በነገረ ሐራ መሬት የነገ #ስጋቴን ብገልጽስ? #ነገን ሰላማዊ ተከታይ ስለማድረግ።
በነገረ ሐራ መሬት የነገ #ስጋቴን ብገልጽስ?
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
#ምዕራፍ ፲፱።
#ጠብታ።
በብልጽግና መንግሥት የተፈቀደለት ሽምቅ ተዋጊ ኃይል በአፋር እንዳለ ሳድምጥ ቆይቻለሁኝ። ለሽምቅ ኃይሉ የፖለቲካ ክንፍ እንደተደራጀለትም ይገባኝ ነበር። ግን የእኔን የመረዳት መጠን መሬት ላይ ካለው የራሱ አካል ማረጋገጫ እስኪሰጥበት ድረስ ጸጥ ብዬ መጠበቅ ነበረብኝ።
ሰሞኑን በአርተስ የዜና ዕውጃ ከስምረት ፖለቲካል ፓርቲ በተገኜ መረጃ መሰረት የኃራው ታጣቂ ሸማቂ ኃይል ክንፋ እንደሆነ ዜናው ያትታል። እኔም አውቄው ስለነበር አላስደነገጠኝም። እንዲህ ገልፆ መናገር መልካም ነገር ነው።
#ጥቃትን መቅደም እና መቀደም።
በጣም ከሚያሳዝኑኝ የዓለም ማህበረሰብ ውስጥ ሊባኖናውያን አንዱ ናቸው። ሊባነን መንግሥት አላቸው። መንግሥታቸው ግን ለህልውናቸው ቀጣይነት የደህንነት ዋስትና የመስጠት አቅም የለውም።
አቅሙ ያለው ከመንግሥት ውጭ የሆነው #ሂዝቦላ ነው። የሂዝቦላ የፖለቲካ ክንፍ የሊባኖስ ማዕከላዊ መንግሥት ሳይሆን አገረ #ኢራን ናት። የኢዝቦላ ተቋማት ሁሉ በሊባኖሳውያን ውስጥነት ታዳሚወች ናቸው። ወጩ የሚሸፈንለት በኢራን መንግሥት ነው። የሂዝቡላ የፖለቲካ ያው ሃይማኖታዊ ነው፤ የታጣቂ ኃይል መሪ የኢራን መንግሥት ፖለቲካ ነው።
ሂዝቦላ ለሚወስደው እርምጃ ዋጋ የሚከፍለው ደግሞ መከረኛው የሊባኖስ ህዝብ ነው። ይህ ወጣ ገብ ሁነት የተፈጠረው ከጥንስሱ የሊባኖስ መንግስት የራሱን የፖለቲካ፤ የሚሊተሪ ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ባለመቻሉ ነው። የዘገዬ እና ፍዝ አቋም ያለውም ነው።
አሁን የሊባኖስ ንጹኃን የሚከፍሉት ዋጋ ተመን ሊወጣለት የማይችል ነው። ከሊባኖስ መንግሥት ይልቅ ተደማጩ፤ ተፈሪው የህዝቡ የመኖርም ወይንም ያለመኖርም ፈቃድ ይለፍ የሚሰጠው በሂዝቦላ ነው።
በሌላ በኩል ራሽያም ፈቅዳ ያደራጀችው አይበገሬ አቅም ነበራት። ከመደበኛ ሠራዊቷ ውጪ። በዩክሬን እና በራሽያ የመቅድመ ጦርነት ላዬ የመከተ በጣም ተፈሪ የታጣቂ ሠራዊት ነበር። #ማፈንገጥ ሲጀምር ጉዳዩ በኤሌኮፕተር አደጋ ተጠናቀቀ።
