#ተናፍቃችኋል። አቶ ኦባንግ ሜቶ የሰባዊ መብት ዓራት ዓይናማ ሞጋች። ዶር ኮንቴ ሙሳ ጭምት ፖለቲከኛ። ጋዜጠኛ ተመስገን ደስአለኝ ትጉህ ሞጋች ሃያሲ ጸሐፊ። ፖለቲከኛ አቶ ክንፋ አሰፋ አምደኛም።
"ሥጋን እንጂ ነፍስን መግደል የማይችሉትን አትፍሯቸው።" (ማቴ ፲፡፳)
#ምዕራፍ ፲፱።
#እፍታ።
መፈላለግ፤ መጠያዬቅ፤ መተሳሰብ ትውፊታችን ነው። ትውፊታችን ማስቀጠል ደግሞ ግዴታችን ነው። ለረጅም ጊዜ አቶ ኦባን ሜቶን አስመልክቶ ፌስቡኩኑም፤ ኤክስ አካውንቱንም ፈታትሼ የት ነህ የሚል ጥያቄ ሳቀርብ ነበር። ድምጹ ከለት ወደ ዕለት እዬራቀ ሲሄድም እንደ አንዲት ኢትዮጵያዊት እህት ሲጨንቀኝ ጭንቀቴን ተጋሩ ብዬ በፔጄ ላይ ስጽፍ ቆይቻለሁኝ።
አሁን ከምርጫ በኋላ በአንድም በሌላም ላያቸው እችል ይሆን ብዬ አስቤ ነበር። ግን አላየኋቸውም። ስለሆነም በጸረ ህወሃት ትግል ትጉህ የነበሩ ወገኖቼን በጥልቀት አሰብኳቸው። #ቆጥረን ባንሰጥም።
1) አቶ ኦባንግ ሜቶ የሰባዊ መብት ዓራት ዓይናማ ሞጋች።
2) ዶር ኮንቴ ሙሳ ጭምት ፖለቲከኛ።
3) ጋዜጠኛ ተመስገን ደስአለኝ ትጉህ ሞጋች ሃያሲ ጸሐፊ።
4) ፖለቲከኛ አቶ ክንፋ አሰፋ አምደኛም።
አቤቱ አጤ "መደመር፤ የመደመር ትውልድ፤ የመደመር መንግሥት።" እነኝህን ሊቀ - ትጉኃን የአገር ልጆችን #ቀነሰ ወይንስ አከለ? አፋፋ ላይ አስቀመጠ ወይንስ አገተ? አጠነከረ ወይንስ #አቀበ? አሰበለ ወይንስ አጠወለገ? የሚለውን አደባባይ ላይ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድን ልንጠይቃቸው፤ ልንሞግታቸው ይገባል ባይ ነኝ።
ጠቅላይ ሚኒስተሩም እንደ ቀደምት መሪወች "ላም እረኛ ምን አለ?" ብለው ጆሯቸውን ዘንበል አድርገው ሊያደምጡን፤ መልስም ሊሰጡን ይገባል ብዬ አስባለሁኝ። ከውጥኑ እስከ ዛሬ ድረስ ስለሳቸው አቅማችን፤ ጊዜያችን አፍስሰናል። ሙግቱ የሁሉም ኢትዮጵያን በፍቅር በተፈጥሮኛ ከመናፈቅ የተነሳ ነው። ሂሳችን ቢጠቅም እንጂ አይጎዳም። ዝምታችንም ቢጠቅም እንጂ አይጎዳም። እንዳላዬን የምናልፋቸው ጉዳዮችን ሁሉ ቸል ሊባሉ አይገባም።
በመራራቅ፤ "ባለመናገር ደጅ አዝማችነት ይቀራል" ይላሉ ባለ ቅኔ ጎንደሮቹ። እኔም በጎንደርኛ የአማርኛ ቋንቋ ዘዬ ውስጤ የሚለኝን ይፋነትን ፈቅጄ እንሆ እነኝህን፤ የእኔም የእርስወም ወንድሞቻችን የት አሉ ብለን እንጠያዬቅበት ዘንድ ፈቀድሁኝ?
