የጨዋ ህዝብን መንፈስ #ማዋለል ለምን? የመልሰን "#እናጤነዋለን" ቀጠሮው ለመቼ? #መወሰን ያቃተው ነፍስ መኖር አልጀመረም።
"አቤቱ የቤትህ ቅናት በላኝ። "
#ምዕራፍ ፲፱።
ይገርመኛል የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁልጊዜ #በቀጠሮ። "ቁርጥ ያጠግባል" ይላል ባለ ቅኔው ጎንደሬ።
ይህ አሳረኛ ህዝብ እየተገበረ አሳሩን አዬ። ፍቅሩን በንጹህ ልቡ ቢሰጥም፤ መዝኖ ቢያስተዳድርም
ስቃዩ ሊያባራ አልቻለም። መሻልን ለማሳዬት ሆኖ መገኜት ነው። ኢትዮጵያን ያህል አገር ለመምራት
እራስ ሲታጭ ምን አለኝ ብሎ መነሳትን በእጅጉ ይጠይቃል። አገር ሱቅ በደረቴ አይደለችም።
#እፎካከራለሁ ስትል አቅምህን ነው እምታቀርብ እንጂ አንደበትህን አይደለም። ሙሉ አገርን
ለመምራት የሰከነ፤ የሚዘልቅም ራዕይ፤ የተሰናዳ የተግባር ቅደም ተከተል፤ ብቁ መንፈስ እና
ተመክሮ ይጠይቃል። ከምትፎካከረው፤ ከምታጣጥለው፤ ከምታቃልለው ይሁን፤ ከምታከብረው
የፖለቲካ ድርጅት መሻልህን ህዝብ መስማት ሳይሆን ማዬት ይሻል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ይሁን ኢትዮጵያ ፍቅሩንም፤ ክብሩንም፤ ዕውቅናውንም ለሁሉም በገፍ ሰጥቶ አይቷል።
ተፈታትሿል። የኢትዮጵያ ህዝብ ስልጡን ህዝብ ነው። ቅኑ እና ቀናው ህዝባችን ምን እንዳለው፤ ምን ደግሞ
እንደሌለው ያውቃል። በዝምታው ውስጥ እራስ እግሩ ብልህነት #ተደላድሎ የሰከነበት ህዝብ ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ ፍጹም አድማጭም ነው። ፍጹም ቻይ ህዝብም ነው።
የሚገርመኝ ግን በመንፈሱ ስለምን በተለያዩ በሚዋልሉ፤ በሚያረገርጉ፤ እርስ በርስ በሚጠላለፋ ሃሳቦች፤
መሻቶች እና ፍላጎቶች ይሁኑ አቋሞች ላይ #እንዲቀጣ እንደሚደረግ አላውቅም።
መወሰን ያቃተው ነፍስ መኖርን አልጀመረም። 15 ቀን ለቀረው የምርጫ ጊዜ "መልሰን እናጤናዋለን?"
በማን ህሊና ነው እንዲህ የሚቀለደው? በማን ዘመን እና ዕድሜ ነው እንዲህ በዋለለ ሃሳብ መንፈስ
#መቀጣጫ የሚሆነው?
ሳይንቲስቷ ኢትዮጵያ፤ ፈላስፊት ኢትዮጵያ፤ ዩንቨርሷ ኢትዮጵያ እኮ በዓለም ውስጥ አሉ ከሚባሉ ሊቃናት አቻ
የሆኑ በዝምታ ውስጥ ያሉ ሊቀ - ሊቃውንታት ያሏት አገር ናት። ምን ይታዘቡ ይሆን እንዲህ ባልሰከነ ፍላጎት፤
#ርጋ ባላለ ራዕይ እና ግብ፤ በሚያረገርግ ተለዋዋጭ የፖለቲካ አቋም እንዲህ በሚዋልል መሻት የህዝብን
ህሊና አቅሉን እንደ ቅል ስታንጠለጥሉት?
