#የአገር መሪን የሥልጣን ጊዜ ስለመገደብ የእኔ ዕይታ። "ላም አለኝ በሰማይ ወተቷን የማላይ።"
#የአገር መሪን የሥልጣን ጊዜ ስለመገደብ የእኔ ዕይታ።
"ላም አለኝ በሰማይ ወተቷን የማላይ።"
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
#ምዕራፍ ፲፱።
ብዙ ተቃዋሚወች ይሁኑ ተፎካካሪወች ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድን አቅልሎ የማዬት የወል ባህሪ አይባቸዋለሁ። ልምድ እንደሌላቸውም ሲናገሩ አድምጫለሁኝ።
በቂ ልምድ አላቸው። ሚሊተሪ ላይ ሠርተዋል፤ በተመድ ፕሮጀክት ተሳትፈዋል፤ ከኢንሳ መስራችነትም አሉበት በዛው ተቋም መሪነቱም ታክሎ ልምድ ይገበይበታል፤ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂን በሚር ደረጃ መርተዋል፤ የኢህአዴግ የፓርላማ አባል ነበሩ፤ በኦሮሚያ የተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ ሠርተዋል። ይህ በቂ ነው።
የኢትዮጵያ መሪ ከሆኑ በኋላ እሳቸው የሚያምኑበትን መስመር ተግተው ነው የሚሠሩት። ቢሮክራሲው ላይ የሉበትም መስክ ላይ፤ ፕሮጀክት ተኮር ጉዳዮችን ይወጥናሉ፤ ይፈጽማሉም። ዳሽ የሆነው ሰብአዊነት ላይ ነው የማጽናናት፤ አይዟችሁ የማለት፤ በተከፋት ቀዬ በህዝባቸው ውስጥ ተገኝተው ጥግ የመሆን አቅም አለመኖር። እስር ላይ ያለው የማይገፋ ተራራ። ሌላው ዳሽ የሆነው የቢሮ አስተዳደራዊ ሥራም ነው። በተጨማሪም የሌሎችን መከፋት #አቅለው ማዬታቸው፤ ለመፍትሄው አለመትጋታቸው ዳሽ ነው።
ጠቅላይ ሚር መለስ ዜናዊ የትኛው ተቋም ላይ ሠርተዋል? ከጫካ ህይወት ቤተ- መንግሥት። በቃ! ዕውነቱ ይሄ ነው። ያለውን #ዕውነት #ማስከፋት አያስፈልግም። ከዚህም ሌላ መሪነት ፈቃደ እግዚአብሄር፤ ቅብዓ ስለመኖሩም ማመን ያስፈልጋል።
የሆነ ሆኖ አገራዊ ምክክሩ ለምን እንዳስፈለገ፤ ከዛ በፊት ለሙከራ አቋቁመው ያፈረሷቸው ኮሚሽኖች ሁሉ በመደዴ ታስበው የተከወኑ ናቸው ብዬ አላስብም። እእ።
1) ያን ጊዜ ጎላ ብለው የወጡ አመክንዮችን ለማረጋጋት፤
2) ጠንከር ያሉ ተጽዕኖ ፈጣሪወችን ውስጣቸውን ፈታትሸው፤ ሙቀታቸውን ለካክተው የሚቀርቡትን ለማስቀጠል የሙከራ ማዕከል ነበሩ። ፖለቲካዊ ትርፍም ዝቀውበታል።
#ገለልተኝነት እንዴት?
