ሃሳብ ጎዳና መሪ ነው፤ ስለምን ይፈራል?
ሃሳብ ጎዳና መሪ ነው፤ ስለምን ይፈራል?
(ቅዱስ ዮሐንስ ምዕራፍ ፩ ቁጥር ፩ - ፫።)
#ምዕራፍ ፲፱።
ሃሳብ ስለምን የቂም ፈል ማምረቻ - ለምን ይሆናል?
ሃሳብ የፖለቲካ #መበቃቀያ---- ስለምን ይሆናል?
ሃሳብ ስለምን እንዲታመቅ ወይንም እንዲታቆር ይፈለጋል?
የልዩነት ሃሳብ #ጠሐይን እንዳያይ ለምን ይበየንበታል?
ሃሳብ ወልጋዳ እንኳን ቢሆን ገርቶ ህዝብ ጠቀም ለማድረግ እንዴት ያቅታል?
ለመሆኑ ፖለቲካ ለሙጃው ወይንስ ለአቦካዶ?
ፖለቲካ ለበቀል መፈልፈያ ወይንስ ለአብሮነት ማብቀያ?
ፖለቲካ ለተፈጥሮ ህልውና ወይንስ ጥቃትን ለማበረታታት?
ትትርናው ሃሳብን #በድቅድቅ ጨለማ እንዲከዘን ስለምን ይፈረድበታል?
" ሁሉ በእርሱ ሆነ፤ ከሆነውም አንዳችስ ስንኳ ያለ እርሱ
አልሆነም። በእርሱ ህይወት ነበረች፥ ህይወትም የሰው
ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ይበራል። ጨለማም
አላሸነፈውም። (ቅዱስ ዮሐንስ ከምዕራፍ ፩ ቁጥር ፫ - ፭)
እኮ ጋብቻ ምንድን ነው?
ጋብቻ ከሃሳብ አይደለምን የሚነሳው?
እናስ --- ጋብቻ የትውልድ መሠረት አይደለምን?
ሥልጣኔ - ታሪክ - ሃይማኖት - ባህል - ወግ - ልማድ
ትውፊት - ዕምነት - ዕውቀት - መኖር - የሃሳብ ውጤቶች አይደሉምን?
ይህ ከሆነ ለምን ሰው የተሰጠውን የማሰብ አቅሙ #ይታሠርበታል?
የማይገባኝም እንዲገባኝም የማልፈቅድለት በሃሳብ ዙሪያ ታቅዶ
#ጥቃት የሚፈጸምበት የፍራቻ አዟሪት ነው።
#ለመሆኑ ………
ፖለቲካ እራሱ የራሱ ማንነት አለው። ቤተ - ፖለቲከኞችም
በተናጠል ይሁን በወል ማንነት አላቸው።
ግጭቱ ከማንነት ቀውስ ጋር የፖለቲካው ርዕዮት ወይንም
ዕሳቤ ከቀውሱ ጋር ከተዋህደ ቋያ ይሆናል። ጠቡም ከሁሉም አመክንዮ
ጋር ይሆናል። በዚህ ውስጥ #ስጋት ይጠነሰሳል። ጥርጣሬ ይፋፋል።
ስጋት --- ፍርሃት --- በራስ መተማመንን - ዘላቂ ተስፋን የሚንድ #ፈንጅ ነው።
በራስ መተማመን ከሌለ አቅል፤ አደብ፤ ስክነት #ይመንናሉ ወይንም ይሰደዳሉ።
በዚህ ውስጥ ብስጭት ዘውድ ይደፋል።
ብስጭቱ የጭካኔ ሞተር ይሆናል። ይህ ገጠመኝ
የርህርህናን፤ የአይዟችሁን፤ የማፅናንት አቅምን ያሰድዳል።
ስደት በራስ ማንነት ውስጥም ይኖራል እያልኩ ነው። ስደት
ከአገር መውጣት ብቻ አይደለም። ከፋክት ጋር ጠብ ካለ
ስደት በራስ ውስጥ ተንሰራፍቷል ማለት ነው።
እራስን ማመን፤ ለራስ ጉዞ እና ትልም በተሰጠው ልክ መሆን
ከተሳነ ስደቱ በራስ ውስጥም ይሆናል።
እና ------- በራስ ውስጥ ስደት፤ በራስ ውስጥ የማንነት ቀውስ
ይህ ሂደት በቀጥታ በትውልድ ተስፋ ላይ ጫና ያበራክታል።
በዚህ ውስጥ #አድን የሆነ ሃሳብ፤ ፈውስ ቀማሪ ሃሳብ ተቀብሮ ሊቀር፤
ለአደባባይ ሳይበቃ የጋን መብራት ሆኖ ሊቀር ይችላል። ወይንም
በጉልበተኞች ሊረሸን ይችላል። የሃሳብ #መረሸን----------
አገር የመከራዋ ሂደት የሚጀምረውም በዚህ መስመር ነው።
በሃሳብ የተፈጠረ የሰው ልጅ፤ ለተፈጠረበት የህልውና ማዕከል
ነፃነት መስጠት ከተሳነው አጤ ሂደት ሲፈጠር ቃሬዛ ላይ ይፈጠራል
መጨረሻውም …………
ሃሳብ የጠራ ይሁን የተስረከረከ፤ የጎሼ ይሁን የተዥጎረጎረ፤ አካል ያለው
ይሁን ያነከሰ ነፃነቱን ሰጥቶ መድረኩን መፍጠር በአንድ በራሱ ላይ
ሙሉ ዕምነት፤ በሙሉ አቅም፤ ሙሉ ኮንፊደንስ በሙሉ አቅል ካለ አገዛዝ
ይሁን አስተዳደር ከሌለ #ጋዳ ነው።
ለቀጣይ የአደራ እርክክብ ይሁን ለማግሥት ተስፋ አስተምሮው
የፍርኃት ግልገል-- የመረባበሽ ደቦል፤ የመሸበር ጫጩት በህሊና ሲጸነስ
የትውልድን ግንባታን ያመሳቅላል።
ስለሆነም በቅርፊቱ ሳይሆን በእንቅጩ መነጋገር ያስፈልጋል። መሸነጋገሉ ቋት አይገፋም።
ትውልድ በስጋት ድግስ አይገነባም። ትውልድ በፍርሃት ቆፈን አይጠነስስም። ትውልድ በጫን ተደል
ጭንቀት አስክኖ መፍጠር አይቻልም።
ስለዚህም የኢትዮጵያ ፖለቲካ #ጥሞና ወስዶ እራሱን ሊያርም፤ እራሱን ፈቅዶ ሊገስጽ
ይገባል። ለማረም ይሁን ለመታረም መፍቀድም የሃሳብ #ጥራት ብቃት እና ድፍረት ያስፈልጋል።
#ክወና።
በነገራችን ላይ የመበቃቀልን ታሪክ ማስቀጠል የክፋ ሃሳብ #ቤተኝነትን መፍቀድ ነው።
አዶኛወቼ ቤተ ሥርጉትሻ እንዴት አድራችሁ አረፈዳችሁልኝ?
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
መሸቢያ ጊዜ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
05/07/926.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