፲ #ኤርትራ፤ ፳ ሰሜን ሱዳን፤ ፴ ግብጽ አያስደነግጡኝም - እኔኑ። #ለምን? #ይልቁንስ እኮ ……… #ምን???
"አቤቱ የቤትህ ቅናት በላኝ።"

#ምዕራፍ ፲፱።
፲ #ኤርትራ፤ ፳ ሰሜን ሱዳን፤ ፴ ግብጽ አያስደነግጡኝም - እኔኑ። ለምን?
ፈላስፊት ኢትዮጵያ ------አትለካም።
ሳይንቲስቷ ኢትዮጵያ -------አትሰፈርም።
ዩንቨርሷ ኢትዮጵያ --------አትመዘንም።
ህጊት ኢትዮጵያ ---------አትገመትም።
ቤተ - ይሉንታዊቷ ኢትዮጵያ -------------#አትከነዳም።
ሱዳንም በቀደመው ጊዜ ወራ በመተማ በኩል፤ ግብጽ ዕድሜ ልኳን ታግላ፤ በዞግ አደራጅታ ባህር በር ይሁን ወደብ አሳጥታ፤ የአፍሪካ ቁልፍ ቀንድነቷን ፈትና፤ ኢትዮጵያ ግን አለች የአፍሪካው ህብረት #ዋና ጽህፈት ቤት ሆና፤ የዓለም ፬ኛ #የዲፕሎማሲ ዓይንም ሆና ቀጥላለች።
ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያኒዝም እንደ አሻው በሆነ አካል የሚኮሰምን፤ #ቃ የሚል፤ #ዳ የሚፈትነው፤ ስብራት የሚጎበኜው ማንነት አይደለም። ብዙ ያለው፤ ያለውን ልቅና በልዕልና መስጥሮ የተቀመጠ አንቱ ማንነት ነው ኢትዮጵያዊነት። የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና "#በደራሽ ሱናሜ፤ በምኞት ፈረስ ፍርስርሱ ይሁን ብትንትኑ የሚወጣ" ማንነት አይደለም ተፈሪው ኢትዮጵያዊነት።
በብልጽግና ዘመን እራሱ እኮ ብዙ ፈተናን አስተናግዷል። ተቋማቱ ሁሉ ፈተና ላይ ነው የባጁት። የኢትዮጵያኒዝም አማንያን ያላዩት የአሳር፤ የፍዳ ዓይነት የለም። ሎጎወች ኢትዮጵያን ከሚገልጹ ንጥረ ነገሮች ሁሉ በእጅጉ ከድንቁ የኢትዮጵያዊነት ማንነት የራቁ ናቸው። አንድ ቀን ለራሳቸው ለጠቅላይ አብይ አህመድ ሰባስቤ አቀርብላቸዋለሁኝ። በዚህው በቤተ ሥርጉትሻ።
ኢትዮጵያ ላንቃ ላይ ወይንስ የውስጥ ሆና ደልደል ብላ ተቀምጣለች የሚለውን ይለኩበታል ዶር አብይ አህመድ። ለሳቸውስ አብይዝም ወይንስ ኢትዮጵኒዝም ማን ይበልጥባቸዋል? የህሊና ዳኝነቱን ለዓለሙ የሰላም አባት ለሎሬት ጠሚ አብይ አህመድ አሊ ይሆናል። ኢትዮጵያ በ፬ቱም ማዕዘን ጭንቅ ላይ ስትሆን ተግ ማለት ይገባል። ሙግቱን ማስታገስ። የተሻለ የፌስታ ጊዜ ለብልፄው ሲሆን ግን አክብሮ በማስተዋል መሞገት ይገባል።
የእያንዳንዱን የዘመኑን አሻራ መምርምሩት፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚጫን፤ የሚያገል ነው። ገደልነው፣ አደበዘዝነው፣ ድብ አደረግነው ብለው ሲያስቡ ግን ኢትዮጵያኒዝም ቀን ሲሰጠው ጎልቶ እና ጎልብቶ ሲወጣ መሪ አካላቱ #ይደነግጣሉ። ስትራቴጂያቸው ፋርሽ ስለሚሆን። ኢትዮጵያዊነትን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሊቃናት ለምን እንደሚቀኑበት፤ ለምን እንደሚፋለሙት አይገባኝም። መውደቅ ይናፍቃልን?