ያ የሆነው ጥቃትን መቅደም ስለተቻለ እንጂ የሰናፍጭ ታክል መዘናጋት ቢኖር ዛሬ ያለው የዓለም ፖለቲካ የኃይል አሰላለፍ ሁኔታ ሊቀይር፤ አዲስ የዘመን ምዕራፍ ሊከፍትም ይችል ነበር። ራሺያ ከዓለም የኃያልነት ደረጃዋ ዝቅ ልትልም ትችል ነበር። በትኳ ህልመኛው ዘለንስኪዝም ጉብ ሊሉበት ይችሉ ነበር ዛሬ አሜሪካ፤ ቻይና እና ራሽያ ፊትለፊት ገጥለገጥ ብዙም ባልተበላለጠ ሁኔታ የሚታዩት ፑቲንዚም በራሱ፤ በውስጡ አደራጅቶት የነበረው ልዩ አቅም ከሥሩ የማንጠፍ ፖለቲካዊ ሂደት በፍጥነት በመከወኑ ነው።
ፑቲንዚም ህግም፤ ደህንነትም፤ ዓውራ መሪነትም በዘለቀ ልምድ እና ተመክሮ ማጎልበቱ ጉዳዩ ከቁጥጥር ውጪ ሳይሆን መዳፍ ላይ አይሆኑ መሆን ችሏል። ብዙ አስቸጋሪ እና ፈታኝ ሁኔታወች ለአየአገሮችም፤ ለዓለምም የሚፈጠረው እንደ ዋዛ አንዱን ቁስል ለመፈወስ፤ ሌላ ቁስልን በሙሉ አቅም አደራጅቶ በመምራት የሚያመጣው ጠንቅ ነው። ጠንቁ ማገዶ ይፈጃል። ማገዶው ደግሞ የሰው ልጅ፤ ሥልጣኔ እና የስጋት ካንፓኒ ተፈቅዶለት #አና ይላል። አንድ ኃይል ከገነገነ በኋላ ከዳር አልመለስ ከማህል አልታረስ ይልና የቀውሱ ሁሉ ማከፋፈያ ይሆናል።
#ነገን ሰላማዊ ተከታይ ስለማድረግ።
ህወሃት ዓለም ዓቀፍ ዕውቅና በሁሉ የባህሬ ዓይነቱ የሚታወቅ ድርጅት ነው። ህወሃት የፖለቲካ ስልጣኑን ፈቅዶ ሲለቅ የተገኜው ልዩ ታምራዊ የእዮር ዕድል በአግባቡ ማኔጅ ማድረግ ባለመቻሉ፤ ይኽው ኢትዮጵያን ቁሚ ተቀመጪ እያለ በስልጣን ከነበረበት ዘመን በከፋ ሁኔታ የሰላሟ ጠንቅ ሆኖ ሁልጊዜ መሳሪዬን እየወለወልኩ ነው ድርሳኑ ነው።
ከጦርነቱ ማግስት በመጀመሪያው ዕድል ነበር። የደቡብ አፍሪካው ሌላ ሁለተኛ ዕድል ነበር። ሁሉም ዕድል እንደ ዋዛ አመለጠ። አሁን ህወሃት በተደራጄ አቅም እንደገና ከወደቀበት ለመነሳት ትግል ከራሱ፤ ትግል ከውስጡ ከሚታገሉት ጋር እያደረገ ነው።
የትግራይን የኢትዮጵያ ቤታዊነት በጊዚያዊ ይሁን በቋሚነት ለማምጣት "ስምረት" ተመሰረተ። በሰላማዊ ትግል። በሌላ በኩል ለትጥቅ ትግል ደግሞ ሌላ ክንፍ ተደራጄለት። በብልጽግና መንግስት ብቸኛው ሙሉ የሎጅስቲክስ ድጋፍ እየተሰጠው ያለ የሽምቅ ኃይል ተደራጄለት። በጣም ነው የሚገርመው። ምንም ሁነኛ የፖለቲካ ክንፍ የሌለው ፋኖን ዓይንህ ለአፈር የሚል ብልጽግና የሥምረትን ሽምቅ ሲያደራጅ ግን ቅጭጭ አላለውም።
