ቋንቋ ማወቅ ሊቀ ሊቃውንትንት እንጂ መወቀሻ ሊሆን አይጋባም።

       ቋንቋ ጥበብ ነው ለእኔ፤
 እንጂ መወቀሻም፤ መነቀሻም 
ሊሆን ከቶውንም አይገባም።
ከሥርጉተ ሥላሴ (Sergute©Sselassie)
06.05.2018 (ከገዳማዊቷ ሲዊዘርላንድ።)

„አንተን ማወቅ ፍጹም ክብር ናት፣ እንተንም ማወቅ የነፍስ ህይወት ናትና“ 
(መጽሐፈ ጥብብ ምእራፍ ፲፩ ቁጥር ፫)

የኢትዮጵያ ጽናት!

  • ·         ጠብታ በብዕር ገባታ።

ጤና ይስጥልኝ ውዶቼ እንዴት ሰነበታችሁልኝ? ደህና ናችሁ ወይ? እንሆ አንዱንም በቅጡ ሳንጥግበውም ሳንፈታትሸውም፤ የተግባር ሰብሉ በምርት ላይ ምርት ሆነ እና ትንሽ ዘነጥ፤ ትንሽም ቀበጥ በማለት ስንጥር ስንለቃቅም ውለን እናድራለን። ቅንነትን ለፈቀደ ሰብእና የፈጣሪን ህግ መተላለፍ ስለሆነ ቅኖች „የቤትህ ቅናት በላኝን“ የልብ አምላክ ዳዊትን ትጥቅ ለህሊናቸው ቢፈቅዱለት የተገባ ነው እላለሁ በትሁት መንፈስ አክብሮትም ልከል። መልካሙ መንፈስ አይደለም ጎልቶ እንዲወጣ የሚፈለገው፤ መልካሙን የሚጫን ሰባራ ሰንጣራ በደቦ በማከማቸት እንጂ። ውስጣችን ቢታይ ምን ያህል ተስፋ ቆራጭነት ሲንጠን እንደ ነበር ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው። እግዚአብሄር ይመስገን መሬት ላይ ያለው ህዝባችንም ያን መሰል ጭንቀት ላይ እንደ ነበረበት ሳይፈራና ሳይቸር እዬተናገረው ነው። 

እስከ ትንሳኤው ዜናው የምሥራችም ሲጠብቅ እንደ አመሸም አዳምጠናል። ባለቅኔዎም የኢትዮጵያዊ ሰው/ ባለቅኒያዊት ኢትዮጵያዊት አንስት በማለፊያ አንደበት ግማዱን ዘመን እዬተቃኙበት ነው። የ27  ዓመቱ ዕምቅ ፈተና ባለቅኔዎቹ እያፈነዱት ነው። ድምፃቸውን መስማት ዓይናቸውን ማዬት መቻላችን ለእኔ ልዩ ትርጉም አለው። አዋሳ ላይ አንድ ቀደምት ፖለቲከኛ የዘሬ የቡና ነጋዴ ተስፋቸው ሳይታሰሩ ቤት በሰላም መግባታቸው ስለመሆኑ ገለጡት። እሥር እስከ መቼ? ይህ በቅጡ ካልተያዘ መጪው ዳፍንታም ሲታለም የሁለት ወይንም የሦስት ገላጋይ ሐገሮች የቁንጫን መወጣጫ ብንሆን ተብሎ ሲታሰብ ደግሞ መልሰን ሁዳዴን በተመስገን ዳግማዊነት እንድንዘክር ግድ ይላል። ሶርያን ያዬ። የቀደመውን ርውንዳን ያደመጠ ይህ የምህረት ቀን ብሄራዊ ቀን የሚያስወስን ነው። ለሌላስ ድፍን ብንዳረገስ ተብሎ ሲታሰብ ክፋቱ ይገዝፋል።

 አሉታዊ ሆነ ግራጫማዊ መንፈስ ካልታከተው ይሄም ሙሉ መብት ነውና በባለመብቱ ልክ ይወሰናል። ፈቃጅም ነሽም የለም ….ችግር የሚመጣው አንቺ መብት የለሽም አትናገሪም ስባል ብቻ ነው … እኔም የተፈጠርኩበት የሰውነት ሙሉዑ ሰብዕና በአማላኬ በአማኑኤል ተስጥቶኛል እና። ውስጤን እንድገልጽበትም አባቴ ጸጋውን አልነሳኝም። ስለዚህ በምድር ስኖር የተሰጠኝን ጸጋ ሳልጫነው መኖሩን እንዳኖረው እንድፈቅድለት ግድ ይላል። ይህንስ ማን አይቶበት ባይም ነኝ። ቅን መሆን መልካምነትን ይመግባል።
  • ·         ትክ የለሽ ከግማሽ መንገድ … 

ወዳዚህ ዋናው አወያይ ጭብጤ ከመግባቴ በፊት ግን እኒያ እጅግ የምሳሳላቸው ብዕረኛ ወይንም ከታቢ ጦማሪ አቶ ስዩም ተሾመ ጭንቀታቸው ሰው ሰራሽ ክንፍ ላይ ስለመሆኑ ግርም አለኝ። ፈረሰኛ እኮ ለአማች ብቻ ነው። ቅልጥምም እንዲሁ። እንዴት ሞሳድን ያህል ዕድሜ ጠገብ፤ ጥልቀት ጠገብ፤ ሚስጢር ጠገብ፤ መሆን ጠገብ የጽዮናዊነት ሰማያዊ ባላ እና ወጋግራ በባለቤትነት፤ በርቀት ከሲአይኤ የጽድቅ ርቁቅ ጥበቃ ጋር ያን በስንት ጭስ፤ በስንት ነጎድጓድ፤ በስንት ወጀብ መሃል ከጅቦች መንጋ ጉድጓድ ውስጥ ቻለው ተብሎ የተወረወረ ባተሌ መንፈስ ለአንድ ደመነፍስ ንዴታም ቀልሃ ለመዳረግ ተመቻች ተብሎ የሰላ ወቀሳው እጅግ ወረደብኝ። „ትኬት ቆርጦ ሲሄድ እንይ¡“  ጊዜውም ሁኔታውም አይደለም። 

ያ የበረራ ፕሮግራም እኮ በኢትዮጵያ አዬር መንገድ የበረራ ሰሌዳ እንጂ የጠ/ ሚር ቢሮ አይደለም የሚተዳደረው። አሁን እኮ ዘመቻ ላይ ነው ቢሮው። ነፍስ አቅሏን ስታ ተንጠልጥላ አፋፍ ላይ ነበረች። እንቅልፍ ተኝቶ የሚያድር ሰው እኮ እንብዛም ነበር። ማን እንደሚጠልፈው፤ ማን እንደሚያሰምጠው እኮ ባለቤት የለውም። ማልዥያ አውሮፕላን፤ የጀርመን ዊንግ፤ የራሽያን ሰቆቃ ያዬ ለአንድ በብክነት ላይ ላለ ነፍስ መላሽ አረጋጊ አለማሰብ ምን ይባል? መዳንን አለማድመጥ።

እኔ እራሱ ጣሊያን ላይ ስብሰባ ቢዘጋጅ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች እንዲሄዱ አልፈቅድም። በፍጹም። ደቡብ አፍሪካም፤ እስራኤል ላይም በስካይፒ ነው መሆን ያለበት። አንድ የፖለቲካ ድርጅት መሪ የአንድ ጭልፋ አፈላሎ አይደለም። ወይንም የአንድ ፋጋ ወገሚት አይደለም። የፈለገ ብሄራዊ የተፎካካሪ ድርጅት መሪ ጥቃት እንዲፈጸምበት አልሻም። ጥቃቴ ነው። ስለሆነም ራሳቸውን መጠበቅ አለባቸው። ልሞግታቸው፤ ልተቻቸው፤ በሰላ ሂስ ልከትክታቸው እኔው አንጅ በጠላት እጅ እንዲወድቁ ወይንም ነፍሳቸውን እንዲያጡ እንዳጣቸው አልፈቅድም NO NO NO ! ለዚህም የእኔ ባልላቸው፤ ባላቀርባቸው አንድም ነገር አልጭርም ነበር። አሁን ሰለ ኡጋዴን ነፃ አውጪ ምን ብዬ አውቃለሁኝ። ምንም። ስለ ግራቀኝ ፈርስቶችም እንዲሁ።

የሆነ ሆኖ የጦማሪው የናፍቆት፤ ትዝታው ሲነስተኛ የከራረመው ያ ብዕር የኢትዮጵያ መከራ ቀርቶበት ሽልንግ ቆጠራ ገባ። ምን ልባለው ድንብልብል። ይቅርታ እኔ እዚህ ነኝ እርስዎ የማከብረዎት እና የምሳሳለዎት ጦማሪ አቶ ስዩም ተሾመ ረመጥ እየረገጡ ነው የሚኖሩት በበላህሰቦች ገዢ መሬት፤ ቢያንስ ከድብደባ እንዲወጡ መደረጉን ማክበር ያለበዎት መሆኑን መግለጽ ግዴታዬ ነው። በተፈጥሮ ጸጋዎት ላይ እንደ ጎንደሮች ተብዕታት ግዑፋን ቢያደርጎዎት እኮ ዓይነዎትን በዓይነዎት ለዘለቄታ ማዬት አይችሉም። ከተፈጥሮ ውጪ ይሆናሉ። ተተኪን አለማዬቱ ብቻ ሳይሆን የዕድሜ ልክ ስቃይ ነው። እዬፈለጉ አለመቻል። 


ተፈጥሮዊ ስሜት አይገደልም። አካል ቢገደልም ስሜቱ በተለመደው መልክ መቀጠሉ አይቀሬ ነው። ይፈትናል። ያሰፈታችሁ የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁን ማዠዣ ትእቢትን፤ አለስልሶ በግትርነት ሳይሆን በማግበባት የአዲሱ የጠ/ ሚር ቢሮ በልዩ ትእዛዝ ነው። እዛም ጥቃት እንዳይፈጸምባችሁ አታውቁትም እንጂ ተግቷለኝ መንፈሱ፤ ጥበቃ አድርጓል። ተጽዕኖም ፈጥሯልኝ። መቼም ተመስገን የለም።

የሆነ ሆኖ ትምክህትን በፈጣሪ መሆኑን ሥቼ የተፈጠርኩበትን ተልዕኮ ርክክብ ይፈጽማሉ ብዬ እማስባቸው ጦማሪ አቶ ስዩም ተሾመ የቁስ ጭንቅት ከዛ ከነበራቸው ጥልቅ የእኛዊነት መንፈስ አዱኛው ጋር አልመጠነልኝም። ያ ብቃት፤ ያ አርቆ የማስተዋል አቅም ምነው እስር ቤት ቀረን አሰኜኝ? ወይንም አዬሩ መርዘኛው ንድፍ ቢጤ አደረገን? የተመረዘ አዬር እኮ ነው ያለው። የጊንጥ ጅራት መንፈስ ነው ያለው። ይህን ቅዱስ መንፈስ የሚያስጠጋ ቀርቶ አላውቅህም ብሎ፤ በውስጡ ሸፍቶበት በራሱ ተግባር ላይ የሚተጋ ድርጁ መንፈስ ቢኖር ምንኛ በታደለች ኢትዮጵያ። ያንኑ ሲያነሳ ሲጥል ውሎ ያድራል። 

የሆነ ሆኖ  እኔ ሞትን አቅፌው ስለምተኛ ብሞት በፈለገው መስመር በምንስማማትም ሆነ በማንስማማትም መስመር ይተኩኛል የምላቸው ነበሩ ጦማሪ አቶ ስዩም ተሾመ። ደፋር እና የሰላ ትችት ማቅረብ ዘመድ የለሽ ነው የሚያደርገው። ያን የደፈረ ለዛውም ሲኦል ውስጥ ሆኖ የጀግኖች ቁንጮ ነው ለእኔ። ከዛ መከራ ቤት የቆዬ ጽድቁ ከመንፈሱ በርቅቅና አለና። አቦ ታዬ ደንዓ ለኢትዮጵያዊነት መንፈስ ለዶር አብይ አህመድ የሰጡት ዕውቅና ወድጀዋለሁኝ ሳላመሰግናቸው ማለፍ የለብኝም። ይኑርልን ብያለሁኝ። ስትታሰሩ በኸረ አጀንዳ ነበራችሁ አሁን ምን ያህል በኽረ አጀንደነታችሁ እንደ ቀጠለ እንደሆነ የሚያውቁት የሚመዝኑት ቅኖች ብቻ ናቸው። አቅም መባከን ያለበት ከሚሆን ቦታ ነው የምለውም ለዚህ ነው። መከራህን የተጋራ ደስታህንም ለመጋራት ተፈጥሯዊ መሆን ሲገባው ግን እኛ ዘንድ አይቻልም። የነፃነት ፍለገው የውሃ ልክ እስተዚህ ድረስ ነው … ጫናው እስሩ ግድያው ሲቀጥል ይመስለኛል አድባሩ ሞቅ ደመቅ የሚለው … ብቻ መልካም ዜና ለመስማት ለማዬትም ስናገኘውም አልታደለንም … ፈጣሪ ይሁናት እናትዬን …    
  • ·         ይገርመኛል።