በአሁኑ ጊዜ ጸጋቸው በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? ተደመሩ ወይንስ ተቀነሱ? የሚለውን በኽረ ጉዳይ ይመልሱልኝ ዘንድ አቤቱታዬን እንሆ በትህትና ማቅረብን ፈቀድሁኝ። በድምጽ ብሰራው በወደድኩኝ። ሁኔታው ከረባበሸኝ ላለቅስም ስለምችል እዚህው ብራና ላይ ውስጤ የሚሆነውን ይሁን ብዬ አሰብኩኝ።
1) ከእናት ልጀምር። ወይዘሮ ፋናዬ ደስአለኝ፤ ሁለት ወንድ ልጆች አሏት። አንዱ አርቲስት ነው። የፊልም ኢንደስትሪ ኢትዮጵያ ላይ #ቃሬዛ ላዬ ስለሚገኝ በምን ህይወቱን እንደሚመራ አላውቅም።
ሌላው የወ/ሮ ፋናዬ ደስአለኝ ልጅ ትንታጉ ጋዜጠኛ ተመስገን ደስአለኝ ነው። እናት ፋናዬ በተሜ ተሰቃይታለች። እናም ከመጨረሻው እስር በኋላ ለእናት ፋናዬ እረፍት ይሰጣት ዘንድ ተሜን እዚህው ፌስቡክ ላይ ተማጽኜው ነበር። #እንዲክሳትም። አግብቶ ፈቃዱ ከሆነም የልጅ ልጅ እንዲያሳያት ሰርጉን እጠብቅ ነበር።
የጋዜጠኛ ተመስገን ብዕር የኢትዮጵያ ብዕርና ብራና ካፒቴን መሆን የቻለ፤ ልዩ ጣዕም፤ ልዩ ለዛ፤ ልዩ ውበት፤ ልዩ ቃና፤ ጥልቅ የምርመራ ዘገባን እያዋዛ የሚሞግት #ታምረኛ ባለጸጋ ነበር። በኢትዮጵያ የብዕር ሙግት ውስጥ የተሜ ብዕርና ብራና ፍልቁ፤ ጌጣማ፤ ውብ፤ የማይሰለች ውበት በትጋት ያሳዬ ዓራት ዓይናማ ጋዜጠኛ እና ጸሐፊ ነው።
ተሜ የግንባር ስጋ፤ ፈተና የሚፈቅድ፤ ያልታዩ፤ ያልተዳሰሱ ቀን ያልሰጣቸውን የሃቅ እና የዕውነት ዕውነቶችን ለድል የሚያበቃ ሊቀ - ትጉኃን ብቁ ጸሐፊ ነው። ተሜ እና ብዕሩ፤ ተሜና የሃሳብ ጥራቱ፤ ተሜ እና ጭብጡ፤ ተሜ እና ብራናው ለሥነ - ጽሁፍ ውበት በፖለቲካው ዘርፍ የሃያሲ የውሃልክ ነው። ይጠማል። ይርባልም።
የተሜን ነገር እያሰብኩት የመጣሁት በ2018ዓም ለጥምቀት #ጎንደር ሳይሄድ ሲቀር ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ውስጤ ይሰጋል። ጎንደር ለመሄድ ታግዶ ወይንስ ፈቅዶ? ይህ ጥያቄ የሁላችንም ሊሆን ይገባል። ተሜ የዚህ ዘመን ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ትውልድም አብነት ነውና። አንከሩ ጸሐፊ ጋዜጠኛ ተመስገን ደስአለኝ የት ይሆን ያለው? በምን ሁኔታስ ይሆን የሚገኘው??? ኃይል እዮራዊ ጸጋው ምን እክል ገጠመው? አድናቂወቹ፤ ደጋፊወቹ፤ ተከታዮችስ ምን ይሉ ይሆን። ዝም። በቃ #ዝም????