ሁለቱም ቁልፍ መሪወች በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያላቸው ናቸው። እንደ ፈንታሌ ሚዲያ መረጃ ኢትዮጵያን በቀጣይ ማን ይምራት? ለሚለው የዚያ ሰሞን የአየር ሁኔታ ከቀረቡት ሦስት ኢትዮጵውያን ለጠቅላይ ሚኒስተርነት አቀረቡት እጩወች ጄኒራል ፃድቃን አንዱ ነበሩ። በሌላ በኩል በዓለም ዓቀፍ ሚዲያ ጄኒራል ፃድቃን ገ/ ተንሳኤ ከፍ ባለ ብቃት እንደ አላቸው በመካከለኛው አፍሪካ አሉ የሚባሉ ስለመሆናቸው ምስክርነት በዓለም ዓቀፋዊ ሚዲያ ሳደምጥ ነበር።
አቶ ጌታቸው ረዳም የኢትዮጵያ አንደበት፤ በኋላም የህወሃት የጫካ ትግል ልሳን የነበሩ ናቸው። ሁለቱም በዲፕሎማሲው ማህበረሰብ ከጠቅላይ ሚር አብይ ባላነሰ፤ በአቻነት ወይንም በለጥም ሊል የሚችል ተቀባይነት፤ ዕውቅና ያላቸው ናቸው። በሌላ በኩል የዲፕሎማሲው ጉዳይን መውጫውንም ይሁን መግቢያውን ጠቋሚ፤ መንገድ መሪ የማይሹ ናቸው። ኔትም ይኖራቸዋል።
ይህ የነገረ ሃራ መሬት ጉዳይ #የፖለቲካ ክንፍ አለው በብልጽግና ተፈቅዶለት። ማዕከላዊ መሪ አለው። ለጊዜው ዲስፕሊኑን የጠበቀ ሊሆን ይችላል። ለመሪወቹ ህይወት ስለሚያስፈልገው። ነገስ ነው ጥያቄዬ???
ለሥምረት ፓርቲ የተፈቀደለት ሁለገብ ትግል፤ ሌላ ፓርቲ ቢጠይቅ ይፈቀድለታልን? ገና ትሆናላችሁ ተብሎ ስንት ሰብ ነው ለካቴና የተዳረገው?
ነገ "ቁጭ ብሎ የሰቀሉትን ቁሞ ማውረድ" ሊቸግር ይችላል። ከየትኛውም ከፋኝ ካለው ሽምቅ ተዋጊ በላይም፤ ከአቅም በላይ ሊሆን የሚያስችል ህሊናዊ፤ ሞራላዊ፤ ክህሎታዊ አቅም አለው ሥምረት ፓርቲ። ትንሽ መንጠላጠያ ነው የሚፈልገው። ይህ እኔን በእጅጉ #ያሰጋኛል።
ቀለል ያለውን ችግር ለማስወገድ ወደ #መርግ ወደ ሆነ ፈተና መግባት ስልትም የተበጠሰበት፤ ጥበብም የሳሳበት፤ ነገንም አጀንዳው ለማድረግ ያልፈቀደ የምንግዴ ተግባር ነው - ለእኔ። ነገን ሰላማዊ ተከታይ ለማድርግ ፈጽሞ በጥልቀት ያልታሰበበት እርምጃ ነው። የፖለቲካ ክንፍ ያለው ሽምቅ በሎጅስቲክ ሙሉ ድጋፍ በመንግሥት ፈቅዶ ማስጀመር ለነገ ዳጥ በአቀበት ይሆናል።
የፖለቲከኞች ስምምነት ቋሚ አይደለም። እንደ አየሩ ጸባይ ወጣ ገብ ነው። በተለይ የመሳሪያ ትጥቅ ተፈቅዶለት የሚደራጅ ሽምቅ ለአገር በብሄራዊ ደረጃ ብቻ ሳይሆን፤ ለቀንዱ፤ ለአህጉሩም ጤናማ ትንፋሽ አይደለም። ለትውልድም ስጋት ማዳበሪያ ነው። በየአካባቢው የታጣቂ ክንፍ????
