#እናታዊነት ታላቁ የህላዊነት ህቅታ፤ ኖታዊ አንከር፤ #የትውልድም እዮራዊ ብራ!
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፈጠርልኝ።" አሜን።
#ምዕራፍ ፲፱።
እናትነት የርህርህና፤ የደግነት፤ የፍቅር ኃላፊነትን ጠንቅቆ የመወጣት እዮራዊ አቅምን፤ ክህሎትን፤ ብቃትን፤ ልቅናን በልዕልና የሚያመሳክር፤ የሚያነብ፤ የሚተረጉም እና የሚያመሳጥር ፍፁም የሆነ ጸጋ ነው።
እናትን በትክክል ሊገልጹ የማይችሉ ቃላት፤ ሐረጋት፤ ሥንኛት፤ ቅኔያት ሁሉ ሊገልፆዋት አለመቻላቸው ይገርመኛል። ይደንቀኛልም። የሰው ልጅ መቻልን የሰጠው በቻለው ልክ ስለመሆኑ የሚያመሳጥርልንም እናትነትን በሚስጢሩ ልክ ሊሸከም የሚችል አቅም የፊደል ገበታ አለመኖሩ ነው። ታዋቂው የራሺያ ጸሐፊ ፑሽኪን ማስተር ፒሱ "#እናት" የሚለው መጸሐፋ እንዲሆን ያደረገው በእሱ ልክ ለመግለጽ አቻ ከዛ በፊት ያልነበረ መሆኑ ይመስለኛል።
ያም ሁኖ ከዛም በፊት ይሁን ከዛም በኋላ መጸሐፍት፤ ፊልሞች፤ ተውኔቱች በዓለም በእናት ዙሪያ ተሰርተዋል። ጥያቄው የእናትን እናታዊ እዮራዊ ጸጋ መተርጎም ችሏል ወይ ነው ቁምነገሩ። ዕውነት ለመናገር እኔ ድሮ ……… ድሮ ዜማወች፤ መጸሐፍት ስለእናት የገለፆዋት ይመስለኝ ነበር። እናቴን የበሞቴ ልዕልቴን፤ የእሽታ ንግስቴን፤ የናፍቆት እመቤቴን እቭዬ ሆዴን በሥጋ ካጣሁ በኋላ ግን እናት ተመስጥራ የምትገኝበት ቀመር መኖራችን ትንፋሹን፤ ህቅታውን አስቀጣይ ሌላ ተጨማሪ ሚስጢር ሆኖ ነው ያገኜሁት።
#እትብታዊ ፍልስፍናዬ ለ፬ ዓመታት እራሴን የሞገትኩበት።
እናት እና ስደት በእናት ህልውና ብቻ የታነጸ ነው። እናት ጋር መራራ ስንብት ሲሆን ቀጥ ይሆናል። ቃ ይመጣል። ዳ ያሸንፋል። ውበት ይሸበሸባል። እራስ ይጠፋል። ዙሪያ ገባው ፈተና ይሆናል። ከዚህ አንፃር አገርንም ትመረምሯት ዘንድ ይገባል። ዛሬ አገር አለን። ዛሬ ባለ አገር ነን። ዛሬ ተቀበልናትም አልተቀበልናትም፤ ተሰደድንም እዛው ኖርን እትብት እትብት ናት። ስንሰደድ የመጀመሪያው ጥያቄ ዜግነት ነው። ያ መልስ ካላገኜ ስደተኛ ሂደቱ አይጀመርም።
ተሰደን ባለንበት አገር ችግር ቢገጥም ዙሮ መግቢያ የእናት ጓዳ ነው። ቢያንስ ለመንፈሳችን አገር አለኝ ማለቱ አልሚ ምግብ ነው። ሁልጊዜ እማነሳት የራዲዮ ጋዜጠኛ ኩርድሽ ባልደረባዬ እረፍቴ ይህችን ዓለም ስሰናበት ትላለች። ብትን አፈር መኖር የመኖር ህቅታ ነው።
የፈላስፊት፤ የሳይንቲስቷ ባለ ይሉኝታ ማርዳዋ የኢትዮጵያ ልጅ መሆን በአፍሪካ፤ #በጠይም ዕንቁው ዓለም ያለው ማህባ እኛ ብናውቅበትም ይሁን ባናውቅበት መለዮችን ነው። ካጣነው ግን አይደለም ከቀደምቶቹ ተርታ በቅርብ ከተፈጠሩት ከእነ ደቡብ ሱዳንም ጋር መለካካት አይቻልም። ለሁላችንም እናታዊ አገር #ቅርባችን እንጂ ሩቃችን ልትሆን አይገባም። የልጅነታችን በኽረ አመክንዮ ፈቃድ ሰጪም ነሺም ባለመብት የለም። የዜግነት እርቦ እና ሲሶ ስለለው። ሁላችንም በዜግነት እኩል ነን።
#የሆነ ሆኖ በእናት በሥጋ መለዬት እሬታዊ አብሻዊነቱ ምን ይሆን?