ውዶቼ የነጻነት አርበኞቻችን ዘሃቸው መውጣታቸው ምን ያህል ፈጣሪን እንደምናመሰግነው ብነለካካ ወቄቱ ምን ያህል ይሆን? እግዚአብሄርን ማመስገን ማለት ምክንያት ፈጥሮ ለሰጠው ትንፋሽ አክብሮት ቀርቶበት ወቀሳን መተው ማለት ነው። ሃሳብን ቤት ውስጥ ከቤተሰብ ጋር ያለ አንጋች መግለጽ የልብ የልብን ማውጋት፤ በስልክም በሚዲያም ሃሳብን እዬገለጹ ነፃነት ምድረበዳ ላይ እንዳለ ማሰብ/ ማሳጣትም ያስተዛዝባል። መተንፈስ እራሱ ሲሳይ ነው። ውሃ በተፈለገው ጊዜ መጠጣት። 

የታሠሩት አርበኞቻችን ሲፈቱ አንዲትም ቅንጣቢ እውቅና ለለማ እና ለገዱ የትጋት መንፈስ አለሰጡትም፤ ከስክነት አባዎራው ከኮ/ ደመቀ ዘውዱ እና ከማስተዋል አራጌ በስተቀር። እሱ ነበር ፍንጭ ያወጣው ኦህዴዶች የእስረኛ ቤተሰቦችን እዬደወሉ አይዟችሁ ይሉ እንደ ነበረ ሚስጢር ያወጣው አባ ቅንዬ። አንድ ሰው ልጁ ዓይኑን ትንፋሹን እንዲመጠው እድል ሲያገኝ ለእሱ ቀርቶ ለልጁ ማሰብ አለበት። የሚፈልጉት ያህል ላይሆን ይቻላል አሁን ያለው ነፃነት፤ ነገም እነሱ ቢይዙት ከዚህ የተሻለ ስለመሆኑ ጋራንቲ የለም፤ የሆነ ሆኖ በተለይ ልጅ ያላቸው የልጆቻቸው መንፈስ መሰብሰቡን የእኔ ማለት ይኖርባቸዋል። 

የልጆችን ነገ በእጅ ባለው ለመጠበቅ አለመፍቀድ ቀለል ባለ ቋንቋ መተላለፍ ነው። እግዚአብሄር ሲመሰገን ስለ እለት እንጀራም ነው። ልጆች ተጎድተዋል። የትዳር አጋሮች ቆስለዋል። እናቶች ተሰቃይተዋል፤ ድክሟቸዋል፤ የኢትዮጵያ ህዝብም ደክሞታል። መኖርም ዝሏል። ለዚህ ሲባል የግልን አዎንታዊ ኢጎ ማስታገስ ግድ ይላል። በማይመችን ውስጥ ያለውን ቅንጣቢ የሚመች መንፈስ ለማስፋት፤ ሙሉ የሚመችን ዘመን ለማምጣት ስልትን ምራኝ ማለት ያስፈልጋል። ለተገኘው ማናቸውም መልካም ነገር ሁሉ ዕውቅናም መስጠት። ምስጋና አላልኩም ፈጣሪ እራሱ ሲፈጥረው መርቆ ስጥቶታል - ለቅንነት ዘበኛው።

ከዚህ በላይ የፍቅርም ስጦታ የለም። በጣም ብዙ ሰው ነው እዬጸለዬላቸው ያለው። እኔ ከ4 ዓመት በላይ ውጪ ላሉት ቤተሰቦቼ ስልክ ሳነሳላቸው ኖሬ ያች ቅጽበት አዬር ላይ ጠ/ ሚር አብይ ጎንደር ለህዝብ ንግግር ሲያደርጉ ያን ከፍተው ነበር የደወሉልኝ። ታነሳልናለች ብለው አላሰቡም ነበር፤ እኔም የደስታዬ ሰሞናት ስለነበረ በፍሰሃ አነሳሁላቸው። እልልታው፤ ሳቁ፤ ፍንደቃው አሁን ተረድተንሻል መባሌ፤ ይቅርታ መጠዬቃቸው ሁሉ ግርም ነው ያለኝ። ይደውላሉ „ፓለቲካ ይቅርብሽ፤ አሁንም ቅድምም ኑሮሽን ኑሮሽን፤ ምን ሲያደርግልሽ አዬሽ ፖለቲካ ወዘተ ወዘተ“ ጭቅጨቃው መረረኝ፤ ከዚህ መከራዬን ያሰዩኛል እነ አቤቶ ዘመንተኞች በግራና በቀኝ ስልኬ ማረፌያ የለውም ለረብሻ፤ ከዛ ደግሞ እነሱ እና 4 ሙሉ ዓመት እኔ እህታችሁ ዝግት አደረኳቸው። ምን ይደረግ። እህቴ „አብይ እርቅ ነው“ ነበር ያለችኝ ድምጼን ስታገኘው። የሚገርመው አብረዋት የሚሠሩት ሁሉ አብረው ከእሷ ጋር እንደ ተጨነቁ ደስታዋንም እንደተጋሩ ነግራኛለች፤ በሥነ - ሥርዓት እህታማቾች ሰብሰብ ብለው ፕሮግራም ይዘው ለጤናችን ብለዋል። አክስቶቼም እንዲሁ በሀገረ አሜሪካ በተለያዩ እስቴቶች ነው የሚኖሩት። እኔ ከዚህ ተነጥዬ ነው የምኖረው። ለነገሩ እንደሚሉት ብሄድላቸው አያሰሩኝም ነበር። አስረው ለማስቀመጥ ነበር ህልማቸው - አላሳካሁላቸውም። መንፈሴን መቆጣጠሩ በኔትም አልሰራም።

ብቻ የአስታራቂው አብይ መንፈስ ጽኑ ተቀናቃኞቻቸው ድካማቸው አሳዘነኝ የውነት። የቤተሰቦቼን ሐሤት ሳዳምጥ። መንፈሱ ተገዝቷል። አሁን ዲታ ነው የአብይ መንፈስ። ካናዳም እንደዛው ነው የተሾሙ ዕለት እንኳን ደስ አለን ሊሉ ዜናው እንደተሰማ ደውለውልኝ ነበር። አብርን ነበር ያነጋነው። ለዚህ ብስጩ አዬር ለስላሳ ሰው በእጅጉ ያስፈልገናል። „በስጩኝ“ ሆነናል። የሌለነን ናፋቂ ሆነናል። እሱ ብቻ ሳይሆን በግራ ቀኝ የተደገሰልን ከውስጡ ማድመጥ ተስኖናል። የትውልድ ብከነት እንዲቆም አለመፈለግ ያሳዝናል። እስቲ ስለ ልጆች እንሰብ።

·         በተያዬዘ ሁኔታ እኛ ከዚህም አልፈን 30 ቀን ባልሞላቸው የቤተ መንግሥት ልጆች ቆይታ ታች ወርደን በረድ ልከናል። ለዛውም ለወያኔ ሃርነት ትግራይ በደህንነቱ አፋሽ አጎንባሽ አራሽ ፈዋሽ ተኑሮ። አለማፈር። እጅግ በሚያሳፍር ሁኔታ ወርደናል። ይሄን ነጮች ሲሰሙት ምን ይሉን ይሆን? ልጆች ምን አደረጉ? የአባታቸውን ፍቅር ፈልገው ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ሄዱ፤ የአንድ የሙሉ ቀን የአባታዊ ፍቅር ናፍቆት እንኳን ሊሰጧቸው አልቻሉም። እዬባከኑ ነው ጠ/ ሚሩ። ሰው መሆን ግን እንዴት? የገዘፈ ሥጋ ተሸክመን አንቱ ተብለን … እ።

·         ኢትዮያዊነት በሥሙ ውስጥ ለመኖር መፍቀድ ማለት ሞራሉን መጠበቅ አለማለት
አስካኝ፤ አረጋጊ፤ አግባቢ መንፈስ በህብረት ብንጠብቀው ለራሳችን ነው። ለእያንዳንዳችን። የአብይ የተመሰጠረው ንዑድ መንፈስ ለሁሉም እኛ እንዳሻን ለምናብጠለጥላቸው፤ ትንሽም ራፊ ለማናክልላቸው፤ አክብሮትም ለምንነፍጋቸው፤ አንድ ቀን ለእኔ አልተመቸኽኝም ግን ድካምህ ሊመሰገን ይገባል ለማንላቸው መከረኛ የነፃነት አርበኞቻችን፤ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ከሚያስቡት በላይ ለመንፈሳቸው ጥንቁቅ ነው። ተጨናቂም ነው። አሁን አጋጣሚው ቢመቻች እኛን አፍንጫችሁን ላሱ ብሎ፤ እኔ ለፍቅር ነው የተፈጠርኩት „ሀ፣ ሐ፤ ኀ፤ ሃ፤ ሓ፣ ኃ“ ስድስቱም ሃዎች ህሊናዬ ናቸው። 

ሁለቱም  ጸዎች „ጸፀ“  ውስጤ ናቸው። ሁለቱም „ሠ፤ ሰ“ ሰዎች የልቤ ናቸው ብሎ እኛን ማህል ቤት ገትሮ የተፈጠረበትን የሰማይ የፍቅራዊነት ጥሪ ይከውንበታል። ጠቅላይ ሚ/ር አብይ አህመድ ፍጥረታቸው የተለዬ ነው። ደግነቱ አሁን ሰው ምን አይነት እንደ ሆን ከታች ሳሉ እና ላይ ሲሆኑ የበለጠ ማዬት ችለዋል። እኔ ንግግር ተውኔት መሆኑን በተፈጥሮው አንድ ወገኔ መላ አካላታቸው አዬር ላይ በወጀብ እንደሚናጥ እንደተንጠለጠ ከፈን ነገር ሲያስኬዱት ደቡብ አዋሳ ላይ እንደዛ ሲሆኑ ሳይ፤ በሌላም ቦታ አንዲት ነገር ተነጥላ የሳት ላንቃ ያለ ቅንጣቢ አክብሮት ፊት ለፊታቸው ሲወረወር ሳይ፤ ድካማቸውን እርካብ ለመሳያዝ ፈተናቸው ይታዬኝ እና አነባለሁኝ። ሁሉንም አዳምጨዋለሁኝ። ዛሬ ዛሬ የነጮች ዜና ሁሉ ተረሳ። የእውነት ከእውነት ጋር ተፋተናል። አንድ ቃል „አንተን በማዬታችን፤ እኛን መከረኞችን ለማዬት በመፍቀድህ ደስ ብሎናል“ ይሄ ይበልሃል መቅደም ነበረበት። ከዛ ሌላው ጫን ተደል ጉድ ቻል ቢባል ምን በነበረ። ብቻ ኢትዮያዊነት በሥሙ ውስጥ ለመኖር መፍቀድ ማለት ሞራሉን መጠበቅ አለማለት እንደሆነ የተረዳሁበት ድካሜን የመዘመዘ አጋጣሚ ነበር። ከማንነታችን ኤቲክስ ጋር አንተዋወቅም። ዳንቴል ሲተረተር አይነት ነው የሆነው …
  • ·         ሥነ - ቋንቋ የልቀት ዕውቀትነቱ የንጥረ ነገራት ተፈጥሯዊ ነፃነት ነው።

ፊደል መናገር። ላዳመጡት መመለስ። ጮኽ ብሎ ማንበብ። ስሜትን በፊደላት ወርብ አሳምሮ በምላስ መድረክ ላይ መተወን። ከቶ ተሳሳትኩ አንዱ የትግል አንኳር የመናገር ነፃነት ይከበር አይደለምን? መናገር እኮ የቋንቋ መገለጫ ምስባኩ ነው። የፍላጎትም ጋላጭ ጉልላት። መናገር ጉልማ አይደለም ተፈጥሮ እንጂ። አርስሄማ። ቋንቋ የላቀ ሥነ -ጥበብም ነው። ውበት አለው። ቋንቋ ጥበብን የሠራ፤ የፈጠረ መቅድመ ተፈጥሮ ነው - ለሥርጉተ። ጥበብም ቋንቋን የፈጠረ ለቋንቋ ተፈጥሮ የተፈጠረ ነው። ለም መሬት እና ዘር። በመጀመሪያ „ቃል“ ነበረ። ሲባል እኮ „ቃል“ ቋንቋ ነው። ነው አይደል? እንዴት ነው ነገሩ? „ቃል“ ባይኖር እንደ ቃሉ እግዚአብሄርም ሰው ሆኖ ከመርገመ ሃጢያትን እና ፍዳ አይድንም ነበር። ያ የመስቀል የምህርት ቀን የተገኘው ሚስጢሩ „ከቃል“ ነው። „ቃልም“ ቋንቋ ነው። የሁለት ፊደላት የአናባቢያት ሰብል። ቋንቋ የፈጠረው እኮ ራሱ ፈጣሪ ነው። 

