#በአናርኪዝም ውስጥ ተስፋም፤ ሰላምም ሊበቅል አይችልም። #ኢትዮጵያኒዝም እና #ህወሃት።
• #በአናርኪዝም ውስጥ ተስፋም፤ ሰላምም ሊበቅል አይችልም።
"ህግ ተላላፊወችን ጠላሁኝ።"
#ምዕራፍ ፲፱።
#ጠብታ።
እንዴት ናችሁ ማህበረ ቅንነት? ደህና ናችሁ ወይ? እጅግ አድካሚው፤ እጅግ አሰልቺው፤ እጅግም ግትሩ የዞግ የፖለቲካ ድርጅት ህወሃትን ተሸክማ የኖረች ኢትዮጵያ መጥኔ ለእሷ፤ ለትግራይ እናቶችም መጥኔ።
#የማይደመጥ የለ።
ህወሃት እና #ጠማዳ ድርጊቱን እያዳመጥኩ፤ እያዬሁም ነበር ያደኩት። ስለሆነም አንዲት ደቂቃ ለህወሃት ብኰሩና አቅም አፍስሼ አላውቅም። ተሰቃይተን ነው ያደግነው። ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ዘወትር ሲያለቅስ ይኖራል እንዲሉ።
ሰሜን ጎንደር ሙሉ ዘመኑን በህወሃት በጋመ የበቀል ወላፈን ሲንገረገብ ኖሯል። ይህ በስማ በለው ሳይሆን ኖሬበት፤ ህይወቱን ያዬሁበት ነው። ለረጅም ዓመታት በምድር የሚታዩ በደሎችን ፈጽሞ፤ ያ ሳያረካው ሲቀር ቅዳሜ ገብያን በስልጣን ዘመኑ አነደደ።
የክልሉን ወሰን በማንአለብኝነት ጥሶም ሰብዕናን ተዳፈረ። የህወሃት መራራ ስንብቱ በኢትዮጵያ መንበረ መንግሥቱ የተፈጸመው #ሐምሌ ፭ ነበር። ያን መሰል አዋራጅ ጥቃት ተሸክሞ መዝለቅ አልቻልንም። መቻልም ልክ አለው። ትዕግሥት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል። ፍቅርም ሲያልቅ ትዕግሥት ይሰደዳል።
ህወሃት ቢያውቅበት ለትግራይ ቅርቡ ጎንደር ነው። ሁለመናው ውህድ ነው። ሁለመናው ፌክ ያልሆነ ተፈጥሯዊ ነው። ጋብቻው፤ የሃይማኖቱ ሂደት፤ የመማር ማስተማሩ፤ የሊቃውንታት የመኖር ጥበብ ልዩ ነበር። ጎንደሬ አብዛኛው ሥሙ የኋንስ ነው። ይህ ደግሞ ፈቅዶ እና ወዶ የሚፈጽመው የጎንደሬ ንጥር ዕውነቱ ነው።
ሌላው እቴጌ ትግራይ በከፋት ቁጥር የቅርብ የልብ አድራሿ እቴጌ ጎንደር ናት። ብዙ የተፈጥሮ መከራ እቴጌ ትግራይ አስተናግዳለች። እናታዊ ጓዳዋ እቴጌ ጎንደር ነበረች። ወደፊትም እንደ ተሰጣት ጎንደሪና እንድትቀጥል ምኞቴ ነው። የሊቃውንቱ መወራከብ ምርቃታችን ሊፈትነው ሆነ ሊያስተኛ አይገባም።
የሆነ ሆኖ አቤቱ ህወሃት ከጽንሰቱ ጀምሮ እስከ ስንብቱ ደግሞ የቀጠቀጣት እቴጌ ጎንደርን ነው። በብዙ ሁኔታ ህወሃት በንዴት ጦፎ ጸጉሩ ጭራሮ ሆኖ የሚቆመው ጎንደር ሲነሳ ነው። ፋክክሩ ጤናማ ነው። ሁለቱም በታሪክ፤ በትውፊት፤ በባህል በወግ፤ በዊዝደም በቀደምትነት ዝልቅ ጹዑም ማንነት ቢፎካከሩ የተገባ ነው። ተቀራራቢ ጸጋ እና በረከት አላቸውና።
በተለይ በመንፈሳዊ የብቃት ልዕልና ይሁን ልቅና። ስለሆነም አወንታዊ ቅናትም ይለፍ ሊሰጣው ይችላል። በጠላትነት መተያዬት፤ በበቀል ፋስ ጊዜ ሰጠኝ ብሎ መከሳከሱ ግን የርግማን ነው። ምርቃትም ያስነሳል።
