ከማጣጣል ሂደቶችን በስክነት መከታተል ይበጃል - የአባ #ጠቅልልን የነገረ አጤ ሂደት - በማስተዋል። • የአቅም #ግኝት #ፍለጋው የሚያስተምረው ድርጁ ተመክሮ ስላለው።

 

ከማጣጣል ሂደቶችን በስክነት መከታተል ይበጃል - የአባ #ጠቅልልን የነገረ አጤ ሂደት - በማስተዋል።
• የአቅም #ግኝት #ፍለጋው የሚያስተምረው ድርጁ ተመክሮ ስላለው።
 
"የእግዚአብሄር ተራራ የለመለመ ተራራ ነው።
የጸኑ ተራራወች ለምን ይነሳሉ?
የእግዚአብሄር ይህን ተራራ ያድርበት ዘንድ
ወደደው፤ በዕውነት እግዚአብሄር ለዘላለም
ያድርበታል።" (መዝሙረ ዳዊት ፷፯ ከ ቁ ፲፭ - ፲፮።) 
 
#ምዕራፍ ፲፱።
 
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ፤ ከተወዳጁ ተጓዥ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ጋር ውይይት ነበራቸው።
የውይይቱ ፍሬ ነገር ሳይሆን #ገፊ ምክንያቱ ምንድን ነው የሚለውን ሳስበው ሰነበትኩኝ።
 
የሆቴል ሥራ #ብራንዱ የጀግና አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ ሥላሴ ነው። የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ በኽረ
ፕሮጀክታቸው ሆቴል መሥራት ነው። 
 
ሌላው የጠቅላዩ የጫካ ፕሮጀክት ትኩረታቸው ነው። ሰፊውን ጊዜ የሚሰጡት። የደን ልማት ፕሮጀክትም አላቸው።
የአባይ ግድብ አሻራ #ሁለት ሰብዕና ጎልተው ይወጡበት ነበር። የቀድሞው ጠቅላይ ሚር አቶ መለስ
ዜናዊ እና ኢንጂነር ስመኜው በቀለ። በፕሮጀክቱ ግንባታ ልክ ሰብዕናቸውም ተገንብቶበታል።
 
የፕሮጀክቱ በአዲስ መሃንዲስ ተጠናቋል። በአባይ ግድብ ዙሪያ አጀንዳ ከኖረ የቀደሙት ሥሞች በማህበራዊ ሚዲያ
ጎልተው ይወጣሉ። ይህ ባይፈቀድለትም ግን እየሆነ ያለ ዕውነት ነው።
 
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ላጠናቀቁት ፕሮጀክት ፊድባኩ የሚነግረን መነሻ መሰረት የጣሉትን አክብሮ ይነሳል።
ይህ ማለት በአባይ ግድብ ዙሪያ የነበረውን ቀደምት ዕውነት የህዝብ ህሊና ሴብ እንዳደረገው አስተውላለሁኝ።
በነገራችን ላይ ስለ ጎርጎራ ፕሮጀክት ደርግ የሰራበት መዝናኛ ነበር። ከዛ ሻለቃ ኃይሌ ሊሠራበት ቅድመ ዝግጅት
የሃሳብ እያደረገ እያለ ነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቀለሉት።
 
የኦሮምያ የከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ እያሉ ጎንደር ከተማ ላይ ስብሰባ ነበራቸው። ያንጊዜ በንግግራቸው ውስጥ
#ጎርጎራ አልተጠቃለም። ወደ ሥልጣን በመጡ ጊዜ በተከታታይ አማራ ክልል ሲመላለሱ ነገረ ጎርጎራ አላነሱትም።
ሻለቃ ኃይሌ ሲያስበው ግን ነቁ። ፈጸሙት።
 
የደን ልማት በሚመለከት እንደ ዋዛ ከፃፋት ሰወች በማስተዋል አድምጠው እየሰሩበት ያለ ፕሮጀክት ነው። የሚንቁት
የአቅጣጫ ጠቋሚ ሁነት የለም። 
 
ጠቅላይ ሚር አብይ ይቅርብኝ ብለው የሚተውት #የብራንድ ጉዳይ የለም። ሂደቱን በማስተዋል ሁናችሁ
ስትመረምሩት ከጥቃቅኑ እስከ ገዘፈው ጉዳይ ድረስ የማይከታተሉት ምንም ነገር የለም። ምን አልባት
ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት ጎልተው የሚመጡ የብራንድ ሥሞችን ተከታትለው ይሆናል። 
 