ስለዚህ ፈጣሪ የፈጠረውን ቋንቋ ስለምን እንታገለዋለን? ስለምንስ እንፋለመዋለን? ይገርማል። „ቃል“ ባይኖር የስብከት ሐዋርያትም ባለኖሩን፤ የቃል ነብያት ባልተነሱ፤ የቃል መፈጸሚያ ቤተ ዕምነቶች ባልነበሩን። ቤተ ሃይማኖቶችን የሚያስተዳደሩ ሊቃውናታት፤ ካህናት፤ ዲያቆናት ጳጳሳት፤ ኤጵስ ቆቦሳት አቮው፤ መርጌታዎች፤ መምህራኖች፤ ነብያት፤ ሸኽሆች፤ ኡስታዞች ሆኑ ሃጂዎች እና ማሳውም ባልነበረ። መሪም ሰው ተመሪም ህዝብ ባልኖረ። ቃል ባይኖር ቤተ ሚዲያ፤ ቤተ ፓለቲካ፤ ቤተ መኖር፤ ቤተ ቤተሰብ፤ ቤተ - ትውልድ፤ ቤተ ፍለስፍና ወዘተ ባልኖረ …

ቋንቋ አልቦሽ እውቀት አይታሰብም። ሥነ - ጥበብም እንዲሁ። የዕውቀት ተቋማትም። ሥልጣኔም። ታሪክም። ቋንቋ ባይኖር የዓለም ከርሰ ቁመና ምን ይመሰል ነበር ኳረኮንች፤ ድቃቂ፤ ድብ ያለ፤ ድብልብል፤ ድንቡልቡል … ምን? ግን ሰው ራሱ እኮ „ቃል“ ነው አይደለምን? ቋንቋ ሥነ ህይወት ነው። ህይወትን ይሰጣል። ህይወትን ይፈጠራል። ህይወትን ይመራል። ቋንቋ ፍቅር ነው ፍቅር የነፍስ መድህን ነው። ፍቅር ህይወት ነው። ህይወት ኑሮ ነው። ኑሮ ቋንቋ ነው። ነፍስም የመኖር ቋንቋ ነው። መተንፈስም የመኖር ቋንቋ ነው። ማዘንም መደሰትም ቋንቋ ነው። መበሳጨት መከፋትም ቋንቋ ነው። ለቅሶም ቋንቋ አለው። እልልታም ቋንቋ አለው። መኖርም ሞመትም ቋንቋ አለው። ቋንቋ አንደበታዊ እና አካላዊ ሊሆን ይችላል። ባለፈው ስለ ወዳጄ አቶ ኦባንግ ኢትዮጵያ ሜቶ በጻፍኩት ወግ ቢጤ ላይ ስላብራራሁት ወደ እዛ መሄድ አያስፈልገኝም።
  • ·         ቋንቋ ተመስጦ ነው (Inspiration)

ቋንቋ እኮ አንደበት አለው። የአንደበቱ መሳሪያም አለው አፍና ሠራዊቱ በፈጠሪ የተፈጠረ የተፈቀደለትም። አካላዊ ያልሆነው በአንደበት የሚገለጸ ቋንቋ በልሳን የሚነገር ቋንቋ ሙዚቃም ነው። ምት አለው። ዜማዊም ነው ለዛ መሳጭ ንድፍ አለው። ቃና አለው ሰውነትን ያፍታታል። ቋንቋ ተራኪ፤ ጋላጭም ነው። ቋንቋ ለአፍ ስፖራታዊ ጨዋነት ነው። መንፈስን ይፈውሳል። ምቱ ለሰውነት የውሃ ያህል እርካታን ይሰጣል። ቋንቋ ደም ነው። ትንሽ ሊከብድ ይችላል ይህ አገላለጽ። አዎን ቋንቋ የደም ውጤትም ነው የሚወረስ። አፍ የተፈጠረው ለቋንቋ ሙሴነት ነው።
  
ቋንቋ ባህል - ወግ - ልማድ አካባቢም ነው። ወግ የባህል ደህንነት አስከባሪው ህግ አውጪው እንደ ማለት። ልማድ ደግሞ ለባህል የሚኒስቲሮች ጉባኤው ነው። ሲጣመሩ ቋንቋ መንፈስንም፤ ህሊናም፤ አካልንም የሚያስተዳድር ሙሴ ነው። ከወገብ በላይ እና በታች አገናኝ ሰቁ ነው። ቋንቋ ሥራም ነው። ቋንቋ ሌላውን ከመሥራቱ በፊት ራሱን የሠራ አስገራሚ ጥልቅ ክስተት ነው። ቋንቋ ሰውን ሠራ ሥንል የሰው ልጅ ኑሮውን ለምራት የሚያስችለውን ነገር ሁሉ ማህንዲሱ ቋንቋ ነው ማለት ነው። የወል ሥጣኔ ዝክረ አውዱ ቋንቋ ነው። የሰው ልጅ የኑሮውን ሸክም ለማቃለል የሚያደርጋቸው ምርምሮች፤ ፍልስፍናዎች የዕወቅት ምጥቀቶች ሁሉ መሠረታቸው ቋንቋ ነው።

ቋንቋ ዕለታዊ አይደለም ትርታዊ ነው። የልብ ነው። ለዚህም ነው ቋንቋ ፍቅር ነው ማለትን የሚያስደፍረው። ቋንቋ ተፈጥሯዊ ነው፤ ተፈጥሮን አክብሮ መነሳቱ ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮን ሚስጢር የመሸከም አቅም ስላለውም ነው። ቋንቋ ታጋሽ ብቻ ሳይሆን የመቻቻል ተቋምም ነው። ይሄ ማለት እንዴት ነው? ቋንቋ ተፈጥሮን አንዳለ የሚቀበለው ብቻ አይደለም። ቋንቋ የፈቃድ ብላክቦርድና ቾክ ያስፈልገዋል። ይለፍ ወረቀት ወይንም ቪዛ። ተወዶ በህሊና ሰሌዳ የሚጻፍ ሲሆን ተፈጥሮን ከውስጡ የሚያነብ፤ የሚተረጉም፤ የሚያመሳጥር ብቻ ሳይሆኑ መኖሪያ ጎጆው ተፈጥሮ ነው። ቋንቋ ተፈጥሮን እና ሰውን የሚያዳራድር አደራዳሪ ሽማግሌ ነው። ትዳሩ ከተፈጥሮ ጋር በኪዳን ውል በቀለበት በተክሊል ነው። ስለዚህ ቋንቋ የተፈጥሮ አንባቢ፤ የተፈጥሮ ተነባቢም፤ ተርጓሚ እና የተፈጥሮ አመሳጣሪ ነው ሲባል የዬሐገሩ ገዢዎች አይደሉም ቋንቋን የሚመሩት እሱ እራሱ አገረ ገዢ እንጂ … ከልብ መግባት ሲሹ አሱን ማባበል ግድ ይላቸዋል መሪዎች ሁሉ። ከልብ ጠብ የሚል ነገር ለማፍለቅ ተጊ መኖር ግድ ይሆናል። ከማህል አልታረስ ከደንበር አልመለስ ግን ለሰሚው ግራ ነው።  
  • ·         ቋንቋ ቆጥቋጣ አይደለም።

ቋንቋ ለፈቀደው ስስታም አይደለም። ሁሉን የሚሰጥም ለጋስና ቸርም ነው። ሌላው ቀርቶ ህገ - ደንቤን ጣስክ/ ጣሽ፤ ሰዋሰው አፋለስክ/ አፋለስሽ ብሎ ፍርድ ቤት አይገትርም። በነጩም፤ በጥቁሩም ሰዋሰዋዊ አግባብ ተፈጥሮውን ላከበር / ወይንም ስዋሰዋዊ ህጉንም ተጥሶ እንኳን ለሁሉ እኩል ፍቅር እና ሥህነ - ምስጠት አለው። ቋንቋ አክብሮትም ነው። ቋንቋ አክብሮት የሚሆነው የተፈጥሮን ውስጡን ለማወቅ በመፍቅዱ ነው። ቋንቋ ፈቃድ ነው። ይለፍ ልበለውን ከቶ? የአንድ ሐገር ወይንም መንግሥትን ህጉን መጠበቅ የሚቻለው ቋንቋ ሲታወቅ ነው። የግልን መብት እና ግዴታን ሚዛናዊ ማድረግ ሲቻል የሰው ልጅ ለህግ ተገዢ ለመሆን ይቻለዋል እንደ ማለት። ቋንቋ ካልተቻለ ግን የህግ ጥሰት ይገጥማል። ስለዚህ ቋንቋ የተፈጥሮ ሥራዓት አስከባሪ ወታደር ነው ግን ፍንዳታ አልቦሽ። ቋንቋ ተሟጋች ስለሆነ ህይወቱ የአደባባይ ነው። ጥድት ያለ ነጭ ለባሽ ነው። ነጭ ለባሽነቱ የውስጥ ነው ፍቅር ለማድርግ ስንቀበለው። ልባዊነት!
  • ·         የቋንቋ ንግሥና። 

ቋንቋ ሚስጢረኛ ጓደኛም ነው። አሁን ግዕዝን የወደዱ ጓደኛቸው ያደረጉ ሁሉ ህሊናው አዝማራቸው የተጠፈበት ሊቀ - ሊቃውንትነት ነው። ከግዕዝ የሚገኘው ሚስጢር ሰማያዊ ነው። ጀርመን የዓለምን የመዳህኒት የምርምር ዘርፍ በባህላዊም ሆነ በገሃዳዊውም ዓለም ተጠሪ የሆነው „በመጸሐፈ ፈውስ“ ነው። እሱን ደግሞ በዩንቨርስቲዎች ስላተቀበለ ዕውቅናውን ከግርማ ሞገስ ጋር ሽልም ስለሆነ ነው። ግዕዝ ጀርመን ውስጥ በተለያዩ ዩንቨርስቲዎች ይሰጣል። እኛ የራሳችን ጥለን ከማርክስ ጋር ልባችን ጥፍት ብሎ ዘመናችን በኪሳራ ቀዳዳ እና በብክነት ነዳላ ስንሸምን ጀርመን ግን ቀጣይ ልጆቹን ግዕዝ ያስተምራል። ብራና ገልጦ ቀለም አቅልሞ። ልባም። ስለምን ሚስጢሩን ከዓናቱ ለመቆጣጠር። ይኸው እኛ የሙጥኝ ብለን የሞኝ ለቅሶ ሰንደረደርለት የካራል ማርከስን ንድፍ ሃሳብ፤ ወንዳታው ጀርመን ግን ያን የእትብቱን የቀለም ፍልስፍና ጠብታ አሸንቅጥሮ እኛ ያቃለልነውን፤ እኛ ባሊህ ያላልነውን፤ የናቅነውን የነፍስ አባቴ አቤቶ ግዕዝ ሆይ! ብሎ ታጥቆ አደግግደጎ ከኢትዮጵያውው ግዕዝ ጋር የሙጥኝ ብሏል … ልባምነት ይሏችኋል።
  • ·         የቋንቋ ጣዝማነት።

የቀደሙት የኢትዮጵያ ሊቃናት ሁሉ የሊቅነታቸው ጣዝማ ምንጩ ግዕዝን ሥራዬ ብለው፤ የእኔ ብለው ስለያዙት ከሚስጢራቸው ስለተነሱ ነው። ብዙ ሚስጢራትን ያውቃሉ። መጸሐፍ ቅዱስ እኮ ሐዋርያት በጥቅሉ የሠሩትን የእኛ የእድምታ ሊቃውንት በምን ሁኔታ ላይ እንድንውጠው እንዳደረጉት ተጠቃሚው ያውቀዋል። ለዚህም ነው የወያኔ ሃርነት ትግራይ በፖሊሲ ደረጃ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሥራዓተ ህግጋት ላይ ስውር ደባውን ሲከውን የኖረው። 