መጥኒ ላንቺ አዲረመጥ። በቀጣይም አዳርቃይ፤ ጠለምት፤ ማይጠምሪም።
የሚገርመው ሙሉ 8 ዓመት በታቀደ የበቀል ቀውስ እየተቀጠቀጠ የሚገኘው የአማራ ክልል፤ #የማይካድራ፤ #የጭና ላይበቃ የሥምረት ክንፍ ተግባሩን የሚከውንበት በዕት #ማይጠምሪ ነው፤ የሚቀለው የነበረው ሁለቱ የራያ ቁንጮ ፖለቲከኞች ቅድሚያ በህወሃት እጅ አሳሩን እያዬ ላለው እትብታቸው ለተቀበረበት ባድማ ለራያ ሊደርሱለት በተገባ ነበር። ቅርባቸውም ነው ለውስጣቸው።
ጉዳዩ ስለምን #አዲረመጥ ላይ እንደተወጠነ ይገባኛል። በረጅሙ ይገባኛል። ቅያሴው ምን ለማስገኜት፤ ምን ለማስተረፍ እንደሆን ታቅዶ እንደሚከወን አውቀዋለሁ። ዛሬ ለአማራ ነገ ግን ለመካከለኛው ምስራቅ አፍሪካ ዕዳ ከሜዳ ሊሆን ይችላል። ከህወሃትም የከፋ ገጠመኝ #ሊጭን ይችላል።
በቲም ስምረት በኩል ከህወሃት ፍላጎት ያፈነገጠ ሆኖ ነው የቀረበው። አንድም የትግራይ የፖለቲካ ሊቅ፤ ሊቃውንት ሊሂቃን በስልትም፤ በስትራቴጅም ወጥ ናቸው። የሚለያዩት ጊዜን በማድመጥ ብቻ ነው። አንዱ የተጋሩ የፖለቲካ ድርጅት ከሌላው የተለዬ ፍላጎት የለውም። ተቆርቋሪነቱም #ራስጌም፤ እግርጌም የለውም። ሁሉም ልብ - ተኩላሊት፤ ህሊና - ከመንፈስ የተዋህደ ፍላጎት ነው ያላቸው።
ቤተ - ስምረት የሚለየው ከህወሃት #Timing ማድመጥ መቻሉ ነው። ቤተ ሥምረት ከየት እንደገዛው ባላውቅም ትልቅ ጆሮ አለው። አሁን ባለው የብልጽግና የይሁንታ ሃዲድነት ሙሉ አቅም ተጠቅመን፤ ጊዜውን አዳምጠን፤ በምንችለው ጅማሮ #የማንቻልበትን መንገድ እንምረጥ ነው። ይህ ብልጥነት ሳይሆን ፖለቲካዊ ብልህነት ነው።
በሌላ በኩል እኔ ደስ የሚለኝ በቋንቋ የሚታደኑትን የተጋሩ መንፈስ ወከባ ሥምረት ያረጋጋ ይመስለኛል። ጥሩ እርምጃ ነው። ያልተመቸኝ ሽምቅ ስለተደራጀለት ነው።
የብልፄው ደጋፊወች፤ አክቲቢስቶች፤ ሚዲያወች፤ ፕሮፖጋንዲስቶች፤ ተከታዮች፤ የመንግሥት ሚዲያወች፤ የመንግሥት ሙሉ ላዕላይ እና ታህታይ መዋቅሮች፤ በጀቱ፤ ፍቅሩ፤ መተማመኑ በሽ ነው። ቤተ - ብልጽግናወች አጀንዳቸው #ሥምረት ነው።
ይህን አደራጅተው የመምራት ብቃቱም፤ ክህሎቱም ቤተ - ሥምረቶች አላቸው። በብልጽግና ይለፍ አልጋ ባልጋ፤ በሞዝቦልድ ፈልሰስ ብለው ፍላጎታቸውን የማስፈጸም አቅም አላቸው። ቲካቲካ የለም። ግልምጫ የለም። መገለል የለም። ተጫኝነት የለም። ተከብረው እንክህ እንክህ ተብለው፤ በክት ልጅነት ተቆላምጠው ተይዘዋል። ብልጽግና የስትራቴጄ ቁልፍ በማለት ብቻ ሳይሆን ደጋፊወቻቸውንም የማረጋጋት እና አቅምን የማከል ሁኔታም አለ።
ህወሃት ኦህዴድን ሲያደራጅ የጋራ ጠላታችን የሚሉትን አማራን #በመደሰቅ ነበር። ህወሃት ያሳደገው ኦህዴድ ደግሞ አድጎ፤ ደርጅቶ ህወሃትን ከመንበረ ማዕከላዊ መንግሥቱ ነቀለው። ህወሃት ዕድል ቢያገኝ ይህን መስመር የወደቀበትን እንደማይደግመው 100% እርግጠኛ ነኝ። የጸጸቱ፤ የእልሁ ምንጭም ይህ ነው። እና በዚህ አጋጣሚ "ጥምዶ" በተለይ ለአማራ መቃብር ቆፋሪ ይሆናል።
