#በአገራቸው ፓርላማ #ስደት ላይ የነበሩት የህዝብ ተመራጭ እንደራሴ ዶር ደስአለኝ ጫኔ #በቃኝ! አሉ።

 

#በአገራቸው ፓርላማ #ስደት ላይ የነበሩት የህዝብ ተመራጭ እንደራሴ ዶር ደስአለኝ ጫኔ #በቃኝ! አሉ።
 
"አቤቱ የቤትህ ቅናት በላኝ።"
 
#ምዕራፍ ፲፰።
 
የዜግነት እርቦ፤ የዜግነት ሲሶ፤ የዜግነት እኩሌታ ያዬሁበት የፓርላማ ጊዜ ነበር ዶር ደሳለኝ ጫኔ እና አራት ጓዶቻቸው በህዝብ ሙሉ ድምጽ ተመርጠው አህዱን …… ክለቱን……… ሰለስቱ……… አርባዕቱ ………፭ኛው ዓመት እንሆ በጣት የሚቆጠሩ ወራት ቀሩ።
 
ለኢትዮጵያ ፓርላማ #የመተንፈሻ #ቧንቧ የነበሩት የህዝብ እንደራሴው ዶር ደስአለኝ ጫኔ #በቃኝ! ሲያንስ ነው ባይ ነኝ። ለምን? ያን ሁሉ ግልምጫ፤ ያን ሁሉ ስላቅ፤ ያን ሁሉ መዘባበቻነት፤ ያን ሁሉ ግልምጫ፤ ያን ሁሉ መታፈን፤ ያን ሁሉ የሰው ክቡሩነት የተናቀበት ሂደት ተሸክመው እዚህ መድረሳቸው የሚገርመኝ፤ የሚደንቀኝ ገጠመኝ ነበር።
 
እኔ በተፈጥሮዬ መጀመሪያ የማዬው #ገጽን ነው። ገጹ የተከፋ የማንኛውም ሰብዕ ሁነት ከተመለከትኩ፤ ከዛች ቅጽበት ጀምሮ #ወራጅ አለ ነው።
 
#እንዲህም ሆነላችሁ። 
 
በአንድ ወቅት ህዝባዊ ስብሰባ በርን ነበር። ከቪንተርቱር በርን በራሴ ወጪ ተጓጉዤ ሄድኩኝ። የጋበዙኝ ሰወች፤ ለማደሪያም ቦታ እንደተዘጋጀልኝ ተነግሮኝ ነበር የሄድኩት። ቃል የገቡት ግን አልተገኙም። እኔ ግን ቀድሜ ተገኜሁኝ። የተፈለግሁበት መሠረታዊ ምክንያት #አሽሙር እንዳደምጥ ነበር። እኔ ሥርጉተሥላሴ የየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ቁሮ እንጨት ወይንም ልጥፍ ከሰል ለመሆን መቼውንም አልፈቅድም። የራሴ እንደራሴ እራሴው ነኝ። 
 
እናላችሁማ #ቆፍጣናዋ ጎንደሬ የሄደችው "#የፈራ ይመለስ" 500 ወጣቶች ቲሸርት በራሳቸው ወጪ አሰርተው የበዓቴ አንበሶች ህወሃትን በመሞገታቸው ፤ ነበር እነሱን ለማሞገስ የተጓዝኩት። ታስታውሱ ከሆነ የደምሂት መሪ አቶ ሞገስ አስጎዶም ለህወሃት እጅ መስጠትን አስመልክቶ ነበር 500 ወጣቶች በጎንደር ከተማ ተቃውመው ሰልፍ የወጡት። ስለ እነሱ ተጋድሎ ገንዘብ ደጉሜ የአቅሜን #ለማዘከር ነበር የተጓዝኩት። ከጌንጫ ንቅናቄ በፊት የቀደመው ይህ ንቅናቄ ነበር። "ወልቃይት ብረሳሽ" የተጠነሰሰውም ከዚህው ነው።
 
የሆነ ሆኖ የባድማዬን ጀግኖች አዘክሬ እና የዕለቱ የስብሰባው አለቃ እዬተናገረ #አቋርጬ ወደ ቤቴ ተመለስኩ። ማንም በእኔ ቁጥብ ሰብዕና ለመረማመድ ፈቃድም ይለፍም ሊሰጠው አይገባም እና። እሱ ማን ነውና እኔን የሚዳፈር።
 
በኪነ ጥበቡ ዘርፍ የስብሰባው የአለቃቸው የቲም አባላት የተሰናዱበትን ዝግጅት በዛች ቀንበጥ ዕድሜዬ ሳንሱርድ የምታደርግ ወጣት ቀዳማይ ፖለቲከኛ በዛ አለቃቸው ስሸሞር ስወስን ደቂቃ አልፈጀብኝም። ወሰንኩኝ። ከዛች ቀን ጀምሮ እስከ ህይወቴ ፍፃሜ በምንም ዓይነት ህዝባዊ ስብሰባ፤ ሰላማዊ ሰልፍ ላለመሳተፍ ወሰንኩኝ። ፈጸምኩትም። በየትኛውስ የፖለቲካ አቅም??? 
 