2) አቶ ኦባንግ ሜቶ። የኢትዮጵያ ውድ ልጅ ከጋንቤላ። ኢትዮጵያዊነት በውስጡ ያደረ፤ የተዋህደ ጠይም ዕንቁ ነው ኦባንግሻ። ኦባንግሻ መለያችን ነው። ኦባንግሻ የወገኖቹ ችግር አለ በተባለ ቁጥር ፈጥኖ ደራሽ፤ መፍትሄ አፈላላጊ፤ ትጉህ ስለ ሰብዓዊ መብት የሚተጋ ውዳችን ነው።
እንደ እኔማ ቢሆን በተመድ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ባለሥልጣን አንባሳደር ለመሆን ይሁን ለኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚር ለመሆን ብቁ ወንድማችን ነው ብዬ አምናለሁኝ። ለፓን አፍሪካኒዝም ልዩ ስጦታ ሽልማትም። ከሁሉም ሰዋዊነትን፤ ተፈጥሯዊነትን ውስጡ ላደረገ አገር፤ መሪ፤ ካቢኔ፤ ፓርላማ የውሃልኩ አቶ ኦባንግ ሜቶ ነው። ድምጹን ካልሰማነው ዓመታት ተቆጥሯል።
ኦባንግሻ የመጀመሪያው "አብይ ጠቅላይ ሚኒስተሬ ነው" ብሎ ያወጀ #ቅን ሰው ነው። እሱ ይህን ሲል በዲፕሎማሲው ማህበረሰብ ዘንድ የበለጠ ጠቅላይ ሚ/ር አብይ ዕውቅና እንዲያገኙ ካደረጋቸው አንዱ ዘርፍ ይህ ነበር።
ታላላቅ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች በፍቅር ለጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ያደረጉት አቀባበል ለወሳኝ ጊዜ ወሳኝ እርምጃ ነበር። ያን ጊዜ ማንም የማያውቃቸውን ዶር አብይን ምንም ሳይሰሩ የኖቤል ተሸላሚ፤ የተለያዬ እርዳታም፤ ሙገሳም፤ ዕውቅናም እንዲጎርፍላቸው ሆኗል። "አንገት የተሰራው አዙሮ ለማዬት" ነበር። ይህ ለመደመር መንግሥት ይሥራ አይሥራ ባላውቅም። ለነገሩ የማህበረ ኦነግ ፖለቲካ እኮ ይሉኝታ የሚባል ብቅ ብሎበት አያውቅም። እንደምን ይህ ሥልጣን እንደተገኜ ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው። የእነሱ መስቃ ደግሞ ሰማይን ይቀዳል።
የሚገርማችሁ በ100 ቀናት ውስጥ ትልልፍ አይ ስለነበር ለኦባንግሻ ደውዬ ትጥቁን እንዳይፈታ በ2010 ነሃሴ ወር አሳሰብኩት። ስልክ መደወልም፤ ማንሳትም አልውደም። ግን ነገረ ሰባዊነት ባለቤት እንዳያጣ ነበር ስጋቴ። ግን ኦባንግሻ በሁለት ሳምንት ልዩነት ኢትዮጵያ የክብር አቀባበል ሲደረግለት አየሁኝ።
አገር አትግባ አልነበረም ዕይታዬ ሂደቱን #አጥናው ነበር ጥያቄዬ። የኢንጂነር ስመኜው በቀለ የአሟሟት ሂደቱ አልገባኝም ነበር። ምን አለ? ከውስጡስ ማን አለ? የሚል ጥያቄ ነበረኝ። ነገረ ህወሃትም ቀላል ፈተና አልነበረም። ኦነግም እንዲሁ። ገና ያልረጋ ሁኔታ ስለነበር ሁኔታውን አደብን አብዝቶ ማጥናት ይጠይቅ ነበር። #ተግ ብሎ ማድመጥን።
የሆነ ሆኖ አቶ ኦባንግ ሜቶ ኢትዮጵያ ገብቶ የህዝቡ አቀባበል፤ የመንግሥት አቀባበል ልዩ ነበር። ያ ያበሳጨው፤ ያ ያስቀናው ሰብዕና ክብሪት ቢጤ ለኳኮሰ፤ ያን ጊዜ ወጥቼ ፃፍኩኝ። #እንተዛዘን፤ እንተሳሰብ ብዬ።
ህወሃትን ያህል ሞገደኛ ድርጅት ፊት ለፊት አስቀምጦ አቅም መሰብሰብ ሲገባ መበተን በፍጹም ለወቅቱ የተገባ አልነበረም። ያ ፍንጭ ለኦባንግሻ አደጋ ሊፈጥር እንደሚችል አሳሰበኝ። የሰው ልጅ ከራሱ በላይ ማንን ሊወድ ይጠበቃል? ይህ ፋክት ነው። የሆነ ሆኖ ኦባንግሻ ጠፋብኝ? የት ነው ያለው? በምን ሁኔታ ላይ ነው ያለው????