አገራዊ ምክክር መወጠኑ መልካም ጅምር ነው። ግን ገለልተኛ ሆኖ ቢደራጅ ለመፍትሄው ቅርብ ሊሆን ይችል ነበር። በሌላ በኩል #በጀቱ ከብልጽግና መንግሥት ነው። #ሹመቱም ከብልጽግና መንግሥት ነው የተሰጠው። የአገራዊ ምክክሩ የገለልተኝነት ጉዳይ የሚያነጋግር ሊሆን አይገባም።
የአገራዊ ምክክሩ ቀዳሚ የማን ፍላጎት ዕውን እንዲሆን እንደሚሠራ ቀመር አያስፈልገውም። ስለዚህ ገለልተኛ ነው ብሎ ለማመን ሎጅኩ አያስኬድም። እራሱ የአደረጃጀት ሞቲቡ ይሁን አፈፃጸሙ መልሱን ይሰጣል።
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ቀድመው ያደራጁት ኮሚሽን ህልማቸው በሚያሳካው ልክ ብዙ ገጭገው ሳያጋጥመው ለማሳካት ከፈጠሯቸው ቱሎች አንዱ ነው። ፍላጎት አላቸው ሁሉንም ሁነት በአብይዝም ህልም መሠረት ማስያዝ። #ፕሬዚዳንታዊ የመንግሥት አደረጃጀትም ናፍቆታቸው ይመስለኛል። ለዚህም ነው ፓርቲያቸው መሪው ፕሬዚዳንት የሚል ቅጥል የተሰጠው።
ወደ አገራዊ ምክክሩ አወቃቀር ስንመለስ የተማሩ፤ የደረጄ ተመክሮ ያላቸው፤ የራሳቸው የሆነ አቅም ያላቸው ሙሁራንን፤ ለጠቅላይ ሚር አብይም ለሥልጣናቸው የማያሰጓቸውን፤ የማይጠረጥሯቸውን ሊቃውንተ ኢትዮጵያን አስጠግቶ ራዕይን ማሳካት አንዱ መንገዳቸው ነው።
#ሥልጣንን መገደብ፤ እንዲገደብ መፍቀድ የማድነቅ አቅም ያንሰኛል። ለምን???
ምርጫ 2013ዓም ከመካሄዱ በፊት ወደ ሦስት ዓመት በሽግግርነት ቢያዝ፤ ምርጫ 2013 ዓም ሲታከል ሙሉ 8 ዓመት ይሆናል። ምርጫ 2018 ሲጨመርበት 13 ዓመት ይሆናል። 7ኛው አገራዊ ምርጫ ብልጽግና #ደልደል ብሎ ምርጫ በሚካሄድባቸው አብዛኛው ቦታ ላይ 50+ አምጥቶ ያሸንፋል።
ስለዚህ በሁለት የምርጫ ዘመን ሽግግሩን ቆየን ብለን እንኳን 2013 /5 ዓመት + 2018 /5 ዓመት ይሆናል ሙሉ 10 ዓመት #የመሪነት ዕድሉ ይኖራል። የምክክር ኮሚሽኑ ከምርጫ 2018 ዓም በኋላ ነው የምርጫ ተርሙን ገደቡን ፕሮፖዛል የሚወስነው።
የምክክር ኮሜሽኑ ሲደራጅም ታቅዶ ነው። ሲጓተትም የባጀውም ለዚህ ተልዕኮ ነው። "ሰነፍ፤ ደካማ መሪ" ይህን መሰል ስልታዊ ሁነት ፈጥሮ በዚህ ልክ የሥልጣን ዘመኑን የማራዘም ዕሳቤን በተጠና እና በተቀናጄ ይሁንታ ሊያሳካ ይችላል ወይ? በፍጹም። አብዛኞቹን መድረክ ላይ ያሉ እራሳቸውን ለእጩ መሪነት በአንድም በሌላም የምናውቃቸው ይህን መሰል የረቀቀ እና ጥልቅ መስመር አይከተሉም። የሚያስቡትም አይመስለኝ። ምርጫ ሲደርስ ነው #እፍግቡ።
የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ የሥልጣን ዘመን የ13 ዓመቱ #አልታዬህም፤ አልተሰማህም ተብሎ ገደቡ ሁለትም ይሁን ሦስት ተርም የሚቆጠረው በያዝነው ዓመት ከሚካሄደው ምርጫ ዘመን ውጪ ይሆናል ማለት ነው። ይህን የማድነቅ አቅም እኔ የለኝም። የዚህ የዘመኑ ምርጫ ይካተት ቢባል እንኳን ይሁን ማለት ይቻላል። የተከበሩ ኒልሰን ማንዴላ ያን ሁሉ መከራ አስተናግደው፤ እራሳቸውን ገዝተው ታሪካቸውን ዕንቁ ያደረጉት ለሥልጣን መሻት ተገዢ ባለመሆናቸው ነው።
ጠቅላይ ሚር አብይ ነገን ጠብቁ ይላሉ ሁልጊዜ። በሳቸው ውስጥ ያለውን ድሪም ልብአውቃ ግን በማናውቀው፤ ባልፈቀድነውም ፕሮጀክት ውስጥ እንደ ተከደነ ደስይበላችሁ ይሉናል። እሳቸው ንድፋቸውን ስለሚያውቁት ይፍነክነኩ። እኛ ግን በማናውቀው፤ ባላየነው ፕሮጀክት ሳቅ ሆይ ብቅ በል ብንለው አሻም ነው የሚለን። ቢመጣም ፌክ ይሆናል።