#የማይደመጥ ጉድ የለም ህወሃትን ናፋቂ #ጎንደሬ ሳደምጥ፤ ሳይ ይቀፈኛል? የገረመኝ ሰሞኑን አንድ ቃለ ምልልስ ሳዳምጥ "አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ጠቅላይ ሚኒስተር ቢሆኑ ኖሮ" የሚል ተረበኛ ዕድምታ አድምጫለሁኝ። ድንገቴው የመንበረ መንግሥት ህወሃት ሥልጣን መልካም ድንጋጤ ዱብ ዕዳው የሁሉ ስለመሆኑ አስተዋልክ።
ለዚህ ነው የዘመን ለውጡ ድርሻውን ለፈጣሪ እንስጠው የሚለው። ማንም ባላሰበው ሁኔታ ዊዝደም ስለነበረ። ይህን ያለማወቅም ነው ብዙ ዕድሎች ባለቤት አጥተው መቆም ተስኗቸው የምናዬው።
በተነሳው ጉዳይ ላይ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ይሁኑ የሚል ይለፍ የዲፕሎማሲው ዓለም በእጅ አይልም ነበር። ይህን ጎምዛዛ ዕውነት በሃቅነቱ መቀበል በጸጸት እራስን በየጊዜው ከመግረፍ ይፈውሳል። መታገል፤ መልፋት ብቻውን ለድል አያበቃም። ዒላማ በመደዴ አይለቀቅም እና። ያ ከሆነ ተስፋው ይከሽፋል። ቃለ ምልልሱን እያዳመጥኩ እስቅ ነበር።
እንዲህም እንዲያም፤ መሰናዶ ቢስ ከተሆነ ለምን ይደከማል? የውርንጫ ድካም። ይልቅ የሚጠቅመው የፖለቲካ መሪነቱን በብቃት ለማስኬድ አቅሙ አልነበረንም - ያስማማናል። ምን ችግር አለ ማገዶነቱ ማስቀጥል የሚጎድልበት አክተር በኢትዮጵያ ፖለቲካ የለም --- ና። ብዙ የለፋ መንፈስ የመሪነት ቀጣይ አቅምን ለመተንበይ እንዲህም አቅም ሲያንሰው ሰማዕታቱ አንጀቴን ይበሉኛል። መሪነት #ነብይነትንም አምጦ መውለድ ይጠይቃል።
ያ ሽግሽግ አይጥመኝም፤ አልጣመኝም ያለ መንፈስ እኮ አየር መንገድ ላይ ወረፋ አይዝም ነበር። በብዙ ክብራዊ አቀባበል እና ሽልማት ቅምጥልጥል ሲባል ተባጅቶ አሁን ማጣወር ይቀፋል። በሌላ በኩል ጊዜ ቢገኝስ ስንት ዘመን ይፈጅ ነበር ሽፈራዊዝምን አሰናብቶ የራስን አቅም ለመትከል? ዕውነቱ ግን ህወሃትን ለመንቀል ሆነ ለመትከል ድካሙ ነበር፤ የብልህነት አቅሙ አልነበረም።
አፈፃጸሙም ዱብ እዳነቱ ለሁሉም የነበረው ለዚህ ነው። ለወደፊትም ድካምን መጥኖ በሚያሳኩት ላይ አቅም ማፍሰስ ጠቃሚ ይመስለኛል። ይህ መስዋዕትነቱን በተለይ የንጹኃንን ይቀንሳል። "ልክን ማወቅ ከልክ ያደርሳል" የጎንደሮች ብልህነት ይጠቅማል።
#ቁም ነገር።
ኢትዮጵያን እንደ አንድ ሌላ የአፍሪካ አገር አትታይም። በግልጽም ይሁን በረቀቀ መንገድ ቀልባቸውን፤ አደባቸውን የሚለግሷት ታላላቅ የፖለቲካ ሊቃናት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ አሏት። ወጀብ ውስጥም ብትሆን ነበልባል ቢታከልም እንዳሻው አትባልም ……… ኢትዮጵያ። በበ2013 እኢአ ኢትዮጵያ ረቂቅ መንፈስ ናት ብዬ የፃፍኩትም ለዚህ ነው።
