«#ፍቅር እስከ መቃብር» በደቡብ አፍሪካ። የላቀ #ሐዋርያነት በእማማ አፍሪካ።
"ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም።"
የሐዋርያው፤ የድንግሉ የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ፩ ወደ ቆሮንቶስ ሰወች፦ ምዕራፍ ፲፫ ቁጥር ፰። እኔ ይህ መልዕክትተ - ቆረንቶስ የያዛቸው ዶግማወች ሁሉ የዓለም መዳኛወች ናቸው ብዬ አምናለሁኝ። ከባዶች ናቸው። የሚችሉ ግን ህይወቱን እንዲህ ይኖሩበታል።
ባለጠጋው በመጨረሻም ወደ ህዝብ መጣ! Eyoha Media |Ethiopia | Habesha
የባለጠጋ ሚስት ለመሆን ከሃገር ወጣሁ! ከባዱን የኔን ሚስጥር ዛሬ ላጋራችሁ ነው! Eyoha Media |Ethiopia | Habesha
#ጠብታ።
የዮሃ ሚዲያ ላይ የወጣውን ክፍል ፩ የክብርት ኤንጅልን ታሪክ እህቴ ልካልኝ አዳመጥኩት። ከዛ ክፍል ፪ ስጠብቅ ወጣ እና ሁለት ጊዜ አዳመጥኩት። #ሐዋርያዊ ተልዕኮ ያለው ገጠመኝ ነው።
ለማህበረ ቅንነት በትህትና የማሳስበው መጀመሪያ ክፍል ፩ አድምጦ፤ ክፍል ፪ መቀጠል የሚገባ ይመስለኛል። ታሪኩ ልበወልድ አይደለም። መሠረት ያደረገው የዕውነት #ዕውነትን አድርጎ ነው። ለጋብቻ ውጭ አገር የሄደች ኢትዮጵያዊት ሴት፤ የኤድስ ፈተናን እንደምን እንደተጋፈጠችው፤ የፈጣሪ ስጦታ ከሆኑት ክቡር ሚስተር ኬኒ ጋር ነው ታሪኩ። ይመስጣል። ያስተምራል። የፍቅር ተፈጥሮን የፈተና ስቅዛቶች እና ጀግኖች ሲገኙ ደግም እንደምን መቋቋም እንደሚችል ያስተምራል። ቁሞ #ይሰብካልም።
የገኃዱን ዓለም የሥጋ ፈቃድ ተቋቁሞ፤ እራስን ገዝቶ፤ ፈተናን በዊዝደም ማለፍ ለትውልድ አዲስ የመማሪያ #ካሪክለምም ነው። እንዲህ አይነት ለታማኝነት ፍጽምና ለእኔ ሰማያዊ ቅድስና ነው። የእኔ መስፈርት ለየትኛውም ግንኙነት ተማላ ሳይሆን ፍጹም ታማኝነት ነውና። ለእኔ ከሥነ - ምግባር ሁሉ እንደ ታማኝነት የውስጤ ጌታ የለም። ሰውን እምለካው ታማኝነቱን ነው። ይህን ካጣሁ ይቋረጣል።
የሆነ ሆኖ የመኖርን ለማሸነፍ ለጊዜያዊም ይሁን ለዘለቄታ፤ በተፈጥሮ ምክንያትም፤ በሃይማኖታዊ ዶግማም የሰው ልጅ ትዳር ይመሰርታል። ትዳር ከባዱ የኃላፊነት እና የተጠያቂነት እርካብ ነው።
በህይወት ውስጥ ከሚወሰዱ ወሳኝ እርምጃወች ግዙፋ ትዳር ለመመስረት የሚወሰደው እርምጃ ይመስለኛል። ምክንያቱም የኃላፊነት እና የተጠያቂነቱ ጣራ እና ግድግዳ ከብረት ቁርጥራጭ የተሠራን ጥንካሬን፤ ብርታትን፤ ጽናትን ስለሚጠይቅ።