ነገስ ብልጼው ስምረትን መንግሥት አድርጎ አደራጅቶ፤ መከላከያውን ጨምሮ አደራጅቶለት፤ ለህወሃት ፈተና እንዲሆን እያደረገ ነው። ቤተ - ስምረት ተሳክቶለት የእቴጌ መቀሌ ጌታ ቢሆን ማን የበላይ? ማን የበታች ይሆን ይሆን? ይንጋና እናዬዋለን።
በዚህ ማህል የትግራይ፤ የወሎ የጎንደር ህዝብ አለ። በየዘመኑ እንዲህ ተፈቅዶላቸው በሚደራጁ ባለመሳሪያወች ትውልድ መኖሩን፤ መፈጠሩን ያጣል።
#ኢዜማ ሲደራጅ መንግሥት እና ፓርቲ ሆኖ ነው።
ግን እስከ አሁን በምከታተለው ልክ ታጣቂ፤ ሸማቂ የለውም። ሥምረት ግን ታጣቂ፤ ሸማቂ አለው። የፖለቲካ ክንፍ + የታጣቂ ክንፍ= ለስምረቱ ቅርብ ነው። ወጪ የለበትም። ወጪ የምለው ከፍተኛው ወጪ የመንግሥት የይለፍ ፈቃድን ነው።
የሆነ ሆኖ ለነገ የትኛው ይሆን ለኢትዮጵያ መንግሥት ስጋት ሊሆን የሚችለው? ሥምረት ወይንስ ኢዜማ? ኢዜማ ብዕር እና ብራና፤ ሥምረት ብዕር፤ ብራና፤ ጠበንጃ በፖለቲካ በበሰሉ መሪወች።
የአመራር ብቃት ችግር በሥምረት ፓርቲ የለም። ዓለም ዓቀፍ ዕውቅናው አንቱ ነው። አቶ ጌታቸው የኢትዮጵያ አንደበት የነበሩ፤ ጄኒራል ፃድቃን ገ/ ተንሳኤ ደግሞ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ሠራዊት የመሩ ናቸው። ደረጃውም ከፍ ያለ ነው።
የህወሃት መንበረ ሥልጣን ፈቅዶ መልቀቁ እየዋለ ሲያድር ጸጸት፤ ቁጭት አይኖርባቸውም ልል አልችልም። ለዛም ነው ዝቅ ብለው፤ ያለውን ተቀብለው፤ ባለው ዕድል መሰላልነት በእልህ ሳይሆን #በብልህነት መሪነቱን እያባበሉ የሚገኙት።
ይህ እንዳይሆን ነው ስጋቴ። ሥምረት ሁሉ አለው። በህጋዊ መድረክ ላይ ይለፍ የተሰጠው #ሁለገብ ታጋይ የፖለቲካ ድርጅት ነው። በትጥቅም በሰላማዊ መንገድም። አቤቶ ስምረትን የኢትዮጵያ የደህንነት አካላት #ለእኔሲል ብሎ ቢሰይመው ትክክል ነው። ከአንድ ወንዝ የተቀዱ። አህቲ መንፈስ ነው ያላቸው። እና ብልፄው ነገን ተከታይ ለማድረግ ……
#ክወና።
"ውል ያዋውላል፤ ታንኳ ያሻግራል።" ይላሉ ጎንደሬወች። ውል ይኖራቸው ይሆን #ብልፄው እና #ሥምረትሻ? ጥርት ያለ #ውል ያስፈልጋል። ውሉ በጓዳ ሊሆን አይገባም። ነገ ድረስልኝ የሚባለውም ህዝብም በቂ ዕውቀት በየትኛውም ለሰላም ጥበቃ በሚያደርጉ ውሎች እንዲሳተፍ፤ እንዲያውቀው ሊደረግ ይገባል። ከሁሉም ለኢትዮጵያዊነት የታወቀ ህጋዊ ሰነድ ያስፈልጋል።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
22/05/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ዕውነት ወጌሻ ወይንም ጋራጅ አያስፈልገውም።
See less
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