ኢትዮጵያ ባላት አንጡራ ሃብቷ ከተጠቀመች የምትደርስበትን ያውቃል። ትውልዱን ከሚስጢሩ መንቀል ባንዳዊ ተልዕኮው ስለነበር። መሬት የተረገመች እንድትሆን ተግቶ ሰራበት ወያኔ። የኢትዮጵያ የተፈሪነት ምንጩ በጥበብ የተቀለመው በቋንቋው ጥልቅነት ነው። ሥርዐት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ጥበቡ ማንም ኢትዮጵያዊ ዬትኛውም ሃይማኖት ይከተል ግን ሊያጠናው፤ ሊማረው የሚጋባ የራሱ አንጡራ ብሄራዊ ሃብቱ ነው። ግዕዝን ማጥናት ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ ብቻ ሳይሆን ለእስልምና እምነት ተካታዩም አጀንዳው ሊሆን ይገባል። ከአረብኛ ይልቅ ግዕዝ  ለኢትዮጵያዊው ሙስሊም ይቀርበዋል። 

ይሄ የ ኡስታዝ አህመዲን ጀቢል ተልዕኮ ሊሆን ይገባልም እላለሁ። ኡሳታዝ አህመድን ጀቢል ለሰው ልጆች እኩልነት ለመታገል ስለወሰነ ከዚህ ጥልቅነት ጋር ቢገናኝ ይጠቅማዋል ብዬ አስባለሁኝ።  አፈነገጥሽ ተብዬ ካልተከስኩ / ብከሰስም የለመድኩት ነው። ኢትዮጵያዊው ቁራን በግዕዝ መጻፍ ይኖርበታል፤ ቁራን መቀራት ያለበት በግዕዝ ነው። እምነቱ ዶግማ ሆነ ቅኖና መጠናትም ያለበት በግዕዝ መሆን አለበት እላለሁኝ። መቼስ ሥርጉተ ያፈነገጠች ናት እና ይህ ሊጎረብጥ የሚችል በውስጤ መስጥሪ ያያዝኩት ዛሬ ግን መውጣት አለበት ብዬ እማምንበት ነው፤ ጀርመኖች እኮ ፕሮቴስታንት፤ ካቶሊክ አይድያሊዝም፤ በተፈጥሮ የሚያምን ህዝብ እያላቸው ግን ግዕዝ እጬጌያቸው ነው። ብዙ ነገር አመልጦናል እኮ ከግእዝ ለነገሩ እኛስ መቼ ተግተንበት። 

የኦርቶዶክስ ተዋህዶን የሚያምኑ የዓለም ዐብያተ ቤተክርስትያንት አሉ። ግን እንደ ኢትዮጵያ እና እንደ ኤርትራ በጥበብ የሰከነ አይደለም። ተገኝቼ አይቸዋለሁኝ። ስክነቱ ምንጩ ቋንቋው ያሰናዳው መክሊት ነው። የቤተ እግዚአብሄር የራሳችን የሆነ ያልተዋስነው ቋንቋ አለን። እጬጌው ግዕዝ። በእጬጌው ከፍጥረተ መቅድሙ ጀምሮ ሳይለጠፈበት ግን የተፈጠረበት ግዕዝ ዕዝል፤ አራራት - ዜማ፤ ተክሌ ዝማሚ፤ አቋቋም፤ ሃዲስ፤ ብሉይ፤ ኪዳን፤ መጸሐፍ፤ ንባብ፤ ድጓ፤ ጾመ ድጓ፤ ቅዳሴ፤ ማህሌት፤ ዝማሬ ቅኔ ሁሉም እያንዳንዳቸው ብቻ ዬራሳቸው የፍልስፍና ዘርፍ እና አውታር ቅስር አላቸው። የመዋለ ዕድሜም ትምህርት ናቸው። የሚያልቅም የሚጨረሰም አይደለም … ሰማያ ሰማያትን ያዘለቀ ምርተ - ዝቀሽ ነው።

ዛሬ ዓለም የደረሰበት የሳይንስ ጥበብ ሁሉ የእኛ መሠረት ነው። ትምህክት አይደለም። ውስጣቸን ስላሾለክን ራሳችን ማክበር ስለተሳነን እንዲህ ሆነን እንጂ ወደ ትውስት የሚያስኬድ አንዳችም ነገር አልነበረም። ሁሉ ያለን ግን ያለወቅንበት ነን። በግዕዝ ውስጥ ሥነ - ተፈጥሮ፤ ሥነ - ፍልስፍና፤ ሥነ - ሃይማኖት፤ ሥነ - ሳይንስ፤ ሥነ - መኖር፤ ሥነ - ነፍስ፤ ሥነ - ምህዋር፤ ሥነ መልዕካምድራዊ አቀማመጥ፤ ስለ ከክርስትና ሃይማኖት ውጪ ስላሉ ሌሎች ሃይማኖቶች ዶግማ እና ቅኖና ለዛውም በአክብሮት ሁሉም አለ። ሥነ - ሃይማኖት የተዋህዶን ብቻ ሳይሆን የዓለም ሃይማኖቶችንም በጥልቀት ግዕዝ አሳምሮ ፈታትሾታል። 

እስያውያን የሚያምኑትን ሃይማኖት ዓይነት ሊቀ ሊቃውነቱ አያቴ ነግሮኛል። ሲያሰረዳኝ በተቃውሞ አልነበረም በዕምነት ፍልስፋና ጥበብ እንጂ እንዲያውም አንድ ቀን መንገድ ላይ አግኝቸው ወደ ምሄድበት ይዤው ሄድኩኝ መንገድ ላይ እያለን አላህ ወአክብር ሲባል አዬሽ ልጄ እኛ አሁን የምንሄድበት ለገሃዱ ዓለም ጉዳይ ነው፤ እነሱ ደግሞ በዚህ ሰዓት ፈጣሪን ያመሰግናሉ አለኝ። ይህ እንግዲህ የዛን የመላክብርሃናትን ሊቅነት ምጥቅነት ያሰዬኝ የሃቅ ትውፊት ነበር። የማዳምጣትን በስነ ልቦና ተቀብዬ አስቀምጣታለሁ። ለዚህም ነበር በኢትዮጵያዊው እስልምና የመብት ጥያቄ እርሾነት የተጋሁበት ምክንያት። የጎረስኩት የፍልስፍና ቅንነት ስለነበር፤ ቁርሾ አላስተማሩንም፤ ቂም አላወረሱንም አቮው ፍቅርና አክብሮትን እንጂ።
  • ቋንቋ የነፍስ ተውኔት ነው።   

ጥብብ በሥነ - ጹሑፍ፤ በሥነ - ሥዕል፤ በሥነ - ተውኔት ይቀርባል። አሁን ወረብን ከሥነ ተውኔት፤ ከዝማሜ ከዜማ ጋር፤ ከሥነ ሥዕል ጋር ተዋህዶ ሲታሰብ ምጡቅ ነው። ስለዚህ የትወና ጥበብ  ከሥርዓት ተዋህዶ ተገኘ እላለሁ እኔው። ይህም ከቶ እንደ ማፈንቀድ ይታይብኝ ይሆን? ፍለስፍናዬ የነ ሸክስፔርን የሚሞግት ነው። ይህ ከተነሳ አንድ ሌላም አለኝ። አንድ ጊዜም አንስችው ነበር በኮመዲ እና በትራጄዲ ማህል የቀረ አንድ ትዕይንት አለ። ይህም ሁለቱን አጣምሮ የሚይዝ መገናኛ ነው። ቀለሙ ግራጫማ ልበለው ሥያሜውንም የሲቃሳቅ፤ ባህሪው ዝንቅንቅ። ለቋንቋ ውበትም ተጨማሪ ካባው ነው ይሄው የሥርጉትሻ ፍንጋጣ ምልከታ ነው ብላ ታምናለች። ብቻ ቋንቋ ተውኔት ሲሆን ፍሬ ዘለቅ ዝቀሽም ነው።

ኢትዮጵያዊው ግዕዝ ጽናጽሉ፤ መቆሚያው፤ ማጠንቱ ሲታከልበት ደግሞ ሌላ ዓለም ነው። ምን ለማለት ነው ቋንቋን በፈቀድነው ቁጥር ትርፍ እንጂ ኪሳራ የለውም። ህይወታችን ታታሪ ይሆናል። ለከንቱ ነገር ጊዜ አይኖረንም። አሉታን በክፈለ ጦር/ በብርጌድ አደራጅተን በመልካም ነገሮች ላይ ውጋ፣ ስቀል፣ ንቀል፣ አንልም። በመልካሙ ላይ በመትጋት ከአይቻልም ይቻላል፤ ከአይሆንም ወደ ይሆናል የሚል አዲስ የለውጥ አቅም መሸጋገር ይቻላል። ግን ቅኖችን መንገዳችን ካልን ብቻ።
  • ·         ቃል አዋቂነት ልብ ይጠይቃል። 

ሰሞኑን የጠ/ ሚር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ሱማሌ ጉዞ መክፈቻ ላይ ሱማልኛ ሲናገሩ እኔ በድንቀት በግራሞት ነበር የተመለከትኳቸው። በስስት። ሲጀመርም እኔ ለዶር ምህረት ደበበ እና ለዶር አብይ አህመድ ያን ጊዜ አቶ ነበሩ አብዝቼ እሳሳላቸው ነበር - አሁንም። የሆነ ሆኖ ጅጅጋን እራሱ የሥራ መጀመሪያ ማድረጋቸው በራሱ ለእኛ ያልተገለጠልን የሰማይ ጸጋ ነው። በግርድፉ እዬዳከርን ካልሆነ በስተቀር „የደም ማድረቅ“ እርምጃ ነበር። በራስ ላይ ተጽዕኖ አድርጎ ለፍቅር መርሃ ግብር መበርክክ ነበር። ትውልድ ፍቅር እንጂ እኛ ባለፍንበት ብክንት መቀጠል የለበትም እምለውም ለዚህ ነው። እስከ አሁን ሙሴ አልነበረንም አሁን ግን አሉን የእኛዊነት አርበኞች። በቀል፤ ቁርሾ አንድ ቦታ መቆም አለበት እያልን የጮኽነውን ድምጽ ያደመጠ ታላቅ ታሪካዊ እርምጃ ነበር። በዚህ ከቀጠለ አዬሩ ሰይጣንም ድል ይሆናል። ለዚህም እኮ ነው ቅድስት እናታችን ክርስቶስ ሰምራ ፈጣሪዋን፤ አምላኳን ስለምን ከሰይጣን ጋር አትደራደርም ይህን ያህል ነፍስ በዲያቢሎስ እሳት ከሚቃጠል ብላ አሻቅባ የሞገተችው።

ፈጣሪ ከእኛው ከወረቀት ዲሞክራሲያውያን በላይ ስለሆነ፤ አሁን ሳዬው በኢትዮጵያ ያለውን ጠጨባጭ ሁኔታ ፍቅር የመልካም ዕድል ትርፈኛ አለመሆኑን ነው።  የሆነ ሆኖ ፈጣሪ አምላክ ለእናታችን ለሰብዕዊ መብት ተሟጋቿ ለቅድስት ክርስቶስ ሰምራ የክብር ተክሊል አቀዳጃት። እናታችን ፈጣሪን ከዲያቢሎስ ጋር ለማስማት ቅደመ ሁኔታ አላስፈለጋትም። የከረረ አቋም አላሰኛትም። ሸካራ አያያዝን አልመረጠቸውም። ዝቅ ብላ በትህትና ነበር የጠዬቀቸው ያግባባች። 

እንደ እናትነቷም ጸጋዋን ሳትተላለፍ በርህርህና ነበር የቀረበችው። እሷ እኮ ሥጋቸው ላለፈው፤ በህይወት ለሉት ተጋች? እኛ ምድር ላይ ላሉት፤ በህይወት ለሚኖሩት ለህጻናት እንኳን መራራት ተሰናን። ፍቅር ቀላል አይደለም። በህይወት ከባዱ ችግር፤ ከባዱ ጉዞ የፍቅር ነው። ከባዱ ፈታና የፍቅርን ተፈጥሮ መርህ መፈጸም ነው። ለዚህ ነው እኔ ስለስብዕ ለሚተጉት የፍቅርን ተፈጥሮ እንደ መደበኛ ትምህርት መሰጠት ብቻ ሳይሆን የማናቸዋም የሥራ መስክ፤ የማናቸውም የከፍተኛ ተቋማት መግቢያ ሰብዕና መለኪያ መሆን መቻል አለበት የምለው። የፍቅር ተፈጥሮ መርህ ፈላስፋ፤ ሳይንቲስት፤ ተማራማሪ፤ ኤክስፐርት፤ ተቋማት፤ ውይይቶች፤ ሰሚናሮች ዓለም አቀፍ ቀኖች ዕውቅና ሲያገኝ ናፍቆኛል እያልኩ እምጎተጉታቸው ለሚችሉትም ለዚህም ነው። ይህን ስንስት እንደማለን/ እናዳማለን።