እነኝህ ጥንዶች ክቡር ሚስተር ኬኒ እና ክብርት ኤንጅል ፈጣሪ የፈጠረውን የትዳር ተልዕኮ በጀግንነት በመወጣት ላይ የሚገኙ ክስተቶች ናቸው።
ስለዚህም ትውልድ ይማርበት ዘንድ፤ የሥጋ ፈቃዳቸው ብቻ ለሚመራቸው አቅመ ደካሞችም ይማሩበት ዘንድ፤ በክፋ ሃሳብ ወረርሽኝ፤ አቅመ ደካሞችን በመተባበር የታደሙ ወገኖች በጋብቻ ዙሪያ የሚፈጽሙትን፤ የፈጸሙትን፤ ወደፊት ሊፈጽሙት የታቀደም ይሁን ያልታቀደ ገጠመኝ በቅጡ የሚገራ፤ የሚያርቅ፤ እኛን እና እኛነትን የሚያስታርቅ ክስተት ስለሆነ ንጹኃንንየበደሉ፤ ንጹኃንን ያስበደሉም፤ #ንስሃ ገብተው፤ እራሳቸውን በጸጸት ፈቅደው ገርፈው ፈጣሪ አምላካቸውን #ይቅርታ ሊጠይቁ የሚገቡ ሰብዕናወችም ስለሚኖሩ ይህ ሐዋርያዊ ክስተት የፊደል ገበታ ሊሆን ይችላል።
ጭንቅላት ድንቢጥም አላት። ይህ የምግባርም፤ የድርጊትም አስተምኽሮ ህሊና ላላቸው ይረዳል። በሥጋ ፈቃድ የሚባንኑ ከንቱወች በየትኛውም ሁኔታ ይኖራሉ። ምንም የማይጎድላቸውን፤ ጤነኛ የሆኑትን ሳይቀር የትዳር አጋራቸውን ገፍተው፤ እንግልትን አምርተው፤ በሰው አገር፤ በስደት አምነዋቸው የተጠጓቸውን ህይወት ላመሰቃቀሉ ሁሉ የሐዋርያው የሚር ኬኒ እራስን የመግዛት ልዩ የመሰጠት አቅም በኽረ - መምህር የሚሆን አስተምህሮ ነው።
#እፍታ።
በክፍል ፩ የእዮሃ ሚዲያ ትሁት አዘጋጅ ኢትዮጵያ ውስጥ የጋብቻ ጥያቄ በጋዜጣ ላይ እንደነበር ግር ብሎታል። ነበር። ኢሠፓ ወድቆ ህወሃት ሥልጣን ሲይዝ ብዙ ጋዜጦች፤ መጽሄቶች ለወረት ተፈቅዶ ነበር።
ስለሆነም በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሰሩ ጋዜጦች ነበሩ። እህታችን ኤንጅልም ይህን ተጠቅማ ነበር፤ በዚህ መስመር ውስጥ ህይወቷን ያገኜችው። በዛን ጊዜ ከአገር መውጣት ጉጉት ነበር። ስለዚህም ኢትዮጵያን ከልቡ የፈቀዱ፤ ያስተዋሉ አንድ የደቡብ አፍሪካ ተወላጅ ክቡር ሚስተር ኬኔ ለጋብቻ ኢትዮጵውያንን ስለመረጡ የጋዜጣ ላይ ውድድር አደረጉ።
ከተወዳደሩ ከ20 የማያንሱ ወጣት ሴቶች አንዷ እህታችን ክብርት ኤንጅል ነበረች። ትህትናዋ ነው እኔ ክብርት እንድል ያስወሰነኝ። ለተከበሩ ሚስተር ኬኔ የክብርት ኤንጅል ደብዳቤው የደረሳቸው ዘግይቶ፤ የተመረጠው ግን ቀድሞ ነበር። በዚህ ውስጥ ነው የእዮብ ፈተና የተከሰተው። ቅዱስ እዮብ የተፈተነበት መንገድ ሌላ ቢሆንም፤ ይህ ደግሞ ረቂቅ በሆነ ደፍረን ልንናገረው፤ ልንጽፍበት በማንችለው ረቂቁ ክቡር ጋብቻ ፒላር በሆነው የኃላፊነት እና የተጠያቂነት ጥልቅ፤ ተፈጥሯዊ ፈተና ነው።
