#ጥምዶ ለህወሃት፤ ጥምዶ ለአማራ ፖለቲካ ይበጃልን? #በጥምዶ ተጠቃሚውስ ማን ይሆን?
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።

#ምዕራፍ ፲፱።
በጥምዶ ውስጥ የነፃ ዓውጪ ግንባሮች እንዳሉበት አዳምጫለሁኝ። አማራ ጨቁኖኛል ያለ የነፃ አውጪ ግንባር ሁሉ ህወሃትን ጨምሮ "አማራ #አልጨቆነኝም" ብሎ ይሆናል ከአማራ ጋር ሊሠራ የሚችለው።
ይህን ካሉ የነፃ አውጪ ግንባራት ሁሉ #ይፈርሳሉ። ተደራጀን ያሉበትን ጭብጥ በካዱበት ቅጽበት ህልውናቸው ይጠናቀቃል። ይፈጠማሉ። ማናቸውም የነፃ ዓውጪ ግንባራት ህልውናቸው አይቀጥልም። ይህ ዕውነት የት #ይሸሸግ? በየትኛው የማቆያ ሩምስ ይቀመጥ? የትስ ይደበቅ? ፋክት ነው። ፋክት ተሸሽቶ ስኬት የለም።
በሌላ በኩል የአማራ ፖለቲካ ሥረ - መሠረቱ፤ #ዘሃ ግራው የህወሃት ይሁን እሱ የፈጠራቸው የነፃ ዓውጪ ግንባሮች በደሉኝ ነው አይደል? ህወሃት ህገ - መንግሥት ሳያጸድቅም ጫካ እያለም፤ መንበረ ሥልጣን ላይ እያለም ጨክኖብኛል። ተበቅሎኛል ነው።
ይህ አልተፈጸመብኝም ብሎ የአማራ ፖለቲካ ከህወሃት እና ከፈጠራቸው ጋር አብሮ መሥራት ሲጀምር እስከ ዛሬ የተደከመበት፤ የተለፋበት ዘመንም፤ አቅም፤ መዋለ መንፈስም፤ ሰማዕትነትም ሁሉ አድራሻ ቢስ ይሆናል። ለቀጣይ ትግልም እርሾ አልቦሽ ነው የሚኮነው። ሂደቱም ውሳኔውም፤ አስደንጋጭ ነው።
"አለባብሰው ቢያርሱት በአረም ይመለሱ ነው።" ዕድሉን ደግሞ ቢገኝ የህወሃት በቀሉም የሚቻል አይሆንም። ህወሃት ከመንበረ ሥልጣኑን ማን እንደ ነቀለው፤ በኋላም ተስፋውን ማን እንዳሳረረው ጠንቅቆ ያውቃል። ህወሃት እኮ አዛውንት ድርጅት ነው። ልምዱም ተመክሮም አለው።
#ህም።
መቼም የአማራን ህዝብ መበድል፤ መገፋት፤ መገለል፤ አድማጭ ማጣት፤ አቅሙን፤ ቅንነቱን፤ ሰዋዊነቱን እንደማስረዳት ያህል #ከባድ ፈተና የለም፤ ለኢትዮጵውያንም ይሁን ለዲፕሎማሲው ማህበረሰብ። ያን ጋራ ንዶ የህወሃት ሥልጣንን መንበር ነቅሎ፤ በአዲስ ለመተካት ይሁን ከዛም በኋላ እስከ መሸለም ያደረሰው ፋክት መና ቅር ይሆናል። "ህወሃት አልበደለንም አጋራችን ነው" ይላል የጥምዶ ፊድባክ። በቀጣይም የመታገያ ፋክት ያስፈልጋል - ለአማራ ፖለቲካ።
"ህወሃት አልበደለኝም የሚል ፍንጭ ይሰጣል፤" ካሳም // ይቅርታም ሳይጠየቅ ሌት እና ቀን የደከሙ፤ ሰማዕትነትን የተቀበሉ የአማራ ልጆች፤ ዕውነት የመሰከሩ የኢትዮጵያ ልጆች ሁሉ ልፋታቸው #ከንቱ ይቀራል።
አገረ ኤርትራን በሚመለከት ህወሃት ኤርትራን አጋር ስታደርግ፤ "ኤርትራዬ #አልበደለችኝም" ማለት ግድ ይሆናል። ይህ ማለት በጦርነቱ ጊዜ ከህወሃት ጋር ለቆሙት የውጭ ዲፕሎማቶች ሁሉ እጅግ ፈታኝ ዳገት ይሆናል፤ ለህወሃትም የገዘፈ ፈተና ያመጣባታል። #መታመኗን ያሳጣታል።
በአማራ በኩል ከኤርትራ ጋር መሥራት የሚያስከትለው ጫና፤ ኤርትራ በዓለም ማህበረሰብ ባላት ተቀባይነት እና ዕውቅና ልክ ይሆናል። ዓለማችን ኤርትራን እንደምን ያያታል? በዛ ልክ ይሆናል ትርፋም ይሁን ኪሳራው።
#የአማራ ተጋድሎ በተዘጋ አጥር ውስጥ ሆኖ እንዴት ለድል ይበቃል የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል።
ጥያቄው አግባብ ነው። የተሻለውን መምረጥ ትግል ላይ ያሉ የአማራ ፖለቲከኞች ጉዳይ ይሆናል። በስክነት እና በእርጋታ አስቦ መነሳት #ከጸጸትም ማህበራዊ መሠረትን ከማጣትም ያድናል። እኛ ውጭ ሆነን ልንወስንላቸው አንችልም። ድፍረቱ ከየት ይገኛል?