ስለዚህም የትናንቷ የተፈጥሮ የፍቅር ጸጋ ጮራ ሐረር በደም ጨቀዬች። በቋሳ አረንቋ እና ጨቀጨቅ ተዘፈቀች፤ በሃጢያት እክክ ተበከለች። ያ ታቅዶ የተከወነ መከራ፤ በደሉን የተሸከመው ተባዳዩ እራሱ እቦታ ድረስ ፍቅርን ይዞ ሄዶ ፍቅር መቀለቡ የተራራው የቅዱሳን ስብከተ አስተምህሮት ነበር ልብ ላለው። ይህ ብቻ በበቃን። በዬዘመኑ የትውልድ ብርንዶ ለሚያሰኘው አውሎ። ፍቅር ለመቀበል ጥሪ ያለበት መንፈስ ያደረጋቸው ክንውኖች ሁሉ አቅሙ የፈጣሪ ነበር። ጥበቡም ፈጣሪ የሰጠው። „በራሳችን ወጪ እዚህ ድረስ ተፋናቃዮችን ወደ ቦታቸው እንመልሳለን አሉ“ የፍቅር ሐዋርዮቻችን። 

ይሄ ብቻውን በአሉታ ሰጋር በቅሎ መጭ እያለ ያለውን የሚዲያ ማህበር በታሪክ አቆሞ ይሞግተዋል። 600 ሺህ + 50 ሺህ ህዝብ ፍዳን ተሸክሞ ግን ያን ጫናውን ችለው፤ ሳይታወኩ ከእርካባዊ ግባቸው የደረሱት የዘመኑ የተግባር ስክነቶች ፍቅርን ሆኑበት። በስንት ዘመን ቂሙን ማወራረድ ይቻል ነበር? ብንገፋው // ብንገፈትረው // ልቅናው የአደባባይ ጸሐይ ነው። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ፍቅር ያነደደው ህዝብም መሪውን በአልልታ ተቀበለ። ፍቅር ቀልቦ ፍቅርን አፈሰ። ለአቦ ለማ መግርሳ እና ለዶር አብይ አህመድ ያ ሁሉ ሰቀቀን ተሸከመው ኢትዮጵያን በፍቅር ሽልማት፤ የጥላቻ አንከሊሱን ኩፍኝም በልስልስ አንደበት መፈወስ ነው መንገዳቸው። ቃል አዋቂነት እንዲህ ይገለጻል። በማድመጥ። የሰይጣን አምልኮ የሌለበት ልሙጡ ብሄራዊ ሰንደቃችን አረንጓዴ ቢጫ ቀዩም ደምቆ ያዬሁበት ጉባኤም ከዛ ነበር። ኢትዮጵያ በሳጅን በረከት ሳንጃ በኮሜቴ እዬተማራች ነው ሟርትም እርቃኑን ያስኬደው ይሄው የመጀመሪያ እርምጃ ነበር። ከዛ ከዛማ ያዬነውን አዬን …
  • ·         አንቦሻ! አንቦ የኢትዮጵያዊነት ቤተ መቅደስ ነው።  

ከጅጅጋ ቀጥሎ አንቦ ነበር። አንቦ እኮ ግንድ ነው። አንቦ እኛ የማናውቀው፤ ያልደረስንብት የጥበብ ትምህርት ቤት ነው። እዛ የሎሬቱ ታቦት አለ። ታቦት በፈተና፤ በመስቀል፤ በጽናት መከራ የታጠረ ነው። ያ መሬት ያፈራው ፍሬ የዓለምን ልብ ቀልብ የሳበ ዛሬንም አፍርቷል፤ አርበኛ ፈይሳ ሊሊሳን ሚሊዮኖች ምንም ሳይገድባቸው የዘመሩለት፤ የተቀኙለት፤ ያወደሱት፤ ያከበሩት የነፃነት ቀንዲል ባለሃብት ነው። ዕድሜ ልካቸውን ለነፃነት የታተሩ፤ በዬዘመኑ የካቴና ሰለባ የሆኑ አንቱ የሚባሉ አባ እና እማወራዎች የሐገር ተስፋ ቦታ ነው - አንቦ። አንቦ ቀድሞ እንደ ጎንደር ደም ገብሯል። ጎንደር እያልኩ ስጽፍ ስሜንና ደቡቡ ማለቴ እንደሆን ይታወቅልኝ። ለደቂቃም አስበነው ስለማናውቅ ነው ጎንደር ብቻ እያልኩ እምጽፈው። የሥነ - ልቦናችን አህታዊ ድሩ ልዩ ረድኤታችን ነው። መክሊታችን። ትንቢቱን ከጎንደር ጋር በቅኔ ተጋድሎውን በታሪከ ልቅና ሆኖበታል። የበቀሉ እሳትም ፈሶበታል። ስለዚህም አንቦ አእምሮ ስለሆነ የልጆቹን የመስዋዕትንት እፍታ ተቋዳሽ የቅድሚያ የእፍታው አህዱ ለመሆን መታጨቱ የህሊና ብቃት መሊከያው መስታውት ነው። ውስጠ ጠገብ ትልም ነው።

በዚህ ወቅት ጠ/ሚር አብይ አህመድ እንደ ወንጀል የታዬባቸው ደግሞ በኦሮምኛ ቋንቋ / አፋን ኦሮሞ/  መናገራቸው ነው። ምነው የሞራል ቅኑ አቦ በቀለ ገርባ፤ ሳይንቲስቱ የፖለቲካ ሊቀ - ሊቃውንቱ ዶር መራራ ጉዲናም እኮ የብሄራዊ የአርበኝነት መሪዎቻችን ናቸው። እነሱም እኮ በኦሮምኛ ነበር የተናገሩት። ቃለ ምልልሳቸው ሁሉ በአፋን ኦሮሞ ነበር። አቦ ለማን መግርሳ ሆነ ዶር አብይ አህመድ እኮ መነሻቸው ለዚህ ሥልጣን ያበቃቸው መሬት ላይ ያለው ያልገዛም መንፈስ ነው። 

የክብራቸው እርስተ ጉልት ይህ ማህበረሰብ ነው። ስለዚህ መነሻቸው ላይ መነሳት መቻላቸው ሊሂቅነታው ምራቁን የወጣ ስለመሆኑ ችሎት ነው - ለቅኖች። አላስገባም ብሎ ወያኔን የተፋለሙትም ልክ እንደ ጎንደሮች አንቦዎች ብቻ ናቸው። 27 ዓመት ሙሉ የበቀሉ እሳትም የነደደው በእነሱ ላይ ነው፤ በስውርም በግልጽም አንቦ እና ጎንደር የገበሩትን ሊሂቃን ብዛት ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው። … ሁለቱም በልዩ ሁኔታ መስቃውንም በቀሉንም ሰርግና መልሱ የወያኔ ሃርነት ትግራይ የተከወነባቸው፤ የወያኔ በቀል የከተከታቸው ናቸው። እጅግ በከፋ ሁኔታ ፊት የተነሱ የተጎዱ አካባቢዎች ናቸው። ከዛ የተፈጠሩትም። አንቦ ለትግራይ አዋሳኝ ቢሆን እስከ አሁን እንደ ጎንደር ጭልጥ ብሎ ተወስዶ ወይንም ተሞጥልፎ ነበር። ምንም እንኳን በልማታዊ መንግሥት በባለሃብቶች የቅርጫ ቀረምት ባይተርፍም።
  • ·         ታላቅ የዕውቀት አባት፣ አንባም ነው ቋንቋ። ሥህነ -  ዐዕምሮ ነው።

ቋንቋ ዕወቀት ነው። ቋቋ ሙያ ነው። ቋንቋ ሳይንስ ነው። ቋንቋ የነፍስ መዳህኒት ነው። ቋንቋ በማውቅ ትርፍ እንጂ ኪሳራ የለውም። ዕወቀት ሲጨምር ከእውቀቱ ጋር የሚመጡ የመኖር ጥበቦች፤ የመኖር ትውፊቶች ይዋህዳሉ። ሥርዓት መተላለፍም የለም። ከዚህ የሰው ሐገር ቋንቋ ለመማር መከራ በልተን እሱም አልሆን ብሎ ተለያይተን እዬኖርን፤ የራሳችን፤ ጠረናችን፤ ወዛችን የሆነውን ቋንቋ ስለምን እንደምናገለው አላውቅም። አሁን እኔ OBN ማዳመጥን እፈቅዳለሁኝ። ግን በምን እንግባባ። የአቦ ለማ መሳጭ ልስልስ አንደበት አብዝቶ ይናፍቀኛል ግን እንዴት? ቋንቋ አዕምሮን ብቻ ሳይሆን ህሊናን ገዝቶ ወደ ተፈለገበት አቅጣጫ ይገራል። ቋንቋ በራሱ የመኖር ማስልጠኛ ተቋም ነው። ቋንቋ በጠላትነት በጥርስ ነክሶ መያዝ ጤነኝነት አይደለም። ቋንቋ ቢያግባባ ቢያስማማ ቢያፍቅር ቢያቻችል እንጂ ጠብ ጠማኝ አይደለም። ቋንቋ እኮ የነፍስ ጸበለጻዲቅ ነው - የሥጋ ሳይሆን። ቋንቋ ቅዱስ መንፈስ ነው፤ የሚፈቅዱት። የሚጠብቅም። 
  • ·         ግን

በዚያ የአንቦ የምሥራች ቀን ሥብሰባ ላይ ጠ/ ሚር አብይ አህመድ አፋቸውን በፈቱበትን ቋንቋ ንግግር ማድረጋቸው ምኑ ነው ክፋቱ? ለእሳቸው ደግሞ አስተርጓሚ ያስፈልጋቸውን? አዳሜ ሲያጣ የጦመውን …. ወያኔ ሃርነት ትግራይ የመኖርን ሃዲድ  ያጨለመው የኦሮሞ ማህበረስን ለኢትዮጵያዊነት ባይታዋር ለማድረግ ያሰበው የቁቤ ትውልድ እኮ አፋን ኦሮሞ ብቻ ነው ቋንቋው። ትውልዱ እኮ ተላያይቷል። ሌላ ቦታ እኮ አማርኛ ይነገራል ኦሮምያ ላይ ግን ጠላትህ ነው ስለተባለ ተነጥሏል። የፖለቲካ ተንታኞቹ እና ጋዜጠኞቹ አቶ ኤርምያስ ለገሰ እና አቶ ምናላቸው ስማቸው እኮ በአማርኛ እያወያዩን ማህል ላይ በእንግሊዘኛም በፈረቃ አስደምጠውናል። እንግሊዘኛውን ቋንቋ ተርተር ሲያደርጉልን አስተውለናል። የጠ/ ሚር አብይ አህመድ ሲሆን ስለምን ይመረናል? ለዛውም በሀገር በቀል ቋንቋ? ኢሳቶች ሌላም ከእንግሊዘኛ ጋር ካነሳሁት የጨረታ ዲግሪ ባለቤቱን የወያኔ ሃርነትን መሪዎች ከሚተቹበት አንዱ እንግሊዘኛ አለማወቃቸውን ነው። እንግሊዘኛ እኮ ሐገራዊ ቋንቋ አይለም። እርግጥ ነው ግሎባል ቋንቋ ነው፤ ተወዳጅም ነው። ብቻ የትችቱ ማህለቅ የመምራት አቅሙ በዚህ ይለካ ነው ነገርዬው።

 እንግሊዘኛ አለማወቅ ከሊሂቅነት ከፍም ዝቅም አያደርግም - ለሥርጉተ። የሥር ቋንቋው ከታወቀ በቂ ነው። የቀደሙት ሐገርን ያህል ትልቅ እርስት ያቆዩን በእንግሊዘኛ ቋንቋ አይደለም። ኢትዮጵያ ሚስጥርነቷ ምንጩ ኢትዮጵያዊው ቋንቋ ባለውለታነት ጥልቀነት መመርምር ይገባል። ቢሆን ጥሩ ነው ቋንቋ ዕውቅት ስለሆነ ግን ኢትዮጵያ የእኔ የምትለው በነፃነቷ ልክ ያስከበረቻቸው በርካታ ብርቅዬ የቋንቋ ባለቤት መሆኗ ብቻ ሳይሆን ዘዬው ዓለም ቀረብን የሚለው ነው። ለዚህም ነው አክብሮቱ ግሎባል ስለሆነ ቀኝ ጌታ ጉግል ያነገሠው …

የሆነ ሆኖ ይህን መንገድ አዋሳ ላይ፤ ቤንሻንጉል ጉምዝ ላይ፤ ሱዳን ላይ፤ ጁቡቲ ላይ የፕሬስ ጉባኤውን እንዲያውም በአማርኛ ነበር ያቆላመጡት ይህን ጎንደሮቹ ሲቃኙት „ይታደሉታል እንጂ አይታገሉቱም“ ይሉታል … ይልቅ ከመይንም? ፈያንም? ከተቻለ ቢማሩት የፍቅር ጥገት ነው … ሲሆን ሲሆን በቁጭት ተነሳስቶ ተኩራዟ ላይ መቸከል ድንቅ ለነገ የመሪነት ውድድር … ይሁን ሽግግር …  
  • ·         የጠብ ገረፍታ።

