#ፕሮቶኮሉ እንደ ኢትዮጵያዊ አልተመቸኝም።

 

#ፕሮቶኮሉ እንደ ኢትዮጵያዊ አልተመቸኝም።
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 
#ምዕራፍ ፲፱።
 
“PM Abiy Appointed AU Champion for AI and Digital Health.”
«ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአፍሪካ የAI እና ዲጂታል ጤና መሪ ሆነው ተመረጡ | PM Abiy Ahmed AU Champion |”
 
#የሹመቱ ፕሮቶኮሉ በፍጹም አልተመቸኝም። ኢትዮጵያ መመረጧ መልካም ነገር ነው። በዘርፋም ጥረት እንደ አለ እከታተላለሁኝ። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድም በዲጅታል ደህንነት ላይ የሠሩ፤ ሙያውም ያላቸው ናቸው። ከፍ ያለም ዝንባሌ እንደ ነበራችው ቀደም ባለው ጊዜ አስተውል ነበር። እዚህ ደረጃ ሳይደርሱ እከታተል ነበር። 
 
በተለይ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስተር ሳሉ። አንድ ብሄራዊ ውይይት አዘጋጅተው ነበር። "#ከእርምጃ ወደ ሩጫ" የሚል ሞቶ የነበረው። ይህን ዕርስ ወስደው ስለ አባይ ግድብ ውይይት ሲደረግም ያዬሁ ይመስለኛል። ባለቤቱ እሳቸው ናቸው እና በትምህርተ - ጥቅስ ማስገባት ይገባል። ሥንኙን መጠቀም የሚሹ ግለሰቦች ይሁኑ ሚዲያወች። እንዲህእንዲህ ዓይነት ሞቶ ዶክተር አብይ ይወዳሉ። "ከጎዳና ወደ ፓርላማም ብለውን" ነበር። ሂደቱ እራሱን የቻለ ፈተና ገጥሞታል።
 
የሆነ ሆኖ በዛ " ከእርምጃ ወደ ሩጫ" በጉባኤውም፤ ከዛም በኋላ በአገኙት የሚዲያ አጋጣሚ ሁሉ በዲጅታሉ ዘርፍ ዓለም ጥሎን እንዳይሄድ የቀረንበትን አስተካክለን አብረን መጓዝ የሚያስችል እርምጃ መውሰድ ካልቻልን፤ መጪው ጊዜ አብሮ ለመራመድ ይቸግረናል ሲሉ ከ10 ዓመት በፊት አዳምጫለሁኝ። አሁን ጠቅላይ ሚኒስተር ሲሆኑ በሙሉ አቅም እየሠሩበት ነው። 
 
በዚህ ይመስለኛል የአፍሪካ አንድነት ይህን "#ሹመት" የሰጣቸው። ሹመቱ #ለኢትዮጵያ ቢሆን መልካም ነበር። ይህ ማለት እኮ በአፍሪካ አንድነት መሪ #ሥር የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ አመራር እየተቀበሉ መሥራት ነው ቀጥተኛ ትርጉሙ። ይህ ነው እኔን ያልተመቸኝ። ልክ እንደ ኢጋድ ጸሐፊ ዶር. ወርቅነህ ገበዬሁ ማለት እኮ ነው። ለእኔ የሚገባኝ እንደዚህ ነው። 
 
አሁን ዕድሉን ያገኜችው ጁቡቲ ናት። ለእኔ ግብረ መልሱ የሰጠኝ ምላሽ ምቾት አልሰጠኝም። የብልጽግና ደጋፊወች በደስታ ነበር ሲዘግቡት የነበረው። 
 
ኢትዮጵያ #ተመረጠች ቢባል እኔ ደስ ይለኛል። ከእነ ኢኮኖሚ አቅሙ ማነስ፤ በዘርፋ ከሚደርሰው የፍትህ አፈፃጸም ጫና፤ ካለው የነፃነት ልክ ጋር እንኳን ሳላነፃጽር #ኢትዮጵያ ተመረጠች መልካም ዜና ነው። በተመረጠችበት የሥልጣኔ ልክ ዘርፋን ለማስቀጠል ሁኔታው እስከፈቀደላት ድረስ።
 
ግን የአንድ አገር መሪ፤ የጦር ኃይሎች አዛዥ በበአፍሪካ አንድነት በቴክኖሎጂ መምሪያ ሥር፤ ከዛ በላይም ሌላ ሰብዕና ኖሮ በመሪውም ሥር መሆን አይመችም። #የፕሮቶኮል ዝንፈት አለበት። የአንድ አገር የውጭ ጉዳይ የነበሩሰብዕና፤ በተጨማሪም እሱ ከሚመራቸው ዋና መምሪያወች ሥር የኢትዮጵያ መሪ???
 
ባለፈው ጊዜም አንስቸው ነበር። ዕድልን #መምለጥ ብልህነት ያነሰው ጉዞ በሚል ጭብጥ አንድ የወግ ገበታ ጽፌ ነበር። ቦታውን ኢትዮጵያ ልትወዳደርበት ትችል ነበር እኮ። አይደል? ዕድሉም ሰፊ ነበር። ፕሬዚዳንት ታዬአጽቀ ሥላሴ፤ ወይንም የቀድሞዋ ፕሬዚዳንት ክብርት አንባሳደር ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴን አወዳድሮ ማሸነፍ ይቻል ነበር። ያ ቢሆን ኢትዮጵያ በየትኛውም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጉባኤ #ሁለት ድምጽ የመግባት ዕድል ይኖራት ነበር። ሌላም ሌላም። ታሪካዊ ክስተትነቱም ልዩ ግርማ ሊኖረው ይችል ነበር።
 
