የአማራ ትግል የህልውና ከተባለ ለምን "መግደል፤ መጨከን፤ ማስጋት፤ #ዛቻ አጀንዳ ሊሆን ቻለ?

 

የአማራ ትግል የህልውና ከተባለ ለምን "መግደል፤ መጨከን፤ ማስጋት፤ #ዛቻ አጀንዳ ሊሆን ቻለ?
 
የሰው ልጅ ሰርክ ሞቱ ከሆነ እንደ እህል #ያልቃል?
#መገደልን ለማስቆም አነጣጥሮ #መግደል መፍትሄ አይሆንም።
ማስጨነቅን ለማስቆም ጫናዊ ማስጨነቅ ጎዳና ሊሆን አይችልም።
መሳደድን ሃራም ለማለት #ዛቻ ስጦታ ሊሆን አይገባም።
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 
#ምዕራፍ ፲፰።
 
እኔ የአማራን ትግል በሁለት ከፍዬ አየዋለሁኝ።
 
1) የማንነት ትግል።
2) የህልውና ትግል ብዬ።
 
ይህን የምልበትን አመክንዮ ፌስቡክም ሳልጀምር፤ ከ፲፪ ዓመታት በላይ ብዙ ጊዜ በዝርዝር ስለፃፍኩበት ደክሞኛል። የአሁኑ ዝምታዬም ማህበራዊ መሠረቱ የተናደበት ሁሉ ወደ ዘርፋ #ስለተመመ በጥሞና ማድመጡ ይበቃል ብዬ ስለወሰንኩኝ ነው።
 
"በሉት! በርቱ! አሳዱት! ግረፋት!" የሚላችሁ የሚዲያ ባለቤት ሁሉ ሙሉ ሦስት ዓመታት የተፈጠሩበት የደቡብ ቀጠና፤ ለብልጽግና ቀጥ ለጥ ሰጥ ብሎ እየተገዛ መኖሩን አስከብሮ ይገኛል። ደቡብ ጫካ ጠፍቶ ነውን አንድ የፋኖ ሻለቃ ማደራጀት ያቃተው? ዛሬ በብልፄው ካቢኔ ውስጥ 50+ ደቡብ ነው። በዘመነ ህወሃትም እንዲሁ።
 
ድል ቢቃረብ እዛው ሚዲያቸው ላይ እንደተለመደው የእንቶኔ የነፃነት ፋኖ ተብሎ ተደራጅቶ የድል አጥቢያነቱን ሲታወጅ እናዳምጣለን። አሁን ግን ሰርክ ሞት፤ መከራ፤ ጭንቅ፤ ፍርሃት በገፍ ይቀናለታል ለአማራ "ጀግና" በሚል ቅጥያ። 
 
እነሱ ህዝባቸው #ማገዶ እንዲሆን ፈጽሞ አይፈቅዱም። ፡ተቋሞቻቸው ደርጅተው ሙሉ አገልግሎት እንዲሰጡ፤ ተጨማሪም አዳዲስ ፕሮጀክቶች ተወጥነው ከግብ እንዲደርሱ ነው የሚጥሩት። በብልፄው መዋቅርም ከውጭ ጉዳይ ጀምሮ ደህንነቱም የጠቅላዩ የጽህፈት ቤት ኃላፊም በጭምቱ ደቡባውያን የተጥለቀለቀ ነው።
 
የደቡብ ሊቆቻቸው ያስተዋሉ ናቸው። ነዲዱን በባዕታቸው አይፈቅዱም። ፈጽሞ። ህዝባቸው የውስጥ ሰላሙ እንዲታወክ አይፈልጉም። እህሳ? የተንጠራራ ሚዲያ ዲያስፖራ ላይ ይደራጃል፤ አንጋቹ አማራ በየዘመኑ ይማገዳል???? ትናንትም ዛሬም በማያባራ ሁኔታ ማገዶው ገራገሩ እና ቅኑ አማራዬ ነው። የአብነት ትምህርት ቤት ሊቃናት ጎጃም፤ የፖለቲካ ሊቃናት ጎንደር ላይ ይገበራል። የሰው ግብር የማይሰለቻቸው። 
 
ህወሃትን ፈቅዶ ከመንበሩ ያስነሳው የጫካ ትግል አይደለም። በሰላማዊ ትግል የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶችም አልነበሩም። የጨመቱ ብልሆች በተከታታይ በሰሩት ጠንካራ እና ትጋት ያልተለየው ተግባር ነበር ፈቃደ እግዚአብሄር ታክሎበት የሆነው፤ የሆነው። 
 