ከዚህ አንፃር ዶር ደስአለኝ ጫኔ በዛ #በከፋ ገጽ እዬተገረፋ፤ በአገራቸው ፓርላማ ላይ #ስደተኛ ሆነው ቻል አድርገው ሲንገበገቡ ሳይ ጥቃቱ ውስጤን ያጨሰው ነበር። በንግግር ጥበብ እንደዚህ ዓይነት ተጋራፊ ኦዲዬንስ ሲገጥም ስልታዊ እርምጃወችን ጥበቡ ይጠይቃል።
 
የሆነ ሆኖ #ደሳለኝዝም የወከሉት ህዝብ ሁሉ አብሮ እንደተንገላታ መንፈሱ አስባለሁኝ። ግፍ ተፈጽሞባቸዋል። ደራሽ ታጋዮች ያን ያህል ሲወርዱባቸው መቻልን አስችለው ከስብሰባው ሲወጡ ደግሞ ሌላ የሚዲያ ሠራዊት ይጠብቃቸዋል። ላዩ - እሳት፤ ታቹ - እሳት እንደ ሙጌራ ዳቦ ተቀቀሉ። እኔ ፎቶ ማዬት እወዳለሁኝ። ከንግግር ጥበብ ውስጥ ከተናጋሪው ይልቅ #የአድማጩ ግብረ መልስ አርት ይስበኛል። ብዙ ክሊፖችን፤ ፎቶወችን ጉባኤው ካበቃ በኋላ ስመረምረው #ጥላቻ ምን ያህል በውስጥ ጎዝጉዞ እንደተቀመጠ አስተውላለሁኝ።
 
 የህዝብ እንደራሴ ሆኖ መየረጥ እኮ ተከብሮ የሚያስከብር የመጨረሻው የሥልጣን መንበር ሆኖ ግን በክብሩ ልክ መሆን ሲያቅት ውስጤ ያዝናል። በሰሞኑ የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ቃል "#ይሁነኝ" ብለን ለቀጣዩ ምርጫ ዥንጉርጉርነት እንሠራለን ብለዋል። የውስጡ #ጥላቻ ላይ ቢሠራበት ቀድሞ ይገባል ባይ ነኝ። ለዛች ለአፍታ ደቂቃ አደብ፤ አቅል፤ ፍቅር መስጠት እያቃተ ነገን በተስፋ መጠበቅ የገዘፈ ጉዳይ ይመስለኛል።
 
የኢትዮጵያ መንግሥት መሥራት ለህዝቡ #ችሮታ ሳይሆን #ግዴታው መሆኑን ዕውቅና ሊሰጠው ይገባል። ሙገሳ ሳይሆን ጠቃሚው መንገድ መወቀሱ ነው። ፍጽምና ከማንም የለም። ካለ ያ የሰው ልጅ ሳይሆን ማሽን ነው። ሰውኛ ግድፈት እንዳይደገም፤ አትኩሮት ያጡ አመክንዮች ትኩረት እንዲያገኙ ሲጠቆም ከግልምጫ፤ ከፍጥጫ፤ ከማጣጣል ይልቅ ፈገግታ እና ምስጋና ሊቀድም ይገባል። ይህን አላዬሁም። ለወደፊትም አዲስ ፓርላማ ይህ ይስተካከላል ብዬ አላስብም። 
 
ንቀት እና ጥላቻ ሥር ሰዶ ስለምመለከት። የትዳር አጋሮቻቸው የፖለቲካ ሰብዕና ያላቸው አንስቶች ቁጭ ብለው ተከታትለው፤ ግድፈቱን ያለ ይሉኝታ ትዳራቸው እንዲያርም ሊያደርጉ ይገባል። በባለፈው ስገረም ያለፈው ሳምንትም ተደገመ። በተለይ ሴቶች ትዳራቸውን የመግራት አቅም ቢኖራቸው ኖሩ ይህ የአደባባይ ግለት በተከታታይ ባልተከሰተ ነበር። 
 
