#ሰውኛ #ሥልጣኔ ይናፍቀኛል።

 

#ሰውኛ #ሥልጣኔ ይናፍቀኛል።
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 
 May be an image of one or more people, people smiling and jewelry
 
ምዕራፍ ፲፱።
 
ሽው የሚለኝ ሰውኛ = ሥልጣኔ፤
የሚናፍቀኝ ተፈጥሮኛ = ሥልጣኔ፤
የሚያጓጓኝ = ይቅርታ እና ምህረት፤
የሚርበኝ = ቅንነት እና ርህርህና፤
የሚጠማኝ #ትቅቅፍ
 
የሚያሳሳኝ በብሩህ ዓይን መተያዬት።
አንባጓሮ፤ ግጭት፤ ጦርነት ግለት፤ ጭቆና ስልችትችት ብሎኛል።
የምር ሰው ሆነን መፈጠራችን ገሃድ ነው። ሰው ሆነን መኖርን ያሰለጠንበት ጎዳናም ዕጹብ ነው።
ያቃተን ግን በተፈጠርንበት የሰውኛ ቃና እና #ቅኔ መቆም አለመቻላችን ነው።
 
ምንም -- የሚያጠላላ፤ -- የሚያቃቅር፤ ፊት የሚያዞር --- እኛ ያልሰራነው ሸር የለም፤
ምንም እኛ ያልታደምነበት የሴራ ማግ እና ድር የለም፤ ምንም እኛ የሌለንበት
የምቀኝነት ኔት የለም።
 
ምንም እኛ ያላሰለጠነው የጥፋት #ጥላቻ የለም። ምንም የሰው ልጅ ማህበርተኛ
ያልሆነበት በቀል የለም። ምንም የሰው ልጅ የሌለበት ማሸበር፤ ማስፈራራት፤
ማሳቀቅ፤ ማስደንገጥ የለም።
 
ከተፈጥሮ አደጋ በመለስ ያሉ የሰው ልጅ እልቂቶች፤ የሰው ልጅ ፍልሰት፤
የሰው ልጅ የሃዘን ዕንባ፤ የሰው ልጅ ጭቆና፤ የሰው ልጅ መገለል የለም።
ከተፈጥሮ ችግር ባሻገር ያሉ ሰቅጣጭ ግድያወች፤ ዘረፋወች፤ ውድመቶች ሁሉ የሰው ልጅ
እንደ ዳንቴል በእጁ የሠራቸው፤ እንደ ጨርቃ ጨርቅ የሸመናቸው ናቸው።
 
አንድ ቀን ቀርቶ በአንድ ሰከንድ ውስጥ ስንት የክፋ ሃሳብ ጎርፍ እንደሚያጥለቀልቀን እሰቡት።
ስፖርት የፍቅር ተፈጥሮ መተግበሪያ ቱል ነው ብዬ አምናለሁኝ።
 
እንደ እኔማ የፍቅር ተፈጥሮ ከእናት እና ከስፖርት ማልያ ብቻ ይገኛል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ።
በናፍቆት፤ በጉጉት ይጠበቅ የነበረውን የ23ኛው የዓለም ዋንጫን ከውስጣችሁ ሁናችሁ እዩት።
ፈተናው የሰው ልጅ #ሥልጣኔው እስከምን እንደሆነ ያስረዳችኋል። ይህን ለናሙና የተፈጠሩ
አሳሳቢ ክስተቶችን አንዘርዝሮ ማዬት ይገባል። በችኮላ፤ በብስጭት ሳይሆን ከልብ ሆኖ
መሰጠታችን ላይ መበዳደልን የፈቀድንበትን መንገድ መመርመር ይገባል።
 
ታዲያ በመበዳደል ውስጥ እኔ፤ እርስወ፤ እኛ አለንበት ወይ? ይህም ስኩን ድፍረት
ይጠይቃል። እራስን እንደመመርመር ከባድ የቤት ሥራ የለምና።
የቆዳ ቀለም የውስጥ ኦርጋናችን ልብስ ነው። የእኔ የልቤ ተግባር ከሌላው
ጋር ፋንክሽኑ ተመሳሳይ ነው። ሳይዙ ሊለያይ ይችላል። አይደለም የሰው የዶሮ ልብ እኮ እንደ
እኛ ነው። የዶሮ ደሙም ያው እንደ እኛ ቀይ።
 
#ክፋ ሃሳብ ግሎባል ነው።
 
ክፋ ሃሳብ ወሰን፤ ደንበር፤ አህጉር፤ ክልል የለውም። የተለየ ህዝብም፤ የተለዬ
ማህበራዊ መሠረትም የለውም። ክፋ ሃሳብን ከብካቢው እንሰሳት ሳይሆኑ
ተግባሪው የሰው ልጅ ነው። ክፋ ሃሳብን #ሃራም ለማለት አቅም ዓለማችን የላትም።
ለምን? ክፋ ሃሳብን የሚመክት ሲስተም ዓለማችን አልሰራችም እና። አጀንዳዋም አይደለም።
የክፋ ሃሳብ ተጠቂወች ሰው እና ተፈጥሮ፤ የክፋ ሃሳብ #አጥቂ የሰው ልጅ። ተጠቂም እኛ እና
ተፈጥሮ፤ አጥቂውም በቡድን ይሁን በተናጠል እኛው የሰው ልጆች። 
 
