀመጥ ስለሆነ ለወደፊቱ ቢያስቡበት መልካም ነው። ለማይረዳ ነገር፤ ለማያተርፍ ጉዳይ ጊዜ ማባከንም አይጠቅም። ተወቃሹንም አያርምም፤ አያስተምርም። ዛሬን ፈቅደን ገድለን፤ የነገን ኢትዮጵያ በተስፋ መጠበቅ ሹልከት ነው። "ሰው የዘራውን ያጭዳል።" መምህራችን ነው።
 
#ክወና። መተዛዘን ይቅደም። 
 
ሰው እራሱን ሊከላከል በማይችልበት ሁኔታ እያለ እጅግ በገዘፈ ኢሹ መክሰስ በፍጹም የተገባ አይደለም። አቶ ጃዋር መሃመድ እስር ቤት እያለ፤ አቶ ኦባንግ ሜቶም ኢትዮጵያ እያለ፤ ጋዜጠኛ አበበ ገላውም ኢትዮጵያ እያለ እነሱን የሚያሳጣ ፍሬ መረጃ ተሰጠ። በሚዲያ። ያን ቀን አልተኛሁም። ፃፍኩበትም። የተወሰነው ፍሬ ነገር አስብሎ ስኬት እንዳገኜላቸው ባለመረጃወች አይቻለሁኝ። በአሁኑ ወቅት አቶ ኦባንግ ሜቶ የት ነው? መልስ የለም። 
 
የሆነ ሆኖ እስር ቤት ያለወገን የሚፈልገው እርዳታ ከኖረ - ማገዝ፤ በስተቀር ዝምታ ማንን ገደለ? የፖለቲካ ድርጅት አባልነት፤ ጓዳዊነት እናት ወልዳ እህት፤ ወንድም ከምትሰጠው በላይ የቅርብ ነው። የውስጥም ነው። ዛሬም እኔ ለጓዶቼ ስስታም ነኝ ለዛውም በአክብሮት። ለነገሩ የዘመኑ የፖለቲካ ድርጅቶች ደንብ የሚባልም ያላችሁ አይመስለኝም።
 
መጨካከን! ለምን?
 
ዘለፋስ! ለምን?
 
በግራ ቀኙ ጎራ ያዬሁት ጉዳይ ያረገረገ ወይንም የዘበጠ ነው። ከደከምን ላይቀር፤ ጊዜ ጉልበት ማፍሰስ ካልቀረ ትውልድን - ታሪክን - ትውፊትን - አደራን ሰውን - ሊያተርፍ፤ ሊያስተምር የሚችል ሊሆን ይገባል።
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
03/03/2026
 
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ፍቅር ሲያልቅ ትዕግሥት፤ ይሰደዳል።
ትዕግሥት ሲያልቅም ፍቅር፤ ይሰደዳል።
"የአማራ ክልል 95 በመቶ አካባቢ ሰላም ነው" ጋሻው መርሻ የአብን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ»
#ብሄዊ የምህረት ዓዋጅ አስፈላጊነት እና፤ ለአፈፃጸሙ አክብሮትን ስለመመገብ።
"የአማራ ክልል 95 በመቶ አካባቢ ሰላም ነው" ጋሻው መርሻ የአብን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ - BBC News አማርኛ

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።