እሳቸው ወደ ሥልጣን ከመጡ ተጀምሮ የተጠናቀቀ የጥበብ ተግባር የለም። ሳያልቅ ከውኑት ይባል ይመስለኛል።
ዶር አብይ ከመጡ ተጽዕኖ ፈጣሪ ተዋናይ የለም። የፊልም ኢንደስትሪው መዳከም አንጋፋ ባለተስጥዖወች
እንግዳ አወያይ ሆነዋል። 
 
ኢትዮጵያ በታሪኳ ይህን መሰል ዘመን አይታ ከሆነ ልትነግሩኝ ትችላላችሁ። የሰሞኑ ውይይትም እኔ እማዬው
ከዚህ አንፃር ነው። ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም #ተፈጥሯዊ ነው። ኢትዮጵያም የተፈጠረችበት አመክንዮ ተፈጥሯዊ
ነው። ጋዜጠኛው ተፈጥሮን እና የሰው ልጅን በውስጡ አስመችቶ አክብሮም የመያዝ አቅም ያለው ቅን ሰው ነው።
ጨምሬ የለጥፍኳቸው ማገናዘቢያወችን እዩት።
 
ምን ያህል ግሎባል የሆነ የተፈጥሮ መሰጠትም፤ መመሰጥም እንዳለው። ፎቶወቹ ከራሱ ፌስቡክ ላይ የወሰድኩት ነው።
ፎቶ ማዬትም መነሳትም እወዳለሁኝ። ስለሆነም በርከት አድርጌ አቅርቤያለሁኝ። ታዩት ዘንድ።
 
ኢትዮጵያን ህሊናው አድርጎ ድካም የማይሰማው ጋዜጠኛ #አለባበሱንም እዩት። እስከ አንገቱ ድረስ #ይቆልፋል
ሸሚዙን። የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ለለቱ የመረጡት የአለባበስ ዘይቤ እና ቀለምን በአስተውሎት መርምሩት።
በዝም ብሎ የተከወነ አይደለም። ታቅዶ የተከወነ ነው። ስለዚህም ነው ማጣጣሉ፤ ማቅለሉ ሳይሆን ከውስጥ
ሆኖ ማስተዋሉ ይለፍ ይሰጠው የምለው።
 
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ አውቀዋለሁ ብሎ ደፍሮ የሚናገር የቅርብ ሰው ይኖራል ብዬ አላስብም።
ምን አልባት ባለቤታቸው፤ ግን ቀዳማዊቷ እመቤት በደህናቸው ነውን ከአደባባይ #የተሠወሩት? በአዲስ
ምዕራፍ ምክንያት ወይንስ???
 
የሆነሆኖ ምን ፈለጉ እና ከጋዜጠኛው ጋር ተቀመጡ? የተፈጥሯዊነት ብራንድ፤ ውስጡን የሰጠበት ዝልቅ
ተመክሮ፤ ዕድሜውን በፀጋ ያበረከተበት የተጓዡ ጋዜጠኛ አስተምህሮ፤ ምኑ ሳባቸው። በዚህ ውይይት በህሊና
#የተመሰጠረው ነገር ምን ይሆን?
 
ሁለገቡ የፊልም ፕሮዳክሽን እና የፎቶ ባለሙያ አቶ ሰውመሆን ይስማው ሶሚክስ እና አጤ አስቻለው ፈጠነ
አሞራው ከአሞራው የሚል የአርበኝነት ጸጋ ዝማሬ አላቸው። በዝማሬው ጎልቶ የወጣ ዕውቅ ባለታሪክ
የአርበኛው አሞራው ውብነህ ታሪክ ላቅ ብሎ ሲደመጥ የተመቼ ነገር አልሆነም። እኛ እየሰማን ነው
ያደግነው። ስለሆነም ን ስር እና አሞራን አፎካክረው ጯሂ እና ቆሻሻነት ለአሞራ ተሰጠ። 
 
ያ ብዙ የተደከመበት ዝማሬ ቅስሙ ምን ሊሆን እንደሚችል እሰቡት። "ፍቅር እስከ መቃብር" በሚመስጥ አኳኋን በብዙ
ድካም በፊልም ተሰራ ገና ባፍላው ቆመ። "በፍቅር እስከ መቃብር" ውስጥ ኢትዮጵያ ተደላድላ የተቀመጠችበት ሁነቷን
ይገለፃል፤ ተዋህዶ ሥርዓቷ ይነግሥል፤ ቅኔው ጎጃም ይገዝፋል። 
 