ጥንዶቹ ክቡር ሚስተር ኬኒ እና ክብርት ኤንጅል ፈተናው በወል፤ በጋራ የተወጡበት መስመር በህይወታቸው ውስጥ የእግዚአብሄርን ጥሪ ከልብ፤ ከውስጥ፤ ከህሊና በማድመጥ እና በዛ ቃለ - ህይወት ውስጥ ለመኖር ከመወሰን ይመነጫል።
"በመጀመሪያ ቃል ነበር፥ ቃልም እግዚአብሄር ነበር፤
ቃልም በእግዚአብሄር ዘንድ ነበር። ቃልም እግዚአብሄር ነበር።
ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሄር ዘንድ ነበር። ሁሉ
በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳችስ እንኳን ያለ እርሱ አልሆነም።
በእርሱ ሕይወት ነበረች፤ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች።
ብርሃንም በጨለማ ይበራል። ጨለማም አላሸነፈውም።"
"ቅዱስ ዮሐንስ ምዕራፍ ፩ ከቁጥር ፩ - ፭" በዚህ አካል በሌለው የእግዚአብሄር አገልጋይ ቃለ ወንጌል ውስጥ እነኝህን ባለ ጥሪወች እኔ በግሌ አግኝቻቸዋለሁኝ።
የማከብራችሁ፤ የምናፍቃችሁ የአገሬ ልጆች ሆይ! በዚህ ቃል ውስጥ እነኝህን ጥንዶች እኔ በግሌ አግኝቻቸዋለሁኝ ስል ለፋንታዚ እንዳይመስላችሁ። ከልቤ ነው። ስለሆነም አስተምኽሮው ግዙፍ ስለሆነ ዛሬን ፈቅጄ እና ወድጄ ቅድሚያ ለዚህ #የዳነ፤ #አዳኝ መንፈስ ሸለምኩት።
ክቡር ሚስተር ኬኒ ለዓለማችን ሽልማት ናቸው ብዬ ላስብ ፈቀድኩኝ። ይህን ያህል የጽናት ጀግንነት ዓለማችን ማግኜቷ ተስፋዬን አበራልኝ። የኮርስፖንዳስ ጋብቻ እጅግ ፈታኝ ከምለው ገደላገደል ብለው ይቀለኛል።
የሌላ አገር ዜጋ እግዚአብሄር ለሰጠው ነፍስ ይህን ያህል ጥንቃቄ፤ ይህን ያህል እንደ ክርስቶስ እራስን አሳልፎ መስጠት ከየት ይገኛል? ሁሉም ተሟልቶለት እንኳን፤ ጤነኛ - ብቁ ትዳር ተሰጥቶት እንኳን በሥጋ ፈቃድ #የወፈፈ፤ ያመጣትን እህት የመከፋት ድግስ ደግሶ፤ ትመለስ ብሎ ኢ- ሰብአዊ ድርጊት የሚፈጽም ጨካኝ እና ተበቃይ ጋር ያልተነካካ ብቁ ሰብዕና የሚስተር ኬኒ ድርጊት ከእእምሮ በላይ ነው የሆነብኝ። ዜጋው ላልሆነች ነፍስ ይህን ያህል ግራጫማ ፈተናን ጨምቶ ማስታገስ ሥጦታው የእዮር ነው።
"እግዚአብሄር የሰጠኝን ስጦታ፤ በታማኝነት ስወጣ እግዚአብሄር በእኔ ይኮራል" ይላሉ ክቡር ሚስተር ኬኒ። በፈጣሪያችን በአምላካችን ያላቸው ዕምነት በምድር ያሉ አይመስሉም። በፍጹም።