3) ዶር ኮንቴ ሙሳ። ኢትዮጵያዊ ሊቅ ከአፋር። ዶክተር ኮንቴ ሙሳን መጀመሪያ ያዬኋቸው ግንቦት 7 "አገራዊ ንቅናቄ" የሚል ተቋም ባደራጄ ጊዜ ነበር። ከቲሙ ውስጥ እርጋታቸው በጣም ነበር የመሰጠኝ። ከዛ በኋላ የሚሰጡትን መግለጫ እከታተል ነበር። በኋላ ላይ ኢሳትም ላይ ተሳትፎ እንደ ነበራቸው አዳምጥ ነበር። አሁን ከአገር ውጭ ይሁን አገር ቤት ያሉበትን አላውቅም።
መረጃው ያላችሁ ሹክ በሉኝ። እኔ ደህንነታቸው ብቻ ነው የሚያስፈልገኝ። ከዛ ያለፈ ወይንም የተረፈ መሻት የለኝም። በአካልም በስልክም አላውቃቸውም።
በአሁኑ ወቅት ዶር ኮንቴ ሙሳ አገር ቤት ኢትዮጵያ ወይንስ ውጭ የት ነው ያሉት? ዶክተር ኮንቴ ሙሳ ከዶር ለማ መገርሳ ጋር ይመሳሰሉብኛል። ሁለቱም #ጭምትነቱን አብዝቶ የሰጣቸው ናቸው። አንድ ቢሮ ቢሰሩም የሚዘልቁ ይመስለኛል።
የተለያዬ የፖለቲካ አቋም ቢኖራቸውም። ጭምቶች መቻቻልን በድርጊት ስለሚሸልሙ። በዚህ አጋጣሚ ጭምቱ ፖለቲከኛ ዶር ለማ መገርሳን በአደባቸው ጥልቀት ምስጥ እንደምል ላስታውሳቸው እወዳለሁኝ። አመሰግናቸዋለሁም። የትውልድን መንፈስ አለማብከንከን ትልቅ እርዳታ ነው።
4) በሙያ ፖለቲከኛ ነው። የተማረ። ከዶር ወርቅነህ ገበዬሁ ጋር አብረው በትምህርት ቆይታ እንደነበራቸው፤ በዘመነ ህወሃትም ተጠይቆ ፈቃደኛ ያልሆነው፤ የመምህሩ የፕሮፌሰር ዶር መራራ ጉዲና ልዩ አክባሪ አቶ #ክንፋ አሰፋ የት ነው ያለው???