እነሱ በጥንቃቄ ነው ሠራን የሚሉት። ሙሉዑ የብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀለም እንዳይወጣ፤ ብቅ እንዳይል በሰፊው ተሰርቶበታል። ጭምቱ ኢትዮጵያዊነት ግን በደም ውስጥ ስለተቀመመ በቦታው አለ። ዕውነት ቦታውን ለቆ አያውቅምና። ማን ደፋር ነው በእኔ በሥርጉትሻ ደም ውስጥ ኢትዮጵያዊነትን ለመፈተን የሚደፍረው? እእ። አይቻልም። መቼውንም አይቻልም። ፈጽሞ።
ትናንት ከጀርመን ጋር ኩሩሳኡ የሚባል የደሴት አገር ለዓለም ዋንጫ ያደረሰው ሚስጢር የማንነት ብቃት ነው። ህውከት ያልገጠመው፤ ወጀብ ያልናጠው ማንነት ከ150 - 158 ሺህ ህዝብ ለዓለም ዋንጫ ውድድር ቤተኛ ነበር። ከድንቅ በላይ ነው።
ከጀርመን ጋር በነበረው ውድድር መሸነፋ የልምድ፣ የተመክሮ ጉዳይ ነው። ግን ከዚህ የደረሱት ሚስጢር ግን ክስተት ነው። ክስተቱ ማንነታቸውን የሚታገል ጣውንት አመራር ስለለባቸው፣ ጥንካሬያቸው በተፈጠረበት ልክ ጉልላት ሆነ።
#ማንነትን ከውስጡ አምኖ የተቀበለ መሪ ሲኖር ለአይበገሬነትን እንዲህ የአቅም ታብሌት ይመግበዋል። ያቺ ቀደመት ሁሉ ያላት አገር ግን እሷኑ እየፈተኑ ትውልዱን መቅኖ አሳጡት። ትውልዱ መኖሩን ይሰብ ወይንስ ከትውልዱ የዓለም በረከት ጋር እኩል ይራመድ? እናታቸው በምትፈልጋቸው ልክ አቅማቸውን እራሱን ለማሰናዳት ትንፋሽ ያጥራል?
በሌላ በኩል የጀርመን የውስጥነት ፖሊሲ #ጽንሱ ነው ስለአገሩ እየዘመረ የሚፈጠረው። የጀርመናዊ ዜግነት፤ ብሄራዊነት እንደ ኢትዮጵያዊነት #ሸምቀቆ የለበትም። ነፃ ነው። ሳር ቅጠሉ ጠረኑ ጀርመንኛ ነው። ከውስጣቸው ማንነታቸው ይበቅል፣ ይፀድቅ፣ ያሰብል ዘንድ፣ ፖለቲከኞች ተግተው ይሠራሉ። እናም የጀርመናዊነት ማንነት በሥልጣኔ ግስጋሴ ላይም ነው።
በኢትዮጵያዊነት ላይ ግን ዘወትር ሰይፍ ይታዘዝበታል። ሀሁ ፊደል አስቆጥራ ባሳደገች ቅድስት ሃይማኖት ላይም ቀዝቃዛ ጦርነት ይታዘዝባታል።
ኢትዮጵያን የነፃ አውጪ ግንባሮች መንፈስ ተፈራርቀው ገዝተዋል፤ እየገዟትም ነው። ግን እርግጥ ነው #የኢትዮጵያን መንፈስ የሆነውን ኢትዮጵያኒዝምን መርታት፤ ማሸነፍ ፈጽሞ አልቻሉም። ወደፊትም።
ለምን? ለሚለው መልስ ያለፈውን ዕይታዬን እደግመዋለሁኝ። ማንም ተመራምሮ፤ ማንም ተፈላስፎ የማይደርስበት #miracle አፈጣጠሯ ምኞቱን ሁሉ #ብል የበላው ጨርቅ ያደርገዋል።
ብልጽግና ኢትዮጵያን በስውር የሚታገልበትን መስመር ካልገታ የሚያስፈራኝ ይኽው ነው። አሁን አሁን እያስፈራኝ፤ እያሰጋኝ የመጣው ብልፄው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ #ተዋህዶ ጋር በግልጽም፤ በስውርም #ለማልፋት የሄደበት እርቀት እራሱን አክስሞ ኢትዮጵያን አዳጋ ላይ ይጥላት ይሆን እያልኩ ስጋት አድሮብኛል።