የፋኖ ትግል አነሳሱም ሆነ ሂደቱን ስመለከተው የገዘፈ መስዋዕትነት የተከፈለበት ነው። በዚህ ምክንያት መስዋዕትነትን የቀነሱ ብዙ በጣም ብዙ በሰላማዊ ትግል ብቻ የሚገኙ በረከቶችም እንደ ተወጠኑ #ጊዜው አለፈባቸው። ዛሬ ዓለማችን ሌላ ትራጀዲ ውስጥ ናት። ጨርሶም ማሰብ አይቻልም። ለዓለማችን የቅደም ተከተል ጥያቄ ስለሚያፋጥጣት።
 
የሆነ ሆኖ የከተማ ኑሮ፤ የድሎት ኑሮ፤ የመሃያ ኑሮ ይበቃኛል፤ የተፈጠርኩበትን ህዝብ የመኖርም፤ የመከበርም፤ እኩል የመደመጥም፤ እኩል የፖለቲካ የውክልና አቅምን ለማምጣት፤ ብልፄው አልሰማኝም በዱር ቤቴ አሳካለሁ በሚል የፋኖ ትግል ከተጀመረ ስለምን የአማራ ልጅ ተጨማሪ ጭንቅ ውስጥ እንዲገባ ይደረጋል? ለምንስ ይገደላል በራሱ ልጆች? ለምን #ዛቻ ይታዘዝበታል በራሱ ፍሬወች? 
 
የአማራ ህዝብ የሚያዋጣውን ያውቃል። ወጀቡን ለማሳለፍ እንደምን መሻገር እንዳለበት የህይወት ዘመኑ መምህሩ ነው። እና? ስለምንስ የፈቀደውን፤ የወደደውን፤ ይመቸኛል ያለውን መርጦ መኖሩን እንዲመራ #አይፈቀድለትም። 
 
ፋኖ የሚይዛቸውን ከተማ ይዞ፤ ማስተዳደር በቋሚነት ካልቻለ፤ በመንግሥት በኩልም የህዝብን መገበር ካልፈለገ በስተቀር ለምን ቢያንስ በከተሞች ያለውን ሰላማዊ ህዝብ የመኖር ዋስትናውን አያስጠብቅለትም??? ይህ ህዝብ ማንን ይመን? ማንንስ ይጠጋ? ማንንስ ተስፋ ያድርግ?
 
መቸስ ከቋያ /// ቋያ …………
ከነዲድ /// ነዲድ …………
ከረመጥ እረመጥ አይመረጥምና??? …………
 
ከ35 - 50 ሚሊዮን የሚጠጋ የአማራ ህዝብ ጫካ ልውጣ ቢል ይቻለዋልን? ልፋንን ቢል? ልሰደድስ ቢል ይሆንለታልን? ስለምን እነኝህ አመክንዮወች በጥሞና ተመርምረው ህዝብን ከስጋት፤ ከጭንቀት፤ ከመታገት፤ ከሞት የሚታገድ መስመር መከተል ያቅታል???
በሌላ በኩል ደግሞ ፋኖ ማረኳቸው የሚላቸውን የራሱን ቤተሰቦች ለጊዜው ይዞ፤ መክሮ፤ አስተምሮ ወደ ቀየው መመለስ ወይንስ ገድሎ መቀጣጫ አድርጎ መራራ ስንብቱን እንደ ድል፤ እንደ ፌስታ መቁጠር? የትኛው ይሆን ለአማራ ተጋድሎ ጠቃሚው መንገድ? ሰው እኮ እንደ እህል #ያልቃል
 
እኔ ጋይንት አውራጃን በሚገባ ነው እማውቀው። ሦስት ወረዳወች ነበሩት።
 
1) ላይ ጋይንት።
2) ታች ጋይንት።
3) ስማዳ የስይቴ ነጭ ጤፍ የሚመረትበት ማለት ነው።
 
ጋይንት ደጋ ነው። ህዝቡ ለቃሉ ያደረ ጠንካራ፤ ንብ የሆነ ህዝብ ነው የሚኖርበት። ቤቱ እራሱ በሌሎች የጎንደር አውራጃ እና ወረዳወች ያላየኋቸው ነበሩ። ፎቅና ምድር ይበዛበታል። መሬት የያዘ ከሆነም #በጅብ ገደል ነው የሚሠራው። ይህ ማለት ግማሹ በድንጋይ ነው የሚታነጸው። ለዚህም ነው #ራስ ጋይንት የሚባለው። የገብርዬ መፍለቂያም ራስ ጋይንት ነው።
 