ከዛ መልስ የቤተ መንግሥቱ የራት ግብዣ እና ዕድምታው ሰፊ ነው፤ እሱን ትቼ የትግራይ ጉዞ ነው። ትግራይ መንፈሷ እንኳንስ ከኢትዮጵያ ጋር ከእኛም ጋር አልነበረም። ሁሉ ነገር አርቲፌሻል ነው። ግንኙነቱም፤ አብሮ መሥራቱም አብሮ ዝክር መታደሙም፤ አብሮ ማስቀደሱም፤ አብሮ ድዋ ማድረጉም፤ አብሮ መማሩም፤ አብሮ መሥራቱም ሁሉም የውሸት ነው። ሁላችንም አልነበርነም። ነገም አብረን በውስጥነት ለመዝለቅ የፈጣሪ ጥበብ ነው። ይርዳን! አሜን! ከእያንዳንዱ ነፍስ ጋር የትግራይ መንፈስ ተጣልቷል፤ ተጋጭቷል፤ ቆስለናል። ቁስል በአያያዝ ጥበብ ነው የሚድነው አንጂ በማግለል ወይንም በአዋጅ አይደለም። ደግሞስ እኛ ቁስሉን እንዲህ እያነፈረቅነው፤ እዬሾቀሾቅነው እንዴት ቁስሉ ሊፈወስ ይችላል።

 ፍቅር ከባድ ነገር ነው። ፍቅር ለመቀበል ፍቅር የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን ፍቅርን ለመቀበል የሚፈቅድ ተፈጥሮ ያስፈልጋል። በባዕለ ሹመቱ እኮ አትቅረበኝ ተብሎ ሲገፋ አይተናል። ጠ/ ሚር አብይ አህመድም አማርኛ በነበረው ውይይታቸው ላይ ወደ ቀድሞው ተመለሱ ብለዋቸዋል። ፍቅር ሳትሰጡ ፍቅር አይገኝም፤ ገፃችሁን ፈታ አድርጉት አግባቢ አቀባባል ማድረግ ስትችሉ እንግዳ መምጣት ይችላል ብለዋል።
  • ·         ጥኔ! „ይብላኝ ለወለደሽ ያገባሽስ ይፈታሻል“ ነው  …

ጠ/ ሚር አብይ አህመድ በትግረኛ ቋንቋ መናገራቸው የትግራይ እና  ኦሮሞ ማህብረሰብን መንፈሱን ከጎን ለማሰለፍ የትግረኛ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን የኦሮምኛ ቋንቋ ሚደያ በከፈተው ሚደያ የኢሳት ብሄራዊ ተንታኙ ጋዜጠኛ እና ጸሐፊ አቶ ኤርምያስ ለገሰ ውስጡን ቅጥል ያለበት ሁኔታ ነበር ያዬነው። አጋጣሚው የውስጥ መንፈስ ማውጫ ሰነድ ሆኗል። ቀድሞ ነገር የትጥቅ ትግሉ ያለው ኤርትራ ነው። ኤርትራ ደግሞ ብሄራዊ ቋንቋዋ ትግረኛ ነው። በዛ ላይ እዛውም የተፈጸመ ነገር ነበር ጉባኤውና መፈክሩ። ያን ጊዜ ያልተነሳ ሰይፈ ነበልባል ትግራይ ላይ ሲሆን በቃ ቃታው ተሳበ የጮለም ተጮለ። 

የተሰበሰበ መንፈስ ሁሉ አጋጣሚው ተገኘ እና ተወቃ። ኦሮምኛ ቋንቋንም ቢሆን የሥራ ቋንቋ እንዲሆን አንተጋለን መባሉስ የት ይሂድ? ያው እነ አቦ ሌንጮ ለታ የአፍ መፋቻ ቋንቋቸው ኦሮምኛ አይደለምን? አብሮ ለመስራት ሲታሰብ እንዲህ ከውስጥ ሳይኮን ነበርን? የአገራዊ ንቅናቄው የወደፊት ዕጣ ፈንታስ? ያው ተባባሪው ሊቀመንበር/ የሥ/ አ/ ሰብሳቢው ከዛ የወጡ ናቸው አይደለምን? ልሳናቸውን ይህን ያህል የሚፈታተነው ከተሆነ ቀጣዩ ተስፋው ምን ሊሆን ነው የትንሳኤው መባቻ? በዛ ላይ የቅኔው አርበኛ አትሌት ሊሊሳ ፈይሳ እስከ አውሮፓው ማህበር ያስጋበዘው ልቅናስ የት ይቀመጥ? ከውስጥ ሳይኮን ለመናጆ ነበርን? መጥኔ! ብለናል።  
ጥያቄው ደግሞ የቄሮም ነው። 

ቄሮም የእኛ ነው የሚል ነገር ከሰሞናቱ የBBC ጠንካራ ሙገታዊ ውይይትም አዳምቻለሁኝ ቄሮ እኮ ቋንቋው ኦሮምኛ ነው እና እንዴት ነው ነገሩ? ፍላጎቱ እና ኩነቱ ተነጣጠለ። „ሲወዱ እስከ ንፍጥ ልጋጉ ይሉታል ጎንደሬዎች።“ ይሄ ችግር በውነቱ ድርጅቱ ግንቦት 7 ሊያስብበት ይገባል፤ በአንድ በኩል ሲገነባ በሌላ እዬተናደ የዘለቀ የሃስብ ጦርነት ያስከትለው ወጥ የሥነ ልቦና የመርህ አመራር ጥበብ ስስነት ነው። ግንባታ ከፍ ማለት ሲኖርበት ንፋስ ገብ ማድረግ የጥንቃቄ ጉድለት ነው። ለዚህ ማርከሻው ኦህዴድ ነው። ለዬትኛውም ቃለ ምልልስ ሙግት ጥንቁቅ ነው። የሚከፍተው ቀዳዳ የለም። 

የ ኦሮሞ ማህበረስብ የእኛ ከሆነ፤ ተጋድሎውን ከአደነቅን ኦሮምኛም የእኛ ነው አይደል? ነው አልተስማምቶም ይሆን? ኦሮምኛ ቋንቋን በሚመለከት እንዴት እና እንዴት ነው የምናሰበው። ተቆርቋሪነቱ ለአማርኛ ቋንቋ ቢሆን የግንቦት ሰባት የኤርትራው ጉባኤ መፈክሩ በትግረኛ ስለነበረ እንደ ሚዲያ ኢሳት በአጀንዳ ይሞግታው ነበር። ለብሄረሰቡም ቢሆን የአማራ ድምጽ በኢሳት ይኖር ነበር። ጠረኑም የለም። ብሄራዊ ፓርቲ ነው አገር ይምራልም የሚባልል የእጮኝነት ቀለበት ስለምን ተልዕኮ እንደ ነበር ባለቤቱ ያውቀዋል። ያው „ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ“ ይለዋል ጎንደሬ ይህንም። የሆነ ሆኖ ይህም ሲተች አላዬነም አልሰማነም? ቅናት ነው እንዲህ የሚያዝ የሚጨበጥ ያሳጣው። መታመስ … የሴራው ጋንታ አቶ በረከት ስምዖን ኢትዮጵያ ከዚህ ደግሞ ሌላ መከራ። ቅን ነገር ለምን ተደመጠ ብሎ ጉግስ። ቄሮ ያን ያህል መስዋዕትነት ከፍሎ ለዛች ደቂቃ ደስ ቢለው ምንአለበት? መከራ ሲዘንብበት የከረመ ባዕትም እኮ ነው … አልመተዛዝን። ይሄ ድርብ አንጀትነት ነው። በደስታ የምንቀና ጉዶች።
  • ·         ማዊ ልሳነወርቅ።   

የትግረኛ የትውውቅ ንግግሩን እኔ እንደ ምን ልበላችሁ ያዬሁት ለዛውን፤ ዘይቤውን፤ ዜማውን እንደ ክስተት። ለትግረኛ ትረካ ራሱ ድምጻቸው የጠ/ ሚር አብይ እጅግ ምቹ ነው። ጥሞኝ ስለነበር 6ጊዜ አዳምጫለሁኝ - ትግረኛውን። በተወሰነ ደረጃ እኔ እሰማለሁኝ ለትግረኛ ዱዳ አይደለሁኝም። እዛ የተፈጠሩት ይህን ያህል ዜማዊ ቃና አላቸው ለማለት አልችልም፤ ሊኖሩ ይቻላሉ ግን አልገጠመኝም። ብቻ ያ ጽዑም የድምጽ ቅላጼ መቼውንም አልረሳውም። ከድንቅ በላይ ነበር። ሳቢ ነበር አወራረዱ። 

መንገዱ ብልህነቱ ወደር የለህ ነበር። ፍቅር ለመስጠት መፍቀዱ ልባዊ ነበር። የትግራይን ማህበረሰብ ሆነ ኤርትራንም ጨምሮ የልቤ ባይለው የአብይ መንፈስ ይህን ያህል ትግረኛ ቋንቋውን እጬጌዬ አይለውም ነበር። እንዲህም ማዕከላዊ የልብ ቁልፍ አግኘቶ በፍቅር አይፈርሽም ነበር። መድህን! መሪነት ይህን ሁሉ ማሰብ አለበት። ለመሪነት ራስን ሲያጩ ሙሉ ትጥቃና ስንቅ ያስፍልጋል። ዝግጁነት። ዓይነታው ሁኖበታል! Proud! አስቀድሞ ህዝብ የእኔ ሲባል ክህሎቱ በዚህ መልክ ብልጹግ ይሆናል። 

የአብይ መንፈስ መሪነት በመዋዕለ ዕድሜው ቆራጣ ጊዜ ያላባከነ ነው። በተገኘበት፤ በኖረበት ሁሉ ውስጡ አድምጦ ተስማማቶ መኖር ብቻ ሳይሆን የ እውቀት አዳራሹ እንዲሆን ፈቅዶታል። ፈጣሪም የመረጠው የባረከውም ለዚህ ነው። ሁሉን አክብሮ ተነስቷል። ሁሉን አፍቅሮ ተነስቷል። ሁሉንም ዕድል ተጠቅሞበታል። ስለሆነም በትንሹም በትልቁም ወጭት ጥዶ ከመቆዘሙ ይልቅ ያመለጠውን ለመጨበጥ መትጋቱ ይበጃል ለፖለቲካ መሪዎችም ለተንታኞችም ወደ የኔታ ቤት መጪ ማለት የጥብብ ጣዝማ ፍለጋ፤ ሐገር ገዢ ለመሆን ከተሰላ ይላሉ። እነማን? ሌላ ማን ሊሆኑ ሥርጉተ እና ብዕሯ።

ይህን ያህል መራራቅ ከናፍቆት ጋራ። ኢትዮጵያዊነት እኮ የዚህ ሁሉ ህብራዊነት ነው። በዛ የተቃውሞ ናዳ የብዙ ሰው መንፈስ ነው የተሰበረው። የመሸግንበት ሸጎሬ በፍጹም አያዋጣም። በፍጹም ኢትዮጵያን አያድነንምን። በፍጹም ለማግስታዊነት አይረዳም። መንቀል ሳይሆን መትከል ነው የሚገባ። ለድርጅታችን ክብር ማሰጠትም የሃላፊነት፤ የህሊና ቃል ኪዳን ነው። እኛ ፆም በሻርን ቁጥር ልኩ የሚለካው በመጠኑ ነው - የድርጅታችን በኛ መጠን ልክ ነው። የመተላለፍን  ስሜትን አጡፎ ከመሰንዘር መገራት መላቅ አለበት። መስከን! በጥሰት ከሚመጡ ቀውሶች ድርጅትን መታደግ። የግድ ከሆነ ድርጅቱ ይጠራ ካለ ወቀሳ ማደግ ስለማይቻል፤ ግን እንዲህ መንፈስን በሚንድ፤ ነገን በሚያርቅ ለዛውም በኤርትራ ልብ ለሚተነፍስ የሁለመና ነፍስ? ጋዳ ነው ከባድ ነው? ጥንቃቄ እኮ ያተርፋል እንጂ አያከስርም።    