በአሁኑ የቅርብ ጊዜ ፓርላማ ጉባኤ እንኳን ጭምቱ ዶር አበባው ደስአለው ሃሳብ ሲያቀርቡ ይላክ የነበረው #የዓይን ቦንብ ከባድ ነበር። ከዚህ እርሾ ስነሳ ነገ በእጅጉ ያሳስበኛል። የሰው ልጅ በባዕቱ ባይተዋር እንዲህ ከሆነ እኛ ተሰደን የምኖረው ከዚህ የባሰና የከፋ ምን ይደርስብናል?
 
የዜግነት ክብር ተፈቅዶ፤ ተወዶ፤ ተናፍቆ ሥራ ላይ ሊውል ይገባል። በእያንዳንዱ ሁነት silent Discrimination ገኖ የታዬበት የፓርላማ ቆይታ ነበር ያዬሁት። ይህ በፍጹም ሁኔታ ሊታረም ይገባል። እኔ ማናቸውንም ጉዳይ ከውስጥ ነው እማዬው። የትውልዱ ጉዳይ ግድ ስለሚለኝ። 
 
#ወደ ነገረ ዶር ደሳለኝዝም ስንመጣ ……
 
ሰብዕናቸው የሥልጣን መሻት አይደለም። በፍጹም። የአብን ሊቀመንበርነታቸውን በፈቃዳቸው ለቀቁ። አሁንም እጩ ተወዳዳሪነታቸውን እንዲሁ ፈቅደው መተዋቸውን አሳወቁ። ይህ በራሱ ብቁ ሞዴልነት ነው። ቁጭ ብሎ እያለ #የለለነትን የፈቀደው ፓርላማ የሚተነፍስ አባል እንዳለው የሚታወቀው በዶር ደስአለኝ ጫኔ ነበር። በድፍረት በሁሉም ጉዳይ ላይ ሃሳብ ያቀርባሉ። ይሞግታሉ። 
 
የባከነ ጊዜ የላቸውም። እንደዛ እየተጠሉ በትጋት እና በተከታታይነት ሲሞግቱ ቆይተዋል። በሙሉ ሃሳባቸው ለሚስማማ ይሁን ለማይስማማ ድምጽነታቸው ግን የጥንካሬያቸው መለያ ነበር ማለት ይቻላል። በሰሞኑ ፓርላማ አቀማመጣቸው ፈጽሞ አይረሳኝም። ገፃቸውም ጭስ የጸነሰ ነበር። የኢትዮጵያ ወጣቶችን በእኩልነት የሚያስተናግድ የፖለቲካ ዘመን ይመጣ ዘንድ እመኛለሁኝ። 
 
የሆነ ሆኖ ዶክተር ደስአለኝ ጫኔ ለውሳኔያቸው ሁለት መሠረታዊ ምክንያት አቅርበዋል። መወሰናቸውን አክብሬ ውሳኔያቸው ያሳረፋበት ሁለት አንኳር አመክንዮችን ግን አላሳመነኝም።
 
«የፓርላማ አባሉ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ "ለፍትሐዊ ምርጫ ምቹ መደላድል ባለመኖሩ" በዕጩነት እንደማይቀርቡ አስታወቁ»
 
1) በቀዳሚነት የጠቀሱት "ነፃ፣ ሰላማዊ እና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ምቹ መደላድል አለመኖሩ" ነው።
ለዚህ ጥያቄዬ ባለፈው ጊዜስ???? ከአሁን የተለዬ ምን የመስከን አየር ነበር ----ን???
2) በተጨማሪም እስካሁን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነበራቸው ቆይታ "በፓርላማ ውስጥ ተጨማሪ 5 ዓመታትን በመቆየቴ ለሕዝቤ የሚያበረክተው የረባ ጥቅም የሌለው መሆኑንም ተረድቻለሁ" ብለዋል።
 