ማንም ይሁን ማን፤ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በሁሉም ዘርፍ በላቀ ልቅና በልዕልና የሚበልጠው ህሊና በግሎባል ደረጃ
በዝምታ ውስጥ እንዳለ ሊያውቅ ይገባል። አክብሮት የሚጀመረው በተናጋሪውም በአድማጩ ህብረተሰብ ሊሆን ይገባል።
የጨመተ ህዝብ ያልተስረከረከ፤ ኮለል ያለ አቅል እና ውሳኔ ይናፍቀዋል።
የቅንጅት አቅምን መፍጠር ማሰቡ ባይከፋም፤ የዘመኑን የፖለቲካ ባህሪ፤ የትውልዱን የሥነ - ልቦና
ግሎባል ልክ ማወቅ ያስፈልጋል። ማህበራዊው ሚዲያ በራሱ ልዩ ሞገድ ነው። ሚዲያ ላይ በተወጣ
ቁጥር በተለዋዋጭ ስሜት በህዝብ ህሊና ላይ እንዲህም፤ እንዲያም መሆን አይገባም። አጋድሜ ነው
እየፃፍኩ ያለሁት። ትክክለኛውን ስሜቴን ብጽፈው ይከብዳል።
#በጣምተጠንቅቄ ለስለስ ያሉ ቃላትን ነው እየተጠቀምኩ ያለሁት። ምክንያቴ አገር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ
ድርጅቶች በግልም፤ በተቋምም ደረጃ ያለባቸውን፤ ጫና ጠንቅቄ አውቀዋለሁኝ። ስለዚህም ስሜታቸውን
እንዳልጎዳ ከተመሳሳይ ትርጉም ካላቸው ውስጥ፤ ለብ፤ ለስለስ ያሉትን እየመረጥኩ ነው የፃፍኩት።
ደጋፊወቻቸው፤ አድናቂወቻቸውም ሊታሰብላቸው ስለሚገባ። ከሁሉ አክሰሱ ላላቸው ታዳጊወች በብርቱ
መጠንቀቅ ግዴታችን ሊሆን ይገባል። በራስ ላይ ፈቅዶ ግዴታን መጫን ያስፈልጋል።
#ወደቀደመው ሃሳቤ ………
አቅም ያለው ግለሰብ ይሁን ተቋም ተናጋሪውም፤ አድማጩም፤ ተፎካካሪውም አቅሙ ብቻ ነው መለኪያ የሚሆነው።
የአቅም ስስነት ብስጭት፤ ቁጣ፤ ኩርፊያ፤ ማጣጣል፤ ማቅለል፤ የሃሳብ መዋለል ያመጣል። ግልምጫም፤ ዛቻም
ይሁን ፋከራም የሚመጡት አቅም #ሲውተረተር ነው።
አይደለም ለብሄራዊ ጉዳይ ለግል ህይወትም በቅድሚያ ሃሳብን አደራጅቶ መነሳት ይጠይቃል። ሃሳብ መደረጀቱም
ብቻ በቂ አይደለም። የተደራጀውን ሃሳብ ዕውን ለማድረግ የሚያስችል ልምድ፤ ከፍ ሲል ክህሎት ይጠይቃል።
የአንድ ቀበሌ ሊቀመንበር ከአንድ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ወይንም ፕሮፌሰር በላይ በህዝብ ውስጥ መኖርን ያውቀዋል።
ዕድልም ነው። የማይገኝም።
ተናጋሪነት ብቻውን ድርጊት አይሆንም። ለተናጋሪነቱ መሰላል ያስፈልገዋል። የሥራ ልምድ። የአንድ ወይንም ከዚያ
በላይ የሆነ ዕውቀት ምሩቁ መሆን ብቻውንም ራዕይን አያሳካም። በተለይ አገራዊ ራዕይ ከኖረ። ልምድ ወሳኝ ነው።
አንድ ፖለቲከኛ ህዝብ የኖረውን ኑሮ ፈቅዶ መኖር ሲጀምር ይሆናል የመሪነት አቅሙ ሀሌታ ላይ የሚጀምረው።
ሌላው አንድ ሰው ሁለት እግር አለኝ ብሎ በተመሳሳይ ቅጽበት ከሁለቱ መሆን አይቻልም። አይሆንምም።
"ምርጫ አትሳተፋ" ለሚለው ወገን አልወሰነም፤ ምርጫው እንዳያመልጥ ደግሞ "በሂደቱ ውስጥ ነን?" እንዲህ
ዓይነት ጨዋታ ለእናንተ ማህበራዊ መሠረታችሁን እንዳታጡ ሊጠቅም ይችላል፤ ህዝቡን ግን መንፈሱን
#እየቀጣችሁት ነው። የዛሬ ጹሁፌ አስኳል ይህ ነው። ቢያንስ በመዳፋችሁ ባለ የነፃነት አቅም ለህዝባችን የህሊና
ነፃነት አቅዳችሁ እንድትፈጽሙት ነው በትህትና የማሳስባችሁ።
መደመጥን ለማግኜት በመሪነት ዲስፕሊን ውስጥ መገኜት ግድ ይላል። ለህዝብ ህሊና ነፃነት መሳሳት፤ ልዩ ጥበቃም
ማድረግ የመሪነት ጥራታዊ አቅም ነው። ለዛውም በየዘመኑ ምርጫ፤ ብሄራዊ በዓላት፤ ለውጥ፤ ጦርነት መጣ በተባለ
ጊዜ ሁሉ እራሱን ሳይሳሳ ያለዋጋ ለሚሰጥ ህዝብ ልዩ የህሊና ጥበቃ ማድረግ መርኽ ሊሆን ይገባል። ቋሚ መርህ።
#አቤቱ ትብብር ለኢትዮጵያ ሆይ!