መጽናናት ስለምን ይረቃል?
የመኖር ተስፋ ስለምን ይኮበልላል?
የምኞት ኔት ለምን ይበጣጠሳል?
ስለ ማግሥት ማሰብ ለምን ይጨንቀዋል?
{} ይህ ለምን ይሆናል?
የተጀማመሩ የግል ፕሮጀክቶች ስለምን ይቆማሉ?
#እናት የህቅታ ዊዝደም ናት።
ብዕሩም ይሁን ብራናው እናትን አይገልፃትም። ገልፆትም አያውቅ። እናቱን ያጣ በየትኛውም ዕድሜ የሚገኝ ሰብ ሙሉዑ አይደለም። ለምን? የሚለውን ሙሉ ፬ ዓመት በመደበኛ ተመራምሬ የደርስኩበት ዕውነተኛ ሚስጢር ጽንሰት ላይ አንድ እትብት ይኖራል። ስንፈጠር ያ ሐዲድ ለጊዚያዊነት ይቆረጥ እና ወደ የግል ተፈጥሯችን ይመጣል። ከዛ ዕድል ካለን አብረን እንኖራለን።
???? ……… #ዕድል ሲሸሽስ?
አንዳችን በሥጋ እንለያለን። ይህ ማለት በሥጋ የተለየው እትብት አፈር ውስጥ ይቀበራል። በህይወት የቀጠለው ቆሞ ይሄዳል። በሁለቱ መሃል ስበት ይኖራል። ህልው የሆነ። ስለሆነም ልጅ ቀድሞ በሥጋ ሲለይ እናት የማትችለው የገዘፈ ፈተና ይገጥማታል። እናትም በሥጋ ቀድማ ከተለየች ልጅ የተለዬ የሃዘን ጊዜ ይገጥመዋል።
*** መኖር ይሳነዋል።
**** ተስፋ ይደክመዋል።
****** ራዕይ ይጎሳቆላል። እናት የማንነት መጠሪያ መሆኗ ይታወቃል።
ስለሆነም እናቱን ያጣ ልጅ፤ ልጇን ያጣች እናት አዲስ ማንነት ይኖራታል። እብዬ ሆዴ እናቴ ወንድሜን ሃይልዬን አፋበት ግንባር ሲቀማት በአባቷ መማል ቀረ፤ እስከ ዕለተ መራራ ስንብቷ ድረስ ኃራሜ ነው፤ ኃይልዬ ይሙት ካለች የውሳኔዋ መቋጫ ነበር።
በሌላ በኩል በህይወት ያለሁት እኔ ጭምተኛውን አቨይን አጥቼ፤ እምሳሳለትን ጀግናዬን ኃይልዬን አጥቼ፤ ከእጄ ላይ ያለፈውን እንዳልክዬን አጥቼ የተጽናናሁበት ሁነት ይገርመኛል።
አላውቅም በቤተሰብ፤ በጓደኞቼ ተከብቤ አገሬ ስለነበርኩ ሊሆን ይችላል ተጽናናሁት። የእሽታ ውዴን እናቴን አጥቼ ግን ጽናቴ፤ ጥንካሬዬ፤ ሁለገብ ትጋቴ ተፈተነ። ይህ ማለት የመኖራችን #ሴል እናት ብቻ መሆን ሳይሆን እናት አልባ ህይወት ዳገት እና ድጥ መሆኑን ተረዳሁ። ዕውነት ብነግራችሁ ይህ እዮራዊ ሚስጢር ቢገለጥልኝ ኖሮ ስደት ምርጫዬ በፍጹም አይሆንም ነበር።
#ልጆች ሆይ!