እያንዳንዱን ገበሬ መንደር በአካል ነው እኔ የማውቀው። በጣም ማተበኛ፤ ጠንካራ፤ ጽኑ ህዝብ ነው የጋይንት ህዝብ። ምክትል ከንቲባውን ፋኖ ቃለ- ምልልስ ሲያደርግላቸው አየሁኝ። ያ ……… ሰብዕና በውስጡ እራስን ለማስከበር ወይንስ በዝቅታ እንዲታይ ለማድረግ ይሆን የቀረበው። ከውስጤ አዝኛለሁኝ።
 
የአማራ ሊቃናት በብልጽግናም ይሁን በፋኖ በብዛት ያለቁት ጎንደሬወች ናቸው። ሙሉ ፲ ዓመታት የፖለቲካ ሊቃናቱ በአንድም በሌላም ተሰውተዋል። ይህን ክፍተት ለመሙላትም ለነገም ይቸግራል። ለምን? ትምህርት ቁሟል። ትምህርት መቆሙ ብቻ ሳይሆን በገባ ወጣነት የሚማሩ ቢኖሩ እንኳን በስጋት እና በጭንቀት ቀለሙን ወይንስ ፍርሃትን ይማሩት????
 
1) የት ይድረስ ይህ ህዝብ?
2) የት ይጠጋ? 
 
እያንዳንዱ አባወራ ቤተሰብ አለው። ቢያንስ አንድ ሰው ለአምስት ነፍሶች ተጠሪ ነው። አንድ ሰው በሥጋ ሲለይ አምስት ነፍሶች የጎዳና ተዳዳሪ ይሆናሉ? 
 
ይህ ክብር ነው?
ይህ ማዕረግ ነውን?
ይህ ሰማዕቱን ዶር አንባቸው መኮነንን ያስደስታልን?
ይህ ጀግና ሻለቃ አጣናው ዋሴን ያስደስታልን?
ይህ ጄኒራል ኃይሌ መለስን በአጸደ ነፍስ እረፍት ይሰጥ ይሆን?
ይህ ሻለቃ አጥናፋ ገላውን ነፍሱን እረፍት ይሰጣት ይሆን?
 
1) ፋኖወች ብትገዙ የሰለጠነ የፖለቲካ ሊቅ - ከጎንደሬወች አትፈልጉምን?
2) አሁንም ፋኖወች ዕድል ቢያጸድቅላችሁ የተደራጁ ከተሞች አያስፈልጋችሁምን?
3) ፍርሃት፤ ስጋት ያለበት ሰብዕ በራስ የመተማመን አቅሙ ይሟሽሻል። በራስ የመተማመን አቅሙ ከሟሸሸ ደግሞ በሽተኝነት አይቀሬ ነው። ህመምተኛ ያውም የሥነ - ልቦና ሰብዕና ምን ኃላፊነት እና ተጠያቂነት ሊወጣ ይችል ይሆን? በወና የፖለቲካ ውክልና አዲስ ምዕራፍ ቢኖራችሁ ዕድል ቢቀናችሁስ - ሐሤታችሁ የት ላይ ሊያርፍ ይችል ይሆን? ጸጸት አንድን ሰው ከሞት መልሶት አያውቅም? አንድ ሰብ ደግሞ ያው እራሱ ብቻ ነው። ለዚህም ነው የሰው ኮፒ የሌለው።
 
4) ፋኖወች በምታስቡት አዲስ ስርዓት ውስጥ ስንት ጠቅላይ ሚኒስተር ይኖር ይሆን? ይህን ያህል የሚከፈለው ግብር ስንት የአማራ የካቢኔ አባላት ይኖራችኋል? ክልላት የአማራ ብቻ አይደሉም እና???? 
 
በምንም ተአምር ከጎንደሬ ጠቅላይ ሚኒስተር ፈቃድ ያገኛል ብላችሁ ሃሳቡን እንኳን አታስቡት። ፋኖ ውባንተ ሲሰው ዜናው በማን ይሠራ ነበር? በጥልቀት እሰቡት። ትማገዳላችሁ ግን ለመሪ ዜናነት እንኳን በቅታችሁ አላየሁም። እእ። እንኳንስ ቤተ- መንግሥት ጠቅልሎ ለመያዝ ???? ይህም ብቻ አይደለም በአማራ ሰማዕትነት ሌላ ፈጽሞ የማታስቡት ገጠመኝ ነው ትወናው የሚሆነው? 
 