ኢብን ይህ ዕድል ኖሮን ቢሆን፤ ኢትዮጵያዊ ይዞት ቢሆን እንኳን ለኢትዮጵያ መሪ ደረጃው #አይመጥንም። ሌላ ሰው ከተግባሩ ጋር ቅርርብ ያለው፤ #በIT እንዲሁም በጤና ዘርፍም ጥምር ዕውቀት ያለው ኢትዮጵያዊ መወከል ነው የነበረበት የኢትዮጵያ መንግሥት። የሚመዘገበው እኮ በጠቅላይ ሚኒስተር አብይ ዘመን ይባላል። የአባይ ግድብ ወደ ሥራ የገባው በቀድሞው ጠቅላይ ሚር መለስ ዜናዊ ዘመን እንደሚባለው ማለት ነው።
 
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ በIT ሙያው ቢኖራቸውም በጤናው ዘርፍ የሉበትም። ሙያው ደግሞ የራሱ ኤቲክስ፤ የራሱ ፍልስፍና ያለው ጥልቅ ነው። ዶር አብይ እንደ አገር መሪ ጥቅል መረጃ ሊኖራቸው ቢችልም ሙያዊ ዕውቀት ብቻ ሳይሆን #ክህሎት ይጠይቃል።
 
ኢትዮጵያ ጀማሪ በመሆን ደረጃ ከተመጣም ብቸኛዋ " የሰላም ሚር" የፈጠረች፤ በጀት መድባ የምታሠራ ግን ለስኬት ለአቅመ አዳም ያልደረሰ ተቋም ነው የሰላም ሚኒስተሩ ጽህፈት ቤት። ሲጀምርማ የኢትዮጵያን ወሳኝ የሆኑ አንከር ጉዳዮችን ተጠቅልሎ የተሰጠው ነበር።
 
 ለአንድ ሚኒስተር። በዘርፋ ሚኒስተር መ/ቤቱ ምን አተረፈ? ያ ሁሉ ባጀት፤ ያ ሁሉ የሰው ኃይል ተመደበ፤ ግን ሰላም እና ኢትዮጵያ? ለመሆኑ #ብቸኛው ኢትዮጵያዊው የሰላም ሚኒስተር ለመሆኑ #ትርታው አለን?
 
ይረሳል። አንዲት ቀን ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ የዓለም የሰላም አባት ሎሬትነታቸው ትዝ ብሏቸው አያውቅም። ሽልማቱ የኖቤል አንስተውት አያውቁም። እሱን የፈለጉት ለዛ ወቅት ብቻ ነው።
 
ይህ ሹመትም "መሪያችን በአፍሪካም ስለነገ ሥልጣኔ ተመረጠ፤ ብልጽግናን ይምረጡ! ብልጽግናን መምረጥ ማለት ነገን መምረጥ ማለት ነው፤ ይህን መሰል ዕውቅና አገር እንድታገኝ …" ለማለት ለሰሞናት ሆኖ እንዳይቀር ምኞቴ ነው። ምክንያቱም ዘርፋ ከአንድ ሰብ ክብር በላይ የአፍሪካን የነገ የጭንቅላት አቅም የሚቀርጽ ስለሆነ። 
 
ይሄ ለጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ " ክብር " ነው ብዬ አላስብም። ሹመቱ ደረጃውን የጠበቀ ነው ብዬ አላስብም። ሌሎች ኢትዮጵውያን ሊሸፍኑት የሚችሉት ቦታ ነው። በቅርብ በማማከር ማገዝ ይቻል ነበር። 
 
ጠቅላይ ሚር አብይ ተሾሙበት የተባለው አህጉራዊ ኃላፊነትም ዘርፋ #ሰላም ያስፈልገዋል። እጅግ የላቀ፤ ሥልጡን ዩንቨርስን የሚያመሳጥር ነውና። የውስጥ፤ የህሊና ሰላም ይጠይቃል። ጸጥታ እና ቁጭ ብሎ መሥራትንም ይሻል። የመስክ ተግባር አይደለም። ሙያው ከህሊና ማሳ ጋር የተዋህደ ነው። 
 
የሆነ ሆኖ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዛሬ ባለው አብይዝም #ፕሮቶኮል ክፍተት አለበት። እራሱን አስችዬ ጽፌበታለሁኝ። ዲስፕሊን ስለሆነ። ልቅ የሆኑ ሁነቶች አደጋ አላቸው። የሚሰበስብ ልጓም፤ ማህለቅ ያስፈልጋል ለአመራር። ለነገሩ ጠቅላይ ሚኒስተሩም ለፕሮቶኮል የሚመቹ አይመስለኝም።
 
የሆነ ሆኖ በዚህ መሰል አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ፕሮቶኮል መጠበቁ ከአገር ብሄራዊ #ልዕልና ጋር ሊታይ ይገባል ባይ ነኝ። የክብር ጉዳይ ነዋ። ለመታዘዝ መፍቀድ፤ ይሁንታ መስጠት መልካም ቢሆንም፤ ብሄራዊ ውክልና ላለ ቁንጮ ሰብዕና ግን ጥንቃቄ የሚጠይቁ ረቂቅ ጉዳዮች አሉበት። ኢትዮጵያ ተመረጠች። እሰየው። ወኪሏ ደግሞ #እከሌ ከኢትዮጵያ ቢባል ይሻላል።
 
እንዴት ዋላችሁ ማህበረ ቅንነት?
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
 
ሥርጉ©ተሥላሴ።
Sergute©Selassie.
01/05/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ዕውነት ወጌሻ ወይንም ጋራጅ አያስፈልገውም።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።