የሆነ ሆኖ እስኪ ከ10 ዓመት ወዲህ ያለውን ጊዜ እንኳን ብንመለከት ህወሃት 24 ሰዓት ስብሰባ ላይ ነው። ስብሰባው መዋለ ንዋይ ነው። ብክነት። መደበኛ ሥራቸው ህወሃት ተኮር የሆኑ ሚዲያወችም ጉሮሮ ሆኗል ነገረ ህወሃት። ህወሃት ያው ልዝ እና ፍዝ ሃሳቡን ይዞ ያምሳል። ይህ የወንበር ሥልጣን የሚባል ነገር በሽታ መሆኑን ዛሬ ዛሬ ተረድቻለሁኝ።
ለመሆኑ ኢትዮጵያ እና ዜጋዋ ይህን ያህል በህወሃት ምክንያት አሳር ማዬት አለባቸውን? ሁልጊዜ ውልግድግድ ያለ ዕሳቤ እና ረብሻ፤ ሰላም መንሳት ለየትኛው ትውልድ ሊጠቅም ይችል ይሆን?
ብዙ ጭካኔን የመራ መንፈስ ተሸክሞ ዳግም ኢትዮጵያን መመኜት የጅልነትም ዓይነት አለው። ህወሃት ዕድሉን አፍስሷል። ደግሞም የኢትዮጵያን የቁንጮ መሪነት፤ አራጊ ፈጣሪነት ያገኜዋል ብዬ አላስብም። ወርቅ ከቀለጠ አይታፈስም። በፈርኃ እግዚአብሄር ሥር መሆን ተሳነ። አሁን መዝለፍለፍ። እሱ ብቻ ሳይሆን በአፍቅሮተ ህወሃት የተከዘኑ ነፍሶችም ስላሉ ነፍስ ይማር ብለናል።
ለህወሃት ኢትዮጵያኒዝም በውስጡ ተፈጥሮ አያውቅም። የነፃነት ግንባር በሚል ማንኛውም መንፈስ አገር ተሰርዛ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ኢትዮጵያን ህወሃት የሚቀናባትን፤ የሚጠላትን አገር ነበረች ህወሃት ይሁን ቤተኞቹ ግንባሮች ለኢትዮጵያ አልታገሉም። ሰማዕትነትንም አልተቀበሉላትም።
አቤቱ ህወሃት በለስ ቀንቶት ለረጅም ጊዜ መሪ ዓውራ ሆነ። ለዚህም ነው መንበረ መንግሥቱን ፈቅዶ ለቆ እንኳን በልኩ የራሱን ድርሻ ለመወጣት እንዲህ ተሳነው። ሲባትት፤ ሲባንን፤ ሲያጣውር፤ ሲያሳቅል ውሎ ያድራል።
ኢትዮጵያዊነት ከህግ በላይ የማያደርግ፤ "በህግ አምላክን" የሚያከብር ልዩ ጸጋ ነው። ህወሃት ደግሞ ከህግ በላይ ነኝ፤ ህጉ እኔ እንጂ ኢትዮጵያዊነት አይደለም ባይ ነው። የህወሃት ልጆች እና የልጅ ልጆችም የሰማይ እና የምድሩን ህግ ሲጠቀጥቁ ቅጭጭ አይላቸውም። ፈርኃ እግዚአብሄር፤ ፈርኃ አላህ ስደት ላይ ነው በኢትዮጵያ ፖለቲካ።
ህወሃት ከዛ ሁሉ ውድመት፤ ድቀት፤ አመድነት በኋላ ፈጣሪ ረድቶት ትንፋሹ መቀጠሉን ተመስገን ብሎ፤ ከጥፋቱ ተጸጽቶ፤ የኢትዮጵያ ህዝብን ይቅርታ ጠይቆ፤ በእጅጉ ተጸጽቶ እራሱ በአረቀቀው፤ ባጸደቀው፤ ሥራ ላይ ባዋለው ህገ - መንግሥት መመራት፤ እራሱ ያዋቀረውን የምርጫ ቦርድ ድንጋጌ ተቀብሎ እራሱን በዛ ማስገዛት ሲገባው "ታጥቦ ጭቃ" ነው የሆነው።
እንሆ አሁን ህግ ጥሶ፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ተፈታትኖ መሪው እኔ ነኝ ሲል ቁልጭ ያለ አናርኪዝም ነው። አንድ ሙሉ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ሰብዕ እንደምን የአናርኪዝም ደጋፊ ሆኖ ሊገኝ ይችላል?????