ተችሎ ምርጫ በተካሄደባቸው ቦታወች ሁሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ #ልሙጥነት፤ በዛ ላይ ግድያው፤ መቃጠሉ፤ ቤቷ መዘጋቱ፤ ምዕመናን በገፍ ከበዕታቸው መነቀላቸው፤ ተዋህዶ #ማጆሪቲ በሆነበት አካባቢም ያለው አሉታዊ የውክልና #ዴሞግራፊ፤ በተጨማሪም የውስጥ ለውስጥ ዕንባ አትኩሮት ማጣት፤ የአመራር ዝበት፣ የጨመተ፤ የሰከነ ድምጽ አልቦሽ የቅድስት ተዋህዶ ቅዱሳን ዕንባ ለብልጽግና ምኞት እና ስኬት ብላሽ ሊያደርገው ይችላል።
ብልፄው ጥምዶን ሳይሆን ይህን ይፍራ። ብልፄው ኤርትራን፣ ሱዳንን ግብጽን ሳይሆን የኢትዮጵያ ቅድስት ኦርቶዶክስን የውስ የዕንባ ምጥ ይፍራ። እኔ የሚያስፈራኝ ይህ ነው።
ህወሃት በፈቃዱ ይለቃል ተብሎ ከጥዋት ከማታ አልታሰበም። በፈጣሪ ታምር ድምጽ ሳይሰማ የሥልጣን ሽግግር ባልታቀደ ቀን እና ሰዓት ተከወነ። እዮራዊው ውሳኔ ነበር። በሰው እጅ ያልተሰራ።
ሰሞኑን የአማራ ዕውነተኛ አክቲቢስት (በአማራ በደል ላይ ሙሉ መረጃ ያለው) አቶ ሙሉቀን ተስፋው ለውጡ ሳይሰናዱ፤ ፕላን A// B// C /// ሳያዘጋጁ ስለመሆኑ ቃሉን ሰጥቷል። ዕውነቱን ነበር። ለእኛ ይጠቅም የነበረው "አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ቢሆኑ ነበር" ሲል ግን ደንግጫለሁኝ። አሁንም ሳስበው ያስደነግጠኛል። ምክንያቱም ትግሉን ለመቀጠል ይረዳል ባይ ነው ሙሌ።
ዛሬም ቢሆን ትናንት የነበረው አምላክ ዛሬ ስላለ የቤተመቅደስ መደፈር መከራው የከፋ ይሆናል። ኢትዮጵያ ለፖለቲከኞች ፖለቲካዊ ግድፈት ሰማዕት እንዳትሆን በእጅጉ ያሰጋኛል።
#ቀነ ገደብ።
ጠና ካሉ ተቃዋሚወች ሰፋ ያለ ምኞት በቀነ ገደብ ተተምኖ አዳምጣለሁኝ። መቀናጀቱም አለ። ይህ ሁሉ እኔን አያሰጋኝም። የቅድስቷ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ የህቅታ ዕንባ ግን በእዮር ከተደመጠ የሚያሳካውን ሊያሳካ ይችላል።
ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሰርታ ባስከበረቻት አገር ስደቷ መራራ ሆኗል። መስቃውም ጋራ። ተሠርታ፤ ተደራጅታ በጠበቀች አገር እኮ ነው ዛቻውም፤ መስቃውም፤ ግርፋቱም አና ያለው።
#የሆነ ሆኖ……
ሳይመሽ በግዜ ብልህነትን የሰነቀ፤ ማስተዋልን ምራኝ ያለ፤ ተጨባጭ #የይቅርታ እና የአገር ባለቤትነት ልዩ ዓዋጅ ለቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በጽኑ ያስፈልጋታል።
ልጆቿም ያለ ሰቀቀን በማተባቸው ጸንተው ይኖሩ ዘንድ ሰላማቸው ሊከበር ይገባል። እንግልቱ ከአቅም በላይ ሆኗል። የአብይዝምን ሥርዓተ - መንግሥት መንቀል ለሚፈልጉ ተቃዋሚወች፤ ልዩ የነጠረ አቅም ሊሆን የሚችለውም ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ መሥጥራ የምታነባው የሰርክ ዕንባ ይሆናል። በዓለም ውዱ ፈሳሽ የሚቀዳው ከዓይን ብቻ ነው ያለው።
መስቀል ሊሳደድ አይገባም!