የኢትዮጵያ ህዝብ እናንተ አላችሁኝ ብሎ በእርግጠኝነት እንዳይቆም "#አልወሰነም" ትሉታላችሁ፤ ይሻለኛል የሚለውን
ለመምረጥ ህሊናዋን እንዳያሰናዳ ደግሞ "አለን ከሂደቱ አንወጣም፤ በምርጫው ብላችሁ ሚዲያ ላይም፤ ብሄራዊ ምርጫ
ቦርድ የሚሰጠውን መመሪያ ትፈጽማላችሁ።" እናንተ የውስጣችሁን ውሳኔ ስለምታውቁ መድረካችሁ ላይ ናችሁ ተረጋግታችሁ፤
ህዝቡ ደግሞ #አፋፍለአፋፍ ታማስኑታላችሁ።
ሰላማዊ ምርጫ ሰላማዊ ሂደትን ብቻ ነው የሚጠይቀው። የሥልጣን ፋክክሩም ሰላማዊ፤ ህግና ሥርዓትን የተከተለ
ነው ሊሆን የሚችለው። ታመነበትም አልታመነበት በኢትዮጵያ ህገ - መንግሥት ሥር መሆንን ይጠይቃል። ለሰላማዊ
ታጋይ የሥልጣን መሻቱን የሚያሳካበት ቱሉ ምርጫ ብቻ ነው። ምርጫው ደግሞ ሙሉ የህሊና፤ የአካል መሰናዶ
ይጠይቃል። ጥሞና እና ስክነትንም አጥብቆ ይናፍቃል።
#የማዬው ይሁን የማዳምጠው ግን … ያቆስላል።
ሀ. መልስ ነው። ልክ ነው።
ለ. መልስ ነው። ልክ ነው።
ሐ. መልስ ነው። ልክ ነው።
መ. ሁሉም ልክ ነው። መልስ ነው።
ሰ. ሁሉም መልስ አይደለም። ልክ ነው። ይህ ጉዞ ብቻውንም ከመሻት ጋር አያገናኝም። ፖለቲካ ለሰው እና ለተፈጥሮ
ነው። ሰው እና ተፈጥሮ ደግሞ በእንጥፍጣፊ የሃሳብ ውለት ሳይሆን በንጥር የአቋም ብቃት እና በኮስታራ የመወስን
ልኩ ይዳኛል። ይህን በውነቱ አላየሁም።
"ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል …… "
"ባልዘፈንሽ፤ ከዘፈንሽ ባላሳፈርሽ ………" ይህ የቀደምቶቹ አስተምኽሮ ለእኛ የህይወት መሃንዲሳችን ነው።
#እ።
1) "ሰላማዊ ሰልፍ "ሚዚያ 30/2018 ዓ.ም።"
2) "ሰላማዊ ሰልፍ ተራዘመ። ለግንቦት 30.2018 ዓም።" መጣን ስትሉም ስትቀሩም ዝም ያልኩት ለዚህ ነው።
ቀድሞ ነገር የፖለቲካ ማንነት የውሳኔ ማንነት ነው። ከዚህ ጋር ከተላለፈ ብሄራዊ የመሪነት መሻት ጋር ግብግብ ይሆናል።
በልኩ ያልተሰፋ ሽብሽቦ ወይ ጥብቆ፤ ወይ ልቅ ይሆናል። አስቦ ሊያስነሳ የሚገባው የፖለቲካ አቅም በእጅ ሲኖር ብቻ
ሊሆን ይገባል። ሞገድ ላይ አይደለም ህይወት ያለው።
3) ቅድመ ሁኔታ ………
3.1) ካልተሟላ …………
3.2) ከተሟላ ………… ዋልሎ የሚያዋልል ፖለቲካ ለትውልድም፤ ለታሪክም ፊፋን ናፋቂ ይሆናል። የፊፋ ጉሮሮ ያለው
ከድንቡልቡሏ እና ከሜዳዋ ነው። የሰው ልጅ ህሊና የኳስ ሜዳ አይደለም። ለዛውም ዛሬ?