የኢትዮጵያኒዝም አቀንቃኝ ነን የሚሉ ሰብዕናወች "የህወሃትን ከኢትዮጵያ የመነጠል መሻትን" ተቀብለው፤ ለዛ ጥብቅና ሲቆሙ ይገርመኛል። አናርኪያዊ ጉዞውንም "ጎሽ" ሲሉ ይገርመኛል። ጎንደሬወች ባለ ቅኔ ናቸው "ሸማ በየዘርፋ ይለበሳል ይላሉ" እሚታዬ ጽግሽ ደግሞ ይህን መሰል የግርግር ማህበርተኝነት ሲገጥማት "ብልሃት የሌለው ቅላት" ትለዋለች።
በሌላ በኩል ግን በአናርኪዝም ውስጥ በሰጠመው የህወሃት አካሄድ ደጋፊ መሆን መብት ነው። ግን ኢትዮጵያኒዝም አቀንቃኝነቱን እንደ ቅርፊት ማድረጉን ቢያቆሙት ጥሩ ነው። መምሰል ሳይሆን መሆንን ስለሚጠይቅ ኢትዮጵያኒዝም።
ኢትዮጵያዊነት በልኩ ውስጡን የሚሰጥ አላገኜም። በእውነቱ ኢትዮጵያዊነት በገብያ ህግ የሚተዳደር ማንነት አይደለም። እራሳቸውን ለመሪነት የሚያጩ ሁሉ እራሳቸውን ሊመረምሩ ይገባቸዋል። ማደናገራቸውንም ቢያቆሙ መልካም ነው። ብጥበጣቸውንም ተግ ያድርጉ። የሚበጠብጡት ንጹሁን ኢትዮጵያዊነት ነውና።
#በምንም ሁኔታ አናርኪዝም ሊደገፍ አይገባም።
የህወሃት የፖለቲካ ሂደት እልሃዊ አናርኪዝም ነው። ዶር ደብረጽዮን እኮ መጋቢት ወር 18/ 2010 ዓ.ም በነበረው የኢህአዴግ የመንፈቀ ሌሊት የሥራ አስፈፃሚ ጉባኤ #ሁለት ድምጽ ብቻ ነበር ያገኙት። ይህ ማለት ኢህአዴግም አቅም የለወትም ብሎ አሰናብቷቸው ነበር ማለት ነው። "አንፈልግህም" የተባለ የፖለቲካ ሰብዕና እንደምን እንደገና ሥልጣኑን እንደሚያስብ ይገርማል።
ዶር. ደብረጽዮን አቅም ቢኖራቸው እኮ ኢህአዴግን ማስቀጠል ይችሉ ነበር። ኢህአዴግ እኮ አቅም አንሶት #ቃሬዛ ላይ ሆኖ እኮ ነው ሹም ሽር የሆነው። የትናንት ታሪክ እኮ ነው ይሄ። የሚያስደነግጠኝ በሥልጣን ራህብተኛው ዶር. ደብረጽዮን መሪነት ደስታቸውን የገለጹ አዲስ ገብ ታጋዮች አይቻለሁኝ። ህወሃት ሥልጣኑን ለቀቀብኝ እዬያቸውን ሁሉ በትዝብት ሳስተውል በዝምታ ቆይቻለሁኝ። ተጠቃሚነት ሲቀር ድንኳን ጥሎ *ደመር መከወን መብት ነውና።
*** ደመር በጎንደር የቀጠሮ የሃዘን ቀን ማለት ነው። ተቀጣጠሩ እና እርማችሁን ብታወጡ ጥሩ ነው። ኢትዮጵያዊነትን ማወኩን ብታቆሙትም ፍላጎቴ ነው። ሰብዕና በልበጣ አይጠቅም።
#እቴጌ ትግራይን በሚመለከት።
ህወሃትን አሻም ማለትም ይሁን፤ ይሁንታ መስጠት ለህወሃት መብቱ የትግራይ ክልል ህዝብ ነውና፤ ህዝቡ ያሻውን ይወስን። ሊቃናቱም እንዲሁ። ግን እንደ ሰው ድጋሚ ለትግራይ እናቶች የዕንባ ዶፍ እንኳን ደህና መጣህ ልል እኔ በግሌ አልችልም። መቼውንም። ትግራይ በአናርኪዝም አመራር ለሚደርስባት መጪ ቀውስም ከልቤ አዝናለሁኝ። አናርኪዝም ለህፃናት፤ ለነፍሰጡር እናቶች፤ ለአዛውንታት፤ ለህሙማን፤ ለአቅመ ደካሞች ውሃ ያዘለ ተራራ ነውና።