በኢትዮጵያ የትናንትም የዛሬም ዓይን እንዲሆን የታቀደው ግን የአንድ ሰው ሰብዕና ብቻ ይመስላል። በሁሉም ዘመን
#በመንፈስ ነበርኩኝ ዓይነት ሂደት አስተውላለሁኝ። መቼም ይሄ ከዕዕምሮ በላይ የሆነ ቻሌንጅ ነው። አልባሌ ሰው
አይደሉም። የአገር መሪ፤ የዓለም የሰላም አባት የኖቤል ተሸላሚም ናቸው ጠሚ አብይ አህመድ አሊ። ጉዟቸው እና
ጎዳናቸው ኢትዮጵያን ይዞ ነው። 
 
ከቅርቡ ዘመን አይደለም፤ በመካከለኛው ዘመን ኢትዮጵያ፤ ከዛም በቀደመው የተፈጸሙ #ገድሎች፤ ታምራቶች ብራንዳቸው
ተበውዞም ይሁን ተሸርክቶ በዘመነ አብይዝም ይሆን ዘንድ ይፈለጋል። "እየሠራሁ አታዩም፤ እየደከምኩ አታደንቁም" የሚሉት
ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አባጠቅልል ልፋታቸው ኢትዮጵያ ሀሌታ ካለችበት ዘመን ጀምሮ ያለው ታሪክ የፈቀዱትን በአንድም
በሌላም የሳቸው ይሆን ዘንድ እየተጉ ነው። 
 
ኢትዮጵያ አምሳለ አብይዝም እንድትሆን ይፈለጋል። #ላቀች መሆን ግን አይፈቀድላትም ነገረ አሞራ፤ ነገረ ለማኝነት
የመጣው እኮ እናት ጉልላትነቷ በአህቲ መንፈስ ውስጥ ስትዘልቅ ነው።
 
በቀደመው ይትብኃል ላሊበላ - በገና፤ ጎንደር በአስተርዬ፤ ሬቻ በዘመን መለወጫ መባቻ ይከወናሉ። ሁለንም ወደ አዲስ አበባ አምጥተው ወደ መሠረታቸው ለበረከት የሚሄደው ሁሉ ቱሪስቱም ጨምሮ ወደ አዲስ አበባ ይሆን ዘንድ ተጀምሯል። 
 
የዛሬ 10/15 ዓመታት ይህን እሰቡት ደብረዘይት፤ ላሊበላ፤
 ፋሲል የሚሄድ እየሳሳ ይሄዳል። ከቅርቡ ዓይነታው ሳይሆን ኩረጃው
ከተገኜ ለምን ይሄዳል በዕል አክባሪው? አንጋሹ። 
 
የተፈጥሮ ባለ ብራንዱ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ጋር የነበረው ውይይትም ቀደም ብዬ ያነሳሁት አምክንዮ ሃሳብ ቤተ - ዘመድ
ነው። ስለተፈጥሮ ስናስብ በህሊናችን የታተመው የተፈጥሮ አንባሳደሩ ተጓዡ ጋዜጠኛ ነው። አይደል? 
 
የጫካ ፕሮጀክቶች፤ የቱሪዝም መዳረሻ ተብለው የተሠሩ ፕሮጀክቶች መነሻቸው ከጋዜጠኛው ትትርና ጋር በውል የተዋህደ ነው።
እርግጥ ነው እስከዛሬ ብራንዱ የባለቤቱ ነው። ውይይቱ ይህን ለማመጣጠን ይመስለኛል። #ነገስ? አሳቻ ነው። መተንበይ
አይቻልም። የማይደክም፤ የማይተኛ፤ የማይዝል ነፍስ እና መንፈስ ትልሙን እየከወነ ነው።
 
እንዲህ ዓይነት ሂደት ማንኛውም ለጠቅላይ ሚኒስተርነት እራሱ ወይንም ሌላው ያጨው አያስበውም። አያቅደውም።
የግለሰብ ጥረትን ተከታትሎ ባለው ሥልጣን፤ የኢኮኖሚ አቅም ተጠቅሞ ጉልላት የሆኑ ባለብራንዶችን እያለሳለሱ
ወደ እራስ ማሸጋገር በጥልቀት የታሰበበት፤ ነገን - ያማከለ፤ ከነገ - ወዲያን በራስ ሰብዕና ልክ ሁለገብ የብራንድ፤
የአሻራ ባለቤት ለመሆን ታቅዶ እየተሰራበት ነው።
 