አቅምን አስችላችሁ እናት ጋር ያላችሁ ግንኙነት ትንፋሻዊ ይሁን።
#ሌላው እናታዊነት አበክሮ ሴትን፤ መውለድን መዋለድን የተሰጠው ቢሆንም ………
በማናቸውም ጊዜ በሚፈጠሩ የታሪክ ገጠመኞች ተባዕታት የተሰጣቸው እርህርህናን ገቢራዊ ለማድረግ አቅም ካላቸው፤ ልጆችን በጉድፊቻ፤ በማር ልጅነት የሚቀበሉ የሚያሳድጉ የበጎ አድራጎት ተቋማት፤ (ክብርት ልዕልት አበበች ጉበና)ደጎችም፤ ልጆች እናታቸውን ወይንም ሁለቱንም ወላጆቻቸውን ሲያጡ የእናትነት ድርሻቸውን ያለ አቅማቸው ተረክበው በማይቻል ሁኔታ በቁማቸው ሰማዕትነትን ሲቀበሉ እንደ እናት ሊከበሩ፤ ሊፈቀሩ፤ ሊመሰገኑ ይገባል ባይ ነኝ።
#ላሂ።
ታላቅ ወንድም ይሁን ታላቅእህትም የእናትነት ላሂ ካላቸው ክብር ሊሰጣቸው ይገባል።
ስለ እናትነት የሚፃፋ፤ ስለ እናትነት የሚነገሩ፤ ስለ እናትነት ዕውቅና የሚሰጡ ጉዳዮች ሁሉ ከላይ የዘርዘርኳቸውን አሟልተው የድርሻቸውን ለሚወጡ አንቱወች፤ በሁሉም ሚዛን በእኩል ሊታዩ ይገባል ባይ ነኝ።
የዛሬው ዕርዕሰ ጉዳዬም ጭብጡ ይህ ነው። እናት ግዴታዋን ለመወጣት እክል ሲገጥማት፤ ወይንም በሥጋ ስትለይ ያን የእሷን የከበረ ሞገሳዊ ኃላፊነት ፈቅደው የተቀበሉ የትውልድ ጀግኖች ሊከበሩ፤ ሊደነቁ ይገባል ባይ ነኝ። በዚህ ዙሪያ ዓለማችን ምን እና ምን እንደሆኑ በማስተዋል ሊታይ ይገባል። እኛስ????
አጽናኝነት ሁሉም የማይከውነው ግን ከእዮር ለሁሉም የሰው ልጅ የተሰጠ ጸጋ ነው።
የተከፋን፤
የተቸገረን፤
አደፍ ያለ የለበሰን፤
ዕድል የሳሳበትን በአስተውሎት ቅርብ ብሎ ማጽናናት እንደዚህ ዓለም ዓቀፍ ዕውቅና በሚሰጣቸው ቀናት በወግ ሊከወኑ ይገባቸዋል። ይህም ለአንድ ቀን ሳይሆን በተከታታይ እና በትጋትም ሊከወን ይገባል።
#እቅፍ።
ቀን የሸሻቸውን ምንዱባን እቅፍ ውስጥ አስገብቶ ለጥቂት ደቂቃ እቅቕፋዊ ሙቀትን መለገስ ለፈፃሚው ቀላል፤ ለተቀባዩ ግን ተስፋ አዳሽ ፈዋሽ እርምጃ ነው። ጤና ነው። ለእኔ እቅፍ አድርገው ሙቀትን እየመገቡ አይዟችሁን ያጸኑ ብፁዓን የጤና ሃኪም ናቸው ብዬ አስባለሁኝ።
አንዳንድ ደጋጎች ዕንባን በመዳፋቸው ማበስ ብቻ ሳይሆን፤ ዕንባውን በእጃቸው የሚቀበሉም ህይወት ትሰጣችኋለች።
ይህ የቆዳ ቀለምን፤ ዘውግን፤ ሠፈርን አይመለከትም። ይህ ገጠመኝን እንዲዩ የተፈቀደላቸው ጥብቆ ከሆነ መስክ በፍጹም ሁኔታ በቅጽፈት ይርቃሉ። ለምን? " እግዚአብሄር በአንድም በሌላም ይናገራል፤ ሰው ግን አያስተውለውም" ይህ ዶግማዊ አስተምህሮን የማወቅ ጸጋቸውን የተረጎሙ ስለሚሁኑም። መመረቅም ነው። አላህ እግዚአብሄር የሰጠንን ፈቅዶ መስጠት ፃድቅነት ከዚህ በላይ ምን አለና?