#የህወሃት የማዶ አሻቅቦ የማዬት መሻት።
ህወሃት ይሻቅላል - ህወሃት ይራወጣል - ዓለም ዓቀፍ ዕውቅና በቁልምጫ እንደዛ ጦርነቱ ጊዜ ለማግኜት። በዚህ ዘመን ተናጠላዊ የሆነ ድጋፍ ሊያገኝ ይችላል። ከታዋቂ የዓለም የፖለቲካ አንቱወች። የተደራጄ ተቋማዊ ድጋፍ ለማግኜት ግን ዳገት ነው። ይህ የሆነው ህወሃት ማስተዋል ትነት ካልገጠመው በስተቀር ከሰኔ መግቢያ 2023 እኤአ ጀምሮ ሁሉም ነገር ተቀይሯል።
በየጊዜው ከነጩ ቤተ - መንግሥት ህወሃትን በህረ አጀንዳ ሆኖ የሚዲያ ብሪፊንግ ተቋርጦ ከምል ቆሞ ነበር። " ምዕራብ ትግራይም፤ ይሁን ዳግም ኢትዮጵያን የመምራት እጮኝነትም ህወሃትን የማሰብ ህልምም" ቆሞ ነበር። የህወሃትን ቅልጣን የሚያስተናግድ፤ የሚያሞላቅቅም ኃያላን መንግሥት ዛሬ ላይ የለም።
አሁን ደግሞ የዘመኑ የፖለቲካ ባህሬ እየተለወጠ ነው። ብዙ ጊዜ በብዙ ዓመታት ውስጥ አንድ ጊዜ የዘመኑ የፖለቲካ ባህሬ ይለወጣል። በዘመናችን #ከትራንፒዝም መምጣት ጋር ቋሚ የዘመን የፖለቲካ ባህሪ አለ፤ ይህ ነው፤ እንዲያም ነው ብሎ ለመተንበየም ይሁን በራስ አጀንዳ ለመመራት ገጠመኙ ተለዋዋጭ ሆኗል። ለግሎባል ፖለቲካ የኃይል አሰላለፍ፤ ኢኮኖሚ፤ ሰብዓዊ ሁነት እጅግ አስቸጋሪ ነው።
ዓለም አቀፍ ተቋማት፤ አህጉራዊ ተቋማት፤ አገራዊ ተቋማት እራሳቸው ፈተና ውስጥ ናቸው። በዚህ የዘመኑ ተለዋዋጭ እና ቋሚ ባልሆነው የፖለቲካ መንፈስ ውስጥ፤ አናርኪዝምን ለሚያራምደው ህወሃት ጥላ ከለላ ለመሆን የሚቻልበት ወቅት በፍጹም አይደለም።
ዲታ አገሮች ለዛሬ 30/40 ዓመታት የያዟቸውን ትልሞች ሁሉ እንደ ገና ሪባይዝ የሚያደርጉ ይመስለኛል። ዲታ አገሮች ፈተና ላይ፤ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች መሰናክል ላይ፤ ደሃ አገሮች ደግሞ የሚያረገርግ ተስፋ ላይ ናቸው። ከዚህ አንፃር የህወሃት ሠርግ እና መልስ፤ የአናርኪያዊ ፋንታዚ ዋልሎ ነው የሚቀር።
#ካለ ቅድመ ሁኔታ የህወሃት የድርድር ጥያቄ።
ከህግ በላይ ተሁኖ ድርድር የለም። ሊኖርም አይችልም። ህግ አክባሪ፤ በህግ ለመመራት የሚተጋ እኮ ያ ዓለም ዓቀፍ መዋለ መንፈስ፤ መዋለ ንዋይ የፈሰሰበት የደቡብ አፍሪካ ድርድር እኮ በቂ ነበር። ለዛውም የስትራቴጂ ወዳጄ ለሚላችሁ ብልጽግና ጋር ኬኒያ ላይ ሌላ የሽሽግ ፍር ላይ ነበራችሁ።