#ኦኦ። ይህ ፈጽሞ ስህተት ነው። 
 
2.1 ጉባኤው መተንፈሱን እናረጋግጥ ነበር።
2.2 ወክለው ለተገኙበት ጉዳይ ሙሉ ተልዕኮወትን ፈጽመዋል።
2.3 ለትውልዱ የመቻል አቅምን ካሪክለም ነድፈዋል።
2.4 በዜግነት ውስጥ ያለ፤ ለዛውም በህዝብ ተወካዮች ማዕድ ላይ፤ የስደትን ዓይነት አሳይተውናል።
2.5 የእናትን መራራ ሃዘን ችሎ፤ ሳይዝሉ በዚህ ልክ ትጋት የሚደንቅ የመጽናናት አስተምኽሮ ነበር - ለእኔ።
2.6 በህይወተወት አዲስ ምዕራፍ ከፋች ባለታሪክ ሆነዋል።
2.7 የብዙ ፖለቲከኞች የማያስተውሉት ወይንም የሚገፋት ዕድሉ ልዩ ነበር። ያም በመንግሥዊ ሥርዓት ውስጥ አዲስ ልምድ፤ አዲስ ተመክሮ ዝቀውበታል።
2.8 በሥጋ ከተለዩወት ውድ እናተወት I am praud if you ምርቃት ይመጣል።
2.9 በመላ አገራችን ኢትዮጵያ እና በውጭ የምንኖርም ወገነወት ብቻ ሳንሆን ዓለም ዓቀፍ የውጭ ዜጋ የፖለቲካ ሰወች፤ ሚዲያወች የእርሰወን አቅም፤ ችሎታ፤ ሰብዕና ሁላችንም እናይ ዘንድ ሁኔታው ተመቻችቷል። ወዘተ ………
 
ይህ ህዝበ ጠቀም ጉዞ ትርፍ እንጂ ኪሳራ ጎዳና አልነበረም። ወእንደ እኔ እንደ ሥርጉተ©ሥላሴ እኔ ከጠቀስኩትም በላይ አሳክተዋል። እግዚአብሄር አምላክ በጠራወት ቦታ ተገኝተው የጥሪወት ፖስተኛ ሆነው በቅንነት፤ በቻይነት እና በፍጹም ታማኝነት አገልግለዋል።
ስለዚህም መጪው ጊዜ የተረጋጋ፤ የውስጥ ሰላም የሰፈነበት ይሆንለወት ዘንድ ከልቤ እመኛለሁኝ። ላደረጉት ተሳትፎ ሁሉ አመሰግነወታለሁኝ። መልካም መደበኛ የሥራ ዘመን ይሆንለወት ዘንድ እመኛለሁኝ። 
 
 
ዴሞክራሲ የተፈለገው ነጥብ ብቻ ተለይቶ የሚደመጥ፤ የተፈቀደው ብቻ ተነጥሎ ፊት የሚሰጠው፤ ወይንም የፈካ ገጽ የሚነፈገው አይደለም። ዴሞክራሲ መራራ፤ የሚጎረብጡ ሃሳቦችን አዝናንቶ ማስተናገድ የመቻል ዊዝደም ነው። እኛ ገና ነን። ገና መሆናችን ለመቀበል እራሱ ገና ነን።
 
ስለዚህ ትውልዱ ብዙ ጥረት ያደርግ ዘንድ በትህትና ላሳስበው እሻለሁኝ። እኛ ዘመናችን እያጠናቀቅን ነው። ዛሬም ነገም የእናንተ ነውና ወጣቶች መቻልን ለማስቻል እራስን ማብቃት የሚጠበቅባችሁ ይመስለኛል። በዶር ደስአለኝ ጫኔ ያዬሁት አቅም በየአቅጣጫው የነበረውን ጎመራዊ ወጀብ ችለው ክስትም፤ ብለው በአገራቸው - ተገፍተው፤ ተገላምጠው እንሆ እዚህ ደርሰዋል። ከሳቸው መልካም እና ጠቃሚ የሆኑትን ነቅሳችሁ አውጥታችሁ ብዙ ልትማሩት የሚገባ ቁምነገር ያለ ይመስለኛል። ሰክናችሁ መርምሩት። 
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
 
ደህና እደሩልኝ። አሜን።
 
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergure©Selassie
09/02/2026
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው። 
 
የBBC ዘገባ እንሆ ………
 
«በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባዎች ላይ ጠንካራ ጥያቄዎች እና ትችቶችን በመሰንዘር የሚታወቁት የፓርላማ አባሉ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፤ በመጪው ሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ ላለመወዳደር መወሰናቸውን አስታወቁ። 
 
ዶ/ር ደሳለኝ እዚህ ውሳኔ ላይ ካደረሷቸው ምክንያቶች አንዱ "ነፃ፣ ሰላማዊ እና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ምቹ መደላድል አለመኖሩ" እንደሆነ ገልጸዋል።
 