ከሁሉ የከፋው ኤርትራ ለተመድ አሳውቃለች። በጣም ነው ይህን ዜና ስሰማ የደነገጥኩት። ይህ ዕውቅና የጓዳውን ድርጅታዊ ሥራ ካለመጠለያ ያስቀረው ይመስለኛል። " #የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት" የሚለው አካሄድ አምክንዮው ብዙ የሚያስኬድ አይመስለኝም።
ምክንያቱም ኢትዮጵያ መንግሥት አልባ አገር አይደለችም፤ ህዝቧም በመንግሥት የሚተዳደር ስለመሆኑ ሩቅ ሳይኬድ የሰሞናቱ የምርጫ ሂደት ይመሰክራል። #የአፍሪካ አንድነት፤ ፬ኛዋ የዓለም የዲፕሎማሲ ርዕሰ መዲና መሆኗም ይታወቃል።
#በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የማደምጣቸው ጉዳዮች አለኝ።
የብልጽግና መንግሥት ሺ ዓመት ግዛኝ ያለን ቅን፤ ገር፤ ፍጹም ታማኝ ህዝብ የስትራቴጂ አገር ማድረግ ቀርቶ የታክቲክ ወዳጅ ለማድረግ ፈቃደኛ አልነበረም። "ከጎዳና ወደ ፓርላማ" ያለውን ቃሉን እንኳን አልጠበቀም። መቻልን ሳያስችል እንደ ቀረ እኔ ታዝቤያለሁኝ። በፓርላማ ውስጥ አንዱ ልጅ ሌላው የእዳሪ፤ አንዱ ሲቀረብ ሌላው ፊት ሲዞርበት አይቻለሁ። ይህ የተገባ አልነበረም። የኦሮሞ ፖለቲከኞች ለአማራ ህዝብ ከፍለው የማይጨርሱት ውለታ ነበረባቸው። ግን የአማራ ህዝብ እጁ አመድ አፋሽ ነው ሆኖ ያዬሁት።
ጭንቅ ላይ፤ ትንፋሽ ሲያጥር ዓራት ዓይናማው የአማራ ልጅ ከች ይልና እጅን ይዞ ከረግረግ ያወጣል። አንድ የማከብረው ቲክቶከር ጋዜጠኛ አለ። ጋዜጠኛ ቴዲ አዋሳ የሚባል፤ ተቆርጣ በወጣችው ንግግሩ "አይደለም ለጠቃሚ ሁነት በስብሰባ ዙሪያ ድምቅ የሚለው" የአማራ ልጆች ሲገኙ ነው የሚል ዕድምታውን አዳምጫለሁኝ።
በዚህ አጋጣሚ ለዚህ ቅን ዕይታው ምስጋና ላቀርብለት እፈልጋለሁኝ። እሱ አደባባይ ላይ ያለውን ገሃዱን የብቃት ልክ ነው። ኧረ ስንት አንጀት አርስ ጥቃት አውጪ ግን አንገተ ደፋታ ትጉኃን የአማራ ልጆች አሉ። የተናገረው ዕውነት ነው።
እራሱ ለሥልጣኑ የአማራ ልጆች ይሁንታ ባይሰጡ #ኦህዴድ ለዚህ ድል በፍጹም 100% አይችልም ነበር። ኦህዴድ ከአማራ ህዝብ ያገኜውን ፍጹም ታማኝነት ከምንም አልቆጠረውም። በንጽህናም አላስተናገደውም።
ኦህዴድን፤ ኦዴፓን የተካው ብልጽግና እና ህወሃት ጦርነት በከፈቱበት ጊዜም የአማራ ንጥረ መንፈስ በገፍ በቅንነት በግንባር ተማግዶ #የመሰንበቻ መተንፈሻ ትንፋሽ ለግሶታል። ብልፄው ይህንንም ከቁብ አልቆጠረውም። የሰሞኑ ከምርጫ ጋር ተያይዞ የድጋፋም ሰልፍ ይሁን፤ ህግ የማክበር ዕውነት የአማራ ህዝብ ቅንነት ወደፊትም #ሊከዳ ይችላል። እንደ ተለመደው።