የሆነ ሆኖ እሳቸው ቢሮን ከማሳመር ጀምሮ፤ ምንጣፍ ወጥ ካማሰናዳት፤ የመንገድ ዳር አበባወችን ከልጅ በላይ መንከባከባቸው እናም እሳቸው የሚያውቁት፤ እኛ የማናውቀው ዘለግ ያለ ሰፋፊ ፕሮጀክቶችን አቅደው እየተንቀሳቀሱ ያሉት። አሁኑ አዲሱ የኤርፖርት ንድፋን እሰቡት። ይህን የገዘፈ ፕሮጀክት #አሻራውን ምናቸው ሞኝ ነው ከሳቸው ውስጥ ለማን ሊሰጡት ይችላሉ? አትሰቡት።
ስለዚህ ሁለት ተርም ይሁን ሦስት ተርም ከተባለ በ2023 የሚካሄደው ምርጫ አህዱ ተብሎ ይቆጠራል። በሁለት ተርም ስናስበው 3 + 10 + 10= 23 ዓመት ይሆናል። የአብይዝም ትውልድ አብሮ ዕውን ይሆናል። ከሥር እየሠሩ ያሉትን እኛ የምናዬውን ብቻ እንዳይመስላችሁ፤ የማይታዩ የአብይዝም አዲስ ትውልድም መንፈሱን እየፈጠሩ ነው።
ኢብን ይህ ከሆነ በኋላም ከአፍሪካ መሪወች የሥልጣን መሻት ጋር ተያይዞ #ህግ ሊገዛው የማይችል ስለሆነ የምክክር ኮሚሽኑን ለሁለት ተርም ዘንቦ ተባርቆ ቢያስወስኑ እንኳን፤ ጊዜው ሲደርስ አዲስ ሌላ አቋቁመው ለውሳኔው ተጨማሪ #ሜክአፕ ይሠሩለታል። ጠቅላይ ሚር አብይን አቅላችሁ አትዩ፤ አታውቋቸውም እምለው ለዚህም ነው። እራሳቸው ለአቀዱት ፕሮጀክት ጀምረው ያጠናቅቁታል።
በዚህ ዙሪያ የሁለት ሚዲያወች ዕይታ። (ሉዓላዊ አዲስ ኮንፓስ።)
#ሉዓላዊ ሚዲያ የጠቅላይ ሚኒስተሩ የሥልጣን ዘመን ከዚህ ቀደም ልቅ፤ ያልተወሰነ ነበር። አሁን ግን የተሻለ ዕድል ሊመጣ ነው ባይ ነው።
#ሌላው አዲስ ኮንፓስ ሚዲያ ዳኛ ፍሬህይወትን የጠቅላይ ሚኒስተሩን ሥልጣን ስለመገደብ ተስፋቸውን ጠይቆ ነበር። የህግ ባለሙያው "ተስፋ አለኝ" ነው ያሉት። ይህን ስኬት ነው ጠቅላይ ሚር አብይ የሚሹት። ፍላጎታቸውን በህግ ኤክስፐርቶች ሳይቀር ዕውቅና እንዲያገኝ ማስደረግ። በዚህ ምን ያህል እርካታ እንደሚያገኙ እሰቡት።
በእኔ በኩል የመሪ የስልጣን ዘመን ተበየነ ብዬ የሚሰማኝ የውስጥ ሐሴት የለም። ዕድሉን ያገኜ ሰብዕ #ለርህርህና፤ ለአጽናኝነት፤ ለአይዟችሁ ባይነት ቅርበቱ ነው የሚናፍቀኝ። ካለ #አጃቢ የሚሄድ መሪም ሁልጊዜ ይናፍቀኛል።
በህዝብ ውስጥ ኑሮ የህዝቡን ኑሮ ለመኖር ፈቅዶ፤ ወንድም ዓለም አንተዬ እያለ ህዝብ የሚጠራው፤ ፈጽሞም የማይፈራው መሪ ይናፍቀኛል። ህዝባችን ተጎድቷል።
ወጣትነታችን የገበርንበት ሰብአዊነት እና ተፈጥሯዊነት በአገራችን ዕውን የሚሆንበት ሁነት ይናፍቀኛል። ኢትዮጵያ አመሠራረቷ ኦርጋኒክ ነበር። ግን ለሁላችንም ከብዳናለች። የእኛን ስሜት እንጂ እምናቆላብሰው፤ ከሷ ተፈጥሮ ጋር ተራርቀን ነው የቆዬነው። ይህ መሪሽ ነው ስትባል አክብራ የምትቀበልን አክባሪዋን አገር #ማክበር የተሳነን፤ አክብሪዋን ህዝብ ማክበርን የማናውቅበት ነው የሆነው። ዘለፋ፤ ዛቻ፤ ህግ ተላላፊነት ነው ያለው።
ወደ ቀደመው ስመለስ ዳኛ ፍሬህይወት ፈጽሞ አላወላዱም ጠቅላይ ሚር አብይ የሚሹትን፤ የተመኙትን ዒላማዋን ሳይስቱ እንቅጩን ገልጠውላቸዋል። ከዛሬ 15 ዓመት በኋላማ እኛም በህይወት አንኖርም። ፈጣሪ ሊያደርግ የሚችለውንም አናውቅም። ለአንድ አገር የሥርዓት ለውጥ ከውጪው ይልቅ የውስጡ ነው ሊያሰጋውም ሆነ እርግጠኛ ሊያደርገው የሚችል።
#ነገረ ዱብዕዳ እስከመቼ?