ከአለም ሁካታ፤ ድልቂያ እና ድብልቅልቅ፤ ግርግር የወጣ ሰብዕና ሽልማት ነው። ስለ ኢትዮጵያም ያላቸው ምልከታ ይለያል። "ቅኝ ያልተገዛችው አገረ ኢትዮጵያ መልካችን እናታችን ናት" ይላሉ። ይህ ወደ ውስጥ የማስተዋል፤ ማስተዋልን የማድመጥ፤ በወሰኑት ውሳኔ የመዝለቅ አቅም ልዩ ጸጋ ነው።
#በመጸሐፍቶቼ አዘውትሬ የፃፍኩት አለ። በፔጄ ላይም አዘወትረዋለሁኝ።
1) እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መክሊት ይዞ ይወለዳል።
2) እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መልዕክት ይዞ ይወለዳል። ፖስተኛ ነው።
3) እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ ጥሪ ይዞ ይወለዳል።
ሦስቱንም በተከበሩ ሚስተር ኬኒ፤ እና በክብርት ኤንጅል ውስጥ አገኜሁኝ። እግዚአብሄርንም አብዝቼ አመሰገንኩኝ። ራስን አሸንፎ፤ መቻልን እንዲህ ማስቻል አናባቢም፤ ተነባቢም ክስተት ነው።
የራስን የእትብትን ታለንት፤ ጥሪ፤ ፖስተኝነት በሚያቀል፤ በሚያጣጥል፤ በሚጠየፍ፤ ለማድነቅ ቀርቶ ለማድመጥ ለመስማት በሚያቅለሸልሸው፤ በሚያቅረው፤ ፈጽሞ የቅርቡን ልቅና ለማቅረብ የማይፈቅድ ገጠመኝ አለ - ና። በብዙ ፈተና ውስጥ ላለፈ ነፍስ ቅንጣት አክብሮት እና አትኩሮት ለመስጠት የሚተናነቀው፤ አልፎም አለርጂው የሆነ የራስ ነፍስ እና ሥጋ ገጠመኝ አለ። ይህን በስማ በለው ሳይሆን በዕውን የማየው የፋክት የወርቅ እንክብል ነው።
እንኳንስ በሞት እና በህይወት ማህል #አሳሯን ለአንድ ሰከንድ፤ ለአንድ ደቂቃ፤ ለአንድ ቀን፤ ለአንድ ሳምንት፤ ለአንድ ወራት አይደለም። ከ፳ ዓመታት በላይ ላለፈ ጊዜ ሚስጥርን ጠብቆ፤ ተስፋ --- ሆኖ፤ ፍቅር -- ሰጥቶ፤ ፍቅር --- ሆኖ፤ ትንፋሽን የሚያስቀጥል ይህን መሰል ደግነት፤ ይህን መሰል አጽናኝነት፤ ይህን መሰል አይዞሽ ባይነት ለእኔ የተራራው ቅዱስ ስብከት ነው።
ለሌላው - ባክነው፤ ለሌላው - ባትለው ለራሳቸው ያልኖሩ፤ ግን ተስፋ የሚመግባቸው የቅርብ ነፍስ ያጡ፤ የነጡ ስደተኛ ምንዱባን መኖራቸውን በተጨባጭ ስለማውቅ፤ የክብርት ኤንጅል ፈተናን ክቡር ሚስተር ኬኒን ስለሰጣት እግዚአብሄርን አዘውትራ ልታመሰግነው ይገባል ባይ ነኝ።
#ለክብርት ኤንጅል።
1) ጠባቂዋን ፈጣሪ ሰጣት።
2) ተስፋዋን በየሰከንዱ የሚያድስ ቅዱስ ሰው ሰጣት።
3) የፈጣሪን ልዩ ምክንያት ጠንቅቆ ተረድቶ ልዩ ውሳኔ የሚሰጥ ሽልማት ፈጣሪ ሰጣት።