አመክንዮዊ መሆን ያስፈልጋል። በምን ሁኔታ "ጦርነትን ቁም፤ ጦርነቱን አቁም፤ የታሠሩትን ፍታ" ወዘተ የሚባሉ ሐረገ
ጉዳዮች አዛዥ እና ታዛዥ ይሆናሉ ብሎ ማሰብ ይገባል። የእናንተን ፍላጎት ለመወሰን አቅቶ የሌላውን አቅም ፈትኖ
እንደምን መርታት ይቻላል?
የብልፄው እና የህወሃት ጦርነትን ለማስቆም ስንት ጊዜ እንደፈጄ፤ ስንት ዓለም ዓቀፍ ሁነት እንዳሳተፍ አታውቁም?
የኢትዮጵያ እስረኞች በየጊዜው በዘመነ ህወሃት በርከት ብለው ሲፈቱ፤ ኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኛ የሌለባት ሁና የዩኒስኮን
ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስፈጸመችው መነሻው እንደምን በአይበገሬ ትጋት እንደተከወነ አታውቁትም።
ፖለቲካ ሂድ ሲባል የሚሄድ። ቁም ሲባል የሚቆም አይደለም። ሊያመርት የሚችል የህሊና መሰናዶ ይጠይቃል። ቋሚ አጋር
ተደማጭ እና አቅም ያለው የሌላ ተጽዕኖ ፈጣሪ አገር አጋርነት ይጠይቃል። ዝም ብሎ የሚታፈስ ሰብል የለም።
በቋሚነት በተከታታይ የሚተጋ ቋሚ ተጨማሪ፤ ተጽዕኖ ፈጣሪ ያስፈልጋል። ይህን የተረዳው የለም። ከምርጫው ጋር
በተያያዘ ኢትዮጵያ ውስጥም ውጪም ያሉ ዲፕሎማቶች ቅርብ ሊሆኖ ይችላሉ። በጊዜያዊነት።
ተኖ የቀረው ባልደራስ ኢትዮጵያ ያሉትን የዲፕሎማሲ ማህበረሰቦች በራሱ መድረክ አወያይቷል። የተሻለ ተደማጭነትም
ነበረው። ባልደራስ 6ኛው አገራዊ ምርጫ ማሸነፋ ቀርቶ ህልውናውን ማስቀጥል ችሏልን? እእ።
አዲስ አበባ ብዙ ዋጋ የከፈለችለት ተስፋዋ ባልደራስ አረገም፤ ሰመጠም ሊባልለት ለማይችል ድርጅት ነበር። ከዛ መማር ያስፈልጋል። ታሪክ እንዲህ ዓይነት ገጠመኝ ኑሮት አያውቅም። በፈተና ውስጥ ጉባኤ አካሂዶ፤ ያን የፈተና ዕድል ደግሞ አይሆኑ የሆነበት።
መምረጥ መብት ነው። አለመምረጥም መብት ነው።
መመረጥ መብት ነው። አለመመረጥም መብት ነው።
መብትን አውቆ ግዴታን መወጣት ደግሞ የህግ ተገዥነትን ይጠይቃል። መብት ካለ ግዴታ፤ ግዴታ
ካለመብት አልተፈጠሩም። አንድ ብቁ ዜጋ መብቱን ሲጠይቅ ግዴታውን አውቆ፤ ለግዴታው ተፈፃሚነት
ተግቶ ሊሆን ይገባል።
አንድ ብቁ ዜጋ ግዴታውን እየተወጣ መብቱ ሊነፈግ አይገባም። ይህን ማሳካት የሚቻለው በፖለቲካ
ድርጅቶች በአቅም ጥራት እና ግንባታ ነው። ይህን ለማምጣት ሂደት አለ። ለሂደቱ ግን ታቁሮ ሳይሆን
በሂደቱ ውስጥ በመሆን ሆኖ በመገኜት ነው።
ህዝባችን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተንገላታ። በጣም ተንገላታ። ደከመው። ምርጫ በመጣ ቁጥር ጫን ተደል
ቻል ይባላል። ዛሬ ዓለምም ምጥ ላይ ባለችበት ወቅት ነው የኢትዮጵያ ምርጫ ሂደት የሚከወነው።