ህወሃትን መንበሩን በማስለቀቅ በድምጽ አገር ቤት፤ ውጭ በሎቢ የአማራ ቀመራዊ ስኬት ነበር። ግን አማራ የእዳሪ ልጅነት ያህል እንኳን ክብርም ዕውቅናም እስከዚህች ደቂቃ ድረስ አላየሁም። በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ በዓቱ የጦርነት ዓውድማ ነው የሆነው።
 
መገደልን ለማስቆም መግደል መፍትሄ አይደለም።
 ማስጨነቅን ለማስቆም ማስጨነቅ ጎዳና ሊሆን አይገባም።
መሳደድን ሃራም ለማለት ዛቻ ተስፋ አይደለም።
 
ነፃነት ስለ አንድ ሰው ከማሰብ ይነሳል። ተስፋ ያጣ ህዝብ ተስፋውን አለምልሞ፤ አስብሎ መመገብ ተስፋ እንጂ ጠቀራ ገጠመኝ ፈጥሮ ማስጨነቅ ለአማራ ህዝብ ተስፋው ሊሆን ፈጽሞ አይችልም። ሙሉ ለ፲ ዓመታት ጎንደር እና ጎጃም በዕቱ ለምን ቀራንዮ እንዲሆን ይፈቀዳል?
 
በህክምና ዘርፍ ያለቁትን ዘመን የማይተካቸውን እሰቡት? በመታገድ፤ በመሰወር የተሰቃዩትን እሰቡ። በመፈናቀል የተሰቃዩት ይታሰቡ። በመደፈር የተንገላቱትን አስሉት። ህፃናቱ ከትምህርት ገበታ የተገለሉበት ሁነትን ገምግሙት። 
 
ተጎጂው፤ ተገባሪው፤ ተሳቃቂው፤ የመሞከሪያ ጣቢያው የአማራ በዓት እና ህዝብ ነው። ይህም ሆኖ የአንድ የአማራን ልጅ ነፍስ በሰብአዊነትም እዩት። መሬቱ በድሮን፤ በከባድ መሳሪያ ሲነድ የአየር ንብረት ይዛባል። ብርቅዬ እንሰሳት ይሰደዳሉ። መሬቱ መርዝ ያበቅላል። ትውልዱ አካሉን ያጣ ሊሆን ይችላል።
 
ከሁሉ ጠያፋ ነገር ህወሃት ፈጽሞ ሊዬው፤ ሊሰማው የማይፈልገው ነገር #ጎንደሬነትን ነው። የሚሆነው ሁሉ፤ የሚደረገው ሁሉ ለህወሃት ሊቃናት ሠርግና መልስ ነው። የህወሃት ምርኮኝነት በምን ስሌት? በምን ሂሳብ???? በጦርነቱ ዕድል ሲያገኝ ንፋስ መውጫ ላይ ምን እንዳደረገ ያላችሁበት ነው። የህወሃት የበቀል ሠርገኝነት በራስ ላይ መፈጸም????? ኦ! አምላኬ።
  
 
 https://www.bbc.com/amharic/articles/c0mj018z432o

"በደቡብ ጎንደር ዞን የፋኖ ኃይሎች በፈጸሙት ጥቃት ባለሥልጣናት መገደላቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ
ከ 4 ሰአት በፊት
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የፋኖ ኃይሎች በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ስር በሚገኙ "የሥራ ኃላፊዎች እና የፀጥታ መዋቅር" ላይ በፈጸሙት ጥቃት ቁጥራቸው ያልተገለጸ ባለሥልጣናት መገደላቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ የደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳደር ምንጭ፤ የወረዳ ዋና አስተዳዳሪዎችን ጨምሮ ቢያንስ አምስት የአካባቢው ባለሥልጣናት እንደተገደሉ ገልጸዋል።

ከአንድ ወር በፊት በዋና ከተማው ደብረ ታቦር የሚገኙ የመንግሥት ተቋማትን ያወደመ ጥቃት ያስተናገደው የደቡብ ጎንደር ዞን፤ በመዋቅሮቹ ላይ ጥቃት የተፈጸመው ረቡዕ መጋቢት 09/2018 ዓ.ም. እንደሆነ ገልጿል።" .....
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ኑሩልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ.
Sergute©Selassie.
21/03/2026
 
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።