አቶ ወንድም ክንፋሻ ይጽፋል፤ ይሞግታል፤ ስብሰባ ያዘጋጃል በጸረ - ህወሃት ትግል ከአዕምሮ ጋዜጠኞች ቲም ቀጥሎ በሆላንድ ትግሉን ያስቀጠለው አቶ ክንፋ አሰፋ ነበር። አቶ ክንፋ አሰፋ ቀስ ያለ፤ ድምጹም ለስለስ ያለ፤ ኢትዮጵያን ውስጡ ያደረገ ትጉህ፤ ታታሪ ወጣት ፖለቲከኛ ነው።
ክንፋሻ ለአሜሪካ የእግር ኳስ ውድድር፤ ለአውሮፓውም መሪ ካፒቴን የነበረ ታታሪ ፖለቲከኛ ነው። ለታሰሩ ወገኖች የሚጮህ፤ ለጋዜጠኞች ጥግ፤ ጠበቃ የሚሆን ሰውኛነትን የተላበሰ ጨዋ ፖለቲከኛ ነው።
በአካል አላውቀውም። በዘሃበሻ እና በሳተናው ጋዜጣ ቋሚ አምደኛ ነበር እንደ እኔው። ተግቷል። ታግሏል። ይህ ኦህዲድ ያገኜው ድል በብዙ ተደክሞበታል። ድካሙ ስለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ነበር።
በ2013 ዓም የ፮ኛው አገራዊ ምርጫ ከልጅ መስፍን አማን ጋር፤ ልጅ ክንፋ አሰፋ ሆላንድ ላይ ሁነው የዘሃበሻ ጊዚያዊ ስትዲዮ ፈጥረው በአገር ጉዳይ ሲወያዩ "ማን #እንዲያሸንፍ ትፈልጋለህ?" ለሚለው ጥያቄ ሁለቱም ልጅ መስፍን አማን፤ እና ልጅ ክንፋ አሰፋ #ብልጽግና እንዲያሸንፍ እፈልጋለሁ ሲባባሉ በጆሮዬ አዳምጫለሁኝ። የሁለቱም ምኞት ብልጽግና እንዲያሸንፍ ነበር።
የሚገርመው ልጅ መስፍን አማን የባልደራስ የአውሮፓ ተጠሪ፤ የባልደራስ የሊቃውንት የምክር አገልግሎትም እየሰራ በምርጫው አሸናፊ እንዲሆን የተመኜው ግን #ብልጽግናን ነበር። ልጅ መስፍን አማን ፖለቲካን በተለምዶ፤ የእግረ መንገድ ተግባሩ ሳይሆን በፖለቲካ ሳይንስ ሊቅ ነው የተማረም ነው።
ሌላ ጊዜ ደግሞ ልጅ ክንፋ አሰፋ እስር ላይ ከሚገኜው ከጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ጋር በነበረው ቆይታ "ጠቅላይ ሚር አብይን አምናቸዋለሁኝ" በሚል ሙግት ገጥሞት ነበር። ብልጽግና እንዲያሸንፍ የተመኜው፤ ጠቅላይ ሚር አብይን ሰብዕና ሩህሩህ አድርጎ የተቀበለ ንጹህ ልቦና፤ ንጹህ ህሊና፤ ገራገር ሰብዕና የት ነው ያለው? በነገራችን ላይ ጋዜጠኛ ተመስገን ደስአለኝ እና ፖለቲከኛ አቶ ክንፋ አሰፋ ወንድማማች ነው የሚመስሉት። ተሜን አውሮፓ ጋብዞት ነበር።
የክንፋሻ ውስጥ የሰውኛ አቅሙ፤ የማህበራዊነት ደረጃው ይለይብኛል። ከኦባንግሻ በስተቀር በስልክም፤ በአካልም አላውቃቸውም። ድርጊታቸውን ብቻ ነበር እምከታተለው። በውነት ጎድሎብናል። #አጉድለውብናልም ለሰላማዊ አመክንዮዊ ተጋድሎ። የህዝብን መከፋት በልኩ #ሳያንቦጀቡጁ በትክክለኛው የመቆርቆር አቅም ተናፋቂ ሰብዕና አላቸው። ያው መሪ አጀንዳቸው ኢትዮጵያ ናት።
ጠቅላይ ሚር አብይን ለመደገፍ ከሚኖሩበት የስደት አገር ወደ አገር ገብተው ያሳዩት የመታመን አቅም ትምህርት፤ ሞገስ ሊሆን ሲገባ እንዲህ ተያይዘው ጥፍት ሲሉ እንደ አገር ልጅነት ጭንቅ ይላል። ሁሉም እናት አለው። የእናቶች ጉዳይ ደግሞ ውስጤ ነው። ዘመኔን ሁሉ በቅንነት የመገብኩት ጎዳናዬም ነው።