4) ከሁሉ ሚስጢሯን ጠብቆ፤ እራሱን የሚገብር ቅዱስ አምላኳ ሰጣት።
5) "ፈጣሪ ከነጎደሏችን ይወደናል" በሚል መርህ የተካኑ የተግባር ሊቀ ጳጳስ ሰጣት።
6) ፈጣሪ አምላክ ለሰው ልጅ የሚሰጠውን ቅን፤ ደግ፤ ርህርህና - በቤቷ፤ በጓዳዋ፤ በመዳፏ እንዲሆን አደረገ። እግዚአብሄር ትልቅ አምላክ ነውና።
#ቀጣይ እርዳታ።
ባለጠጋው ለተሰጠው የመታመን አቅም ስለአበረከተ፤ በቀጣይ ህይወት ለማስቀጠል አለመቻሉን ከቃለ- ምልልሱ ተረዳሁኝ። ስለሆነም በዓለም ያላችሁ የህክምና ባለሙያወች ይህን ጥሪ እባካችሁ መልስ ስጡበት ስል በትህትና እጠይቃለው። ይህን ወደው እና ፈቅደው የሚያግዙ የሰብአዊ ድርጅት ተቋማትም በውጭ አገር አሉ። እነሱንም ማስተባበር አንድ ትልቅ የኃላፊነት መስክ ይመስለኛል። ይቻላልም።
#መላዕክን መንከባከብ የሚል መጸሐፍ።
የተከበሩ ሚስተር ኬኒ የሚዲያ ሰው ናቸው። አነቃቂም ናቸው። ጸሐፊም ናቸው። ስለሆነም በህይወት ታሪካቸው ተኮር የሆነ መጸሐፍ በአማርኛ ቋንቋ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋ በቅርቡ እንደሚወጣ ተናግረዋል። ስለዚህም በመግዛት፤ በማከፋፈል መርዳት ዓለምን ከክፋ ነገር #ጭስ የመታደግ ሐዋርያነት ነውና በዘርፋም ተሳትፎ ማድረግ የተገባ ይመስለኛል።
#ፊልም። "መላዕክን መንከባከብ።"
ይህ መጽሐፍ ወደ ፊልም ለመቀየር የሚያስችል አቅም ስላለው፤ የፊልም ባለሙያወች እንደ ጋሼ ኃይሌ ገሪማ ዓይነት ዓለም ዓቀፍ ዕውቅና ያላቸው የፊልም ባለሙያወችም ትኩረት ቢሰጡት፤ ከሰባዕዊነት አንፃርም የመታደል ቤተኝነትን ያጎለብታል የሚል ዕምነት አለኝ።
#ቃለ ምልልሱን ለማድመጥ ትዕግስትን በአጽህኖት ይጠይቃል። ለምን?
1) አገር ቤት እያለሁ በኤድስ የተጠቃች እህት ድምፆዋ ተቀይሮ ነበር።
2) በሌላ በኩል በሥነ - ልቦና ህመም የተጠቃች አንዲት አንስትም በመጨረሻ መሰል ችግር እንደ ገጠማት አይቻለሁኝ።
3) በከፋ እና በመረረ ሃዘንም ቋንቋወች ይሰወራሉ።
4) ውጭ አገር ረጅም ጊዜ የኖሩም በአማርኛ ቋንቋ ሆነ በሌሎች አገራዊ ቋንቋወች በአገላለጽ ሊቸገሩ ይችላሉ።
5) ውጭ አገር ተወልደው የሚያድጉም ልጆች የቃና ዘያቸው የሚጣፍጥ ግን ያልተሟላ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ትዕግሥትን ይጠይቃል ማለት ነው።
ይህን የፃፍኩት ክብርት ኤንጅል በአንዱ ወይንም በአመዛኙ ምክንያት የአገላለጽ ችግር ሊኖርባት ይችላል። እኔ ክፍል ፩ ይሁን ፪ በደንም አዳምጨዋለሁኝ። ሁለተኛውን ደግሜ አዳምጨዋለሁኝ። በሚገባ ተረድቸዋለሁኝ።