ሌላው ኢትዮጵያዊ ሰው ደስ ሲለው/ ሲላት ስለምን ይሆን እኛ የምንጨረጨረው? ለመሆኑ ሁሉንም ነገር መጥላት አለብን? እኔ ከዚህ ሱዳናዊ/ ሱማሊያዊ አልፎ አልፎ ሲዊዛዊዎችም „እንደምነሽ ደህና ነሽ“ ሲሉኝ በአማርኛ ቋንቋ ሴት ሲሆኑ እጃቸውን ጨበጥ አድርጌ ጎንበስ ብዬ አስፈቅጄ እስማለሁኝ። ከደስታዬ ብዛት። ግንኙነታችን ሰዋዊ መሆኑ ቀርቶ ግዑዝ እንዲህ ይሁን? ወይ አለመታደል? ሌላውም ይቅር ድለ - አድዋ የምሥራቹ ዜና ከነምንጩ እንዴት ይረሳል? ያ ትንታግ ኮ/ አብዲሳ አጋ እንዴት ይተርጎም? ሁሉም ይቅር ያ ቀንበጥ አርበኛ ዘርአይ ደረስ፤ አብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም እንዴት ይረሳሉ። 

በእነዚህ ፍልቆች ውስጥ እኮ ትግረኛ ቋንቋ አለ። ኦሮምኛ ቋንቋ አለ። ለመሆኑ ትውልዱን እንዴት ይሆን ልንገነባ ያሰብነው? 27 ዓመት እኮ ተለያይተን አሁን አያሰማን ነው ቅቤ ጣባሹ የወያኔ ቴሌቪዥን 77ኛው የድል ቀን የአርበኛ ቀን ኢትዮጵያን ያቆዬ እያለ ልባችን ትናንት ሲወልቀው ነበር። ባለውለታውን ብሄራዊ ሰንደቁን አስሮና ጠርንፎ፤ መጀመሪያ ያን ያስፈታ ትዕቢተኛው የወያኔ አሀርነት ትግራይ ሚደያ። እኛ ታዲያ ከዚህ የት ነን? መንገዳችን የትኛው ነው? ከውስጥ ሆነን ተኝተን እነሰበው።
  • ·         ስጢር ካለ አስተርጓሚ።

ያው ፕ/ ኢሳያስ አፈወርቂ አማርኛ ቋንቋ ጠላታቸው ነው። አንደበታቸው ከሚያወጣው አፍር ቢገቡ ይሻላቸዋል። ብቻ  ከእንግሊዘኛ ቋንቋ ከመወያዬት ይድናሉ። እርቅ የሚባለው ሆኖ ኤርትራ ቢሄዱ እኮ አስተርጓሚ አይሹም ጠ/ ሚር አብይ አህመድ ከኤርትራ ህዝብ የህሊና ልብ ውስጥ በፍቅር ገብተው ጉዝጉዝ ነው የሚሉት። ከፕ/ አሳያስ አፈወርቂም ጋር ቢሆን ሚስጢራቸውን የብቻቸውን መኮምኮም ይችላሉ፤ ቋንቋ ሲታወቅ ልብ ይከፈታል። ፍቅር ይቀናል፤ ይሸመታል። ቋንቋ የመኖር ሃዲድ ነው። ይሄ የዶር አብይ አህምድ የትግረኛ ቃና፤ ይሄ ጣዕም፤ ይሄ ጥርኛ እንኳንስ ለተፈጠረበት ለእኛ በተለይ ለወሎ እና ለጎንደር ይስበናል። ጎንደር ትግረኛ፤ አማርኛ፤ ሱዳንኛ ዘፈኑ ፍቅሩ እኩል ነው የነበረው የአሁኑን አላውቅም። ከስፖርትም ሳይክል ውድድር በእኔ ዕድሜ ጎንደር ከተማ ላይ ተወዳጅ ነበር። 

ያልታደልነው እኛ በሥም ጦርነት እንገባለን አዳማ፤ ቢሸፍቱ፤ ደብረዘይት፤ ናዝሬት ያዋጋናል። ደስ የሚላቸው አዳማ ቢሸፍቱ ከሆነ ስለምን ደስታን ለመስጠት እንስታለን? ለምን? ይሄ ቁርሾ ካለ ለላንቲካ ነው የትግረኛ እና የኦሮምኛ የዜና አንባቢዎች እንዲኖሩ የተደረጉት። መክፋትን፤ ማስከፋትን ስለምን እንፈቅደዋለን? ለምንድነው ውስጣችን ለማጠብ ፈቃደኛ የማንሆነው? ቂም ምን ይሠራልናል? ጠብ ጠማኝ መሆን ማንን ያተርፋል? ነፃነት ፍለጋ በምን ቀመር ይተርጎም? ባህሉን ቋንቋውን ልማዱን ዕሴቱን ተጸይፈህ ሰው ሆይ ለሥልጣን ፍቀደኝ አለን? ተባበረኝ፣ ተዋህደኝ፣ አብረህኝ ሥራ አለን? ምንድን ነው የምንፈልገው። 

ደቡብ ላይም መሰሉ ነበር መግቢያ ላይ የፈጸሙት፤ ጁቡቲ ላይ ለፕሬሱ ጉባኤ በአማርኛ ነበር መልስ ሲሰጡ የነበሩት፤ ትናንት ሱዳን ላይ ሲጨርሱ ሽኩሪን በማለት ነበር ያሳረጉት። ይሄን የህዝብ ዓይን የሆነ የፍቅርን ተፈጥሮ እንዴት እንታገለዋለን? ደካማ ሰው እንዲመረጥ ፈልገን ነበርን? የዓለም ዐቀፉ ማህብረሰብ ጫና አቅደው ከነበረ አልሆነም። ፈጣሪ ኢትዮጵያን ማዳን ስለነበረበት ነብያትን አስነሳ። 108 ነብያት ድምጻቸውን ያከበሩለት መንፈስ የሰማይ ነው። ሳማያዊ ቀለም ያለው „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“  የእኔን መሰል የሞኞችን መርህ በ108 ድምጽ ብቻ ሳይሆን በሚሊዮኖች ከበረ።

የከበረን ነገር አውርደህ ጭቃ ላይ እለጥፈዋለህ ማለት የራስን ደረጃን ቁልቁል ልይህ ማለት ነው። መመኘት ግን መብት ነው … ለማድረግ ግን የሰከነ መሬት የያዘ የሞጠረ የማደራጀት ተግባር ያስፍልጋል። ስሜትን ለማግኘት በቅቶ መገኘት። ንግግር ሳይቻል መሪነት አትሰቡት … መሪነት ዓራት ዓይናማ ተናጋሪ ብቻ ሳይሆን ሃሳብ አፍላቂነት፤ አወያይነት፤ ሃሳብን አቀናጅቶ በተፈለገው የመስኖ ልማት ማዋልን ይጠይቃል። ለሚጠዬቁት ጥያቄዎች ሁሉ የተደራጀ የሃሳብ ቅንብር ያስፈልጋቸዋል። ንግግር ጸጋ ነው። ክህሎቱን በስልጠና ማሳደግ ወይንም ማበልጸግ ይቻላል። የኢትዮጵያ ጠ/ ሚር ዶር አብይ አህመድ ሁሉ አላቸው። ሰብሳቢም፤ ተናጋሪም፤ አወያይ፤ መካሪም፤ አግባቢም ናቸው። ዲፕሎማሲያወነታቸው የምህረትን ፍስፍና ከይቅርታ ልብ ጋር ተስጥቷቸዋል። ቤሻንጉል ጉምዝ ላይ „ የአፍ ወለምታ“ ሲሉ ተቃኝተውታል ባለ ቅኔው ጠ/ሚር። ሁሉም ሚዲያ አምፆ እዛም ያለው ቆራርጦ፤ አስረክርኮ ቢያቀርበውም የደረሰው ደርሶናል። ይልቅ የሰለቸኝ ለዛዛው እና ደንዛዛው የሪፖርተሮች ማብራሪያ ነው … መቦጫረቅ።
  • ·         ያ ጥላዬ የነፃነትትግል

የነፃነት ትግል ስልት የሚባል፤ የሃይል አሰላለፍ የሚባል አለ? ጊዜ፤ ቦታ እና ሁኔታም ይህም ይቅር አንዲት እህቴ ደቡብ ላይ „ተቃዋሚ ጠላቴ ይመስለኝ ነበር ። አሁን ተፎካካሪ ሲሉ ራሴን አስተካከሉኩኝ“ ብለዋል። እዛው ላይ ሌሊቱን ሙሉ ዜና ስንጠብቅ አድረን አንተ ስትሾምልን ተኛን አሉ ሌላው ሊሂቅ አባት ከንጉሦች ንጉሥ ከዐጤ ቴወድሮስ እሰከ ንጉሦች ንጉሥ ዐጤ ሚኒልክ የሀገር ባለውለታነት ፍቅር መግበው። እኛ እራሳችን የህዝባችን ስሜት በያለንበት ባህሉን፤ ልማዱን፤ ወጉን፤ የረሳነውን ነገር ሁሉ በተመስጌን እዬጠለፍንበት ነው። የ እያንዳንዱ ቀን ተግብራ ዘለቅ እርምጃ መጸሐፍ ነው። ምን ዓይነት ህዝብ እንደ አለን፤ ምን አይንት ፍላጎት እንደ አለን፤ ምን ዓይነት የመናገር ጥበብ እንደ አለን? ምን አይነት ባህል ወግ ልማድ የምርቃት ሥርዐት እንዳለን፤ ምን ያህል አፈና እንደነበረ ከምነውቀው በላይ መረጃ አግኝተናል። ምን ያላዬነው ነገር አለ። አሁን ጋንቤላ አፋር ሲታከል ኬኒያ ስትጨመር ሙሉ ሰው መረጃ ይኖረናል ስለቀጣዩ አቅጣጫ። የደቡቡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት አባት ምርቃቱ „ነፍሴ አዳምጣሃለች“ ነበር ያለት። ሌላው የሴቶች አቅም እንደ እሳተ ጎመራ ነው የፈነዳው።

በአንድ ወር ውሰጥ የተከወኑትን ዕለታዊ ምግባረ የትህትና ጉዞ፤ ይህን ስንዱ አዕምሮ ለመተንነትን አድማጭ አቅም አለኝ ወይ ብሎ ራሱን መጠዬቅ ይኖርበታል? ሰብል በሰብል ነው የሆነው። መንፈስ እኮ በመስኖ መልማት ይፈልጋል። እዬለማን እኮ ነው። ስለ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አሰተሳባችን እያደገ ነው እኮ፤ ከራሳችን ጋር እዬተጋልን ነው … እርቅ እንዴት ይፈራል? ምህረት ማድረግ እንዴት ያርዳል? ኧረ የኛውስ የጉድ ነው? ሥርጉተ የማታውቀው ሀገር አይናፍቃትም። ይህን ለመፈተሽ ጊዜ እሻለሁኝ። ከጅምሩ ጀምሮ ከተጋሁበት ጉዳይ መልካሙ ነገር እጅግ የገዘፈ በአናጻሩም ግድፈቶችም የነበሩበት ነው። ስለሆነም ግድፈቶችን በተመለከት በራሱ ጊዜ መልስ ተሰጥቶበታል። ብቸኩልበት ኖሮ ጸጸት እቅፌ ይሆን ነበር።

አሁንም ቢሆን በሂደት አዳዲስ ፈታኝ፤ ሞጋች ገጠመኞች ይኖራሉ ብዬ አስባለሁ ሂደት ነው። ስለሆነም የራሴን ዕይታ በዝግታ እና በማስተዋል እዮባዊነቱን ቀልቤ መመዘን እሻለሁኝ። ይህ አዲስ መንገድ ነው፤ አዲሱ መንገድን ሥራዬ ብዬ ሳጠነው ቆይቻለሁኝ ለወደፊትም አጠናዋለሁኝ። ለትችትም፤ ለማብጠልጠልም አልቸኩልም። ለዛ በቂ ጊዜ ወደፊት አለን መኖሩ ከተገኘ። ሆደ ባሻ ስስም ስሜታዊም መሆን በዚህ ዕድሜዬ እና ባላፍኩባቸው ዝቀሽ የተመክሮ ማሳዬ ማስተናገድን አልፈቅድም። ልኬ አይደለምና! ይህን መልካም አጋጣሚ በመልካም ሥነ ምግባሩ ለማድመጥ በውስጥ ያሉ ግድፈቶችን እና ፈተናዎችን እኩል በተደላደለ ስብዕና አስተናግዳቸዋለሁኝ። መቸኮል ብዙ ነገር ያሳጣል።

የኔዎቹ እስኪ የገጣሚ ፍጹሜ አስፋውን „ቅን ልቦች“ በተለይ አገር ቤት ያለችሁት ተከታተሉት በሳምንት ሁለት ቀን ነው ትእዛዝ ግን አይደለም። ነፃነት እኮ ቋንቋን ነጥለን፤ ሰብዕናን ነጥለን፤ ልማድና ነጥለን፤ ደስታውን ተጭነን፤ ባህልን ነጥለን፤ ትውፊትን ነጥለን፤ ለህዝብ ልባዊነት መስጠትን አቅበን፤ የአቤቶ ጥርስን ተፈጥሮውን ታጋፍተን እና ደፍጥጠን፤ ራስ ዳሽን ያህል ከንፈራችን ተራራ አሳክለን፤ ፊታችን ግራጫማ አድርገን በኮሶ ለውሰን እንዴት ይሆናል? አካል የሌላቸው፤ አቧራ ላይ የወደቁ ማህበረሰብ አለን፤ እድፍ ለብሰው የሚኖሩ። ሰውነታቸውን መቆጣጠር የተሳናቸው በሽተኞች አሉን። 