የሆነ ሆኖ የአብይዝም እና የህወሃት ጦርነት ሲቆም ሁላችን ወህ ያሰኜ። እኔ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ሁሉ ተው ብያለሁኝ ግራ ቀኙን። በጦርነቱ ጊዜም የግራ ቀኙን ጉዳት ከማምናቸው ዓለም ዓቀፍ ሚዲያወችን የማገኛቸውን ብቻ እዘግብ ነበር።
ህወሃት ዕድሉን ሲያገኝ አገግሞ አማራ ክልል እና አፋርን ሲበቀል፤ እራሱ ያለማውን ወደ ትቢያ ሲቀይር በእጅጉ ነበር ያዘንኩት። በኋላ ሰላሙ ሲበሰር የቀደመኝ አልነበረም። ዜናውን ሼር ለማድረግ። ወህታን ማን ይፃረራል፤ ዕብን ካልሆነ በስተቀር። ስምምነቱ የጎረበጣቸው በአፍቅሮተ ህወሃት የተነደፋ ፖለቲከኞች እንደነበሩ፤ በብስጭት ውስጥ ሆነው የሰጡትን ቃለ ምልልስም አዳምጫለሁኝ። አሁንም የሚረብሹ እነሱው ናቸው። አይጠቅምም።
#ቀውስ።
ወጣት እያለሁ አንድ የትርጉም መጸሐፍ አንብቤ ነበር። " ሞገድ ይባላል" ሞገድ መጽሐፍ ሽብር በማፍያ ቡድን እንደምን ተደራጅቶ የሚዲያ ስንቅ አቅራቢ እና አትራፊ መሆን እንደሚቻል ነበር የሚተርከው። የጭብጡ አስኳል የተደራጄ ማፍያ ቡድን የማይደፈር ዓለም ዓቀፍ ቅርስን ይዘርፋል፤ ዘረፋው እና ዜናው እኩል ይወጣል። ለዘረፋ ለምሳሌ 3 ሚሊወን ዶላር ቢወጣ፤ ዜናው 6 ሚሊወን ዶላር ይሸጣል። በሽብር የሚገኝ የንግድ ተቋም እንደማለት።
ኢትዮጵያ ውስጥ ሙሉ 8 ዓመታት ያዬሁት ይህን ነበር። ፌስቡኬ ላይ ራሱን አስችዬ ወደ 7 ጊዜ ጽፌበታለሁኝ። በቀውስ የተፈጠረው ህወሃት እራሱም የቀውስ አባወራና አከፋፋይ ሲሆን፤ የሽብር ፊደል አስቆጣሪ ህወሃት ነው።
የህወሃት ልጆቹም ከህወሃት ተመግበው ያደጉትን የሽብር ጥሪት አላባከኑትም፤ ስለሆነም የህወሃት የልጅ ልጆች የአባታቸውን ውርስ ዕውን በማድረግ ኢትዮጵያ ታመሰች። የሚገርመው አሁን አሁን ሳስበው "በዚህ ቀን፤ በዚህ ቦታ አደጋ አለ ተብሎ ሁሉ ይዘገብ ነበር።" በተባለው ቀን፤ በተባለው ቦታ የሰው ልጅ የተናጠል፤ የወል ፍጅት፤ እገታ፤ ስወራ ነበር።
የሚገርመው የሚሰቃየው ማህበረሰብ አቅጣጫው ወጥ እና የተያያዘ ሰንሰለትማ ነው። ቅጣቱ የተበዬነው በአማራ ህዝብ እና በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ተስፋ ላይ ነበር። ቀድመው በተደራጁ ከተሞችም ላይ ዘመቻ ነበር። የከተሞች ፍልሰት ታቅዶ ተከናውኗል።