በ2013 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ ተቃዋሚውን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ወክለው ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቡት ዶ/ር ደሳለኝ፤ ይህንን ውሳኔያቸውን ያሳወቁት ዛሬ አርብ ጥር 29/2018 ዓ.ም. በፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ነው።
ዶ/ር ደሳለኝ በስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ የባሕር ዳር ከተማን ወክለው ከተመረጠ በኋላ ከ2014 ዓ.ም. መጀመሪያ አንስቶ በአገሪቱ ሕግ አውጪ ምክር ቤት ውስጥ አባል ሆነው ቆይተዋል።
 
የምክር ቤት አባሉ፤ በመጪው ግንቦት ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ በዕጩነት ስለመመዝገብ አለመመዝገባቸው ከመራጮች፣ ከደጋፊዎች እና ከመገናኛ ብዙኃን "በተደጋጋሚ" ጥያቄ ሲቀርብላቸው መቆየቱን ገልጸዋል።
 
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው የጊዜ ሠሌዳ መሠረት ጥር 1 ቀን የጀመረው የዕጩዎች ምዝገባ በመጪው እሁድ የካቲት 1 ቀን ይጠናቀቃል።»
 
ቀድሞ በሊቀ መንበርነት ጭምር ከመሩት አብን የለቀቁት ዶ/ር ደሳለኝ፤ ሌሎች ፓርቲዎችን ወክለው በመጪው ምርጫ እንዲወዳደሩ ጥያቄ ቀርቦላቸው እንደነበር አመልክተዋል።
 
"አንዳንድ ፓርቲዎችም ባሕር ዳርም ሆነ አዲስ አበባ በፈለግሁበት ቦታ በዕጩነት እንድቀርብ ዕድሉን ሰጥተውኝ ነበር" ብለዋል።
በግል ዕጩነት ቀርቦ የመወዳደር ሀሳብንም "በጥልቀት" እንዳሰቡበት አስረድተዋል። "ሆኖም ግን በመጪው 7ኛው ዙር ምርጫ ራሴን በዕጩነት ላለማቅረብ መወሰኔን ለሕዝቤ ይፋ ማድረግ እፈልጋለሁ" ሲሉ ውሳኔያቸውን አሳውቀዋል።
 
ዶ/ር ደሳለኝ እዚህ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ ያደረጋቸው ዋነኛው ምክንያት በአሁኑ ወቅት "በሀገራችን ካለው ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተያያዘ" እንደሆነ በጽሁፋቸው ገልጸዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘም ሁለት ጉዳዮችን በምክንያትነት አንስተዋል።
 
በቀዳሚነት የጠቀሱት "ነፃ፣ ሰላማዊ እና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ምቹ መደላድል አለመኖሩ" ነው።
በተጨማሪም እስካሁን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነበራቸው ቆይታ "በፓርላማ ውስጥ ተጨማሪ 5 ዓመታትን በመቆየቴ ለሕዝቤ የሚያበረክተው የረባ ጥቅም የሌለው መሆኑንም ተረድቻለሁ" ብለዋል።
 
በመጪው ሰኔ የሚያበቃው የአሁኑ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥልጣን ዘመን "እስኪጠናቀቅ ድረስ ባሉት ጥቂት ወራት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደራሴነት" ተግባራቸውን አከናውነው የአገልግሎት ጊዜያቸውን እንደሚያጠናቅቁ አስረድተዋል።
 
አክለውም "ወደፊት ሀገሬን እና ሕዝቤን እንዴት ለማገለግል እንደምፈልግ የማሳውቅ ይሆናል" ብለዋል።
 
ዶ/ር ደሳለኝ እስካሁን በነበራቸው ቆይታ "ያልተቆጠበ ድጋፍ፣ ፍቅር፣ አክብሮት እና ጽኑ እምነት" አሳይቶኛል ላሏቸው "የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች፣ ለመላው የአማራ ሕዝብ እና ለኢትዮጵያውያን ወገኖች" ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
 
"ባለፉት ዓመታት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ በኩሩው የባሕር ዳር ከተማ ሕዝብ ተመርጨ፣ እናንተን ወክዬ፣ ለሕዝባችን ሀቀኛ ድምፅ በመሆን ለማገልገል በመቻሌ ታላቅ ክብርና ኩራት ይሰማኛል" ብለዋል።"
የፓርላማ አባሉ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ "ለፍትሐዊ ምርጫ ምቹ መደላድል ባለመኖሩ" በዕጩነት እንደማይቀርቡ አስታወቁ - BBC News አማርኛ

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።