የአገላለፆዋ ቃና ለእኔ ጥሞኝ ነው ያዳመጥኩት። ለሁሉም "#ውዴ" የምትለው የአጠራር ዘይቤዋ የሰብዕናዋን የትህትና የውሃ ልክ ያዬሁበት ክስተት ነው። ሁለት ደጎችን ፈጣሪ አገናኜ። ግን ዳጥ እና ምጥ የሆነ የፈተና ጋራ /// #በጋር ገጠማቸው። ሁለቱም ግን 150% ተወጥተውታል።
#በእግዚአብሄር ተስፋ ውስጥ የከተሙት ክቡር ሚስተር ኬኒ።
1) ሚስተር ኬኒ ዕውነተኛ የሰባዕዊ መብት ተሟጋችነትን በህይወታቸው ውስጥ እንደ ወርቅ ተፈትነው ያሳኩ የድርጊት ጀግና ናቸው - ለእኔ። ስለሆነም ኢትዮጵያ አገራችን፤ አፍሪካ አህጉራችን ሊሸልሟቸው ይገባል። ዓለምዓቀፍ የኤድስ ተቋማትም ይህን ጉዳይ ባሊህ ቢሉት ጥሩ ነው።
2) ክቡር ሚስተር ኬኒ በፈጣሪያቸው ላይ ያላቸው ዕምነት መንፈስ ቅዱስ ነው። አሁንም - ለእኔ።
3) ክቡር ሚስተርኬኒ አሁንም፤ ዛሬም በኤድስ ህመም እና በተያያዥ ህመም ከምትንገላታው አጋራቸው ልጅን ተስፋ ያደርጋሉ።
ያው ቀደም ባለው ጊዜ እንደምታውቁት እኔ ለተስፋ ትጉህ ነኝ። #ተስፋ የመጀመሪያው የዓዋቂወች የሥነ - ግጥም መጽሐፌ ነው።። ሁልጊዜ በጸጋዬ ራዲዮ ሙሉ ፲፰ ዓመታት መግቢያው በተስፋ ነው። ወላጆች ልጆቻቸውን እንዴት ሊይዙ ይገባል የሚለው ፮ኛው መጽሐፌም #የተስፋ በር ነው ዕርዕሱ።
በተስፋ፤ ስለተስፋ ተቆርቋሪው ነኝ። እና ይህን በዕውን በክቡር ሚስተር ኬኒ አግኝቻለሁኝ። ተስፋ መኖር፤ እርቅ፤ ምህረት፤ መዳን፤ ሥርየት፤ ይቅርታ፤ ቀና ጎዳና፤ ትህትና፤ የሰላም ሐዋርያ፤ የፍቅር ተፈጥሮ ቅዱስ ምስባክ ወዘተ ነው።
ቤተ - ሚስተር ኬኒ ሃሳባቸውን እግዚአብሄር አሳክቶ ምዕራፍ ፫ በክብሩ ልክ ያከበሩት ንጉሥ ክርስቶስ ደግሞ ያሳቡትን አሳክቶ፤ በህይወትም አቆይቶ ያገናኜን ዘንድ እለምነዋለሁኝ።
ማህበረ ቅንነት እዮኃ ሚዲያ ውስጥ ገብታችሁ ታሪኩን ታዳምጡት፤ ትማሩበት፤ እርዳታ ለሚያስፈልገው ቤተሰብም አይዟችሁን በትህትና ሰጥታችሁ ከአማኑኤል በረከትን ታፍሱበት ዘንድ በአክብሮት አሳስባችኋለሁኝ።
እዮኃ ሚዲያ እና ቲሙን ዓለምን ለሚያድን ይህን መሰል የቅድስና ዕውናዊነት የያዘ መስናዶ ስለአቀረበልን ምስጋናዬ ከህሊናዬ ነው። ተባረኩልኝ። አሜን።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie።
21/03/2026።
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