ይህ ሂደት በመደዴ፤ በዘውታ፤ በሞቅታ የተከወነ አይደለም። የመከታተል አቅምን ይጠይቃል። ውርሱን ለማስፈጸም
አቅዶ መነሳትን ይጠይቃል። እንዲህ ዓይነት ሰብዕና "ቢገፋት ይወድቃል፤ አንድ ሃሙስ ቀርቶታል።" ማለቱ እራስን
ሊያጽናና ይችላል። ሂደቱ እና ክንውኑ ግን #በብልጫ እየመራ መሆኑን ያሳያል። ይህን መሰል ውይይት ይኖራል ብሎ
የሚያስብ የለም። ብዙ ነገር ደራሽ ነው። ወደፊትም ደራሽ ይቀጥላል።
 
በዚህ ሂደት ውስጥ የሚያሳስበኝ ዘለግ ያለ፤ ዘለቅ ያለ ብራንድ ያላቸው ወገኖች ብርቱ #ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል።
ባይ ነኝ። የውስጥ ውበታቸው ተፈላጊነት ……… ይህ እነሱ የገነቡት የህይወት መስመር ለእነሱ ምንም ሊሆን ይችላል። 
 
ነገር ግን የብራንድ ናፍቆት - ስስት - ጉጉት ላለበት ግን የሰብዕና ልቅና በልዕልና ጉዳይ ነውና በችለታ የሚታይ ነገ አይኖርም።
" የጎንደር ሰው ልብ ያለው ሸብ" ይላሉ። አጤ ሂደት ይህን ጠይቋል፤ ተጽዕኖ ፈጣሪነትህን፤ ተወዳጅነትህን፤ የቋሚ ብራንድ
ባለቤት መሆንህን ካለ ምንም ቅድመ ሁኔታ #ስጠኝ ሲል። ለጥ ብሎ ሰግዶ ማስረከብ ነው። 
 
ቀደም ባለው ጊዜ ሥልጣን ያስጎመጃል፤ ያጓጓል። አሁን የደከምክበትን፤ የባተልክበትን፤ ክፋ ደጉ ያዬህበትን አስረክብ
ነው። ደስ ብሎህ ለአጤ ሂደት ማስረከብ ነው። በቃ። ለነፍስህ ማደሪያ አማኑኤልን መማጸን ነው።
 
አጤ ሂደት #በሰጨኝ ሊል ስለሚችል ዞርም ማለት ያስፈልጋል - ከተቻለ። ዓይነ ገብ፤ ህሊና - ገብ፤ መሆን
የስለት ልጅነት ነውና ወጀቡም ዶፋም ግፋ በል ሳይል ቋያው፤ ወበቁ ግርፊያ ሳይጀምር ወይና ደጋ ላይ መሰጠትን
ማስጠለል። ከተለመደው ውጪ ጉዳይ ሲገጥም በአመጋገብ፤ በአኗኗር፤ በአኳኋን ዘይቤን ቀየር ይበጃል።
ጥንቃቄ ያተርፋል እንጂ አያከስርም።
 
"ልብ ያለው ሸብ" ቢደምጥ፤ በዛ ውስጥ ለመኖር ቢፈቅድ አብሮ ተማግዶ ስንቁ ማጠር ባልሆነ ነበር። እና
አንድ የህይወት ምዕራፍ በራሱ ጊዜ አዲስ ፈር ሲቀድለት ቁጭ ብሎ ማሰብ፤ ጥሞና ያስፈልጋል። ብርቱ
ጥንቃቄ ካፒቴን መሆን ይችል ዘንድም መፍቀድ ይገባል። ጸሎት በትጋት።
 
ሁሉም ነገር ይረሳ እና ከህወሃት ጋር በተለያዬ ኃላፊነት አብሮ የሰራ፤ ከብረት በተሰራ ቁርጥራጭ፤ ሜታል በሆነ
ዲስፕሊን ከዛ ሁሉ የፊት ረድፍ የህወሃት ሊቃናት፤ ከፍተኛ ማዕረግ ካላቸው መኮነኖች #ቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስተር
ሲሆን ይህ በራሱ እኮ ብዙ በጣም ብዙ የሚያስተምር አመክንዮ ነው። እንዴት ይህ ሊሆን ቻለ? መሆን የማይችለውን
የቻለ ሰብዕና አቃሎ ማየት አይገባም። የኖቤልን ጉዳይም እሰቡት። 
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
03/07/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።


አስተያየቶች