በ2013 ኮረና ነበር። የፋመ የጦርነት ወላፈንም ነበር። በ2018 አጤ ሆርሙዝ በሁላችንም ቤት
ረሃብ ያወጀበት ዘመን ነው። ሁለት ወረርሽኞችም አሉ።
በዚህ ጊዜ የተደራጄ መንፈስ ይጠይቃል። አገርን ተረክቦ አገርን ለመምራትም ሙሉ የተደራጄ።
ብቁ የተሰናዳ የፖለቲካ አቅም ይጠይቃል። የዘመኑ የፖለቲካ ባህሪ አዲስ ክስተት ውስጥ ነው። ህዝብ
ዋጋ ከመክፈሉ በፊት ይህ ይጠና - ይመርመር። የዘመኑ ባህሪ በአጽህኖት የተረጋጉ፤ የሰከኑ መንፈሶችን
እንጂ የሚዋልሉ፤ የሚያረገርጉ፤ የሚያስጨንቁ ቡፌወች አያስፈልጉትም።
ታስታውሳላችሁ የዶር ቴወድሮስ አድህኖም የዓለም ጤና ድርጅት ዲያሪክተር የሁለተኛ የምርጫ ውድድራቸው
እቴጌ ዓለማችን ተወዳዳሪ አላቀረበችም። በዝምታ ግን አንድ ሁነት ተፈጸመ። ለምን? ዓለም በብልህነት በላቀ
ዊዝደም በዝምታው በአኃቲነት ስለወሰነ። ምን ብላ? ይ --- ቀ ---- ጥ --- ሉ -----
በውነቱ በምርጫ ዙሪያ ዝምታዬን እወደዋለሁኝ። ግን ዝም እንዳልል የአገሬ የኢትዮጵያ ህዝብ ያሳዝነኛል።
ከፋኝ ያሉ ታጣቂወች ወዮ! ብለዋል፤ እርምጃም እየወሰዱ ነው። ራስ ጋይንትን ለናመና መውሰድ ይቻላል።
በብልፄው በኩልም ምርጫ ካልተሳተፍክ ያው ወዮን! ደግሞታል። ራስ ጋይንትን ለአብነት ውሰዱት። በሁለቱም
ወዮታ ዕንባ ተንሰራፍቷል። ይህ ያሳዝነኛል። ምርጫ ባለመሳተፍ የሃሳብ ጽንሰት #ሞት፤ ምርጫ ለመሳታፈ የሃሳብ
ጽንሰትም #ሞት። ራስ ጋይንት ከግራ ቀኙ ምህረትን አጥቶ ተሰቃዬ። ይህ ስቃዩ ውስጤን በሃዘን ይቆርሰዋል።
*** ሰላማዊነት የስትራቴጂው ግቡ ምርጫ ነው።
በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን ያሉት ደግሞ የህዝቡን ህሊና እንዲህ በማዋለል፤ ህዝባችን የመምረጥ
ይሁን የመመረጥ መብቱን ማቀድ፤ መወሰን፤ መፈጸም እንዳይችል ያደርጉታል። ምርጫ እኮ ትልቅ የፖለቲካ
#ምኽዋር እኮ ነው። ምርጫ ዲሞክራሲ በሚናፍቃቸው አገራት ሰርክ በወጣ ገባ የሃሳብ አዙሪት ሊተበተብ
የማይገባው ሰፊ የህሊና ብቃት፤ የተግባር ሁነት የሚለካበት ነው።
ህሊና ቢሰለጥን የፍላጎት እና የመኖር #ልቡ ምርጫ ነው። ወጪም ነው። ብዙ የአገር ሃብት የሚፈስበት።
ሚሊዮኖች መንፈሳቸውን ሳይሰስቱ የሚመግቡት። ምርጫ የሚጠይቃቸው መስፈርቶች አሉ። በአለው
ነገር ተሳትፎ ነው ጎደለ የሚባለውን ማሳካት የሚቻለው።
ምርጫ ነፃ፤ ፍትሃዊ፤ ገለልተኛ ይሁን። ሁላችን የምንሻው ነው። የመራጩን ህዝብ መብት ህሊናውን #በማባተል
የምርጫን ፍትህነት ለሚጠይቅ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅት የማይሆን መንገድ ነው። የመራጩን ህዝብ የህሊና
ነፃነት በገደብ፤ በጥርጣሬ፤ በማዋለል እኛን ብትመርጡን በሚቀጥለው የምርጫ ዘመን ነፃ የምርጫ ዘመን