ብዙ በጣም ብዙ ለህሊና የሚሰቀጥጡ ትራጀዲወችን አይተናል። ለጅብ የሰውን ልጅ አስከሬን ከመስጠት፤ ሰማዕትነትን የተቀበለን ዘቅዝቆ መስቀል፤ ገድሎ ማቃጠል ምን ያልታዬ አሰቃቂ አረማዊነት አለና። አብረን እንፈር የምለውም በዚህ ነው። ኢትዮጵያ የከበደችን ለሁላችንም ነው የምለውም ለዚህም ነው። ሰብአዊነታችን ተፈትኖበታል።
በብዙ ሁነት የቀውስ አባወራው ህወሃት ሲሆን፤ ብዙ የጭካኔ ትዕይንቶችን፤ የዜና ሽፋኖችን፤ የእጅ ሥራው በሆኑ ልጆቹ እና የልጅ ልጆቹ ተቀጣጥሎ አስተውለናል። በዚህ ውስጥ "ህወሃት ይሻለናል" የሚል ድምጽ እየሰማሁ ነው። በተለይ ከጎንደሬወች ሲሆኑ ይከረፋል። ልጅነታችን ሁሉ እኮ አናውቀውም። የልጅነት የጨዋታ ጊዜ አልነበረንም። በዕታችን የጦርነት ቀጠና ነበርና።
#ቀውስ ስለማቆም።
ቀውስ መፍጠር፤ ቀውስ ማደራጀት፤ ቀውስ መምራት፤ ቀውስ ሥራ ላይ ማዋል የህወሃት እና የቤተ - ህወሃታውያን ፌስታ ነው። ቀውስ አምራቾች በዛው በሚተዋወቁበት መስመራቸው የእጅ ሥራ የሆነውን ቀውሳችን ይቁም ብለው ሲወስኑ፤ እፎይ ይላል የኢትዮጵያ ህዝብ። ለዚህ ፈቃድ ሰጪውም ነሺውም የቀውስ ባላንባራሶች ይሆናሉ።
በተለይም ጭምት ፖለቲከኞችን የፈተነው ተግባር ይህም ነበር። ስቃይ አለ፤ ስቃይ ሠሪው ግን ባለቤቱ ያደናግር ነበር። ህግ ፊት ቀርቦ ቅጣት የተቀበለም አላዬንም። ቁልፍልፍ ያለ ትብትብ ጉዳይ ነው ኢትዮጵያ የገጠማት።
#እራስን የመግዛት አቅም ወናነት።
እራስን የመግዛት አቅም እንደ አጀንዳ አይታይም በኢትዮጵያ ፖለቲካ። በአረገረገ ዕሳቤ ትውልድ ታጨደ። የኢትዮጵያ እናቶች ተሰቃዩ። በቃችሁ! ስቃዩ ለማለት ሰባዕዊነት + ተፈጥሯዊነት ምራኝ ሲባል ነው። ይህን መፍቀድ መሸነፍ አይደለም። ፍርሃት፤ ስጋት ቀምሮ ይምራህ ከማለት ይልቅ ቅንነትን ሰንቆ ሰዋዊነት እና ተፈጥሯዊነት እንዲመራ መድፈርን ይጠይቃል።
ለመሆኑ ይህን ሁሉ መከራ ዘመን ተዘመን የተሸከመ ህዝብ ለምን ይወረፋል? ለምን ይቃለላል? ስለምንስ ዛቻ ይደርስበታል? አንጎል ድንቢጥም አላት። ሰዋዊነት እኮ ህሊናዊነት የተሰጠው እንዲመዝን፤ እንዲያስተውል፤ አንደበቱን እንዲያርም፤ የተሰጠውን ዕድል በአግባቡ እንዲያስተዳድር ነበር። የኛ የተገላቢጦሽ ነው።
ጭካኔ፤ ጥላቻ፤ ማግለል፤ መበቀል መደበኛ የህይወት መስመር ሆኗል። ይህ ይምራን ከሆነ የነገ ተስፋ ከመምጣቱ በፊት ይሸሻል። ተስፋ ደንጋጣ ይሆናል። ስለዚህም የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች በጊዜያዊ ሁነት ሳይሸነፋ ዘለግ ያለ ጥሞና ሊያደርጉ ይገባል።