በመጨረሻ የአቶ ክንፋ አሰፋ ጉዳይ እያሳሰበኝ የመጣው "#ከእዮሪካ" በኋላ ነው። ለቴዲ አፍሮ ክንፋሻ ትንፋሹ ነው። በፈተናወቹ ሁሉ ፊት ለፊት ወጥቶ በብዕሩ የሚማገትለት። የሚቆሰቆስለት ሁነኛ #ዋቢው ነው። በአሁኑ "የእዮሪካ" አልበም የክንፋሻ ድምጽ መጥፋት ጭንቀቴን ጨምሮታል።
ከዚህ ላይ ላስታውሳችሁ የምሻው ዶር ወርቅነህ ገበዬሁ በዘመነ ህውሃት እስከ ውጭ ጉዳይ ሚር የደረሱ ናቸው። አሁንም የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ናቸው። ቁልፍ ሰው ናቸው ለቀንዱ አገሮች።
ለቀጣይ የኢትዮጵያ መሪነትም ያጯቸው እንዳሉም ጭምጭምታ ነበር። አብሮ የተማረው አቶ ክንፋ አሰፋ ግን ሁሉም ቀርቶ፤ ሹመቱም ሆነ ሽልማቱም ሳያስፈልግ፤ ደህና ቢሆን፥ ተጣድፎ የሄደውም #ስለእናቱ ነበርና የእናቱን #ሳቅ ማስቀጠል ይገባል። የኢትዮጵያ መንግሥት ስለእናት የእኔ ኃላፊነት ነው ሊል ይገባል። በተለይ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ።
የሚገርማችሁ ከህወሃት የጥበብ አቅም ማቀብ፤ ልቅና እገዳ በኋላ ቴዲ አፍሮ አደባባይ ላይ ባቀረበው ኮንሰርት ከሆላንድ ተነስቶ፤ ኢትዮጵያ ሄዶ ታድሞበታል። ቃልኪዳነኛ ነው። ሰውን እምትለኩት ለእናንተ ስላደረገ ሳይሆን፤ ለወገኖቹ በችግርም በሐሤትም ጊዜ ሲገኝ፤ ደራሽ ሲሆን ነው።
ታሪክም፤ የጤነኛ ትውልድ ቀረፃም መስተካከል የሚችለው እንዲህ ኃላፊነትን እና ተጠያቂነትን በቅጡ አዋህደው ድርጊት ላይ የሚያውሉ ጀግኖች ሲኖሩ ነው። እና እናማ አብይዝምን ምን እንበለው? የመደመር መንግሥት ወይንስ -----? ዳሹን እናንተው በይኑበት።
1) ታታሪው ሰውኛው አቶ ኦባንግ ሜቶ የት ነው ያለው?
2) ተፈጥሮኛው ፖለቲከኛ ዶር ኮንቴ ሙሳ የት ናቸው?
3) ትንታጉ ብዕረኛ ጋዜጠኛ ተመስገን ደስአለኝ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?
5) ስኩን ፖለቲከኛ አቶ ክንፋ አሰፋስ ምን ሆነ?
እኔ የሁሎችም የማህበራዊ ሚዲያ ተከታይ፤ ጓደኛም አይደለሁም። የአገር ልጅነት ነው #ክሩ።
በጤናም ከሆነ፤ ዕገታም ካለ፤ #የቁም እስርም ከኖረ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ብይን ሊሰጡበት ይገባል ብዬ አምናለሁ። ለነገሩ ኮነሬል ጎሹ ወልዴም አገር ከገቡ በኋላ ድምፃቸው የለም። አንባሳደር ካሳ ከበደም ከብዙ ዝምታ በኋላ በሥጋ መለየታቸውን አዳምጫለሁኝ። ፈጣሪ አምላክ ነፍሳቸውን በገነት ያኑር አሜን።
ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ትልቁ ብልህነት የአቅምን ማሰባሰብ ሲቻል ይመስለኛል። ሁሉም የአቅሙን ያህል ያወጣ ዘንድ ነፃነቱን መስጠት ይገባል። የትውልድ ቅብብሎሽ ጥርጣሬ፤ ስጋት፤ ፍርሃት ባይሆን ምርጫዬ ነው። የሁሉም መክሊት ኢትዮጵን ይጠቅማል። ኢትዮጵያ እንድትቀጥልም ደግሞ ሆደ ሰፊነት በቅንነት ይጠይቃል።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ.
Sergure©Selassie.
11/06/926.
ጊዜ ራዲዮ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