እናመጣለን እንዴት ይሆናል? እያንዳንዱ የፖለቲካ ቅንጣት ላይ ከራስ ነው መጀመርን ይጠይቃል።
የሚያስፈልገው? ፋክክሩ እኮ ለነፃ፤ ፍትሃዊ ገለልተኛ ለማግስ ምርጫን ለማስፈን ከሆነ። በዛሬ መሻትህ ውስጥ
አንተው እራስህ ሳትገኝ፤ የነገ መሻትን ያሳካልኛል ብሎ ህዝብ ሊያስብ አይችልም። የታረቀ መንፈስ፤ እርስበርሱ
የማይደባደብ የሃሳብ ፈቃድ ያስፈልጋል። "እራስ ሳይጠና ጉተና" ስለሚሆን። የቆረጠ፤ የወሰነ ቆፍጣና የፖለቲካ
ድርጅት አቅሙን ለክቶ ይነሳል፤ የስኬቱ ሥራ #አስኬያጅ አቅሙ ይሆናል።
15 ቀን ለቀረው ምርጫ "እናጤነዋለን?" ምንድን ነው? ለማንስ ይሆን የሚጠቅመው? ህዝባችን ተሰቃዬ።
ህዝባችን አሳሩን አዬ። ለእናንተም ብሎ የታሰረ፤ የተንገላታ፤ በክፋ ዓይን የታዬም ይኖራል እኮ።
በግለሰብ ደረጃ ከተፈጥሯዊነት፤ ከሰብአዊነት ጋር ዕውነት የሆኑ ሰብዕናወችን አይቻለሁኝ። እነኝህ
ሰብዕናወች ይሰቡበት። ዕድላቸውን #ላለመድፋት። በሚዲያ ክርክር እላፊ ከመሄድ የተቆጠቡ፤ ጠንካራ ሁነት
ሲገጥማቸው እጃቸውን አጣምረው ዝም የሚሉ። ሲመልሱትም ዋጥ አድርገው በትህትና ለመመለስ የቻሉ ሰብዕናወች
አዳምጫለሁኝ። እነኝህ በጠባቡ ዕድልም ቢሆን ተጠቅመው ዕድሉን ቢሞክሩ፤ ኢትዮጵያ ተስፋ ላይ የዋንጫ ያህል ይሆናል።
ለነገም እርሾ ነው።
ዕድሉን ከመተው አጋጣሚን አስተዳድሮ መሳተፋ የሚታይም፤ የማይታይም ጥቅም አለው። እርግጥ ነው
በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳድረው ያሸነፋ፤ አሁን ካቴና ላይ ያለ እንዳሉ አውቃለሁኝ። ቢሆንም ፖለቲካ ድርጅት
መስርቶ ከታጋለ አንድ ሰብ ሁልጊዜም መሞከር የግድ ይሆናል። የፖርላማ አባላት፤ የምክር ቤት አባላት መንገላታታቸው
እየታዬ ስለሆነ የምርጫ ሂደት ውስጥ የተገባው።
በተረፈ አሁን ባለው የዘመኑ የፖለቲካ ባህሬ የሚጠቅመው ባለው አቅም፤ ባለው ጊዜ መጠቀም ይበጃል።
ሁሉም አገር በራሱ ችግር ውስጥ ነው ከትሞ ያለው። አቤቱታን የሚያደምጥም እንኳን አይገኝም።
#ክወና።
አዲሱ ትውልድ በፍጹም #ሴራ ሊናፈቅ አይገባም። በተለይ አዲሱ ትውልድ የማይጠቅመውን መንገድ ሊከተል አይገባም።
ምክንያት ሴራ #ገደል ስለሆነ። ኢትዮጵያ ለሁላችን የከበደችን ለሁላችንም የሆነው፤ የሚሆነውም የሴራ ፖለቲካ ተጠማኞች
ስለተሆነ ነው።
ግን እንደምን አረፈዳችሁ ቤተ - ቅንነት?
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
22/05/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
See less
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