#ተዚህ ላይ።
 
ዓለማችን በጎነት የላትም እያልኩ አይደለም። ቸርነትን የተጎናጸፋ ደጋጎች በየትኛውም ዓለም
አሉ። የእኔ ሐሳብ እንደ ፕላኔት ምድራችን በጎነትን የሚረክሱ ድርጊቶችን ለመቋቋም
አቅም አልፈጠረችም ነው። ተቋምም የላትም። ተቋም አለ። ተመድን የመሰሉ። ግን በተፈጠሩበት ልክ
ነው ወይ ተክለ ቁመናቸው? እእ።
 
ለዚህ ነው እኔ የፍቅር ተፈጥሮ #ካሪክለም ተነድፎለት መደበኛ የትምህር አካል ይሁን።
መብቱን አውቆ ግዴታውን የሚወጣ ትውልድ ለማብቀል፤ ወንጀልን ነውሩ በማድረግ
የወንጀል ድርጊትን ለመመከት ህግ የጥቂት ባለሙያወች ብቻ ሳይሆን የማህበረሰቡ
ሊሆን ይገባል። ልጆች ከመዋለ ህፃናት ጀምሮ #ህግን ይማሩ ዘንድ ካሪክለሙ
ይሻሻል ብዬ እምሞግተው።
 
እያንዳንዱ ለትምህርት የደረሰ ልጅ የየአገሩን ህገ - መንግሥት እና የታህሳስ 10/1948
የተመድን ድንጋጌ፤ በተጨማሪም ተፈጥሮን ስለመጠበቅ የወጡ ድንጋጌወችን ሁሉ
ማጥናት፤ መመርመር ይችል ዘንድ #የተዘጋው በር ሊከፈት ይገባል።
ግዴታውን የማያውቅ እንደምን ለግዴታው ተገዥ ይሆናል?
 
መብቱን የማያውቅ እንደምንስ የራሱን መብት አስከባሪ ዘብ አደር ይሆናል?
እኔ "ወንጀለኛ፤ አሸባሪ" የሚሉ ምድባወችን እምለካው ከዚህ አንፃር ነው።
 
#ህግ ከባድ ነው። ህጋዊነትም እንዲሁ።
 
በነገራችን ላይ የህግ ድንጋጌወችን ማንበብ ሁላችንም እንችላለን። መተርጎም
ግን ባለሙያ ይጠይቃል። የቃላት፤ የሥንኛት፤ የሐረጋት ፍቺ በህግ አግባብ የተለዩ ናቸው።
ብዙ ጊዜ የህግ ሙያ ያጠኑ ውስጣቸው የተረጋጋ፤ ቁጥብ፤ ከእላፊ ንግግር፤ ከፍረጃ በጣም
የራቁ ናቸው። ከግጭት፤ ከጸባዊ ጉዳይም ጋር ማህበርተኝነትን አይደፍረም። ጥንቁቅ
ናቸው። ሞዴልም ናቸው በሰብዕና አገነባብ ላይ።
 
ይህ ዕድል የማህበረሰብ ይሆን ዘንድ ዓለማችን ትትጋ ነው የእኔ ፍላጎቴ። የእኔ ዕምነት
" በአባሸሪነት በሃይማኖት ይሁን በፖለቲካ" ከተፈረጁት ጋር ዓለማችን በተለይ ተመድ ገጽለገጽ
በየትኛውም የማህበራዊ ሚዲያ ፎርማት ሊወያዩበት ይገባል ብዬ አምናለሁኝ። ሰው #ሰለጠነ
እምለው ለነገ ትውልድ ሰቀቀን የማይሆን ዓለም ሲፈጥር ብቻ ነው። የህጉን ድንጋጌ ካላወቀ
አቶ "#ሀ" ህግ ሊተላለፍ ይችላል? ጥፋቱ የማን --------- ነው????
 
ዓለማችን ሌሎች ፕላኔቶች ለሰው ልጅ ይበጃሉ ወይንስ አይበጁም ረቂቅ ተግባር ላይ ትገኛለች።
ይህ የሥልጣኔ አቅም ጥላቻን፤ በቀልን፤ ቂምን፤ ጭካኔን፤ አድሏዊነትን፤ ግለትን፤ ንፋግነትን፤ ሴራን፤
ሸርን፤ ምቀኝነትን፤ አረማዊነትን፤ ዘረኝነት የመቋቋም አቅሙ ምን ያህል ነው? የእኔ ጥያቄ ይህ ነው።
"#አሸነፈ! #ድል አደረገ! #ተሸለመ! #ተመረጠ! #ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆነ! #ምርጥ!" እነኝህ ውስጥ  
#የሰውኛ ሰውነት ድርጊታዊ አቅም አለ ወይ? የተፈጥሮኛ መስተጋብሩስ? 
 
ሥልጣኔ ጭካኔን - ጥላቻን - ግለትን #ያሸነፈ ካልሆነ፤ ለእኔ ሥልጣኔ የሚለው ኃይለ ቃል ለመረዳት ይከብደኛል። 
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
 
ኑሩልኝ። አሜን።
 
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
13/06/026.
 
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።