ኢትዮጵያ በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ ሆና አክባሪዋ፤ ፈላጊዋ፤ አድናቂዋ፤ ተስፈኛዋ ዘመን ፈትኖ የማይረታው ባለ ዕድልነት ነው። ይህን ዕድል ሲገኝ ቅብዓው የኢትዮጵያዊነት ስለመሆኑ ልብ ሊባል ይገባል።
በዚህ ብሄራዊ ምስቅልቅል ውስጥ አወንታዊ ጉዳዮች ወደ ኢትዮጵያ ሲቀርቡ በእናት አገር ኢትዮጵያ ያጎደልንባት ምንድን ነው ብሎ በጸጸት እራስን ማረም ይገባል። መታበዩ አይገባም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ዛሬ የተሠራች የምትሠራም የውበት ሳሎን አይደለችም እና። በኢትዮጵያዊነት ላይ ሽፍትነትም ያንደላልጣል፤ ይላልጣል።
ከህወሃት ውድቀትም ለመማር መፍቀድ ብልህነት ነው። ህወሃት አናርኪዝም ላይ ሆኖ ጀገንኩ ሲል እራሱን ነው የሚያታልለው። {} ስለሆነ። መውደቅን - መራቆትን - ማመን እና መቀበል ሽንፈት አይደለም። ብልህነት ነው።
ህወሃት መቀሌን እንደያዘ ሌላ ጥቃት ከመክፈት እራሱን አርሞ ተፎካካሪ ሆኖ የመውጣት ዕድሉን አባክኗል። አብይዝም በዝምታ ውስጥ ሆኖ "አያ ሆይ ሳሩን አዬህ እንጂ ገደሉንማ" እያለው ነው። አብይዝም ለአማራ የትኛውም ተቋም የማያደርገውን፤ ለኮትኩቶ አሳዳጊው ለህወሃት ግን አብዝቶ ታግሶታልም። መታገስ ሲገኝ በቅጡ ማስተዳደር ይገባ ነበር። ይህን ዶር ደብረጽዮን አቅመ ቢስ ስለሆኑ ሊጠቀሙበት የትዕግስትን አያያዝ ይሁን አጠቃቀም አልቻሉበትም።
#የነፍስ መዳን ፍርፋሪ።
ደቡብ አፍሪካ እና የህወሃት የነፍስ አባቶች በጥረት ያደረጉት ነገር ሬሳ ሃሳብ አንጋቹን ህወሃትን የነፍስ ቀጣይ ፍርፋሪ፤ ጉሮሮ ማርጠቢያ እንዲያገኝ መደረጉ ነበር። እዛው ከጎደበበት ጉድጓድ ውስጥ እንደ #ጎደጎደ፤ በአጓጉል ሁኔታ ለወግ ለማዕረግ ሳይበቃ ዕድሜ ይፍታህ ይሆን ነበር።
ይህም ሆኖ ያ የሰማይ ታምር ተጠቅጥቆ ጉሮወሸባዬ መቀጠሉ ፋንታዚ ነው። መቸውንም ህወሃት መንበረ ሥልጣኑን በተረከበበት ዘመን ያለው አቅሙን መልሶ የማግኜት ዕድሉ ልሙጥ ነው። ፈቃዱ የእሱ ብቻ አይደለምና።
በቃሽ ይበላትፈጣሪ ኢትዮጵያን። አሜን። እቴጌ ትግራይም የምትስቅበት ቀን ፈጣሪ #ይመርቅላት። አሜን።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
15/95/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ዕውነት #ወጌሻ ወይንም #ጋራጅ አያስፈልገውም።
See less
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