የብልጽግና መንግሥት የአማራ ህዝብን በገፍ የሰጠውን ቅንነት በቅጡ ሊያስተዳድረው አልቻለም። ጸጸት አይቸም አላውቅም - ዛሬም። ሥሙን ለማንሳት ይቸግረዋል " አማራ ለማለት "። ብልፄው የአማራን ህዝብ የማቅረብ፤ ጥያቄወቹን አክብሮ ለመመለስ ፈቃደኛ አይደለም። ብልህነት ለፖለቲካ ስኬት ጎዳናው ነው። ካልታወቀበት ግን ህልም ብቻውን ለግብ አይደርስም።
ከወቀሳ፤ ከነቀሳ በፊት እራስን ማረም ይገባል። በምን ታምር በምን ሁነት የአማራ መንፈስ ከብልጽግና እጅ ወጥቶ #ጥምዶ ጋር ተገኜ? ብሎ ማሰብ ይገባል። ወርቅ ከቀለጠ ይፈሳል።
የአማራ ፖለቲከኞች ከአንዱ መከራ ወደ ሌላ ችግር የሄዱበት ምክንያት መንፈሳቸው ጥግ እንዲያገኝ ሽተው እንጂ እናት አገራቸውን ኢትዮጵያ #ክደው አይደለም። ስለሆነም " ካህዲ ባንዳ" የሚለው ዘለፋ አይጠቅምም። አያቀራርብም።
በዚህ አግባብ ቅጥልጥል ዘለፋወችን ማስታገስ "ምን ልካስ?" ያሉት የጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አመራር መልክ ሊያስዘው ይገባል። በዚህ በአማራ ጉዳይ ላይ ልዩ ጥሞና ያስፈልጋቸዋል ካቢኒያቸው። የማቅረብ አቅማቸው ሁልጊዜ ስስ ሆኖ ነው እምመለከተው። ለዛውም ብሄራዊ ፓርቲ መሠረትኩ ብለው።
#የአማራ ህዝብ ለብልጽግና ምኑ ነው?
ጣውንቱ ወይንስ የቅርቡ? የቅርቡ እንዲሆን ተጨባጭ ንቅናቄ፤ የድርጊት ሂደት ይጠይቃል። በሰፊ ልቦና፤ ከፍ ባለ ማስተዋል ጉዳዩ ተገቢው ዕውቅና ተሰጥቶት ድርጊትን መጀመር ያስፈልጋል። ብልጽግና የአማራ ውስጥነት ስለምን አመለጠው ቢባል በራሱ የፈጠረው ችግር ነው። ይንቃል። ያቃልላል። ያጣጥላል። ምን ያመጣሉ ይላል - ብልፄው።
አቅም በተለይ መንፈሳዊ አቅም ውስጥን ሲሰጥ አክብሮ፤ ተንከባክቦ ለእኔ ይቅርብኝም ተብሎ ለረዳ፤ ላገዘ፤ በቅንነት እንኳን ደህና መጣህ ላለ አስተዋይ ጭምት፤ ምራቁን ለዋጠ ህዝብ አክብሮቱ ቢቀር ጥያቄውን ማድመጥ ማንን ገደለ? አሁንም ጊዜ አለ። ጊዜ ግን ትህትናን በቅንነት፤ አክብሮትን በማስተዋል ብልህነት ይጠይቃል። ፖለቲካው ለሰው ከሆነ።
#ነገረ ጥምዶ።
የህወሃት ዝማሬን ስሰማ ልጅነቴ ታወሰኝ። እረግረጉም ታዬኝ። በእኔ በኩል ጥምዶ ስብሰባውን ሳይ የአማራ ማህበረሰብ #የተገለለበት #ተጫኝ ሂደት ነው ያስተዋልኩት። አማርኛ ቋንቋ እራሱ #ሽሽት ላይ ነበር። የስብስቡ ፈቃድም ተጠይቆበታል። የአማራ ህዝብ የውክልናው አቅምም ለአማራ ህዝብ አንጀት አርስ ሆኖ አላገኜሁትም።
ብዙ በጣም ብዙ ዋጋ በቅብብሎሽ የተከፈለበት ነው የአማራ ተጋድሎ። ዛሬም ደከመኝ፤ ሰለቸኝ ሳይሉ በላይም በታችም እንደ ሙጌራ ዳቦ እየተንገበገቡ የሚተጉ የአማራ ፖለቲከኛ ታጋዮችን አያለሁኝ።
ያ ሁሉ ልፋት የቀደመው፤ ያ ሁሉ ድካም እንዲህ #ተጠማኝ ሆኖ በባዕድ የሱዳን መሬት ማየት #ያማል። ያ አይበገሬ ተጋድሎ ለማሟያነት በተጠማኝነት??? ያቆስላል። የአማራ ታጋይ ከማን አንሶ? ከየትኛው ሰብዕና ኮስሶ ታያቸው ይሆን? ነገም ዕድሉ ቢገኝ የአማራ ሊቃናት የተለመደው የበቀል ካቴና ይጠብቃቸዋል። "አካሄዱን አይቶ ሸክሙን ይቀሙታል" ቅኔኛው ጎንደሬ።