እነሱም አኮ የእኛ ሥጋ እና ነፍስ ናቸው። አንዴት አድርገን ነው እቅፍ የምናደርጋቸው? የነፃነት ጉዞችን ነጭ ለባሽ ብቻ ፈላጊ ነውን? አይሆንም … ወደ ተፈጥሯችን እንመለስ። ፈጣሪ የተቆጣ ዕለት እኮ ሁላችንም አንድንም፤ የትም እንኑር የትም።  … ሁላችን መዳኛችን የምህረት በር ብቻ ነው። ተቋስለናል። ከእኛ ዕድሜ በታች ያሉ ግን በህሊና የበቁና የጸደቁትን መንገድ ለመከተል ምንድነው የሚያግደው? ወንበር? ሥም ዝና? ውዳሴ? ቋንቋን ስንታገል ፈጣሪን መታገላችን አልገባንም? ስለዚህም ልናፍር ይገባል ህሊናው ከኖረ። ዝግ እንበል! እንስከን! ሁላችንም ጥያቄ አለን? ጥያቄውን የመመለስም ደግሞ የሁላችንም ግዴታ ነው። አንዲት በጎ ሃሳብ ሳናዋጣ፤ ሁሉም እኩል የወያኔ ሃርነት ሚዲያ የውስጥ ቁስል መሻሪያ ሆኖ ነው ያረፈው። ሰው ይታዘበኛል አለማለት። 

የፍቅር ውስጡ ነደደ። ወያኔ ሃርነት ትግራይ „ኢትዮጵያ“ የሚለውን አልበሙን የቅኔውን ዕንቡጥ ያን የመሰለ በዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የትውልድ ማትረፊያ ቃና ስለምን ዕውቅና ተነፈገው፤ በሀገሩ መሬት ባይታዋር ሆነ ብለን ብለን ኢትዮጵያን በውስጡ አድርጎ አገሬ የሚለው ሁሉ በወል በውስጡ ተቃጠለ፤ ነደደ፤ ከዚህም ታልፎ የ ዓመቱ ድንቅ ተብሎ ተሸለመ። ጎሽ ይገባል ተባለ።
ዛሬ መንፈሱ ባልጠበቅነው ሁነታ ዕውቅና አግኝቶ አስቸኳይ ጊዜውን በስልት አና በጥበብ እዬጣሰ ወደ ፊት ሲገሰግስ ደስ ሊለን ሲገባ ወያኔ ሆይ ያገድከው ትክክል ነበር እኛም ታላቅ አድርገን የሸለምነው ተሳስተናል እያልነው ነው። የአብይ መንፈስ ግን ሰብልት እና በጥበብ ያለውን እንኩሮ ጉድ የታቀደለትን የሙት በቃ ስለሚያውቅ የሆዱን በሆዱ አድርጎ በስልት መሬት ላይ ወርቅና ዘሃ እዬሸመነ ነው። ለመግዛትም እኮ የሰከነ ህዝብ እና ሐገር ያስፈልጋል። ህዝብን እመራለሁ ሲባል ማሳ መሬት ያስፈልጋል።

 ድርጁ መንፈስ ያስፈልጋል። ይሄን እኮ ነው እዬደለደለ ያለው ባለቅኔው ጠ/ ሚር። ጊዜው እያመለጠ ነው። ከጉግስ፤ ከስሞታ ወጥቶ ተፎካካሪ ሆኖ ለመውጣት ኢትዮጵያዊነትን መማር፤ በውስጥ ማደራጀት፤ ከዛም መንፈስን መሰብሰብ እናም አዲስ ሃሳብ አፍልቆ ተወዳድሮ ለማሸነፍ መትጋትን ይጠይቃል። … ትችት አያሸንፍም። የተያዘ የተረዘዘውን ሁሉ ጠልተንም አይሆንም። ሰው በመሆናችን ህሊና ያለን ስለመሆነ ህሊናችን ይሞግተናል። ሰው ባይስማማ ይተዋል። ቤት ባይሰማማ ይለቀቃል። ሥራ ባይስማማ ይቀዬራል። ሀገር ባይስማማ ይሄው ተሰደድን ህሊና ባይስማማ ግን ምን ይደረጋል? የትስ ይደረሳል። ብልህነት ይጎድለናል።
  • ·         አንድ ነገር እንደ ማከያ።

እኔ ለማውያን ነኝ ብዬ ስተጋ አንድ ብልህ ነገር ተናግሬ ነበር። የኦህዴድን ድርጅታዊ አቅም እና ብሄራዊ ሃላፊነት የመወጣት አቅሙን በብቃት ፖለቲካዊ ግንዛቤ የሚያስጨብጡን ውጭ ሀገር የሁለመና ሊሂቁን ዶር ከሳ ከበደን፤ ሐገር ቤት ደግሞ የድርጅት ቋሚ ተቋሙን ጓድ ገ/ መድህን ጠይቁ። እኔ ስህተተኛ ከሆንኩ ብዬ ነበር። ሰሞኑን ኢሳት ጋር ከ2 ሰዓት በላይ ውይይት አድርገዋል። ያው የኔው በግልጥነት እሳቸው በዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ ገልጠውታል። ከዛ አቅም ለመድረስ እና ለመፎካከር ይከብዳል። ለዚህ ነው ድብልቅልቅ ብሎ ለያዥ ለገራዥ በሚያስቸግር አቅጣጫ የለሽ ቀዥቃዣ አውሎ ናፋቂዎች የተሆነው። ሚስጢሩ ይኸው ነው። አቅም ሲጠፋ ግርግር ይናፍቃል። አቅም ያለው „ሙያ በልብ“ ብሎ እያንዳንዷን ደቂቃ ወርቅ ያፈስባታል። የዚህ መንፈስ ባለቤት ስልቹ አይደለም። ፍርሻ አይጠማውም፤ አለስፈላጊ መስዋዕትነትም አይከፍልም። ስክነትን በምህረት ልቦና ማስበል ልባሙ ብልሃት። ልቡን ሞልቱ ካልተመቸንህ ማውረድ ትችላለህ፤ የተሻለውን መምረጥ ያነተ ድርሻ ነው ይላል እንዲህ በድፍረት። ዕዮባዊነትን ለሰነቀ ይህ ብሄራዊ አዋጅ ነው። ሜዳውንም ፈረሱንም ይዘህ ከምትፈቅዳቸው፤ ከምትመርጣቸው ከእኛ ከተሻሉት መሪዎችህ ጋር ሽምጥ ስትጋልብበት ትታያለህ ብሏል የሎሬቱ ልጅ። …
  • ·         ይወሰን ለክወና። 

ግብጽ? ሊቢያ? ያ ነበር የናፈቅን። ወይንም ስለት እምናስገባው አንዱ ጠንቀኛ እጩ ተወዳዳሪ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ አሸንፈው ቢሆን በስንኩል አቅም ጫና ለመፍጠር ነበር፤ በዚህ ማህል ሊፈጠር ስለሚችለው ህዝባዊ አዳጋ አናስበውም። ብዙ የማይታወቁ ሸጎሬዎች አሉ። እጅግ መጠነ ሰፊ ሽርክት አቅጣጫዎች አሉ፤ „ወትሮ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል …“ እንዳይመጣ በተለይ አገር ቤት ያላችሁ ቅኖች ትጉበት፤ …  በዚህ ቀና መልካም መንገድ። መከራው ለእናንተ እንጂ እኛም ከሞቀው ሆነን ነው። ሁለቱም የማዕከላዊ መንግሥት አፈ ጉባኤዎች በዚህ ዘመን ሴት ናቸው። በዬውይይቱ የሴቶች አቅም የጉድ ነው፤ ለእድሉ ተጠቃሚነት ስልት፤ ጥበብ፤ ቅንነት ግን ያስፈልጋል። የሚታዩ፤ የሚጨበጡ፤ የሚዳሰሱ መልካም ነገሮች ይኖራሉ ለቅኖች አሁንም መተንተን ይቻላል። የለማ የተባ የሚቆጠር የሚዘረዘር ሰብል አለ።    

ራሱ የነፃነት አርበኞች ከእስር መፈታት የለማ፤ የአብይ፤ የገዱ መንፈስ ዕውቅና አልተሰጠውም። ያቆስላል። ተጋድሎ ብልህ መሪ ካለገኝ እንደ ግብጽ ባክኖ ነው የሚቀረው።  እነሱ ባይኖሩ ምን ሊሆን እንደሚቻል ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው። በወያኔ እጅ ለወደቀ እስረኛ ብድግ ብሎ ተነስቶ መጸዳጃ ቤት መሄድ በራሱ ብቻ ይበቃል። እንቅልፍ ሲመጣም መተኛት። መስቃው፤ ሲገቡ ሲወጡ፤ ግልምጫው፤ መዳህኒት ሲወሰድ እስር ቤት በተመጠነች ውሃ ነው። ሽንት እንዳይመጣ፤ የዕድሜ ልክ በሽታ ነው ተይዞ ነው የሚወጣው … ተመስገን መቼም የለም። ፈጣሪ/ አላህ እንዴት ያዝን፤ ድንግልዬስ ምን ይከፋት? ነፍስ ይዞ መውጣት ራሱ ነፍስ ነበር። እርግጥ ነው ነጻነት አይጠገብም የሰው ልጅ ፍላጎት ማለቂያ ዳርቻ ስሌለው፤ ነገር ግን የፊት የፊቱን እያከበሩ መሆን አለበት። ደግሞስ አገር ውስጥ ያሉ ተፎካካሪዎች እኮ ኢህዴግን ተወዳደረን እንሸንፋለን ከሆነ እሳቤው ምነው ዛሬ ያ ወኔ ጠፍቶ አቋራጭ አሰኛቸው። ምረጫ በመጣ ቁጥር ተስፋ ቢስ በሆነ ጉዞ እኮ የግንባር ሥጋዎች ተገበረዋል፤ ከዚህም ባለፈ አንድ ዓመት እኮ በበረዶ ግግር ድርድር ተብሎ በአቶ በረከት የሴራ ጋንታ ስንት የህሊና ስንቅ ባክኗል። አሁን የተሻለ አማራጭ ሲመጣ ያ ግግር በረዶ ወንበር ማሟሟቁ ይሻለናል ይሆንን? ግራ!  

·         ኢትዮጵያዊው ሰው ለትዳሩ፤ ለልጁ፤ ለወላጆቹ፤ ለሙያው፤ ለሃይማኖቱ የሚሰጠውን ፍቅር እንዴት ለኢትዮጵያ ለመስጠት ይስስታል? ቀጥ ብሎ ሄዶ ከፍቅር መንገድ ጋር ውጊያ? ይገርማል? ለመፈረካከስ፤ ተያይዞ መጥፋት ይህን ያህል ህልመኛ መሆን? ውስጣችን ስለሚያውቅ ነው ፈጣሪ አምላክ ራሱ የበቃውን መርጦ የቀባው። በተረፈ፤ በተረፈማ ቋንቋ ነፃነት ነው፤ ለነፃነት እዬታገሉ ከቋንቋ ጋር ጉግስ መግጠም ያስገምታል ለዛውም ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ተንታኝ ላይ ሲሆን አያምርም። የታመቀውን የነፃነት ቤተ ራዕይን ዓውድንም ተፈተሽ ማለት ግድ ይሆናል። 

አቤቱ ፈጠሪ አምላኬ ሆይ ደመላሼ ነህ እና እስከ እስትንፋሴ መጨረሻ ድረስ ከሥርህ ወድቄ አመሰግንሃለሁኝ።
·         ነባር ጹሁፎቼ ለሚያሰኛችሁ ቅኖች፤ ስብስቡን በጥቂቱ ለማካተት ጀምሬያለሁ ግን ጀምሬዋለሁኝ። አዲስም ይታከልበታል።



ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።

ክብረቶቼ ለነበረን የመተሳሰብ ጊዜ ለጥ ብዬ እጅ ነሳሁ፤ እናም ሰንበትን መልካም እንዲሆንላችሁ ከነፍሴ ተመኘሁ። ካለ እናንተ እኔ ምንም መሆኔን አውቃለሁኝ። ደጋፊዎቼም ተቸዎቼም ኑሩልኝ! መሸቢያ ጊዜ!

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።