#የህቅታ ጸሐይ እናታዊነት።
እናታዊነት ይብራ። አሜን።
እናትነት ይለምልም። አሜን።
እናትማ ይጽደቅ። አሜን።
የእናትነት ፍልስፍናው ነጭ ለባሽን ፈላጊ ብቻ ፤ ብቻ አፈላላጊ አይደለም። ለእናትነት መፈጠር ትዕዛዙ ማታ እና ቀን ዥንጉርጉርነት አይደለም። የእናትነት መክሊቱ ለቤት ተደልቶ ሌላውን አሳስቶ ማዬት አይደለም። እናትነት የተጣፈ የለበሰችውን፤ ድንጋይ ተሸካሚዋን፤ ባል ሆኖ ግን ኃላፊነትን መወጣት ተስኖት ሊለምን ያፈረን ጎልማሳን፤ አካሉ እክል ገጥሞት መኖሩ ያነከሰበትን የሰው ልጅ "ለላም ቀንዷ አይከብዳትም" ሊተረጎም ይገባል።
እናትነት ውሃ በቀጠነ በገጭ ገው፤ በህውከት፤ ወይንም ደመቅ ብለው በወጡ ገዢ ክስተቶች ላይ ሳይሆን አስተዋሽ፤ ባለቤት ያጡ ጉዳዮችን ሳያሳቅቁ እቅፍ ድግፍ አድርጎ አለሁልህ ማለትን ይጠይቃል። አይዟችሁ ካልተሸሸ እናታዊነት የፆታ፤ የዕድሜ፤ የቆዳ ቀለም፤ የዞግ መሆኑ ያከትማል። ሞቶው ለእኔስሰው መሆኔ ብቻ ይበቃኛል ይሆናል።
#እራስን ስለመለወጥ።
በተለይ በእኔ ዕድሜ ልክ ያለ፤ እኔንም የሚበልጡኝ ቢሆኑም የስክነት የምርምር ጊዜ ሊኖረን ይገባል። ባተረፍነውና ባከሰርነው ጉዳይ ግምገማ ልናደርግ ይገባል። ጥንካሬ ላይ ሳይሆን ድክመት ላይ፤ በጎደለ ጉዳይ ላይ አተኩሮ መሥራት ያስፈልጋል። የሚቀድመው እራስን መለወጥ ይሆናል። ባጀታችን የእናትነት ማህጸን ፍሬ ከሆነ፤ ፍሬው እንዲጨነግፍ፤ እንዳያሰብል አረም አብቃይ መሆን የተገባ አይደለም። በጀቱ ከፋይናስ በላይ ማህጸን ከሆነ የገጠመኞች ስኬት ደረጃ ሊመዘን ይገባል።
#የእናት ማህጸን ሊሳሳለት ይገባል።
የማህጸን ስፔሻሊስቶችን፤ አዋላጆችን መፍጠር ምስጉንነት ነው። በሌላ በኩል የእናት ማህጸን የወይራ፤ የክትክታ፤ የአባሎ፤ የግራዋ፤ የብሳና ግንድ ውጤት አይደለምና ሁልጊዜ ማገዶ መናፈቅ ለእንጀራ መጋገሪያ እንጂ ለእናቶች ማህጸን #ቄራነት ሊሆን አይገባም። አንዲት ፔና ገዝቶ ያላስተማረ ርን ስለመሆናችን በጥልቀት ልናስበው ይገባል። ይህ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የኢትዮጵያ ተጨማሪ አቅም ፈላጊወች ሁሉ የጋራ መለያ ነው።
የአንድ አክተር ልጅ አይደለም የቅርብ ቤተሰብ በዛ የማያቋርጥ የሰው ልጅ የማገዶ ምኞት ሰርክ አቅርቡልኝ ማዕቀፍ ውስጥ የለም። በማን ሰብል ማገዶነት ማን ይክበር? ከራስ ሊጀምር ይገባዋል። እናቴን እወዳለሁ፤ ከእናት ተፈጥሬያለሁ የሚል ሁሉ አህዱነት ከራስ ይነሳ። የእናት ማህጸን የዬትኛውም ክፋ ሃሳብ መፈተኛ ኦብጀክት ሊሆን አይገባም። ባልተሳካ ጉዞ የተሰዋው ማህጸን በቃህ ከሚል ስምምነት ላይ ሊደረስ ይገባዋል።
መጸጸት ቢፈቀድ እናትን - እናታዊነትን - እናትነትን የተንገላታበት - የተጎሳቆለበት - የተረበሸበት- የተሸበረበት - ሁነት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አስተዋፆ ያደረግንባቸው ክስተቶች ከኖሩ ዝቅ ብሎ ይቅርታ መጠየቅ ይገባል።