በአማራ ህዝብ ጉዳይ የሚተጉ በውጭም በአገር ውስጥም ያሉ ወገኖቼ ምን ችረው? ምንስ ሊያተርፋ? በተለይ በጥልቀት ቢያስቡበት ዱር ቤቴ ያሉት የትጥቅ ታጋዮች ጥሩ ነው። ዛሬም ይሁን ነገ በህይወት መስዋዕትነቱ በአንድም በሌላም መኖሩንንም አውቀው ጥንቃቄ ቢያደርጉ ጥሩ ነው። የሊቃናቱ ቀጣይ ህይወትም ይታሰብበት እንደማለት። ጥንቃቄ ያተርፋል እንጂ አያከስርም።
ጥምዶ ለህወሃት አንፃራዊ ትርፍ ሊያስገኝለት ይችል ይሆናል፤ ለአማራ ህዝብ ግን አዲስ ሰንሰለት ነው። ለዛውም ረግረግ ውስጥ የሰመጠ። እራሱ ለአማራ ፖለቲካም ፋክት አልቦሽ አድራጊ ነው። በጥሞና በድጋሚ ደጋግሞ ማሰብ ይገባል። ብዙ አቅም እና አቅል ከመፍሰሱም በፊት፤ "በሞኝ ክንድ ዘንዶ ይለካበታል" ሆኖም ሰማዕትነትም የአካል ጉዳትነት ከመምጣቱ በፊት። ጉዳት ጭንቀት አልባ የጦርነት ሂደት የለምና። የአማራ ህዝብ አቅሙም የህሊና ጥሪቱ ይፈለጋል፤ አንጋችነቱ ይመኙታል፤ ሥልጣን ግን ሙጣጩም አይቻልም።
የተቆረጠ ቃለ ምልልስ አዳመጥኩኝ። አቶ ኤፍሬም ማዲቦ ያነሱት አንኳር ነጥብ ነበር ስለ ነገ ፍንጭ ይሰጣል። የኢትዮጵያ መንበረ - ሥልጣን በሚመለከት "ፕሮፌሰር ዶር ብርሃኑ ብቻ ሳይሆን እኔም አንተም እምናምንበት ነው" አሉ። ጠያቂውን ጋዜጠኛ መሳይ መኮነን መሆኑ ነው "አንተም" ሲሉ ሰምቻለሁኝ። ጋዜጠኛ መሳይ ስለ ፕሮፌሰር ዶር ብርሃኑ ነጋ ስሜን ነክ ጉዳይ አንስቶ ሲጠይቅ ነው በግልጽነት ዕምነታቸውን የገለጹት። ነገረ አማራ ጉዳዮቹን፤ መሻቶቹን ሁሉ በጥንቃቄ ማዬት ይኖርበታል።
#እርገት ይሁን።
ሌላው እጅግ አሳሳቢው ጉዳይ በነገረ ጥምዶ፤ በቀጣይ ደግፋን፤ እርዱን የሚሉ የአማራ የሎቢ ነፃ ሠራተኞች በምን መሰረታዊ የትግል አስኳል ይሆን መበደላቸውን መግለጽ፤ ማሳመን የሚችሉት ከህወሃት ጋር አብሮ መሥራቱ - ከተፈቀደ። በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲህ ይፋ ከሆነ። የእስከ ዛሬው ዕለት ድረስ የሚከፈለው ሰማዕትነትስ ማን ይካሰው???
በጥንቃቄ ቢታይ፤ የአማራ ሊቃናት ያላቸውን ልዩነት ማስታመም ትተው ቁጭ ብለው ሊመክሩበት የሚገባ ጉዳይ ይመስለኛል። ትዕዛዝ አይደለም። ትሁታዊ አስተያዬት ነው። ውጥኑ ያላማረ ነገር ፍፃሜውም የፈለገ ቢጠጋገን ስኬቱ ይርቃል።
*** ጥምዶ የአማርኛ ሥሙ ነው። ገድፌ አይደለም።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
09/06/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