የታሪክ ሽሚያውም ሊቆም ይገባል!
የፖለቲካው በርም ለተዋህዶ ሊቃናት መከርቸምም ጥበብ የራቀው ደረቅ ይሆናል። የደረቀ ሁነት ይሰበራል። ጥበብ የነፈገው ሂደትም ይፋድሳል። በመጨረሻም ሊተን ይችላል።
የፓርላማ የውክልና ሂደት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋህዶን ደረጃ ያሳያል። እሷ ይሁንብኝ ብትልም ፈጣሪዋ ዝምታዋን ላይፈቅደው ይችላል። በዛ ላይ ነው ተቆርቋሪ ባለሥልጣን ስለለላት መከራው - መገፋቱ - መገለሉ - ማሸማቀቁ - መገደሉ፣ ብወዛውም #በዝቷል።
መሪነት ያጋደለ ሊሆን አይገባም። ኢትዮጵያን እመራለሁ ሲባል በኢትዮጵያዊነት ውስጥ የገዘፈውን ድርሻ የያዘችውን ቅድስቷን ተገፍትራ ሊሆን አይገባም።
በባዕቷ ስለምን ቅድስቷ ትሳደድ? በብልጽግና መንግስት አለን የሚሉት ፋክቱ ሁሉ ያፈነግጣልና የቁርጡ ቀን ከመጣ። የተዋህዶን ቅድስና ንጽህና - ልዕልና - ልቅና - የተጠየፈ የትኛውም አካል መጨረሻው አያምርም።
እግዚአብሄር ሲሰጥ ከሰጠው በላይ ውለታውን በገቢር በትህትና እና በአክብሮት መመለስ ሲገባ ጭራሽ ሰጪውን ማሳደድ? የተዋህዶ መከራ እና በደልን ሁሉ ፈጣሪ ዝም ብሎ እስከመጨረሻው ላያይ ይችላል። ማስተዋል ያስፈልጋል። ጠንካራ ማስተዋል።
እንደ መከወኛ።
ሌላ ለውጥ ከዕንባ በተጨማሪ ከውጭ የሚመጣ አይሆንም። ከኔፓል፤ ከማዳጋስካር፤ ከሲሪላንካ፤ ከኬኒያ አይታፈስም። ይህን ተገን ሁልጊዜ የሚያደርጉ ሰብዕናወች አሉ። ይህ ገጠመኝ ሲፈጠር ተቋም በማደራጀት የእለት እርካታን የሚናፍቁ። ባይከፋም ምኞት አሳኪነቱ ግን የዚያን ያህል ነው። እርግጥ ነው አጋዥ መሆን ይችላል። ወሳኙ ግን ከውስጥ ከራሱ ከብልጽግና፤ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወይንም ሙሉ አቅም ካለው ሳይለንት ማጆሪቲው።
ይህም ቢሆን እግዚአብሄርን አላህን አስቀድሞ ሲነሳ ነው ዘላቂ የተስፋ ስንቅ የሚገኜው። የሆነ ሆኖ ብልፄው በውስጡ በቅድስት ኦርቶዶክስ የፈጠረውን ጦርነት ፈጥኖ፤ እራሱን አርሞ ሊያቆመው ይገባል። ይቅርታም የሙሉ ጥበቃ ልዩ ህግም ያስፈልገዋል። የመንግሥቱ ሰርኩላሪዝም ሃይማኖታዊ ካልሆነ። ይህም ስጋት አለብኝ እኔ።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
15/06/026.
ትዕግሥት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