የፖለቲካ ድርጅት መሥራቾች መሻትን በቀመር፤ መሻትን በባለሙያ ይሁንታ በሚሰጥበት አግባብ ለማድረግ አያቅዱም፤ ዕድሉ ሲገኝ ደግሞ ዱብዕዳ ነበር፤ አልተሰናዳንም ነበር ይላሉ። ከሰሞኑ ሌላ የገረመኝ ነገር ከዚህ ጋር አያይዤ ላቅርብ።
ከአብይዝም በፊት በአማራ ጉዳይ ላይ ከውስጡ ጠንክሮ ይሠራ የነበረው አክቲቢስት ሙሉቀን ተስፋው ደስ ብሎት አገር ከገቡት ወገኖች ውስጥ አንዱ ነው። ፈርሰስ ሲል ባጅቶ አሁን ውጭ አገር ነው ያለው። ከሃሳብ ገበታ ጋር የነበረውን ቆይታ አዳመጥኩት። አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ጠቅላይ ሚር ቢሆኑ ምርጫው እንደ ነበር፤ ሳይሰናዱ ህወሃት ስልጣን እንደለቀቀ ሃሳብ ሲሰጥ አዳመጥኩት።
ትግሉን ለመቀጠል አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ቢሆኑ የተሻለ ዕድል ሊኖር ይችል እንደነበር ጠቅሷል። ያን ጊዜ በትጋት ሲታገል በነበረበት ወቅት ግቡን #ሳይሰናዳበት ስለመሆኑ ስሰማ ደነገጥኩ።
ሌላው አቶ ሽፈራው ሽጉጤን ይለፍ ሊያሰጥ የሚችል ምን የዲፕሎማሲ አቅም ነበረ ተብሎ እንዳይጠይቅ ጠቅላላ አልተሰናዳንበትም ስላለ ቀጣይ ጥያቄ አያስፈልገውም።
ዕውነቱን እኔ ብነግረው አቶ ሽፈራው ሽጉጤን #ይለፍ የሚሰጣቸው አልነበረም። እሳቸውም አቅደው የተሰናዱበት ፕላን ይኖራቸው ነበር ብዬ ለማሰብ አልደፍርም። በአጭሩ ጉዞው ይጨነግፍ ነበር። ህወሃት በሚያገኜው ጊዜ ተጠቅሞ በቀሉን በተዳፈሩት ላይ ያከታትለው ነበር። ይቀጥል ነበር።
ነገን ተከታይ ለማድረግ አስቦ መነሳት የለም በኢትዮጵያ ፖለቲካ። ልምዱም የለም። ተመክሮውም እንዲሁ ቀን የጎደለበት ነው። አሁን እራሱ አገር ተረከቡ ቢባል ማን? ምን አለው? "ጥምዶ" ብላችሁ እንዳታስቁኝ።
ኦኬ የአሁኑ ይቅር ለዛሬ 10 ዓመት የሚደርስ #እሸት ቅመሱስ ይኖር ይሆን???? ሁልጊዜ ማገዶ። ሁልጊዜ ከኤርትራ መንግሥት ሥር፤ ለሚሳካም ለማይሳካም ህልም የታላቅ አገር ህዝብ ቀደምትነቱን ስቶ ከጀማሪ አገራት የሃሳብ ብድር ለዛውም #በአራጣ።
ቤተ - ሥርጉትሻ እንዲህ ገባ ስል በቃ እተገትገዋለሁኝ። ጥፍት ስልም ያው ነው።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
22/05/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ዕውነት ወጌሻ አይናፍቀውም፤ ጋራጅም አያሰኜውም።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