በብስጭት፤ በንዴት ውስጥ ሆኖ ትልልፋዊ ንግግር፤ ትልልፋዊ እርምጃ፤ ትልልፋዊ ዛቻ፤ ትልልፋዊ ማቃለል በቀጥታ በእናት ማህጸን የሚወረወር ጦሮ ስለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል። እናት በህይወትም ኖረች በሥጋ ተለየች እናት እትብቷ ህልው ነው።
ልብ አምላክ ዳዊት " ህግ ተላላፊወችን ጠላሁ" ሲል ለክርስትና አማንያንም ይህን ማለቱ ነው። ያልተደራጁ፤ ያልተፈተሹ፤ እርማት የሌላቸው ንግግሮች ንዴትንን አክለው ሩጡ ከተባሉ ጉዳቱ የውስጥ ነው። ውስጥን ለማዳን ጥረት ካለ፤ ውስጥን ከሚጎዳ ሰይፋዊ የአነጋገር ዘይቤም መታቀብ የግድ ይገባል።
ሰው ነን። እንበሳጫለን። ግን የመድረክ ዕድሉ ሲገጥም ብስጭት ጦር ነውና አስታግሶ ዕለቱን ይቅርብኝ እለፈኝ ማለት ይገባል። ይህ ቁርጠኛ የማስተዋል አቅምን፤ እራስን የመግራት የራስ የመሪነት የአቅም ልክ ነው። ለተሰጣቸው። በየትኛውም ዓለም በንግግር ቁጥቦች ይከበራሉ። ይናፈቃሉ። ቋሚ መወደድን ያተርፋሉ።
በንግግር ጥበብ ጥሩ ተናጋሪነት፤ የታረመ አንደበትን ይጠይቃል። ንግግር ጥበብ ነው። ክህሎቱን በስልጠና ማሳደግ ይገባል። በሌላ በኩል አንድ የንግግር ጸጋ የተሰጠው ሰብ ሁልጊዜ ተናጋሪ ከሆነ የአዘቦት ይሆንና የተሰጠው ጸጋ ይሸበሸባል። ይሰለቻል። አመሉ ነው ይባላል። በብቁ ዓራት ዓይናማ ተናጋሪነት ውጭም ይሆናል። አድማጩም ይሸሻል። ተናጋሪ ህግ ጠባቂ፤ በብርቱ ተናፋቂ፤ በቃላቶች ቁጥብ፤ ግብረ መልስን አድምጦ እራሱን ማረም የሚችል ሊሆን ይገባል።
የሆነ ሆኖ በተለይ የፖለቲከኞች ንግግር የሚያሰማራው፤ የሚያሰልፈው አቅም ዒላማው የእናት ማህጸን ፍሬን በማያቋርጥ ሁኔታ መሻት ነው። ይህ ሁልጊዜ ሲሆን ይከብዳል። የደከመች እናት ፈቃዷ ሊጠየቅ ይገባል። በተለይ ከ40 ዓመት በላይ ለሆነ ሰብዕ እራስ ሲገዛ እናትነት ባለተስፋ ይሆናል፤ እራስ መግዛት ሲሳን እናትነት ተስፋውን ይዘረፋል። ይህ ሂደት በጥሞና ተመርምሮ ከሰከነ አመክንዮ ሊያደርስም ይገባል።
#እናትነት እናታዊነት ሰማዕትነቱ ሲፈጠር ነው።
ይህን የሰማዕትነት ጸጋን እረፍት ልንሰጠው ይገባል።
ወህ! እንዲል ልንፈቅድለት ይገባል።
ባዕላቱን በብቁ ማይክ፤ በውብ አዳራሽ፤ በተሽቆጠቆጡ አዳራሽ፤ ነጭ ለብሰን አብበን ደምቀን ማክበር ብቻውን የእናትነትን ውለታ፤ እኛነትን የሰጠን ጸጋ አክብሮ ሊያስከብር አይችልም። እናትነት ዝቅ ብሎ ዝቅ ካሉት ጋር ህይወትን በገቢር መጋራት የተራራው ስብከት ይኽው ነው።
ስለ እናታዊነት ጥልቅነት ጊዜ ይሰጠው። ቢያንስ የቃላት ጦር ለመሐጸን ከመላክ እንቆጠብ። አንጎል ድንቢጥም አላት። ከድንቢጥ የተለየነው ህሊናዊነታችን ነው። ህሊናዊነቱ እራስ ገዝነቱ በህግ ይመራ ዘንድ፤ ሁሌ ማህጸን ተገበርልኝ ዕሳቤ ጋርም ቁጭ ብሎ ተወያይቶ መወሰን ይገባል።
ክብረቶቼ እንዴት አደራችሁልኝ። እኔ አምላኬ ክብሩ ይስፋ ደህና ነኝ።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
03/05/026.
እናታዊነት የሰው ልጅ መፈጠር #ህቅታ ነው።
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